ዋጋ ግሽበትን ያባባሱ የአገር ውስጥ መንስኤዎችን ለመቆጣጠር መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው -- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2004 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋጋ ግሽበትን ያባባሱ የአገር ውስጥ መንስኤዎችን
ለመቆጣጠር መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥቃየቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህ ወቅት እንዳሉትም በተለይም ለግሽበት ሰበብ ከሆኑት ከገንዘብ አቅርቦትንና ከውጭ ምንዛሪ ክምችት ጋር ተያይዘው አባባሽ መንስኤዎችን ለመቀነሰ እየተሰራ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የግብርና ግብአት አቅርቦት መጨመር፣ የግብይት ስርአቱ ለውድድር የተጋለጠ አለመሆኑና በአለም ላይ ያለው የዋጋ መዋዠቅ ለዋጋ ግሽበቱ መንስኤ ናቸው ብለዋል። ለዚህም መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የሚበደርበትን መቀነስ፣ የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት ከውጭ ገብተው በሚሰራጩ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የሚደረገውን ስርጭት በአግባቡ መቆጣጠር እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ለሚደረገውን ጥረት ትኩረት መስጥት ይገባል ብለዋል።
ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለውን ግነኙነት በተመለከተም በድርድር ለመፍታት የሚደረገው ጥርተ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው የኤርትራ መንግስት የሚያደርገውን ትንኮሳ እስካላቆመ ድረስ ተመጣጣኝ ምላሽ የመስጠቱ ሂደት እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሶማሊያ ስለሚገኘው ሰላም አስከባሪ ሃይል በሰጡት ምላሽ በቦታው የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቅርቡ ተልዕኮውን ጨርሶ እንደሚመለስ ተናግረዋል።
እስከ ሰኔ 30 ድረስ የዋጋ ግሽበት መጠኑ እየቀነሰ እንደሚሄድም አመልክተዋል።
ፓርላማው በዛሬው መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግስት የ2004 በጀት አመት ተጨማሪ የበጀት ጥያቄን ለሚመለከተው ክፍል መርቷል።