ፕረዚዳንት ኢሳያስና የዘመነ ቪክቶርያዋ ጉብል
ተድላ ደስታ 4/30/12--
አስገራሚውን የሰሙኑ ወሬና የፕረዚዳንት ኢሳያስ ሞትን አሽንፎ የመከሰት ትንግርት እንቆቁልሽ ለሆነባቹህ አንባቢዎች የሚነገር ወግ አለኝ። ድሮ በዘመነ ቪክቶርያ እንግሊዝ አገር የሆነ ታሪክ ነው። ያኔ ሰዎች ከምንም በላይ ለግል ታሪካቸውና ዝናቸው የሚጨነቁበት ዘመን መኖሩን እያስታወስን።
አንዲት በአለባበስዋም በአኳሃንዋም “ለክብሬ መዋች” ዓይነት ወጣት ተስብሰበው የሚያውካኩ ጎረምሶች ባሉበት አካባቢ እያለፈች ነው። ጎረምሶቹ ልክ እንዳዩዋት አንዳች ክብርዋን የሚነካ ነገር ተናግረው በኃይል ሳቁባት። ወንዶች ናቸው፤ ብዙ ናቸው። በዛ ላይ ሁኔታቸው “ጸብ ያለሽ በዳቦ”ን ይመስላል። ክብርዋ ስለተነካ ምላሽ ሳትሰጥ ማለፍ ስብእናዋ የሚፈቅደው ነገር አይደለም። ከሰዳቢዎቿ ጋር አፍ መካፈቱ ደግሞ ለባሰ ውርደት መጋለጥ ነው። በጉልበት ብትቀጣቸው ደስታዋ ነበር፤ ግን እንዴት ሆኖ?! አሁን ምን ታድርግ? ለጊዜው አንድ መላ ታያት። እናም አደረገችው።
አእምሮው እንደሳተ ሰው ተዘለፍልፋ ወደቀች። ይህን ያዩ ሰዎች ደነገጡ፤ ተሳዳቢዎቹም ጭምር። ክብሯን ለመጠበቅ ምን ያህል ርቀት እንደምትሄድ አሳየች። የተቃጣባትን ጥቃት መከተች። ጎረምሶቹንም ከዘለፋ ወደ ጸጸት ወሰደቻቸው። በዚህ ሁኔታ ሁኔታውን አስቀየረች።
ፕረዚዳንት ኢሳያስ ለግል ክብራቸው የሚጨነቁት መጨነቅ ላስተዋለ ሰው ከቪክቶርያ ዘመኗ ጉብሊት ጋር ያላቸው ልዩነት የጾታና የዘመን እንጂ የአኳኋን እንዳይደለ ይገነዘባል። እሳቸውም በዘመናቸው በርካታ ክብረ-ነክ ሁኔታዎች አሉባቸው። ባድመ በእጅ የለችም። ትክሻቸው ሁለት ማዕቀቦችን ተሸክሟል። ኢጋድም እንዳገዳቸው ዘልቋል። ኢሳያስም የጓደኛቸው ሬሳ አግደው ደጋፊዎቻቸውን ጭምር አስኮርፈዋል። ፓይሎት የተባለ ኃይለኛ የውስጥ አዋቂ ነውሮቻቸውን ለአደባባይ እያዘራ በየቀኑ ወጣቱን እያሳደመባቸው ይገኛል። ዓይናቸው እያየ ኢትዮጵያ የወሰደችው የመጋቢቱን ጥቃት ምን ያድርጉት?! ከሁሉ የከፋ የሆነባቸው ደግሞ በአህጉራዊና አለምአቀፋዊ መድረኮች የሚደመጡ መሪ አለመሆናቸው ነው። ፍላጎታቸው ሌላ፤ ተጨባጩ ሁኔታ ሌላ።
አሁን አሁን በኢትዮጵያውያኑ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ጎረቤቶቻቸው ሊደፈሩ ነው። በቅርቡ የየመን አሳ አጥማጅ ጀልባተኞች “ሁለት የኤርትራ ባህር ኃይል ወታደሮችን ማረኩ” የሚል ዜና ሰምተናል። ይህ ሁሉ ችግርና ትኩረት ማጣት እንዴት-ወዴት ያስቀይሱት?!
የዘየዱት ሞቻለሁ ብሎ በማስወራት እንደገና ደግሞ “አልሞትኩም” በማለት አንድ አሸናፊ የሚሆኑባት የማስቀየሻ ድራማ መተወን ነው። ይህም የጥንቷ ኮረዳ ከወሰደችው ምርጫ ጋር የሚማሳሰል ግብረ-መልስ ነው። ልዩነቱ ወጣቷ ያጋጠማት ችግር እርሷ በፈጸመችው ስህተት የመጣ ሳይሆን ዱብዕዳ ነበር። የኢሳያስ ደግሞ እንዳንዷ ችግር ራሳቸው የጎተቷት ናት። በዚህ ልዩነት ምክንያት ለወጣቷ የሚታዘላት ያህል ኢስያስ ደግሞ ከጥቂት ጥቅም ተጋሪዎቻቸው በቀር ብቻቸው የቆሙ ሰው ናቸው።
ለነገሩ አሁን ከሚገኙበት ደካማ ሁኔታ አንጻር የፕረዚዳንት ኢሳያስ መኖርና አለመኖር ለኤርትራ ህዝብ ያለውን ወሳኝ አንድምታ ያህል ለጎረቤት ህዝቦችም ሆነ ለተቀረው ዓለም እምብዛም ነው።በቀላል አባባል፣ ኢሳያስ በዚህ አጭር የኤርትራ አገራዊ ህልውናና በሳቸው ረዥም የስልጣን ዘመን የተጓዙባችው ምዕራፎች የሚከተለው ይምስላሉ። ብርቱ ወዳጅ- ብርቱ ጠላት- ደካማ ጠላት- የማይጎዳ ጠላት። አሁን በመጨረሻው እርከን መጀመርያ ላይ እንደደረሱ ይታመናል። ለኤርትራ ህዝብ ግን እያንዳንዷ የኢሳያስ ቀሪና ቀጣይ የስልጣን ዘመን ከባድ ጉዞ ናት። ቶሎ በገላገለው!!!