ከንቱ የዊክሊክስ ብርበራ በዊክሊክስ የምናነበው፤ በይፋ የምናየውን ብቻ ነው!

Articles

ከንቱ የዊክሊክስ ብርበራ በዊክሊክስ የምናነበው፤ በይፋ የምናየውን ብቻ ነው!በአቤል ፍሬሰናይ ከአዲስ አበባ - በቅርቡ በአይጋፎረም ድረገፅ ላይ አቶ ገነነው አሰፋ በዊኪሊኪስ መረጃ ላይ ተመስርተው ይፋ ያደረጓቸውን ሃቆች ተመስጬ በአድናቆት ካነበብኩ በሁዋላ በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው ይህ ፅሁፍ ወደ አማርኛ ቋንቋ ቢተረጎም የበለጠ ጥሩ ይሆናል በሚል ያሰቡኩትን ለፀሃፊው ሳማክራቸው ፈቃደኝነታቸውን በደስታ ስለገለፁልኝ ፅሁፋቸውን በሚከተለው መልኩ ተርጉሜ አቅርቤዋለሁ መልካም ንባብ ለአይጋ ድረገፅ አንባቢዎች፡፡

የዊክሊክስ መረጃ ይፋ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ቀንደኞቹ የኢህአዴግ ጠላቶች የገዢውን ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ለመክሰስ የሚያስችል ተጨማሪ ማስረጃ ፈልፍለን እናገኛለን በሚል የዊክሊክስን ዶሴ ሲበረብሩ ከርመዋል፡፡ ያንቀላፋውን የፀረ-መንግስት ቅስቀሳ ፕሮጀክት ለመቀስቀስ የሚረዳ አንዳች ነገር ማግኘታችን አይቀርም የሚል ሙሉ እምነት የነበራቸውም ብዙዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች የላቀ ጥበብ አለን የሚሉት ወገኖች፤ ዊክሊክስ ጠለቅ ተደርጎ ከተፈተሸ፤ ፍፁም አስደንጋጭም ባይሆን ከዛ የማይተናነስ ጉድ የሚያፈላ ምስጢር ማግኘታችን አይቀርም የሚል ተስፋ ነበራቸው፡፡ የፌደራል ሪፐብሊኩን እና መሥራች መሪዎቹን በአንድ ጀምበር ህጋዊነት የሚያሳጣ ተደብቆ የቆየ መሣሪያ አናጣም የሚል ሙሉ እምነት ይዘው ነበር፡፡ እንዲያውም በዚህ ነገር አብዝተው የታመኑት ሰዎች፤ ጊዜው ቢያልፍም «በምርጫ 97 አሸናፊዎች እኛ ነን» የሚለውን የተቃዋሚዎች መሰረተ ቢስ አቤቱታ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ እስከ ዛሬ በብረት ሣጥን ተቆልፎ የቆየ ብርቱ ምስጢር እናገኛለን በሚል ጮቤ ረግጠው ነበር፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል እፈሩ ሲላቸው፤ እንዲህ ዓይነት መረጃ በዊክሊክስ አልተገኘም፡፡ በዚህ ነገር በእጅጉ የተበሳጩት ሰዎች፤ አስደንጋጩ የኮምፒውተር ጎሮዶማን (Hacker) ዊኪሊክስ፤ ሳይታሰብ ይፋ ያደረገውን ስንክሳር የሆነ የአሜሪካ ኤምባሲ ምስጢራዊ የኬብል መልዕክት በመበርበር በርካታ ጊዜ እና ጉልበት በከንቱ አባከኑ፡፡ ምክንያቱም ጉድ በተባለው በዚህ የመረጃ ሰነድ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግስት ዋና ዋና አመራሮች ላይ አስደንጋጭ ክስ ለማቅረብ እና የጥላቻ ቅስቀሳ ለማካሄድ የሚረዳ ነገር ማግኘታችን አይቀርም የሚል እምነት በተቃዋሚዎች ዘንድ ስለ ነበረ ነው፡፡ ሆኖም፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ተደብቆ የተወሰደ በሀገሪቱ ላይ መዘዝ የሚያመጣ አንድም ውሳኔ አለመኖሩ ታየ፡፡ እናም ከዚህ አንፃር ኢህአዴግን በተመለከተ ማለት የሚቻለው፤ «በዊክሊክስ የምናነበው፤ በይፋ ሲሆን ያየነውን ነገር ብቻ ነው» ይሆናል፡፡

የሱዳኑ ጋዜጣ «ሱዳን ትሩቢውን» የጎረቤት ሀገራት መንግስታት በአፍሪካ ብቸኛ በሆነው የእስላማዊ መንግስት መሪ ላይ በስውር እያሰቡት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ የዊክሊክስን መረጃ ሲያበጥር መቆየቱ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመው ይኸው የሱዳን ዕለታዊ ጋዜጣ ኃላፊነት በጎደለው የኤዲቶሪያል ውሳኔ፤ ለሰራው ዘገባ ስሜታዊ ርዕስ በመስጠት፤ አቶ መለስ የሱዳኑ አቻቸውን አስመልክቶ ለአሜሪካኖች መከሩ በሚል የቀረበውን መረጃ አንሸዋሮ በመተርጎም ያቀረበውን ዘገባ፤ ወትሮም ነገሩ ፍሬ ከርስኪ ስለሆነ፤ የሱዳኑን ፕሬዚዳንት ጨምሮ፤ ማንም ስም ያለው ትልቅ ሰው ዘገባውን ቀልብ ሰጥቶ አልተመለከተውም፡፡

ሌላው ቀርቶ፤ በውጭ ሀገር ከሚገኘው የፀረ-ኢህአዴግ የፖለቲካ ክንፍ አባላት መካከል የተለየ ትኩረት የሰጡት ብቸኛ ሰው፤ የግዕዝ ስማቸው አልመች ያላቸው የሚመስሉትና ራሳቸውን አል-ማርያም ብሎ መጥራት የመረጡት፤ ደግሞም በጭቃ ጅራፋቸው የሚታወቁት፤ ፕሮፌሰር ኃ/ማርያም ገ/ማርያም ናቸው፡፡ እኚህ ሰው ራስን በማታለል ዘዬ፤ ራሳቸውን ከአል-ጎር ያልተናነሰ የጠራ ያንኪ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ አል-ማርያም የዘር ሀረግ ምንጭ ከአፍሪካ ስለሆነ የተፈጠረባቸውን በራስ የመተማመን ችግር ለመጠገን አስበው የሚሰሩት ይመስል፤ በአጠቃላይ የአፍሪካ መሪዎችን፤ በተለይ የኢትዮጵያን ጠ/ሚ ሚኒስትር፤ ነክሰው ይዘው በይፋ የውግዘት ዘመቻ ከፍተውባቸዋል፡፡ በተለይ በአቶ መለስ ላይ ያላቸውን እንቅልፍ የሚነሳ የጥላቻ አባዜ፤ በደንብ ለማያውቃቸው ሰው እንኳን እንዲታይ አድርገው እርቃን አውጥተውታል፡፡ በአፍሪካ ላይ ከሚያወርዱት የመረረ የእርግማን መዓት በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው፤ ድቅል ኢትዮ-አሜሪካዊ ማንነት ለቸሯቸው ወገኖች ምን ያህል ጠቃሚ ሰው እንደሆኑ የማሳየት አቅል የሚነሳ የስሜት ግፊት ተጠናውቷቸዋል፡፡ ማንነታቸውን ለመፋቅና ለመርሳት አሳራቸውን አይተው፤ ኢትዮጵያዊ ምንጫቸውን አምርረው ከማውገዛቸው በፊት ሳይሆን ከዛ በኋላ ድርጊታቸው ሳያሳፍራቸው አልቀረም፡፡

ስለዚህ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ጥርሷን እንድትነክስ ለማድረግ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ታይቶ በጠ/ሚኒስትሩ አስተያየት ላይ የተጀመረው የሚዲያ የነገር ሽመና ውስጥ አል-ማርያም ዘለው ጥለቅ ማለታቸው የሚያስገርም አይሆንም፡፡ አሁን የተጠናወታቸው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የጥላቻ ዘር የመዝራት ተራ መንፈስ፤ ቀደም ሲል ሲነዳቸው ከቆየው የሸፍጥ መንፈስ ጋር የተጣጣመ ነው፡፡

ለዚህ አስረጅ ከተፈለገ፤ አሁን ከነመፈጠሩም የተረሳውን «HR13» የተሰኘ ማዕቀብ ሰበብ በማድረግ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በቁጣ እንድትነሳሳ ለማድረግ ምን ያህል እንደ ደከሙ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ሆኖም፤ አልማርምን እፈሩ ሲላቸው፤ የዓለም ዓቀፉ ፍ/ቤት በፕሬዚዳንት አልበሽር ላይ የእስር ትዕዛዝ በቆረጠባቸው ጊዜ፤ አቶ መለስ ከእርሰቸው ጎን የቆሙት፤ ይህን ደፋር አቋማቸውን ጣል አድርገው ከጀርባ ሊወጓቸው እንዳልሆነ ተረድተውታል፡፡ ፕሬዚዳንት አልበሽር፤ የክፉ ቀን ጓዴ ብዬ ያቀፍኩት ሰው ከመጋረጃ ጀርባ በእኔ ላይ ያሴራል የሚል ስሜት ቢኖራቸው ኖሮ፤ በቋፍ ሆኖ ያልተረጋጋው የሱዳን ሰላም እንዲደላደል ኢትዮጵያ እገዛ እንድታደርግላቸው ተደጋጋሚ ጥሪ ባላቀረቡም ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ ያጤነ ሰው፤ ባለፈው ጊዜ ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጋር ፊት ለፊት ሲገናኙ፤ ‹አቶ መለስ በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ፅኑ ፍላጎት ያላቸው፤ በአህጉራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ለሱዳን ጥቅም ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱ ወዳጃችን ናቸው› በማለት አልበሽር መናገራቸው አስገራሚ አይሆንበትም፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ፤ በዊክሊክስ ቀረበ የተባለው መረጃ አል-ማርያም በመሰሪ መንፈሳቸው አንሸዋረው ካቀረቡት ትርጉም ፍፁም የተለየ መልዕክት ያለው መሆኑ ከአልበሽር የተሰወረ አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ አቶ መለሰ ሲናገሩ ማስታወሻ የወሰደው ሰው፤ የማስታወሻ አወሳሰዱ በክፉ መንፈስ የተነሳሳ ሰው ጉዳዩን አንሸዋርሮ ለመተርጎም እንዲችል በር የከፈተውን ያህል በቅን ልቦና የሚያነብበውም የተሳሳተ መልዕክት እንዲወስድ መንገድ የሚከፍት ሳይሆን አይቀርም፡፡

የሆነ ሆኖ፤ አቶ መለስ የሱዳን መንግስት አመራርን በተመለከተ ተናገሩ ተብሎ የቀረበው ቃል በደንብ ሲጤን፤ በቃልም ባይሆን በመንፈስ፤ ከታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መመሪያ እና ተጨባጭ ተግባር ጋር የሚጣላ አይደለም ነው፡፡ ኢትዮጵያ፤ ምንም ዓይነት ምክንያት ቢቀርብ፤ በየትኛው የውጭ ኃይል የሚገፉ የሥርዓት ለውጥ አጀንዳን እንደማትደግፍ በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በፅኑ የሚያምነው፤ መንግስትን የመምረጥና የመለወጥ መብት የሀገሩ ህዝብ መብት መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ አስረጂ ማቅረብ የሚያስፈልግ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ለዚህ መርህ የማይናወጽ አቋም እንዳላት የሚያመለክቱ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያለውን ለአስራ አንድ ዓመታት የዘለቀ ሰላም ወይም ጦርነት የማይባል ሁኔታን የማስወገድ ግዴታውን ለመወጣት በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተቀርፆ የቀረበውን ባለአራት ነጥብ የሰላም ሃሳብ ማንሳት ይቻላል፡፡ ማንም እንደሚያውቀው የአካባቢው የሰላም ጠንቅ የሆኑትን፤ በርካታ ኤርትራዊያን እና ኢትዮጵያውያንም ፍፃሜያቸውን ለማየት የሚጓጉላቸውንና የዱቼ ሞሶሎኒ አፍሪካዊ መንትያ የሆኑት ኢሳያስ አፈወርቂ ፍፃሜ እንዲበጅላቸው (በተለይ መጀመሪያ ላይ) የውስጥ ግፊት እያለ፤ የተጠቀሰው የሰላም ሃሳብ የኢትዮጵያ የሰላም ፍላጎት መግለጫ ሆኖ አሁንም እንደፀና አለ፡፡

ኢትዮጵያ ለሰላምና ለዓለም አቀፍ ህግ መከበር ያላት ቁርጠኝነትና አቋም ይህን ይመስላል፡፡ በእርግጥ አሁን በአስመራ ቤተ መንግስት ያሉትና ማን አህሎኝነት የሚጠይቃቸው የኤርትራው አምባገነን ፕሬዚዳንት፤ ከውስጥ በሚነሳ ትግል ከሥልጣን ወርደው በምትካቸው እንደሳቸው ጦር አውርድ የማይል ሌላ ርዕሰ ብሔር ቢመጣ ከኢትዮጵያ በላይ የሚደሰት ሀገር አይኖርም፡፡ ያም ሆኖ፤ ኢትዮጵያን የዋሽንግተን ግሎባላዊ የኃይል እርምጃ ፕሮጀክት ጋሻ ጃግሬ አድርጎ የማቅረቡ የሥም ማጥፋት ዘመቻ ዛሬም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ታዲያ ይህን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ለመደገፍ ዘወትር በአስረጅነት የሚቀርበው ጉዳይ፤ ኢትዮጵያ «እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት» በሚል የሚጠራውን አሸባሪ ቡድን ከሞቃዲሾ ለማስወጣት በ1998 ዓ.ም የወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃ በተባበሩት መንግስታት እውቅና በተሰጠው የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ቡራኬ የተፈጸመና በራሷ ነፃ ውሳኔ የተወሰደ ንፁህ ኢትዮጵያዊ ተልዕኮ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎችም አሉ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ፤ ኢትዮጵያ ጅሃዲስቶቹን ለመመከት እና ራሷን ለመከላከል ይህን ወታደራዊ እርምጃ ስትወስድ ማንንም ሳታማክር በራሷ ነፃ ውሳኔ የተንቀሳቀሰች መሆኑንና በወቅቱም አሜሪካ መንግስት ተቃውሞ እንደነበር የሚያረጋግጥ መረጃ በዊክሊክስ ይፋ ባደረገው የኬብል መልዕክት ውስጥ አለ፡፡ ይልቅስ በአሜሪካ ኤምባሲ የኬብል መልዕክት ልውውጥ ውስጥ የሌለው፤ ኢትዮጵያ በጅሃዲስቶች ላይ የወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ ለድል መብቃቱ በግልፅ መታየት ሲጀምር የአሜሪካ ከፍተኛ መኮንኖች የኢትዮጵን የድል ካባ ሰርቆ ለመደረብ እንዴት ዓይነት ጥረት እንዳደረጉ የሚጠቁም ቃል ወይም ሀረግ ነው፡፡ ይህን ሆን ተብሎ እንዲታፈን የተደረገ እውነት ዛሬ እንደገና ማውሳት ያለው ፋይዳ ብዙ መጋነን የሚገባው አይደለም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን ጠቀስ አድርጎ ማለፍ ኢትዮጵያ ጅሃዲስቶችን ባሉበት ለመግታት ያደረገችው እንቅስቃሴ ለምን ሰፊ ጥርጣሬ እንዳጠላበት ያመለክተን ይሆናል፡፡ በእርግጥ፤ የሃገር ውስጥ ተቋዋሚ ኃይሎች በዚህ ረገድ የያዙት አቋም ለጊዜው እንተወውና የምዕራቡና ፅንፈኛ የሆኑት የአረብ ሚዲያዎችን በአንድ እንዲሰለፉ ያደረጋቸው አንድ ጉዳይ ቢኖር በኢትዮጵያ ወገን ያለውን እውነታ የማጣጣሉ ሥራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ ግዛት ተወስና በመንግስት የሚታገዝን የአሸባሪነት እንቅስቃሴ በእንጩጩ ለመቅጭት ስትንቀሳቀስ የሚሰማው ጆሮ አደንቋሪ የተቃውሞ ጩኸት መነሻው ይኸው እውነታን ሆን ብሎ ያለ መቀበል የተደራጀ ተመሳሳይ ሸፍጥ ነው፡፡ ያለ አንዳች ማጋነን፤ የኢትዮጵያ መንግስት የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ተገድዶ እርምጃ ሲወስድ፤ እርምጃው ዘወትር በአሉባልታ እና በጥርጣሬ ይታጀባል፡፡ ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያ የምትወስደውን እርምጃ በጥርጣሬ የሚያዩት ወገኖች ደግሞ ሀገሪቱ ከአሜሪካ ወይም ከእንግሊዝ ያልተናነሰ ግሎባላዊ ባህርይ ያለው የአሸባሪነት አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን መቀበል የሚሹት ወገኖች ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ኢትዮጵያ የወሰደችውን የፀረ-ሽብር እርምጃ ለማብራራት የምታወጣው እያንዳንዱን መግለጫ፤ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተዋናዮች ዘንድ ሁሌም በጥርጣሬ ይታያል፡፡ ትምክህት የሞላባቸው እነዚህ ተዋናዮች ሀገራት የሚወስዱትን እርምጃ በማስመልከት ከሚያወጡት መግለጫ የትኛው ቃል ሊታመን እንደሚገባ የመዳኘቱ መብት የእነርሱ ብቻ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ በተለይ ዓለምአቀፍ የሰባዓዊ መብት ተሟጋች የሚባሉት ተቋማት ኢትዮጵያ የምታወጣውን መግለጫ ሁሉ እየጠበበ ያለውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለመሸፈን በማሰብ የሚፈጠር ደመና አድርገው በማቅረብ ማጣጣልን የተለመደ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ ሴፕቴምበር 8 ያስተላለፈውና ዊክሊክስ ይፋ ያደረገው የኬብል መልዕክት በጨረፍታ መመልከት፤ ኢትዮጵያ የደህንነት ሥጋቶችዋን ለመመከት ሳይቃጠል በቅጠል ብላ የምትወስደው የህግ እርምጃ በምን ዓይነት ጥርጣሬ እንደሚታይ በጉልህ የሚያመለክት ነው፡፡ በተጠቀሰው በዚህ የኬብል መልዕክት፤ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ አጋር ተደርጎ የሚወሰደው የአሜሪካ ኤምባሲ የኢትዮጵያ መንግስት የኡጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ሰርጎ ገብ አሸባሪ ቡድኖችን አስመልክቶ በሰጠው ይፋ መግለጫ ላይ የጥርጣሬ ጥላ ሊጥልበት ይሞክራል፡፡

በወቅቱ፤ በሽብር ተግባር የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች ህዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮች ለማጥመድና ለመቅበር አቅደው የያዙት ፈንጂ በራሳቸው ድንገት ስህተት ፈንድቶ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ለሞት ተዳርገው ነበር፡፡ ሆኖም የአሜሪካ ኤምባሲ ከዚህ እውነተኛ መግለጫ በተቃራኒ ለሀገሪቱ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያስተላለፈው የኬብል መልዕክት፤ «የኢምባሲው ምንጮች እና ህቡዕ የመረጃ ዘገባዎች የሚጠቁሙት፤ በእርግጥ ይህ የቦንብ ፍንዳታ በኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ኃይሎች የተቀናበረ የቦንብ ፍንዳታ ሳይሆን እንደማይቀር ነው» የሚል ነበር፡፡

አዎ፤ በኋላ እንደታወቀው የኤምባሲው «ታማኝ» ህቡዕ የመረጃ ምንጭ ከሆኑት አካላት መካከል አንዱ ሌላ ሳይሆን፤ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ እንዲህ ሲባል፤ የዶ/ር መረራን የአደባባይ ገፅታ በነሲቡ ለሚወስዱ አንዳንድ ሰዎች ነገሩ አስገራሚ ይሆንባቸው ይሆናል፡፡ ሆኖም፤ እውነቱን አፍረጥርጠን እንነጋገር ከተባለ፤ የኢትዮጵያን ገፅታ ለማጥፋት የሚያግዝ የተሳሳተ መረጃ ማግኘት ሲፈለግ፤ ከዶ/ር መረራ በበለጠ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ዊክሊክስ፤ ተለይቶ በተጠቀሰው በዚህ ጉዳይ መረራ ጉዲና ላደረጉት ድካም በአጎት ሳም ምን እና ምን ያህል እንደ ከፈላቸው የጠቀሰው ነገር የለም፡፡ የሆነ ሆኖ፤ እርሳቸው ጥቂትም ቢሆን ቆንጠር ማድረግን ቸል የማይሉ ሰው በመሆናቸው ለፊርማቶሪ አገልግሎታቸው ያገኙት ክፍያ ከ30 ዱቡሎ የሚበልጥ አይሆንም፡፡

እንዲሁም፤ ዶ/ር መረራ አልፎ-አልፎ እንደ ተዋናይ እያሞናሞኑ እና እያከረሩ ስለሚያቀርቡት ፀረ - ኢምፔሪያሊስት ዲስኩር ኤምባሲው ያለው ሃሳብ ምን እንደ ሆነ ዊክሊክስ የጠቀሰው ነገር የለም፡፡ በግልፅ ማየት እንደሚቻለው፤ ዳረጎት ሰጪዎቻቸው፤ በዶ/ር መረራ ላይ አልፎ-አልፎ የሚታየው ወደ መኢሶን ዘመን ወሰድ የሚያደርግ አባዜ ብዙም ያሳሰባቸው አይመስሉም፡፡ ሰውዬው፤ ከአሜሪካ ኤምባሲ የመረጃ መስኮት ድረስ ወረደው በጆሮ ጠቢነት ለማገልገል ከማሸርገድ ወደ ኋላ የማይሉ ሰው መሆናቸውን ሲያዩ ይህ ነገር ለምን ደንታ ይሰጣቸዋል? ነገሩን ዝም ብለው ሲያዩት በመረራ ላይ እንዲህ ያለ ብያኔ መስጠት ተገቢ ያልሆነና የጭካኔ ቃል ሊመስል ይችላል፡፡

የሆነ ሆኖ፤ የአሜሪካ ኤምባሲ እና በእርሱ ቅፅር የመሸጉት ሌሎች ተቀጽላ ተቋማት፤ ኦፊሴላዊ ያልሆነ መረጃ ለማግኘት በፈለጉ ጊዜ አለኝታ አድርገው የሚመለከቷቸው አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ዶ/ር መረራ ብቻ አይደሉም፡፡ ነገሩ ፍፁም አሳዛኝ ቢሆንም፤ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ወደ ውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች ሲሮጡ፤ አቤቱታቸውን ብቻ ይዞ አለመሄድን የተለመደ ተገቢ ተግባራቸው አድርገው ይዘውታል፡፡ ወደ ኤምባሴዎቹ ሲሄዱ አቤቱታን ብቻ ሳይሆን መቅረብ ጆሮ ለሚሰጣቸው የውጭ ሀገር ሚሲዮን ሁሉ በደስታ ሹክ የሚሉትን በወሬ ለቃሚዎች መንደር የተናፈሰ የ«ውስጥ አዋቂ መረጃ» ያላቸው ሰዎች መስለውም ይቀርባሉ፡፡

የታማኝ ተቃዋሚነት ሀሳብ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ፍፁም እንግዳ ወይም ከማንነታቸው ጋር የማይጣጣም ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ፤ ማዕቀብ እንዲጣልና የኢህአዴግ መንግስት በዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ዘንድ ህጋዊ ተቀባይነት እንዲያጣ ለማድረግ ዘወትር ከውጭ ኃይሎች ጋር ሲዶልቱ የሚገኙትም ለዚህ ነው፡፡ አንድ ጊዜ መንግስት ህጋዊነት እንዲያጣ ካደረጉ በኋላ ቀጣዩ ተግባር ቀለም-ጠቀስ አብዮት ወይም በሰሞነኛ ፋሽን አረባዊ አመጽ እንዲቀሰቀስ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ራዕይና አርቆ አሳቢነት የሚጎድላቸው በመሆኑ፤ የሚጣለው ማዕቀብ ኢህአዴግ ከሥልጣን ከወረደ በኋላ በሀገሪቱ ላይ ሊያስከትል የሚችለው የረጅም ጊዜ ዘላቂ ጦስ ፍጹም ደንታ አይሰጣቸውም፡፡ በተመሣሣይ በውጭ ኃይሎች ላይ አብዝቶ መታመን ከሁሉም በላይ ወሳኝ ኃይል በሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ምን ዓይነት ምስል እንደሚያሰጣቸው ማሰቡን እንተወውና፤ ደጅ በሚጠኗቸው ምዕራባውያን ዘንድ የሚኖራቸውን አክብሮት ምን ያህል ዝቅ ሊያደርገው እንደሚችል እንኳን አይታያቸውም፡፡ ለምሣሌ፤ ሴፕቴምበር 20፤2009 ዓ.ም በተላለፈው የኬብል መልዕክት፤ መድረክ በተቋቋመ ማግስት የፓርቲው አመራሮች የሆኑት እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ ግዛቸው ሽፈራው፣ ቦህ ሁሴን ወዘተ. ከአሜሪካ ባለሥልጣናት የመጀመሪያ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ባለስልጣናቱ ስለ መድረክ የተናገሩትን ቃል ልታነቡት ትችላላችሁ፡፡ በተጠቀሰው የኬብል መልዕክት የሰፈረው ቃል፤ «..ይህ ቡድን [ማለትም መድረክ]…በወጉ የተደራጀ አማራጭ የወደፊት ራዕይ ይዞ አልቀረበም፡፡

እንዲሁም፤ አንድ ዓይነት አቋም እና የፖለቲካዊና ማህበራዊ ፕሮግራም ያላቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ በግልጽ እንደሚታየው የድርጅቱ አመራሮች አንድ አቋም እንዲይዙ ያደረጋቸው በጉዳዩ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋርጦ የማየት ጥልቅ የጋራ ፍላጎታቸው ይመስላል፡፡ ለዚህ አስረጅ ማቅረብ የሚያስፈልግ ከሆነ፤ በኬብል መልዕክቱ «ቦህ ሁሴን፤ አሜሪካ የምትሰጠው ያልተቋረጠ የምግብ እርዳታ፤ ኢህአዴግ የሰብአዊ እርዳታን በስልጣን ለመቆየት የፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም ያችለዋል… በማለት ቅሬታቸውን በፅኑ ገልፅዋል» በሚል የሰፈረውን ቃል መመልከት ይቻላል፡፡ ታዲያ ይህ ሀሳብ የሁሴን የግል አስተያየት ይሆናል የሚል አንዳች ጥርጣሬ እንዳይድርብን፤ ይኸው የኬብል መልዕክት አክሎ፤ «በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ለኤምባሲው ባለስልጣናት ተመሳሳይ ስሜታቸውን ገልጸዋል…» ይላል፡፡

ይህ ለአሜሪካ የቀረበ እና ብሄራዊ ስሜት የራቀው አቤቱታ በግልፅ የሚያሳየን መድረክ የተዘፈቀበትን ፈርጅ ብዙ የሞራልና የፖለቲካ ክስረት ነው፡፡ በአንድ በኩል፤ የተቃዋሚው ጎራ ያለ ውጪ ኃይል ዕርዳታ የኢህአዴግን የፖለቲካ የበላይነት ለመገዳደር ብቃት አለኝ የሚል በራስ መተማመን መንፈስ የሌለው መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል፤ መድረክ በስልጣን ላይ ያለው ኃይል የጥንካሬ ምንጭ አድርጎ የሚወስደው ጉዳይ ምን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ የመድረክ አመራር፤ አሜሪካ ቀድሞም እየቀነሰ የነበረውንና ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የምግብ እርዳታ በአስቸኳይ ቀጥ ብታደርገው ኢህአዴግ በእጅጉ ይዳከማል የሚል እምነት እንዳለው ግልፅ ነው፡፡

መቼም ስለ ኢህአዴግ እጥረት የቀረበው ይህ ግምገማ ፍፁም አሳዛኝና ጨርሶ የተሳሳተ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ፤ በመድረክ ግንባር ቀደም አመራር ኃይል ዘንድ ያለውን ሥር የሰደደ ችግር ፍንትው አድርጎ ያመላክተናል፡፡ በሌላ አገላለፅ፤ ለዊክሊክስ ምስጋና ይግባውና፤ መድረክ በጅ አዙር የምግብ እርዳታውን ለጠባብ የፖለቲካ አጀንዳው መጠቀሚያ ለማድረግ የሞራል ልጓም እንደ ሌለው ለመረዳት ችለናል፡፡ ታዲያ ምፀታዊ የሚሆንብን፤ የነፍስ አድን የምግብ ዕርዳታን በፖለቲካ ደጋፊነት ስሌት እያሰራጨ ነው የሚል መሰረተ ቢስ ውንጀላ ለበርካታ ዓመታት ይቀርብበት የነበረው ኢህአዴግ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፈው ዓመት ጥር ወር እንኳን ኢህአዴግ ከእርዳታ ለጋሾች ያገኘውን የገንዘብ ድጎማ ለድርጅቱ የፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚያ ማዋሉን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በሚል ማስታወቂያ በተነገረለት አንድ የቢቢሲ የዶኪመንተሪ ፊልም ተመሳሳይ ውንጀላ አቅርቦ ነበር፡፡ ማንም እንደሚገምተው በዚህ ዶኪመንተሪ ኮከብ የመረጃ ምንጭ ሆነው የቀረቡት ለታዳጊው የኢትዮጵያ ሪፐብሊክ አንዳች አስተዋፅኦ የሌላቸው መረራ ጉዲና፣ በየነ ጴጥሮስ እና መስፍን ወ/ማርያም ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዶክሜንተሪው ሲቀርቡ፤ በኢትዮጵያ የነፍስ አድን እርዳታ ሲሰጥ የተረጂው የድምፅ አሰጣጥ ታሪክ እየታየ መሆኑን ለማሳየት አሌ የማይባል ምስክርነት ያላቸው ሰዎች ተደርገው ነው፡፡

ሆኖም ከስነ ምግባር በራቀ ጥበብ ተቀናብሮ በቢቢሲ የዜና ክፍል የቀረበው ይህ ውንጀላ ያሳሰበው የእንግሊዝ መንግስት የራሱን ማጣራት አደረገ፡፡ እናም የማጣራቱ ውጤት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበቢቢሲ ምርመራ ተብዬ ዘገባንም ሆነ ሳያውቁት የዚህ ድራማ አካል በመሆን ምስክርነታቸውን የሰጡትን የመረጃ ምንጮች የሚደግፍ አንድም ማስረጃ ያልተገኘበት ሆነ፡፡ ይህ ድንቃይ ተውኔት በተሰራጨ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ከፍተኛ የእንግሊዝ መንግስት ባለስልጣን ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የተናገሩት «አዎ እናንተ ከጠቀሳችኋቸው ውንጀላዎች መካከል አንዱ፤ የምግብ እርዳታው በአግባቡ ለተረጂዎች እየተሰጠ አይደለም የሚል ነው፡፡ ይሄንኑ መሰረት በማድረግ ከ6 ወይም ከ7 ወር በፊት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ዝርዝር ፍተሻ አድርገው በምግብ እርዳታ አሰጣጡ ላይ ሥርዓት የያዘ ብልሹ አሰራር መኖሩን የሚያመለክት አንድ ማስረጃ አላገኙም» የሚል ቁርጥ ያለ ቃል ነበር፡፡

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሞራል ክስ የሚያስነሳ የብልሹ አድራጎት ውንጀላ ቀርቦበት ነጻ ሲወጣ የአሁኑ ሦስተኛው እንጂ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ከዚህም በኋላ በኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ አመራር ላይ ተመሣሣይ የብልሹ ድራጎት ክስ ቢቀርብበት የሚደንቅ አይሆንም፡፡

አሁን-አሁን ቋሚና ተገማች ቅርፅ ይዞ ስለሚታይ በኢትዮጵያ ላይ ሌላ ክስ መምጣቱ፤ ለጋሹም ማህበረሰብ ነገሩን ለማጣራት ሌላ አጣሪ ቡድን ለመሰየም መገደዱ አይቀርም፡፡ ያም ሆኖ፤ ኢህአዴግ በመንግስት ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የምዕራብ ለጋሾችን ዕርዳታ አላግባብ በመጠቀም ውንጀላ ላይ ሚካሄድ የማጣራት እንቅስቃሴ፤ ውጤቱ ካለፉት የተለየ እንደማይሆን በፍፁም እርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ታዲያ የምዕራቡ አጋር በሚባል ሌላ እርዳታ ተቀባይ መንግስት ላይ እንዲህ ያለ ውንጀላ እና በደል ቢፈፀም ለአመራሩ በርካታ የይቅርታና የማስተባበያ ጋጋታ ይዥጎደጎድለት ነበር፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ኢ ፍትሃዊ በደል ከመሸከም በቀር እስከ ዛሬ አንድም የይቅርታ መግለጫ ደርሶት አያውቅም፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የማያቋርጠው የውንጀላ፣ የማጣራት፣ ከዚያም ነጻ የመውጣት ዘወትራዊ ክስተት ታግሶ ዝም ማለቱ አስገራሚ ይሆንብናል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች፤ በአንድ በኩል ከምዕራቡ ሀገራት የሚያገኙትን ገንዘብ እነሱ ለፈለጉት ዘርፍ እንጂ ለጋሾቹ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በሚሉት ፕሮግራም ላይ አያውሉም እስከ ማለት የሚደርስ አለመጠን በራስ የመታመን ክስ ይቀርብባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ምዕራባውያኑ እንዳሉት የሚያድር ተንበርካኪ መንግስት በሚል ይታማል፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ምዕራባውያን በኢህአዴግ ላይ ጫና እንዲያሳርፉ በማግባባት ያሰብነውን ማሳካት እንችላለን የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ ያደረጋቸውም፤ የኢትዮጵያ መንግስት፤ ምዕራባዊውያን እንዳሉት የሚያድር መንግስት ነው የሚለው ይኽ ሀሳብ ነው፡፡ ለምሳሌ ምርጫ 97ን ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ፤ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በኋላ ላይ ቢፀፀቱም፤ በዚህ ጅል ሀሳብ ተነሳስተው በለጋሾች በእጅጉ ታምነው እንደ ነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም «ሁሉ አይጥሜ» የሆኑት የዲያስፖራ ትምክህተኞች ባንዲራ እያውለበለቡና የሀገር ወዳድነት ጩኸት እየጮሁ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የአሜሪካ ኮንግረስ አባላትን እንዴት እንደ ተማፀኑ ማስታወስም ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛ የሚባሉ ደግሞ ኋይት ሀውስ ጠንካራ «የማባበል እና የማስፈራራት» (Carrot and stick) ፖሊሲ በኢህአዴግ ላይ እንዲጭን አግባቢ ደላሎችን በመቅጠር ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ሆኖም፤ አል-ማርያምን ጨምሮ በአካዳሚያዊ ማዕረጋቸው እና የአሜሪካን ባህል ጠንቅቀው በማወቃቸው የሚጀነኑ በእንዲህ ዓይነት ሥራ የተካኑት ወገኖች ሁሉ ተመሳሳይ ቅዠት ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ እናም በዚሁ ቅዠት ሰክረው የኋይት ሃውስን ድጋፍ ከያዝን፤ በስልጣን ላይ ያለው ኃይል ፍፁም ተቀባይነት የሌለውን ጥያቄያቸውን እንዲቀበል ማስገደድ እንችላለን ብለው አስበው ነበር፡፡ ይህ ጅልና ኃላፊነት የጎደለው ስትራቴጂ እንደሆነ መናገር የሚቻለውን ያህል፤ ስትራቴጂው የመነጨው እነሱ በምራባውያን ዘንድ የሚሰማቸውን አቅመ ቢስነት በኢህአዴግ ላይ አንጸባርቆ ከማየት ችግር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ ችግሩ፤ የኢህአዴግ አመራር «ዝለል!» ሲባል «ምን ያህል ሜትር?» የሚል ምስኪን - ደካማ እንዳልሆነ አለማወቃቸው ነው፡፡

አዎ፤ ዊክሊክስ ይፋ ያደረገው መረጃ፤ ተቃዋሚ ኃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያራምዱት ፖለቲካ መለያ ቀለም በሆነው ከንቱ ጦረኛነት እና በእውነተኛ አገር ወዳድነት መካከል ያለውን ልዩነት፤ እንዲሁም በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከልም የሚታየውን ልዩነት በጉልህ የሚያንፀባርቅ ብርሃን ይፈነጥቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዊክሊክስ ይፋ ያደረገውና የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ የነበሩት ወ/ሮ ቪክ ሀድልስተን ስለ ግንባር ቀደሙ የኢህአዴግ አመራር ያቀረቡትን ግምገማ መመልከት በቂ ነው፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው፤ ወ/ሮ ሀድልስተን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በድህረ 97 ምርጫ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ለመሻት የሚያግዙ የአሜሪካ መንግስት መልዕክተኛ ሆነው ነው፡፡ እናም የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ከባድ አጀንዳ ሲፈጠር የትኛው ወገን ከጠባብ ፖለቲካው ወጥቶ ከፍ ያለ መርህን ሊከተል እንደሚችል ለመገንዘብ፤ የዓይን እማኝ መረጃ የማግኘት ዕድል እና ከኢህአዴግም ሆነ ከተቀዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር የመገናኘት በርካታ አጋጣሚዎች ነበሯቸው፡፡ በዋና ጉዳይ አስፈጻሚነት ኢትዮጵያ ውስጥ በቆዩባቸው ዓመታት በእንግድነት ስለተቀበለቻቸው ሀገር ኢትዮጵያ እና በሀገሪቱ ስላለው አመራር በቅርብ ለመረዳት የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው፡፡ ወ/ሮ ሀድልስተን «የኢትዮጵያን መንግስት ለማሳመን የሚያስችሉ ትክክለኛ እና የተሳሳቱ መንገዶች» የሚል ንዑስ ርዕስ ሰጥተው በፃፉት የስንብት ደብዳቤ የሚከተለውን ማሳሰቢያ አስፍረዋል፡፡

«ኢትጵያን የማገዝ ቁርጠኝነታችንን የማጠናከር ድፍረት ካገኘን፤ ብዙ የምናገኘው ጥቅም ይኖራል፡፡ ነገር ግን በአሜሪካ ያለውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ፣ እንዲሁ አንዳንድ የኮንግረስ አባላትን እና ጥቂት የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖችን ለማስደሰት ብለን በመለስ ዜናዊ ላይ ይፋ ተፅዕኖ ማድረግ ከጀመርን የኢትዮጵያን ወዳጅነት እናጣለን… አቶ መለስ ወርልድ ባንክና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን አጋርነት አበላሽተዋል ብለው በማመናቸው እነዚህ ተቋማት ሊሰጧቸው ያሰቡትን የ3 መቶ ሚሊየን ዶላር እርዳታ ለመተው ዝግጁ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እስከ አሁን ድረስ ከእኛ ጋር በወዳጅነት የቆየ ቢሆንም ነገሩ እየከፋ ሄዶ ወዳጅነታችን ከተበላሸ፤ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለውን የአጋርነት ትስስር መልሶ እንዲጠገን ማድረግ ይበጀኛል የሚል አመለካከት የመያዙ ጉዳይ አጠራጣሪ ይሆናል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ለሀገሪቱ የሚሰጠው እርዳታ ወደ ቀድሞው ደረጃ የተመለሰ ቢሆንም አቶ መለስ ከአውሮፓ ይልቅ ቻይናን እንደ አስተማማኝ ወዳጅ ተመልክተው ፊታቸውን ወደ'ሷ አዙረዋል፡፡ አቶ መለስ የማንንም ጥያቄ ከመቀበል ይልቅ ለሀገራቸው ብሄራዊ ጥቅም ይበጃል የሚሉትን ነገር የሚያደርጉ ናቸው» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡

ይህ በምንም ሚዛን ቢታይ፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አመራር ባህርይ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይና በትክክለኛ ሚዛን የተሰጠ ግምገማ ነው፡፡ በግልፅ እንደሚታየው፤ ወ/ሮ ሀድልስተን በአሜሪካ እና በእንግድነት በተቀበለቻቸው ኢትዮጵያ መካከል ዘላቂ ወዳጅነት እንዲፈጠር ለማድረግ የፖሊሲ አውጭውን አካል በተጨባጭ ሚዛን መገምገም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበዋል፡፡ የዲፕሎማሲ ሥራን አጋር ከመፍጠር አንጻር ሳይሆን የአሜሪካን አድራጊ ፈጣሪነት (hegemony) ከማረጋገጥ አኳያ ብቻ የሚመለከቱ ኃያል ኃይሎች በዋሽንግተን መኖራቸው ሲጤን፤ ይህ የሀድልስተን አካሄድ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ነገሩ ግራ አጋቢ የሚሆንብን፤ በአይዲዮሎጂ ፈረስ የሚጎተተውን ይህን አመለካከት የሚጋሩት ብቻ ሳይሆን፤ የዲፕሎማሲ ሥራ ማጠንጠኛ እንዲሆን የሚሹ ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊያን አሉ፡፡ ነገሩ ለመቀበል የሚከብድ ቢሆንም፤ አዲስ ማንነት የተቀበሉት እነዚህ ሰዎች፤ ጉዲፈቻ ባነሳቻቸው «የነፃዎች ምድር» እና በትውልድ ሀገራቸው መካከል የሞቀ ወዳጅነት መፈጠሩ የሚያስፈራቸው ይመስላል፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ ሥጋት ያላቸው አል-ማርያም ብቻ እንዳልሆኑ የሚገምት አንባቢ፤ ግምቱ ትክክለኛ ነው፡፡ አዎ፤ አል-ማርያም ብቻ አይደሉም፡፡

ሆኖም፤ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ፤ በተለይም ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በተመለከተ በድንቁርና አካሄድ ሀሳብ ከሚያቀነቅኑት ሰዎች መካከል እርሳቸው ቀንደኛው መሆናቸው እሙን ነው፡፡ አል-ማርያም፤ በቀላሉ ሊታወቅ በማይችል ሥነ-ልቦናዊ ችግር የተነሣ፤ ከአሜሪካ ጋር በንፅፅር ስትታይ እጅግ-እጅግ ደካማ የሆነችን ኢትዮጵያን በረጅሙ የኋይት ሀውስ እጅ ለመቅጣት አምርረው የተነሱ ሰው ናቸው፡፡ አል-ማርያም፤ ወ/ሮ ቪኪ ሀድልስተን፤ HR13 የተሰኘውን የማዕቀብ ረቂቅ ከንቱነት የገለፁበትና ኒውዮርክ ታይምስ በኖቬምበር 8/2007 ዓ.ም እትሙ በኤዲቶሪያል ገፅ ያተመው ጽሁፍ፤ እንዴት እንዳብከነከናቸው በቅርብ ካስነበቡን ጹሑፋቸው መመልከት ይቻላል፡፡ ወ/ሮ ሀድልስተን እንደ አል-ማርያም ያሉ ኢትዮ-አሜሪካውያን እንዲያፍሩ፤ «HR13»ን እውነተኛ ይዘት በማውጣት አጋለጡ፡፡ ይህ በክፉ መካሪ ቅስቀሳ የተረቀቀ ፀረ-ኢትዮጵያ ህግ፤ ይባስ ብሎ የአሜሪካንም ዘላቂ የሆነ ጥቅም የሚቃረን ህግ ነበር፡፡ አል-ማርያም ከቁጥጥር በላይ የሆነ ንዴት ሰፍሮባቸው፤ በህይወት ዘመናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የያዙትን ብቸኛ የፖለቲካ ተልዕኮ፤ ማለትም በትውልድ ሀገራቸው ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የማድረግ ተልዕኮ ምን እንደሆነ ባጋተጡት በወ/ሮ ሀድልስተን ላይ እሣት ጎርሰው- እሣት ለብሰው ተነሱባቸው፡፡ በንዴት ተንጨርጭረውና ገንፍለው የፃፉት ፅሑፍ የቋንቋ አጠቃቀም፤ ለረሽ ሊምባውፍ እንኳን ፀሐፊዋን ለማዋረድ አስፈላጊ ከሆነው ድንበር ዘልቆ የሄደ ዘግናኝ ዘለፋ ሆኖ ሳይሰማው አይቀርም፡፡

አል-ማርያም (የቋንቋ ድንፋታቸውን አቅበው) የሀድልስተንን ሙግት ለማጣጣል የሚያስችል ምሁራዊ ብቃት ቢቸግራቸው፤ ያረረ አንጀታቸውን ለማራስ የመረጡት ነገር፤ በሀድልስተን ላይ «አገሬውን የሆነች ዲፕሎማት» (a diplomat ‘gone native’) የሚል ታፔላ መለጠፍ ነው፡፡ ከዚያም፤ «አገሬውን ሆነች» (gone native) የሚለው የወፍ ቋንቋ ግራ ይሆንባቸው ይሆናል ብለው ያሰቡን ጥቂት ሰዎች ግር እንዳንሰኝ፤ ተቻኩለው የቃሉን ፍች ወደ መግለጥ አመሩ፡፡ እናም «አገሬውን መሆን» ሲባል፤ አንድ ዲፕሎማት በሄደበት ሀገር ባህል ተወርሶ ሲጠፋና የሚያቀርበውም የፖሊሲ ሀሳብ በሥራ የቆዩበት ሀገር የሚያራምደው ፖሊሲ ሲሆን ነው ይሉናል፡፡ እንዲህ ያሉ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችም «አገሬውን ሆኑ» (gone native) እንደሚባሉ አብራርተውልናል፡፡

ታዲያ ወ/ሮ ሀድልስተን፤ እንዲህ ያለ የልግጫ ቃል የሚሰነዘርባቸው ምን ቢያደርጉ ነው? በይፋ ከሚታወቀው ነገር ከተነሳን፤ ወ/ሮ ሀድልስተን «የማዕቀብ እርምጃው ሊኖረው የሚችለው ውጤት ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ማሸሽ ብቻ ነው» በማለት የአሜሪካ መንግስትን አስጠነቀቁ፡፡ ከዚህ ሌላ ያሉት የለም፡፡ እናም ለመንግስቱ ታማኝ እንደሆነ አንድ የመንግስት ሠራተኛ፤ «የኢትዮ- አሜሪካ ወዳጅነት ይበልጥ ሊጠናከር የሚችለው በጋራ የመከባበር መንፈስ በመሥራት ብቻ ነው» አሉ፡፡ እውነተኛ አስተያየትን መግለፅ ሥነ-ምግባራዊ ግዝት ሆኖባቸው ይህንኑ ተናገሩ፡፡ በቅርብ አይተው ከተረዱት ነገር በመነሳት፤ በዲያስፖራ የሚገኘውን እና በሀገር ቤት ያለውን ተቃዋሚ ኃይል የልብ ልብ ከመስጠት በቀር ሌላ ፋይዳ የሌለውን ማዕቀብ ከማፅደቅ የትዕቢት እርምጃ መንግስታቸው ይጠበቅ ዘንድ አስጠነቀቁ፡፡ ምክንያቱም፤ እንደ እርሳቸው አስተያየት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይል፤ የኢትዮጵያን ብሄረሰባዊና ሀይማኖታዊ ብዙህነት ለማስተናገድ የሚያስችል አቋምና ዴሞክራሲያዊ ባህርይ የሌለው ስለሆነ የሀገሪቱን አንድነት የማስጠበቅ ችሎታ ያለው አይደለም፡፡ ከዚህም በቀር፤ ሀድልስተን በHR13 ላይ ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ብቸኛ ሰውም አይደሉም፡፡

የኢትዮጵያን ምድር ረግጠው የማያውቁ በርካታ የኮንግረስ አባላትም፤ እርሳቸው የጠቀሷቸውን በርካታ ተመሳሳይ ምክንያቶች በመንተራስ በአዋጅ መልክ የሚወጣውን ማዕቀብ ተቃውመዋል፡፡ እናስ፤ እነዚህ የኮንግረስ አባላት ማዕቀቡን የተቃወሙት እንደ ሀድልስተን «አገሬውን የመሆን» ችግር ገጥሟቸው ይሆን? አዎ፤ አል-ማርያምን እረፍት የነሳቸው ሀድልስተን የኢትዮጵያን መንግስት መሪዎች በቀላሉ የማይቀመሱ ሰዎች አድርገው የማቅረባቸው ነገር ነው፡፡ እናም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሂላሪ ክሊንተን በቅርቡ በተካሄደ አንድ ህዝባዊ መድረክ ላይ በመገኘት ስለኢትዮጵያ የተናገሩት ቃል ምን ያህል ቁርጠት እንደሚለቅባቸው ማንኛውም ሰው ለመገመት አይቸገርም፡፡

የሚኒስትሯን ቃል መስማት የአል-ማርያም ጆሮ እንደ እሾህ የሚሸቀሽቀው ቢሆንም፤ ወ/ሮ ክሊንተን ኢትዮጵያ ማብቂያ የሌለው ከሚመስለው የምግብ ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ያላትን ቁርጠኝነት ከማሞገስ በቀር ሌላ የወጣቸው ነገር አልነበረም፡፡ አል-ማርያምን ጨርሶ እርር-ድብን ለማድረግ ያደሙ ይመስል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርዋ አወንታዊ ግምገማም፤ ወ/ሮ ሀድልስተን የኢትዮጵያ መንግስት «በእምነቱ አዳሪ» (assertive) መሆኑን በመጥቀስ ካሰፈሩት ትክክለኛ ግምገማ ጋር የሚጣጣም ነው፡፡

ቃላቸውን ለማስታወስ ያህል፤ በእርሳቸው አመለካከት የኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች የሚሰሩት የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም በላቀ አኳኋን የሚያስጠብቁ ነገሮችን ብቻ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች የሚኖራቸው አመለካከት ምንም ይሁን ምንም፤ የቱንም ያህል ኃያላን ይሁኑ፤ በኢትዮጵያ ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉት አይዲዮሎጂም ምንም ዓይነት ይሁን፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሌም የሚሰራው የሚያምንበትን ነገር ብቻ ነው፡፡ ይህን አመለካከት በማንፀባረቅ ረገድ አሁንም ሀድልስተን ብቸኛ ሰው አይደሉም፡፡ ለምሣሌ፤ በእርሳቸው እግር ተተክተው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ፤ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያቀረቧቸው በርካታ አቤቱታዎችም፤ ሀድልስተን ኢህአዴግ የማይታጠፍ የነጻነት ስሜት ያለው ፓርቲ ስለመሆኑ ያቀረቡትን ዘገባ ተዓማኒነት በድጋሜ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሆኖም አል-ማርያም ከማንም ባልተሰወረ ምክንያት ሴፕቴምበር 5/ 2011 ዓ.ም በዊክሊክስ የተደረገውን የአምባሳደር ያማማቶ የኬብል መልዕክት እንዲች ብለው ሊጠቅሱት አይፈልጉም፡፡ ሆኖም እኛ አንባቢያን ይህን የኬብል መልዕክት እንዲያነቡት እንጋብዛለን፡፡

ይህ የኬብል መልዕክት፤ አሜሪካ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ ይዛ የመጣች ሲመስለው ኢህአዴግ እንዴት አሻፈረኝ ባይ እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችል ዓይን ከፋች መረጃ ነው፡፡ አምባሳደር ያማማቶ በገዥው ፓርቲ ላይ ያቀረቡትን ረጅም የቅሬታ ደብዳቤ እዚህ እንደገና ለመጥቀስ ሥፍራ ይገድበናል፡፡ ስለዚህ አጠር ባለ መንገድ የደብዳቤውን ይዘት ለማየት አንኳር ጉዳዮችን ብቻ መጥቀሱ ይበቃል፡፡ አምባሳደር ያማማቶ ደብዳቤአቸውን የሚጀምሩት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ዓመታት IRS እና NDI የተባሉ የአሜሪካ ድርጅቶችን ከሀገር የማባረር እርምጃ የወሰደች የመጀመሪያ ሀገር መሆኗን በመጥቀስ ነው፡፡ ይህ እርምጃ እንደ እርሳቸው ቃል፤ የዋሽንግተንን የፖለቲካ ተሳትፎ ጨርሶ የሚያመክን ነው፡፡ አምባሳደር ያማማቶ ይህን ካሉ በኋላ አክለው፤ የአሜሪካን የንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ለማቋቋምና ሥራ ለመጀመር የቀረበውን የምዝገባ ጥያቄ «የኢትዮጵያ መንግስት ለአንድ ዓመት ያህል እንዲጓተት አድርጓል፡፡ በቴሌኮሙኒኬሽን ሴክተር የተለያዩ አካላት እንዲሳተፉ ያደርግ ዘንድ ከኤምባሲው የቀረበለትን ምክርም ሳይቀበለው ቀርቷል ይላሉ፡፡ አያይዘውም፤ «በሰው የሚከናወን የአየር መከላከል ስርዓት አደጋ» እንድታስወግድ (the threat of man-portable Air Defence system) አሜሪካ ያቀረበችውን ሀሳብ የኢትዮጵያ መንግስት አለመቀበሉን ይጠቅሳሉ፡፡ እንዲሁም፤ በሰሜን ኮርያ ድጋፍ የተቋቋመው የአምቦ የመሣሪያ ፋብሪካን ለማሳየት እንዳልፈቀደና «በእርስ የሚገኝን አንድ ሰው FBI ለመርመር ያቀረበውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ጠቅሰዋል፡፡

ይኸ ሁሉ ነገር የኢትዮጵያ መንግስት ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት የሚል መንግስት ነው የሚለው የተቋሚ ፓርቲዎች ሀሳብ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፤ ምንም ዓይነት መሸንገያ እና ማስፈራሪያ ቢመጣ፤ በግዛቱ ውስጥ ተገቢ መስሎ በታየው መንገድ የማስተዳደር ሥልጣኑን የሚገድብ ምንም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነትን አይቀበልም፡፡ መቼም «ተገቢ መስሎ በታየው መንገድ» ሲባል፤ በህግ ቅፅር ተወስኖ የመሥራት ጉዳይ መሆኑን ማውሳት አስፈላጊ አይሆንም፡፡ አሜሪካን የሚያህል ኃያል መንግስት የዓለም አለቃ የመሆን ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ በመተግበር ረገድ የገጠመውን እንቅፋት አስመልክቶ የሚናገረውን ነገር ተቃዋሚዎች ልብ እንደሚሉት ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እናም፤ ተቃዋሚዎች የአርበኝነትን ወይም የሀገር ወዳድነት ካርድን በማንሳት ኢህአዴግን ለማሳጣት የሚያደርጉትን ከንቱ ጥረት እርግፍ ይተውት ይሆናል፡፡ ደግሞም፤ ወ/ሮ ሀድልስተን ስለ ኢህአዴግ ሀገር ወዳድነት የሰጡት ምስክርነት፤ በተዘዋዋሪ መንገድ በአምባሳሩም የተደገመ መሆኑን በማጤን፤ አል-ማርያም የያዙትን አስረጅ የሌለው የስም ማጥፋት ተግባር ያቆማሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የሆነ ሆኖ፤ በቃሉ ሰፊ አተረጓጎም «አገሬውን ሆነ» (gone native) በሚል ሊጠቀስ የሚገባው ሰው ካለ፤ አል-ማርያም ብቻ ይሆናሉ፡፡ ሲጀምር፤ ሀድልስተን በኢትዮጵያ የኖሩት ለጥቂት ዓመታት ነው፡፡ እርሳቸው በኢትዮጵያ የቆዩበት ጊዜ፤ ሌላው ቀርቶ ነባር ባህሉን በቀላሉ እርግፍ አድርጎ የሚተው ሰው እንኳን «አገሬውን ለመሆን» የሚችልበት በቂ ጊዜ አይደለም፡፡ ይልቅስ በተቃራኒው አል-ማርያም ከሀገራቸው ከወጡ ጀምሮ አንድም ቀን ወደ ኢትዮጵያ ሳይመለሱ ለ40 ዓመታት በአሜሪካ ኖረዋል፡፡

እዚያው አሜሪካ ሆነው፤ ቢያንስ ላለፉት 37 ዓመታት አይተዋት ስለማያውቋት ሀገር በፍጹም ድፍረትና እርግጠኝት እየጻፉም ይገኛሉ፡፡ ከሀድልስተን ጋር ሲነፃፀር፤ አል-ማርያም ለረጅም ጊዜ በባዕድ ሀገር እንደ መኖራቸው መጠን ከወይዘሮዋ ይልቅ እርሳቸው «አገሬውን የመሆን» ሰፊ ዕድል አላቸው፡፡ ከዚህም በላይ፤ «የጠራ አሜሪካዊ» መስለው ለመታየት አሳራቸውን የሚበሉትና ቀኝ እጃቸውን ልባቸው ላይ ለጥፈው ለአሜሪካ ባንዲራ ያላቸውን ታማኝነት በመግለጽ ዜግነታቸውን የለወጡት አምባሳደርዋ ሳይሆኑ፤ «ናቹራላይዝድ» የሆኑት [ቀድሞ ተፈጥሮአዊ እንዳልነበሩ ዓይነት] ስደተኛው አል-ማርያም ናቸው፡፡ በሌላ በኩል፤ ሀድልስተን ኢትዮ-አሜሪካዊ የመባል ምንም ዓይነት ፍላጎትም ሆነ፤ ኢትዮጵያዊ ለመምሰል በስማቸው ላይ «ለታይ» የሚል ቅፅል የመጨመር አንዳችም ዓይነት አንገብጋቢ ምኞት ያላቸው አይደሉም፡፡

ሆኖም አል-ማርያም፤ ሀድልስተን ስለ ኢህአዴግ አመራር የሰጡት ምስክርነት በጌቶቻቸው ዓይን ታይቶ፤ ስንት ውቂያኖስ አቋርጦ ከሚገኝ ስፍራ ሆነው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ በፍፁም እርግጠኝነት ሲሸጠሸጡ የከረሙትን ነገር ውሃ እንዳይበላው ለመከላከል፤ ወይዘሮዋን «አገሬውን የሆነች» በማለት የዲፕሎማትነት ማዕረጋቸውን ገፈፉ፡፡ ምናልባት፤ ወ/ሮ ሀድልስተን ኢትዮጵያን በጦር ኃይል እንውረራት የሚል የኬብል መልዕክት ወደ ዋሽንግተን አስተላልፈው ቢሆን ኖሮ አገር ወዳድ አሜሪካዊ ይሏቸው ነበር፡፡ አል-ማርያም፤ ኢትየጵያ ከዓለም ካርታ እና ከታሪክ መዘክር በተፋቀች ጊዜ፤ ቀሪውን ዕድሜያቸውን በመረጡት ዲቃላ አሜሪካዊነት ላይ «ኢትዮ» የሚል ተቀጥላ ሳይለጠፍበት፤ ቀሪ የዕድሜ ዘመናቸውን ያለ ሰቀቀን ለመኖር ይችሉ ነበር፡፡ ከዚህ ከማይወዱት ቅፅል ተላቅቀው፤ እስከ ዛሬ ሲያደርጉት እንደቆዩት፤ በማይረቡ የአሜሪካ የፖለቲካ ፀሐፊዎች ስም ምለው እየተገዘቱ፤ ከጽሑፋቸውም ያለመታከት እየጠቀሱ፤ (ከአፍሪካ ፈላስፎች ጠብቀኝ እያሉ)፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ስለምትጥለው ማዕቀብ አስፈላጊነት ለማሳመን መዘብዘባቸውን ይቀጥሉ ነበር፡፡

ያኔ፤ በአውሮፓውያን የካርቦን ልቀት በአፍሪካ አህጉር ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሣ ይሰጥ የሚለውን ጥያቄ ያለ ሀፍረት የሚቃወም ብቸኛ ጥቁር አፍሪካዊ በመሆን ለፈጸሙት ጥፋት ይቅርታ ይደረግላቸዋል፡፡ ታዲያ ይህን ስንመለከት «አገሬውን ሆነ» የሚል ቅፅል የሚገባ ለማነው? ሥነ አመክንዮን ተከትለን ካየነው፤ ይህ ቅጽል የሚገባው ለሀድልስተን ሳይሆን ለአል-ማርያም ነው፡፡ በኔ ይሁንባችሁ! እንደ አል-ማርያም ያሉ ሰዎችን ልንሰጣቸው የሚገባው ስያሜ «የቤት ውልድ» ወይም ለፈረንጅ አምላኪዎች መጠሪያ የሆነውን «አጎቴ ቶም» (Uncle Tom) የሚለውን መጠሪያ ነው፡፡ ሆኖም፤ አል-ማርያም ስነ-ፁሁፋዊውን እና ኢ-መደበኛውን የአሜሪካ ቋንቋ ዘዬ አጥርተው የሚያውቁ በመሆናቸው፤ ለመጥፎ የፖለቲካ ታሪካቸው ፍጹም ተገቢ የሆነውን ቃል የመምረጡን ሥራ ለእርሳቸው እንተዋለን፡፡


Videos From Around The World

 


 
 


 Mark Your Calendar

 


 


 


 


 


 


 Custom Search

 


Opinions and Views published on this site are those of the authors only! Aigaforum does not necessarily endorse them. © 2002-2018 Aigaforum.com All rights reserved.