እውነትም ባለ ራዕዮች አይሞቱም!!!

ARTICLES

እውነትም ባለ ራዕዮች አይሞቱም!!!ከብርሃኑ ተሰማ(ኢዜአ)
ሕይወትና ተስፋ አይነጣጠሉም። ሕይወት ያለ ተስፋ ተስፋም ያለ ሕይወት ተነጣጥለው የሚቀሩ አይደሉም'። አገርም እንዲሁ ነች። ራዕይ የሌላት እንዲያው በመላ የምትጓዝ ከሆነች ተስፋ የላትም። የነገውን አሻግሮ የሚመለከት መጪውን የሚያስብ ብቃት ያለው አመራር የሚሰጥ መሪም ጎድሏታል ማለት ነው።

ዓለማችን ብቃት ያለው አመራር በመስጠት ራዕያቸውን የሰረጹና ለትውልዶች የተረፉ መሪዎች አላጣችም። በራዕይ ተመርተው አገራቸውን ለከፍተኛ ደረጃ ያደረሱና የሕዝባቸውን ሕይወት የለወጡ በዚያም ተመርተው ለታላቅ ግብ ያደረሱ ታላላቅ መሪዎች ያገኝችባቸው መልካም አጋጣሚዎች አሉ።

በዚያው ልክ በዕድገትና በልማት ሳይሆን ባሉበት በመርገጥ ሕዝባቸውን ሊያሳልፉት ቀርቶ የአገር ሀብት ለራሳቸው መንደላቀቂያ አድርገው ታሪክና ሕዝብ ሲረግማቸው የሚኖሩ መሪዎችም አልታጡም። አገርና ሕዝብን ወደ ውርደትና መቀመቅ ከተውም ራሳቸውንና አገራቸውን ያዋረዱ ማፈሪያዎች በታሪክ ተመዝግበዋል።

አገርና ሕዝብን ወደ አኩሪ የታሪክ ምዕራፍ ካሸጋገሩ ባለ ራዕይ መሪዎች መካከል የቱርኩ የነጻነት ተዋጊና ዛሬ ለደረሰችበት ዕድገት ያበቋት ሙስጠፋ ከማል ''አታቱርክ'' ይገኙበታል። ዘመናዊቷን ቱርክ ከድህነት አውጥተው ለብልጽግና ያበቁት ከጦር ሠራዊት መኮንንነት እስከ አገሪቱ ፕሬዚዳንትነት ድረስ ባሉት ደረጃዎች በመምራት ሕዝቧን በመሠረታዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ያደረጉም ጠንካራ መሪ ነበሩ።

በእሳቸው አስተዳደር በሺህዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች በመላው አገሪቱ ተገንብተዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በነጻ እንዲሰጥ ያደረጉ ሲሆን፣ዜጎች ትምህርቱን መከታተል ግዴታቸው ሆኗል። በአርሶ አደሩ ላይ የተጣለውም ታክስ እንዲቀነስ አድርገዋል።

ከማል አገራቸውን ለ15 ዓመታት በመምራት ቱርክን ከድህነት አውጥተው መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እንድትሆን መሠረቱን ጥለዋል።

የአገሪቱ መንግሥት በዚህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1934 ገና በሥልጣን ላይ ሳሉ እኚህን ታላቅ ሰው ''አታቱርክ'' ወይም የቱርክ አባት'' የሚል ስያሜ እንዲሰጥ ወስኖላቸዋል። ስያሜው ለሌላ ለማንም የአገሪቱ መሪ የማይሰጥ ማዕረግም ሆኖ ተደንግጓል።

ቱርካውያን ዛሬም በመሪያቸው ክብርና ኩራት እየተሰማቸው የነጻነት ትንፋሽ ይተነፍሳሉ።

ሕንድን ለትልቅ ደረጃ ያደረሰውን ዘመናዊ አስተዳደር የመሰረቱት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀዋህራል ኔህሩ ደግሞ ሌላው ባለ ራዕይ መሪ መሆናቸውን በታሪክ ተመዝግቧል። ኔህሩ የሚመሩት መንግሥት ሕንድ አሁን ላለችበት የዕድገት ጎዳና መንገዱን በመጥረግ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል።

የአገሪቱ ሰላምና የነጻነት ታጋዩ ማህተማ ጋንዲ አገሪቱን ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ በማውጣት ያደረጉትን ተጋድሎ ኔህሩ ብቃት ያለው አስተዳደር በመዘርጋትና ሕዝቡን ለሥራና ለዕድገቱ የሚያነሳሱ ተግባራትን በመፍጠር አግዘዋል።ለዘመናዊት ሕንድ መፈጠር ያላሰለሰ ሚናም ተጫውተዋል።

ሕንድ አሁን ለደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የተጣለውና ከአምስቱ እጅግ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አገሮች (የብሪክስ አገሮች)ተርታ የተሰለፈችው አርቆ አሳቢው መሪዋ መሪዋ ባስቀመጡላት መሥመር በመጓዟ ነው።

የአብራካቸው ክፋይ የሆኑት ሦስተኛዋ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢንድራ ጋንዲና የልጅ ልጃቸው የአገሪቱ ስድስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ራጂቭ ጋንዲም አገሪቱን በብቃት ለመምራት ችለዋል። በዚህም የኔህሩ ቤተሰብ ሕንድን ለመምራት የተፈጠረ እስከመባል ደርሷል።

በእስያ አህጉር የምትገኘዋን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላትንና ራሷ እንደ አንድ ንዑስ ክፍለ አህጉር የምታክለዋን ሕንድ ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮች በመፍታት የተሻለ ሕይወት እንዲመራ ያደረጉት ኔህሩ ሚናቸው ዛሬም ይወሳል።

ኔህሩ ከአገራቸው አልፈውም የገለልተኞች አገሮች እንቅስቃሴም በመመስረት ከፍተኛ ድርሻ ከነበራቸው መሪዎች አንዱ ናቸው።

ሊቀመንበር ማኦ ዜዱንግ ሕዝቡን በማስተባበር የቻይናን አብዮት በመምራት አገሪቱን ከኢምፔሪያሊዝምና ከምዕራባውያን ጥገኝነት ነጻ በማውጣት ታሪክ ሰርተዋል።

ሆኖም በኢኮኖሚ መስክ ቻይናን ከሌላው ዓለም እንድትገናኝ በማድረግ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ዴንግ ዢያዎ ፒንግ የተባሉ ዕውቅ መሪ ናቸው ፒንግ የገበያ ኢኮኖሚን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ መሪም ናቸው።

ፒንግ የአገሪቱን ሕዝብ የሥራ ባህል በማሳደግና የንግድ ልውውጡን መጠን በመጨመር ብቃትና ጥራት ያላቸው ምርቶችን ለገበያ አቅርቦ እንዲጠቀም ያደረጉ መሪ ናቸው።

አገራቸው የምትከተለውን የኮሙኒዝም ፖለቲካ መሥመር መሠረቱን ሳይለቅ በኢኮኖሚ ፖሊሲ ታግዞ እንዲሰራ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ቻይና ዛሬ ላለችበት የኢኮኖሚ ዕድገት እንድትበቃ መሠረቱን የጣሉትና ሕዝቧ በዚያ ጎዳና ለማራመድ የበቃችው ባለራዕዩ መሪ በቀየሱት ጎዳና ተጉዛ ነው።

ኢተዮጵያ በተሰናባቹ ዓመት መጨረሻ ታላቁን መሪዋን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በሚቆጭ ሁኔታ አጥታለች።ተፈጥሮን አይሞግቱት ሞትን አያስቀሩት ሆኖ ሕዝቡ በቆራጡና በደፋሩ መሪ ህልፈት እስካሁን ከማዘን አልወጣም። በኢህአዴግና በሚመሩት መንግሥት ፍላጎትም ጭምር የማይገባ ተደርጎ በሚወሰደው ራስን ያለማስተዋወቅ ባህል ምክንያት ሕዝቡ መሪውን ማወቅ የቻለው ካለፉ በኋላ ነው።ቅየሳውን እንጂ፤ዋናውን መሐንዲስ ሳያውቅ መለየታቸው በእጅጉ አሳዝኖታል።

ሕዝቡ የአገሪቱን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ያውቃል። ከዚያ ጀርባ ያለውን ነገር ግን ሳያውቅ ኖሯል። ለዚህም ነው መሐንዲስ መለስን ሲያውቅና ህልፈታቸውም ያስከተለበትን ኅዘንና ቁጭት ለመወጣት በአንደኛው ዙር ያደረገውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ አስተዋጽኦ ያለማቅማማት ለሁለተኛ ዙር ሊደግም የተነሳው።

ቢችል ቢችልማ ግድቡን ከተያዘለት ጊዜ ገደብ አስቀድሞ በማጠናቀቅ ለኢንዱስትሪው ዕድገት መሠረት የሚሆነውን የኃይል አቅርቦት ከወዲሁ በማግኘት ዕድገቱን ለማፋጠን ይጥራል። ታላቁን መሪ እያስታወሰ ወደ መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የዕድገት ጉዞውን ያፋጥናል።

ይህም ምነው በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ፍቅርና ክብር ሳያውቁት መለየታቸው የሚያሰኝ ቁጭት ፈጥሯል። እንዲያውም አንድ ወዳጄ እንዳለኝ ሕዝቡ ቀደም ሲል መለስ እንዲህ እንዳሁኑ ቢያውቃቸው ኖሮ፤ በጎዳናዎች ያለ አንዳች አጃቢ በፈለጉት ሥፍራ መንቀሳቀስ ይችሉ ነበሩ ብሎኛል።ዛሬ በሕዝብ ልብ ውስጥ እንደገቡት ሁሉ፤በየቤታችንም እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ለመግባት ይችሉ ነበር ለማለት በመሆኑ ወድጄዋለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከሕዝብ ለሕዝብና በሕዝብ ሆነው በዚህች ዓለም የተሰጣቸውን ዕድሜያቸውን አጠናቀው ወደዚያኛው ዓለም ታሪክ ሰርተው ሄደዋል።ጥለው የሄዱት አኩሪ ታሪክ ድርጅታቸው ኢህአዴግ እንደሚያስቀጥለውም ጅምሮቹ እያሳዩን ናቸው። አቶ መለስ ጥለውት የሄዱት ትሩፋት ብዙ ነውና እንጽናናለን።

ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት ዘንድሮ እንደ ሌሎች ዓመታት በደስታና በተድላ አልተቀበሉትም። ባለፈው ዘመን በተለይም በዓመቱ መጨረሻ የቤተሰቡን አባል ያጣ ሰው እንደሚሆነው ሁሉ አገርም መሪዋን አጥታ ያለ አባወራ ወይም እማወራ የሆነች ያህል ሆና ሌላውን የተፈጥሮ ዑደት ተቀብላለች።መለስ በአመራርም ሆነ በሕይወት የሌሉበትን የመጀመሪያውን አዲስ ዓመት።

ሕዝቡ በባለ ራዕዩ መሪ ህልፈት በእጅጉ ያዘነው የጀመሩት እንዳይቋረጥበትና ያሳዩት ብርሃን እንዳይጠፋበት ነው። ብሎም እሳቸውን የሚስተካከል መሪ አላገኝም በሚል ቁጭት ጭምርም አዝኗል። መለስ ያመጡለትን በልፋቱና በድካሙ ራሱን ጠቅሞ አገሩን የሚገነባበት አቅጣጫ፣ መሠረታዊ ችግሮቹን የሚያቃልሉ ተቋማትን የመገንባትና መሠረታዊ ጥቅሞቹን ማስከበር ነው።ሕዝቡ እነዚህ ስለጠቀሙት እንዲቋረጡበት ወይም እንዲስተጓጎሉበት አይፈልግም።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕዝቡ የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት የድህነትና የኋላቀርነት ሕይወት አብቅቶ ለተተኪው ትውልድ ኑሮ ምቹ የሆነች አገር ለማውረስ የሚጥር ትውልድ ፈጥረው አልፈዋል።አንድ ኢትዮጵያዊ እንዳለው በተለይ ለወጣቱ ድንጋይ ዳቦ እንደሚሆን አሳይተዋል።ሌላውም እንደ አቅሙ ሥራ ፈጥሮ ራሱን የሚያስተዳድርበት መንገድ አይቷል።

እኚህን ታላቅ የዘመናችን ምርጥ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የአሁኑና የወደፊቱ ትውልዶች ጭምር የሚያስታውሱባቸው የሚከተሉት ነገሮች ቢፈጸሙ አስተያየቴን አቀርባለሁ፥

ታላላቅ ፕሮጀክቶች በስማቸው ቢሰየሙ(የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ)

በአገሪቱ ታላላቅ ከተሞች የሚገኙ ዋነኛ አደባባዮች፣ ጎዳናዎችና ወደፊት የሚገነባው ብሄራዊ ስታዲዬም በስማቸው ቢሰየም

የገንዘብ ኖትም በምስላቸው ቢወጣ

የመታሰቢያ ቴምብሮች ቢታተሙላቸው

ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በስማቸው ቢጠሩ

የተወለዱበት ግንቦት 1 ቀን በስማቸው ተሰይሞ በስማቸው ቃል ኪዳን የሚገባበትና ገድላቸው የሚዘከበርበት ቢሆን አይበዛቸውም እላለሁ።እናንተስ?

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለታላቁ መሪው ያሳየውን ፍቅርና ክብር ራዕያቸውን በማሳካት በተግባር ይተርጉመዋል!!!


Opinions and Views published on this site are those of the authors only! Aigaforum does not necessarily endorse them. � 2002-2019 Aigaforum.com All rights reserved.