ከስሮ ዕርቃኑን የወጣው አስተሳሰብና የአቀንቃኞቹ ዝምታ

Articles

ከስሮ ዕርቃኑን የወጣው አስተሳሰብና የአቀንቃኞቹ ዝምታዘአማን -ከአዲስ አበባ 11/5/11-
“…የ20ኛውን ክፍለ ዘመን ርዕዮተ-ዓለማዊ ጦርነት ሊበራል ዴሞክራሲ አሸንፏል፡፡ የሶቭየት ህብረት ካምፕ በመፈራረሱም ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎቹ መላውን ዓለም እያጥለቀለቁት ነው፡፡ እናም ሊበራሊዝም የታሪክ መጨረሻው ነው፡፡…”

ይህ አባባል ሰሞኑን አይጋ ፎረም በተሰኘውና የኢትዮጵያ ጉዳዮች በሚተነትኑበት ድረ- ገጽ ላይ አቶ ጌታቸው መኳንንት የተባሉ ብዕረኛ፤ ፍራንሲስ ፍኩያማ የተባለና በታሪክ ዑደት ላይ “የሞት ብያኔ” በመስጠት የሚታወቀው ምሁር እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም ያሳተመውን መጽሐፍ በመጥቀስ ያቀረቡት ነው፡፡

ይሁንና አቶ ጌታቸው እንደሚስማሙበት፤ ሊበራሊዝምና ኋላ ላይ እርሱን ተከትሎት የመጣው አዲሱ ሊበራሊዝም (Neo-Liberalism) የጃፓን ደም ያለው አሜሪካዊው ፍኩያማ “ በሐሰተኛ መሲህነት” እንደተነበየውና የርዕዮተ ዓለሙ አራማጅ ሀገራት እንደሚያቀነቀኑት ዓለም በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ተሸብባ አልቆመችም፡፡

እርግጥ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያ ጀምሮ የኒዮ - ሊበራሊዝም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሳቤዎች በግድ እንዲሲፋፉ ቢደረጉም፤ ሰሞኑን የአመለካከቱ አቀንቃኞች በሆኑት በአሜሪካና በአውሮፓ(በተለይም በአሜሪካና በእንግሊዝ) እንደ ሰደድ እሳት በበርካታ ከተሞች እየተዛመተ ያለው “የህዝቦች ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል” ጥያቄን ያነገበው ሰላማዊ ሰልፍ፤ ኒዮ - ሊበራሊዝም አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ የተሳነውና አስተሳሰቡም ከስሮ ዕርቃኑን እየወጣ መሆኑን የሚያመላክት ትዕይንት ሆኗል፡፡

የዓለም ህዝቦችን አስተሳሰብ እንደ ሃውልት በአንድ ቦታ ላይ ገትሮ ለማቆም ያሰበው የፍኩያማ “የመጨረሻው ዘመን ትንቢት” ፖለቲካዊ -ኢኮኖሚ አመለካከቶቹን በዓለም ሀገራት ላይ በኃይል ሲጭን የነበረው ኒዮ - ሊበራሊዝም ለመውደቅ እየተንገራገጨ መሆኑን በርካታ አመላካች ዋቢዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የቅርብ ጊዜውን ብቻ እንመልከት ብንል እንኳን፤ የሰሞኑን የአሜሪካ ህዝቦች “የፍትሐዊነት ያለህ!” ጩኹትን በእማኝነት መጥቀሱ በቂ ይመስለኛል፡፡ “ዎል ስትሪት” የተባለውን የገበያ ማዕከል የወረሩት የዚያች ሀገር ዜጎች “እኛ 99 በመቶ የሆነውን መካከለኛ የህብረተሰብ ክፍልን (middle class) ከአንድ በመቶ ባለጸጋዎች ለመታደግ ነው ሰልፍ የወጣነው” የሚል መፈክርን የተመለከተ ማንኛውም ሰው፤ እርግጥም የኒዮ - ሊበራሊዝም ርዕዮተ - ዓለም ፍትሐዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማስፈን ተስኖት ህዝቦችን ምን ያህል ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ይህን መሰሉ “ፍትሐዊ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም” የሚል ጥያቄ ያልተነሳባቸው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሀገራት፤ ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሚከተሉት ርዕዮተ - ዓለም ትክክለኛ መሆኑን የኒዮ-ሊበራሊዝሙ አስተሳሰብ ክስረት አንፃር ህያው ማረጋገጫ ሆኗል ይቻላል፡፡

ይህም የሀገራችን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን በአላዋቂነትና በጭፍን በማጣጣል እንደ ኢትዮ-ሚዲያ፣ ኢትዮጵያን ራቪው፣ ወዘተ. … በመሳሰሉ ድረ- ገጾችና በሀገር ውስጥ አንዳንድ “ጉዳይ ፈጻሚ” የግል ጋዜጦች አማካኝነት ሲያላዝኑ የነበሩት እንደ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም እና ዶክተር አክሎግ ቢራራ ዓይነት ሰዎችን በሃፍረት እንዲሸማቀቁ ያደረገና በአሁኑ ወቅት እምጥይግቡ ስምጥ የማይታወቅ እስኪመስል ድረስ አፋቸውን እንዲዘጉ ያደረገ ክንዋኔ ነው፡፡

እስቲ በቅድሚያ ለአንባቢዎቼ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፤ የአቶ ጌታቸውን ሃሳብ በመውሰድ የፍራንሲስ ፍኩያማን “የኋላኛው ዘመን ትንቢት” ተከትሎ ኒዮ -ሊበራሊዝም የተጓዘባቸውን የተሳሳቱ አካሄዶችንና ለክስረት ያበቁትን ክስተቶች ልቃኝና፣ የርዕዮቱ አቀንቃኞች ተቋማትን እንዲሁም በስመ “ፕሮፌሰርነትና ዶክተርነት” የሊበራሊዝም ደቀ-መዝሙር ሆነው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አሰራሮችን ሲያጣጥሉ ወደ ነበሩት ጨለምተኛ ምሁሮች ዝምታ ልመለስ፡፡

… እንደሚታወቀው የሶቭየት ህብረትን ሶሻሊስታዊ ጎራ ያፈራረሰው ከፖለቲካዊ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ነው የሚሉ በርካታ ተንታኞች አሉ። ሆኖም የሊበራሊዝም ርዕዩት በሁለት ጎራ ተከፍሎ የነበረውን የዓለም ካምፕ ወደ አንድ ዋልታነት ሊያጠበው መቻሉ በወቅቱ “አሸናፊ” አልነበረም ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ታዲያ ይህን ተከትሎም የአስተሳሰቡ አቀንቃኞች የሆኑት ሀገራት “የአሸናፊነት” መንፈሱን ምርኩዝ በማድረግ አመለካከቱን ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለማስረፅ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡

በዚህም የኒዮ - ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ዋነኛ መሰረት የሆነውን ‘ሁሉም ነገር ለገበያና ለግሉ ባለሃብት መተው አለበት፤ መንግስት ህግና ሥርዓትን ከማስፈን ውጪ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም” የሚሉ አክራሪ አመለካከቶችን በዓለም ላይ እንደ ወረርሽኝ በግድም ይህን በውድ ለማዛመት ጥረት አድርገዋል፡፡እናም አስተሳሰቡን የማይደግፉትም ይሁን የሚደግፉት ሀገሮች በግዳጅ እንዲቀበሉት የርዕዩቱ አራማጆች ባቋቋማቸው ሚዲያዎችና የተለያዩ ስያሜዎችን በተቸሩ “ድርጅቶች” አማካኝነት ጫና ሲፈጥሩ ነበር፡፡

ይሁንና ገና ከጅምሩ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ህዝቦች የእነ ፍራንሲስ ፍኩያማን ብያኔ በመቃወምና ትክክለኛነቱን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት፤ ‘ስለምን የኒዩ - ሊበራሊዝምን አስተሳሰብ እንደወረደ እንቀበላለን?’ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ፖለቲካዊ -ኢኮኖሚ አስተሳሰብን ለማክሰም የኒዮ - ሊበራሊዝም አቀንቃኞች መፍትሔ ያልሆነ መፍተሔን ተከትለዋል፡፡ በዚህም እነዚህ ሀገራት “ወደ ታሪክ የመጨረሻው ምዕራፍ” መሸጋገር የማይፈልጉ “አሜኬላ- እሾሆዎች” ተደርገው በመቆጠራቸው የሊበራሊዝም የፈጠረመ ጡንቻ ሰለባ ሊሆኑ ችለዋል፡፡

የእምነቱ አራማጆች በውጭ በራሳቸው ሚዲያዎችና “ድርጅቶች” እንዲሁም ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የኛዎቹ ምሁር ተብዬዎችን ዓይነት ግለሰቦችን በማጥላላት ስራ ላይ አሰማርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም፤ በሀገራቱ ውስጥ ተቃዋሚዎችን በማደራጀት “አብዮት” ከሚለው ቃል ፊት ለፊት የለተያዩ ህብረ - ቀለማት ያላቸውን የፍራፍሬ ስያሜዎችን እየሰጡ ማመሳቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ከማንኛችንም የተሰወረ ሃቅ አይደለም፡፡ ይህን እንጂ፤ “ትልቁ ዓሳ ፣ ትንሹን ዓሳ ይውጠዋል” የሚለው ብሂል ከሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ውጪ፣ በሊበራሊዝም የሃይል ጫና ሊሰራ የማይችል መሆኑን አልተገነዘቡትም፡፡

በፖለቲካው ረገድ፤ ከነባራዊ ሁኔታቸው ጋር የማይሄደውን የኒዮ - ሊበራሊዝምን አስተሳሰብ በቀለም አብዮት መፈንቅለ መንግስት አማካኝነት እንዲቀበሉ ያደረጓቸው እንደ ዮክሬይን ዓይነት ሀገሮች፣ የማታ ማታ የርዕዮተ -ዓለሙ አካሄድ የተሳሳተ መሆኑን አብነታዊ ማረጋገጫ ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡ የዩክሬይኑ “ብርቱካናማ አብዮት” አቀጣጣዩች በከፍተኛ የኒዩ-ሊበራሊዝም ድጋፍ የስልጣን እርካብን እንዲቆናጠጡ ቢደረግም፤ ከዓመታት ቆይታ በኋላ በዚች ሀገር በተደረገው ምርጫ የአብዮቱ መሪዎች በህዝቡ ምሬት ከስልጣን እንዲባረሩ ተደርገዋል።

በስልጣን ዘመናቸው የራሳቸውን ሃብት ከማከማቸት በስተቀር ለዜጎቻቸው ያመጡት አንዳችም ነገር ባለመኖሩ፣ በፈጸሙት የሙስና ቅሌትና የስልጣን ብልግና እንዲከሰሱና ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲቀጡ ተደርገዋል፡፡ ይህ ሃቅም በዴሞክራሲ ሰበብ “በዓለም ላይ እኔ ብቻ ነኝ ትክከል” በሚል እሳቤ ከሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ፖለቲካን በኃይል መጫን አግባብነት የሌለው አካሄድ መሆኑን ከመመስከሩም ባሻገር፤ የኒዮ - ሊበራሊዝም ርዕዮተ - ዓለም በዓለም ህዝቦች ዘንድ ተቀባይነት እያጣ መሄዱን የሚያመላክት ነው፡፡

እርግጥ የኒዮ- ሊበራሊዝም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በተከታዩቹ ሀገራት ህዝቦች ጭምርም እየተወገዘ ነው፡፡ ርዕዮቱ በባህሪው በጥቂት የግል ባለሃብቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ ማህበራዊ መሰረቱ ይኸው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ እናም እጅግ የሚበዛው የህብረተሰብ ክፍልን የዘነጋው ይህ ስርዓት፤ መንግስታዊ መሰረቱ ጥቂት ባለሃብቶች ስለሆኑ ዴሞክራሲውም ለእነርሱ የቆመ ነው።

ሰሞነኛው ከ1400 ከተሞች በላይ ዜጎች የተሳተፉበትና በስርዓቱ ላይ የተቃጣው የ99 በመቶ ህዝባዊ ውግዘት የክስተቱ አንዱ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ በመዛመት ላይ በሚገኘው ስልፍ ላይ የዚያች ሀገር ዜጎች፣ “This is what your democracy looks like” (የእናንተ ዴሞክራሲ የሚመስለው ይህን ነው) የሚል የምሬት መፈክር ይዘው መውጣታቸው፤ በርዕዮተ -ዓለሙ ውስጥ የዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑን በአደባባይ የሚገልጽ እውነታ ነው፡፡ በፖለቲካው ረገድ በውጭና በውስጥ በእነዚህ ሁኔታዎች ኪሳራዊ ማንነቱ በአደባባይ ተገልጦ የታየው ኒዮ-ሊበራሊዝም፤ በኢኮኖሚው በኩልም የገበያ አክራሪነትን (market fundamentalism) እንዲሁም ‘መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም’ የሚሉ አስተሳሰቦችን በሌሎች ሀገራትና በራሱ ውስጥ ገቢራዊ ቢያደርግም፣ መጨረሻው ሰሞነኛውን ክስተት ማስተናገድ የግዱ ሊሆን ችሏል፡፡

በቀደሙት ጊዜያት በፍኩያማ “የታሪክ መጨረሻ” ተብሎ የሐሰት ትንቢት የተቸረው አስተሳሰቡ በተጀመረባቸው ሀገራት ውስጥ እንኳን ”የመጨረሻው አመለካከት”ሊሆን አልቻለም፡፡ የርዕዮተ -ዓለሙ መሰረት የሆኑት ጥቂት ባለሃብቶች እጅ የሚገኙት ባንኮች እና ኮርፖሬሽኖች፤ ባለፉት ዓመታት በፈጠሩት ጣጣ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ እንዲፈጠር አድርገዋል።ሆኖም መንግስታቱ አብዛኛውን ህዝብ ከቀውሱ ከማውጣት ይልቅ፣ አነዚህን ድርጅቶች በመደጎም በጣት የሚቆጠሩ ባለሃብቶችን ከኪሳራ ለማዳን ተሯሩጠዋል፡፡

ታዲያ ይህ ድርጊታቸው በየሀገራቱ ውስጥ ከስራ መቀነስንና ስራ አጦችን መፍጠርን እንዲሁም “ማህበራዊ ፍትህ ተጓደለብኝ” በሚለው ዜጋ ላይ የታክስ ጭማሪ ማስከተልን፣ በጡረታ ያለመታቀፍን እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶችን በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ፈጥሯል፡፡ ሰሞነኛዎቹ “ጥቂት ባለሃብቶችን ታክስ አስከፍሉ፣ የስራ ዕድል ፍጠሩልን፣ ከስርዓቱ መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋ በሐብት ክፍፍሉ ፍትሐዊነት ተጠቃሚ መሆን አልቻለም ወዘተ.” የሚሉትና በመገንፈል ላይ የሚገኙት ብሶቶች፤ ኒዮ-ሊበራሊዝም እንኳንስ ለሌሎች ሀገሮች ሊጠቅም ቀርቶ፣ በሀገሩ ውስጥም ተቀባይነት ማጣቱ በግላጭ እንድናየው ያደረገን እውነታ ነው፡፡

ይሁንና ይህ የኒዮ-ሊበራሊዝም ክስረትና የህዝቦችን አመፅ እንዲሁም በየሀገራቱ ህግና ስርዓትን ለማስከበር የተወሰደውን ርምጃ ሥርዓቱ በአምሳያው የፈጠራቸው ሚዲያዎች፣ በሰብዓዊ መብት ሽፋን የተቋቋሙ እና “የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነን” የሚሉ ድርጅቶች ላለማመን ሲጥሩ እንዲሁም አፋቸውን ሲለጉሙ አስገራሚ ክስተት ሁኗል፡፡ ይህም ተቋማቱ ዓላማቸው “ተሰማርተንበታል” ከሚሉት ተግባር ጋር የማይገናኝ መሆኑን በገሃድ ያረጋገጠ ሌላው ክንዋኔ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ለወትሮው በአንድ ሀገር የተከሰተ ሁነትን በስሚ ስሚም ይሁን ውስጥ ገብቶ በመፈትፈት፣ በማራገብና በማቀጣጠል የሚታወቀው የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ፣ በስርዓቱ ላይ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ በቅድሚያ ባለማመን ላለመዘገብ ዳተኛ ሆኖ ነበር፡፡ ይሁንና ተቃውሞው እያየለ ሲሄድና ሌሎች ሚዲያዎች ዕውነታውን ሲገልፁት፤ እንደምንም እየተውገረገረ ትንሽ ሽፋን ለመስጠት ተገድዷል፡፡

በሌሎች ሀገር የተከናወኑ ድርጊቶችን እየነቀሰና በሚመቸው እና የራሱን አጀንዳ በሚያሳካለት መልኩ እየተነተነ በማቅረብ የሚታወቀው ይህ ሚዲያ፤ በራሱ ውስጥ የተከናወነ ህዝባዊ ትግልን እጅግ አነስተኛ በሆነና ባልተሟላ መልኩ ለማቅረብ መሞከሩ፣ የተቋቋመበት

ዓላማ የኒዩ-ሊበራሊዝምን ልዕልና መጠበቅ መሆኑን የገለፀልን ተጨባጭ ድርጊት ነው፡፡ ይህም ሚዲያው አንደ ቀኖና እከተለዋለሁ እያለ ይሰብከው የነበረውን “እውነትን የመንገር መርህ” (the principle of truth telling) የማይከተል ከመሆኑም በላይ፤የጋዜጠኝነት ስራውም የአብዘኛውን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ለማስጠበቅ ያልቆመ መሆኑን ያሳያል፡፡

በዓረቡና በሌሎች ክፍለ - ዓለማት ውስጥ ያሉ መንግስታት አለመረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ለመቆጣጠር የሚወስዱትን እምጃዎች በሰብዓዊ መብት ስም ሲያወግዙ የኖሩት እነ ሂዮማን ራይትስ ዎችም፤ አሜሪካና እንግሊዝ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ከተሞቻቸው ውስጥ በተቀሰቀሱ ሰላማዊ ሰልፎች ሳቢያ መረጋጋትን ለመፍጠር የወሰዱትን ህግና ስርዓትን የማስከበር ጥረት አይተው እንዳለዩ በመሆን አፋቸውን ሸብበዋል። በዚህ አስገራሚና አሳፋሪ ተግባራቸውም ሂዮማን ራይትስ ዎችና መሰሎቹ በተግባር የሰው ልጆች መብት ተቆርቆሪ ሳይሆኑ፣ የኒዮ -ሊበራሊዝም “እምባ አባሽ” መሆናቸውን በግልጽ ነግረውናል፡፡

እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች ካላቸው የርዕዮተ - ዓለም ልዩነት በመነሳት ትናንት “የኢትዮጵያ መንግስት ‘ኢሳት’ን አገደ፣ የኢንተርኔት ሽበባ (jamming) አደረገ … ወዘተ” በማለት መንግስት የህዝቦችን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ ያደረገውን ጥረት ሲያብጠለጥሉ የነበሩ ተቋማት ናቸው፡፡ ይሁንና ዛሬ የእንግሊዝ መንግስት “ፕሬስ ቲቪ” የተሰኘውን የቴሌቪዥ ጣቢያ በሀገሩ እንዳይሰራጭ ሲያግድ አፋቸውን በመለጎም ያልተገባ ወገንተኝነታቸውን በይፋ ማሳየታቸው ማንነታቸውን በገሃድ አስረድተውናል፡፡

እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገው የየትኛውም ሀገር መንግስት እንደሚያደርገው ለህዝቦች ሰላምና ልማታዊ እንቅስቃሴ ደንቃራ የሆኑ ጣቢያን ማገድ ነው፡፡ ልክ አሜሪካና እንግሊዝ አል-ቃዒዳ የተሰኘው የሽብር ቡድን በሀገራቸው የትርምስ አጀንዳውን የሚያራምድበት የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲከፍት እንደማይፈቅዱ ሁሉ፤ የሀገራችን መንግስትም “ኢሳት” የተሰኘውን የሽብርተኞችን ተግባር የሚያራምድ ጣቢያ አግዷል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ “የእንግሊዝ መንግስት በአሰራሩ ከፍተኛ ሙያዊ ይዘት የተላበሰውን “ፕሬስ ቲቪን” ሲያግድ ጸጥ ያሉት እነ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ለምን የኢትዮጵያ መንግስት የአሸባሪዎች ጣቢያን ሲያግድ ይንጫጫሉ?” የሚል ጥያቄን ስናነሳ፤ አንድ በግልጽ ከሚታይ እውነታ ጋር መጋፈጣችን የግድ ነው፡፡ ይኸውም እነ ሂዮማን ራይትስ ዎች ጉዳያቸው

የሰብዓዊ መብትን ማስከበር ሳይሆን፣ በገዛ ህዝባቸው የተጠላን ርዕዮተ-ዓለም ሌሎችን በግድ በመጋት የስርዓት ለውጥን ለማምጣት መውተርተር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከሂዩማን ራይትስ ዎች ጋር በተቀናጀ ቅብብሎሽ የሚሰራውና “ለጋዜጠኞች መብት ቆሜያለሁ” በሚል የሽፋን ስም የሚንቀሳቀሰው “ሲ.ፒ.ጄ”ም ሌላኛው ተጠቃሽ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ተቋም ‘ዊኪሊክስ የተባለው የመረጃ መረብ ስለማንነቴ ያቀረበው ዘገባ አስደንግጦኝ ጠፉሁ’ በሚል “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” እንዲሉት ሰበብ ፤ማንም ሳይናገረው ከሀገሩ ፈርጥጦ ለጠፋው አርጋው አሸኔ የተባለ ጋዜጠኛ ሳይቀር መንግስትን በማብጠልጠል መግለጫ ማውጣቱን አስታውሳለሁ። ሆኖም “ፕሬስ ቲቪ” የተሰኘው ጣቢያ በእንግሊዝ መንግስት ሲታገድ በስም “የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነኝ” እያለ በተግባር ግን እንደ “የትግል አጋሩ” ሂዩማን ራይትስ ዎች አንዲት ቃል ትንፍሽ ለማለት አልፈለገም፡፡

እርግጥ ሲ.ፒ.ጄ አጀንዳው ለጋዜጠኝነት መብት መቆርቆር ቢሆን ኖሮ፤ በሙያዊ አሰራር ደረጃው “አንቱታን” ያተረፈው “ፕሬስ ቲቪ” በእንግሊዝ እንዳይሰራጭ ሲታገድ ማውገዝ በተገባው ነበር። እውነተኛ ዓላማው የመብት ጉዳይ ከሆነም፤ በራሱ ፍርሃት ለተሸበበውና የኢትዮጵያ መንግስት አንዳችም ነገር ላልተናገረው አንድ ጋዜጠኛ መግለጫ ከማውጣት ይልቅ፣ አፍንጫው ስር ስለታገደው “ፕሬስ ቲቪ” ቢያንስ ለይስሙላ እንኳን አንድ ነገር መናገር ነበረበት።

ይሁንና የሲ.ፒ.ጂ ዓላማ ከጋዜጠኞች መብት መከበርና አለመከበር ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት ስለሌለው እነዚህን “ስያሜያዊ” ተግባራት መከወን አይችልም። እውነተኛ ዓላማውንም በርካታ ምስጢሮችን በመጎልጎል የሚታወቀው ዊክሊክስ በቅርቡ ይፋ አድርጎታል፡፡ ነገሩም እንዲህ ነው፡፡… ሲ.ፒ.ጂ ከርዕዮተ -ዓለም ልዩነቱ ተነስቶ እንደለመደው የኢትዮጵያ መንግስትን የማይመለከተውን የአርጋው አሽኔን የመጥፋት ጉዳይን በማንሳትና በማብጠልጠል “ዊክሊክስ የሚያወጣቸው ምስጢሮች በመረጃ ምንጭነት የሚያገለግሉ ጋዜጠኞችን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያዊው አርጋው አሽኔ የተባለ ጋዜጠኛ ከሀገሩ እንዲሰደድ አድርጓል፡፡ ይህም የአደጋው አንዱ አመላካች ነው፡፡ …” የሚል መግለጫ ያወጣል፡፡

ዳሩ ግን እንኳንስ የእነ ሲ.ፒ.ጄን ማንነት ቀርቶ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትንም ምስጢር ፈልፍሎ በማውጣት የሚታወቀው ዊክሊክስም “…ሲ.ፒ.ጂ ስራው ለጋዜጠኞች መብት መቆርቆር አለመሆኑን እናውቃለን፡፡ …” ሲል ምላሽ ሰጥቶታል፡፡ ይህም ሲ.ፒ.ጂ ስያሜውና ድርጊቱ የማይተዋወቁ መሆናቸውን መረጃ መረቡ ለዓለም ህዝብ ያረጋገጠበት ወሳኝ ምስጢር ነው ማለት ይቻላል፡፡

እነዚህ በግልፅ የሚታዩ “የድርጅቶቹ” መገለጫዎች የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር፤ ኒዮ - ሊበራሊዝም በአምሳያው የፈጠራቸው ተቋማት “በአንድ ራስ ሁለት ምላስ” (double standard) እንዲሉት ዓይነት መሆናቸውን ነው፡፡

ይኸውም በአንድ በኩል የጋዜጠኝነት ሙያን እንዲሁም ሰብዓዊ መብትን ሽፋን አድርገው ከእነርሱ ርዕዮተ -ዓለም ውጭ የሚመራ ሀገርን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በቅብብሎሽ በማብጠልጠልና የአመለካከት የበላይነትን ለመቀዳጀት የሚሰሩ ሲሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸው ሀገራትም ይሁኑ ሌሎች የርዕዮተ-ዓለሙ ተከታዮች የሚፈጽሟቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ይሁን የጋዜጠኝነት ሙያዊ ህፀፆችንና ሽበባዎችን ሆን ብለው በዝምታ የሚያልፉና በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት የሚቆጠቡ መሆናቸውን ከተግባራቸው ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ልክ እንደ ኒዩ-ሊበራሎቹ ተቋማት ሁሉ፤ በተለያዩ ጊዜያት “ከጳጰሱ ቄሱ” እንዲሉት ዓይነት ሆነው የስርዓቱን ትክክለኛነት ሲደሰኩሩና ልማታዊ አመለካከትን ለማቀጨጭ ሲሯሯጡ የነበሩት ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የሀገራችን ጽንፈኛ ተቃዋሚ ምሁራኖች ስለ ርዕዩቱ ክስረት አንዳች ነገር ሊተነፍሱ አላሻቸውም፡፡

የዓረቡን ዓለም አመፅ በተለያዩ ድረ -ገጾችና በሀገር ውስጥም ተመሳሳይ እሳቤ ባላቸው አንዳንድ ጋዜጦች ላይ ሲያራግቡ የነበሩት እነዚህ ወገኖች፤ የአሜሪካ ሚዲያዎች እንኳን በጥቂቱም ቢሆን ስለ ኒዮ-ሊበራሊዝም ክስረት ለማውራት በሚውተረተሩበት በአሁኑ ወቅት፣ስለ ርዕዮተ -ዓለሙ ቅሌት ምንም ለማለት አለመፍቀዳቸው አግራሞትን የሚያጭር ነው፡፡

እናም እነዚህ አቀንቃኞች እዚያው ባህር ማዶ ቁጭ ብለው ነገር ግን የት እንዳሉ በማይታወቅበት ሁኔታ በሃፍረትና በቅሌት አፋቸውን ለጉመው ተቀምጠዋል፡፡ በእኔ እምነት የእነዚህ ፅንፈኛ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች ዝምታ ምክንያቱ ‘አሜሪካ አንድ ነገር ከሆነች መግቢያ የለንም’ ብለው ስለሚያስቡ ነው ። ለምን ቢባል፤ በተለያዩ ጊዜያት አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርገውን ልማታዊ አስተሳሰብ በመኮነን የገዛ ህዝባቸውን ሲጎዱት የኖሩ በመሆናቸው ነው፡፡

ይሁን እንጂ፤ የኒዩ-ሊበራል ተቋማም ሆኑ የሀገራችን ተቃዋሚ ምሁሮች ያሻቸውን የማጥላላት ድርጊት ቢፈጽሙም “ከኒዮ - ሊበራሊዝም ውጪ ሌላ አማራጭም አለ” ያሉ ሀገራትን ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር የሚጣጣም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነቡና ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት ግስጋሴያቸው እንዲስተጓጎሉ ሊያደርጓቸው አልቻሉም፡፡

በዚህ ረገድ በልማታዊ ዴሞከራሲያዊ አሰራራቸው ዕድገታቸውን እያስወነጨፉ ያሉትን እነ “ብሪክ” (BRIC -ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና) በተምሳሌትነት ልንጠቅሳቸው እንችላለን፡፡

የላቲን አሜሪካዊቷን ሀገር ብራዚልን ብቻ ለአብነት ያህል ብንወስድ እንኳን፤ የሀገሪቱ መንግስት ሁሉንም ነገር ለገበያና ለግሉ ባለሃብት ባለመተው እንዲሁም በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ ገብቶ ድሃ አባወራዎች ላይ ያተኮሩ ማህበራዊ ፖሊሲዎችን በመቅረፁ በሀገሪቱ ውስጥ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊ የሐብት ክፍፍልን ማጥበብ መቻሉን በቅርቡ የወጡ መረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ያለ ኒዩ-ሊበራሊዝም ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ እሳቤ ማደግ እንደሚቻል የሚያሳይ ሃቅ ነው።

በአፍሪካም ውስጥ ቢሆን በራሷ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ እየተመራች የአንፀባራቂ ዕድገት ባለቤት የሆነችው ሀገራችንም ሌላኛዋ ማሳያ ናት። ኢትዩጵያ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በዕድገት ባቡር ላይ ከተሳፈረች ሰምንት ተከታታይ ዓመታት አስቆጥራለች፡፡

በዚህም በየዓመቱ በአማካይ የ11 በመቶ ዕድገት ባለቤት ሆናለች። ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እንደመሰከሩት፤ ልማታዊው መንግስት በቀየሰው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በማህበራዊ ዘርፎች መስክ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ለዚህም ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የ11 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገትም ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍልን በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ድርሻ ማበርከቱ የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ ተጨባጭና ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ የተገኘው የሀገራችን መንግስት ከራሱ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በቀየሰው የፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ስርዓት እንጂ፤ ክስረቱ በዓለም ፊት ተጋልጦ የሃፍረት ሻማ በተከናነበው የኒዮ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ አይደለም፡፡

እናም መንግስት በቀጣይነትም ልማትን እንደ ህልውና ጥያቄው በማየት፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ከግሉ ባለሀብት በተነጻጻሪ ነጻ በመሆን እንዲሀም በሂደት የልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነትን በመፍጠር ዕድገቱን እንደሚያፋጥን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ያኔም የእነ “ፕሮፌሰርና ዶክተር “ ተብዬዎቹ የተሳሳተ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝነት ይበልጥ መጋለጡ አይቀሬ ነው፡፡


Videos From Around The World

 


 
 


 Mark Your Calendar

 


 


 


 


 


 


 Custom Search

 


Opinions and Views published on this site are those of the authors only! Aigaforum does not necessarily endorse them. © 2002-2018 Aigaforum.com All rights reserved.