የመድረክ ስብስብ ከሥልጣን ጥማት ውጪ-----

Articles

የመድረክ ስብስብ ከሥልጣን ጥማት ውጪ-----ቃልቤሳ ኦላና-ከፊነፊኔ- ሰሞኑን መድረክ ከቅንጅት ወደ ግንባር መለወጡን ገልጿል፡፡ ግንባርን በግንባር በሚል ኢህአዴግን ለመፎካከር መደራጀቱን አስታውቋል፡፡ ህዝቡም ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ ስላለን ተሰባስበናል እያለ ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ ባረጋገጠው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በፈለጉት የአደረጃጀት ዘይቤ መደራጀት መብት ነው፡፡ ይህ ለክርክር የማይቀርብ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ነው፡፡

ዋናው ጉዳይ መድረክ ግንባር የመሠረተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ከኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ የእድገት ፖሊሲና ራዕይ ይዞ ነው ግንባርን በግንባር የሚል ፉካሬ የሚያስተጋባው የሚለው ነው፡፡ ኢህአዴግን ለማስወገድ ለመተባበር ወይም ለመሰባበር ከመሰለፍ ያለፈ ለህዝብና ለሀገር የተሻለ አማራጭ መያዙን ሲገልፅ አይታይም፡፡ ለምን? የሚሉትና ከሌሎች ህጋዊ፣ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎችስ ምን የተለየ አማራጭ እንዳለው ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ ማድረግ አለበት፡፡

የሰላማዊ፣ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ድርጅት ዋነኛ መወዳደሪያ ጉዳይ የተሻለ አማራጭ ፖሊሲና የተሻለ ራዕይ ለህዝብ አቅርቦ በምርጫ ተቀባይነት ማግኘት ነው፡፡ የመድረክ ስብስብ ግን ኢህአዴግን ከቻለ ለማስወገድ ያለውን ፍላጐት ከመግለፅ ባለፈ የእድገት አጀንዳዎቹን ሲገልፅ አይስተዋልም፡፡ ኢህዴግን ለማስወገድ መሰባሰቡን እንጂ የተሻለ አማራጭ ቀይሶ ሀገርንና ህዝብን ለማሣደግ ዝግጁ መሆኑን አያረጋግጥም፡፡

መድረክ በአባል ድርጅቶቹ መካከል የነበረውን ልዩነት ለማጥበብ ለረዥም ጊዜ ውይይት ካካሄደ በኋላ ወደ ግንባር መለወጡን ቢገልፅም አሁንም መሠረታዊና ቁልፍ ልዩነቶች አልተፈቱም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ይዘትና ቅርፅ ምን መሆን እንዳለበት፣ በቡድንና ግለሰብ መብቶችና ነፃነቶች፣ የመሬት መሸጥና መለወጥ ጉዳዮች - - - ወዘተ መግባባት አልተደረሰባቸውም፡፡

በእነዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረታዊ ጥያቄዎችና የልዩነት ማጠንጠኛ መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ሳይግባቡ ተመሰረተ የተባለው ግንባር የሀገርንና የህዝብን የወደፊት እጣ ፈንታ በሚወስኑ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም አለመያዙን ያሣያል፡፡ ለመድረክ ረጅም ጊዜ የወሰደበት ውይይት ለሀገርና ለህዝብ የተሻለ አማራጭና ራዕይ ለማቅረብ ሣይሆን በስብስቡ በታቀፉት ከጠባብ እስከ ትምክህት ፅንፈኛ አስተሣሰባቸውን፣ እርስ በርሱ የሚቃረን አቋምና ርዕዮታቸውን እንዳለ ይዘው ከኢህአዴግ ጋር ግንባር በግንባር ለመግጠም ባቀዱት ግጥሚያ ለመተባበር ወይም ለመሰባበር ነው፡፡ የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ህዝቡ ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ ስላለን ነው ግንባር የመሠረትነው እያሉ ያሉት አባባል ይህንኑ ያረጋግጣል፤ የትኛው የህዝብ ክፍል እንዳላቸው ባይገለፅም፡፡ እነዚህ በጭፍን ጥላቻ የሀገርንና የህዝብን መሰረታዊ ጥቅም በመዘንጋት ኢህአዴግን ለማስወገድ ብቻ የፈጠሩት ግንባር ከኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና መሰል አሸባሪዎች ጋር ለመሰለፍስ ምን ያግደዋል? ጉዳያቸው ስልጣን ማግኘት ስለሆነ። በመሆኑም ይህ የመድረክ የግንባር አደረጃጀት ፍካሬ መሠረታዊ የዴሞክራሲ፣ የመድብለ ፓርቲ መርህና ህገ-መንግስታዊ የህዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን አመንጭነት የሚጋፋ ቅኝት የተከተለ ነው፡፡ የፍካሬው ቅኝት የዴሞክራሲያዊ መርህ የተከተለ አይደለም፡፡ በዴሞክራሲያዊ መርህ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ተመርጦ ስልጣን የሚይዘው ባቀረበው የተሻለ የመወዳደሪያ አማራጭ ፖሊሲ ነው፡፡ መድረክ ግን ኢህአዴግን አስወግዶ የሽግግር ጊዜ እንደሚመሠረት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአሜሪካ ድምፀ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል፡፡ በህገ መንግስቱ መሰረት ኢህአዴግን ከስልጣን የሚያወርደው ህዝቡ በድምፅ፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው እንጂ በመድረክ ፉከራ ከቶ ሊሆን አይችልም፡፡ የመድረክ ግንባር ለህዝብ ያቀረበው ለተሻለ እድገት የተሻለ አማራጭና ራዕይ ሣይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎችን ለመፍታት ባለፉት 2ዐ ዓመታት የተሰጡትን መፍትሔዎችና ብዙሃነታችንን የሚያስተናግደውን ስርዓት ለመቀልበስ ያቀደው የሽግግር ጊዜ ነው። ይህ አካሄድ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን መቀልበስ ማለት ነው፡፡ የተገኙትን የዴሞክራሲ ድሎች እና ልማቶችን ይዞ በመቀጠል የተሻለ መሥራት አይደለም አካሄዱ፡፡ ሁሉንም አፍርሶ ከዜሮ መጀመር ነው ። መድረክ ግንባር ሆንኩ ኢሀአዴግን አስወገጄ ሽግግር ጊዜ ይመሰርታለው የሚለው ጉዳይ የህዝብን አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጠው የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመግታት ነው፡፡

የመድረክ የግንባር ፍካሬ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መርህን የሚቃረነው ደግሞ እውነተኛ ፣ጠንካራ ፓርቲ ነኝ፤ ኢትዮጵያን መምራት ያለብን እኔና እኔ ብቻ ነኝ በሚለው አካሄዱ ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ በተረጋገጠው የመደራጀት መብት የተመሠረቱትን ህጋዊ፣ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች በሰፊው ያጣጥላል፡፡ ከእነ ኦነግ፣ ግንቦት 7 እና መሠል ሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ደግሞ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚለው አስተሳሰብ መተባበር ይቀናዋል፡፡ ይህ አካሄድ መድረክን ፀረ-መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ያደርገዋል፡፡

መድረክ ሁሌም ኢህአዴግን ከስልጣን በማስወገድ ስልጣን ለመያዝ መሰባሰቡን እንጂ በህገ-መንግስት ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ከሆነው ህዝብ ሥልጣን በህገ መንግስታዊ አግባብ የሚያገኝበትን ሁኔታ አይገልፅም፡፡ መድረክ በህዝብ የስልጣን ባለቤትነት የሚያምን ቢሆን ግንባርን በግንባር ለመግጠም ለመተባበር ወይም ለመሰባበር መዘጋጀት ሣይሆን መቅደም የነበረበት የነጠረና የጠራ የተሻለ አማራጭ ፖሊሲና ራዕይ ይዞ ወደ ህዝብ መቅረብ ነበር፡፡ የመድረክ ግንባር ስለህዝቡ ፍላጎትና ጥቅም ምንም አልሰራም፤ አቋምም ባለመያዙ ምንም አያወራም፤ የህዝቡ ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር ፍላጎቶቹ ምን እንደሆኑም አልተገነዘበም። በስልጣን ጥማት ብቻ የታወሩ ነው። በመሆኑም መድረክ እየተከተለ ያለው አካሄድ በህገ-መንግስቱ የተረጋገጠውን የህዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን አመንጭነትን የሚቃረን ነው፡፡

መድረክ በ2ዐዐ2 ምርጫ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ኢህአዴግ ስልጣን ያጋራን የሚለው አባባል ለዚህ አቋሙ እንደ ማሳያ የሚወሰድ ነው። ኢህአዴግ የሚያጋራው ስልጣን የለውም፡፡ ስልጣን የህዝብ ነው፡፡ ኢህአዴግን ከስልጣን እናስወግዳለን፤ ኢህአዴግ ስልጣን ያጋራን የሚሉት አባባሎች መድረክ በህዝቡ የስልጣን ባለቤትነት የማያምን ስለመሆኑ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ መድረክ የተሰባሰበውም በህዝባዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በመመስረት አይደለም፡፡ በየትኛውም መንገድ ስልጣን ለማግኘት ብቻ ነው፡፡

በመድረክ ስር ተሰባስበው ያሉት ስብስቦች የአስተሳሰብ ማጠንጠኛና ቅኝት እሣትና ጭድ መሆናቸው ከዚህ በፊት ተረጋግጧል፡፡ እነ ኦፌዴንን ከመሰሉ በጠባብ ብሄርተኝነት ከሚታሙ ድርጅቶች ጀምሮ ስለብሄሮችና ብሄረሰቦቸ መብትና ነፃነቶቸ ማንሣት ሀገር መበታተን አድርጐ የሚያስበው አንድነት ያሉበት ጫፍ የረገጡና ፈፅመው የማይታረቁ ድርጅቶች ያሉበት ነው። እነዚህ አንድ ላይ መቆም የማይችሉ እሣትና ጭድ በመሆናቸው ለሀገርና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ቀርቶ ለራሣቸው መልካም ነገር እንደሌላቸው የተረጋገጠ ነው።

መድረክ በምርጫ ፖለቲካ የሚያሸንፍበት ምንም ህዝባዊ ድጋፍ እንደሌላው በመረጋገጡ በ2ዐዐ2 ምርጫ ፖለቲካ ሥልጣን ለመጋራት የተለያዩ የአመፅ ሞዴሎችን ለመተግበር ተንቀሣቅሶ ነበር፡፡ የአሁኑ የመድረክ የግንባር ፍካሬም ምንም የጋራ አቋም ፣የጠራ የአመለካከት፣ የአደረጃጀት፣ የአሰራር አንድነትና ዲሲፒሊን የሌለው ነው። በመሆኑም በማምታታት፣ የማደናገሪያ ሀሳብ በማምረትና ግርግር በመፍጠር ስልጣን ለማግኘት የሚያደርገው በቆየው አካሄዱ መቀጠሉን የሚያሣይ ስለሆነ ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አይጣፍጥም ዓይነት ነው፡፡ አሁን በመድረክ ስር የተሰባሰቡት ድርጅቶች ያልፈጠሩት የህብረት፣ የቅንጅት እና የመድረክ አይነት የለም፡፡ የፖለቲካ ድርጅት ለህዝብና ሀገር የቀረፀውን የተሻለ አማራጭ ለህዝብ አቅርቦ በአማራጩ በመመረጥ መንግስታዊ ስልጣን መያዝ እንጂ ምንም አማራጭ ሳይዙ እሣትና ጭድ ሆነው ተደራጀን ብለው ልዩነታችንን ለህዝብ እናቀርባለን የሚለው የመድረክ ሙግት የፖለቲካ ብስለትና ህዝባዊ ራዕይ የሌላለው መሆኑን ከማሣየቱም በተጨማሪ ግንባሩን የደካሞች ስብሰብ ያደርገዋል።

በመሆኑም የመድረክ ስብስብ አሁን እየተከተለ ያለው አካሄድ በሚገባ መጤን አለበት። በ2ዐዐ2 በግርግርና በብጥብጥ እንደ ኬንያና ዚንባቡዌ ስልጣን መጋራት በሚል የተራመደ ሲሆን አሁን ግንባር ሆንኩ የሚለው ደግሞ በህጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንቀሣቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች በማንቋሸሽ የውጥረት ፖለቲካን እያራመዱ ለሽብርተኛ ድርጅቶች ጠበቃና አጋር ሆኖ የሀገሪቷን እድገት በዜሮ እያበዙ የሚካሄድ ፖለቲካ የእድገትና የግንባታ ከቶ ሊሆን አይችልም።Videos From Around The World

 


 
 Mark Your Calendar

Follow US on Facebook
Custom Search
Opinions and Views published on this site are those of the authors only! Aigaforum does not necessarily endorse them. © 2002-2020 Aigaforum.com All rights reserved.