ጥቂት ነገር ስለሀገሬ ጋዜጦች

Articles

ጥቂት ነገር ስለሀገሬ ጋዜጦችዮናስ (ከባልደራስ) 10/26/11
የዛሬው ጽሁፌ የትኩረት አቅጣጫ የጋዜጦቻችን ሰሞንኛ አጀንዳ፤ በተለይ የአንዳንድ ጋዜጦቻችን ያፈነገጠ አቋም ነገር እያሳሰበኝና እያስገረመኝ እየመጣ መሆኑ ነው፡፡ የተወሰኑ የሀገራችን መገናኛ ብዙሀን ከመንግስት ጋር "ሽብርተኝነትን" ባማከለ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ሙግት ስለመግጠማቸው ወቅታዊ አምዶቻቸው ይመሰክራሉ። "የጋዜጠኞቻቸው መታሰር"ን በዋናነት በማንሳት፣ "መረጃ የማግኘት መብት መነፈግ"፣ን "ሃሳብ የመግለጽ መብት መቀማት"ን፣ ወዘተ ጉዳዮች በጉልህ ይጠቀሳሉ።

የተለያዩ ሀገራትን ህገ መንግስት አንቀፆች በማጣቀስ፣ ያደጉ ሃገራትን፣ የግል ልምድ በማስደገፍ "የግዙፍ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትን" ምርምሮች በማካተት የችግሮቹ ፈጣሪ ነው ላሉት የኢትዮጵያ መንግስት አቤቱታቸውን እያቀረቡ ነው። እንዳውም "ነፃ ፕሬሱን ለመግደል በመንግስት የተቃጣ የመጨረሻ እርምጃ" እንደሆነ በመግለጽ። ባለፉት ሶስትና አራት ወራት ይሄንን "የግል" ጋዜጦቻችንን አቤቱታ ለብቻው ሳይሆን ከመንግስት የጸረ ሽብርተኝነት እርምጃና ምላሾች ጋር እያዋሃድኩ ለመመርመር ሞክሬያለሁ። በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ "በሽብርተኝነት ስለጠረጠርኳቸው አስሬያቸዋለሁ"፣ በሚለው መንግስትና "መንግስትን ስለተቸን ብቻ ሽብርተኛ መባል የለብንም" በሚሉት ጋዜጦቻችን እና ጋዜጠኞች መሃል ቆሜ በርካታ ጥያቄዎችን አነሳለሁ። "የግል" የተባሉትን ጋዜጦች ያለፉ ወራት ዘገባዎች እንደ ማነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች አይነት እንደማሳያ የምጠቀም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዛ በፊት ለዛሬው አጀንዳዬና ከማነሳው ርዕሰ ጉዳይ ጋር የቀጥታ ግንኙነትና አስረጂነት አላቸው የምላቸውን ጥቅምት 3 እና 4/2004 ለህትመት የበቁትን "ፍትህ" እና የ"አውራምባ ታይምስ" ጋዜጦች ርዕሰ አንቀጽና በተለይም በአውራምባ ታይምስ "የፀረ - ሽብርተኝነት ህግ ፤ በጋዜጠኞች ላይ የተቃጣ ሰይፍ" በሚል ርዕስ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው "ቢሮ ኦፍ ኢንቨስትጌቲቭ ጆርናሊዝም" ዘጋቢ የሆኑት ሴይላን ባር ያቀረቡትን መጣጥፍ የዚህ ጽሁፍ አንባብያን ሁሉ ከኔ መጣጥፍ ጋር በማዛመድ በጥልቀት ታነቧቸው ወይም ትፈትሿቸው ዘንድ በቅድሚያ እጋብዛለሁ። ወደ አጀንዳዬ ስመለስ፦ "የሚዲያ፤ የመንግስትና የሽብርተኝነት የዝምድና ሃረግ የት ድረስ ይረዝማል?፣ ነፃ ፕሬስ የቱ ነው?፣ አፋኙ ፣ አሳሪው መንግስትስ የቱ ነው?፣ ታሳሪዎቹ ጋዜጠኞችስ እነማን ናቸው? ዓለም አቀፋዊ ተሟጋቾቹስ?" ወዘተ ስል ያነሳኋቸው ጥያቄዎች ናቸው ለጽሁፌ ማእከላዊ ነጥብ የሆኑኝ። ለመጣጥፌ ማዳበሪያነት ከተጠቀምኳቸው ሙያዊ ትንታኔዎች ውስጥ የ “Raphael F. Peel ጥናታዊ ዕሁፍ ሚዲያችን፣ በተለይ "የግል" የሚባሉቱ ጋዜጦቻችን የቱጋ ነው ያሉት? ስል ላነሳሁት ጥያቄ በቂ ምላሽ ሰጥቶኛል።

"ሽብርተኝነት፤ ሚዲያና መንግስት፦አተያዮች የተለመዱ አካሄዶችና ለፖሊሲ አውጪዎች የቀረቡ አማራጮች "Terrorism the media and the government perspectives, trends and option for policy makers) ይላል የ Raphael ጥናታዊ ጽሁፍ። ሰውዬው በአሜሪካ ምክር ቤት አለም አቀፋዊ ጉዳዮች፣ የውጭ ጉዳዮች እና ብሔራዊ መከላከያ ክፍል ስፔሻሊስት ናቸው።

የኚህ ምሁር ጥናታዊ ወረቀት የሃገሪቱ ምክር ቤት የምርምር አገልግሎት ማዕከል ወይም Congressional Research Service--CRS ስለሽብርተኞች፣ ስለሚዲያ አጠቃቀምና ስለመንግስታት የጋራ አቋምና ትስስር (The nature of The relationship of terrorist initiatives ) አስመልክቶ ባካሄዳቸው በርካታ ምርምሮች የተሰጠ ምላሽ እንደሆነ በፅሁፉ የመግቢያ ክፍል ላይ ተገልጿል። ባጠቃላይ የRaphael ጽሁፍ ከላይ በቀረበው ርዕስ ስር የሚዲያውን ተግዳሮቶች፣ የመንግስትን ፈተናዎችና አካሄዶች እንዲሁም የሽብርተኝነትን ባህርያትና ፍላጎቶች በስፋት ይቃኛል። ጥናቱ ሁሉም አካላት በተለይ ሚዲያውና መንግስት ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚናን እና ለአሜሪካ ኮንግረስ የሚቀርብ የመፍትሔ ሃሳብን በመጠቆም ይጠቃለላል። ቀደም ብዬ በመግቢያዬ ላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት የጽሁፌ አላማ "ነፃ ነኝ" በሚሉ የግል ፕሬሶችና በሀገሪቱ መንግስት መካከል የነበረውን ሰሞንኛ ሙግት መቃኘት በመሆኑና በተለይም ለነዚሁ "ነፃ" የተባሉትን ፕሬሶች አቤቱታ ከፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ጋር በማያያዝና ዓለም አቀፍ "የምርምር" ውጤቶችን በማጣቀስ የመንግስት ምላሽ ተቀባይነት የሌለውና ሚዛን የሚደፋ እንዳልሆነ በነዚሁ ፕሬሶች በተደጋጋሚ ይገለፃል፣ ብቻ ሳይሆን የህጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ህገመንግስትና ህገመንግስቱን መሰረት አድርጎ ከወጣው የፀረ ሽብርተኝነት ህግ በላይ ለነዚሁ ፕሬሶች በማመሳከሪያነት የሚቀርቡት የፈረንጆች ትንታኔ እና ማብራሪያ በመሆኑ እኔም ለሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ከአሜሪካዊው ፀሐፊ የወሰድኳቸውን ነጥቦች በማጉላት "የግል ጋዜጦቻችንን" እና የመንግስትን ሰሞንኛ አጀንዳ በተወሰነ ደረጃ ለመመርመር እሞክራለሁ። ምናልባት አቀራረቤ "ፈረንጅ አምላኪ" በሆኑት ዘንድ ተቀባይነት የማያገኝ ሊሆን ይችላል። "ነፃዎቹ" ጋዜጦቻችንና ሽብራቸው

ይህ ንዑስ ክፍል የሚመለከታቸው "ነፃ ሆነን በመተቸታችንና በመፃፋችን ሽብርተኛ ተብለናል" የሚሉትን የሃገሬ ጋዜጦችንና "በመፃፋቸው ሽብርተኛ ተብለዋል" የሚሉትን የውጭና የብእር ጠበቆቻቸውን እንዲሁም የተልዕኮ አምደኞቻቸውን ብቻ ነው። ወዴት? የሚል ጥያቄ ከተነሳ እንደ አንዳንድ ወገኛ ተብዬ "ፀሀፊ" ጋዜጠኞች "በቅንፍ፣ ይመዝገብልኝ፣ የታች ሰፈር፣ የላይ ሰፈር ልጆች….. " ይሉ አይነት አሽሙራዊ ደባደቦ ቅጽሎችን መጠቀም ሳልሻ አንዳንድ "የግል" ጋዜጦችና እራሱን "ዓለም ዓቀፍ የጋዜጠኞች ተሟጋች ነኝ" የሚለውን ተቁዋም (CPJ) እንዲሁም የነዚሁ ጋዜጦች አምደኛ የሆኑትን እንግሊዛዊ ሴላይን ባርን እና መሰል "ተቆርቋሪ"ና ቅቤ አንጓች አምደኞችን ነው።

ስለዚህም እናንተ ፦ሌላው በሰራው ከዘራ እየተደገፍን፣ አንዱ ለአላማው የፃፈውን ሌላው (ያለ?)አላማው እያነበበ፣ በሌላው ማትረፍ፣ ሌላው እየተጎዳ በተጎዳው መነገድ ወዘተ በተለመደባተ የነፃ ፕሬስ ዓለም ውስጥ እየኖርን "ነፃ ነኝ"፣ "ፖለቲካ አልወድም"፣ "መሃል ሰፋሪ ነኝ" የምትባለው ነገር ለኔ አልተመቸችኝም። ጥግ የለሹ የግል ፍላጎት እያለና እየታየ "መሃል ሰፋሪ" የሚባል አቋም አይኖርም። የተቃዋሚ አልያም የገዢ ፓርቲ ደጋፊ አለመሆን "ከፖለቲካ ነፃ" አያሰኝም። መረረም ጣፈጠ የጥላቻ ፖለቲካ "የፖርቲ አባል" ከመሰኘትም በላይ ብቻ ሳይሆን ህልውናችን/ኑሮአችን ነው። ቀመር ዘርግቶ፣ አካሄድን/አስልቶ በአደባባይ የመታየት ያለመታየት ጉዳይ እንጂ ሁላችንም ፖለቲከኞች ነን "ነፃ ነን" የምንባለውን ጋዜጠኞች ጨምሮ።

በተለይ፣ በተለምዶ ( በእርግጥ ህጉም ይላቸዋል) የግል የምንላቸው የሃገራችን ጋዜጦችና ጋዜጠኞች ከፖለቲከኛነት "ነጻ ነን" ከማለታቸው ጋር ተያይዞ እርስ በርሱ ሲላተም ላለፉት 20 ዓመታት የታየና የተለመደ የነሱ ስር የሰደደ ማንነት ነው። በነገራችን ላይ የግልም ሆኑ የፖለቲካ ማህበር ጋዜጦች ፖለቲካዊ አቋማቸውን በግልጽ ማራመድ ስለመቻላቸው ከተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ አይተናል፣ ተምረናልም። በ2004 የታላቋ ብሪታንያ ምርጫ ሲካሄድ የሃገሪቱ አንጋፋ ጋዜጦች የሚደግፏቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች በመደገፍ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ አካሂደዋል። የኛዎቹን የግል ጋዜጦች አቋም በተመለከተ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት "ግራ መጋባት" ብሎ ከማለፍ ውጪ ለጊዜው አማራጭ አይኖረኝም። "የህዝብ ድምፅ ነን"፣ "ግድፈቶችን ከማጋለጥ ወደኋላ አንልም"፣ "በሚዛናዊ መረጃ አቀራረብ ላይ አንደራደርም" ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን አስቀድመው በመቃወም ከጀርባቸው (በፅሁፋቸው ማእኬላዊ ጭብጥ) በተቃውሞ ፖለቲካ የተሞሉ ገፆቻቸውን ይዘው ብቅ ይላሉ፡፡

ይህን በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፡፡እነዚህ ለዛሬው አጀንዳ ማሳያ ናቸው ስል ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው ጋዜጦች (ፍትህና አውራምባ ታይምስ በዋናነት) ገበያ ውስጥ ሞልተዋል፤ አከፋፋይና አዟሪው ከፊት አስቀድሞ ይይዛቸዋል። ለህትመት የሚበቁት ደግሞ "በፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ የምታተኩር" የሚል የህግ ተቀፅላ ይዘው ነው። በረጃጅምና በወፋፍራም ፊደላት ከተሰሩት የፊት ገጽ ርዕሶቻቸው ስር የመንግስት ባለስልጣናት፣ የመንግስት መስሪያ ቤት አልያ "አንገብጋቢ" የፖለቲካ አጀንዳን የሚያሳይ ፎቶ በጉልህ ያኖራሉ፦ ከዛም፦

 ሽብርተኛው ኢህአዴግ! የህዳሴው ግድብ ቀጣይ ፈተናዎች! ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በረሀብ ጥላ ስር!' ፓርላማው ሞተ ፋይዳ ቢሱ የታክሲ የዞን ስምሪት 'የመሬት ዝርፊያው ተጧጡፏል'አሸማቃቂው የሽብርተኝነት አዋጅ! 'ቱንዚያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያ ቀጥሎስ?' አፋኙ የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ወዘተ

የሚሉት የየጋዜጦቹ የፊት ገጽ ርዕሶች በምሳሌነት መቅረብ የሚችሉ ማስረጃዎች ናቸው። ያው የጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተቀጣጣይ ነገር በእጁ የያዘ የአረብ ወጣት፣ አሽሙርና ተረብ ብቻ የታጠቀ ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወዘተ ፎቶዎችና ካርቱን ስእሎች በእርግጠኝነት ከየአምዶቻቸው ላይ አይጠፉም። በየትኩሳቶቻቸው ስር በሚለው አምድ ስር ስለገዢው ፓርቲ መበስበስ እናነባለን፣ በየወጎቻቸው ትንታኔ ስለመንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ድክመት ያወጉናል፣ ኢኮኖሚ በሚለው አምድ ስር መንግስት አስመዘገብኩት የሚለው ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ፕሮፓጋንዳ መሆኑን አንድ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የኢኮኖሚክስ ምሁር የሆኑ ግለሰብ ጥናት አመለከተ ይሉናል። ጭምጭምታቸው በበኩሉ የህዳሴው ግድብ ለገዢው ፓርቲ ስልጣን ማቆያ የተዘጋጀ ፊልም እንደሆነ ያንሾኮሹክልናል። በነሱ ቤት እየሆነና አየተደረገ ያለውን የሚያይም ሆነ የሚሰማ የለም።

የባህር ማዶውን የሚመልን "ባህር ማዶ"ም እንደሰደድ እየተቀጣጠለ ያለው የአረብ ሃገራት የፖለቲካ እሳት የኢትዮጵያን ቤተመንግስት ለማውደም ቀናት እንደቀሩት ያብራራልናል---%ረ ረስቻት "ርዕሰ አንቀጽ" የሚሏት ደግሞ አለችላችሁ----አጀማመሯም፤ አስተዳደጓም አደማደሟም አንድ አይነት ነው። ጋዜጦቻችን ተደዋውለው አሊያም ተደውሎላቸው እንደሚጽፏት ታስታውቃለች። ዓረፍተ ነገሮቻቸውም ሆኑ ቃላቶቻቸው ከአንድ ምንጭ የፈለቁ ይመስላሉ። "ከደመራው አናት የሚውለበለበው የገዢው ፓርቲ ባንዲራ! ልብ በሉልኝ ይህ እንግዲህ ርዕስ መሆኑ ነው። ከዚያ ትቀጥላሉ "ሃይማኖታዊ በአላትን ተገን በማድረግ ገዢው ፓርቲ ፖለቲካውን እያቀጣጠለ እንደሆነ፣ ይህ አካሄድ በሃገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ያልታየ ተሞክሮ እንደሆነ፣ በሃይማኖቶች መሃል የማይፈቱ ልዩነቶችን እንደሚፈጥር ስለዚህም በጊዜ ሊቀር እንደሚገባ በማስጠንቀቅ አቋም በመያዝ የመጨረሻዋ አራት ነጥብ ላይ ይደርሳሉ። ምስኪኖቹ ርዕሰ አናቅጽ። ያልኳችሁን ታምኑ ዘንድ ያለፉትንም ሆነ ያሁኖቹን አልያም መጪዎቹን ርዕሰ አንቀጾች ተመልከቱ "ኮፒ ፔስት" የሚለውን ተገለባቢጦሽ በተጨባጭ ማረጋገጥ ትችላላችሁ ።

እስቲ አምዶች ተብለው በየገጹ ከሰፈሩት የየጋዜጦቹ ዘገባዎች ውስጥ ገንቢ ሀሳብ፣ ቅን ሂስ፣ አሻሻይ ጥቆማ፣ የተለየ አተያይ አፋልጉኝ፤ የለም። ዜማቸው በሙሉ ስለአንድ ነገር ብቻ ነው። ብዙዎቹ በህገ ልቦና ሳይሆን በስሜት ይጻፋሉ ወይም የተፃፉ ናቸው፣ የባእድና የጠላት እጅ ደግፏቸው ይታያል፣ መገንባት ከማፍረስ ብቻ እንደሚጀመር ያምናሉ፣ የወላይታ መንገድ ቢጎረብጥ የሃዋሳ መንገድ ምቾቱን፤ የሃዋሳው ቢጎረብጥ የደሴው መለስለሱን፤ መስማት አይፈልጉም፡፡ ከጥሩው መጀመር ለነዚህ ጋዜጦች ሞት ብቻ ሳይሆነ የሞት ሞት ነው። በየትኛውም ሃገር ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ለሀገሩ ልማት የማይጨነቅ ለሀገሩ ብልፅግና የማይደክም የግል ጋዜጣ/ነፃ ፕሬስ የለምና። ይቅርታ በጋዜጦቻችን ላይ አመረርኩ መሰለኝ። ወድጄ አይደለም። ሁላችንም ፊታችንን ወደልማት ብናዞርና ከድህነት ብንወጣ ብዬ ነው ።

ወደ አሜሪካዊው ተመራማሪ የጥናት ወረቀት ልመለስና የማምረሬን ምንጭ ላመላክት። ሽብርተኞች ከሚዲያው ምን ይፈልጋሉ? (What terrorist want from Media?) በማለት ገና ከመግቢያው የቀጠለው የጥናቱ ጥያቄ ወደ ስድስት የሚጠጉ የሽብርተኞችን ፍላጎቶች በዋናነት ዘርዝሯል --- ከጋዜጦቹ ጋር የተያያዙትን ብቻ አጀንዳዬ ስለሆነ እንያቸው እንጂ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው በኩል ያሉትንም የሽበረተኞች ፍላጎቶች ጥናቱ በግልፅ አስቀምጧቸዋል። በቅደሚያ ግን ጥናቱ በሽብርተኝነቱም ሆነ በፀረ ሽብረተኝነቱ ዘመቻ ውስጥ ሚዲያ ያለውን ሚና ከምንም በላይ አግዝፎ እንደሚያይ ልጥቀስ፡፡ ጥናቱ የሚዲያና የሽብርተኝነትን ቁርኝት ሊያሳየን የሚሞክረው ከማርጋሬት ታቸር ንግግሮች ውስጥ የሚከተለውን በማስታወስ ነው፡፡ (Publicity is the Oxygen of terrorism ) ብለዋል ሴትዮዋ ይላል ጽሁፉ። ሲያብራራውም Margaret Thatcher’s metaphor that publicity is the oxygen of terrorism underlines the point that public perception is a major terrorist target and the media are central in shaping and moving it for terrorism, the role of the media is critical ይለዋል። ሽብርተኞቹ ከሚዲያ /ከጋዜጦች አንፃር/ ወደሚፈልጓቸው ነገሮች እንመለስ። እንደራፋኤል ጥናት ፣

1. ሽብርተኞች ድርጊታቸው በሙሉ እንዲዘገብላቸው ይፈልጋሉ። በተለይ የማይከፍሉበትንና የማይገዙትን የሚዲያ ሽፋን ሁልጊዜ ይፈልጉታል። ምክንያቱም የትኛውም ሽብረተኝነትን አስመልከቶ የሚሰጥ የሚዲያ ሽፋን ለዓለም መልእክት ያስተላልፋል። በሽብረተኝነት አስተሳሰብ እርማት (edit) ያልተደረገ የመሪዎቻቸውን መልእክት በሚዲያ ማስተላለፍ እንደ ሽልማት ይቆጠራል። ለምሳሌ በግንቦት 1997 CNN ከሳውዲ አረቢያው የፖለቲካ ተቃዋሚ፣ ሽብርተኞች መልማይና የገንዘብ ድጋፍ ሰጪው ኦሳማ ቢንላድን ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ለዚህ ማስረጃ ነው። ይህ ለሽብርተኞቹ ስኬት ነው።
2. ከድርጊታቸው ይልቅ ምክንያታቸው እንዲወራላቸው ይፈልጋሉ። ማንም ሰው ድጊታቸውን እንደሚቃወመው ስለሚያውቁ የፈፀሙበትን ምክንያት በመግለፅ የህዝቡን ድጋፍ ማግኘት ይፈልጋሉ። ህዝቡ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው፣ በመጥፎና በጉልበተኞች እጅ አንደወደቀ፣ ብቸኛው አማራጭም ሽብር እንደሆነ ማስረዳት ይፈልጋሉ። ሚዲያዎችን ለይተውም ጥሩ ግንኙነት ለመመስረት ይፈልጋሉ።
3. ጥሩ ግንኙነት ብቻ መመስረት አይደለም በማለት በሶስተኛ ደረጃ ያስቀመጡት ደግሞ በገንዘብ አቅማቸው የተዳከሙ፣ በፖለቲካ ስርዓቱ የተበሳጩ ጋዜጠኞችን ፈልገው በመደጎም ከተሻለም ትንንሽ የዜና ተቋማትን መመስረት ይፈልጋሉ።
4. ህጋዊ እውቅና ማግኘትን ይፈልጋሉ። በተለይም በጠላቶቻቸው ዘንድ የሚፈጠረውን ልዩነትና መከፋፈል በሚዲያ በማስነገር የነሱን ህጋዊነትና አስፈላጊነት ማጉላትና ሽብርተኝነትንና ፖለቲካዊ ርዕዮተ አለማቸውን መሳ ለመሳ ማካሄድ ይፈልጋሉ። በርዕዮተ ዓለማቸው እንዲመሰጥ ያደርጉና ህዝቡን ተከታያቸው ያደርጋሉ።
5. የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማቋቋም፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች በማድረግ፣ የትምህርት ተቋማትን በመገንባት፣ ወዘተ ሚዲያው እውቅና እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። Islamic Association For Palestine (IAP) በቴክሳስ የሚገኝ ትልቅ ተቋም ሲሆን ሙሉ በሙሉ የሚደገፈው ግን በ Hamas ነው ።

6. በተቃዋሚዎች ላይ ክስረት ለማምጣት፣ ተቃዋሚዎቻቸውን የሚያዳክም መረጃ ለማቀበል ሚዲያውን ይጠቀሙበታል። በተለይ ይህ ነገር የሚዘወተረው ድርጊቱን/ወንጀሉን የሚፈጽሙበት በቂ ምክንያት ሲያጡ ነው። ያኔ ሚዲያው በህብረተሰቡ ውስጥ ፍርሃት እንዲያስተጋባ፣ ስጋት እንዲያሰራጭ፣ የኢኮኖሚ ድቀት እንዲያፋጥን ለምሳሌ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መስኩን በመጉዳት ህዝብ መንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ በማድረግ፣ ህዝብና መንግስትን ላልተፈለገ ብጥብጥ በማነሳሳት ወዘተ እያለ ይቀጥላል ጥናታዊ ጽሁፉ።

እንግዲህ አስደንጋጩ እውነታ ከዚህ በኋላ ግልጽ እየሆነ የመጣ ይመስላል። እስቲ ሌሎቹን እንተዋቸውና በተራ ቁጥር 6 ላይ የተቀመጠውን የሽብርተኞች ፍላጎት መለስ ብለን እንቃኘው። በቀጥታ ለመቃወም ብቻ ይኖራሉ ያልኳቸው የግል ጋዜጦቻችንን አጠቃላይ ሁኔታ ከዚሁ ነጥብ አንፃር ብንመረምራቸውና በየፊት ገጾቻቸው ላይ ይዘው የሚወጧቸውን ርእሰ ጉዳዮች ብንፈትሽ ያለው ሁኔታ የምር ያስበረግጋል።

መስቀል አደባባይንና የግብጽን ታህሪር አደባባይ በግድ ለማመሳሰል ከመሞከር የሚሻል የሽብርተኛ ድረጊት ከየትም አይመጣም። የሊቢያው እሳት አዲስ አበባ ውስጥ ካልነደደ ሞተን እንገኛለን የሚሉ ጋዜጦቻችንን ቤት ይቁጠራቸው። ዛሬ የግል ጋዜጣ የሚያዘጋጁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከቀናት በፊት የት እንደነበሩና ገበያው ከሞላጎደል ከየት እንደሚመጣ መጠየቅ ላይከብድ ይችላል።

ጎረቤቶቻችን እነማን እንደሆኑ ይታወቃል እኮ። የአልሸባብ እጅ፣ የኢሳያስ አፈወርቂ ናቅፋ እስከ አንዳንድ ግል ጋዜጦቻችን ቢሮ አይደርስም ማለት አይቻልም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከላይ በተራ ቁጥር 1 የተቀመጠው የሽብርተኞች የሚዲያ ፍላጎት (ጥናቱ እንዳለው ከድርጊቶቻቸው ይልቅ ምክንያቶቻቸው እንዲወራላቸው ይፈልጋሉና ነው። ይህ እውነት ቁልጭ አድርጎ የጋዜጦቻችንን የአሁን ወቅተ ተግባር ያሳየናል።) ለሃገራችን አንዳንድ መረን ለለቀቁ ጋዜጦች እንደማንቂያ ደወልና የገቢ ምንች ያገለግላል። ሁለቱም የየራሳቸውን ደካማ ጎኖች አገጣጥመው ይሰፉታል።

አንባቢያንስ ብንሆን ሚዛናዊ ዘገባ ሰራን በሚል ሽፋን ከየድረገፁ የምንቀበላቸው "ጥናታዊ" እና "የምርምር" ጽሁፎች ስለምን እንደሚያወሩ ፈትሸን ይሆን? ጋዜጠኞስ ግዙፎቹ የእርዳታ ድርጅቶች ይፋ የሚያደርጉዋቸውን የጥናት ውጤቶች ተርጉመን ጋዜጦቻችን ላይ ስናወጣስ ምን እያሰብን ይሆን?፣ የተከፈለንን ዶላር፣ ውሎ አበል፣ ወይስ የመረጃውን ጀርባ?ዝም ነው መልሱ።


Videos From Around The World

 


 
Tigrai Telethon July 28, 2019
Armed with a slogan "Tigrai bi Tsifrina!" organizers were expecting to raise around 250 million but Tigrai Telethon has surpassed 600 million and still counting!!! The Diaspora Community is yet to be counted but the plan is in the works to raise more funds from North America in the coming months! Congratulations!!


 Mark Your Calendar


Atlanta for Tigrai 2019 Event

 


To All Northern California Tigreans!!

August 25, 2019

 Ashenda Boston 2019 Event

 Victoria Australia for Tigrai 2019 Event

 Ashenda Philadelphia 2019 Event

 Ashenda Dallas 2019 Event

 Ashenda San Diego 2019 Event

 Ashenda London 2019 Event(updated!)

 Ashenda Portland 2019 Event

 Ashenda Houston 2019 Event

 Seattle Ethiopian New Year Event

 


Follow US on Facebook

 Custom Search

 


Opinions and Views published on this site are those of the authors only! Aigaforum does not necessarily endorse them. © 2002-2018 Aigaforum.com All rights reserved.