የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች

Articles

የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች



ራሄል ከመገናኛ- ሳምንታዊ ጋዜጣ የሆነችው ፍትህ ለህትመት በምትበቃበት እለተ አርብ መስከረም 12/ 2004 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹‹የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ሲጋለጡ›› በሚል ርእስ አንድ የግሌን አስተያየት የያዘ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡ የጽሁፌ መነሻና መድረሻም አንዳንድ የግል ፕሬሶች የመጻፍና የመናገር ህገመንግስታዊ መብትን ከለላ በማድረግና የአመጽ ጥሪዎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እየጠሩ ስለመሆናቸውና፤ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ከግሉ ፕሬስ ጋር ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በመፍጠር በሰላማዊ ትግል ሽፋን ባልተገባ ድርጊት ውስጥ የሚገኙ እንደሆነና ይህንንም በቅርቡ በቁጥጥር ስር ከዋሉትከ ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች እና የፓርቲ አባላት ገር በተያያዘ የሃገራችን የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ያለውን እንደምታ የሚዘረዝር ነበር፡፡ ሆኖም ተጠርጣሪ ያልኳቸው በግልጽ የፍርድ ቤት ውሳኔ ያላገኘን ግለሰብ ወንጀለኛ ብሎ መደምደም እንደማይቻልም በጽሁፌ ሰፍሮ ሳለ ግና በማግስቱ ለህትመት የበቃችው አውራምባ ታይምስ ጽሁፉ የኔ የራሴ የግሌ ሆኖ ሳለ በርእሰ አንቀ አሸባሪ ተብለናል ፣እያስፈራሩን ነው የሚል አቋሟን ይዛ ብቅ አለች፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ የፍትህ አምደኞች እና ዋና አዘጋጅ ጽሁፉን መነሻ በማድረግም የመስከረም 19/2004 ዓ.ም እትማቸውን በኡኡታ ሞሉት፡፡ ዋና አዘጋጁም ‹‹እኔም ….አሸባሪ ነኝ!›› ሲል ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ ደግሞ ‹‹….ሰላይ ወይስ አሸባሪ ጋዜጠኛ?›› ሲል ጠይቋል፡፡ ደሳለኝ በዛብህም ‹‹…..ጸረ ሽብር ሽብር እንዳይሆን በደንብ እናስብበት›› ሲል አቤ ቶክቻውም ‹‹የሽብር ምንቸት ውጣ፣ የጎመን ምንቸት ቁጭ በል! ›› ሲል አሸሙሯል፡፡ መስከረም 19/2004 ዓ.ም ለህትመት በበቃችው ፍትህ ጋዜጣ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የ‹‹በግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ሲጋለጡ››ን በማጣመምና የመንግስት አቋም እንደሆነ በማስመሰል ብዙ ብዙ ነገር የተባለ ቢሆንም ቀልቤን የሳበኝና ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ግን “ኢህአዴግ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና አዲስ ዘመን” በሚል ርእስ ዳንኤል ተፈራ የተባሉ ጸሃፊ ያስነበቡን ጽሁፍ ነው፡፡ በዚህ ርእስ ከተጻፈው ጽሁፍ አንዲቷን አንቀጽ ልጥቀስና ወደራሴ አስተያየት ላምራ፡፡

“ እነዚህን ሁለት የመንግስት ሚዲያዎች በጨዋ ቋንቋ ለመውቀስ እንድነሳሳ ያደረገኝ ደግሞ እነዚህ ሚዲያዎች በመንግስትና በህዝብ መካከል በመሆን እንዲሁም በመንግስትና በተቃዋሚ መካከል በመሆን ሚዛኑን የጠበቀ ዘገባ ማቅረብ ሲገባቸው አንድ የፓርቲ ልሳን የሚፈጽመውን ተግባር በመፈጸም፣ እንደ አንዳንድ መፍቀሬ ኢህአዴግ የለከፋቸው ወይም ያሣበዳቸውና በግል ጋዜጣና ሬድዮ ስም በተቋቋሙ ሚዲያዎች የሚተገበሩትን ኢ-ስነምግባራዊ የሆነ ተግባር የሚደግም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡” ይላሉ ጸሀፊው፡፡

በመጀመሪያ ለጸሃፊው ማስገንዘብ የምሻው ‹‹እብድና ልክፍተኛ›› እርሶ እንደሚሉት የጨዋ ቋንቋ አይደሉም፡፡ ምናልባት በናንተ ቋንቋ የጨዋ ቋንቋ ሆነው ከሆነ አስገራሚ ይሆናል፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ማንም እንደማይመለከት አዲስ ዘመንንም ማንም እንደማያነብ እርሶና ሌሎቹም የፍትህ አምደኞች ቢነግሩንምና እንደዚህ ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ሌሎች አድማጭ-ተመልካቾች እንዳሉ ሆነው ቢያንስ እኔና እናንተም ግን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ከሚመለከቱና አዲስ ዘመንንም ከሚያነቡ መካከል መሆናችንን የሚጠራጠር ያለ አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪም ፍትህ ጋዜጣን ጨምሮ አብዛኞቹን የግል ፕሬሶች እኔ እንደማነብ ለራሴ እራሴ መመስከር ስለምችል ሌሎች አያዩትም አያነቡትም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ መጻፍ ተገቢ ስላልሆነ ባንተዛዘብ ጥሩ ነው፡፡ በመቀጠል ፀሀፊው እንደሚሉት እነዚህ የመንግስት ሚዲያዎች በመንግስትና ህዝብ፣ በመንግስትና ተቃዋሚ መካከል በመሆን ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ፤ እኔም በዚህ መርህ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ ምክር ለአዲስ ዘመንና ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቻ ወይስ ለነፍትህ፤ለነአውራምባና ለሌሎችም የግል ፕሬሶች ነው የሚሰራው? በኔ አረዳድ ጸሀፊው ለሁሉም ይሰራል እንደሚሉ እገምታለሁ፡፡ ይህ ከሆነ ታድያ መቼ ነው እነፍትህና መሰሎቿ በመንግስትና ህዝብ፣ በመንግስትና በተቃዋሚ መካከል ሆነው ሚዛናዊ ዘገባ አቅርበው የሚያውቁት? ስል እጠይቃለሁ፡፡ እድሜ ዘላለማቸውን እንደ ተቃዋሚ ልሳን ሆነው እንጂ ልማትን ሲያበረታቱ፤ሚዛናዊ ሆነውና ትክክለኛ መረጃ ይዘው ሲተቹ፤ የጎደለውን ሲጠቁሙ፤ሙያዊ ስነ ምግባሩን ጠብቀው በጨዋ ቋንቋ ሲናገሩ ተመልክቼም ሆነ አንብቤ አላውቅም፡፡ ይህ ታዲያ የሚመለከተው ፍትህና መሰሎቿን እንጂ ሌሎች ይዘታቸውንና/Specific Content/፤ አላማቸውንና ግባቸውን ለይተው፤ሙያዊ ስነ ምግባሩን ጠብቀውና ሚዛናዊ ሆነው እየሰሩ ያሉትን አይደለም፡፡ ጸሀፊው እንዳሉት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ልማትን የሚያበረታቱ፤መንግሥትን የሚተቹ፤ የመንግስትን ህፀፆች የሚጠቁሙ፤ ህብረተሰቡን ለልማትና ለሰላም እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚያነሳሱ አንዳንድ የግል ፕሬሶች ቢኖሩም በነፍትህና መሰሎቿ የሚታዩት እንደ ‹‹ተለጣፊ›› እና በግል ስም እንደሚነግዱ ሆነው ነው፡፡ ይህ አመለካከት ደግሞ ጸረ-ዴሞክራሲያዊና የሌሎችን መብት የሚጋፋ ነው፡፡ እኔ ደግሞ እናንተ በግል ፕሬስ ስም፣ በመናገርና በመጻፍ ህገመንግስታዊ መብት ስም፣ በጋዜጠኝነት ስም ሥራችሁ ሌላ ነው እያልኳችሁ ነው፡፡ ‹‹ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ›› የሚለው ብሂል የሚገኘው ከናንተው መንደር ነው፡፡ ፍትህና መሰሎቿ በይዘት ደረጃ ሲታዩ የአንድነት ልሳን ከሆነችው ‹‹ፍኖተ ነጻነት›› ጋር መመሳሰላቸውን ለመናገር ጥናት የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡ ታዲያ እንዴት ቢያዩት ነው አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የፓርቲ ልሳን ናቸው ለማለት ያስደፈሮት? እነዚህማ የመንግሥት እንጂ የአንድ ፓርቲ /የገዥው ፓርቲ/ የግል መገልገያዎች ሊሆኑ አይችሉም፤አይደሉምም፡፡ መንግሥት ከህዝብ ጋር ሊገናኝና መልእክቱን ማስተላለፍ የሚችለው የግድ እነዚህን ሚዲያዎች በመጠቀም ስለሆነ እዚህ ላይ መንግሥትንና ገዥውን ፓርቲ ለያይቶ ማዬት ተገቢ ይሆናል፡፡ ወደድንም ጠላንም፤የትኛውም ፓርቲ ወደ ሥልጣን ይምጣ እነዚህ ሚዲያዎች የመንግሥትና የህዝብ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ፍኖተ ነጻነት በግልጽ የፓርቲ ልሳን መሆኗን አሳውቃ የምትሰራና የምትታወቀውም በዚሁ ይዘቷ በመሆኑ ይህ በራሱ ችግር የለውም፡፡ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና አዲስ ዘመን የሚሰራው የጋዜጠኝነት መርህ ለናንተ የማይሰራበት ምክንያት ምንድነው? ለምንስ ነው እናንተ በመንግስትና ህዝብ ፣በመንግስትና ተቃዋሚ መካከል ሆናችሁ የማትሰሩት? መቼም የምንካካድ አይመስለኝም፤ መነሻ ያደረኩትን የመስከረም 19/2004 ዓ.ም እትም ብቻ ማየት ለአንባብያን በቂ ማስረጃ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ መንግስትን በማወገዝ ተቃዋሚውን በማንቆለጳጰስ ሥራ ተጠምዶ የሚገኘው ማነው? ለምንስ ነው ሁሉም ሚዲያ ተሰባስቦ በአንድነት የገዢው ፓርቲ ጠላት እንዲሆኑ የምትመኙት? ለነገሩ የናንተ በምኞች ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ሁሉም የገዢው ፓርቲ ስራ እንደታከተውና የገዢው ፓርቲ ጠላት እንደሆነ ደምድማችሁ ነው የምትናገሩት፡፡ አፍቃሪ ኢህአዴግ መሆን ወንጀልና ሃጥያት የሚሆነው በየትኛው መርህ ነው? ለእናንተ መቃወምና መጻፍ መብት እንደሆነው ሁሉ ለኔና መሰሎቼም ደግፎ መጻፍ፤ለሌላው ደግሞ የስርአቱ አካል መሆን መብት ይመስለኛል፡፡ እናንተ ስትጽፉ ጋዜጠኛ ሆነን ነው ትላላችሁ፤ የአዲስ ዘመንና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ደግሞ ሲጽፉና ሲናገሩ ካድሬ ትላላችሁ፡፡ በግላችን ለምንጽፈው ደግሞ ደግፈን ከሆነ የግለሰብ ሳይሆን ጽሁፋችንን የኢህአዴግ አቋምና የፓርቲው ጽሁፍ ታደርጉታላችሁ፡፡ የእኔ ግርምት የመነጨውም ከዚህ የተሳሳተ አመለካከታችሁ ወይም ግምታችሁ ነው፡፡ እኔ እንደማንኛውም አንድ ነጻ ዜጋ ሆኜ የጻፍኩትን የግል እምነቴን /አመለካከቱን የሚጋሩ ሌሎች ዎገኖች ቢኖሩም/እንደ መንግሥት አቋም ወስዳችሁ ስታብጠለጥሉት ሳይ በሁኔታችሁ አፈርኩ፤ምንና እንዴት እየሰራችሁ እንደሆነም ለእኔ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሆኖኛል፡፡ ደግፎ የጻፈ የኢህአዴግ ካድሬ ከሆነ ተቃውሞ የሚጽፈው ሁሉ ደግሞ በናንተ አመክንዮ የተቃዋሚ ፓርቲ ካድሬ የማይሆንበት አግባብ ይኖር ይሆን? ታዲያ ይህ ምን አይነት ፍርደ ገምድልነት እንደሆነ ይታያችኋል? የመንግሥትን ፖሊሲ ደግፎ ለመናገር የግድ የኢህአዴግ አባል ወይም ቀንደኛ ደጋፊ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ማንም ከዚህ ራሱን ነጻ አድርጎ የመሰለውን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ሊጽፍና ሊናገር ይችላል፡፡ ወደ ሌላውና ወደ አስገራሚው የአቶ ዳንኤል ተፈራ ሀሳብ ላምራ በዚሁ ‹‹ኢህአዴግ፣የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና አዲስ ዘመን›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ ተከታዩ አንቀጽ ሰፍሯል፡፡

‹‹አቶ አንዱአለም አራጌና ሌሎች ሁለት የብሄራዊ ምክር ቤቱ አባላት የታሰሩበት አንድነት ፓርቲ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ልቅም ተደርጎ ከተወሰደ በኋላ ለምን ተብራርቶ አልቀረበም? የፓርቲው ሊቀመንበርና ሌሎች ያላቸው ሀሳብ ለምን ለህዝብ አልቀረበም?--እነዚህን ጥቄዎች የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና አዲስ ዘመን መመለስ አለባቸው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች እስካልመለሱ ድረስ ግን የሚያቀርቡት ሀሳብ የአንድ ወገን ብቻ ይሆናል›› ይላል፡፡

የፓርቲው መግለጫ መብራራት ካለበት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወይም በአዲስ ዘመን ጋዜጠኞች ሳይሆን በፓርቲው ወኪሎች በኩል ይመስለኛል። ለምን? ከተባለ መልሱ ያለው እርሶ ጸሀፊው ጋር ሳይሆን የፓርቲው አመራሮች ጋር ነው የሚሆነው፡፡ ዳሩ ግን በመንግስት ሚዲያ መናገርና መጻፍ ተለጣፊ ያስብለናል ከሚል መነሻ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስት ሚዲያ አለመናገርንና መግለጫ አለመስጠትን እንደ አንድ የትግል ስልት መጠቀሚያ እየተደረገ እንደሆነ አናውቅም ወይ? ከዛ ልክ እንደ እርስዎ የመንግስት ሚዲያ የገዢው ፓርቲ ልሳን ሆነ ብሎ ለመጮህና ለማጯጯህ እንዲመች፡፡ እናንተ የተቃዋሚውን መግለጫ ልቅም አድርጋችሁ ስታብራሩ የገዢውን ፓርቲ መግለጫና የመንግስትን የልማት ዜናዎች ስለምን ነው ወደጎን የምትተውት? ይህም ይቅር በስንቱ የመንግስት ፕሬስ ኮንፈረንስ፤ሁነቶች፤የልማት ሲንፖዝየምና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው መድረኮች ተገኝታችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን በትክክልና ሚዛናዊ ሆናችሁ ዘገባና ትንታኔ የሰራችሁ? ለጩኸት የማይመች የመንግስት መግለጫና የልማት እንቅስቃሴ በናንተ በጨዋዎቹ ቋንቋ ‹‹ባዶ ጩኸትና የካድሬ ዲስኩር›› አይደል፡፡ ለዚህ ነው የራሷ አሮባት የምለው፡፡ እየተዋወቅን የምን ወደጎን ነው፡፡ እናፍረጥርጠው ከተባለማ ብዙ ጉድ አለባችሁና እንዲያው በስሱ ጥቂት ማመላከቻዎችን ብቻ እየነካካን ብናልፍ ነው የሚሻለው፡፡

ይህችኑ የመስከረም 19 ፍትህ እንመልከት እኔም ‹‹አሸባሪ›› ነኝ የሚሉት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ሰላይ ወይስ ‹‹አሸባሪ›› ጋዜጠኛ? የሚሉት ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ በጽሁፋቸው ላይ ምን እያሉ ይመስሎታል? ዘላፊ የሚሉትን አዲስ ዘመንና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የበለጠውኑ እየዘለፉት እየዘረጠጡት እያወገዙት እንጂ እየተቹት ይሆን? አሽሙረኛው እንደሆነ አንደኛውን የሚጽፈው አሽሙረኛ ሆኖ እንጂ ጋዜጠኛ ሆኖ ስላይደለ አንገረም ይሆናል፡፡ ምን ጊዜም እንደምታደርጉት ሁሉ እናንተ ‹‹በጨዋ ቋንቋ›› ብላችሁ ጀመራችሁና ግለሰብን ብቻ ሳይሆን ተቋምንም ጭምር በመዘርጠጥ ደመደማችሁ፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የናንተ የጋዜጠኝነት ስነምግባር፡፡

‹‹የመፃፍ ነጻነት ይከበር፣ ኑሮ ተወደደ፣ ገዢው ፓርቲ በሙስና ተዘፈቀ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ የሚሉና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ መጻፍ አሸባሪ የሚያስብል ከሆነ አዎን እኔም አሸባሪ ነኝ›› ለሚሉት የፍትህ ዋና አዘጋጅ በኔ በኩል በግሌ ያለኝ አስተያየት እርሶ የሚሉትን የሚጽፍ አሸባሪ የሚያስብል አይመስለኝም፤ብሎም የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ከጠቃቀስኳቸው ርእሰ ጉዳዮች በስተጀርባ ወደ ዝርዝሩ ሲገባ የሚገኘው የደባ መልእክት ነው ሊያስጠይቅ የሚችለው የሚል አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ አሸባሪ ብሎ የመጨረሻ ብይን የመስጠት መብቱና ስልጣኑ የፍርድ ቤት እንጂ የመንግስት ወይም የአንድ ግለሰብ ወይም የገዢው ፓርቲም አይደለም፣ ሆኖም የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ እራስዎን በዚያ ጥግ ወይም ጎራ የመፈረጅዎ ግን ስለራስዎ ከራስዎ በላይ የሚያውቅ ካለመኖሩም በላይ በበኩሌ ጉዳዩ የግለዎ ስለሆነና ኃላፊነቱን ስለሚወስዱ በዚህ ላይ የምለው አይኖረኝም፤አያገባኝም፡፡ ነገር ግን የህዳሴውን ግድብ ማጥላላት፣ ለግድቡ የሚደረጉ መዋጮዎችን ማኮስመንና ማጣጣል፣ በአርሶ አደሩና በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ላይ ማፌዝ፣ በሰንደቅ አላማ ቀን ላይ ማሽሟጠጥና የመሣሠሉትን መጻፍ ቢያንስ ጸረ ልማትና ሌላም ሌላም ሊያስብል እንደሚችል ግጥም አድርጌ ልነግሮት እፈልጋለሁ፡፡ እኔም እንደእርሶ እደግመዋለሁ ‹‹መርዶ ነጋሪ፣ መዓተኛ፣ ጸረ ልማት ጋዜጠኛ….›› ያስብላል፡፡

ወደ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ ስመለስ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት ጓዶቻችን በርግጥም የታሰሩት የሽብር ወንጀል ተባባሪ ሆነው ሳይሆን እንደጠረጠርነው በጻፉት ጽሁፍ መሆኑን ከመንግስት ሚዲያዎች ስላረጋገጥን ጸሃፊያን ሁሉ ተጠንቀቁ በጋራ እንቁም የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ሆኖም በጻፉት ጽሁፍ ነው የታሰሩት የሚል መግለጫም ሆነ ሌላ አስተያየት ከመንግስት ሚዲያ በኔ በኩል አላዳመጥኩምም አላነበብኩምም፡፡ በግሌ ከጻፉት ጽሁፍ በስተጀርባ እንዲሁም የጽሁፋቸው ይዘት በራሱ የጸሃፊዎቹን ስብእና እና ማንነት፤ለማንና ለምን እንደቆሙ የሚያመለክት ነው የሚል አስተያየት ሰንዝሬያለሁ፤አሁንም ይህ የግል አቋሜ ነው፡፡ አሁንም ደግሜ መናገር የምፈልገው ጽሁፍ ሲባል ይዘቱ ምንድነው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ሽብርተኝነትን የሚያበረታታና አመጽን የሚጋብዝ ጽሁፍ በሽብርተኝነት ህጉ መሰረት በተባባሪነት ያስጠይቃል የሚል አስተያየት ነው ያለኝ፡፡ ምናልባት ጋዜጠኛ ዮናስ እንደሚሉን ምንም ተጻፈ ምን መንግስትን የሚነካ ባለስልጣናትን የሚያስቆጣ ጽሁፍ የሚያሳስር ከሆነ እንደጋዜጠኛ ከነ እንቶኔና እንቶኔ… በላይ ዘለፋና ቀረርቶን የሚጽፉት እነማን እንደሆኑ ስለሚታወቅ ለምን ታዲያ እነሱስ አልታሰሩም? የሚል ጥያቄ እጠይቃለሁ፡፡ ነውረኛ አባባሎችን በመንግሥት ተቋማት ከዚያም አልፎ በመንግስትና ባለስልጣኖችና ግለሰቦች ላይ የሚያዘንቡት የፍትህና ሌሎች የነጻው ፕሬስ አምደኞች ለምን አልታሰሩም? ነገሩ ሌላ ነው፡፡ ዛሬም ጋዜጠኛው ለማወናበድና ለማደናገር ባይጣጣሩ ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ሌላው ስለኤህአዴግና ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና አዲስ ዘመን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆን የጻፉት ጸሃፊ አንዳንዶቹን የግል ፕሬሶች ተለጣፊ ሲሉ የፈረጁበት ተጠየቅ በጣም የሚያሣዝን ነው፡፡ በህትመት ዳሰሳ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ማስተዋወቂያ መግቢያ የፍትህ ጋዜጣ ሽፋን አለመታየቱ ሌሎቹን በግል ስም የተቋቋሙ ተለጣፊ የሚያሥብልበት አመንክንዮ ምንድነው? ምናልባት ጋዜጣዋን ለማስተዋወቅ ተፈልጎ ከሆነ ግን ሌሎች ብዙ አማራጮችን መመኮር እንጂ የፍትህ ሳምንታዊ እትም በመንግስት ሚዲያ ካልታየና ዘጋባዎች ካልተላለፉልን ብሎ ዘራፍ ማለትና ሚዲያውን ሚዛናዊ አይደለም ብሎ መናገር ጉንጭ አልፋ ነው፡፡

እንደማጠቃለያ
ባጠቃላይ ከላይ የጠቀስኳቸው የግል ፕሬሶችም ሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንደሚያወሩት በኢትዮጵያ ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መጠናከር እየሰሩ ሳይሆን ‹‹የሁለት ቢላዋ…›› ጨዋታ እየተጫወቱ ነው፡፡ ህጋዊነት እና ህገወጥነትን እየቀላቀሉ እየተደረገ ያለውን መልካም የልማት እንቅስቃሴና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በማጠልሸት በሂደቱም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በማጋነንና በማጋጋል ህዝቡን ወደ ማይፈለግ አቅጣጫ ማምራት እንዳለበት በማስገደድ ጭምር እየቀሰቀሱት ይገኛሉ፡፡ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ተጠርጥረው የታሰሩትን ግለሰቦች በተመለከተ ጋዜጦቹ እንደጻፉትና በተለይም የአንድነት ፓርቲ እንደሰጠው መግለጫ ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ ወንጀለኛ ሳይባሉ ወንጀለኛ ተብለዋል እያሉ ሲከሱ ለህግ የበላይነት ያላቸውን ጽኑ አቋም በመግለጽም ጭምር ነበር፡፡ ሆኖም መልሰው የፍርድ ቤቱን ነጻነትና ስራ በመጋፋት ሳይጠሩ አቤት እያሉና መመስከርም እየዳዳቸው ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ስለተጠርጣሪው አርቲስት መስክር ብባል ብለው በፍትህ ጋዜጣ ላይ ባሰፈሩት መልእክት አርቲስቱ ንጹህና የሽብርተኝነት ፍላጎትም እንደሌላው አመልክተዋል፡፡

የፍትህ ተቋማቱን ስልጣን መጋፋታቸው አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ፕሮፌሰሩ ያልተገነዘቡት ነገር ለተመኙት የምስክርነት ጥያቄ የሚያበቃቸው ስብእና የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ምርጫ 97ን ተከትሎ መንግስትን በሀይል ለመጣልና ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ ባደረጉት ሙከራ በቁጥጥር ስር ውለው ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በእስር ከቆዩ በኋላ ለህገመንግስታዊ ስርአቱ ተገዢ እንደሚሆኑ ቃል በመግባት የጠየቁት ይቅርታ ተቀባይነትን አግኝቶ በቅድመ ሁኔታ ተፈተዋል፡፡ በቅድመ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ ደግሞ ለምስክርነት እንደማይበቃና በህጉና ህገመንግስታዊ ስርአቱ ላይ አንዳች አይነት አሉታዊ ተጽእኖ ለማሳረፍ ቢሞክር የሚጠብቀውን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ያላወቀ መስለው አሁንም ዜጎች በፍትህ ስርአቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲገባቸው እየቀሰቀሱ ይገኛሉ፡፡

ሌሎቹም የፓርቲው አመራሮች በተመሳሳይ በአንድ ጥግ ተሰልፈው ከርቀት የግንቦት 7ን ድልና ውድቀት ያማከለ ደባ እየፈጸሙ ነው፡፡ ግንት 7 በያዘው አቅጣጫ የተሳካለት እንደሆን ተደባልቀው የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ካልተሳካም ኑሮአቸው ሳይናጋ የሚቆዩበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ ናቸው፡፡ ሽብርተኝነትን እንቃወማለን የሚሉት ፍትህና አውራምባ ታይምስም ቢሆኑ ለአፋቸው ያህል ጸረ ሽብር ሃይል መሆናቸውን ይናገሩ እንጂ በተግባር ያሉበት ሁኔታ ግን ለየቅል ነው፡፡ የእነዚህ ጋዜጦች አዘጋጆችና አምደኞች ለአንድም ቀን ተሳስተው ፓርላማው ሽብርተኛ ናቸው ሲል የፈረጃቸውን ግንቦት 7ትን፣ኦነግንና ኦብነግን ሲተቹ፣ ሲኮንኑና ሲያወግዙ አይቼ አላውቅም፡፡ በአንጻሩ ለሻእብያና ተላላኪዎቹ ጥብቅና ሲቆሙ ነው የማየው፡፡ ለሀገራቸው ተቆርቋሪ የሚመስሉት እነዚህ ጋዜጦች ዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገሮችንና ድርጅቶችን እርዳታ እንዳይሰጡ ሲወተውቱና ሲማጸኑ ነው የሚደመጡት፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቁ ስለሀገራችን መልካም ገጽታ የሚናገር ዲፕሎማት እንኳን ቢኖር ለማብጠልጠል ብእራቸው ፈጣን ነው፡፡ የቀድሞዋን የአሜሪካን ዲፕሎማት ሃድልስተን ከሰሞኑ ምን እያሏቸው እንደሆነ መመልከት ስለጋዜጦቹ ማንነትና ከተቃዋሚው ጎራ ጋር ያላቸውን ስልታዊ ግንኙነት ወይም በሁለት ቢላዋ እየበሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ዝነኝነትን የመሻት አዝማሚያቸው ጣሪያ ከመንካቱ የተነሳ ስለሚጽፉት ነገር እንኳን ልብ ማለት የማይሹት እነዚህ ጋዜጦች አሁን ደግሞ ስማቸውንና የፈረዘ ጸጉር የለበሰ ፎቶግራፋቸውን ብቻ ለኪራይ በማዋል በዘመነ አብዮት ጊዜ የሚጽፉ ግለሰቦችን ጽሁፍ በማስተናገድ ላይ ናችው፡፡ ነገሩ ሁሉ እንዴት ነው ጃል፤በዘመነ አብዮት ጊዜ በአፍሮ ጸጉር፤ዛሬ ደግሞ በፈረዘ ጸጉር መጡብን እንዴ ያስብላል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በምርጫ 97 ዋዜማና በኋላ በነበሩ ጋዜጦች ላይ ሲወጡ ከነበሩ ጽሁፎች በኮፒ ፔስት በቀጥታ ገልብጠው ወይም ቀይጠው እያስነበቡን ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት ሰሞንኛውን ፍትህና ከምርጫ 97 ቀደም ብሎ የነበሩ ጋዜጦችን ማመሳከር ብቻ በቂ ነው፡፡ ዳሩ አላማቸው አመጽ በመሆኑ አልፈርድባቸውም እንጂ ለነጻ ፕሬስ መጠናከር ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መጎልበት ለህዝቡ ኑሮ መለወጥ ፍላጎቱ ቢኖራቸው ኖሮ በሌላ መንገድ ላይ ባገኘናቸው ነበር፡፡

የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ እንዲሉ፤ የበሬ ወለደ የመጫዎቻ ኳሳቸውን እያንቀረቀቡና ሲያሻቸውም ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ እየለጉ ጋዜጦቹ ለተቃዋሚ ተብዬዎቹ ፣ተቃዋሚዎቹ ለጋዜጠኞቹና ለነሂዩማን ራይትስና መሰሎቹ፤እነሱም መልሰው ለተቃዋሚዎችና ለጋዜጠኞቹ እየተቀባበሉ ተመልካች በሌለው ሜዳ ውስጥ ውድድር አልባ ጨዋታ እየተጫዎቱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ታድያ ምን እንጠብቅ ነው መጨረሻው፡፡ የሚጠበቀውንም እያየን ነው፡፡ በጎ ነገርን ሁሉ አነፍንፎ ማጠልሸት፣ ማጣጣል፤ማንቋሸሽ ተቋማትንና ግለሰቦችን መዘርጠጥ…. የፍትህ ሥርአቱን ‹‹የካንጋሮ ፍርድ ቤት›› ያሉ ሰዎች ለምስክርነት ራሳቸውን ሲጠሩ፣ብቻ ምኑ ቅጡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ምንድነች አሉ የራሷን ሳታይ በሰው እንትን የሳቀችው? ነገሩ ሁሉ እንደሱ መሆኑ ነው፡፡ ለማናቸውም ተጠርጣሪዎቹ የሚያገኙትን የፍርድ ቤት ውሳኔ መጠበቅ ነው፡፡ የነዚህ ጋዜጦች መቅበጥበጥ በራሱ ስአት ጡዞ ፈረንጆች እንደሚሉት/Boiling Point/ ላይ በመድረሱ አንዳንድ ጉድም እያሰማን ነው፡፡ እራሳቸው ከሚያውቁት ስራቸው ተነስተው ይመስለኛል አንዳንዶች ጭራሹን ‹‹…..እኔም ሽብርተኛ ነኝ›› በማለት ራሳቸውን መፈረጅ መጀመራቸው ለኔ የጤና አልመሰለኝም፡፡ ለማንኛውም ልብ ያለው ልብ ይበል ነውና የሚያመዛዝንና ቅን ልቦና ለሁላችንም ይስጠን የሚለው መልእክቴ ነው፡፡




Mark Your Calendar

Follow US on Facebook
Custom Search
Opinions and Views published on this site are those of the authors only! Aigaforum does not necessarily endorse them. © 2002-2021 Aigaforum.com All rights reserved.