ርእስ፡- ዝክረ ሕይወት ዘፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ

Articles

ርእስ፡- ዝክረ ሕይወት ዘፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ

የጽሑፍ ዓይነት ፡-ግለ ታሪክ (Autobiography)፣ ጸሐፊው (ደራሲው)፡- አበበ ሥዩም (ፊታውራሪ)፣ የኅትመት ዘመን ፡-2003፣ የገጽ ብዛት፡-344፣ ዋጋ፡-ብር 45.00፣ የታተመበት ቦታ፡-አዲስ አበባ አስተያየት፡- ደረጀ ገብሬ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን የመጻሕፍት ዝግጅትና ኅትመት እንቅስቃሴ ውስጥ አንድ ጉልህ ክንውን እየታዬ መጥቷል፡፡ እሱም የታላላቆቻችን የሕይወት ታሪኮች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች እየተሰናዱና እየታተሙ ለማንበብ መታደላችን ነው፡፡

ዝክረ ሕይወት ዘፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ ግለ ታሪክ መጽሐፍም ከላይ እንዳመለከትሁት በራሳቸው በባለታሪኩ ተሰናድቶ፣ በልጃቸው በአቶ ግርማ አበበ ብርቱ አሳቢነት የታተመ ነው፡፡

በመሠረቱ በእኛ አገር ብዙም የተለመደና በጥብቅም የሚሠራበት አይሁን እንጂ፣ በሌሎች አገሮች የሕይወት ታሪክም (Biography) ሆነ ግለ ታሪክ (Autobiography) ተጽፈው ለአንባቢዎች መቅረብ የጀመሩበት ጊዜ ዘለግ ያለ ዕድሜ አለው፡፡ ከሰማእታትና ቅዱሳን ታሪክና ሥራዎች ጋር ተያይዘው መቅረብ መጀመራቸውን፣ ልዩ ልዩ የእምነት መጻሕፍትን በመመርመር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በተለይ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረውና የሥነ መለኮት ተመራማሪ የነበረው አውግስቲን የራሱን የሕይወት ታሪክ በኑዛዜ መልክ ያቀረበበት ሥራው ለግለ ታሪክ ሁነኛ መነሻ እንደሆነ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ በኛም አገር በመካከለኛው ዘመን የነአፄ ዐምደ ጽዮን፣ የነአፄ ዘርአ ያዕቆብ፣ የነአፄ ልብነ ድንግልና አፄ ሱስንዮስ፣ የአጼ ገላውዴዎስ፣ የአጼ ሠርፀ ድንግልና የነአፄ ፋሲል ዜና መዋዕሎች ከዚያም በፊት ሆነ በኋላ የነገሡ ነገሥታት ዜና መዋዕሎች በሰፊው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ፈላስፋው [17ኛው ምእት ዓመት] የግሉን ሕይወትና የዘመኑን አስተዳደራዊ ውጣ ውረድ፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ሁኔታ ዓይን ከሰበኸት የጠቆመበት መጽሐፍ በእጃችን ይገኛል፤ እነዚህ ሁሉ የሕይወት ታሪክ ማሳያዎች የአገራችንንም ቀደም ያለ ታሪክ በከፊል ለማሳየት የረዱና ወደፊትም የሚረዱ ናቸው ቢባል ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ከታሪክ መረጃነታቸው ባሻገር፣ የሕይወት ታሪኮችንም ሆነ ግለ ታሪኮችን የምናነብባቸው ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ታሪኮቹ የሚያመለክቷቸው ግለሰቦች በኖሩበት ዘመን ያዩዋቸውን፣ የተሳተፉባቸውን፣ የሠሯቸውንና የታዘቧቸውን የኅብረተሰብ ቅጥንብር ለማወቅ፣ በዚያም አማካይነት እኛ የምንኖርበትን ዘመንና ሕይወት ይበልጥ ለመመርመርና ለመረዳት፣ የወደፊቱንም ታላሚ ሕይወት ለማቀድ በማንፀሪያነት ስለሚያገለግሉ ነው፡፡

በትምህርታዊ ጠቀሜታቸውም ረገድ ከቀጥተኛና ሕያው ምስክርነታቸው ጠቃሚ መረጃ ለመምዘዝ፣ በዘመናቸው የነበረውን የአስተዳደር፣ ያስተሳሰብ፣ ያሠራር ልምድ ለመቅሰም፣ ከጥንካሬያቸው ለመማር፣ ከድክመታቸው ለመሸሽ የሚያበቁ መረጃዎች ይገኙባቸዋል፡፡ ግለ ታሪኮችም ሆኑ የሕይወት ታሪኮች ከላይ የተጠቀሱትን ጠቅለል ያሉ ጠቀሜታዎችን የመስጠታቸውን ያህል በዝግጅታቸው ወቅት በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገባቸው ነጥቦችም አሉ፡፡ እነሱም በአጭሩ፣ የቀረበው ታሪክ ለመነበብ ሚዛን የሚያነሣና የሚያጓጓ ነወይ; የቀረበበት ቋንቋ ወይም ያጻጻፍ ስልት ጥበባዊ ደረጃውን የጠበቀ ነወይ; ታሪኩ የተዋቀረበት የቅንብር ዘዴ በአወቃቀርና በቦታና በጊዜ እውናዊና ትክክለኛ ነውይ; በታሪኩ ውስጥ የቀረቡት መረጃዎች ምን ያህል በቀዳማይና በካልአይ ምንጮች ተደግፈዋል; እንዳስፈላጊነቱ ልዩ ልዩ ፎቶዎችና የታሪኩ ማሳያ መግለጫዎች፣ ካርታዎችና የቦታ ማመላከቻዎች አሉበት ወይ; የሚሉና የመሳሰሉ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ በተለይ ግለ ታሪክን በሚመለከት ጠበቅ ተደርጎ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ፣ ታሪኩ ራሱ በአድራጊው የሚጻፍ በመሆኑ እጅጉን ጥንቃቄ የሚጠይቅ፣ የጸሐፊውን ሕሊና የሚፈታተንና የሚሞግት፣ ከአንዳንድ አስቸጋሪና አጠያሚ አጋጣሚዎች ራስን ለመከላከል ሲባል በራስ ሊገለጹ እማይቻሉ ከሚመስሉ ተመክሮዎች ለመሸሸግ፣ ለመደበቅና ለመሸፋፈን የሚገፋፉ አዝማሚያዎች መኖራቸው የሚታሰቡ ናቸው፡፡

ከዚህ በላይ በቀረበው አጭር መንደርደሪያነት ይህ ዝክረ ሕይወት ዘፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ የተባለ ግለ ታሪክ ይዘት ምን እንደሚመስል ባጭር ባጭሩ የምዘና አስተያየቶች ከዚህ ቀጥለው ይቀርባሉ፡፡

የግለ ታሪኩ ይዘት
መጽሐፉ በአጠቃላይ አሥራ ስድስት ምእራፎችና በየምእራፎቹ ስርም ልዩ ልዩ ንኡሳን አርእስት ያሏቸው ጉዳዮች ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም 21 ፎቶግራፎች፣ 6 የጽሑፍ አባሪዎችና 3 የምስክር ወረቀቶች ተካትተውበታል፡፡

በእያንዳንዱ ምእራፍ የሚነሱ ዋና ዋና ሀሳቦች ቢቀርቡም እነዚያ ሀሳቦች የባለታሪኩን ሕይወት እንደ አንድ ሰው አካል አካትተው የያዙ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይህን ነጥብ ትንሽ ላብራራው፡፡ ስለ ውልደታቸውና እድገታቸው ሲተርኩ አባትና እናታቸውን፣ ወንድም እህቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን አያት ቅድመ አያቶቻቸውን፣ አያይዘውም አገራችን ገጥመዋት የነበሩትን ሁኔታዎች፣ በትምህርትም ሆነ በቤተሰብ ትረካ ያገኙትን እውቀትና ልምድ ያቀብሉናል፡፡ ስለትውልድ መንደራቸው ሐሬና ሲጽፉ በወቅቱ በአገራችን ይበቅሉ ስለነበሩ እፅዋትና ስለመልክዓ ምድሩ ፎቶግራፍ እምናይ እስኪመስለን ድረስ ይተርኩልናል፡፡

ስለ ባድመ ታሪክ ሲናገሩ በውስጡ የተሳተፉ ሰዎችንና የተወሰኑ ውሳኔዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ቀድሞ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ስለነበሩ ውሎች ከነምክንያታቸውና ውጤታቸው ያሳዩናል፡፡ ከአድዋ ጦርነት እስከ 1928ቱ የጣሊያን ወረራ ፍንትው አድርገው ያስረዱናል፡፡ እንዲያውም የኢጣሊያ ጦር ጊዜያዊ ድል አግኝቶ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ሁላችሁም ወደቤታችሁ ግቡና በሰላም ኑሩ የሚል አዋጅ በማውጣቱ ብዙ ሰዎች ተታልለው ወደየመኖሪያ ቀዬአቸው ተመለሱ፡፡ እናታቸውም ልጆቻቸውን ይዘው አድዋ ተመለሱ፡፡ በዚህ ጊዜ የእንጀራ አባታቸው ደጃዝማች ዓባይ ካሕሳይ በሽፍትነታቸው ቀጠሉ፡፡ ጣሊያንም ከባልሽ ጋር ትገኛናለሽ በማለት እናታቸውን ያሰቃዩዋቸዋል፡፡

የጣሊያን መልቲ ልፍለፋ እውነት መስሎአቸው እናቴና በርካታ ቤተሰቦችም ከየስደት ቦታቸው ወደ ዓድዋ ተመለሱ፡፡ ባለቤታቸው ክቡር ደጃዝማች ዓባይ ካሕሳይ ግን በጣሊያን ከንቱ ስብከት ሳይታለሉ በረሃ ውስጥ ሆነው በአርበኝነታቸው ቀጠሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የአርበኛ ሚስት ነሽ፤ ከባልሽም ጋር በምሥጢር ትገናኛለሽ እያሉ ጣሊያኖች በተደጋጋሚ ጊዜ እንደላም የእናቴን ጡቶች ሲያልቧቸው አይቻለሁ፡፡ (ገጽ 4) እያሉ የልጅነት አእምሮአቸው የቀረጸውን ሥዕል ያሳዩናል፡፡

የትምህርት ቤት ትዝታቸውን ሲያወጉልን ከአድዋ እስከ አዲስ አበባ የተጉዋዙበትን ነጠላ መንገድ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ያጋጠሟቸውን ልዩ ልዩ ድርጊቶችና ገጠመኞች አቆራኝተው ይነግሩናል፡፡ አድዋ ያጠኑትን መዝሙር አዲስ አበባ መጥተው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ሲማሩ ይዘምሩታል፡፡ የሚገርመው ይህን መዝሙር ዛሬም በቃላቸው ይወጡታል፡፡ በወቅቱ ስለነበረው የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር፣ በአለባበስ ሳቢያ የተከሠተውን የባህል ውዝግብ በሚመለከት ይሰሙት የነበረውን ትረካና የተገጠመ ግጥም በጽሐፉ ውስጥ ስናነብ ዛሬ ያለንበት ጊዜና ሁኔታችን ሁሉ ምንጩ፣ ዳር ድንበሩ የት እንደተጀመረ ግምት እንዲኖረን ያደርጉናል፡፡

አያታቸውን የደጃዝማች መስፍን ወልድሸትን የሚያስታውሱበትንንና ስቃይ መከራቸውን የሚገልጹበትን ምዕራፍ ስናነብ በማንኛውም ደረጃና ሁኔታ ራስን ማክበር፣ ራስን ሆኖ መገኘት፣ ጥንትም በአባቶቻችን የሚታመንበት፣ መስዋእትነትን ለማስከፈልም የሚዳርግ፣ ሐቅ እሚያንቅ መሆኑንም ጭምር ያሳያል፡፡ ይህም የጥቂቶች ጥንካሬ ሆኖ እንደሚዘልቅም እናይበታለን፡፡ በሌላም በኩል በባለ ሥልጣናት ዘንድ ተልመጥማጭነትና እሺ ባይነት ምን ያህል ተፈላጊ እንደነበሩ እንረዳበታለን፡፡ እግረ መንገዳችንን ዮፍታሔ ንጉሤ ገጠሙት የተባለውን ግጥም እናስታውስበታለን፡፡

ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
በዚያን ዘመን የመንግሥት ሠራተኛ መሆንና በስድሳ ብር መቀጠር እንዴት ያስፈነጥዝ እንደነበር የፊታውራሪ አበበን ታሪክ ማንበብ ራሱ ለአሁኑ ትውልድ ፈገግ ያሰኝ ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ የኑሮ ሮኬት የት እንደደረሰች ለመገመት ያስችላልና ቁም ነገር የሚጨበጥበት ምዕራፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የፊታውራሪ አበበ ግለታሪክ በተለይ የመንግሥት ሠራተኛ ከሆኑ በኋላ የተጓዙበት አቀበት ቁልቁለት የአንድ ግለሰብ ታሪክ ብቻ አይመስለኝም፡፡ በዚያን ወቅት የነበሩ ሁሉ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም በማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት ያው በአንድ ሥርዓት ውስጥ ያለ መዋቅርና መዘውር ሆኖ ስለሚሰማኝ ነው፡፡ ፊታውራሪ አበበ በብር 150. 00 ተቀጥረው ትግራይ ሲሔዱ የጠበቃቸው እሳቸው የተመኙት ደስታ አይደለም፡፡ ይልቁንም ምኞታቸውን የሚያጨናግፍ ድርጊት ነበር፡፡ ያንን የሳቸውን ገጠመኝ በሚገባ ይረዱላቸው የነበሩ ታላቅ ሰው በመጽሐፉም ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል፡፡ እዚህ አዳራሽ ውስጥም ያሉ ይመስለኛል፡፡ መንግሥታት ለስም የሚሾሟቸውና ከሥር ደግሞ የሚያስቀምጧቸው ታኮዎች ቀድሞም መኖራቸውን እንድናስተውል ፊታውራሪ አበበ ረድተውናል፡፡

የአሰብ ነዳጅ ማጣሪያ፣ የአዲስ አበባ ሒልተን አመሠራረት፣ የለገዳዲ ግድብ፣ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተሠሩና ምን ምን ዓይነቶች ውጣውረዶች እንደታለፉባቸው፣ የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የፓርላማ ውሎ ምን ይመስል እንደነበረ፣ በየቦታው ይታሰቡና ይሠሩ የነበሩ የልማት ተቋማት ምን ምን እንደነበሩ በዓይን ምስክርነት ያወጉናል፡፡ በትግራይ ውስጥ መንገድ፣ ድልድይና የመጓጓዣ አገልግሎት ለማሟላት ያደረጉትን ጥረትና የደረሰባቸውን ፍዳ ጭምር ፍንትው አድርገው ያቀርቡልናል፡፡

ለከፋ ባላባት ሻሻራሻ የሚል መጠሪያ እንደነበረው፣ በዚህም መጠሪያ ዘውዴ ኦቶሮ የሚባሉ ሰው ይጠሩበት እንደነበር፣ በወሎ ዋግ ሥዩም፣ ጃንጥራር፣ በትግራይ ሹም ዐጋመ፣ ሹም ተምቤን፣ ሹም ገርዓልታ እሚባሉ መጠሪያዎች መኖራቸውን ስናነብ በሌሎቹስ ክፍለ ሀገሮች ምን ምን ዓይነት ስያሜዎች ይኖሩ ይሆን? ሳንል አናልፍም፡፡

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በጣም ትኩረት ተሰጥቶት የሚገኘው ጉዳይ ባድመ ነው፡፡ ባድመ የማን ናት? በሚል ርእስ ሰፊ ማብራሪያ ታገኛላችሁ፡፡ የኤርትራ ሰዎች እንዴትና በምን አኳኋን ወደባድመ እንደመጡ፣ በማን አስተዳደር ዘመን እንደመጡ፣ በመምጣታቸውስ ምን ምን ያደርጉ እንደነበረ፣ ውዝግቡ መቼ እንደተጀመረ፣ ምን ዓይነት ሕዝባዊ ውይይትና ውሳኔ መቼና በነማን ተሳትፎና ኃላፊነት እንደተወሰነ ጥርት ብሎ ታገኙታላችሁ፡፡ ውለኛ የሆነውን ቃለ ጉባኤም ከገጽ 312- 319 በአባሪነት ተያይዞ ይገኛል፡፡ ይህ ቃለ ጉባኤ መቼ እንደሚጠቅመን ግን አሁን መናገር ይቸግር ይመስላል፡፡

ፊታውራሪ አበበ ካቀረቡልን የሕይወታቸው ሒደት ውስጥ የትዳር አጋራቸውን እንዴት እንዳገኟቸው የገለጹበት ምዕራፍ ይገኛል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ትዳራቸው የእግዚአብሔር በረከት የተገለጸበት ስሙር እንደሆነ እምንገነዘብበትን ትሁት ገለጻ እናገኝበታለን፡፡

ፊታውራሪ አበበ በመቅድማቸው ውስጥ እንደጠቀሱት፣ በማዘጋጃ ቤት ሠራተኛነት፣ በኢንስፔከተርነት፣ በአውራጃ ገዢነት፣ በፋብሪካ ሥራ አስኪያጅነት በልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሠርተዋል፡፡ እነዚህኑም በተቻላቸው መጠን አቅርበውልናል፡፡ ከእሳቸው ልምድና ውጣ ውረድ ብዙ እንማራለን ብዬ አስባለሁ፡፡

በመጨረሻም የማነሣው እዚህ ላለነው ሰዎች ብዙም ሩቅ ያልሆነው የስምንት ዓመታት የደርግ እስር ቤት ቆይታቸው ነው፡፡ አገር ሲናድና ሲናጋ፣ ሥርዓት በወጉ ሳይለወጥ ሲቀር የሚደርስን ትርምስ፣ ሰቆቃ፣ ግድያ፣ እስርና እንግልት በወጉ ለመረዳት የሚያስችል ምዕራፍ በዚህ ግለ ታሪክ ውስጥ እናገኛለን፡፡ በእስር ቤት ስንት ዓይነት ሰዎች አብረው እንደታሰሩ፣ በአመለካከት፣ በሸውክ፣ በቆፍጣናነት፣ በርብትብትነት ሁሉ የሚመደቡ የገሀዱ ዓለም ሰዎች በጠባቧ እስር ቤትም ውስጥ ዓይነት በዓይነት እንደሚገኙ እንገነዘባለን፡፡ ከነዚያ ሁሉ ግን የደጃዝማች አሉላ በቀለ ሰብእና፣ እስርና እንግልት እንዲሁም ፍጻሜ እጅግ የሚያስደንቅ፣ እሚያባባና አንጀትም የሚበላ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

በዚህ በዝክረ ሕይወት ዘፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ መጽሐፍ ውስጥ የታዘብኳቸው ፍሬ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ፊታውራሪ አበበ ከፍተኛ የሆነ የማስታወስና የመመዝገብ ችሎታ እንዳላቸው መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ አንድን ነጠላ ሁነት ሲተርኩልን በቅርንጫፍነት ሌሎች አጋጣሚዎች ጣልቃ ይገቡባቸዋል፡፡ እነሱን ካስተናገዱ በኋላ ደግሞ ወደተነሡበት ጉዳይ ሲገቡ አንባቢን ሳያደናግሩ መሆኑንም አጢኜያለሁ፡፡

በልዩ ልዩ አጋጣሚ በወቀሳ መልክ የሚያነሡዋቸው ግለሰቦች ቢኖሩ እንኳን ተገቢውን አክብሮት ሳይነፍጉ ቅሬታቸውን በሥርዓት የሚያቀርቡ፣ ከበቀለኝነት ይልቅ በሥራ ራስን አጉልቶ በማሳየት ላይ የሚያተኩሩ፣ የሌሎችን ድክመት ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ሕጸጽ የማይደብቁ ሚዛናዊ አባት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ትዝብታቸው በራሳቸው፣ በአለቆቻቸው፣ በአጠቃላይ በኖሩበት ዘመን ላይ እንደመሆኑ መጠንም በሳቸው መስታወትነት እኛም ራሳችንን እንድንመለከትበት እድል ሰጥተውናል፡፡

ከአዘጋጁ፡-
አቶ ደረጀ ገብሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡


Videos From Around The World

 


 
Tigrai Telethon July 28, 2019
Armed with a slogan "Tigrai bi Tsifrina!" organizers were expecting to raise around 250 million but Tigrai Telethon has surpassed 600 million and still counting!!! The Diaspora Community is yet to be counted but the plan is in the works to raise more funds from North America in the coming months! Congratulations!!


 Mark Your Calendar


Atlanta for Tigrai 2019 Event

 


To All Northern California Tigreans!!

August 25, 2019

 Victoria Australia for Tigrai 2019 Event

 Ashenda Philadelphia 2019 Event

 Ashenda Dallas 2019 Event

 Ashenda San Diego 2019 Event

 Ashenda London 2019 Event(updated!)

 Ashenda Portland 2019 Event

 Ashenda Houston 2019 Event

 Sheraro Dev 2019 Event

 Seattle Ethiopian New Year Event

 


Follow US on Facebook

 Custom Search

 


Opinions and Views published on this site are those of the authors only! Aigaforum does not necessarily endorse them. 2002-2018 Aigaforum.com All rights reserved.