Back to Front Page

ግመል ሰርቆ አጎንብሦ

ግመል ሰርቆ አጎንብሦ

 

ከዐቢይ ኢካቦድ (09/05/21)

የማይደረገው ማድረግና ተቀባይነትና አግባብነት የሌለውን ማድረግ አቦው በቀላልና ሊገባ በሚችል መልኩ ግመል ሰርቆ አገንበሦ በሚል ይትበሃል ገልጸውታል። ግመልን ያክል ግዙፍ እንሳሳ ሰርቆ፤ ለማምለጥ አጎንብሦ መሄድ ጅልነት ወይም ገራገርነት ነው። በዚህ ርዕስ ዙሩያ ማስተላለፍ የተፈለገው መልእክት ከአሥር ወራት በፊት፤ ቀኝ እጃቸውን በግራ ደረታቸው ደቅተው በድል ተመለስ ብለው የትግራይን ምስኪን ህዝብ ይጨፈጭፍ ዘንድ መረቀውና ባርከው አረሜኔው የፌዴራል ሰራዊት ያላኩት የሃይማኖት ድርጅቶች፤ ከሰሞኑ በሃገሪቱ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሰላሙን ያደርግ ዘንድ ለአምስት ቀናት የፆምና ጸሎት ጊዜ ማዋጃቸው ተንተርሦ ነው።

በዚህ ርዕስ ዙሩያ ሊወሱ የሚችሉ በርካታ ንዑሳን ርዕሶች ሊኖሩ ቢችሉም፤ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉት የሚከተሉት ናቸው። ከእነዚህ ጥቂቶች፦

1)     የሃይማኖቱ ማሕበር አባላት እነ ማንን ያጠቃልላል?

2)    ማሕበሩ እንዴት፤ መቼና በማን ተቋቋመ?

3)    መሕበሩ ከተቋቋመ በኋላ ከማን ጋር ወግኖ ቆመ?

4)    የተለያየ ዶክትሪን ያላቸው ሃይማኖቶች በአንድ ማህበር የማደራጀቱ ፍይዳ ምንድ ነው? ይሄ አደረጃጀትስ በየትኛው ሃገር ተተግብሯል?

5)    በመፅሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር በማሕበር ተቀናጅቶ ፆምና ፀሎት ይዞ ወደ ተለያዩ አማልክት መቅረብ የተገባ ነውን?

የሃይማኖቶቹ ማሕበራት በዋናነት ሀ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰዊት ቤተ-ክርስቲያን፤ ለ)የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን፤ ሐ) የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖትና መ) የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተ ክርስቲያን አማኞች ናቸው። ሦስቱም በክርስትና እምነት ጥላ ስር የታቀፉ መሆናቸው ቢታወቅም፤ በመካከላቸው ለበርካታ መቶ ዓመታት ያወዛገቡ በርካታ አሰተምሕሮቶች እንዳሉ ሳይጠቅሱ ማለፍ የተገባ አይደለም። እኚህ መሰረታዊ የአስተምሕሮ ልዩነቶች በኢትዮጵያ ብቻ የሚከሰት ሳይሆን በዓለም ሁሉ ተንሰራፍቶና ጎልቶ የሚታይ ነው። የቤተ-እምነቶቹ ልዩነት የሚመነጨው ከሚከተሉት አስተምሕሮ ነው። አስተምሕሮን ፍቆና ደልዞ በማንኛውም ፖለቲካዊ ሆነ ሪዕዮተ-ዓለማዊ ምልከታ አንድ የማድረግ አባዜ ተቀባይነት የሌለው ነው። የክርስትና እምነት እምብረት ድርሻና ሃላፊነት አዳኙ ወንጌል ላልዳኑት ሁሉ በፍቅር ማወጅና ማድረስ ስለ ሆነ፤ ከክርስትና ወጭ የሆኑት ሌሎች እምነቶች በፍቅር አስተናግዶ ወንጌልን ይሰብካል እንጂ፤ ጥላቻንና ንቀትን ከቶ አይዘራም። እዚህ ላይ ክርስቲያኑ በወንጌሉ ያለ አንዳች ቅድመ- ሁኔታና ያለ ማመቻመች የሚተጋውና የሚሰብከው መዳን በክርስቶስ ብቻ እንጂ በሌላ ከቶ እንዳይደለ ነው።

Videos From Around The World

የእስልምና እምነት ወይም ሃይማኖት ድነት በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው የሚለው አስተምሕሮ የማይቀበል ሲሆን፤ የራሱ የሆኑ የተለያዩ አስተምሕሮቶች ያቀፈ ነው። በክርስትና ወደ አብና መንግሰተ ሰማይ መግቢያው በርና መሄጃው መንገድ ኢየሱስ እንደ ሆነ የሚታመን ሲሆን፤ በእስልምና ወደ አላህ ወይም ወደ ጀነት የመግቢያው መንገድ በቅዱስ ቁርኣን ተዘግቦ ይገኛል። እዚህ ላይ ጸሐፊው በእስልምናና በክርስትና ሰፊ የአስተምሕሮ ስንጥቅ (Rift) እንዳለ በጨረፍታ ለመጠቆም ያክል እንጂ አቋም ይዞ ይኼ ነው ትክክል ለማለት አይደለም። የፆምና የፀሎት አሰተምሕሮዎችም በተለያዩ ሃይማኖቶች የተለያዩ ስለ ሆኑ፤ አንድ ላይ መጸለይና መጾሙ ፋይዳ አይኖረውም።

የወንጌል አማኞች ዘንድም ከቀላል እስከ ከረሩ የአስተምህሮቶች ልዩነቶች የተዋቀሩ ሲሆኑ፤ ዐብይ አሕመድ ለፖለቲካ ፋይዳውና ፍጆታው እንዲጠቅመው፤ የወንጌላዊያን አማኞች ካውንስል በሚል ስም በመደፍጠጥ አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲፈጠር አድርጓል። በዚህ ካውንስል በሌሎች ወንጌላዊያዊያን አማኞች የሚወገዝውና የሚኮነነው የቃል እምነት አስተምህሮ ተከታዮች እንዲታቀፉ ተደርጓል ብቻ ሳይሆን የአመራር ስፍራ እንዲይዙ ተደርጓል። የቃል እምነት ተከታዮች በርካታ ከሕያው ቃሉ አስተምሕሮቶች ጋር የሚላተሙ ተምህርቶችና ልምምዶች ያልዋቸው ሲሆኑ፤ ክርሰቶስ በመስቀል ሰይጥነዋል፤ ክርሰቶስ ስለ እኛ በመሰቀል ድሃ ስለ ሆነና በመሰቀሉ ቁስል እኛ ተፈወስን ተብሎ በኢሳይያስ 53 ላይ ስለ ተጻፈ፤ ክርስቲያን እስከ አመነ ድረስ ሊታመም ሆነ ሊደኸይ አይችልም በማለት የሚያምኑ ናቸው። እንዲህ ዓይነት መሰረታዊ የሆነ ሰፊ የአስተምሕሮ ልዩነት እያለ፤ ለፖለቲካ ጥቅም ታስቦ አንድ ላይ በካውንስል አዋቅሮ መትከል ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ ፈጽሞ ተቀባይነት ስለ ሌለው፤ አብሮ መጸለይና መፆም ሆነ መምከርና የወንጌል ስርጭት ማካሄድ እንዲሁም ሕብረት ማድረግ የተገባ አይደለም።

የሃይማኖቶቹ ማሕበር የተቋቋመው ዐብይ አሕመድና ፓርቲው ብልጽግና ከተቋቋመ በኋላ በእርሱ አነሳሽነትና ግፊት እንዲሁም እርሱን ብግላቸው በሚያፈቅሩ ከተለያዩ እምነቶች በተወጣጡ ግለሰቦች ነው። ዓለማውም፤ የሃይማኖት ማህበረ ሰቡን በሰበብ አስባቡ በአንድ ጥላ ስር አሰቀምጦ የገዛ መንግስትህን ሃሳብ ለማስተግበር ነው። ይህ ተገቢነት የሌለው የሃይማኖት ስብስብ ዐቢይ አሕመድን በደመ-ነፍስ የሚደግፍና፤ ዘመነ መንግሰቱ እንዲቀጥል የሚያደርግ የመጠቀሚያ ዕቃ ነው። በመሆኑም የዐብይ መንግስት የፌዴራል ሰራዊቱ ሕግን ለማስከበር በሚል ሰበብ የትግራይ ህዝብ ለማጥቃት፤ ለመዝረፍ፤ ለመግደልና ጾታዊ ጥቃት ለመፈጸም ከመነሳቱ በፊት ሰራዊቱን ቀኝ እጁ በግራ ደረቱ በመድቃት ይቅናህ ብሎ መርቆና ባርኮ ልኮታል። ዳሩ ግን ለክርስትያኖቹ በወቅቱ በአዲስ ኪዳን ጦርነትን ደግፎ የሚደረግ ቡራኬና ምርቃት የሚጠቅስ አንድ ጥቅስ አቅርቡ ተብለው ሲጠየቁ፤ መልስ ሳይሰጡ በትግራይ ንፁሕ የእግዚአብሔር ህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለውና የማይረሳ፤ አሰቃቂ ግፍና ፍዳ ይደርሰው ዘንድ መርቀውና ባርከው ለመላክ ተገቢ ያልሆነ ድጋፋቸው ሳይመረምሩና ሳይፈትሹ፤ ሳይፀልዩና ሳይጾሙ፤ ከቃሉ ጋር ተፃርረው የግፈኛውና አረሜነው መንግስት ጋሻ ጃግሬ ሆነው ተሰልፏል።

በዚህ ሰሞን፤ በብልጽግና ፓርቲ የተቋቋመው የሃይማኖቶች ማሕበር ስለ ሃገሪቱ ሰለም ፆምና ጸሎት አውጆ ወደ ፈጣሪ ለመቅረብ አምሰቱ ያጳጉሜ ቀናት ተይዟል ብሎ መለፈፉን መስማት ግራ ያጋባል። ጦር እንዲመዝና ሳንጃ እንዲወድር ይቅናህ ተብሎ ተመርቆና ተባርኮ የተላከው ሰራዊት፤ ምን ፈጸመ? የተላከበትዓላመውንስ አሳካ ወይ? ተብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። እንደ እውነተኛ አማኝ፤ ጥፍትና እልቂት ከመፈጸሙ በፊት በእግዚአብሔር እግር ወድቆና፤ ጾምና ጸሎት ይዞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ መጠየቅና፤ ቅዱስ ቃሉ በአዲስ ኪዳን ጦርነትን እንደማይደግፍ መርምሮ ለመራሄ መንግሰቱ ጦርነቱ አያስፈልግም ብሎ መቃወም የነበረበት ያኔ ከመነሻው ነበር። ሰራዊቱ መርቀው ከላኩ በኋላና፤ ከመቶ ሺሕ በላይ ህጻናት ያለ ወላጅና ያለ ረዳት እንዲቀሩ ሲደረጉ፤ እናቶችና እህቶች ፕላስቲክ በማሕጸናቸው ውስጥ በመከተት ተሰምቶና ታይቶ የማይታወቅ ጀሮን ጭው የሚያደርግ ጾታዊ ጥቃት ሲድርስባቸው፤ የገበሬው እህል ተዘርፎ ሲበላና የተረፈው ህዝቡ እንዲጠፋ አሸዋ ላይ ሲበተን፤ የገበሬው ሞፈርና ቀንበር ተሰባብረው ሲቃጠሉ፤ በሬዎችና ላሞቹን በገበሬው ፊት ሻኛን ለመኮምኮም በግፍ ሲያርዱ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአደባባይ ሲረሽኑና ሲገድሉ፤ ወጣቶችን በጥይት ግንባራቸውን አፍርሰው ወደ ገደል ሲጥሉ፤ የትግራይ ህዝብ የመሰረተ ልማት መዋቅሮች ሆነ ብለው ሲያፈራረሱ፤ ከሹካና ከማንኪያ አንስቶ እስከ ከባባድ መኪኖች ወደ አማራ፤ አዲስ አበባና አስመራ በጠራራ ፀሐይ ተዘርፈው ሲወሰዱ፤ ኣበት በፊቱ የሚሳሳላትና በጉጉት የሚጠብቃት ቆንጆዋ ሴት ልጁ ሲያምፁበትና ሲደፍሯት፤ የእግዚአብሔር ህዝብ ከርስቱና ከጉልቱ እንዲፈናቀል የተለያዩ አስነዋሪ ተግባራትን ሲፈፅሙ፤ መንግሥት ሆን ብሎ ህዝቡ እንዲጠፋ የእርዳታ እህል እንዳይደርስ ሲያደርግ፤ ኤሌክትሪክ ፤ ውሃ፤ ስልክ፤ ኢንተርኔት፤ ነዳጅ፤ ባንክ እንዳይኖር ሲከለክል፤ ባርኮታቹሁና ምርቃታችሁ ትክክል እንዳልነበረ ተገንዝባችሁ ይሆንን? በመጀመሪያው ስለ ተሳሳታችሁ አሁን በጾምና በጸሎት ወደ አምላክ ስለ ሰላም መቅረብ ተገቢ አይደለም ማለት ትክክል አይደለም። ዳሩ ግን መርቃችሁ የላካችሁት ሰራዊትና የምትደግፉት መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው አረሜናዊ ሶቆቃ መዝናችሁ ስፍራችሁ፤ በዚህ ምስኪን ህዝብ ላይ የደረሰው በደል ተገቢ አይደለም፤ በጽድቅ በሚፈርድ በእግዚአብሔር ፊትም ተቀባይነት ፈጽሞ አይኖረውም ብላችሁ፤ አሁን በፆምና በፀሎት ለመቆየት ካወጃሁበት በፊት መጀመሪያው ድጋፋችህ ትክክል እንዳይደለ በንስሃ መቅረብና ለመንግስትም ጦርነት እንደማያስፈልግ ሳያመነቱ መናገር ይጠይቃል። ለመሆኑ ከመጸለያችሁና ከመጾማችሁ በፊት በትግራይ ምስኪን ህዝብ ላይ የደረሰው ዘግናኝ በደል ተሰምቶአችሁ ወደ አምላክና ወደ መንግስት የተሰማችሁን ከልብ በመጸጸት በማቅረብ ይሆን ወይስ፤ የጦርነቱ ወላፈን ወደ ደጃችሁ እንዳይደርስ ለመጸለይ ነው?

የእግዚአብሔር ቃል ማንኛውም ህዝብ የእግዚአብሔር ህዝብ እንደ ሆነ በመደጋገም ይገልፃል፤ ታድያ የትግራይ ህዝብ እንደ እግዚአብሔር ህዝብ በኢትዮጵያ፤ በኤርትራና በአማራ አሬሜናዊ ሰራዊቶች የተቀናጀ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ በደልና ግፍ በክርስቲያኑና በእስላሙ፤ በሽማግሎዎችና በሕጻናት፤ በወንዶችና በሴቶች፤ በገበሬውና በከተሜው ተፈጽሞበታል። እናማ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ስለ እነዚህ በእግዚአሔር ፊት ዘግናኝና ጸያፍ የሆኑት በርከታ ዘግናኝ በደሎች ያላችሁት ይኖር ይሆን ወይ? ይሄን ዘልላችሁና ችላ ብላችሁ ወደ አምላክ የምታቀርቡት ጸሎትና መስዋዕተስ ተቀባይነት ይኖረዋል ብላችሁ ታስባላችሁን? እዘህ ላይ እግዚአብሄር በጽድቅ የሚፈርድ፤ አባት ለሌላቸው አባት እንደ ሆነና፤ መበልቶችን የሚረዳ እንደ ሆነ በማገናዘብ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው በደል በፅድቁ እንደሚፈርድ፤ ወላጆቻቸው ላጡ ከመቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት እንደ ቀን አባት ግድ እንደሚለውና ባለቴት ሆነው ለቀሩት እህቶች እንደሚያግዝ ልብ ልትሉና የእርሱ የጽድቅ መለኮታዊ ባህሪ ተካፋዮች እንድትሆኑ እንደ ተጠራችሁ በጽናት ማሳሰቡና መጠቆሙ እጅግ አስፈላጊ ነው።

በማጠቃለያው በርካታ የወንጌል አማኞች የድሮዎቹና የአሁኖቹ በክርሰቶስ መስቀል ስለ ተገኘው የድነት ድል የተዘመሩትን፤ የዐብይ ሰራዊት ከሚቀዳጀው ድል ጋር በማሰተሳሰርና ከውሸት ትንቢታቸው ጋር በመሸመን በምስባካቸው ዳንኬራ እንደ ነኩበትና ጮቤ እንደ ረገጡበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የትግራይ ህዝብ ሰቀቀንና በደል ሰምተው በህዝቡ ስቃይ ደስ የተሰኙና ገለልተኛ ሆነው ዝም ያሉ ጥቂት አልነበሩም። በትንቢተ አብድዩ ይኼን አስመልክቶ እግዚአብሔር በነብዩ አፍ እንደሚከተለው ይናገራል፦

እንግዶች ሃብቱን ዘርፈው ሲሄዱ፤ ባዕዳንም በበሮቹ ሲገቡ፤ በኢየሩሳሌምም ዕጣ ሲጣጣሉ፤ በዚያ ቀን ገለልተኛ ሆነህ ተመለከትህ፤ አንተም ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆንህ። ክፉ ቀን በገጠመው ጊዜ፤ በወንድምህ ሥቃይ መደሰት አልነበረብህም፤ በጥፋታቸው ቀን የይሁዳ ሕዝብ ሲያዝኑ ሐሴት ማድርግ አልነበረብህም፤ በጭንቀታቸውም ቀን፤ በትዕቢት ልትናገር አይገባህም ነበር። በጥፋታቸው ቀን በህዝቤ በር መግባት አይገባህም ነበር፤ በጥፋታቸው ቀን፤ በጭንቀታቸው ቀን መደሰት አልነበረብህም፤ በጥፋታቸው ቀን ሃብታቸውን መዝረፍ አይገባህም ነበር። ስደተኞችን ለመግደል በመንታ መንገድ መጠባበቅ አይገባህም ነበር፤ በጭንቀታቸው የተረፉትን አሳልፈህ መስጠት አልነበረብህም። በአህዛብ ሁሉ ላይ፤ የእግዚአብሔር ቀን ደርሶአል፤ አንተም እንዳደረግኸው፤ በአንተም ላይ ይደረጋል (ትንቢተ አብድዩ 1፡11-16)

የእግዚአብሔር ህዝብ በሆነው የትግራይ ህዝብ ላይ መርቃችሁ በላካችኋዋቸው ሰራዊት ላይ ሲቃይ ሲደርስ አልተደሰታችሁም ወይ? በትግራይ ህዝብ ላይ ጥፋት ሲሆንስ በሐሴት በምስባካችሁ አላሸበሸባችሁምን? በትግራይ ህዝብ ላይ ጭንቀት ሲነግስስ በሕዝቡ ላይ አላላገጣችሁምን? በትዕቢትስ አልተናገራችሁምን? በሕዝቡ ጭንቀት ወራቶችስ ልባችሁ ደስ አልተሰኘምን? እናማ ይኼን ሁሉ ካደረጋችሁ በኋላ ጥፋቱና ጭንቀቱ ጉያችሁ ዘንድ ስለ ደረሰ ይሆን ወይ የምትፀሙትና የምትጸለዩት? በፆምና በፀሎት ታጅቦ ወደ እግዚአብሔር የምታቀርቡት ልመና ራሳችሁ ካልመረመራችሁና የደረሰው ጥፋትና ፍዳ ተቀብላችሁ በንስሃ ካልቀረባችሁ ፀሎታቹሁ ከቁመታችሁ በላይ ወጥቶ ዝፋኑ በሰማያት ወዳደረገው ታላቅ አምላክ ከፍ ብሎ እንደማይወጣ ማወቅ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር እንዳታዩ በዙሩያችሁ ከቦ ያለውን ጉም እንዲበትንላችሁና፤ በልባችሁ አንዣቦ ያለው የድንዛዜ ድባብ ያርቅላችሁ ዘንድ ተገቶ መጸለይ ያስፈልጋልና ምህረቱን ያውርድላችሁ!!!

 

 

Back to Front Page