Back to Front Page

እንቆቅልሽ ዘኢትዮጵያ:- ሰውየው የየትኛዋ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የሆኑት?

እንቆቅልሽ ዘኢትዮጵያ:- ሰውየው የየትኛዋ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የሆኑት?

ኻልኣዩ ኣብርሃ

10-05-21

ጥቁሯ ሰኞ ተብላ በስራ ጠሎች የምትረገመው ቀን አዲስ አበባ ላይ ግን የፀሃይ ብርሃን ያህል ደምቃ ውላለች። ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ በነገስታቱም ዘመናት ታይቶ የማይታወቀው እጅግ ያሸበረቀ በአለ ሲመት በኢትዮጵያውያን የፓለቲካ ባህል ውስጥ የተንሰራፋውን ግብዝነት የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው። "የንጉሱ አዲስ ልብስ" የሚል ርእስ በንጉሱ ዘመን በነበሩ ሪደር ሲሪስ ተብለው በሚታወቁ የመጀመሪያ ደረጃ ኢንግሊዝኛ ንባብ ማስተማሪያዎች ባንዱ የተተረከ ነው። ተረቱ እንዲህ ነው:- ሁለት አጭበርባሪዎች አንድ የመንግስት አስተዳደር ሃላፊነቱን ወደ ጎን ትቶ ልብስና ድግስ የሚወድ ንጉስ ዘንድ ይሄዳሉ። የልብስ ፍቅር ያሳወረውን ንጉስ አጭበርባሪዎቹ የማይታይ ልብስ እንሰፋልሃለን ሲሉት በአይን የሚታየው የልብስ አይነት ሁሉ የሰለቸው ንጉስ በሃሳቡ ይስማማል። ሰፊዎቹ ስራ ጀምረው እስኪጨርሱ ድረስ ባዶ እጃቸውን እያወናጨፉ የሚሰፉ መስለው ስፓርት ሲሰሩ ቆዩ። ንጉሱና ባለስልጣናቱ ስራውን ሲጎበኙ ምንም ነገር ባያዩም ያምራል በሚል ገምግመው ይመለሳሉ። ልብሱ ተጠናቆ፣ ንጉሱም ለብሶት አደባባይ ላይ ወጥቶ ህዝብ በሆታና እልልታ እያጀበው በኩራት ይራመዳል። በዚህ ፌስታ መሃል አንድ ልጅ እግር "ኸረ ንጉሱ ራቆቱን ነው!" ብሎ ጮኽ። በወሬ የደነዘዘው አድናቂ ሁሉ የልጁን አባባል ሰምቶ ቢደነግጥም ንጉሱ መራመዱን ህዝቡም ሆታውን ቀጠሉ።

አቶ ልደቱ አያሌው በሆነ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ ከአንደበተ ርቱእነታቸው የተነሳ በማታምንበት የሳቸው የአሃዳዊነት አቋም እንኳ ሳይቀር ሊያሳምኑህ ይደርሳሉ። አሃዳዊያን ይግደሉኝ ብየ ብመኝ እንኳ ማንም ሌላ ሳይሆን አቶ ልደቱ ቢሰይፉኝ እመርጣለሁ። በቅርቡ የኢትዮ360 ብሩክ ላቀረበላቸው አንድ ወሳኝ ጥያቄ የሰጡት መልስ ብሩክን ራሱ አስደንግጠውታል። ጥያቄው ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለማዳን ምን ቢደረግ ይሻላል የሚል ነበር። አቶ ልደቱ የሰጡት መልስ አስመስለውና ተመሳስለው ለማደር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ያስመሰከረ ነበር። በተረቱ ውስጥ ያለው ልጅ እግር ህዝበ አዳም ሲደነቅበት የነበረውን የንጉሱን "ልብስ" የሌለ መሆኑን እንደገለፀው ሁሉ በበአለ ሲመቱ ሺህ ጊዜ እየተነሳች የተወደሰችው ኢትዮጵያ እንደሌለች ሃቁን በድፍረት ያፈረጡት አቶ ልደቱ ናቸው። የአሃዳዊትና የፌደራላዊት ኢትዮጵያ ሁለት ባዴራዎች እያፈራረቁ የሚሰቅሉት፣ የሚያነጥፉት፣ የሚለብሱትና፣ የሚያውለበልቡት መሪዎችና እልፍ አእላፍ ደጋፊዎቻቸው ስለየትኛዋ ኢትዮጵያ እንደሚዘምሩ የተገነዘቡ አይመስልም። መቸም አንዷ አሃዳዊት ሌላዋ ፌደራላዊት የሆነች ተጣብቃ የተፈጠረችና አንድ ወጥ የሆነች መንታ ኢትዮጵያ የለችም። ልትኖር የምትችለው ኢትዮጵያ ከሁለቱ አንዱ ሆና ነው። ኢትዮጵያ ፈርሳለች አልፈረሰችም ለሚለው ግምገማ ድምዳሜው ፈርሳለች ነው። አቶ ልደቱ "ኢትዮጵያ ፈርሳለች ነገር ግን ለቃቅመን እንጠግናት እንደሆነ እንጂ" አሉ። ለኢትዮጵያ መፍረስ ዋና ምክንያት የሆነው "ከሃዲዎች፣ የውጭ ጣልቃ ገቦች" በፈጠሩት ችግር አይደለም። በማፍረስ የሚወነጀሉት የውስጥና የውጭ ሃይሎች ድርጊቶቻቸው ውጤቶች እንጂ ምክንያቶች አይደሉም። የአብሮነት ዋስትና የሆነውን የራስ አስተዳደር ሽረው በማእከሉ እንዲዘወሩ ለማድረግ ሲሞክሩና የብሄሮችን ህገመንግስታዊ ሉአላዊ ወሰን እንዳሻቸው ለመቀየር ሲያሴሩ፣

Videos From Around The World

ባለመብቶቹ ደግሞ አሻፈረን ሲሉ በኢትዮጵያ ስም የመወረር፣ የመዘረፍ፣ የመገደል፣ የመቃጠል፣ የመፈናቀል፣ የመደፈር፣ የመራብ፣ ለባእድ አሳልፎ የመሰጠት ግፍ ሲፈፀምባቸው ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግላቸውን አጧጧፉ። ይህ ወንጀል ነው? ይህ የአገር ክህደት ነው? ኢትዮጵያ ልጆቿን በግፍ እየበላች ነው ህልውና የሚኖራት? ዜጎቿስ ግፍ ሲደርስባቸው ምእንተ ኢትዮጵያ ብለው ዝም ማለት ነው የሚጠበቅባቸው? ከሃዲ እንዳይባሉ ማለቅ አለባቸው? የውጭ ጣልቃ ገቦች የተባሉትም ቢሆኑ ኢትዮጵያ በግትርነት በገዛ እጇ ራሷን ለማጥፋት ስትታገል አይተው ለዚች ታላቅ ኖራ እንደጤፍ ያነሰችው አገር ስላዘኑ ነው አደብ ግዙ ያሉት። የማይድን የውሻ በሽታ የያዘው ሰው ከሃኪሙ ጋር ግብግብ እንደሚገጥመው አይነት ሆነ እንጂ ምእራቡ አለም እንኳ ለራሱ ጥቅምም ብሎ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ አይፈልግም። በሞገደኛ ባህር አሳ የሚያጠምዱት ቻይናና ራሽያ አይናቸው የሚቃብዘው ወደ ኢንቨስትመንትና መሳሪያ ሽያጭ እንጂ ህዝብን እንኳን ሰው አውሬ ቢያስተዳድረው ስሜት አይሰጣቸውም። የራሳቸውን አስተዳደር ዴሞክራሲያዊ ሳያደርጉ ስለ ፍትህ በኢትዮጵያ ይጨነቃሉ ብላችሁ ነው?

አሃዳዊነት ፌደራላዊነትን መሸሸጊያ አድርጎ አገሪቱን በፓለቲካዊ፣ ወታደራዊና፣ ማህበራዊ ምስቅልቅል ውስጥ ከቷታል። የፌደላራዊ ስርአት ግንብ የሆነችውን ትግራይን አካሏን በጣጥሶ ህዝቧን በጥይትና በረሃብ ፈጅቶ ከካርታ ለመፋቅ በሚደረገው ትንፋሽ የማይሰጥ ርብርብ ከፍተኛ አመራር ከሰጡት የአሃዳዊነት ቁንጮዎች አንዱ የሆነው አገኘሁ ተሻገር ኮቱን ገልብጦ የፌደራሊስቶችን ቋንቋ እየተናገረና ከጳጳሱ ቄሱ ሆኖ የፌዴሬሽን ምክርቤት መሪ ሆኗል። እሾህን በእሾህ አውጣ እንደሚባለው፣ ወይንም ቀምቃሚዎች ሃንጎቨርን በቀጣይ ዙር መጠጥ ማዳን እያሉ እስከሞት ድረስ እንደሚጠጡት አይነት አሃዳዊነትን ለማስፈን ፌደራሊዝምን ለማጥፋት በፌደራሊዝም መሳሪያዎች መጠቀም የሚያስከትለው ጥፋት ቢኖር አሃዳዊነትም ሳይተገበር ፌደራሊዝም ይጠፋና አገሪቱ ትፈርሳለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መሪዎች እኮ አስደማሚ ናቸው። ፌደራል ህገመንግስት የፈጠረውን ክልል በፕሬዚደንትና ቢሮ ሃላፊነት እየመሩና ጥቅሟን እየተቋደሱ ክልሎች አገር በታኞች ናቸው ይሉናል። የራሳችን ብሄራዊ ክልል ይፈቀድልን እያሉ የሚታገሉት በርካታ የብሄር ዞኖች የብሄር ስሜት ተወግዶ አንዲት ኢትዮጵያ ትኑረን እያሉ የሚሰብኩ በቅራኔ የተሞሉ ናቸው። በችሎታ ሳይሆን በብሄር ኮታ የያዟትን ስልጣን እንዳቦ እየኮመኮሙ አዋቂና ብስል ፓለቲከኛ መስሎ ለመታየት ዳቦ የሚበሉባትን ገበታ ሲያራክሱ ይታያሉ። የለውጥ ሃይል እያለ ራሱን የሚጠራው ስብስብ ፌደራላዊ ስርአቱን ተጠቅሞ ፌደራላዊነትን ለማጥፋት ሲረባረብ ነው ኢትዮጵያ የምትቆምበት ደልዳላ መሬት በማጣቷ ወድቃ የተከሰከሰችው። ታድያ ለመፍረሷ ሃላፊነት መውሰድ ያለበት ህዝበ አዳም ፓለቲከኛና አጃቢው የራሱን ጥፋት ሌላው ላይ እያላከከ የሌለችውን ኢትዮጵያ ደርቦ ልክ እንደ ንጉሱና አድናቂዎቹ በማይታይ ልብስ ሆታውን ሲያደምቅ ዋለ ሰኞ እለት!

መሪዎቹና ህዝቡ ኢትዮጵያን ተነጋግረን ሳይሆን ተፋልመን እናድናታለን እያሉ የሚያቅራሩት በእጃቸው በሌለች ባልጨበጧት አገር ነው። አገር ህልውና አለው የሚባለው ምን ምንን ሲያሟላ ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ኢትዮጵያ ፈርሳለች፣ አልፈረሰችም፣ አትፈርስም ለሚሉት በየስሜቱ የሚነገሩ ድምዳሜዎችን በተጨባጭ ለመተንተን ይጠቅማል። አገር የሚባለው ፅንሰሃሳብ መሬት ለማለት ቢሆን ኖሮ ይህ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ያረፈችበት ስነምድር የምድራችን እድሜ ማለት 4.6 ቢልዮን አመት ያሳለፈ ነው። ስምጥ ሸለቆ ሆነ ዳሸን ተራራ፣ የኦጋዴን ሜዳዎች ሆኑ የደቡብ ኮረብታዎች ሲፈጠሩ እንኳንና ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሰው ልጅም ራሱ በምድር ላይ አልተከሰተም ነበር። አራት ተኩል ቢልዮን አመት የኖረች ኢትዮጵያ ካለች የሃይሌ ገብረስላሴዋ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ህዝብ የሌላት አገር መሆኗ አይደል? ለነገሩ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ እየተባለ አለቶች እንዴት እንደተፈጠሩ ይተረክ የለ! በኦጋዴንና በሶማሊላድ ውስጥ ያለው አለት የተለያየ ይመስል የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ጂኦሎጂ እየተባለ ለየብቻው ይጠናል። ሶስት ሺህ አመት የሚለው የነ ጠቅልለው የኢትዮጵያ እድሜ ቆጠራም የየራሱ ባለቤት ስላለው ወደ መቶ አመቱ እናተኩር። ይህም ቢሆን ስህተት ነው። ኢትዮጵያ ከአክሱም ስልጣኔ ጀመረች የሚለው አግላይ የሆነ እድሜ ቆጠራ መተው ግዴታ ነው፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያን የምስራቃዊና ደቡባዊ አጋማሿ በዚህ የፈጠራ ስእል ላይ የት ላይ እንደምንለጥፈው ግልፅ ስለማይሆን። ይህ ህዝብ የየራሱ አክሱም የነበረው ስለሆነ እኔ ነኝ አባትህና እናትህ እያሉ መመፃደቁ ወንዝ አያሻግርም፣ አብሮነትንም አያጠናክርም። መቶ አመት ሙሉ ኤሪትርያ በሄደችና በመጣች ቁጥር ኢትዮጵያ አንዴ ባለ ቀንድ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዱሽ ስትሆን ቆይታለች። ስለዚህ ኢትዮጵያ እያልን ስለ ቀይ ባህር ስለ ኑብያ ስለ ህንድ ውቅያኖስ ማውራቱን አቁመን፣ ኢትዮጵያ እያልን የቅቤ ጉድጓዷ አዲስ አበባ የሆነች አንዲት ገንፎ አድርገን ከማለም እንታቀብና ሃቁን በመቀበል ኢትዮጵያ ብለን ስለ ልማቷም ስለጥፋቷም መነጋገር ያለብን ይቺ 30 አመት በፊት በፌደራላዊ ህገ መንግስት በተፈጠረችውና 9+1ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ባሏት አገር ላይ ነው። አሁን አሁን በኢትዮጵያ ላይ የሰፈነው ኤሪትርያን ኢትዮጵያ ትግራይን ኤሪትርያ የማድረግ መላቅጡ የጠፋው ኢትዮጵያዊነትም በዚህ ትንተና ትርጉም አልባ ነው። አለም የሚያውቀው ኤሪትርያ ነፃ የሆነች የተባበሩት መንግስታት አባል እገር መሆኗን ነው እንጂ ኢትዮጵያ ገበያ ወጥታ ኤሪትርያን በትግራይ መሳ ለመሳ ቀይራ ወደቤት እንዳስገባቻትና ጦሯንና ደህንነት ጥበቃዋን እንዳስረከበቻት አገልጋይዋ አይደለም። ስለዚህ ኢትዮጵያ አለች የምንለው የህዝቧን መብትና ነፃነት ጠብቃ፣ አጥሯን ሳታፈርስ ጎረቤትን እንደ ጎረቤት አይታ የምትኖር ከሆነ ነው። የጥይቱ፣ የስደቱ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የጤና እጦቱ፣ የዴሞክራሲ የፍትህና አስተዳደር መጓደሉ ይቅርና በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ መንገድ ዘግታ በማስራብ እልቂት የምትደግስ አገር አለች ተብላ ድግስ ተደግሶ የሚምነሸነሹባት ናትን? ንጉሱ 80 አመታቸውን ሲያከብሩ ጆናታን የቀረፀውን አዳራሽ አከል ኬክ እንተወውና አዲስ አበባ ያኔ ብርቅ በነበረው ባለ ቀለም አምፑል ተሽሞንሙና ነበር። ይህ ሲሆን ግን ድርቅ ያስከተለው ረሃብ ወሎና ትግራይ ውስጥ ጥርሱን አግጦ ነበር። ሰውየው በኬካቸው ሲደነቁ አፈር የሚልሰውን ህዝብ አላዩትም አልሰሙትም ተባለ! ቢሰሙስ ኖሮ አረመኔ አልነበሩም እንዴ? በዚህ ቸልታቸው አመሃኝተው የገለበጧቸው የደርግ መኮንኖችም በራሳቸው ድግስ ዊስኪ ሲራጩ በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ በረሃብ አለቀ። ይህ ሲሆን የነበረው ደርግ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያላቸው ህወሓቶች የተራበ ህዝባቸውን ሱዳን ድረስ ወስደው ምግብ ለማብላት መከራ ሲያዩ የነበረበት አመት ነው። ወይ ሽብርተኛ መሆን! ህዝባዊ ሽብርተኛ አለ? አሁንስ ቢሆን የደርግ የአሁኑ ይባስ ወራሾች የትግራይን ህዝብ ለማስራብ መንገድ ሲዘጉ የእርዳታ መግቢያውን ለማስከፈት ሁሉ እናቱ የምትወደው ወጣት ለህዝብ ብሎ እየተሰዋ ነው። ወይ አይሲስ ስምህን እያጠፉት እኮ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ህዝባዊውን ታጋይ ሽብርተኛ እያሉ! በንጉሱና በደርግ የህዝብ እናት የሆነች አገር ነበረች ነው የሚባለው? ህዝቧ መከራ ሲበላ ስሜት የማይሰጣት አገር እንዴት ሆና ነው ህይወት አላት የምትባለው? በኢህአዴግ ዘመን በድርቅ ምክንያት ህዝብ በርሃብ አለቀ የሚል ወሬ የሰማ የኢትዮጵያ ይሁን የአለም ጀሮ አለ? ተቃዋሚህን አሰርክ ነው ወይስ ህዝብን በረሃብ ፈጀህ ነው የገዘፈው ወንጀል? የኢትዮጵያ አንደኛ ወንጀለኛ የተደረገችው ህወሓት ናት ግን ህዝብን እንደ ንጉሱ፣ እንደ ደርግ፣ እንደ ብልፅግና በረሃብ አልፈጀችም። ተቃዋሚ ማሰርን እንደሆነ ንጉሱም፣ ደርግም፣ ብልፅግናም በከፋ ሁኔታ ፈፅመውታል። ልጆቿን አንዱን ጠላት ሌላውን የስለት ልጅ የምታደርግ አድላዊ የሆነች አገር አለች ይባላል፣ በድን ሆናለች ያሰኛል እንጂ?

አለች እየተባለች የሚጮህላት፣ የሚዘመርላት፣ የሚሞትላት አገር የበለጠ የፈረሰችው ባእድ የጎረቤት አገር አስመጥታ የራሴ ነው እያለች አለምን የምታጭበረብርበት የትግራይን ህዝብ ያስፈጀች ጊዜ ነው። ይባስ ብሎ ኢትዮጵያ ትንፋሿ የቆመው መላ አለም እየጮኸና እያነባ በሚልዮን የሚቆጠረውን የትግራይ ህዝብ በረሃብ ለመፍጀት ነገር ማወሳሰቡን በመቀጠሏ ነው። ይህ ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለማዳን የሚወሰደው ህዝብን የማስራብ ዘመቻ ይቺ አገር ለአለም ክፉ የጭካኔ አስተማሪ መሆኗን ያሳያል። ይቺ አገር ናት አልፈረሰችም የምትባለው? በንጉሱና በደርግ ጊዜ ህዝብ በርሃብ ያለቀው የተፈጥሮ ድርቅን ለመቋቋም መንግስታቱ አቅም ስላልሰጡት ነው። ይህ ጭካኔ ደረጃ ሶስት ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም ምግብ የከለከለው የማይሰማው የማይለማው ድርቅ ነበርና። ስለዚህ ማሳበቢያ ነበረ፣ ቀና ባይሆንም። በብልፅግና ጊዜ በትግራይ ላይ የወደቀው የረሃብ አደጋ ግን ድርቅ የሆነው ተፈጥሮ ሳይሆን ብልፅግና ራሱ ነው። ኤል ኒኖ ያመጣው ድርቅ የሚባለው በሳይንስ ተምረነዋል፣ ብልፅግና ያመጣው ድርቅ ግን በሰይጣን ካሪኩለም ይኖር ይሆናል እንጂ  የማንም አገር ትምህርት ሚኒስቴር አያውቀውም። ለዚህም ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪኮርድስ መመዝገብ አለበት፣ ጭካኔ ደረጃ አንድ ተብሎ። የሚተካውም ይኖራል ብየ አላስብም። ትግራይ ብትጠፋ ኤሪትርያ ከኢትዮጵያ ጋር ትገጣጠማለች ብለው ከኢሳያስ እድሜ ባሻገር ያለውን ሁኔታ ያልዳሰሱ ህልመኞች አሉ። ኢሳያስ ሰው ነው፣ ማቱሳላም አልፏል። ትግራይ ግን ስለማትጠፋ፣ ኤሪትርያም በልጆቿ ነፃነቷን ጠብቃ ስለምትኖርና የትግራይን ልማት እንጂ ጥፋቷን ስለማትሻ ያኔ ኢትዮጵያ ከመሞት ብትተርፍም የእንግዴህ ልጅ ሆና ትኖራለች።  በትግራይ ላይ ሞልቶ የፈሰሰው ግፏ እንደ ባቢሎን፣ እንደ ነነዌ፣ እንደ ሰዶምና ገሞራ ከነ አባይ ጳጳሳቷና ፓስተሮቿ ትጠፋለች። "ዓለሙን ስለ ክፋታቸው ክፉዎቹንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኵራት አዋርዳለሁ።" ኢሳያስ 13(11)

Back to Front Page