Back to Front Page

የኢትዮጵያ ህዝብ መገንዘብ ያለበት ምንድነው? በዚህ ሰአት(ምንም የረፈደም ቢሆን እንኳ) ከህዝቡ ምን ይጠበቃል? ምንስ ይመከራል?

የኢትዮጵያ ህዝብ መገንዘብ ያለበት ምንድነው? በዚህ ሰአት(ምንም የረፈደም ቢሆን እንኳ) ከህዝቡ ምን ይጠበቃል? ምንስ ይመከራል?

 

(ዘ.ት  - ከትግራይ) 02-12-21

 

ለመሆኑ ባለፉት 100 ቀናት የሆነው ምንድነው?

(ል.በ:- ለማስታወስ ያህል እንጂ አታውቁትም ለማለት አይደለም)

 

1. እስከ 250 ሺህ የሚገመት የኤርትራ ሰራዊት(43 ክፍለጦሮች እንደሆኑ ተነግሯል) በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ፣ ከፍ ያለ ክፍያም ተከፍሎት አብዛኛውን የትግራይ መሬት ተቆጣጥሮ ይገኛል።

ይህ በቃላት ለመግለፅ የሚከብድ ጭካኔ የተላበሰ፣ በአብዛኛው ከኤርትራ ቆላዎች የመጣ ሰራዊት፣ ከሰብአዊነትና ከስልጣኔ በእጅጉ የራቀ Barbaric ሰራዊት፤

* በርካታ ንፁሐን በጅምላ ጨፈጨፈ- ለምሳሌ- ዕዳጋሓሙስ ማርያም ቤተክርስትያን ውስጥ የተጠለሉ ከ165 በላይ ሰዎችን፤ በአክሱም ማርያም ፅዮን ቤተክርስትያን ውስጥ ከ780 በላይ ህዝብ አረደ፤ በኢሮብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ አረደ ...በሄደበት መንደር ሁሉ ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ አረደ- በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ፤ ከአንድ ቤት እስከ 7 ሰዎችን ገደለ፤ ሌላው ቀርቶ የ3 አመት ዕድሜ ህፃን፣ የ90 አመት አዛውንትም ገድሏል፤

 

* በርካታ እናቶች፣ ወጣት ሴቶች እንደፈለገው ደፈረ፤ 10ና 15 እየሆነም ጭምር ደፈረ፤

 

** የትግራይ ገበሬ ንብረት የሆነ ሁሉ ከማንኪያና ሳፋ ጀምሮ እስከ ወርቅና መኪና- የህዝባችን ንብረት የሆነ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ወደ አስመራ አጋዘ፤ መውሰድ ያልቻለውን አቃጠለ፤ ከቤት የተገኘ እህል ሁሉ ወሰደ፣ አነስ ካለበት ደግሞ ከእበት ጋር ቀላቀለ፣ ደፋ፤

 

* እነ አልመዳ፣ አዲስ መድሐኒት ፋብሪካ፣ ሸባ ሌዘር፣ ኢዛና መአድን፣ ውቅሮ ኢንጅን ፋብሪካ፣ ሰማያታ እምነበረድ፣ ጎዳ ብርጭቆ ፋብሪካና ሌሎች የግልና የመንግስት ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ነቃቅሎ ወደ አስመራ ወሰደ፤ ህንፃዎቻቸው ደግሞ በድማሚትና በእሳት አጋየ፤

Videos From Around The World

 

** የነቃቀላቸው ፋብሪካዎች አስገድዶ እንዲሸከሙና እንዲጭኑ ያደረጋቸው ወጣቶችን ስራቸው ሲጨርሱ ገደለ፤ ለምሳሌ በግዳጅ የጎዳ የብርጭቆ ፋብሪካ ማሽነሪዎች ሲጭኑ የዋሉ ወደ 20 ገደማ ወጣቶችን በስተመጨረሻ ረሸነ፤

 

* የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሙጥጥ አድርጎ ዘረፈ፣ ህንፃዎቻቸው አጋየ፤

 

* ዩኒቨርሲቲዎች(ዓድግራት፣ አክሱም) ሙሉ ለሙሉ መሳርያዎቻቸው(ላብራቶሪዎች፣ የቢሮ እቃዎች፣ ፍራሾች፣ ኮምፒዩተሮች፣ መኪናዎች....ምንም የቀረ ነገር የለም) ፤ መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን አደረገ፤

 

* ማሳ ላይ ያለ እህል ሁሉ አቃጠለ፣ ከቤትም ምንም ምግብ እንዳይቀር አድርጎ ዘረፈ፤

 

* የመስኖ ግድቦች አፈረሰ፤ የመስኖ መተላለፊያ ቱቦዎች ሙሉ ለሙሉ ነቃቀለ፤

 

* ከየቢሮው እየገባ ሰነዶች አቃጠለ፣ እቃዎች ዘረፈ፣  ህንፃዎች በድማሚት አፈረሰ፤

 

2. የአማራ ክልል ሐይል:-

 

** ይህም ሐይል በተመሳሳይ ሁኔታ በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሐን በጅምላ ጨፈጨፈ፤ በጅምላ መቃብሮችም ቀበረ። በማይካድራ ጨምሮ በዳንሻ፣ በሑመራ፣ በወልቃይት፣ በአላማጣ፣ በመኾኒ ወ.ዘ.ተ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በጅምላ ተጨፈጨፉ፤ በተለይም በምዕራብ ትግራይ ሙሉ ለሙሉ Ethnic cleansing ተፈፅሞ ከጎጃምና ከጎንደር ከግማሽ ሚልዮን የሚልቁ ሰዎች በተገደሉና በተፈናቀሉ ተጋሩ ቤቶች፣ ሱቆች፣ እርሻዎች ገብተው በአንድ ጀምበር ባለቤትና ባለርስት ሆኑ፤

 

** በምዕራብ ትግራይ የነበረ ሰሊጥ ታጭዶ ወደ ጎንደር ተወሰደ፤  የነበረ ንብረት ሁሉ ፋኖዎች እንደፈለጉ ተከፋፈሉት፤

 

*በርካታ የትግራይ ህዝብ  ንብረት(መኪኖች፣ ማሽነሪዎች፣ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች) በጉልበት በግለሰቦች(ወረበሎች)ና በመንግስት ደረጃ ወደ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ወልዲያ ተጋዘ፤

 

** ትግራዋይን በጅምላ ገድሎና እንዲሰደድ አድርጎ ትግራይ መሬት፣ የትግራይ ርስት፣ የትግራይ እምብርት የሆነን መሬት ባንዲራውን ተከለ፤

 

3.  የኢትዮጵያ ሰራዊት- እንደ ሁለቱ የትግራይ ህዝብ በጠላትነት ፈርጀው እንዲጨፈጭፉ እንደመጡት ሐይሎች መንደሮችን አጋየ፣ ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ ጨፈጨፈ(በደብረአባይ የተፈፀመው በአንድ ቀን ከ100 በላይ ሰዎች በጅምላ የተጨፈጨፉበት ሁኔታ ማንሳት ይቻላል፤ በወጀራት አካባቢ የተደረገ 147 በጅምላ የተረሸኑበት ሁኔታም እንዲሁ)፤

 

 ሶስቱ ወራሪዎች በሄዱበት ሁሉ  ሰላማዊ ሰዎችን ይጨፈጭፋሉ ፤ ያለ ምክንያት ከተሞችን ያፈርሳሉ፣ ፋብሪካዎች ያጋያሉ፣ መንደሮች ያቃጥላሉ፣ ሴቶች ይደፍራሉ፣ ንብረት ይዘርፋሉ፣ ያወድማሉ ወ.ዘ.ተ። በዐድግራት፣ ሑመራ፣ ዕዳጋ ሐሙስ፣ ውቕሮ፣ ሽረ፣ ወርቃምባ ከተሞች የተፈፀሙ ጭፍጨፋዎችና ከተሞችን የማፈራረስና ትግራይን ወደ "የድንጋይ ዘመን የመመለስ" ተልእኮ ማሳያዎች ናቸው።

 

በዚህ ሁሉ ጭፍጨፋ ደግሞ የUAE ድሮኖችን ማንሳት ግድ ይላል፤ እነዚህ ሚሳኤል ተሸካሚ ድሮኖች እያንዳንዱ 70,000 ዶላር ዋጋ ያለው እስካሁን ባለው አሀዝ ከ1100 በላይ ሚሳኤሎች በትግራይ ምድር በማርከፍከፍ መንደሮች እንዳልነበሩ ሆነው ጠፍተዋል ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችና እንስሳት ተገድለው ስጋቸውና ደማቸው ተቀላቅሏል፤ የትግራይ መሬት በእሳት ተለብልቧል፤ በየመን፣ ሶማልያ፣ ሶርያና ሊብያ ባለፉ 10 አመታት የተተኮሱ የድሮን ሚሳኤሎች ቢደመሩ በትግራይ ምድር ላይ የዘነቡ ሚሳኤሎች በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ። UAE ትግራይ ለማጥፋት በሚደረግ ዘመቻ እጅግ  ተባባሪ ሆና የታየችበት ሁኔታ ነው የታየው(ሀይማኖትን ጨምሮ ሌላ ብዙ ምክንያቶች እንደነበሯት ኋላ ነው ግልፅ የሆነው)።

 

በዚሁ ጦርነት ከሞቃዲሾ የመጡ የሶማልያ(የፎርማጆ) ወታደሮችም ነበሩ፤ ደግነቱ ብዙዎቹ በራያ ግንባር በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው ያለቁት።

 

በጭፍጨፋዎቹ እስካሁን ከ50,000 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ተደፍረዋል፤ መንደሮች ነደዋል፤ የትግራይ የግል፣ የመንግስት፣ የባለሀብት ንብረት የሆነ ሁሉ ተዘርፎ ወደ አስመራ፣ ጎንደር፣ ወልዲያ፣ ኣዲስ ኣበባ ተግዟል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ የገበሬ ቤቶች ፈራርሰዋል፤ የትግራይ ቅርሶች ተዘርፈዋል፣ ነደዋል፤ ትምህርትቤቶችና የህክምና ተቋማት ወድመዋል፤ የቤት እንስሳት ተገድለዋል፤ የመስኖ ግድቦች ፈርሰዋል፤ የውሐ ቦዮች ወድመዋል...ምን ያልተሰራ ነገር አለ- ወራሪዎቹ እንደተመኙት(የአቶ ኢሳያስ ወታደሮችም በአንደበታቸው እንደነገሩን) ትግራይን ወደ "የድንጋይ ዘመን/Stone age" ለመመለስ ብዙ ተደርጓል።

 

በአጠቃላይ ሲታይ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ በአለም ሊፈፀም የሚችል ግፍ ተፈፅሟል(እየተፈፀመም ነው) ፤ ግልፅና የማያሻማ ዘር የማጥፋት ወንጀል ነው  እየተፈፀመ ያለው። መግደል የሚችሉትን ገደሉ፤ ማፈናቀል የቻሉትን ያህል አፈናቀሉ፤ ማሳ ላይ የነበረ ምርቱና ከቤቱ የገባ እህል ያቃጠሉበት ገበሬ እርዳታም እንዳያገኝና የሚቀመስ እንዳያገኝ ላለፉት ሁለት ወራት ያህል የተለያዩ እንቅፋቶች እየፈጠሩ የትግራይ ህዝብ በረሐብ እንዲያልቅ ሰሩ፤ የህክምና ተቋማት ሙሉ በማውደም ደግሞ በረሐብና በውሐ ጥም ላይ ያደረጉት ህዝባችን በተጨማሪም በበሽታ እንዲያልቅ ነው በእቅድ እየተሄደበት  ያለው። ጥይት፣ ረሐብ፣ በሽታ አንድ ላይ ሆነው ህዝባችንን እንዲጨርሱ በአላማና በእቅድ እንደተሰራ ምንም ጥርጥር የለውም።

 

እንግዲህ እዚህ ላይ ባለፉት 100 ቀናት ትግራይ ውስጥ ስለተሰራው የዘር ማጥፋት ወንጀል ብቻ ነው እየገለፅኩ ያለሁት፤ በሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎች በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ተጋሩ ላይ በማንነታቸው ምክንያት የተሰራው በደል- ያ ሁሉ እስራት፣ ግድያ፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት፣ ዝርፊያ፣ ከስራ ማባረር ወ.ዘ.ተ...እሱ ዛሬ እዚህ ላይ አልፅፈውም።

 

በአጠቃላይ በትግራይ ህዝብ  ላይ በጅምላ እየወረደ ያለው መከራና  ፍጅት "ጁንታ" የተባለውን፣ ከሁለት ወር በፊት ደግሞ "ሙሉ ለሙሉ መደምሰሱ" የተነገረንን ሐይል ጋር ከመዋጋት ፤ ህግን ከ"ማስከበር" ምንም የሚገናኝ ነገር የለውም። አሁን እየተሰራ ያለው ግልፅ የትግራይን ብሄር የማጥፋት፣ ትግራይን ከካርታ የማጥፋት ተግባር ነው።

 

ጠላትም ወዳጅም ማወቅ ያለበት እንኳን ከጠላት ጋር እየተናነቀና ጠላቶቹን ከቀን ወደቀን እያመነመነ፣ በውስጥም በውጪም የበለጠ እየተደራጀና አንድነቱ እያጠናከረ ባለበት በዚሁ ወቅት ይቅርና  እንዲሁ እጅና እግሩን አጣጥፎ ቢቀመጥ እንኳ 8-11 ሚልዮን ትግራዋይን ገለህ የምትጨርሰው አይደለም። የእስራኤሎችና የፍልስጤማውያን አይነቱ ቂም ለትውልድ መተው እንጂ ትግራይም ሆነ ትግራዋይነት  ጨርሶ ማጥፋት አይቻልም ብቻ ሳይሆን ዕብደት ነው። ሆኖም ግን ግፉ እየበዛ፣ ከቤት ስድስትና ሰባት ሰው መግደል የሚቀጥል ከሆነ በግሉ ለበቀል የሚነሳ ሰው እየበዛ ይሄድና ለሁሉም በጎ አይሆንም(መቸም 500 በበቀል ስሜት እራሳቸውን ለመሰዋት ቆርጠው የተነሱ ሰዎች በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ሐዘንና ፍርሐት እንዲገባ ማድረግ አይሳናቸውም፤ ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ወደዚያ በአስቸኳይ ካልቆመ አዝማሚያው ወደዚያ መሆኑ እውነት ነው)።

 

ትግራይ ግን ከመፈክርና ከአባባል በዘለለ ሁኔታ ጥፋቷን የሚመኙ ጠላቶቿን ሁሉ ድባቅ መትታ አሸንፋ ትወጣለች። እዚህ ላይ እያልኩ ያለሁት "ቂማችንን አናብዛ" ነው፣ "ተለያይቶ ለመኖር እንኳ የሚያስቸግር ቂም ለትውልዶች አንተው" ነው። ያለበለዚያ ልጆቻችን በማያባራ የመጠፋፋት አዙሪት እንከታቸዋለን።

 

እዚህ ላይ ግን ለኢትዮጵያውያን መልዕክት ማስተላለፍ እችላለሁ፤ ከላይም እንደገለፅኩት የትግራይን ብሄር ለማጥፋት ታልሞ ህፃንና ትልቅ፣ ሴትና ወንድ ሳይል በሚልዮኖች የሚቆጠር የትግራይ ህዝብ በጥይት፣ በረሐብ፣ በበሽታ እንዲሞት በእቅድ እየተሰራ ነው። በተለይም የኤርትራ መንግስትና የአማራ ክልል መንግስት በዚህ ረገድ ያላቸው ፍላጎትና እቅድ በአደባባይ ነግረውናል፤ መሬት ላይም ያንን ነው እያደረጉ ያሉት። በርካታ የአለም ማሕበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይን ህዝብ ላይ እያደረገ ያለውን ጭፍጨፋና እርዳታ እንዳይገባ በመከልከል አስርቦ ለመግደል እየሄደበት ያለውን አካሄድ በመቃወም ድምፅ ከማሰማት አልፈው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጡት እርዳታ እስከ መከልከልና ማዕቀብ እስከ መጣል የሚደርስ ጫና እያደረሱ ባለበት ሁኔታ የሚሰማ ድምፅ ያላቸው የኢትዮጵያ ልሂቃን(ምሁራን፣ የሐይማኖት መራዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች ወ.ዘ.ተ) የዚህን ህዝብ መከራና ጭፍጨፋ ባላየ ከማለፍ አልፈው በእልቂቱ ላይ ከመሳለቅና አቃለው ከማየት የዘለለ ይህ እልቂት እንዲቆም ተሳስተውና ተለሳልሰው እንኳ ትርጉም ያለው ድምፅ ማሰማት አለመቻላቸው በእውነቱ ለወደፊቱ ለልጆቻችንም የሚተርፍ አሉታዊ ውጤት የሚኖረው ነውና ቢያስቡበት እላለሁ።

 

ትግራይ እጅግ ባጠረ ጊዜ ሊያጠፏት የተነሱ ጠላቶች አጥፍታ አፈር ልሳም ቢሆን ትነሳለች፤ በየትኛውም የአለም ክፍል ያለ ትግራዋይ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ፍፁም አንድ ልብ ነው ያለው፤ ሁሉም ባለበት ሁሉ ደግሞ ለህልውናውና ለክብሩ ወታደር ነው፤ በማንኛውም ወቅትና ሁኔታ መክፈል ያለበት መስዋእት ለመክፈልም ዝግጁ ነው።

አሁን ትግሉ የህወሐትም የማንንም ሳይሆን የ8-11 ሚልዮን ትግራዋይ ነው። የህዝብ ትግል ሁሌም አሸናፊ ነው፤ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ሰፊ የማሸነፍ ልማድ ያለው ህዝብ ነው፤ በጠንካራ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ላይም ይገኛል፤ ስለሆነም ባጠረ ጊዜ አሸንፎ ስለመውጣቱ ጠላትም ወዳጅም ስጋት ሊገባው አይገባም።

 

ድል ለትግራይ ህዝብ!!

 

 


Back to Front Page