Back to Front Page

ይድረስ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሚንሰተር

ይድረስ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሚንሰተር

ከዐብይ ኢካቦድ

27-07-21

ይሄን መልእክት ለሃገሪቱ መከለከያ ሚንሰተር እንድጽፍ ያነሣሳኝ፤ የመከላከያ ሚንስትሩ ጽሕፈት-ቤት የትግራይ መንግሥት ባቀረባቸው ባለ ስምንት ቅድመ ሁኔታዊ የመደራደሪያ ነጥቦች ተንደርድሮ በተለይም በቁጥር አንድና አምሰት ላይ ተንተርሶ ባቀረበው ሐተታ ላይ አጸፋዊ መልስ ለመሰንዘር ነው።

ሲጀምር የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስተር በሕገ መንግሥቱ መሰረት የሚሰማራና የሚተጋ ቢሆን ኑሮ፤ ኢትዮጵያ አሁን ገብታበት ባለችው አዘቅት ውስጥ ባልተዘፈቀችም ነበር። ሠራዊቱ ለተቋቋመበት ዓለማ የሚገዛና የሚሰለፍ ቢሆን ኑሮ፤ ሃገሪቱ ለዚህ ውሉ ለጠፋበት ውስብስብ ችግር ባልተጋለጠች ነበር። ሠራዊቱ ለፖሊቲካ ፓርቲና ለግለ-ሰብ መጠቀሚያ ዕቃ ሆኗል ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ የሚገኘው በምድሪቱ የሚደረገውን በቅንነት በመዳሰስና በመቃኘት በቀላሉ ሊመለስ የሚችል ሲሆን፤ ከዚህ በተቃራኒ ሊወጡበት ከማይችሉት አዘቅት ውስጥ ከሰመጡ በኋላ ተቀባይነት የሌላቸው ሃቁን የሚጻረሩ የሃሰት ቃላትን በመደርደር ሊመለስ የሚቻል አይደለም።

Videos From Around The World

የኢትዮጵያ መከለከያ ሚንሰተር፤ ሰራዊቱ በዓለም አቀፍ ደረጃና በሃገር ውስጥ ያለው ብቃትና ችሎታ በማድነቅ ያተተ መሆኑ በጎ ቢሆንም፤ በነበር ጠጅ አይጠጣም እና በአምና የክረምት ውኅ ዘንድሮ አይታረስም እንዲሉ፤ የአሁኑ ሁኔታው ሠራዊቱ ድሮ በነበረው መልካም ቁመናና ግብር ቀባብቶና አሽሞንሙኖ መሳል ተቀባይነት አይኖረውም። ዛሬ ሠራዊቱ ለዓለም አቀፍ ለሰላም ተልዕኮ ዘብ ሆኖ መቆም ይቅርና፤ በገዛ ምድሩ አበሳና ሁከት እንዲሰለጥን የሚያደርግ የጥፋት መሣሪያ ነው። ሠራዊቱን የሚወነጀለውና የሚኮነነው አሁን ከተሰማራበትና ከሚፈጽመው ተንደርድሮ እንጂ፤ በጥልቻና በደመ-ነፍስ እንዲሁ ስሙን ለማጉደፍና ለማጠልሸት እንዳይደለ ሊሰመርበርት ይገባል።

ጦርነት ሁሉም ድንጋይ አንከባብሎ ከጨረሱ በኋላ የሚገባቡት የመጨረሻ ምርጫ ነው። የሃገሪቱ ሠራዊት የኢትዮጵያ መከለከያ ሰራዊት ተብሎ ተጠራ እንጂ፤ የኢትዮጵያ በዳይና አሰቃይ ሰራዊት ተብሎ ባይጠራም፤ በተግባር አሁን ያለበት አቋም ግን፤ የአንድ ሰው የስልጣን ዕድሜ ለማራዘም ይሄንን አንቀበልም ብለው በሚቃወሙት ፓርቲዎች፤ ዜጎችና ሕዝቦች ላይ፤ አፈ-ሙዝ በመደገንና ሳንጃን በመወደር ሕዝቡ ቁም ስቅሉን የሚያሳይ አስፈጻሚ አካል ነው።

ኢሕአዴግ ከፈረሰ በኋላ፤ ከየት መጣ ሳይባል በመደመር ፍልስፍና ድንገት ብቅ ያለው የዐብይ አሕመዱ ብልጽግና (ፒፒ) T P L F የጦዘ ጥላቻና ጥል እንደ ተመሰረተ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ዐብይ አሕመድ በገዛ ከንፈራቸው T P L F ጥሪያችን ተቀብለው ከብልጽጋና ጋር ቢቀላቀሉ ኖሮ፤ ወደዚህ ሁሉ ችግር አንገባም ነበር በማለት ተናግሯል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው፤ የዚህ ሁሉ መዘዝና ጣጣ ጠንቁ T P L F ከፒፒ ጋር አልቀላቀልም ማለት እንደ ነበር ለመረዳት አዳጋች አይደለም። የሠራዊቱ የአሁኑ አቋም ክሩን መዝዞ ቢጓዙ መነሻው ይሄው ነው። በመሆኑም የመከለከያ ሚንስተር በመግለጫው ድርድሩን ያቀረበው አካል ሳይጠቅስ በቁጥር አንድና አምሥት የቀረቡት የድርድር ነጥቦች እኔን ይመለካታሉ በማለት ያቀረበውና ተቀባይነት የላቸውም በማለት ያጣጣለው መግለጫ፤ ወኋ የማይቋጥር ነው።

ለመሆኑ የመከለከያ ሚንስትሩ፤ ከትግራይ ህዝብ ጋር ያደረና የቆየ ቁርሾ ካለው ከነፍስ በላውና ከኤርትራ ሠራዊት ጋር መክሮና ዘክሮ በትግራይ ህዝብ ላይ አረሜናዊ ግፍ ለስምንት ወራት ያክል ማካሄዱ የሚኮራበት ጀብዱ ነው ብሎ ያምናልን? ጦርነቱ ከመከፈቱ በፊት አማራና ትግራይ በድንበር ላይ የሚወዛገቡበት የደቡብና ምዕራብ በትግራይ የሚተዳደር ስፍራ እንደ ነበረ ይታወቃል። ይህ ችግር መፈታት የነበረበት በሕገ መንግሥቱ መሰረት በተለያዩ አግባቦች፤ ገፋ ብሎ ከሄደም በሪፈረንደም መሆን ሲገባው፤ የመከለያከያ ሠራዊቱን ታዝሎና ተንጥልጥሎ የአማራ ክልል በጉልበት ቦታውን እንዲያዝ አድርጓል፤ በሚልየን የሚቆጦሩ ተጋሩም ከቀያቸውና ከአባቶቻቸው ርስት ተባረዋል፤ ሰዎች ተጨፍጭፏል፤ ሴቶች እርኩስ የትግራይነታችሁ ደም እናጸዳዋለን ተብለው በሚዘገንን መልኩ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ አሁንም በምዕራብ ትግራይ ሰራዊቱ የአማራ ክልል ቀኝ እጅ በመሆን ግፉና ፍዳው በኅይል እንዲቀጥል አድርጓል፤ እናማ የመከለከያ ሚንስትሩ መግለጫ በእውን ሰራዊቱ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣንና ኅላፊነት እየተወጣሁኝ ነኝ ብሎ ያምን ይሆን ወይ?

ከኤርትራ ወራሪ ኅይል፤ ከአማራ ተስፋፊና ትምክሕተኛ ቡድን ጋር ተቀናጅቶ በትግራይ ሕዝብ ላይ ዓለም በሙሉ ያወገዘው መልከ ብዙ ነውረኛ ግፍ የሞላበት በደልስ የሃገሪቱ መከለካያ ሚንስተር የሚመካበት ሥራ ይሆንን? ከስድሳ ሺህ በላይ ግራና ቀኛቸው የማያውቁ ሚስኪን ሕጻናት ያለ ወላጅና ያለ ረዳት ማስቀረትስ የማን ሥራ ነው? ስለዚህ አሰቃቂ ፍጻሜስ መከለከያ ሚንስትሩ ምን ይል ይሆን? በትግራይ ሴቶች ላይ በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ጸያፍና ነውረኛ ፆታዊ አመጾችና ድፍርቶች፤ በሃገሪቱ መከለከያ ሰራዊት፤ አጋስስ በሆነ የኤርትራ ሰራዊትና፤ ነውረኛ የአማራ ተስፈኛ ሰራዊት ተራ በተራ በሚዘገንን መልኩ መፈጸም ይሆን የመከለከያ ሚንስትሩ ተግባርና ስልጣን? በሉ እንጂ ንገሩን ጃል! በህገ መንግሥቱ የተሰጣችሁ ስልጣን እነዚህንና የመሳሰሉት አሳዛኝ ድርጊቶች ለመፈጸም ይሆን? ዜጋስ እንዲህ ዓይነት አሳነዋሪና አሳፋሪ ድርጊት በሚፈጸም መከላከያ ሚንሰተር ጥላ ስር ዜጋ ነኝ ብሎ ተማምኖ ሊያድርና ሊኖር ይችላልን? የመከለከያ ሚንስተሩ አሁን ላይ ዝምና ጭጭ ማለት ሲገባው፤ ተገቢው ሥራ የፈጸመ ይመስል አፉን ለመክፈት መዳዳቱ ገራሚ ነው።

የትግራይ ገበሬ እንዳያርስ በሬዎቹ አርደው እየበሉ፤ እህሉን ዘርፈው በገዛ የጋማ ከብቶቹ ጭነው እየነዱ፤ ሞፈር፤ ቀንበርና ድግር ሰባብረው እያቃጠሉ፤ መሬቱን እንዳታርስ ብሎ እየከለከሉ፤ ይሄን መሣይ ኡኩይ ተግባር እየፈጸሙ መከለከያ ሚንስተር ነኝ ብሎ መጥራት ምን ማለት ነው? አታርስም፤ ብሎ መከልከልና በርሃብ እንዲሞት ማድረግ ይሆን የመከለካያ ሚንሰተር ተግባርና ስልጣን? በቀጭኑ የሃገሪቱ ርእስ መስተዳድር ትዕዛዝ፤ የትግራይ ሕዝብ መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ ማድረግና፤ ከቀላል እስከ ከባድ የህዝቡ ንብረቶች፤ ወደ ኤርትራ፤ አማራና አዲስ አበባ ጭኖ መውሰድ ይሆን የመከለከያው ሚንስተር ሥራና ስልጣን? ስንት መኪና ወደ አሥመራ እንዲዘረፍ ተደረገ? ወደ አማራስ ስንት መኪና ተወሰደ? ስንት በግ፤ ፍየልና ከብቶች ከትግራይ ምድር ወደ ጎንደር በሚኒስተሩ መስሪያ ቤት ፈቃድና ይሁንታ ተዘርፈው ተወሰዱ? ለዚህ እኩይ ሥራ ዋናው ተዋናይስ ማን ሊሆን ነው?

የመከለካያ ሚንስትሩ ጤናማ በነበረበት ጊዜ የሚንስተሩ ባልደረባ የነበሩ በርከታ ጀግና ተጋሩ መኮንኖች፤ ተጋሩ በመሆናቸው ብቻ ከየዕዙና ከየክፍለ ጦሮቹ አንጠልጥሎ በሚያስጨንቅ ስፋራ እንዲታሰሩ ማድረጉ ይሆን የመከለያከያ ሚንስትሩ ተገቢ ግዴታየን እየተወጣሁኝ ነው ብሎ የሚያንጎረግሮውና የሚያላዝነው? የክፉ ጊዜ የጦር ጓዶቻችሁንና በውጭም በሃገርም አንጓና የጀርባ አጥንት ሆነው ይዋጉ የነበሩትን ጀግኖቹን የትግራይ መኮንኖች የፍጥኝ አስሮ ማሰቃየት ይሆን የሚንስተሩ ተግባርና ሥራ? በደቡብ ሱዳን ለሰላም ጥበቃ የተሰማሩትን ተጋሩን፤ ወደ አገር ቤት እንዲመጡ በማድረግ አሰቃይቶ ለመቅጣት፤ በቡጡ መደብደብና በዱላ መቀጥቀጥ ነው፤ ሚንስትሩ የቆመበት የሥራ ድርሻ?

ደግሞስ በትግራይ ሜዶች፤ ሰረጓጉጦች፤ ሸንተረሮችና ተራሮች በትግራይ የመከላከያ ኅይሎች ድል የተመታውና በአሥር ሺዎች ሙትና ምርኮኛ የሆነው የሚንስትሩ ሠራዊት የኔ አይደሉም! ብሎ ሙልጭ አድርጎ መካድ ነው የሚኒስትሩ ባለ ሥልጣናት ሥራ? ወታደር ሊያሸነፍ፤ ሊሞት፤ ሊማረክ እንደሚችል የታወቀ ነው፤ የገዛ ሠራዊትህ አባል ተመርኮና ተሸንፎ እያየህ፤ የኔ አይደሉም ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ግን ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ፈጣጠ ውሸት ነው። የውሸቱ ርእሰ-ደብርና የቶውኔቱ ቁንጮ ባጫ ደበሌ፤ በመቐለ የታዩት በሺዎች የሚቆጠሩ ምርኮኞች፤ በማራቶን ሩጫ የተካፈሉት ሯጮች በፎቶ ሾፕ የቀረቡ ናቸው ብሎ ማቅረቡ በሠራዊቶቹ ላይ መከለከያ ሚኒስተሩ ማላገጡና ማንቋሸሹ ቁልጭ አድርጎ የሚያሣይ ነው። በጦርነት ይይደለ፤ ከውሸት ትርክት አምረች ጄነራሎች ከሞሉበት አካል ተንደርድሮ የመከለከያ ሚንስትር ማንነት ለማወቅ አዳጋች አይደለም።

በዚህ ወቅት በትግራይ መከለከያ ኅይል አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ ባለበትና ሰራዊቱ እስከነ ልዩ ኅይሎቼ ድባቅ በተመቱበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ተልካሻና ስንካላ መግለጫ ማውጣት ፍይዳው ምንድ ነው? በትግርኛ እንድሕር ሸለፋ፤ ታይ ተረፋ የሚባል ምሳሌ አለ። ባቷዋ ላይ ከደረሱ ምኑ ቀርቷታልና? ማለት ነው። አሁን እግዚአብሔር በትግራይ አድማስ ላይ አንዣቦ ለስምንት ወራት የቆየውን ጥቁር የሞት ደመና ገፍፎ የጽድቅ ብርሃኑ እንዲበራ አድርጎ፤ ነጻ አውጭዎቹ የትግራይ የመከለከያ ኅይሎች በመከለከያ ሚንስተሩ አፍንጫና ደጅ ስር በቆፍጣናነት ቆሟል። ግፍና ፍዳ፤ በደልና ጥቃት ወጊድ! የሚባለበት ጊዜ እነሆ ደርሷል። ከእንግዲህ በኋላ፤ ወላጆቹ አጥቶ የሚጮኽ ልጅ፤ በግፍ ተገዳ በተደጋጋሚ አመጻ የሚፈጸምባት እህት፤ ልጅና እናት አይኖሩም! ከቤቱና ከማጀቱ እየተደበደበና እየተገደለ፤ንብረቱና ዕቃ ቡሃቃው እንዲሁም ጥሪቱ የሚዘረፍበት ትግራዋይ አይኖርም። መሰረተ-ልማቱና ከባባድ ዕቃዎቹ ዓይኖቹ እያየ የሚነጠቅበት የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በኋላ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፤ የክፉ ድርጊቱ ዋና አስፈጻሚ የመከለከያ ሚንስትሩና እርሱ የጋበዛቸው አውሬው የኤርትራ ሠራዊትና ተስፋኛውና ተስፋፊው የአማራ ሰልፈኞች ከዚህ መራራ የጥፋትና ዘርን የማጥፋት ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተገቢ ዋጋቸው እየተከፈላቸው ነው።

ከዚህ ሁሉ ግፍና በደል በኋላ ትግራዋይ መከለከያ ሚንስትሩን፤ የጥቃትና የበደል ማዕከል ይለው እንደ ሆነ እንጂ የደህንነቴ ጠባቂና እንባየን የሚያብስልኝ መከታየና ጋሻየ ብሎ ለመጥራት አይችልም። የኢትዮጵያዊነት ፋይዳው ምን እንደ ሆነም፤ ከዚህ አኩይ ትእይንት ትግራዋይ በሚገባ ተረድቷል። ለርሱ በእግዚአብሔር ረዳትነት ካለ ልጆቹ ክንድ ጥንካሬና ብርታት አንዳችም እንዳላገዘውና ጭፍጨፋ አይሎበት የረዳት ያለህ ብሎ ላንቃው እስኪበጠስ የጮኸ ጊዜ ማንም ጭንቁን ስላልተጋራና ስልደረሰለት፤ ማን ምን እንደ ሆነ አሁን አሳምሮ ያውቃል። ሰላሙ በልጆቹ ክንድ ካስረገጠ በኋላ የሚጠብቁት አያሌ ሥራዎች ያሉት ከመሆኑ ባሻገር፤ የገዛ ራሱ ዕድል በራሱ ለመወሰን ማንም ሊንፈገውና ሊሰጠው የማይችለው ሬፈረንደም በማካሄድ ሁሉም ነገር ፈሩ ይይዛል። በመሆኑም ለትግራይ ሕዝብ የጥፋትና የኩነኔ ማዕከል የሆንከው የመከለከያ ሚንስትር ተብየ ተቋም፤ ሳትወድ በግድ ገዳዩና አፋኙ ጡንቻህን ቅልጥምህ ደቅቋልና በትግራይ ህዝብ ላይ ያቀረብከው መግለጫህ በሞት ጣርህ የሚታይ መፈረጋገጥ የሚያሳይ ከመሆን አይዘልም።

የትግራይ ሕጸናት፤ ያለ መድፍና መትረየስስ ጭኾትና ጋጋታ፤ ያለ አስደንጋጩና አዋኪው የተዋጊ የአይሮፕላኖች ድምጽ፤ በወለጆችህ እቅፍና ጉያ መኖር ጀምረሃልና ደስታችን ወደር የለውም፤ አየራበህም ቢሆን በገዛ ቀየህ እንደ ሰባ እንበሣ መቦረቅና መፈንደቅ ስለ ጀመርክ እንኳን ደስ ያለህ! ይህን እንድትቀዳጅ ያደረገህ የወገኖችህን ቁርጭምጭሚት እንዲበረታ ያደረገው እግዚአብሔር ነውና ዕልፍ ምስጋና ይገባዋል። አንዳች በደል ሳይኖርህ በዚህ ለጋ እድሜህ ለዚህ ሁሉ ስቃይ የዳረጉህ ዐብይ አሕመድና የክፉ መገልገያ ዕቃዎቹ የመከለከያ ሚንስቱሩና ግብረ አበሮቹ መሆናቸውን ለይተህ፤ ተመሳሳይ ፍዳና መዓት እንዳይፈጸምብህ በልብህ በቀይ ቀለም ጻፈው ዘግበውም።

የትግራይ እንስቶች፤ በገዛ ቤታችሁ የማንም ውርጋጥ ፆታዊ ጥቃት ስለባ ከመሆንና ወጥታችሁ፤ ሲነጋ በስጋት ከመባነንና፤ ሲመሽ ከፍርሃት ስለ ዳናችሁ እግዚአብሔር ይመስገን። የጨካኞቹ የመከለከያ ሚንሰተር ሰራዊት አሰገድዶ ተራ በተራ ፆታዊ ጥቃት ክንውን አሁን በልጆቻችሁ፤ በባሎቻችሁ፤ በወንድሞቻችሁና በእህቶቻችሁ በሆኑት በትግራይ መከለከያ ኅይል የጸና ክንድ ድባቅ ተምቶ እነሆ እፎይና እሰይ ብላችሁ መዋልና ማደር ጀምራችኋል። ከዚህ በኋላ ግን የማንም ጋጠወጥ ጭን በሚዘገንን አስገዳኝነት እንዳይጫንባችሁ፤ ላንዴና ለመጨረሻ እንደ ጉም ተብትነዋልና ፍርሃትና ስጋት ስፍራ የላቸውም። ዋናዎቹ ባላንጣዎቻችሁ ምን እንደፈጸሙባችሁ ግን ምን ጊዜም አትርሱት። በልባችሁ ማህደርም እስከ ወዲያኛው አኑሩት፤ ለቂምና ለበቀል ግን ስፍራ አይኑራችሁ፤ በቀል የእኔ ነውና በራሳችሁ አትበቀሉ ያለውን የአምላካችሁ ቃል አትዘንጉ!

ምስኪኑ የትግራይ ገበሬ፤ አንተ ከትግራዋይ ሰራተኛ በላይ ከሌላ ክልል የሚመጡትን ሠረተኞች የበለጠ የምታሰተናግድ መሆንህ እኔ ሕያው ምስክር ነኝ። ፈሪሃ እግዚአብሄር የሞላህ በደል ከተፈጸመብህ በሕገ አምላክ! በማለት የበዳይህን ሽሽት የምታሰቆምና፤ በዳዩም ይሄንን ሰምቶ ባለበት የሚቆም ሕግን በእግዜር ስም የምታከብር ሕዝብ ነህ። ዳሩ ግን የእጅህ አላገኘህም፤ ቤትህ አቃጠሉት፤ እህልህ በልተው የቀረውን በገዛ አህዮችህ ጭነው ወሰዱት፤ በሬዎችህና፤ በጎችህና ፍየሎችህ በማንአለኝንበት አርደው በፊትህ በሉት፤ ሞፈርህና ቀንበርህ እንዳታርስ ሰባብረው አመድ አደረጉት፤ ወርቅ ላበደረ አፈር ይመለስለታል እንዲሉ የበጎ ውለታህ ክፍያው እንዲሁ ሆኖ ማየቱ ልብን የሚያቀልጥ ነው። ይሁንና እነዚያ የጨለማ ቀኖች ዳግም ላይመለሱ እንሆ አልፈው ብርሃኑ ቦግ ብሎ እንዲወጣለህ የምትታመነው አምላክ አድርጎልሃልና እንኳን ለዚህ ፍጹም ብርሃን አበቃህ።

የከበርከው የትግራይ ገበሬ ሆይ! ለመሆኑ ስለ መከለከያ ሚንስትሩ የሚኖርህ ትውስታ ምን ይሆን? በእውን መከለከያ ሚንስትሩ ለአንተ ደህንነት ዘብ የቆመ ይሆን ወይስ አበሳህ እንድታይ በሲዖል እሳት ውሰጥ ነፍስህ እንድትለበለብ ለስምንት ወራት ገፍትሮ የጣለህ? ከፊት ለፊትህ ሬፈረንደም እንዳለ አትርሳ፤ በዚያ የምርጫ ካርድህ የደረሰብህን ፍዳ መጠን ወርድና ርዝመት እንዲሁም ጥልቀት ግለጽ፤ የዋህነትና ከንቱ የኅይማኖት ትርክቶች እግር ከወርች ቀፍድደውህ በሲዖል እየተሰቃየህ እንዳትኖር ተጠንቀቅ! ነገሮችን በጽሞና ማየት እንድትችል እያሳሰብኩ፤ ለወደፊቱ ለሚደርጉት ወሳኝ እርምጃዎች በጥንቃቄ፤ በእውቀትና በጥበብ እንዲፈጸሙ ወገናዊ ምክሬን እሰነዝራለሁ።

 

Back to Front Page