Back to Front Page

በግል ክፍለ-ኢኮኖሚው የተደረገ የቆረጣ ጦርነት

 

በግል ክፍለ-ኢኮኖሚው የተደረገ የቆረጣ ጦርነት

ሙሉቀን ወልደጊዮርጊስ

12/31/2021

ጥቅምት 24/2013 በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ልዩ የሚባል ስፍራ አላት፡፡ በዚች እለት ጥዋት በርካታ ሰው ከእንቅልፉ ሲነሳ ራሱን ያገኘው አንዳች ነገር ይጠብቅ እንደነበረ በሚያሳብቅ መልኩ “ጦርነቱ ተጀመረ” በሚል ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ላይ ነበር፡፡ እኔም ከባህር ማዶ ተደውሎ “በቃ ጦርነቱ እኮ ተጀመረ” የሚል የአንድ ወዳጄ ጥሪ ነበር ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ሀገራችን ዳግም ወደ ጦርነት ለዛውም የከፋ ጦርነት ውስጥ ትገባለች የሚል ሰው ቢኖር ምናልባትም ጤንነቱ መጠራጠር ቢኖርበት አይከፋም ከሚሉ በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩኝ፡፡ አሳዛኝ እጣ ነበር፡፡ እለትዋም ደርሳ የትግራይ ህዝብን ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ህይወቱን የማመሳቀል ጥቁር ጉዞዋን ሀ ብላ ጀምራለች፡፡ እዚህ ላይ “ጦርነቱ ተጀመረ” ከሚለው የመረጃ ቅብብሎሽ ጋር አብራ ተሰናስላ የቀረበች ትርክት ነበረች “የመከላከያ ክፍላችን አካል የሆነውን የሰሜን እዝ በከሃዲውና በናት ጡት ነካሾች ከኋላው ተወጋ” የምትል ትርክት፡፡ ይህች ትርክት ደረጃ በደረጃ እየዳበረች ወደ ማገባደጃ ላይም የ‘እናቶች ያለቅሳሉ ንግግር ተከትላ የመጣች መሆንዋን ልብ ብሎ ማጤን ምናልባትም ለምን እንዲህ የመሰለ ሁሉን አቀፍ ጭካኔ በትግራይ ህዝብ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የባህል፤ የስነምህዳር ወዘተ) ሊፈፀም እንደተፈለገ ከስር መሰረቱ ለመረዳት ያስችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው ግን ይህች በማር የተለወሰች፤ የተጠናች፤ ጊዜዋ እስኪደርስም እንደስስት ልጅ ስትሽሞነሞን የቆየች ትርክት በአለቃዋ እስትንፋስ አግኝታ ገበያ ከወጣች ወዲህ የዋሁ በልበ እውርነት፤ ትእቢተኛውም በማን አለብኝነት እና ግብዝነት የጦርነቱ አልፋና ኦሜጋ ተደርጋ እሷኑ እንደበቀቀን ሲደጋገም ማድመጥ የሰው ልጅ ነገርን ከስሩ ለማጥራት የተሰጠው አእምሮ በፈቃደኝነት የጣለ፤ ወኔውም አርቆ የቀበረ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡  

ትርክት (Narrative) አንድ የተግባቦት ስልት ነው፡፡ በጽሁፍም ሆነ በቃል በመጠቀም አንድን መረጃ ለሌሎች ሰዎች የሚተላለፍበት መንገድ ሲሆን ታላቅ የማሳመን ሀይል እንዳለው በታሪክ ውስጥ በተለያዩ ቦታና ጊዜያት ትርክቶችን ተከትለው የተከናወኑ አያሌ ድርጊቶች ያስገነዝቡናል፡፡ ትርክት እውነትና ውሸት ያዘሉ መረጃዎች በውስጡ የያዘ በመሆኑ በተለይም በውሸት ላይ የተመሰረተ ትርክት የአድማጩን ቀልብ በመግዛት፤ አእምሮ በመስለብ፤ በወዶ እስረኝነት፤ በሱስ በማንበርከክ “አድርግ” የተባለውን ያለማመንታት በማድረግ አያሌ ጉዳትን ማድረስ የሚችል ከመሆኑም በላይ መልሶ በእውነት ለመጠገን መንገዱ ውስብስብና አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ ትርክቶች የተፈጠሩበት አላማ አሳክተው ወዲያው የሚደበዝዙ ሆነው አንዳንዶቹ ትርክቶች ደግሞ በራሳቸው ሳይቆሙ የሌላ ትርክት ማሳረጊያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ዘመናት “ከሰው ዘር ሁሉ ምርጦቹ እኛ ነን” የሚለውን የሂትለር ትርክት በጀርመኖች አእምሮ ውስጥ አድሮ በሚልዮኖች ለሚቆጠሩ አይሁዳውያን እልቂትና ስደት ምክንያት ሆኖ አልፏል፡፡ በ16ኛው ክፍለዘመን በሰዎች መካከል ተፈጥሮአዊ ልዩነት እንዳለ ለማሳመን እንደነ ፈላስፋው ጆን ሎክ፤ ሳይንቲስቱ አይዛክ ኒውቶን የመሳሳሉት “የቀለማት ሁሉ የበላይ ነጭ ነው፤ የዘሮች ሁሉ የበላይ ነጭ ነው” በሚል የሃሳብ ቀመራቸው የጥቁርን ሰዋዊነት ወደ እንስሳዊነት አውርደው በማስቀመጥ ሲሰብኩ ያው ትርክታቸው አሁንም መቋጫ ሳይበጅለት አለምን በጥቁርና በነጭ ተወሳስባ ሰውን በትምህርት፤ በጤና፤ በስራ መስክ አበላልጣ ፍዳ እያሳየች ትገኛለች፡፡ በዘመናት ርቀትም እኛው አገር የተከስቱት ጉዶች ራሳቸውን በዶለደመ የልሂቅነት ማማ ኮፍሰው የኢትዮጵያን መልካም አሳቢና ተቆርቃሪ የሚመስሉ ሃሳዌ መሳህያን መዳረሻቸው “አንዱ የበላይ ሌላኛው የበታች” የሆነውን ድብቅ አጀንዳቸው በሃገሪቱ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ውስጥ ውስጡን ሲያሴሩ ቆይተው አራት አመት ሊሆነው ጥቂት ወራት በቀረው የጨለማ አመታት ደግሞ በግላጭ ወጥተው አለም በጭካኔው አቻ የለውም የተባለውን ጦርነት በመጫርና ነዳጅ በማርከፍከፍ ሀገሪቱን ከባድ ቀውስ ውስጥ ከተዋታል፡፡  በ21ኛው ክፍለዘመን አንድን ህዝብ በ“ጭራቅነት” መሳል ወይም ከ“ካንሰር” በሽታ ጋር ማመሳሰል በ16ኛው ክፍለዘመን ጥቁሮች “እንስሳ” እና “መትህተኞች” ናቸው ከሚለው ሚሽነሪው ኮተን ማተር አስተሳሰብ ጋር ከዘመናት ርቀት በስተቀር ምን ሊለየው ይችላል? ለኔ “ነጭ ይበልጣል” የሚለው አስተሳሰብ “አንዱ የበላይ ሌላው የበታች” ከሚለው የኛው ጉዶች አስተሳሰብ ጋር በአስተሳሰብ ደረጃ ብዙም ልዩነት የላቸውም እላለሁ፡፡ ልዩነቱ ግን በነጆን ሎክ፤ ኮተን ማተር ሃሳብ ተማርከው በዛው ዘመን የተፈጠሩ እርኩሶች ባቆሙት ስርአት ጥቁሮች አያሌ ዘመነ ፍዳ ያሳለፉ ሲሆን የኛዎቹ ዶልዳሞች ሃሳብ ከስምንት እስከ አስር ሚልዮን የሚጠጋ አንድን ህዝብ “ለታሪክ እንዳይገኝ፤ ከምድረገጽ ማጠፋት” ጋር ሲነፃፀር በኛ አገር የተፈጠሩት እጅግ ወደር የሌላቸው የክፍለዘመኑ ጨካኞች ያደርጋቸዋል፡፡

Videos From Around The World

ከላይ በአንጽሮት የተመለከትናቸው ልሂቃን በአውሮፓም ሆነ በአፍሪቃ ወይም በየትኛው የአለም ክፍል ይፈጠሩ ሁሉም በዚያው በኖሩበት ዘመን ለሰው ልጅ ራስ ምታት የሚሆንን ሃሳብ በማመንጨትና በማሰራጨት፤ በውጤትም ትርምስና ሁከት እንዲነግስ፤ ህዝብም በፍርሃት እንዲኖር ሆኗል፡፡ በእነኚህ መልካም አሳቢ መስለው በሚቀርቡ ሰዎች የተረጨው መርዛማ ሃሳብ ሰንኮፉን ነቅሎ ለመጣል አለመቻል በትውልድ መካከል አለመተማመን በመፍጠር ማለቂያ ለሌለው የሰው ልጅ መበላላት እንደሚያስከትል ግብዞቹ ለደቂቃም ቢሆን ቢያጤኑት ኖሮ የሚረጩት ሃሳብ ምን ያህል ክብደት እንዳለው በተገነዘቡ ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን ማገናዘቢያ አእምሮ ስላልፈጠረባቸው በሰው ቁስልና ችግር እየተደሰቱ እልቂትና ሰቆቃውን እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ አብሮአቸው ይዘልቃል፣ ያለፀፀትና ሃፍሬት ደጋግመው ይሰብኩታል (የኦሮሞና የትግራይ ህዝብ ከሌላው ወገኖቹ ጋር ያስመዘገበው ቀደምት ስልጣኔ፤ ለነጻነት፤ ለእኩልነትና ለፍትህ ያደረገውን ትግል ማንቋሸሽ፣ በቅርቡም የወላይታ ህዝብ ታሪክ ማጣጣል ልብ ይሉታል)፡፡

እንግዲህ በሃገራችን በዚህ “ዘመን” እና በዚህ “መሪ ሃሳብ የተቃኘ” ሃሳብ ሾርት ሜሞሪ ተብሎ የተጠራው ህዝብ በሚያመላልስ ጎዳና ላይ አንዴ ከወጣና መራመድ ከጀመረ (ጂኒው ከጠርሙሱ ከወጣ) ወገኖቼ ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መገመት ነቢይ መሆን አይጠይቅም፡፡ በየመንገዱ ተጽፎ የሚነበበው ታፔላ በሙሉ “መንገዱ ሁሉ ወደ እውነት ያመራሉ” የሚለውን በግልባጩ “መንገዶች ሁሉ በጥፋት ጎዳና ይከንፋሉ” የሚለውን ማንበብ ይሆናል፡፡ የማይነካካው ነገር የለም! ፖለቲካው፤ ኢኮኖሚው፤ ባህሉ፤ ስነምህዳሩ ወዘተ. ሁሉንም እየደረሰ ያጠፋቸዋል፣ ያወድማቸዋል! ያው “እናቶች ያለቅሳሉ፣ መሰረተልማት ይወድማል፣ ወጣቶች ይሞታሉ” ተብሎም የለ!፡፡ በጦርነቱ ወቅት በተጋባዡ የኤርትራ ጦር የተዘረፈ መጠነ ሰፊ የግለሰቦች ሃብት፤ የህዝብ ንብረት (ፋብሪካዎችና ባንኮችን ጨምሮ) ወደፊት በዝርዝር ለሚያጠኑት የታሪክ ተመራማሪዎች ለጊዜው እናቆይላቸውና እስቲ በኢኮኖሚው በተለይም የግል ዘርፉን ውስጥ ምን ሲደረግ እንደነበረ እንመልከት!

ባለፉት ሰላሳ የኢህአደግ የሀገረ መንግስት ግንባታ አመታት ከተከናወኑት ተግባራት አንዱ አገራዊ የግል ባለሃብት እንዲያንሰራራ ጥረት ማድረግ ነበር፡፡ ይህ መልካም የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፡፡ ለምሳሌም በዚሁ የ“መቀራረብ” ፖሊሲ ተጠቃሚ በመሆን ሃብት ካከማቹት መካከል ጥቂት ወፋፍራም ባለሃብቶችን ብንዘረዝር የሚከተሉት እናገኛለን፡፡ እነ በላይነህ ክንዴ፤ ወርቁ አይተነው፤ ወ/ሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ፤ የስታር ቢዝነስ ኮብራዎቹ እነ ምንውየለት፣ ታደለ እና አበባው ከብአዴን ጋር ምላስና ከንፈር ሆነው ከብረዋል፡፡ እነ አለማየሁ ከተማ፤ ድንቁ ደያስ፤ ገምሹ በየነ እና ፈለቀ (የግርማ ብሩ ሸሪክ) ከኦህዴድ ጋር ጥፍርና ጣት ሆነው በቱጃሮቹ መዝገብ ስማቸው አኑረዋል፤ ከደህዴን ጋር አይንና ቅንድብ ሆነው እነ ሃብታሙ ሲላ፤ ተሾመ፤ መኩሪያ እና አሰፋ (የሽፈራው ሽጉጤ የንግድ ወዳጅ) በሃብት ማማ ላይ ተቆናጥጠዋል፡፡ በህወሀት መጎናጸፊያ ውስጥ ተወሽቀው በከፍተኛ ሃብት ማማ ላይ ደርሰው አለማቸውን ሲቀጩ የነበሩ ግለሰቦችም እንደዚሁ በርካታ ናቸው፡፡ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል የሚገኙ ቱጃሮችም ከፀበሉ ተቋዳሽ የነበሩ በስም መጥቀስ እንደሚቻል መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ፓሊሲው ከመነሻው የተሳከረ የሚያደርገው የፓርቲ ወገንተኝነት እንደመስፈርት አድርጎ የተነሳና የሚፈልጉትን ሰው ብቻ እየመረጡ በብርሃን ፍጥነት ወደሃብት ማማ ማድረስ፣ የተቀረው ማህበረሰብ ደግሞ በሩ ተዘግቶበት ወይም በልኩ በተሰፋ ኪስ ብቻ እንዲዘል ሲደረግ እንደነበር፤ በስተመጨራሻውም ቢሆን አሰራሩ ኢ-ፍትሃዊ እንደነበር ራሳቸው ያመኑበት ጉዳይ ነው (የታህሳስ 2010 ሰብሰባ ማጠቃለያ ላይ ያቀረቡትን ሪፖርት ልብ ይሏል)፡፡ ይህ ሁላ ቱጃር ያፈራ ግንባርና ሀገር የግንባሩ መስመር ወደ ፓርቲው መስመር ከተቀየረ በኋላም “የመቀራረብ” ፖሊሲውን ወደፊት ሁለት እርምጃ በማስከንዳት በሃብት ማማ ላይ ይበልጥ እንዲቆናጠጡ አደረገ፤ ገሚሱም የጦር ጀግና ማእርግ ካባ እየደረበ እንዲንጎማለሉ ፈቀደ፡፡ ይህ ፖሊሲ በህወሀት የተፈጠሩት የትግራይ ባለሃብቶች ላይ ሲደርስ ግን እጅ አጠረበት፡፡ እንዳውም እየተለቀሙ ለእስር፤ ለስደት ድርጅቶቻቸውም እንዲወረስ ወይም እንዲዘጋ በቅንጅት፤ በተናበበና በትጋት ተሰራ፡፡ ለምን ይህ ተደረገ የሚለውን ለማወቅ ብዙ ርቀት መሄድ አይጠበቅብንም፡፡ ያው ከላይ የጠቃቀስኳቸው ሀገሪቱ ካበቀለቻቸው አረሞች መካከል ራሳቸውን በዶለደመ የልሂቅነት ማማ ኮፍሰው የሚያስተጋቡት የትልቁ (ግራንድ) አጀንዳቸው “አንዱ የበላይ ሌላኛው የበታች” አካል የሆነው በኢኮኖሚው መስክ የሚያደርጉት ጦርነት አንደኛው ማስፈጸሚያ ስትራቴጂያቸው ነው ከማለት ውጭ ሌላ ማስረጃ ሊቀርብበት አይቻልም፡፡ በነገራችን ላይ መረጃዎቹ የሚያመላክቱት የኢኮኖሚው ጦርነት ከጥቅምት 24ቱ ወታደራዊ ጦርነት በፊት የተጀመረ መሆኑን ነው፡፡ ጦርነቱ በኢኮኖሚው እያሳደረ ስላለው ተጽእኖ ባለፈው ወር ዛዲግ አብርሃ ያደረገውን ማለፊያ ትንታኔ አዳምጫዋለሁ፡፡ ዛዲግ የትንታኔው ማእዘን አድርጎ የተጠቀመበት “አንዱ የበላይ ሌላኛው የበታች” ንኡስ ክፍል የሆነውን “የሰሜን ጦር ከኃላው ተወጋ” የሚለው ትርክት በመሆኑ ቀደም ብሎ በትግራይ ተወላጅ ባለሃብቶች ላይ ሲደረግ የነበረ ቀጥታዊ ጭፍጨፋ ሊመለከት አላስቻለውም ወይም ግድ አይሰጠውም ስለሆነም እውነታው ገልብጦና አንሸዋርሮ ለታዳሚዎቹ አቀረበ፤ ተጨበጨበለት፡፡

ያም ሆነ ይህ ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆንዋን በይፋ በተነገረበት ባሉት ጥቂት ወራት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ ቢመስልም በአዲስ አበባ ከተማና ከትግራይ ውጭ ባሉት በቀሪው የሃገሪቱ ክፍሎች በሆቴልና ቱሪዝም፤ በማንፋክቹሪንግ፤ በእርሻ፤ በኮንስትራክሽን ወዘተ መስክ ተሰማርተው በነበሩት የትግራይ ባለሃብቶች ውስጥ ውስጡን ሲካሄድ የነበረው ድርጊት ተስፋ አስቆራጭ እና የሚያበሳጭ እንደነበር የባለታሪኮቹ ማስረጃዎች እየጠቀሱ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ሆኖም በዚህ እትም በተለያየ ምክንያት የባለታሪኮቹ ስም እየጠቀሱ መዘርዘር አስፈላጊ ባለመሆኑ በተጨባጭ ደረሰ ከተባለው በደልና መድልዎ በመነሳት ሁኔታውን ሊያስረዱ የሚችሉ ጉዳዮች ሰብሰብ ባለ መልኩ ማቅረቡ ተመራጭ ነውና እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ ለስራ ማስኬጃም ሆነ ለካፒታል ኢንቨስትመንት የሚውል ከባንክ የሚገኝ የገንዘብ አቅርቦት ላይ የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠሩ ማዘግየትና መከልከል፤ ለማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግዢ የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄን ማዘግየት ወይንም ተገቢ ባልሆኑ ምክንያቶች መከልከል (በተለይ በአሁኑ ሰአት ከባንኮቹ የስራ ሃላፊዎች ጋር ቅርበት ካለህም እባክህ ይህ ነገር ይቅርብህ እኛንም አደጋ ውስጥ አትክተተን የሚሉ ተማጽኖዎችን መስማት የተለመደ ሆኗል)፤ ጨረታ አሸንፈው በህጋዊ ውል የተረከብዋቸውን ፕሮጀክቶች ያወጡትን ወጪ አለመክፈል ወይንም ማጓተትና ለሌላ ኪሳራ እንዲዳረጉ ማድረግ፤ ከፍተኛ ግብር መጠየቅና እንዲዘጉ ማድረግ፤ በግብር ስም በማስፈራራት ድርድር ማካሄድ (ድርድሩ በከፍተኛ ባለስልጣኖች፣ በሚኒስትር ማእርግ ጭምር የሚያካትት ነው-ድራማው አሳዛኝና አገሪቱ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ግልጽ ያለ ስእል ይሰጣል)፤ ትልልቅ ህንጻም ሆነ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ንብረቶች ለመሸጥ የተለያዩ ጉዳዮችን መደርደር ወይም ከተሸጠ በኋላም የተለያዩ ሸሮች/ሰበቦችን በመፍጠር ገንዘቡ እንዳይጠቀሙበት ማድረግ፤ በውስን ጨረታ ስልት ትልልቅ ጨረታዎች ላይ እንዳይሳተፉ ማድረግ፤ ምክንያት እየተፈለገ ለጥቂት ቀናት በእስር አቆይቶ በማስፈራራት ገንዘብ ተቀብሎ መፍታት፤ ይህ ሁሉ ፈተና አልፈው ህይወታቸውን ለመታደግ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ገለል ብሎ ለመቆየት ወደ ውጭ ለመሄድ በሚሞክሩበት ወቅት የተጋባዥ አገር ደህንነቶች በሚያሽከረክሩት የፀጥታ ሃይል ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ የመሳሰሉትን ይጠቀሳሉ፡፡ ይሀ አልበቃ ብሎም የትግራይ ተወላጆችን በገፍ ማሰርን ተከትሎ እስር ፍራቻ በርካታ ባለሃብቶች ቤተሰባቸውንና የሚወዱትን ስራ ጥለው ከአገሪቱ እንዲወጡና በባእድ ሀገር እንዲኖሩ ተገደዋል (በነገራችን ላይ ይህ ስትራቴጂ ከላይ የገለጽኩትን ህቡእ አጀንዳ አንዱ አካል መሆኑን ያጤኑታል)፡፡ ይልቁንስ ከላይ የተገለጹት እነኚህ ከፍተኛ ተቋሞች በሀገሪቱ ክፍተኛ ባለስልጣኖች አንደበት ሳይቀር ለሀገር ከፍተኛ ግብርን የሚያስገኙ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገቡ፣ ለርካታ የሰው ሃይል የስራ እድል የፈጠሩ ሲሰበክላቸውና ሲመሰከርላቸው የነበረ መሆኑን ሲታይ ምን ማድረግ እንደተፈለገ፣ ስንክሳሩም በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ድርጊት ከጦርነቱ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ አነስተኛና ጥቃቅን ስራዎች (ሻይና ቡና ማፍላትን ይጨምራል) ላይ የደረሰው መዝጋት የሚያካትት አይደለም፡፡

እንግዲህ “ዱልዱም ልሂቃኖቹ” ይዘውት በመጡ ጠንጋራና ዘመኑን የማይዋጅ የኩይሳ ክምር ሃሳብ የት እንዳደረሰን እያየን ነው፡፡ በርግጥ የትግራይ ህዝብ ክፍተኛ በደልና ስቃይ ደርሶበታል፡፡ ይህ ከንቱ ሃሳብ ለመናድ የትግራይ ህዝብ ትግል አንድና አንድ ብቻ መሆኑን ይህም የእኩልነት፤ የፍትህ፤ የነጳነት፤ የሰላምና የልማት መሆኑን ለቀሪው ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ሳይታክት ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡ የትግራይ መከላከያ ሃይል በደረሰባቸው አጎራባች ክልሎች ለህዝቡ፤ ለቅርሶችና ለንብረት ያደረገው እንክብካቤ አንዱ የዚህ ትግል ማሳያ ሊሆን እንደሚችል እረዳለሁ፡፡ ሆኖም በዱልዱሞቹ ልሂቃን ሸውራራ አስተሳሰብ እየተቃኘ ያለው የነ ፋና ዝባዝንኬ ዜናዎችና ዶክመንተሪዎች ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እየደረሰ እንዳልሆነ ከሚያጫውቱኝ ሰዎች መረዳት ችያለሁ፡፡ በሌላ በኩል ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ በወንድሞቹ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃና ችግር ከልብ በማጤን የድልድሞቹ ልሂቃን ከንቱ ቅዠትና ህልም በቃ ሊል ይገባዋል፡፡ መልካም የገና በአል ይሁንልን!

 

 

Back to Front Page