Back to Front Page

የዐቢይ አህመድ ዓሊ መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል?

የዐቢይ አህመድ ዓሊ መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል?

 

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

03-28-21

በማለት እያንዳንዱ ዜጋ

መንደርደሪያ፥ ትግራዋይ፥ ጎረቤት አገር ኢትዮጵያ ብትለወጥ፣ ብታድግ፣ ብትበለጽግ ለምን በለጸገች፣ ለምን አደገች ብሎ የሚያጉረመርም ህዝብ አይደለም። ጎረቤቶቻችን ቢያድጉና ቢለወጡ መልካም ነው። ኤርትራ ካለችበት ጨለማ ወጥታና ተገላግላ አገር ወደ መሆን ብትበቃ የሚደሰት እንጅ የሚከፋ ትግራዋይ የለም። ለምን? የኤርትራ ህዝብ ሆነ የአማራ ህዝብ - ሐዘን ሐዘናችን ነው፤ ደስታቸውም ደስታችን ነው ብለን ስለምናምን። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁምነገር ቢኖር፥ የትግራይ ህዝብ ከምንም በላይ የሚያሳስበውና የሚገደው የራሱን ቤት በመተመለከተ የቤት ስራየን በአግባቡ እየተወጣሁ ነው አይደለም? የሚለውን ጥያቄ እንጅ በሆነ ባልሆነ ነገር ሁሉ ጉዳዩን ትቶ፥ ኤርትራ ምን እየሰራች ነው? ኢትዮጵያስ ምን እየጠበሰች ነው? ሱዳን ለምንድ ነው ይህን የምታደርገው? ኬንያስ ምን እያደረገች ነው? ወዘተ እያለ የመቅበዝበዝ፣ በሌሎች ህዝቦችና አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ለመፈትፈትና ለማመስ፣ የሚቃጣውና ቅናትና ምቀኝነቶ ስልጥኖበት የህዝቦች ሀብትና ንብረት ለመዝረፍ የሚያደባና የሚያሴር፣ ብሎም በህዝብ ላይ የሟሟረት ፍላጎቱ የለውም፤ ኖሮትም አያውቅም። እንዲህ ያለ ነገርም፥ የትግራይ ህዝብ ባህል፣ ታሪክና ስልጣኔ የሚመጥን እንዳይደለ ህልውናችን የሚከነክናቸው ጠላቶቻችን ሳይቀሩ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። ታድያ፥ ይህች ኢትዮጵያ ተብላ የምትታወቀው የደም መሬት ከርሰ-ምድሯ ውስጥ የተቀበረ ህጻን ተወልዶ የማያድግባት ጸረ ሰው የሆነ ዕፅ ቢኖር ነው እንጅ ይህች አገር እንዴት ነው ትውልድ አልፎ ትውልድ በተተካ ቁጥር፥ በባንዴራ፣ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስም የንጹሐን ዜጎች ደም እያፈሰሰች የምትኖረው? በማለት እያንዳንዱ ዜጋ ራሱን ሊጠይቅ ይገባል።

 

ንጹሐን ሰዎች በገዛ አገራቸውና መሬታቸው ለድመትና ለውሻ የሚሰጠውን ክብር ያህል ተነፍጓቸው እንዲሁ እንደ ተራ ነገር እየተመነጠሩ የሞት ሲሳይና የመቃብር ቀለብ የሚሆኑበት ምክንያት ትክክል አይደለም፤ መቆምም አለበት! በማለት ለእውነትና ለፍትህ የማይቆም ሰው ቢኖር ግን ይህ ሰው ከደሙ ንጹህ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ለመሆኑ፥ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስም ሰውን የሚያክል ፍጥረት በመግደል ምን የሚሉት ትርፍ ቢገኝ ነው? የንጹህ ሰው ደም ማፍሰስ ምን ለማግኘት? በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስም ሰውን እንደ ደን እየመነጠርክና እያራገፍክ ስታበቃ የሚቀነቀነው አንድነት ሆነ ኢትዮጵያዊነት ከማን ጋር? በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ስም ሰው ከጨረስክ በኋላ ባንዴራ ከየቅጣጫው ተሰብስበው የባንዴራ ስብሰብ አንድነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ለመፍጠር ነው? ባንዴራ ከሰው ስለሚበልጥ ነው ወይስ ዋልያዎችና ጭላዳዎችን ሰብስበህ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ለመፍጠር ነው? ቢሆን ነው እንጅ።

 

ትግራዋይ ይሁን አማራ፣ ኦሮሞ ይሁን ጋምቤላ፣ የመናዊ ይሁን የአፍጋን ዜጋ፥ ግፈኞች በንጹሐን ላይ እንዳሻቸው እጃቸውን ሲያነሱ፣ በዚህ መልኩ ሲጨፈጭፉትና ደሙን ደመ ከልብ ሲያደርጉት በዓይኑ እያዬ የማያዝን፣ ይህ ነገር ትክክል አይደለም በማለት ድምጹን ማሰማት የማይችል፣ ግፈኞችና ወንጀለኞ በሰፈሩት መስፈሪያ ይሰፈርባቸው ዘንድ የቻለውን ለማድረግ የማይነሳ፣ የንጹሐን ዜጎች ደም በከንቱ ሲፈስ የማይከፋው፣ ፍትህንና ፍርድን እውነትንና ጽድቅን ለማድረግ የማይቀና ሰው፥ ምኑ ላይ ነው ሰውነቱ? ኢትዮጵያዊነት እንስሳዊ ባህሪይ መላበስ ካልሆነ በቀር የዚህ ሰው በህይወት የመኖሩ ትርጉም ምንድ ነው? ከፉና ደጉን ከማያውቅ እንስሳስ በምን ይለያል? በጦርነት ላይ ስለሚያልቀው ጦር ሰራዊት አይደለም እየተናገርኩ ያለኹተይ፤ በንጹሐን ዜጎች ላይ ስለሚፈጸመው ግፍና በደል እንጅ። በትግራይና በተጋሩ ላይ እየተፈጸመ ያለ የዘር ጭፍጨፋ፣ የህዝቡን ሀብትና ንብረቱ የማውደም ዘመቻ እንዴት ሊሰማን አይገባም? ኢምሬቶች በሰማይ፣ የኤርትራና የሱማሌ መንግስታት በሰሜን፣ የዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ሰራዊት በጋራ በደቡብና በምዕራብ ገብተው የትግራይን ህዝብ በጅምላ ሲጨፈጭፉ ሀብትና ንብረቱን ሲያወድሙ ደስታዉን የሚገልጽ ሰው ምን ያህል ሰብአዊነት ባይሰማውና ሰይጣናዊ ባህሪይ ቢላበስ ነው? ምንኛ ፈጣሪ? የትግራይ ህዝብ በዚህ መልኩ ማለቁንና መጨፍጨፉ ሲያይ ደስታና ሐሴት የሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ምን አተርፋለሁ ብሎ ነው የሚያምነው?

 

እዚህ በምኖርበት አሜሪካን አገር ጋብቻ ለመፈጸም የተዘጋጁ ተጋቢዎች ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በላኩት ማስታወሻ ውስጥ አንድ ለየት ያለ ይዘት ያለው መልዕክት አክለው መላካቸውን አስታውሳለሁ። ይኸውም፥ እባክዎን ለስጦታ ዕቃ የሚገዙልን ከሆነ ቻይና ስሪ ዕቃ እንዳይገዙልን ስንጠይቅዎ በታላቅ ትህትና ነው የሚል ነበር። የዚህ ማስታወሻ መልዕክትና ዓላማ ግልጽ ነው። ጎበዝ፥ በቻይና ዕቃ ያላማረረና የማያማርር የዓለማችን ዜጋ የለም። ለምን? የቻይና ዕቃ የሚመስል እንጅ ከምር ዕቃ ስላይደለ፣ ፌክ ወይም ውሸት ስለሆነ፣ ስለማይታመን፣ ዕቃው ከገዙበት ሱቅ በር ሳይወጡ ለኪሳራና ለጸብ ስለሚዳርግ፣ ካሊስም ቢገዙ ጅንስ ሱሪ የሚያቃጥል ነበልባል ስለሆነ ነው። በእውነቱ ነገር፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሰው መሆኑን ብቻ ነው እንጅ ዕቃ ቢሆን ኖሮ የቻይና ዕቃ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ይህ ሁለመናው ፌክ የሆነ ሰው (ዐቢይ አህመድ ዓሊ) በቅርቡ ፓርላማውን ሰብስቦ ፈጣሪ ፊቱን ጽፍቶ አፉን ከፍቶ ያስለፈለፈው፣ ያናዘዘው፣ ተምታትቶ ደጋፊዎቹን ያምታታበትን ውሎ ተንተርሼ አምስት ነጥቦችን በግርድፉ ላስቃኛቹና ወደ ተነሳንበት ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን እንመለሳለን።

Videos From Around The World

 

የዐቢይ አህመድ ዓሊ የፓርላማ ውሎ በእውቀት ሲፈተሽ

 

1.የሰማውን ነገር የሚጠይቅና የሚመረምር ሰው በቁጥር ለማወቅ ቢያዳግትም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በያዝነው ሳምንት ፓርላማውን ሰብስቦ ካሰማቸው በርካታ ትንግርተኛ ንግግሮች መካከል፤ ትግራይ ላይ እየተዋጋኝ ያለ የተበተነ ዱቄት ነው ሲል ብዙዎቻችን ሰምተናል። ዱቄትን የሚበትን ነፋስ ነው። በታኙ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከሆነ ደግሞ ሰውየው ነፋስ ነው ማለት ነው። ታድያ፥ ነፋስን ተከትሎ የሚሄድና በነፋስ የሚታመን ማን ነው? ነፋስን መከተልና በነፋስ መታመን ከንቱ መሆኑ አይደለምን? አንድም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ነፋስ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም ከተባለ ደግሞ፤ በተመሳሳይ መልኩ፥ ትግራይ ላይ እየተዋጋ ያለው ዱቄት አይደለም፤ እንደ ዱቄትም ሊበተን አይችልም ማለት ነው። ከሆነ ደግም፥ ዱቄት እያደረገው ያለ ዱቄት ከተባለ ዱቄት እየሆነ ያለስ ምን ሊባል ነው? ይህ የምለው፥ የተበተነ ዱቄት ሊሰበሰብ እንደማይችል ስለሚታወቅና የተበተነ ዱቄት የተባለው ደግሞ ነገ ለድርድር እኩል ከዐቢይ አህመድ ዓሊ ጋር መቀመጡ ስለማይቀር ነው። ይህ የሚለው እኔ ሳልሆን ዐቢይ አህመድ ዓሊ ራሱ ነው። አሁን፥ ማን ይሁን እውነተኛ፥ ጥበብ ወይስ ካልዋሸች፣ ካላጋነነችና ካልተቀደደች ነግቶ የማይመሽላት ግነት የለመደች የዐቢይ አህመድ ዓሊ ሐሰተኛ ምላስ?

2.     ዐቢይ አህመድ ዓሊ ወያነ ትግራይ ተመልሶ እንደሚመጣ፤ ትግራይ የተጋሩ ብቻ እንደሆነች፤ የተጋሩ ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣንና መብት እንደማይደፈር፤ ትግራይና የትግራይን ህዝብ እንደ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ደቡብ፣ ሐረሬ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ወዘተ በአሻንጉሊቶች፣ በባንዳዎችና በተላላኪ ኃይሎች ሊገዛት እንደማይችል በእርግጠኝነት አረጋግጧል። እንበልና የተከበረው ምክር ቤት ፈቅዶ መንግስትንም እረፍ ብላችሁ እዚያ የተሸሸጉ አንዳንድ ሰዎች መጥተው መንግስት ይሁን ቢባል እና መቐለ ቢመለሱ በምን ዓይናቸው ነው ሚድያ ላይ ወጥተው እንደ ትናንትና መናገር የሚችሉ ይህ የሚለው/ያለው ሃፍረት የማያውቀው አያልቅበት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ነው። አማርኛ የማይገባው ሰው ካልሆነ በቀር፥ አጠፋናቸው፣ ደመሰስናቸው፣ በተናቸው ወዘተ በማለት ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ በውሸት ያስጨበጨበ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ወራሪ ኃይሎችን እየለቀመ ካለው የተራሮችና የኮረብቶች ባለባት ወያነ ትግራይ ጋር ጉዳዩ በጠረጴዛ ዙሪያ ላይ ለመፍታት እንደተገደደና እንደሚገደዱ ከወዲሁ እወቁልኝ እያለን ነው ያለ። ሰውየው የፈራውን እውን ሲሆን ታዲያ የተከበረው ምክር ቤት ፈቅዶ መንግስትንም እረፍ ብላችሁ እንዲል ሽንፈቱንና ኪሳራዉን ከወዲሁ ለማቅለል ያህል በእንቅልፍ ልቡ የሚመላለሰውን በምክር ቤቱ እያላከከ ነው። ዐቢይ አህመድ ዓሊ ይህን ሲል ታድያ፥ ኧረ እኛ አላልንም፤ አንልምም! ለማለት የደፈረ አንድም ደም ያለው የምክር ቤቱ ማህበርተኛ አልተገኘም። ያለ እንደሆነ የሚገጥመውና የሚጠብቀው ስለሚያውቅ። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ሐቅ ቢኖር፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከትግራይ ጋር ያለው ጉዳይ በድርድር ከመፍታት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው አውቆ ለሰላም እጁን እንዲሰጥ ያስገደደው ኃይል ሌላ ማንም ሳይሆን እውነትንና ጽድቅን ከያዘ ከትግራይ ህዝብ ጋር መዋጋትና ጦርነት መግጠም ከግድግዳ ጋር መላተም ስለሆነበት ብቻ ነው። አንድም፥ ጊዜ የወሰድሁ እንደሆነ ወያነ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ያንቀኛል ነው አንድምታው። ሌላ፥ እዚህ ወስጥ የተሰነጠረው ውሸት ተመለከትን እንደ ሆነ እዚያ የተሸሸጉ አንዳንድ ሰዎች የምትለዋን ቃል ነው። የት የተሸሸጉ? አንዳንድ ማለት ስንት ነው? በእውነቱ ነገር፥ የአከባቢው ከስልሳ በመቶ በላይ መቆጣጠር መቻል መሸሸግ ነው የሚባለው? ሌላውን ሁሉ ትተን፥ በቁጥር ሃምሳ አባላት ያሉት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዐቢይ አህመድ ሊይዝ የተቻለው ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው። ምክንያቱም ሁለቱ አዲስ አበባ የነበሩ ናቸው አንደኛዋ ደግሞ በፈቃድዋ እጅ የሰጠ ናት። ከዚህ ውጭ አንድም የተያዘ ሰው የለም። ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ የተደረጉ አምስቱ ሰዎችና ከህግ አግባብ ውጭ በግፍ የተገደሉ አራቱ ሰዎች ከአስርት ዓመታት በፊት በጡረታ የተገለሉና አዛውንት ናቸው። ይህ ማለት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ካድሬዎቹ ሳይጨምር በሺዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛና መካከለኛ ባለስልጣናት ከነ ሙሉ ትጥቃቸውና የሰው ሃይላቸው መሆናቸው ነው። ይህ ውሸት ከሆነ ዐቢይ አህመድ የያዛቸው የማዕከላይ ኮሚቴ አባላት ስም ዝርዝር ለህዝብ ያቅርብና ቃሉ እውነትነት ይኑሮው። ዳሩ ግን ሰውየው በሐሰት ጠኔ የተለከፈ ሰው ስለሆነ እስኪበተን ደረስ እንደ ዱቄት መብነን ስራዬ ብሎ ተያይዞታል። መቼ ይሄ ብቻ ይሁን ቢባል እና መቐለ ቢመለሱ በምን ዓይናቸው ነው ሚድያ ላይ ወጥተው እንደ ትናንትና መናገር የሚችሉ እንዲል። አንባቢ ሆይ፥ በፈጣሪ ይሁኖትና ዐቢይ አህመድ ዓሊ እየነገረን ያለው በጊዜው እውን መሆኑ የማይቀር ነው። ታድያ በዚያን ጊዜ፥ ሃፍረትና ውርደት የሚከናነበው ማን ነው? ላይሰፋ የተቀደደው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ወይስ ታግሎ በሱሪው ማንነቱንና ክብሩን ያስጠበቀው ወያነ ትግራይ?

 

3.     ዐቢይ አህመድ ዓሊ ያላቸውን ደመና ወደ ዝናብ የሚቀይሩ አገራት በጣም ጥቂት አገራት ናቸው። በሰሜን ሽዋ በጎጃም ያያቹት ዝናብ የተፈጥሮ ሳይሆን እኛ ያዘነብነው ነው። ደመናን ወደ ዝናብ በመቀየር ውሃ ማዝነብ ተችሎናል ብሏል። የሚገርመው ግን፥ ከአመት ዓመት ደመናማ መሆኑን የሚታወቀው አከባቢ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የጠቃቀሳቸው ስፍራዎች ሳይሆን የህዳሴ ግድብ የተንጣለለበት አከባቢ ነው። ታድያ፥ ኢትዮጵያ ደመና ማዝነብ ከቻለች፤ ፓርቲያቸው የተከማቸ ደመና በተመረጠ ሁኔታ ማዝነብ የሚችል ከሆነ የቤንሻንጉል ጉሙዝ አከባቢ ዝናብ በዝናብ በማድረግ ግድቡን ያለ አንዳች ጭቅጭቅና ሁከት ውሃ በመሙላት አገሪቱ ሊመጣ ካለው ጦርነትና እልቂት ለምን አይገላግላትም? ወይስ ዐቢይ አህመድ ዓሊ፥ የአማራ ሰው ነጭ ውሸትን እንደ ወተት እያጋቱ በቀላሉ ስልጣን ላይ መቀጠል ይቻላል ብሎ ስለሚያምን ነው? ፍርዱን ለአንባቢ ትቸዋለሁ።

 

4.    ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሴቶች ኮ አሁን - በወንድ የተደፈሩት የኛ ወታደሮች ኮ በሳንጃ ተደፍሯል ብሏል። ይህ የትግራይ ሴቶች በወንድ ነው የተደፈሩት የኛ ወታደሮች በሳንጃ ነው የተደፈሩት! የሚል የዐቢይ አህመድ ዓሊ አባባል በመደበኛ አማርኛ የተተረጎመ እንደሆነ፥ በሳንጃ የወጉን የትግራይ ወንዶች በሳንጃ መውጋት ስላልቻልን የምንችለውና የምናውቀው ወሲባዊ ጥቃት መፈጸም ነው ይህን ደግሞ አድርገናል። ያደረግነውንና የፈጸምነውን አላደረግንም፣ አልፈጸምን በማለት አልካድንም። በትግራይ ሴቶች ላይ በሚገባ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽመንባቸዋል፣ ክብረ ንጽህናቸውን አራክሰነዋል፣ አምጸናቸዋል፣ ደፍረናቸዋልም። እዚህ ላይ የፈጸምነው ስህተት ምንድ ነው? ሲሉን በይፋ በፓርላማ ነው። ህግ በሌለባት አገር የህግ ያለ! ስለማይባል - የፈጣሪ ያለህ! ቢያለሁ።

 

5.     የሱዳኑ ጄነራል፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊን በተመለከተ በይፋዊ መግለጫቸው ላይ የሰውየው የአእምሮ ጤንነት እጠራጠራለሁ ማለታቸውን እናስታውሳለን። ታናጋሪው እውነታቸው ነው። ትግራይን ለመውረር በየአቅጣጫው የተሰማራው ኃይል በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው ጥፋትና በቀጣይነት እየፈጸመው ስላለ የዘር ጭፍጨፋ ፍትሐዊት ለማስረገጥ ውጊያ ጀምረህ ስታበቃ ፊት በጥፊ አይመታም ምናምን አትልም፤ እሱ በቦክስ ውድድር ውስጥ ያለ ህግ ነው ፋወል የሚባለው ብሎ የሚያምነውና የሚለው ዐቢይ አህመድ ዓሊ፤ ይህን የተናገረበት ምራቅ ሳይደርቅ ደግሞ፥ መዝረፍን፣ መድፈርን የፈጸመ ማንኛውም ወታደር በህግ ይጠየቃል ሲል ተደምጧልና። ጥያቄው፥ ከተከናወኑ ሪፎርሞች መካከል በግንባር ቀደምትነት በስኬታማ ሁኔታ ግቡን የመታ! እየተባለ ብዙ የተነገረለና የተዘፈነለት ሠራዊት በትግራይ ሴቶች የፈጸመውንና ያደረገውን ግፍ ያደርግና ይፈጽም ዘንድ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ተቀምጦ ትዕዛዝ የሰጠ ሰውስ? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ግን ዐቢይ አህመድ ዓሊ መልስም ሆነ ማብራሪያ ሳይሰጥበት አልፏል። ምናልባትም ዐቢይ አህመድ ዓሊ፥ እንዲህ ያለ አስነዋሪ ድርጊት አንቀበልም፤ ይህን ያደረገና የፈጸመ በህግ ይጠየቃል! ሲል የሚደመጠው ይህን በማለት አመልጣለሁ ብሎ የሚያምን ከሆነ ሲበዛ የዋህ ነው። አንድም፥ በፖለቲካ ሽፋን በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥፋቶችና በደሎች በህግ ፊት የሚቀርበበት አገባብ አያውቅም ማለት ነው። ሐሰትን ለመዝራትና አሉባልታን ለማሰራጨት የፈጠነች ምላስ እንጅ ለመስማትና ለማዳመጥ ሰሚ ጆሮ ያልፈጠረበት ዐቢይ አህመድ ዓሊ፥ አለማወቅ ከተጠያቂነት አያስመልጥም! የሚለው የህግ መሰረትና ጉልላት ማን ይንገረው?

 

የፍትህ ገመድ ዘላ አትገባም፤ ስትገባም አትታይም፤

የገባች እንደሆነም በከንቱ አትመለስም!

 

ጠቢቡ ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ለመሞትም ፍትህና ፍርድን ለማግኘትም ጊዜ አለው። ዐቢይ አህመድ ዓሊ ኢሳይያስ አፈወርቂን ተማምኖ በትግራይ ህዝብ ላይ ግፍና በደል ለመፈጸም ተችሎት ይሆናል። ይህ ማለት ግን የአንድ ሰውም ቢሆን የንጹሕ ሰው ደም በከንቱ አፍስሶ እንዲሁ በሰላም ተዘልሎ ይኖራል ማለት ግን አይደለም። የዓለም ታሪክ ሆነ በቅድሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈ ማንም ይሁን ምን ሄዶ ሄዶ የማያልፋት ፍትሕ ተብላ የምታወቅ ኬላ ፊት እንደሚቆም ነው የሚመሰክሩልን። በዚህ ዕለትና ሰዓት ይህ ይሆናል ለማለት ባልደፍርም ዐቢይ አህመድ ዓሊ ዛሬ እንደ ጀብድ እያወራልንና እየተረከልን ያለው የንጽሐን ተጋሩ ሞትና እልቂት ስህተት ነበር! ብሎ ስህተቱን አምኖ የሚጸጸትበት ቀን ከፊታችን እንዳለ ስናገር ግን በእርግጠኝነት ነው። የፍትህ ገመድ ዘላ አትገባም፤ ስትገባም አትታይም (ባልጠበቅነው መንገድ ያልጠበቅነው አዲስ ነገር ይፈጠራል ለማለት ነው)፤ ቀስ በቀስ እያባበለችና እየሸረሸረች ትገባለች (እኛ በምንፈልገው ጊዜ ላይሆን ይችላል)፤ ገብታም ስራዋን ትፈጽማለች እንጅ እንዲሁ አትመለስም (እኛ የምፈልገውና የምጠብቀው ዓይነት ቅጣት ላይሆን ይችላል ግን ደግሞ ወንጀለኛ እንዲሁ አያመልጥም)።

 

የኤርትራ ሰራዊት አልገባም፣ መግደል ቀርቶ በክፉ ዓይን የተመለከትነው ትግራዋይ ሳይኖር መቐለ ገባን! እያለ ፓርላማ እያስጨበጨበ የመጣ ሰው ዛሬ፥ ይህን ሁሉ ግፍና ዕብሪት ባወራች አንደበቱ የኤርትራ ሰራዊት መግባቱ ብቻ ሳይሆን የአማራ ጨምሮ የሁለቱም አገራት ሰራዊት በትግራይ ህዝብ ላይ ስለፈጸሙት የጦር ወንጀል ሳይቀር አፍ አውጥቶ ለመናዘዝ ተገዷል። ዐቢይ አህመድ ዓሊ አሁን የሚፈለገው ወጥመድ ውስጥ ገብቷል። ለወራት የካደውን ሐቅ በአደባባይ አምኖ እንዲቀበል ቀጭን ትዕዛዝና ምርጫ ሰጥተው ላስለፈለፉትና የተናገረውን እንዲናገር ላደረጉ ኃያላን፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የኤርትራ ሰራዊትና በሰላማውያን የትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው የጦር ወንጀል በተመለከተ እንዲሁም የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ እንዲወጣ ተስማማ! የሚለውን መግለጫ ብቻውን ነገ እጁ በብረት ሰንሰለት ጠፍንገው ፍትህ ፊት ለማስቆም የሚያስችላቸው በቂ መረጃና ማስረጃ ነው።

 

ጥጉ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ፥ የኢምሬት፣ የኤርትራ፣ የሱማሌና የሱዳን መንግስታትና አገራት በማሳተፍ በፈጠራ ክስ በተቀናጀ መልኩ በትግራይ ህዝብ ላይ ከፈጸመው ወረራ የተነሳ ለህልውናው እየተዋደቀ ያለው የትግራይ ህዝብ በያዝነው ወር መባቻ አከባቢ ሰላም ለማውረድ ካለው ጽኑ እምነትና ፍላጎት የተነሳ ለተግባራዊነቱም ያስቀመጣቸው ዝርዝር ነጥቦች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት አግኝቶ ሰላምን ለማውረድ እጅ ካልሰጠና፥ አጥፍቻቸዋለሁ፣ አልቀዋል፣ ተደምስሰዋል ወዘተ እያለ በኢቲቪ፣ በዋልታ፣ በፋናና በኢሳት ድራማ እየሰራባቸውና እያሰራባቸው ከሚገኙ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወይየትና ቀልዱን አቁሞ ለመደራደር ራሱን ካላዘጋጀ በቀር የዐቢይ አህመድ ዓሊ ፍጻሜ ለማመን የሚከብድ ሊሆን እንደሚችል የታመነ ነው። ምን ሊፈጥር ይችላል?

 

(1)    ዮርዳኖስን አትሻገርም በሚል ርዕስ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ ከወራት በፊት ዝግጅቱን ተጠናቆ በኢትዮጵያ ለማሳተም በነበረው ዕቅድ ብኋላም ከመጽሐፉ ይዘት የተነሳ (ዐቢይን የሚቃወም አናሳትምም ተብሎ) ሳይታተም የቀረው መጽሐፌ ገጽ 53-68 ላይ በሰፊው እንዳብራራሁት ዐቢይ አህመድ በእንቢተኝነቱ ከጸና፥ ከእግዚአብሔር ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ በመስጠት እስራኤልን እንዲወጋ፣ እንዲመታ፣ እንዲወርና ከተሞችዋን እንዲያቃጥል ከሶሪያው ንጉሥ ከወልደ አዴር ጋር የመከረና ውል ያሰረ የይሁዳ ንጉስ የአሳ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው ይችላል። ይህ ማለት፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ልክ እንደ ደርግ ወታደራዊ መንግስት የቀረው ዘመኑ በሙሉ የጦርነት ዘመን ይሆናል ማለት ነው። ምናልባትም በዚህ መኸል ህመሙ ጸንቶበት በሞት ዕድሜው ሊያጥርም ይችላል። በአሁን ሰዓት ዐቢይ አህመድ ዓሊ በእደ ኢሳይያስ የሚዘወር ሰው እንጅ የኤርትራው ሰው ኢሳይያስ አፈወርቂ ዐቢይ አህመድ ዓሊን ከቁምነገር የሚቆጥርበትና የሚሰማበት ጆሮ የለውም። በአሳ ፊት ቆሞ ዕጣ ፈንታውን የነገረው አናኒ የሶሪያ ንጉሥ ጭፍራ ከእጅህ አምልጦአል እንዲል፥ የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ለመውጣት ተስማማ ለማለት አስመራ መሄድ የተገደደው ዐቢይ አህመድ ዓሊ በገዛ እጁ ጋብዞ ካስገባው መካሪው ከሆነ የሰው አውሬ ከኢሳይያስ አፈወርቂ ሊገጥመው ሲለሚችል ልዩ ልዩ ፈተናዎች በሚመለከተ በሚቀጥሉ ነጥቦች እንመለከታለን። በርግጥ፥ ለኤርትራ ብሔራዊ ድህንነት ዋስትና መስጠት አንችልም ተብሎ በምስምስ እንደተገለጸው ሳይሆን ሐቁ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የኤርትራው ሰራዊት አዛዥ የሆነው ኢሳይያስ አፈወርቂን ሰራዊትህን አውጣልኝ ብሎ ለመናገር አቅም ስለሌለው ነው፤ ደግሞም አይችልም። የገባውን አይወጣም፤ የገባው ሠራዊት የገባበት ስፍራ መቃብሩ ይሆን ዘንድ ገብቷልና።

 

(2)   በመጽሐፈ መሳፍንት ላይ ተጻፈው፥ እርሱ ወንድማችን ነው ብለው አቤሜሌክን ለመከተል ልባቸውን አዘነበሉት። ከበኣልብሪትም ቤት ሰባ ብር ሰጡት፤ በዚያም አቤሜሌክ ምናምንቴዎችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት፥ እነርሱም ተከተሉት አቤሜሌክ ሰፊውን ህዝብ አደናግሮና አወናብዶ ድምጻቸው ካገኘ በኋላም ሰባ የሆኑትን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ አረዳቸው፤ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ነበርና ተረፈ ሸሽቶ ከእርድ ያመለጠ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ቆመ፥ ድምፁንም አንሥቶ እንዲህ አለ የሴኬም ሰዎች ሆይ፥ እንግዲህ ለይሩበኣልና ለቤቱ እውነትንና ቅንነትን ዛሬ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፥ እርሱ ደግሞ በእናንተ ደስ ይበለው፤ እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ይውጣ፥ የሴኬምንም ሰዎች ቤትሚሎንም ይብላ ከሴኬምም ሰዎች ከቤትሚሎም እሳት ይውጣ፥ አቤሜሌክንም ይብላ እንዳላቸውና አቤሜሌክን ፈርቶ ወደ ብኤር እንደ ሄደ በዚያም እንደ ተቀመጠ ይናገራል። የሚደንቀው አቤሜሌክ ከነገሰ ከሦስት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው በሰባ የይሩበኣል ልጆች ላይ የተደረገው ዓመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹንም እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሴኬም ሰዎች ላይ እንዲሆን እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሴኬምም ሰዎች በአቤሜሌክ ላይ ተንኰል አደረጉ ይላል። የሆነው ነገር የተመለከትን እንደሆነ ህዝብ ሁሉ አቤሜሌክን ከመናቁ የተነሳ ሥርዓት አልበኝነትና ጋጠወጥነት በምድሪቱ ሁሉ ነገሰ፣ አመጽና ዝርፍያ ተበራከተ። አቤሜሌክ ከሚመራው ህዝብ ጋር እሳትና ጭድ ሆነ፣ ስዎች አለሁ እያለ ላይነሳ ድባቅ የሚመታ ደንበኛ ሴራ መከሩበት፣ አቤሜሌክን አቤ/አቢቹ ያላንተ አይነጋልንም! እያሉ ሲያጨበጭቡለት የነበሩ የገዛ ራሱን ህዝብ እንደ ቅጠል አረገፈው። ታድያ አቤሜሌክ በውጊያ መኸል ላይ ሳለ አንዲት ሴት የወፍጮ መጅ ጣለችበትና አናቱን ሰብራ እንደ ገደለችው፣ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር እንደ መለሰበት፣ እግዚአብሔር የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ እንደ መለሰባቸውና የይሩበኣልም ልጅ የኢዮአታም እርግማን እንደ ደረሰባቸው ቅዱስ ቃሉ ይመሰክርልናል። ሁለቱን መስተዳድሮች ጨምሮ ስምንቱን ክልሎች በታንክና በመትረየስ ታጅቦ ገብቶ፥ የሚሻር ሽሮ፣ የሚታሰር አስሮ፣ የሚገደለም ገድሎ መላ አገሪቱ በቁጥጥሩ ስር ካዋለ በኋላ (በራሱ ላይ ተመልሶ እስኪ መጣበት ድረስ ይህ ሁሉ ሲያደርግ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በጭብጨባ አጅቦታል) በቁጥር አነስተኛ ተብሎ የሚታመነው የቀረው ትግራይ ነበረና የንጹሐን ዜጎች ደም ማፍሰስ የለመደችው እጁ ትግራይ ላይ በእሳት የተያዘችው ዐቢይ አህመድ ዓሊ የአቤምሌክ ጽዋ ሊጎነጭ የሚችልበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። ህዝብ በመንግስት ላይ የሚነሳበት ምክንያቶችና መንገዶች ልዩ ልዩ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ማንኛውም ህዝብ ዐቢይ አህመድ ዓሊን ዐይንህ ላፈር ብሎ ፈጽሞ የሚጸየፍበት ጊዜ አይመጣም ማለት የዋህነት ነው። የአገሪቱ ህዝቦች እርስበርሳቸው ሊጨራረሱ ይችላሉ። የኑሮ ውድነት ክፉኛ እያጎሳቀለው ያለ ህዝብ በቁጣ ሊነሳበት ይችላል። ሆሳዕና በአርያም እያለ በታላቅ ጭብጨባና ደስታ የተቀለው ሰውዬ ስቀለው! ስቀለው! እያለ ለማሰናበት ህዝብ ተክኖበታል። የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለ እጅግ አሰቃቂ የሆነ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አሳስቦት በዐቢይ አህመድ ዓሊ ባይነሳም ጦርነቱ ተከትሎ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሁን በሰፊው እየታየ ያለ የዳቦ ዕጦት ደህና አድርጎ ሲጠብሰውና የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በርሃብ አለጋ ሲገረፍ ግን መጮሁ የማይቀር ነው። ይህ ብቻውን ዐቢይ አህመድ ዓሊ ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችልም ግልጽ ነው። ሌላው፥ ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል ሲካፈል ይጣላል እንደሚባለው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ኢሳይያስ አፈወርቂንና የአማራ ሰራዊት በመጠቀም ትግራይን ከደመሰሰና ካጠፋ በኋላ ቀጥሎ ለማድረግ ወዳቀደው ዕቅድ እግሩን ሲያነሳ፤ ኢሳይያስ አፈወርቂ ከዐቢይ አህመድ ዓሊ ጋር ግንባር በመፍጠር ትግራይን ካበረሰ በኋላ ቀጥሎ ማድረግ የሚፈልገውን ለማድረግ ሲነሳ በዐቢይ አህመድና ዓሊና በኢሳይያስ አፈወርቂ መካከል ሊፈጠር የሚችልው የሁለት ዦሆኖች ጸብ የሚጠበቅ ነው። የሁለቱም አምባገነኖች ፍላጎት በቀጠናው ጎልተህ የመታየት አባዜ ስለሆነ ሊሆን የሚችለው ከሁለቱ አንዳቸው መንበርከክ አለባቸው። አንድም፥ ኢሳይያስ አፈወርቂ ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ የመመለስና የመጠቅለል ዕቅድ ካልያዘ በቀር። የኢሳይያስ አፈወርቂ ዕቅድና ዓላማ እጁን አስገብቶ በፈጠራቸው ተጨማሪ ቀዳዳዎች አገሪቱ በእርስበርስ ጦርነት እየታመሰች እንድትኖር ማድረግና አስመራ ቤተ መንግስት ተቀምጦ መሳቅ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር አያይዞ ዞር ማለትና ስጋት ልት ሆነውና ልትፈጥርበት በማትችልበት ሁኔታ አገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ ማዋከብ፣ በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸመውና በጦር ወንጀለኝነትን በዓለም ፊት አሳጥቶ የለሁበትም ማለት፣ ቁጠባዋን አጠልሽቶ የራሱን እንጀራ ማብሰል፣ ምድሪቱን በደም አጨቅይቶ ዘወር ማለት ለዐቢይ አህመድ ዓሊ አደጋ ነው። እሳቱን አንድ ጊዜ አንድጀዋለሁ የሚጠበስ እዛው ይጠበስ፤ ዐቢይ እንደሆንክም ስራህ ያውጣህ! በማለት ኢሳይያስ ፊቱ በዐቢይ አህመድ ዓሊ አዙሮ ተመልካች መሆን በራሱ ለዐቢይ አህመድ ዓሊ ትልቅ ኪስራና ውድቀት ከመሆኑ በላይ ከዚያ በኋላ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ጥቂት ቀናት መሰንበት ቢችል ነው እንጅ ረጅም ርቀት እንደማይጓዝና በአጭር ጊዜ ውስጥም መንግስትነቱ ሊያጣ እንደሚችል ምንም አየጠራጥርም።

 

(3)   በአቤምሌክ ታሪክ ላይ እንደተመከትነው፥ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ አይሆንም፣ ይህን በማድረግ ያሰቡትን ያገኛሉ አያገኙም የሚለው መከራከያ ነጥብ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን፥ በዐቢይ አህመድ ዓሊ ተለዋዋጭ ባህሪይና ወስላታ ማንነት ሊከፉ የሚችሉ አረመኔዎች (ኢሳይያስና የአማራ ልሒቃን) ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው አሁንም ዕድሜው ሊያሳጥሩት ይችላሉ። እየተንፏቀቀና አንዱ ከሌላውን እያባለ፣ ጓዶቹን ገድሎና አስገድሎ ከቤተ መንግስት መዓድ ለመካፈል የበቃው፣ መሬቱን ለሱዳን አስረክቦ በቤንሻንጉል ጉምዝ ላይ የሚፎክርና ዘራፍ የሚል፣ እንኳንም ትግራይ በተባበሩ ክንዶች ተመታልኝና ተዳከመልኝ እንጅ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በማንሳፈፍ የኦሮሞ ልሒቃን ድባቅ መምታት፣ መጣልና ወደ ስፍራቸው መመለስ አውቅበታለሁ! በማለት ሚኒሊካዊት ኢትዮጵያ ዳግም እውን የማድረግ ህልም ያላቸው በቅዠት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ልሒቃን ሊሰነዘርበት የሚችለው ፍላጽና ሊወረወርበት የሚችለው ጦር፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የፖለቲካ ሴራዎች (መርዝ ጨምሮ) ዐቢይ አህመድ ዓሊ መትተው የመጣ አጋጣሚዎች እጅግ ሰፊ ነው። ዳሩ ግን፥ ሁለቱም ግባቸው ሊመቱ የማይችሉ መንገዶች ከመሆናቸው በላይ ሂደቱ ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚኖራት ህልውና በይፋ የሚያከስሙና የኢትዮጵያ ፍጻሜ የሚያበስሩ ይሆናሉ። ኢሳይያስ ዐቢይ አህመድ ዓሊን አስወግዶ የኢትዮጵያ መሪ የመሆን ፍላጎት የለውም (ህልሙ አይኖረውም አይባልም)፤ የአማራ ልሒቃን አካሄድ ደግሞ አገር ለመበተን በሚደረገው ሂደት ነገሩ ያፈጥነው እንደሆነ ነው እንጅ ተሳክቶላቸው የአማራ ልሒቃን የሚፈነጩባት ምንሊካዊት ኢትዮጵያ ለማየት አይሰምርላቸውም፤ ፈጽሞም የማይሆን ነው። በንጹሐን ዜጎች ደም የሰከረው ዐቢይ አህመድ ዓሊ ለመቅጣት ግን መሳሪያ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።

 

(4)   የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ጨምሮ በርካታ የዓለማችን የቁጠባና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አሁን እያሳዩት ያለው ተነሳሽነት ዳር ደርሶ በኢትዮጵያ ላይ ቁርጥ ያለ እርምጃ የወሰዱ ዕለት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ረጅም ርቀት ሊሄድ የማይችልና አይደለም ከካቢኔውና የክልል አመራሮች ቀርቶ ከገዢው ፓርቲ ውጭ ያሉትን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በቀላሉ ሊያሴሩበትና ሊገለብጡት የሚችል መሰረት የሌለው መሪ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ አምባገነን ሁኜ እቀጥላለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ፤ አምባገነኖች (1) ጠንካራ ርዕዮተ ዓለማዊ እውቀት መሰረትተመክሮ ያለው አንድም (2) የዋህ (naive) አምባገነን ተብሎ ከሚታወቁ ሁለት የአምባገነን ዓይነቶቹ መካከል ዐቢይ አህመድ ዓሊ የጎጃም ገብስ (ቀላልና ሚዛን የማይደፋ) ተብሎ ሊታወቅ የሚችል በሁለተኛው ዘርፍ የሚመደብ ዓይነት ሰው በመሆኑ ነው። የዐቢይ አህመድ ዓሊ ዙፋን ለመነቅነቅና ከዙፋኑ አሽቀንጥሮ ለመጣል የአዲስ አበባ ህዝብ ብቻውን በቂ ነው። ከአዲስ አበባ ጉዳይ በተያያዘ ዐቢይ አህመድ በቀናት ውስጥ ወደ ግዞት ሊወርድ ይችላል። ይህም በህይወት ተርፎ ከተሳካለት ነው።

 

(5)   ቀደማዊ ኢህአዴግ አፍርሶ ራሱ ያቋቋመው ፓርቲ በዓለም ማህበረሰብ በተለይ ከኃያላኑ አገራት ጎራ አይዞ ባይ ካገኘ፣ አገሪቱ መሪ ከማጣት የተነሳ በዓለም መድረክ እየገጠማት ያለው ኪሳራ በትክክል ከታያቸውና የህዝቡ ዕሮሮ ሳይወጠን፣ ህዝቡ እርስበርሱ ሳይባላና ሳይጨራረስ፣ አገሪቱ ፈጽማ ልትወጣው ወደማትችለው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ቁጠባዊ መቀመቅ ከመገባትዋና ሌላ ሱማሌናና ኤርትራ ከመሆንዋ በፊት፥ ሰውየውን ማስወገድ ይሻለናል! በማለት ፓርቲው ራሱ ተመልሶ ሊውጠውና ሳይለቅ እንዲለቅ አንድም በአቅም ማነስ ምክንያት በስምምነት ሊያሰናብተው (በምርጫ ሰበብ በሰላማዊ መንገድና በተጠና ዘዴ) በሃይል ሊያስወግደውና ሊገለብጠው፣ ሊገፈትረው፣ አሳልፎ ሊሰጠውና በይፋ ሊያሰናብተው ይችላል።

 

(6)   ዐቢይ አህመድ ዓሊ ስልጣኝ በቃኝ ብሎ በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን የሚለቅ ዓይነት ሰው ባይሆንም ከሌሎች አገራትና መንግስታት በመተባበር በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመው ወረራ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጽመዋል! የሚል ድምዳሜ የተገለጸው በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልና የጦር ወንጀለኝነት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ጥፋተኛ መሆኑን ከተደረሰበት ምርመራው በይፋ ከመገለጹ በፊት ውስጥ ለውስጥ በሚደረገው ድርድር ለፍርድ ከመቅረብ ይልቅ ስልጣኑ በገዛ ፈቃዱ እንዲለቅ ተደርጎ ሊሰናበት ይችላል አሻፈረኝ ካለም ወደ ፍርድ እንዲቀርብ በማድረግ ቀሪ ዘመኑ በውህኒ እንዲያሳልፍ ይገደዳል።

 

ዐቢይ አህመድ ዓሊ ሰው ነውዛሬ ብርቱ መስሎ ለመታየት ቢምክርና ድካም የለብኝም! ብሎ የሚያምን ዓይነት ሰው ቢሆንም ነገ ሌላ ቀን ነውና፥ ከተክሮ፣ ከአቅምና ከትምህርት ማነስ፣ እንዲሁም ከሰውና ከፈጣሪ ከተጣላ ኢሳይያስ አፈወርቂና ምዋርተኞቹ የአማራ ልሒቃን ክፉ ምክር ተታሎ በንጹሐን ዜጎች ላይ የፈጸመው ወንጀል አምኖ የተመለሰ እንደሆነና ሰማይና ምድር የፈጠረ አምላክ በኪነ ጥበቡ ካላተረፈውና ካልታደገው በቀር በአንድም በሌላም መንገድ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በውርደት መሰናበቱ አይቀርም። ገብቷል አይወጣም። አንድ ቀን ደግሞ የኢትዮጵያ ከተሞች ድንኳን ጥለው ታላቅ ጩኸትና ዋይታ ያሰማሉ። በንጹሐን የትግራይ ህጻናት፣ እናቶችና ሽማግሌዎች ሞትና እልቂት ያጨበጨቡ እጆች ፊታቸውን ለመቧጨርና ጸጉራቸውን ለመንጨት ይጠቀሙበታል። በተረፈ፥ ሰባተኛ ነጥብ ሊኖር ስለሚችል እጁን ይዞ ቤተ መንግስት ላስገባው ትቸዋለሁ።

 

ትግራዋይ በምሳሌ ሲያስተምር፥ ዓሻ ሰብ ንሓደ ክወቅዕ ናብ እኩብ ህዝቢ እምኒ ይድርቢ ይላል። ምሳሌው ወደ አማርኛ የመለስነው እንደሆነ፥ ሞኝ አንድ ሰው ለመምታት ሲል ወደ ተሰበሰበ ህዝብ ድንጋይ ይወረውራል እንደ ማለት ነው። ጥጉ፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ በትግራይ ላይ የፈጸመው ወረራ ሞኝ ብቻ ነው ሊያስበውና ሊፈጽመው የሚችለው። ክፉ ባለንጀራው ኢሳይያስ አፈወርቂ ደቀ መዝሙራቸው የሆነ ዐቢይ አህመድ ዓሊን አስመልክተው ችኩልና ስሜታዊ ነው ሲሉ እንደገለጹት ሰውየው በእውነትም ጥበብ ስለሚጎድልበትና በሚገባ ስላልበሰለም ጦሩን ወደ ትግራይ በማዝመት ይሄው ኢትዮጵያን እያበሰላት ይገኛል። ከዚህ የተነሳም ዐቢይ አህመድ ዓሊ በአሁን ሰዓት ማናችንም ልንገምተው ከምንችለው በላይ የሌሊት እንቅልፍ ሸሽቶት በከፍተኛ የአእምሮ ህመምና ስቃይ የሚገኝ ሲሆን፤ መያዣ መጨበጫ ያጣበት የአገሪቱ ቀውስ (በተለይ ከትግራይ ጋር በተያያዘ) በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዕልባት ለመስጠት ዘግቶም ቢሆን ለመደራደር ድምዳሜ ላይ ይደርሳል የሚል ተስፋ አለኝ። የሚያዋጣውና የሚበጀው፤ የሚያተርፈውና የሚያሳርፈው መንገድ ይህ ብቻ ነውና።

 

በተረፈ፥ እውነት ግን ይህ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሚባል ሰው በትክክል ማን ነው? በማለት ግራ የተጋባና እስከ አሁን ድረስም ስለዚህ ሰው ህቡእ ማንነት ያልተገለጠለና ያልበራለት እውነትን ፍለጋ እንቅልፍ ያጣ ዜጋ የተገኘ እንደሆነ ለዚህ ሰው ላዝለት የምችለው ፕሪስክሪፕሽን የሚከተለው ይመስላል። ይኸውም፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የሚናገርበትን መንፈስ በአግባቡ መለየት፣ የሚለውን በጥሞና በማዳመጥ፣ ገልብጠህ መረዳትና ተቃራኒውን በማሰብ የዐቢይ አህመድ ዓሊ የተደበቀ ሐሰተኛ፣ አጭበርባሪ፣ አታላይና ነፍሰ ገዳይ ማንነቱ ማወቅ እንደሚችሉ ስገልጽሎት በአክብሮት ነው።

 

E-mail: mahbereseytan@gmail.com

Back to Front Page