Back to Front Page

በተከፈተው በር ገብተን ስለ ጎንደር ፓለቲካ ትንሽ እናውራ

በተከፈተው በር ገብተን ስለ ጎንደር ፓለቲካ ትንሽ እናውራ

ኻልኣዩ ኣብርሃ 07-19-21

አቶ ኣገኘሁ ተሻገር የተባሉት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት በከፍተኛ የሽብር ስሜት ተውጠው ነገሩን ባያፈርጡት ኖሮ "የጁንታ አቀንቃኝ" እያለ ወፈ ሰማይ የሆነው ጭፍን የጥፋት አቀንቃኝ ሁሉ የምንናገረውን እውነታ መች ያዳምጣል? "ትግራይ ሊያጠፋህ ነው" እያሉ የአማራ ክልልን ህዝብ ከሚያምሱት ጥቂት ቀንደኛ ጎንደሬዎች ሁለቱ 21ኛው የመረጃ ክፍለ ዘመን ምስጢር አድርገው ያወሩትን ጉድ ሰምተናል። ይህ የመጋለጥ አጋጣሚ የእግዚአብሄር ስራ እንጂ የሰው ሊሆን አይችልም። አገሪቱ በነማን እየተመሰቃቀለች እንደሆነ የሚያሳይ ታሪካዊ መረጃ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም ቆም ብሎ ነገሮችን እንዲያስተውልና አይኑን ተጨፍኖ ወደ ገደል እንዳያመራ ይረዳው ይሆናል። እዛ ማዶ ሆኖ ዶላር በህዝብ ስም በልመና ሊያፍስና ሊያሳፍስ፣ ወዲህ ማዶ ሆኖ ደግሞ "የኢትዮጵያ ጉዳይ በኛ እጅ ነው" እያለ የስልጣን ወንበሩን ሊያደላድልና ከቻለም ሽቅብ ለመውጣት ላለው የግል አላማ የኢትዮጵያ ህዝብ መተላለቅ አለበትን? አሁን እውነቱ ፍንትው ብሎ እየታየ ነው። የጎንደር፣ በተለይ የቤጌምድር፣ ፓለቲከኞች በምእራብ ትግራይ ውስጥ ያላቸውን የማንነት ሳይሆን የኢኮኖሚ ፍላጎት እውን ለማድረግ ምንም የማይመለከተውን የጎጃምን፣ የአዊን፣ የሸዋንና፣ የወሎን ህዝብ በአማራ ስም፣ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ስም፣ እያሳበዱት ቆይተዋል አሁንም በባሰ ሁኔታ ቀጥሏል።

Videos From Around The World

ሰሊጥ እያፈሱ መክበር የፈለጉት የጎንደር ሃብታሞች የሚነዱት ፓለቲካ በአማራ ህዝብ ዘንድ ከትግራይ ወረራ ራስን የማዳን ዘመቻ እንዲመስል ሆኖ ስለተቀመረ ህዝቡ እስካሁን ድረስ አይኑን ትግራይ ላይ ተክሎ ምርት እንዳያመርት፣ ሰርቶ እንዳይበላ፣ ኑሮውን እንዳያሻሽል፣ ጠመንጃ አምላኪ እንዲሆንና ሃሳቡ ሁሉ ትግራይን መውጋትና ማጥፋት ብቻ እንዲሆን አድርገው ማደንዘዣ ወግተውታል። የማንነት ጥያቄ ቢሆንማ የምእራብ ትግራይ ህዝብ ትግራዋይ አይደለም እንዴ? ይህ እኮ ሳይንሳዊ ምርምር አያስፈልገውም። የህዝብ ቆጠራን ውጤትና ለዘመናት የኖረውን የመንደሮች ስያሜ ከስታቲስቲክስ /ቤት ማግኘት በቂ ነው። ማይ ፀምሪ ብሎ፣ ዓዲ ረመፅ ብሎ፣ ዓዲ ጎሹ ብሎ የአማራ መሬት ምን አይነት ድርቅና ነው? ሲሻቸው "በረራ" ነበረችኮ ፍንፍኔ ይሉና አማራ ያደርጓታል። ዓዲ ረመፅንም አማራ ይሏታል! እንደዛ ከሆነ ጎዴም አማራ ናታ! "ጤፍ ካለው ይልቅ አፍ ያለው ያግባሽ" ተብሎ የለ? አማርኛው የነሱ ነውና ሲፈልጉ ይሰብሩበታል፣ ሲፈልጉ ይጠልፉበታል፣ ሲፈልጉ ያጭበረብሩበታል፣ ሲፈልጉ ያደነዝዙበታል። ህገ መንግስቱን ወደ ጎን ትተን እነሱ በሚሉት መከራከሪያ እንኳ ብንሄድ ምእራብ ትግራይና ደቡብ ትግራይ በጎንደርና በወሎ እጅ የቆዩት 35 አመታት ብቻ ነው። ይህ ማለት 1948 እስከ 1983 መሆኑ ነው። ትግራይን በኢኮኖሚ ለማዳከምና የጎንደርና ወሎ ገዢዎች ከፍተኛ የግብር ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ በተደረገ የአፄ ሃይለስላሴ ሴራ ነው ተላልፈው የተሰጡት። የምእራብ ትግራይ ወራሪዎችኮ መሬቱ የነሱ አለመሆኑ አሳምረው ያውቃሉ። ለዚህም ነው ትግራይ ለህዝቡ የሰራችውን የመሰረተ ልማቱን ያጠፉትና የዘረፉት። የራስ ቤት ይወድማል፣ ይዘረፋል? የሚፈልጉት የሁመራን የሰሊጥ መሬትና ከኤሪትርያ ወደብ (ምፅዋ) ጋር የሚያገናኛቸውን ኮሪዶር መቆጣጠር ነው።  የምእራብ ትግራይ ህዝብ አማራ ነው ቢሉም ስለ ልማቱ ጉዳያቸው አይደለም። በጃቸው ላለው ቀሪው የአማራ ህዝብ ምን አደረጉለት? "የኢትዮጵያ ፈጣሪ፣ መከታ፣ አለኝታ አንተ ብቻ ነህ ሌላው አገር አፍራሽ ነው" እያሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲያነካክሱት ከመኖራቸው በስተቀር።

ጎጃምና ወሎ አንዋጋም ማለቱን እንደፈሪ የራሳቸውን የበጌምድር ታጣቂን የሚያኮራ ጀግና አድርገው የፈረጁት የጋይንት (በጌምድር) ተወላጅ የሆነውን የታማኝን ልብ ለማሞቅ መሆኑ ግልፅ ነው። ታማኝ በየነ ከበጌምድር አፍንጫው አልፎ ራቅ አድርጎ የሚያይበት አይን እንደሌለው የታወቀ ነው። ተክሌ የሻው የሚባለውም የደርግ ካድሬ የነበረ ሌላው የጋይንት ቱሪናፋ ነው። ከጎንደር ውጪ የመጣውን ሁሉ "መጤ" የሚል ከመርፌ ቀዳዳ የጠበበ ሰው ነው። ጎንደር አንድ እንዳልሆነ ታሪኩ የትላንት ነው። ስሜንና በጌምድር ለየቅል ነበር። ከዛ አልፎም የበጌምድር ሰዎች ስሜነኞችን የመናቅና ማንኳሰስ ባህል ነበራቸው። ስሜን ማለት ስሜን አውራጃንና ወገራ አውራጃን ያጠቃለለ ሲሆን አሁን ምእራብ ትግራይ የሆኑት ወረዳዎች በስራቸው ነበሩ። ሰሜንና በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በመባል ቢታወቅም አገዛዙን በሞኖፓል ይዘው የኖሩት የበጌምድር (ደብረ ታቦር፣ ጋይንት፣ ሊቦ አውራጃዎች) ልሂቃን ነበሩ፣ አሁንም ያው ነው። በምእራብ ሰፊ ግዛት የያዘው ቀሪው አውራጃ የቅማንቶች አገር የሆነው ጭልጋ ነበር። ይህ በሁለቱም የተገለለ ግን የመተማን መሬት ለማረስ ቆርጠው የሚሄዱበት ነው። የበጌምድር ሰዎች ጎንደር ከተማ ላይ የነበራቸው የአገዛዝ የበላይነት አልበቃቸው ሲል ከጠቅላይ ግዛቱ ስም ስሜን የሚለውን ፍቀው በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ብቻ እንዲባል አደረጉት። ደርግ ሲመጣ ለጊዜው የልብ ልብ ያገኙት ስሜነኞች የክፍለ ሃገሩን ስም በዋና ከተማዋ ጎንደር እንዲሰየም አስደረጉ። ይህ ግን የበጌምድሮችን የበላይነት አላስቀረላቸውም። ሻለቃ መላኩ ተፈራ የክፍለ ሃገሩ አስተዳዳሪ ከሆነ በኋላ የክፍለ ሃገሩን አስተዳደር የሃይማኖቱን ሳይቀር በደብረታቦር ሰው አጨናነቀው። ነፃ እርምጃና ቀይ ሽብር የተካሄደውም በጎንደር ከተማና በስሜነኛ ወጣቶች ላይ እንጂ ደብረታቦር ሆነ ጋይንት ከወላፈኑ ርቀው ልጆቻቸውን ለወግ መአርግ አብቅተዋል። ጎንደር ክፍለ ሃገርን ብቻ ሳይሆን በጌምድር በደርግ ጊዜ የቤተክርስትያንኗን ማእከላይ አስተዳደር ተቆጣጥረው ነበር። ለዚህም ነው በአቡነ ጳውሎስና በአቡነ ማትያስ ላይ በግንባር ቀደምትነት የፀረ ትግራይ ጦር የመዘዙት። ቆየት ብሎም የፀረ ትግራዩ ዘመቻ ወልቃይት የሚል ሌላ አዲስ ግንባር የከፈተው። ሁለቱም ግንባር የጎንደር ስሪት ነው። "ሻለቃ መላኩ ባያሳድደን ኖሮ አሜሪካ ገብተን ከበርቴ አንሆንም ነበር" በማለት ባለውለታነታቸውን እየገለፁ መላኩ በፈጃቸው ወጣቶች ሰማእትነት ላይ የሚያላግጡት ዳያስፓራውን ያጥለቀለቁት የጎንደር ዳያስፓራ አባላት ናቸው። የአማራ ጀግንነት ሲነሳ የሚዘፈነው የጎንደር ዳንኪራ ብቻ ነው። በተረጋጋ አእምሮ ነገሮችን ያስተዋለ ሰው የሚገነዘበው በአማራ ስም በትግራይ ላይ የተነሳው ጎንደሬ መሆኑን ነው። የሚያስደምመው ነገር ግን በትግራይ ላይ የዘር ማጥፋት አጥብቆ ሲሰብክ የከረመው በትግራዩ አፄ ዮሃንስ በደል ደርሶብኛል የሚለው የጎጃም ህዝብ ሳይሆን አፄ ዮሃንስ ከድርቡሽ ጥፋት የታደጉት የጎንደር ውለታቢስ ነው። ታማኝ በየነ የቆመው ለፍትህ ከሆነ ቀልድ ነው። መላኩ ተፈራ የጎንደርን ወጣት ሲጨፈጭፍ ገዳዩን በዛ ስል ምላሱ መድረክ ላይ ወጥቶ ሲያሞጋግስ የነበረ ነው። አሁን የጎንደርን ህዝብ ከትግራይ ጥቃት ለመከላከል በሚል ዶላር የሚሰጡት ጎንደሬዎች ያልተነኩ ያልተነካኩትና ከሞት ያመለጡት ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። በመላኩ የተጨፈጨፉትማ መሬት ውስጥ እንጂ ዳላስና ዋሺንግተን አይገኙም። ወላጆቻቸውም የድህነት ኑሮ ይመራሉ እንጂ አመት እየጠበቁ "በቪዚት" አይዝናኑም። እንግዲህ ልብ በል የአማራና መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ማን ወደ ጥፋት እንደሚነዳህ ጠንቅቀህ ተገንዘብ። የጎንደርንና የስሜንን ህዝብ ከመላኩ ፍጅት በተራ መንደርተኝነት፣ ያልታደገው ታማኝ በየነ የጎንደርን ህዝብ ከትግራይ "አደጋ" እጠብቃለሁ ቢል ተቀባይነት የሚኖረው የመላኩ ጥይት ቅቤ፣ የትግራይ ጥይት ግን እሳት ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው። ሃቁ ግን የትግራይ ጥይት በህዝብ ላይ ቅቤ ሲሆን የመላኩ ጥይት ግን እውነተኛ እሳት ነው።

Back to Front Page