Back to Front Page

ግልፅ ደብዳቤ ለሌ.ኮሎኔር ኣቢይ ኣህመድ

 

ግልፅ ደብዳቤ

ለሌ.ኮሎኔር ኣቢይ ኣህመድ

 

ካሌብ ባራኺ (ዶ/ር) ኣዲስ ኣበባ ጥር 26፣2013 ዓ.ም

 

በሃዋሳ ከተማ በተደረገው የኢህኣደግ ጉባኤ የደርግን ስርዓት በመደምሰስ ይቅር በሕዝብ ኣስተዳደር ወይም ፖለቲካዊ ስራዎች ላይ የጎላ ኣስተዋፅኦ ያልነበርዎት ኣንዳንዶቹን convince ሌሎችን ደግሞ confuse በማድረግ በሴራ ሊቀመንበር ሆነው መመረጥዎ፤በኢህኣደግ ዘመን የዚህቺን ጥንታዊት ሃገርና ታላቅ ህዝብ 4ኛው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ኣድርጎታል፡፡ ስልጣን እንደጨበጡ የወንጌላውያን ልሳን በሚመስል ያደርጉዋቸው በነበረው ዲስኩሮች ፍቅር፤ ሰላም፤ እርቅ፤ መቻቻል፤ ዴሞክራሲ፤...ወዘተ ኣባባሎች ያመዘኑ ስለነበር፤የትግራይ ህዝብ ከወንድሞቹ የኤርትራ ህዝቦች ለ18ዓመታት የቆየውን ሰላምም ጦርነትም ኣልባ ሁኔታ ለመለወጥ ያሳዩትን ተነሳሳሸነት፤የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትና ከሃገር ውጭ በስደት የነበሩ ታጣቂ ሃይሎች ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ እርምጃዎች በመውሰድዎ የኢትዮጵያ ህዝቦች ልብ ገዝተው ነበር፡፡የትግራይ ህዝብና መንግስትም ድጋፋቸውን ሰጥተዎት ነበር፡፡ህወሓትም ወታደራዊና የደህንነት ተቋማትን በበላይነት በተቆጣጠረበት ሁኔታ ለእርስዎ ይሁንታውን የሰጠው በህዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተውን እና ለሃገራዊ ኣንድነት ዋስትና የሚሰጠውን ሕብረ-ብሄራዊ ፈደራሊዝምና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ያስቀጥላሉ ብሎ በመተማመን እንጂ "በህፃንነቴ እናቴ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ንጉስ ትሆናለህ ብላኝ ነበር " የሚሉትን ትንቢት ይፈፀም ዘንድ መንበረ-ስልጣን እንዳልጨበጡ ህሊናዎ ይገነዘበዋል ብየ እገምታለሁ፡፡

Videos From Around The World

ሆኖም ተወዳጅነትዎና ተቀባይነትዎ እምብዛም ሳይቆይ እንደጉም በነነ፡፡ "ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያም ያለ ትግራይ መኖር ማለት መኪና ያለ ሞቶር " እንደሆነ ነው ብለው በ2010 ዓ.ም. በመቀለ ከተማ ያደረጉትን ንግግር ትግራይና የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ሃገር ግንባታ ሂደት የነበረውና ያለውን ሚና በትክክል በገለፁበት ኣንደበትዎ ብዙ ሳይቆዩ በተጋሩ ላይ ያነጣጠሩ በደሎችና ግፎቸች መፈፀም እንደ ስትራተጂ ተያያዙት፡፡ተጋሩ በማንነታቸው እንድያፍሩ፤ኣንገታቸውን እንዲደፉ፤የፈጠራ ዶኩመንታሪዎችን እያሰሩ የጥላቻ ንግግሮች እንዲነዙ ኣደረጉ፡፡ የኢህኣደግ ጉድለቶችን በማረም ጠንካራ ጎኖቹን ከማጎልበት ይልቅ ለሁሉም ጉድለቶች ህወሓትን፤ የህወሓት ኣመራሮችንና የትግራይን ህዝብ ተጠያቂ የማድረግ ዘመቻ ኣወጁ፡፡ በሃገር መከላከያ ሚኒስቴርና ሲቪል መስርያ ቤቶች ይሰሩ የነበሩትን ብዙ ፕሮፈሽናል ተጋሩ ያለ ምንም ማስረጃ እስር ቤቶች ኣጎሩዋቸው፡፡የሃገሪቱን ህግ መሰረት በማድረግ ፍትሃዊ ዳኝነት በመስጠት በነፃ እንዲለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸውን እንዲከበርላቸው የተሰጡ የዳኞች ውሳኔዎች እንዳይተገበሩ እርስዎ በሚሰጡት ቀጥታ ትእዛዝ በጠቅላይ ኣቃቤ-ህጎዎ ኣማካኝነት ኣሰልቺ የፈጠራ ክሶች በየግዜው ይፈበረካሉ፡፡በኣማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚኖሩ ተጋሩ ኢላማ እንዲሆኑም ተደረጉ፤ ታሰሩ፤ ተገደሉ፤ ተፈናቀሉ፤ንብረታቸው እንዲቃጠል ተደረገ፡፡በኣማራ ክልል ባለስልጣኖች ወደ ትግራይ የሚወስዱ የየብስ መስመሮች ከሁለት ኣመታት በላይ እንዲዘጉ ሲያደርጉ እርስዎ ዝምታን ቢመርጡም፤ የሰላሌ ቄሬዎች ከኣዲስ ኣበባ ወደ ጎጃም የሚወስደውን መንገድ ሲዘጉ ግን በሰኣታት ውስጥ የፈደራል ፖሊስ ሃይል ልከው ድርጊቱን ቀልብሰዋል፡፡ የእርምጃው ተገቢነት ኣጠያያቂ ኣይደለም፡፡ጥያቄው የትግራይ ህዝብ ለምን በእንጀራ ልጅ ደረጃ ያዩታል ? የሚል ነው፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በትግራይ እንዲሰሩ በፈደራል መንግስት የተያዙ የልማት ፕሮጀክቶች ኣንዴ "ብድር ኣልተገኘም"፤ሌላ ጊዜ ደግሞ "ፕሮጀክቱ አዋጪ ኣይደለም" እየተባለ እንዲቋረጡ በማድረግ ብቻ ሳይሆን ትግራይን ለኢንቨስትመንት የመረጡ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ ጉዞ እንዳያደርጉ በመከልከልም የትግራይን ኤኮኖምያዊ ኣቅም ሆን ብለው ለማዳከም ኣሲረዋል፡፡ከትግራይ ውጭ በንግድና እንቨስትመንት በተሰማሩ ተጋሩ ላይ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲበረበሩ ኣስደርገዋል፡፡ 'የለውጥ ሃይል' ተብዬ ከፍተኛ ኣመራሮች በኣደባባይ "ተጋሩ ኣዲስ ኣበባ ያፈሩትን ሃብት ትግራይ ላይ ነው ኢንቨስት የሚያደርጉት" እያሉ ያለኣግባብ ከፍተኛ ግብር እንደሚጫንባቸው፤ በመንግስት ግዢ ጨረታዎች ግልፅ ኣድልዎ እንደሚደረግባቸውና የሁለተኛ ዜጋ ስሜት እንዲሰማቸው እየተደረጉ እንደሆነ የትግራይ ባለሃብቶችን ጠርተው ባወያበት ወቅት ስለተነገርዎት "ኣላውቅም" እንደማይሉ እገምታለሁ፡፡

የትግራይ ህዝብ የደርግን ስርኣት ለመደምሰስ ለከፈለው ከፍተኛ መስዋእትነት፤ለደረሰበት ሰብኣዊ ቀውስ፤ ለወደመበት የማህበረ-ኤኮኖሚየዊ መሰረተ-ልማቶች ከፈደራል መንግስት ምንም ኣይነት ማካካሻ ወይም ካሳ ሳይደረግለት ኮረብታዎችን እየደለደለ፤በትግራይ ባለሃብቶችና ዲያስፖራዎች ከፍተኛ ተሳተፎ በገጠር ወረዳዎቸና በከተማዎች የተገነቡትን መሰረተ-ልማቶች "በወያኔ የበላይነት ዘመን ትግራይን የጠቀመ ኢ-ፍትሃዊ ሃገራዊ የሃብት ክፍፍል ስለነበር የማስተካከያ እርምጃዎች ይወሰዳል" በሚል የፈጠራ ፕሮፖጋንዳ የትግራይን ኤኮኖሚያዊ ኣቅም ለማዳከም የፈደራል ፈንድ በእጅጉ እንዲቀነስ ኣድርገዋል፡፡ የኣንበጣ ወረራ ለመከላከል በተጋሩ ዲያሰፖራዎች የተገዙ ድሮኖች ማሳዎች በኣንበጣ እንዲወረሩ ወደ ትግራይ እንዳይላኩ ከልከለዋል፡፡ከኤርትራ መንግስት ጋር ተደረገ የተባለው 'የሰላም ስምምነት' ግልፅነት የጎደለው፤የኢትዮጵያ ህዝቦች የማያውቁት፤ስለኣፈፃፀሙም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያልተወያየበት፤ ይልቁንም ፕረዚዳንት ኢሳያስ በትግራይ ህዝብና በህወሓት ኣመራር ላይ ያላቸውን ጥላቻና ቂም ለመወጣትና ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዘመቻ ላይ እርስዎና መንግስትዎ ግንባር ቀደም ተዋንያን ሆናችኋል፡፡

በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል የሚፈጠሩ ያለመግባባቶች ሕገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ በውይይት መፍታት ሲገባና ሲቻል ለሁለት ዓመታት ከፕረሲደንት ኢሳያስ ኣፈወርቂ ጋር በማበር በተመረጡ የትግራይና ኤርትራ ድንበሮች ላይ፤ በወልድያና ጎንድር በቂ የሰራዊትና ሎጂስቲክስ ዝግጅት መጠናነቁን እንዳረጋገጣቹህ ያወጣችሁትን የዘመቻ እቅድ ለማስፈፀም የኣለምን ኅብረተሰብ ቀልብ ወደ የኣሜሪካው ፕረሲደንት ምርጫ ባደረገበት ወቅት ምቹ ጊዜ መሆኑን መርጣቹህ "የሰሜን እዝ በጀርባው ስለተወጋ 'በወያኔ ጁንታ' ላይ ሕግን የማስገበር ዘመቻ " በሚል ሰበብ በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ኣውጃችሁበታል፡፡ ይህንን እኩይ ተግባር ለማስፈፀም የኢትዮጵያ ህዝቦችን ኣታልለዋል፡፡ በዚህ ቀዳማይ ወረራ 42 የኤርትራ ክፍለ-ጦሮች፤ኤርትራ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና ይወሰዱ የነበሩትን 3000 የሶማልያ ምልምል ጦር፤14 የፈደራል መንግስት ክፍለ-ጦሮች፤የተባበሩት ኣረብ ኤምሬትሰ ድሮኖች እንዲሁም በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የኣማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ሰራዊት፤ ከፊል የኦሮምያ ልዩ ሃይል ተሳትፈዋል፡፡ በቅርቡም የትግራይን ህዝብ ለማጥፋትና፤ የቀሩትን ኤኮኖምያዊና ባህላዊ ሃብቶችን የማውደም ሙሉ ትግራይን የሚያዳርስ የኤርትራ፤ የፈደራልና የኣማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ የተሳተፉበት መጠነ-ሰፊ ወረራ እያካሄዳቹህ ነው፡፡

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን ደህንነት የሚጎዱ መረጃዎችን ኤርትራ ለነበረው የኦነግ ሃይል ይሰጡ እንደነበር [ለግብፅም ይጠረጠራሉ] በኩራት መናገርዎ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ስለሆነ "ኢትዮጵውያን short memory ስለሆኑ ነገሮችን የመርሳት ችግር ኣለባቸው" የሚሉትን ኣባባል ኣላስቸገረንም፡፡ ይህ ሃገራዊ ክህደት ሳያንስ ኣሁን ደግሞ የስልጣን ፍላጎትዎን ለማርካት ሲባል ብቻ የኤርትራ ሰራዊትና ደህንነት ሃይል ኢትዮጵያን እንዲቆጣጠሩ ማድረግዎ ተጨማሪ ሃገራዊ ክህደት እየፈፀሙ ነው፡፡ ትግራይን በ360 ዲግሪ ከቦ በሶስት ሳምንታት ውስጥ የትግራይን ህዝብ ለመደምሰስ ያወጣችሁትን ወታደራዊ እቅድ ለመተግበር ምዕራብ ትግራይና ሱዳንን የሚያዋስኑትን ኣከባቢዎች የሱዳን መንግስት ይዘጋልዎት ዘንድ የኣል-ፋሻቃ ትሪያንግልን "በሰጥቶ መቀበል" መርህዎ መሰረት ስጦታ ማበርከትዎ ተጨማሪ ሃገራዊ ክህደት ፈፅመዋል፡፡ የሚከተልዋችው ዲፕሎማሲ ስራዎች የኬንያው መሪ "childish"ያልዎትን በመድገምዎ የህዳሴው ግድብ ህልውና ላይ ኣደጋ ፈጥረዋል፡፡

"ወያኔ መጥፋት ኣለበት፤ የትግራይ መንግስት የራሱን ምርጫ ማድረግ የለበትም" ካሉት የኤርትራው ፕረዚደንት ጋር በማሴር የከፈቱትን ጦርነት ከ80 ሺ በላይ ለስደት፤ለ50 ሺ በላይ ሰላማዊ ህዝብ ሞት፤ለ2.5-3.0 ሚልዮን የውስጥ መፈናቀል፤ለ5 ሚልዮን በላይ ለረሃብ ፤ለብዙ ሺ ተጋሩ ሴቶች መደፈር፤ በመቶ ቢልዮን ብር የሚገመት መሰረተ-ልማትና ሃብት ውድመት. ዳርጓል፡፡የኤርትራ ሰራዊት ባደረበት ቦታ ምሽግ ቆፍሮ ዙርያውን በፈንጅ የማጠር ልምድ ስላለው ትግራይ ኮረብታዎችና ማሳዎች ፈንጅ ዘርቶባቸዋል፡፡ ይህን ኣስከፊ ሰብኣዊ ቀውስ ያሳሰባቸው ኣለም ኣቀፍ በጎ-ኣድራጊ ድርጅቶችና የተባበሩት መንግስታት ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ያደርጉ ዘንድ መንግስትዎን ከኣንድ ወር በላይ ቢጎተጉትዎትም እንቢተኝነቱን ኣጠናከረው ቀጥለውበታል፡፡ ወታደሮችዎና እርስዎ የጋበዙዋቸው ወራሪዎች በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፅሙትን እልቂት፤ዘረፋፋና ውድመት የዓለም ህዝብ እንዳያውቅ መገናኛ አውታሮች (እንተርኔትና ቴሌፎን መስመሮች፤ መንገድ፤) ዘግተውበታል፡፡

በሰራዊትዎና በኣማራ ወራሪ ሃይሎች በማይ ካድራና በሌሎች የወልቃይትና ፀገደ ኣከባቢዎች በተጋሩ ላይ የተፈፀሙ ዘር የማጥፋት ድርጊቶች 'የኣቢየን ለእምየ' እንዲሉ "በጁንታው የታጠቁ ወጣቶች በኣማሮች ላይ የጅምላ ግድያ ተፈፅሟል፡፡ወደ ሱዳን የሸሹትም እነዚህ ወጣቶች ናቸው፡፡ ጁንታው የጦር ወንጀል ፈፅሟል" በማለት በሞኖፖል በተቆጣጠሩዋቸው የሚድያ ማእከላት ኢትዮጵያውያንና ዓለምን ለማታለል ሞክረዋል፡፡ በእርስዎ የተሸሙት የኢትዮጵያ[የኣማራ] ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ተብየው ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ቃልዎን እንደ ገደል ማሚቶ ኣሳምሮ ኣጭሆሎታል፡፡ የዓለም ህዝብ እውነቱን እንዲያውቅ ጉዳዩ በገለልተኛ ኣካል እንዲጣራ ቢጠይቆትም እምቢተኛ ሆነዋል፡፡ ያገሬ ሰዎች "ሓቂ ትቀጥን እምበር ኣይትስበርን " እንደሚሉት ሆነና በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት፤ዓለም ዓቀፍ ሰብኣዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና በጎ ኣድራጊ ድርጅቶች በህፃናትና ሴቶች ተጋሩ በተጥለቀለቁት የሱዳን ስደተኛ ካምፖች ያደረጉዋቸው ጥናቶች በተጋሩ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መደረጉን ኣረጋግጠዋል፡፡

በትግራይ እየደረሱ ያሉትን ሞት፤ውድመት፤ሰብኣዊ መብት ጥሰቶችና ረሃብን እንደ ጦር መሳርያ መጠቀምዎን፤የተባበሩት መንግስታት፤ሰብኣዊ መብት ተሟጓቾች ፤የኤውሮፓ ህብረት፤የተባበሩት ኣሜሪካ መንግስታትና ኣለም ኣቀፍ የሃይማኖት ተቋማት፤የኤርትራ ፍትህ ፈላጊ ንቅናቄና ዲያስፖራ ሲኮኑኑትና የኤርትራ ጦር ከትግራይ ኣሁኑኑ እንዲወጣ ኣጥብቀው ሲጠይቁ፤ እንዲሁም የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስትያን ስለ ርትእና ፍትህ ስትል በድፍረት የኤርትራ ወራሪ ሰራዊት ከትግራይ ተዘርፈው የተወሰዱትን ንብረቶች ኤርትራውያን እንዳይገዙ ስትገዝት፤ እርስዎ እና መንግስትዎ ግን "የኤርትራ ሰራዊት ወደ ትግራይ ኣልገባም፤ ኣንድም ሰው ሳይሞት ሰርጀሪ ኦፐሬሽን ነው ያደረግነው" ሲሉ ለፓርላማዎ በትእቢት ሲደሰኩሩ ተደምጠዋል፡፡ የህገ-መንግስቱ ትሩፋቶች የሆኑትን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የፈደሬሽን ምክር ቤት፤የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፤የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት፤የሃገር ሚድያዎች ...ወዘተ ኣንዳንነዶቹ "ግፋ በለው" ሲሉ ተደመጠዋል ሌሎቹ ደግሞ ዝምታን መርጠዋል፡፡ የእርስዎ ኣማካሪ የሆነውና በማኅበረ-ቅዱሳን ኣማካኝነት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያንን ሲኖዶስ የተቆጣጠረውን ዲያቆን ዳኒኤል ክብርት ትግራይን ማውደምና የትግራይ ህዝብን መግደል " የኢትዮጵያ ከፍታ" ማሳያ ኣድርጎ መቁጠሩ የኣማራ ሊህቃን ዝቅጠት ያመለክታል፡፡

በሁሉም ወራሪ ሃይሎች በትግራይ ሴቶች ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ጥቃቶች የኣለም ህብረተሰብ በማውገዝ ላይ ባለበት ወቅት፤እንዲሁም ኣንድ የጦር መኮንንዎ በመቀለ ከተማ ወታደሮችዎን ሰብስቦ በስቅታ " በሰላማዊ ሁኔታ እያለን በከተማ እንዴት ሴቶችን ትደፍራላቹሁ?! " ማለቱን በማህበራዊ ሚድያ የኣደባባይ ሚሰጥር በሆነበት ጊዜ የሴቶችና ህፃናትና ወጣቶች ዲኤታ ሚኒስትርዎ ግን በማስረጃ ያልተደገፈ ወሬ ነው ሲሉ በትዊተራቸው መግለፃቻው የትግራይን ህዝብ መናቅና፤ የኢትዮጵያን ህዝቦችን ማታለል ብቻ ሳይሆን ኢ-ሰብኣዊነትም ነው፡፡ ክብርት የኢ.ፈ.ዲ.ሬ. ፕረዚደንት፤ የሰላም ሚኒስትርዎ፤የኢትዮጵያ ሴቶች የሕግ ማህበር ኣመራሮች፤ በሃገሪቱ በሴቶች ጉዳይዮች የሚንቀሳቀሱ ማህበራትወዘተ "በእህቶቻችንና ልጆቻችን እየደረሰ ያለውን የፆታ ትንኮሳ ኣሳሰቦናል" ሲሉ በትላልቅ ሆቴሎች በሚደረጉ ስብሰባዎች ነጋ-ጠባ ሲደሰኩሩ ሲደመጡ በትግራይ በኣንዲት ሴት ላይ እስከ15 የኤርትራ ወታደሮች እየተፈራረቁ ክብር ዋን ስትደፈር፤ የገዳማት ደናግል በወታደሮች ፆታዊ ጥቃት ማድረስ ዕለታዊ ክስተት ሆኖ እያበሆነበት ሁኔታ ግን ዝምታን መርጠዋል፡፡ በጦረኝነትና በጥላቻ መንፈስ የታወሩት መንግስትዎና ፓርቲዎ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትና ብዙዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነን ባዮች "የትግራይን ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው፤ ወገናችን ነው"ለማለት ከቶውንም የሞራል ብቃት ሊኖራቹሁ ኣይችልም!!

በእርስዎ ጋባዥነት የኤርትራ ሰራዊት ትግራይን መውረሩ፤ተጋሩን መግደሉና መዝረፉን ያደባባይ ሚስጢር ሆኖ እያለ እርስዎና ሹሞኞችዎ ክህደትን መርጣቹኋል፡፡የኢትዮጵና የትግራይ ህዝቦች የምትሉትን ሁሉ እንዴት ሊያምናቹህ ይችላል? ይህ ድርጊት በርስዎ ኣምባገነናዊ ኣገዛዝ ሆኖ ነው እንጂ በሃገር ክህደት የሚስጠይቆ ነው፡፡

እርስዎና መንግስትዎ የትግራይን ህዝብ ኣምበርክኮና ኣሻንጉሊት የትግራይ ክልላዊ መንግስት በመፍጠር የሃገሪትዋን ህልውና ማስቀጠል እንደማይቻል በመገንዘብ የሚከተሉትን እርምጃዎች በኣስቸኳይ ይወስዱ ዘንድ እጠይቃሁ፡፡

1. ጦርነቱ ኣሁኑኑ ማስቆምና የኤርትራ፤የሶማልያና የኣማራ ሰራዊቶች ከትግራይ ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ ባስቸኳይ ማስወጣት፤

2. "የትግራይን ህዝብ በርሃብ መግደል እንደ ወታደራዊ መሳርያ የመጠቀም" ስትራቴጂዎ በቅፅበት ማቆም፤ሁሉም የትግራይ ወረዳዎችና ከተሞች ለዓለም ኣቀፍና ኣገር-በቀል የእርዳታ ድርጅቶች ክፍት እንዲሆኑና የእርዳታ ስርጭቱንም በቀጥታ እንዲቆጣጠሩት መፍቀድ፤የእርዳታው ክፍፍል ሂደት ቀልጣፋና ፍትሃዊ ይሆን ዘንድም የትግራይ ህዝብ በባይቶው ኣማካኝነት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን እድል መስጠት፡፡

3. በኤርትራ፤በኣማራ እና በመንግስትዎ ወራሪ ወታደሮች በትግራይ ሴቶች ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ጥቃቶች፤የሰላማዊ ዜጎች ግድያና ዝርፍያዎች ኣሁኑኑ ማሰቆም፡፡በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ሁሉም ዓይነት ግፎችና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች በተባበሩት መንግስታት የሚቋቋም ገለልተኛ ኣካል እንዲጣራ መፍቀድ፡

4. የመብራት፤ቴሌፎንና ሞባይል፤ ትምህርት፤ጤና፤ባንክ፤ውሃ፤መጓኋዣ፤...ወዘተ መሰረታዊ ግልጋሎቶች ለህዝቡ በኣፋጣኝ እንዲደርስ በቂ በጀት መመደብ፤ሰንካላ ሰበብ በመፍጠር ግልጋሎቶች እንዳይቋረ ማድረግ፤

5. የትግራይ ህዝብ ያለ ምንም ገደብ በትግራይና፤ በሁሉም ክልሎች የመንቀሳቀስ እንዲሁም ውጭ ሃገር የመውጣትና ከውጭ ሃገር ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ህገ-መንግስታዊ መብት ማክብር፤

6. በወራሪ ሃይሎች የተዘረፉ የትግራይ ህዝብ ንብረቶች በገለልተኛ ኣካል እንዲጠና መፍቀድና፤ ተመጣጣኝ የጉዳት ካሳ መስጠት፤

7 በፓርቲዎና በመንግስትዎ ትእዛዞች በተጋሩ ላይ ማንነትን መሰረት በማደረግ ለደረሱ ጥቃቶች በይፋ ይቅርታ መጠየቅ፤ጉዳት ለደረሰባቸውም መካስ፤በእስር ላይ ያሉትን ተጋሩ ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ በኣስቸኳይ መፍታት፤ከስራ የተባረሩትን እንዲሁም በክራይ ይኖሩበት ከነበረ መንግስት ወይም ቀበሌ ቤቶች እንዲወጡ የተደረጉትን ተጋሩ መብታቸው እንዲከበር ማደረግ፤

8. በመንግስት ሃላፊዎችና ሹመኞች በተጋሩ ላይ የሚደርስባቸውን ኣድለዎ መኮነንና በተግባር ማሳየት፤

9. በወራሪ ሃይሎች በተለይም በኤርትራ ሰራዊት ሃይማኖታዊ፤ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን የማውደም ዘመቻ ባሰቸኳይ ማሰቆም፤ከለላ ማድረግ እና የተዘረፉትንም ማስመለስ፤

10. "ጁንታው ተቀብረዋል፤ጦርነቱ በድል ተጠናቅቋል" የሚሉትን ማታላያ ዲስኩሮች ከመደስኮር በሃገሪቷ የደረሰውን ሁለንተናዊ ቀውስ ለመፍታት ለፖለቲካዊ መፍትሄ ቅድሚያ መስጠትና በኢ.ፌ.ዲ.ሬ. ሕገ-መንግስት መሰረት የትግራይን ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ማከበር፡

11. ለኢትዮጵያ ነፃነት፤ ሉዓላዊነትና ኣንድነት ልዩ መስዋእትነት ለከፈለ የትግራይ ህዝብ በባዕድ ሃይሎች(ኤርትራ፤ ሶማልያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት) እንዲሁም ወገኔ በሚላቸው የኣማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ሰራዊት እንዲወረርና፤ እንዲገደል፤ የሃገሪትዋን ሉኣላዊነት እንዲደፈር በማድረግዎ በይፋ ለትግራይና ለኢትዮጵያ ህዝቦችን ይቅርታ ጠይቀው በኣስቸኳይ ስልጣን መልቀቅ፤

 

 


Back to Front Page