Back to Front Page

የስድቡ ግንባር፣ ህወሓት የወጡላት ከደርዘን በላይ መጥፎ ስሞች

የስድቡ ግንባር፣ ህወሓት የወጡላት ከደርዘን በላይ መጥፎ ስሞች

ኻልኣዩ ኣብርሃ 07-23-21

በጨዋው መንደር ስም ማጥፋትን፣ ስድብን የሚያነውሩ ብዙ አይነት አባባሎች አሉ። ለአብነት ያህል "ከአፍ የሚወጣ እንጂ ወደ አፍ የሚገባው አያረክስም" ይባላል። ይህ ስለምግብ ወይንም ስለመጠጥ የተነገረ አይደለም። ከአፍ የሚመለስ ምግብ አስቀያሚ ቢሆንም ወደ አፍ የሚገባው ምግብና መጠጥ ሁሉ የጤና ችግር አያስከትልም ማለት አይደለም። ይህ አባባል ከአፋችን ስለሚወጣው ከትውከት የበለጠ የሚያስጠላው ክፉ ቃልን የሚመለከት ነው። መማሪያ ክፍል ውስጥ በገባ ቁጥር ተማሪዎችን በስድብ የሚያዋክብ አንድ አስተማሪ ይህን ድርጊቱን ያየ ጓደኛው "በስድብ ነው ለካ አፍህን የፈታኸው" ብሎ ይተርበው ነበር። ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው። ገና አፍ ሲፈቱ ስድብ የሚያስተምሩ ወላጆች እንዳሉ ሁላችንም የምናውቀው ነው። ልጅ ሲሳደብ በአድናቆት መሳቅና "እሰይ ልጄ አፍህን ፈታህልኝ" ብሎ ፈጣሪን ማመስገን የተለመደ ነው። ታድያ በዚህ ሰልጥኖ ያደገ ልጅ የኋላ ኋላ  የሃገር መሪ ይሁን በረንዳ አዳሪ ዘወትር ከአፉ የሚወጣው ስድብ ነው። ከድሮ ጀምሮ አንድ የኢትዮጵያ አካባቢ በተሳዳቢነት የሚታወቅ አለ። አሁን ስድብ ከፀያፍነት ተላቆ ደረጃው ከፍ በማለቱ የመሪዎች የፓለቲካ ልሳን እስከመሆን ደርሷል! ሌላ ስድብን የሚመለከት አባባል ጨዋን ከባለጌ የሚለየው ቀጭን ድንበር ነው። ክፉ ቃል ወደ ጨዋውም ወደ ባለጌውም አፍ ሊመጣ ይችላል። ልዩነቱ ባለጌው ይተፋዋል፣ ጨዋው ይውጠዋል። "ምራቁን የዋጠ" የሚባለው ስሜቱን በስድብ የማይገልፅ ማለት ነው። ለዛ ነው እንጂ አሁን እድሜ ለአውሮፓ እግር ኳስ ተጫዋቾች ሰው ሁሉ ከመዋጥ ይልቅ በየቦታው ምራቅ መትፋት የተለመደ ሆኗል።

ስድብን እንደ እንድ "የስነአእምሯዊ ጦርነት" ግንባር አድርገው የሚጠቀሙ አሉ። ይህም የጠላትን ቅስም በመስበር የውግያ ሞራሉን ለማኮሰስ የሚደረግ ጥረት ነው። ይህ ግን ሁል ጊዜ ውጤታማ አይሆንም። "ስድብ ጨርቅ አይቀድም" ብሎ ለሚያስብና በራሱ ባህርያት ጥንካሬ ሙሉ እምነት ያሳደረ ወገን ከጠላቱ በኩል የሚሰነዘርበትን የስድብ ውርጅብኝ የተሳዳቢው የድክመትና የመሸነፍ ምልክት አድርጎ ስለሚወስደው (እውነትም ነው) የበለጠ ይጠናከራል እንጂ አይዳከምም። ህወሓት ከፌደራል የስልጣን እርከን ተገልላ በመሰል የትግል ጓደኞቿ ከተተካች ወዲህ ባሉት ጥቂት አመታት ዳቦ ሳይቆረስ ሲወጣላት የከረመው ስም በብዛቱ የአለምን ሬኮርድ የሰበረ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም። ህወሓት ከሌሎች የኢትዮጵያ መሪዎች እጅግ የላቀ እንጂ ያነሰ የአገር ግንባታ ስራ አልሰራችም። ደርዘን ሙገሳ እንጂ ደርዘን ስድብ የሚወረወርባት አይደለችም፣ ያውም አብረዋት በኖሩና በሰሩ ሰዎች። እኔን ግርም የሚለኝ ደርግ እኮ ይህ ሁሉ የዲያብሎስ ስራ ሰርቶ አንዲት የስድብ ስም ብቻ ነው የተሰጠው: "ፋሺሽት" አብዛኛው ህዝብ ግን "ደርግ" በሚል ስም ብቻ ነው የሚያነሳው። ናዚስ ቢሆን? ስድስት ሚልዮን አይሁዶችን ፈጅቶ፣ አምሳ ሚልዮን ህዝብ ያለቀበትን ጦርነት ለኩሶ ያለው ስም ያው "ናዚ" ብቻ ነው። ናዚ ማለት ስድብም አይደለም፣ ከፈፀመው ድርጊት ጋር ተያይዞ ነው እንጂ። ናዚም ሆነ ፋሺሽት የገዢ ፓርቲዎች ስያሜዎች ናቸው፣ እንደ ብልፅግና፣ እንደ ኢዜማ፣ እንደ አብን፣ እንደ ህግደፍ፣ እንደ ሞረሽ፣ እንደ ባልደራስ።

Videos From Around The World

ህወሓት ልትጠራበት የመረጠችው ከአርባ አመት በላይ የኖረው ስያሜዋ "ህወሓት" (ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ነው። ህወሓት ለብልፅግና ከተፎካካሪነት ዘሎ እንደ ጠላት የምትቆጠር ናት። ይሁን ችግር የለውም፣ ያሳደግሁት ውሻ እኔኑን ነከሰኝ መሆኑ ይዘገንናል እንጂ። በሰላማዊ ፉክክር ይሁን በጠላትነት ፓለቲካ የራሱ የሆኑ የስነምግባር ደንቦች አሉት። በፓለቲካ ትኩረት የሚሰጠውና ጥቃት የሚሰነዘረው በተቃራኒው አመለካከት እንጂ አመለካከቱን በያዘው ግለሰብ ወይንም ቡድን ሰብእና ላይ አይደለም። ባይደንና ትራምፕ "እረኛ" ስድብ ቢወራወሩ ይህ ፓለቲካ ሳይሆን ጭቃ መሆን ነው። ህወሓት በወታደራዊ ስነስርአት የተገነባች፣ ከቆሻሻ ቃላት ይልቅ ተግባርን የምታስቀድም ናት። አደባባይ ወጥተው መስመር የያዘ ንግግር ከማድረግ በስተቀር የህወሓት መሪዎች ስድብን ፈብርከው እያከታተሉ እንደ ዘፈን አይለቁም። ስድብ የፈሪ ዱላ ነው። የአዲስ አበባ ዱርየዎች ሲጣሉና ግን መደባደብ ካስፈራቸው የሚወራወሩት ስድብ ለሰሚው ይሰቀጥጣል። ለነሱ የሚመስላቸው ግን ሃይለኛ ስድብ መርጠው ቢወረውሩ የተጣሉትን ሰው አገጭ እንደሚያወልቅላቸው ነው። በርግጥ በህወሓት ላይ የሚወረወሩት የስድብ ስያሜዎች ሚሳይል ሆነው ህወሓትን አያደሙም። ይህ ማለት ግን የሚያደርሱት ምንም ጉዳት የለም ማለት አይደለም። ደርግ ቁጥር ሁለት (ደርግ 2) በሚል የሚታወቀውና እንደ ኮቪድ "ዴልታ ቫርያት" ከደርግ ቁጥር አንድ በመቶ እጅ የባሰው የኢትዮጵያ የፓለቲካ ስብስብ ህወሓትን በህዝብ ዘንድ ከበሬታ እንድታጣና በዛውም አስታከው የትግራይ ህዝብ እንደ አገር አጥፊ ደመኛ እንዲቆጠር በማድረግ በፓለቲካ ግንባር የፊት በር ያጡትን ድል በሸፍጥና በማነካካት በጓሮ በር ለማግኘት ይታገላሉ። የህዝቡ አዞሮ ማየት አለመቻልና በነሱ ላይ ያሳደረው ጭፍን እምነት የእሳት ማራገቢያ የሆነው የስድብ ውርጅብኝ ህወሓትንና የትግራይ ህዝብን ዋጋ እያስከፈለው ነው። የስድቡን ትርጉም በቅጡ ሳይረዱ እንደገደል ማሚቶ የሚያተጋቡ የቀለም ቀንዶችም እልፍ ናቸው። የትግራይ ህዝብ በዚህ የስድብ ጋጋታ አልተንበረከከም። "ውሾቹ ይጮሃሉ፣ ግመሎቹ ይጓዛሉ" ነው። ትግራይ የሃይማኖቶች መዲና ናትና "ከአፍ የወጣ ያረክሳል" የሚለው የመፅሃፍ ቃል ታከብራለች፣ "ጁንታ" እያለ የሚሳደብ ቄስ ሆነ ጳፃስ የላትም። እንደተባለው ምእመናንን ከጥፋት ለማዳን ጠላት ታንክ ላይ የሚወጣ ይኖራል። ጊዮርጊስ ፃድቅ የሆነው ብሩታዊትን ከዘንዶ ስላዳነ አይደል? ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃው ሰማእትነት እኮ "ሁሩ ግደሉ፣ ወድፈሩ" እያሉ ባርኮ መላክ አይደለም። "ሁሩ አስተምሩ" ሲሉ ነበር የኛው ቅን የኔታ ልጆች እያለን የነገሩን።

የህወሓት ስድቦች የሚጀምሩት "ወያኔ" በሚለው ነው። የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች (ደርግ 2) ምን ያህል ጠልቆ የመመርመርና የመረዳት ችግር እንዳለባቸው የሚያሳየው "ወያኔ" የሚለው ቃል ህወሓትን የሚያሳምማት፣ የሚያደማትና የሚያቆስላት ይመስላቸው ነበር። በተቃራኒው "ስድቡ" ህወሓትን የሚያኮራና የሚያስደስት ነበር። ተሳዳቢዎች ህወሓት ከሚለው ስያሜ ውስጥ "ወያነ" የሚል ቃል መኖሩን ዘንግተዋል! የባነኑት "ለውጡ" ከመጣ በኋላ ነው። ለክህደት እግዜር የጁን ይስጠውና ለህወሓት ጫን ያለ አዲስ ስም ወጣላት። ወያኔ እያለ የሰደበ መስሎት ሲያሞግስ የቆየው ምሁር ሆነ መደዴ አዲሱ ስም ተመቸውና እንደኬክ በላው እንደ ማስቲካ አኘከው። ይህን ስያሜ ባደባባይ ያወጀው ህወሓት አቅብጣ፣ አቆላምጣ፣ ምርጥ ምርጡን እያጎረሰች ያሳደገችው የጡት ልጇ ነው። ለኔማ ምን አደረገችልኝ? ችላ ብላኝ አይደል የኖረችው። አዲሱ ስድብ "የቀን ጅብ" የሚል ነው። የእውነቱ ጅብ ራሱ በዚህ አንዱን ነጥሎ ስም የመለጠፍ ነገር ሳይደንቀው አይቀርም፣ ብቻውን ሳይሆን መንጋ ሆኖ እንደሚያድን ስለሚያውቅ። እንግዲህ "ህወሓት እኛ ምንም ሳንነካ እየተቁለጨለጭን ብቻዋን ሆና ካዝና ገልብጣለች" ነው መሰል ውንጀላው። ወይ ጉድ፣ ሳይቀድሙኝ ልቅደም የሆነች አለም! በመሰረቱ በአርአያ ስላሴ የተፈጠረ ሰው ጅብ አይባልም። በተለይ የሃይማኖት ሰው ነኝ ከሚል ሰው አፍ ከቶ ሊወጣ አይገባውም። ኋላ ቀሩ ፊዩዳላዊ ስርአት ብዙ ሰዎች እንዲመለስ ይፈልጋሉ፣ ንጉስና ራስ ብለው ገበሬውን ደፍተው ሊቀማጠሉ። ይህ ስርአት ግን የአገር በቀል ኢንዱስትሪ መሰረት ሊሆኑ ይችሉ የነበሩትን "ባለጆች" ቡዳ ናቸው፣ ሰው ይበላሉ፣ ሌሊት ወደ ጅብነት ይቀየራሉ  እያሉ ሲያገሏቸው ነበር። በነገራችን ላይ የቀን ጅብ ዘራፊነትን ከወከለ የሌሊት ጅብ ጨዋነትን ይወክላል ማለት ነው? የት አገር ነው ጅብ በቀን ከጉድጓዱ ወጥቶ በጠራራ ፀሃይ በረት የሚገለብጠው? የጅብ ነገር ቀደም ብሎም ተነስቶ ነበር። አንድ በኢህአዴግ ጊዜ እንዲሳደብ የተፈቀደለት ተናጋሪ "ወያኔ እንደ ጅብ ሌላ አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ" ብሎ የኢህአዴግ አመራሮችንም አስቋቸዋል። ምን ያድርጉ? ከህሊናው ጋር የተጣላ ሰው ሲበዛ!

ቀጥሎ የመጣውንና ህወሓት ላይ ብቻ ሳይሆን ትግራዋይ በተባለ ላይ ሁሉ የተለጠፈውን ስድብ እንመርምር። ይህ እጅግ አደገኛ የሆነ ፍረጃ "ፀጉረ ልውጥ" የሚል ነው። ፀጉረ ልውጥ ማለት የማህበረ ሰቡ የፀጉር ቀለም ጥቁር ከሆነ ባለ ቡኒ ቀለም ፀጉር ሰው በአካባቢው ሲገኝ ማለት አይደለም። ፀጉረ ልውጥ ባእድ ለማለት ነው። አርባ ምንጭ ታምራለች ይባላልና ሄጄ እዛ ሰንበት ብየ ልምጣ ብሎ የሄደ የትግራይ ተወላጅ ፀጉረ ልውጥ ሊባል ነው! ፀጉረ ልውጥ ከሆነ ደግሞ ተይዞ "ለምን መጣህ ምን ትሰራለህ እዚህ?" ሊባል ነው። ይኽውላችሁ እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት፣ እዩት እንግዲህ የዜግነት መብት! 80 ብሄር ብሄረሰብ ይህ የባዳነት ሰሌዳ የተለጠፈበት የትግራይ ትውልድ ያለበት ነው። ትግራይ ደግሞ የፌደራል ኢትዮጵያ መስራች አባል ክልል ናት። አርባ ምንጭ ላይ በዛ ሰአት የተገኘ የኡጋንዳ ዜጋ ግን "ምን ታደርጋለህ?" ብሎ የሚጠይቀው የለም፣ እያሳሳቁ እንግሊዝኛ መለማመጃ ያደርጉታል እንጁ። ማንም ሰው አይጠየቅ አይደለም። ወንጀል ከሰራ ይጠየቃል፣ ግድ ነው። ይህን ደግሞ የሚመለከተው 80ውን ብሄር ብሄረሰብ ነው። ህገወጥ ሆኖ የሚፈጠር ብሄር የለም፣ ለትግራይ እንዲሆን የተደረገው ግን ይኸው ነው። ፀጉረ ልውጥ በማለት ትግራዋይን በህወሓት አስታከው ዜግነቱን በአደባባይ የገሰሱት መሪዎች "ትግራይ ልገንጠል እያለች ነው" እያሉ በኢትዮጵያና በአለም ህዝብ ፊት ይወተውታሉ። ታዝባችሁ ከሆነ አንዳንድ ካፌ ቤቶች ተቀምጠህ ስትዝናና ወልሉን መጥረግ ይጀምራሉ። መልእክቱ ይገባህና ተነስተህ ልትሄድ ስትል ለምን ትሄዳለህ ብለው ይሟገቱሃል። መሄድህን ጠልተው ሳይሆን ሃላፊነቱን አንተ ላይ ለመከመርና ከወቀሳ ነፃ ለመሆን ነው።

የትግርኛ ስምን ወደ አማርኛ ቀይሮ ስድብ ማድረግም ነበረ። ወደ ዋናው ጉዳይ ከመዝለቄ በፊት አንድ የትርጉም ግድፈት የመሰለኝን ላብራራ። TPLF ማለትና ህወሓት ማለት አንድ አይነት ፍቺ ያለው አይደለም። ህወሓት የሚለውን ወደ ሌላ ቋንቋ መተርጎም አይቻልም ነበር። ለምን ቢባል የተፀውኦ ስም ስለማይተረጎም። አሁን ከበደ የሚለውን ስም " He became heavy" ብለን ልንተረጉመው ነው? የወል ስም የሆነው ላም cow ብሎ መተርጎም ተገቢ ነው። ህወሓት በእንግሊዝኛም ይሁን በአማርኛ መባል ያለበት ህወሓት ነው። እንዲያውም ህወሓት የሚባል በአለም ላይ ሌላ የፓለቲካ ድርጅት የለም። ከበደስ ከሺ በላይ ይኖራል። ያም ሆኖ አይተረጎምም። ህወሓትን የሸወደው ብአዴን የህወሓትን ስም ከትግርኛው ሳይሆን ከኢንግሊዝኛው ትርጉም ተርጉሞ በሊቀመንበሩ አማካይነት ባደባባይ ስድብ ሆኖ ቀረበ። ህወሓት እያሉ (የጉሮሮ ድምፅ እንኳ ሳይሳሳቱ) 40 አመታት ሲያቆላምጧት የቆዩት ጓዶቿ ቀን የጣላት ሲመስላቸው ህወሓት ማለቱን እርግፍ አድርገው ትተው በአማርኛ ትርጉም መጥራት ጀመሩ "ትህነግ" የሚለው ቃል ከእንግሊዝኛው TPLF ቀጥታ በመተርጎሙ "ወያነ" የሚለውን ክቡር ቃል በመተው "ትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር" ማለቱን መረጡ። ማሬ ስኳሬ ሲባባሉ የነበሩ ባልና ሚስት ሲጣሉ አቶ / እከሌ እንደሚባባሉት መሆኑ ነው። ህወሓት ግን የብአዴንን ስም ወደ ትግርኛ ተርጉማ የከዷትን አልሰደበችም። በመሰረቱ ትህነግ ማለት እኮ ስድብ አልነበረም፣ አቶና / ስድብ እንዳልሆነ ሁሉ። የብአዴን ሰዎች በየመድረኩ ሲጠቀሙበት የነበረው ግን ህወሓትን ያንጨረጨሩ ስለመሰላቸው ነው። ይህ "ጅራፍ ራሱ መቶ ራሱ ይጮሃል" እንደሚባለው ነው።

ነገር እየተካረረ ሲሄድ "ህወሓት ሰይጣን ናት" የሚል ደግሞ ሌላ ስድብ መናፈስ ጀመረ። አምላኬ ሆይ! አለም የሚያውቀው ሰይጣን በአይን እንደማይታይና በእጅ እንደማይዳሰስ ነው። ይህ የህፃናት ጨዋታ ነው። የፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ያለና የሚኖር ነው። አምላክ በልእልናውና በጥበቡ ሰውና ሰይጣንን ለያይቶ እንዳይገናኙ መንፈስ ቅዱስን በመሃላቸው አኑሯል። ለዚህ ነውም ሰይጣን የዞረን ሲመስለን የመንፈስ ቅዱስን ስም ጠርተን የምናማትበው። ህወሓት ለዚች አገርና ህዝብ ማንም ሊሰራው ያልቻለ በጎ አስተዋፅኦ አድርጋለች። ሰይጣን እያሉ ለከት የሌለው ስድብ መሳደብ፣ ያውም በመሪዎች ደረጃ፣ የራስን ክብር በእጅጉ ዝቅ ያደርጋል። ኢትዮጵያ በተሳዳቢነትና በውሽታምነት በአለም ዙሪያ መታወቋም የሚጠቅማት አይመስለኝም። በድህነት መጥፎ ስም ላይ ይህ ሲጨመርበት ይገነፍላል። የህወሓት "ሰይጣንነት" ሲነሳ አንድ ስማቸውን የማልጠቅሰው የፓለቲካ ልሂቅ (ህዝባዊ ትግል ላይ ስላሉ) ከህወሓት ጋር መነታረክ ይወዱ ነበር። የፓለቲካ ትችታቸው ሁሉ በአራዳ አይነት ለከፋ የተበረዘ ነው። "አንድ ቀን ሰይጣንና ህወሓት (ወያኔ ነው የሚሏት ጠበቅ አድርገው) ቤት ሊከራዩ ሄዱ" አሉ ህዝብ በተገኘበት ስብሰባ። ቀጠሉ:- "ወያኔ ከፍ ያለ የኪራይ መጠን ስትሰጥ ሰይጣኑ አሳንሶ ሰጠ። የቤቱ ባለቤት ለሰይጣኑ እንዲከራይ ሲወስንለት ተቃውሞ ላቀረበችው ወያኔ የሰጣት መልስ እንዲህ ነበር:-'ቤቱን ስፈልገው ሰይጣንን በድግምት አባርረዋለሁ፣ አንቺን ማለት ወያኔን በምን ላስወጣሽ እችላለሁ?" ተባለ! ተባለንዴ? ያሰኛል። አያችሁ? ይችን ኢትዮጵያ ላይ ሰላምና እድገት አስፍና ለአንድ ትውልድ ያስተዳደረችው ህወሓት ከሰይጣንም በላይ እኮ ነው ተደርጋ የተሳለችው። እንዲህ እያደረገች፣ እጅ እየነከሰች፣ አጥፊዎቿን እየቀደሰች እያወደሰች ኢትዮጵያ በምን ተአምር ነው ከመሬት ተነስታ ከፍ የምትለው? ከፈለገች አጥፊዎቿ በሚተርኩላት ትዝናና። እንዲህ ይሏታል "ኢትዮጵያ ከጨለማ ወጥታ ከፍታ ላይ ነች"! ድንቄም ከፍታ! ኸረ ከመሬት በታች እንዳትወርድ ነው መጠንቀቅ።

በደርግ 2 በህወሓት መካከል የተፈጠረው ቁርሾ ተጋግሎ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጥምረት ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ የደቦ ወረራ ሶስተኛውን የአለም ጦርነት በትግራይ ምድር ተጀመረ። ከወረራው ቀደም ብሎ በትግራይ ህዝብ ድምፅ የተመረጠችው ህወሓት ለሶስት አመታት ከመላ ኢትዮጵያ የተሻለ ሰላም የሰፈነበት ክልል እየመራች ባለችበት ሁኔታ ዱብ እዳ የሆነ የስድብ ጭቃ ተመረገባት። "ጁንታ" የሚል ስም ለህወሓት በአድራጊ ፈጣሪው ታውጆባታል ሲሰማ ወደ መዝገብ ቃላት የሮጠ የለም። ከጅብነት በየትኛው አዝጋሚ ለውጥ ወደ ጁንታነት እንደተቀየረች የቻርለስ ዳርዊንን መፅሃፍ የገለጠ የለም። ምሁሩ መንገደኛው ምኑ ምናምንቴው ሁሉ ለምላሱ ምቾት ሰጠው። ትርጉሙ ከህወሓት ጋር ይግጠም አይግጠም ችግር የለም፣ ዋናው ነገር ህወሓትን መስደብ ነው። "እስቲ ንካው ንካው፣ ግጥሙ ቢገጥም ባይገጥም አንተ ምን ቸገረህ" አለች ሂሩት በቀለ። ዋናው አላማ መንካት ነው! ትከሻ! ስድቡ ቀጠለ። ህወሓት የወራሪው አመጣጥ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን፣ የብርሃኑና የኢሳት ባህሩን የማድረቅ አላማ ያዘለ መሆኑን ስትረዳ ከተሞችን ለቃ ወጣች። ለትግራይ ህዝብና ህዝብ ለመረጣት ውድብ  ደህነት ሲባል ኢንዲያሸንፉ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ትግራይን የተቆጣጠሩት ወራሪዎች ህወሓትን አዲስ ስም አወጡላት:- "የተበተነ ዱቄት"! ወይ ትግራይ፣ ምን አይነት ድብትርና ብትማሪ ነው አንድ ጊዜ የዱር አውሬ ትሆኝና ቆይተሽ ደግሞ የእህል ዱቄት ሆነሽ ነፋስ ላይ ትንሳፈፊያለሽህወሓት "ሸረሪት" ተብላለች። ሸረሪት ሆና ግን መጨፍለቋና ድርዋ እየተጠረገ እንደሆነ ተነገረ። ሲታይ ለካ የሚጠረግ ድር የተባለው የትግራይ ህዝብ ማለት ኖሯል። እኛስ የህወሓት ተራ አባላት ለማለት መስሎን ነበር።

በዚህ ሁሉ የወረራ ወቅት የሰማነው ሰላማዊ ህዝብ በወራሪዎቹ እየተጨፈጨፈ መሆኑ ነበር፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በደቦ እየተደፈሩ፣ የህብረተሰብ ንብረት፣ መገልገያና የኢኮኖሚ አውታር ሲዘረፍና ሲቃጠል እንደነበር ነው። ይህ የሽብሮች ሁሉ እናት ነው። ታድያ ይህንን ግፍ የሚፈፅመው ወራሪ ህዝብን ከጥፋት ለመታደግ የሚታገለውን ህወሓትን "አሸባሪ" ብሎ ሰየመው። ይህ ስድብ በፓርላማ ፀድቆ መውጣቱ ከስድቦቹ ሁሉ የተለየና ታሪካዊ ያደርገዋል። ህወሓት እኮ የተቃዋሚዎች የአሁን ተሳዳቢዎች ጫና ተቋቁማ ነበር 27 አመታት የአልሻባብንና የአልቃይዳን ሽብርተኝነትን የተፋለመችው። ምናልባት የሽብርተኛነት ትርጉም ሰሞኑን ተቀይሮ እንደሆነ ብየ መዝገበ ቃላትን በድረ መረብ ላይ ተመለከትኩ።  ከኦክስፎርድ ኦንላይን ያገኘሁት ትርጉም ይህንን ይመስላል: - "ሽብርተኛ ማለት ለስልጣን ብሎ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ሃይል የሚጠቀምና የሚያስፈራራ ነው" የእውነት ማተብ ካለን ለማተባችን እንነጋገርና ትግራይ ውስጥ ይህን እየፈፀመ ያለው ህወሓት ነው ወራሪው ሃይል? የአማራ ሚሊሻ፣ የህግደፍ አራዊት፣ የኢትዮጵያ ጦር ሃይል ሽብርተኛ ካልሆነ አልቃይዳ ምን በደለ ታድያ ሽብርተኛ ተብሎ የሚጠራው? ከህወሓት ወደ ህዝባዊ ትግል የተቀየረው ትግራይን ከጥፋት የማዳን ዘመቻ ውስጥ ለውስጥ ሃይል ሲያጠራቅም ቆይቶ ድንገት እንደ እሳተ ገሞራ ስለፈነዳና በተዝናኑት ወራሪዎች ላይ ድንገተኛ የሆነ ምስቅልቅል ስለፈጠረባቸው ይህን ራስን የመከላከል ጦርነት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ እንደተቃጣ አደጋ አድርገው ለኢትዮጵያ ህዝብ እያቀረቡለት ነው። ሁሉም ነገር ዘጋግተው ህዝቡ በረሃብ እንዲያልቅ ፈርደውበት ከሸሹ በኋላ "ለምን ራስህን ከእልቂት ለመዳን ትፍጨረጨራለህ፣ ለምን ፀጥ ብለህ አታልቅምና ሰላም አትሰጠንም" የሚመስል አይነት ቁጣ እየተቆጡ አለምን እያስገረሙ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አሁንም አልገባውም ወይንም አውቆ አድፍጧል። ህወሓት ብትጠፋም የትግራይ ህዝብች ሌላ የባሰች ህወሓት ስለሚፈጥር ዋናው መጥፋት ያለበት ፈልፋዩ ነው የሚል በይፋ የማይነገር ግን በአይን የሚገባ እርኩስ አስተሳሰብ አለ። ከዚህም የተነሳ ነባር ግን የታደሱ ስድቦች እየተዥጎደጎዱ ነው:- "የናት ጡት ነካሽ፣ አገር አፍራሽ፣ ከሃዲ" ኸረ ግራ ገባን! ዋናዋ የኢትዮጵያ ጠባቂ ሆና የኖረችው ትግራይን የባህር ዳርቻዎችን ለቅኝ ገዢዎች አሳልፈው የሰጡ ሁሉ ዞረው ተሳዳቢ የሆኑበት አባዜ ምንድነው? ትግራይ አገር አፍራሽ የተባለችው ለጠቅላይ ገዢዎች እሾህ አሜኬላ የሆነባቸውን ፌደራሊዝምን ስላሰፈነች ነው። ምን ችግር አለ ትግራይን እኮ ፌደሬሽኑ አልፈጠራትም። ጥንታዊ የሆነ የታወቀ ወሰን አላት። ይብላኝ ፌደሬሽኑ ከፈረሰ ትናንሽ ክፍላተ ሃገር ወይንም ጠቅላይ ግዛቶች ሆነው ለሚበታተኑት አማራ ክልልና ኦሮሚያ። ወጥ ለራስህ ስትል ጣፍጥ። በህወሓት ሃይልና ጥረት ክልል የሆክ ሁሉ ነገ ጧት እንኳንና ውለታህን በልተህ ወደ ትግራይ ሊዋጋ የምትልከው ልዩ ሃይል ቀርቶ የራስህ የከተማ ትራፊክ ፓሊስም መቅጠር አትችልም።

"የፍፃሜው ጦርነት ነው..." የሚል ሃረግ በኢንተርናሲዮናል መዝሙር ውስጥ አለ። የመጨረሻውና የኢትዮጵያ ህዝብ የማመዛዘን አቅሙ የሚፈተንበት ጊዜ መጥቷል። ለህወሓት-ትግራይ አዲስ ስም ወጥቶላታል። የአሁኑ ወሳኝና አደገኛ ነው። ይህም የሚሆነው ህዝብ ልክ ነው ብሎ ከተቀበለው ነው። ህወሓት-ትግራይ "ካንሰርና፣ አረም" ተብላለች። አንዱ አይበቃም ነበር? "ንዴት እብደት" ነው የሚባለው እውነት ነው። የሚወረውረው ትልቅ ድንጋይ የትም ቢያርፍ ግድ የማይሰጠው እብድ ብቻ ነው። ህወሓት-ትግራይ የኢትዮጵያ ካንሰር ሆኑ ማለት እንደማንኛውን ካንሰር ተጋሩ መጥፋት አለባቸው ማለት ነው። አረምም  አዝርእት እንዳያጠፋ ተነቃቅሎ መጥፋት አለበት ነው። ይህ የዘር ማጥፋት አዋጅ ነው! ብዙዎቹ እየተጨነቁ ያሉትና አገር እጃቸው ላይ እንደጨው እየሟማች ዝም ብለው የሚያዩት ህወሓት አራት ኪሎ ከተመለሰች የአለም ፍፃሜ ነው ብለው እንዲያስቡ በተለያየ ስልት ስለተቀሰቀሱ ነው። አሁንም ስሙን የማልጠቅሰው ከፍተኛ የህዝብ አስተዳደር አባል የነበረ ሰው ባለፈው አመት አንድ ድረ ገፅ ላይ ባሳተመው ፅሁፍ እንዲህ ያለ አስደንጋጭ አረፍተ ነገር አስፍሯል:- "ህወሓት አራት ኪሎ ከምትመለስ ኢትዮጵያ ብትፈርስ ይሻላል" እግዚአብሄር ያሳያችሁ! እኒህ ሰው በቅንነት ስሜታቸውን በግልፅ መናገራቸው እንጂ ይህ ሁሉ ህወሓትን በአገር አፍራሽነት የሚኮንነው ወፈ ሰማይ ስልጣኑን በተጋሩ ከምቀማ ይቺ አገር መቀመቅ ትውረድ ነው። ትዝብቱ ፈጦ ይቀራል እንጂ ህወሓት የአራት ኪሎን ስልጣን በደሮ መረቅ ፈትፍተው ቢሰጧት ብትሞት አትቀበልም፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር መቆራረጥ ካልፈለገች በስተቀር። የኢትዮጵያ ህዝብ በፕሮፓጋንዳ እየተደናበረ መኖር የለበትም። ምንም እንኳን ከዚህ ሁሉ ግፍ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መቆየት ከአባትህ ገዳይ ጋር አንድ አልጋ እንደመጋራት የሚቆጠር ቢሆንም ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር ከቆየች የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ከእንግዲህ ትግራይን በዘፈቀደ የሚወርና የሚያስወርር ሃይል በአራት ኪሎ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ክልል እንዳይኖር ማረጋገጥ ብቻ ነው። ትግራይ የምትፈልገው ራሷን ማስተዳደር ነው። የራስ አስተድዳደር ደረጃው ምን እንደሚሆን ህዝብ የሚወስነው ነው። ትግራይ ከእንግዲህ አብራ ቆየች አልቆየች ስለ ራሷ ልማትና የህዝብ ደህንነት ካልሆነ ስለ ኢትዮጵያ የምትጨነቅበት አንጀት የላትም፣ በእብሪት ተበጣጥሶ አለቀኮ አንጀቱ!!

Back to Front Page