Back to Front Page

ከሰው ክብርና ምስጋና ለማግኘት የሚባዝኑት ዶክተር ወዳጄነህ መህረነ

ከሰው ክብርና ምስጋና ለማግኘት የሚባዝኑት ዶክተር ወዳጄነህ መህረነ

ከዐብይ ኢካቦድ (09/14/21)

የወንጌል ሰባኪና አስተማሪ፤ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር ዘንድ ግዴታ እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ያሳስባል። ከሰው ምስጋናና ክብር ለማግኘት ከቃሉ ውጭ የሚደረግ መሳጭና ሳቢ ቃል ፋይዳ ቢስ እንደ ሆነ ቀድሞ መረዳት በጣም ያስፈልጋል፤ ቅጣት በመጨረሻው ያከናንባልና። ለቃሉ ታማኝ መሆን የሚመነጨውም ሰው ቃሉ እንደሚል ሲናገርና ሲያደርግ ብቻና ብቻ ነው!

ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግል ቢኖርም እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኅይል ለእርሱ ከዘላለም ይሁን፤ አሜን 1 ጴጥ 4፡11-12

ከእነዚህ ሁለት ቁጥሮች አያሌ መሰረታዊ የቃሉ ተገቢ አጠቃቀም መገብየትና መቃረም ይቻላል። ሲጀምር ስለ ነገረ-መለኮት መናገር ወይም መስበክ ወይም ማስተማር የሚፈልግ ሰው መናገር ያለበት እንደ እግዚአብሔር ቃል ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈው መሰረት ሳይቀንስ፤ ሳይጨምር፤ ሳያዛባ፤ ሳያቀጥንና ሳይበረዝ መሆን እንዳለበት የሚያሳስብ ነው። ሁለተኛው፤ አገልጋይም ማገልገል የሚኖርበት እግዚአብሔር እንደሚሰጠው ብርታት ወይም ጉልበት መሆን እንዳለበት የሚያሳስብ ነው። አገልጋዩ ከተሰጠው ጉልበት ወይም ብርታት በላይ ወይም በታች ማገልገል አይኖርበትም። እግዚአብሔር ከሚሰጠው ብርታት ማገልገል ወይም ጭራሽኑ ያለማገልገል ዝንባሌ ግልጽ ቢሆንም፤ ሰው እንዲያገለግል እግዚአብሔር ከሰጠው ጸጋ ውጭ የማገልገል አባዜና፤ ከዚህም በተጨማሪም በተሰጠው ጸጋ ከተሰጠው ብርታት/ጉልበት በላይ ለማገልገል መታከት ተገቢ እንዳይደለ ልብ ልንለው የተገባ ነው።

ከዚህ አኳያ የሁሉም የቃሉ አገልጋዮች ሁኔታ ቢፈተሽ አያሌ ግድፈት ወይም ህጸጽ የሚታይበት ቢሆንም፤ ለዚህ መሰረታዊ እውነት ተገዠ የሆኑ ታማኝ የቃሉ አገልጋዮች መኖራቸው የሚካድ አይደለም። ዛሬ በኢትዮጵያ የሚሰበከው ስብከት፤ የሚነገረው ትንቢት፤ የሚሰጠው አገልግሎት ከሞላ ጎደል ከእነዚህ ቁጥሮች በሚጻረር መልኩ መሆኑ ለመረዳት አዳጋች ከቶ አይደለም። እንደ ቃሉ መናገርና፤ እግዚአብሔር በሰጠው ብርታት መሰረት ማገልገል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ሲሆን፤ ክብርና ኅይሉ ዓለም ዘላለም ለእግዚአብሔር እንደ ሆነ ሐዋሪያው በአጽንኦት አሜን! ወይም ይሁን! በማለት ያጠቃልላል። ከሰው ምስጋና፤ ዝናና፤ ክብር ለማግኘት እነዚህን ሳይጠብቁ የሚደርጉ የቃሉ ንግግሮችና አገልግሎቶች በቃሉ ንጉሥ ቅጣት እንደሚያስከትሉ ማወቅ በጎ ነው። እስቲ ሐዋሪያው ጳውሎስ በ(ሮሜ 2፡28-29) ላይ ምስጋናቸው ከሰው እንጂ ከእግዚአብሔር ስላልሆኑት የሚለውን ለአንድ አፍታ እንይ፦

Videos From Around The World

አንድ ሰው ለይምሰል በውጫዊው ብቻ ይሁዲ ልሁን ቢል ይሁዲ አይሆንም፤ እውነተኛ ግዝረትም ውጫዊና ሥጋዊ ሥርዐት አይደለም። ዳሩ ግን አንድ ሰው ይሁዲ የሚሆነው በውሰጣዊ ማንነቱ ይሁዲ ሆኖ ሲገኝ ነው። ግዝረትም ግዝረት የሚሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፤ በመንፈስ የልብ ግዝረት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ሰው ምስጋናው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ነው

ከእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ተመርክዞ በርካታ አውዳዊ ትንታኔ/ብለታ(exegetical exposition) ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም፤ ዋናው ጭምቀ-ሳብ፤ ከውጭ በሰው በሥጋ ላይ የሚደረገው የሸለፈት ግዝረት፤ ካለ በመንፈስ የሚደረገው የውስጥ/የልብ ግርዘት ፋይዳ የሌለው መሆኑ የሚያስረግጥ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከእግዚአብሔር የሆነ ምስጋና ፤ ከሰው ከሆነ ምስጋና የተለየ እንደ ሆነ በቁጥሮቹ ማጠቃለያ እንደ ተጻፈ ልብ ይሏል። ዛሬ ላይ በቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰው ምስጋናና ውዳሴ የሚሹ ጥቂት አይደሉም። ዶ/ር ወዳጄነህ በዚህ ከሚመደቡት አንዱ መሆናቸው አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል። ራሳቸው እንደሚሉት እንደ የወንጌሉ አገልጋይ እና እንደ የስነ-ልቦና (Psycology) ምሁር ሁለቱን አቀናጅተው በሰው ዘንድ አድናቆትና ምስጋና እንዲያገኙ በብዙ መድረኮች ሲሰብኩ ወይም ሲናገሩ ይስተዋላሉ። ነገር ግን የሚናገሩት እንደ እግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነና፤ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር እንደ አበረታቸው በሰጣቸው ጸጋ መሰረት እንደ ሆነ በጥንቃቄ ሊፈተሽ የተገባ ነው። እዚህ ላይ ሐዋሪያው ጳውሎስ የቃሉ ወይም የወንጌሉ አገልግሎት በንግግር ብልጫና ክህሎት እንዳይደለ ተናግሯል።

ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፤ የእግዚአብሔርን ምስጢር፤ በረቀቀ የንግግር ችሎታ ወይም በላቀ ጥበብ ልገልጥላችሁ አልመጣሁም (1 ቆሮ 1፡1)

ሐዋሪያው ጳውሎስ ወንጌልን ወደ የቆሮንቶስ ሰዎች ያቀረበው፤ በሚያባብልና በሚስብ በሰውኛ የንግግር ዘይቤና በላቀ የሰው ጥበብ አሽሞንሙኖ አልነበረም። ዛሬ ከሰዎች አድናቆትና ምስጋና የሚሹና የሚሸምቱ በርካታ የወንጌሉ አገልጋይ ነኝ ባዮች በረቀቀ የንግግር ልቀትና ችሎታ በድፍረት ሲቀርቡና ምስጋና ከሰው ሲያተርፉና ሲጎርፍላቸው ይታያሉ። ዶ/ር ወዳጄነህ በተለያዩ መድረኮች ከሰው ምስጋናን ለማግኘት በረቀቀ የንግግር ችሎታ ወይም በላቀ ጥበብ ሲቀርቡ ይታያሉ። ዶክተሩ በሚያቀርቡት ወንጌል ላይ ሳቢና መሳጭ ይሆን ዘንድ፤ ከስነ-ልቦና ዕውቀታቸው ዘገንና ቆንጠር አድርገው ያቀርቡታል። በመሆኑም በእግዚአብሔር ሳይሆን በንግግር ክህሎታቸውና በላቀ ጥባባቸው ከተሰበሰበው ህዝብ ምስጋናን ይገበዩበታል።

ወደ ዶክተር ወዳጄነህ አወዛጋቢ ነገረ-መለኮታዊና ፖለቲካዊ ምልከታቸው ከማለፋችን በፊት፤ በጨረፍታ ማን እንደ ሆኑና የት ያገለግሉ እንደ ነበሩ፤ በምን ምክንያትም እንደ ለቀቁ መግለጽ አስፈላጊ ነው። ዶክቶሩ በህክምና ሞያ በጥቁር አንበሣ ኮሌጅ የተመረቁ ሲሆኑ፤ በሙሉ ወንጌል ቤተ-ክርስቲያን በወንጌላዊነት አገልግሏል። በውጭ አገር በምኖርበት ሃገር በአንድ ቤተ-ክርስቲያን በተዘጋጀ ጉባኤ/ኮንፍረንስ ሰባኪ ሆነው ተጋብዘው ለሦስት ቀናት በተከታታይ ባቀረቡት ስብከት የመሳተፍ ዕድል ያጋጠመኝ ከመሆኑ ባሻገር፤ ሎሎች ስብከቶችም በካሴት ሰምቻለሁ።

የወንጌል ስብከታቸው በሳይኮሎጂ ዕውቀታቸው ታጅቦ የሚቀርብ ሲሆን፤ ጳውሎስ ...የእግዚአብሔርን ምስጢር፤ በረቀቀ የንግግር ችሎታ ወይም በላቀ ጥበብ ልገልጥላችሁ አልመጣሁም በማለት የተናገረውን እንዲመለከቱ የሚገፋፋ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሳይኮሎጂ ከነገረ-መለኮት ጋር አዳብሎ ማስተማርና መስበክ፤ ለሰሚው የሚጣፍጥ ቢሆንም ጎጂ እንደ ሆነ በርካታ ስለ ሳይኮሎጂና ነገረ-መለኮት በ Goole የቀረቡ ጽሑፎች ማየት ይቻላል። የዶክተር ወዳጄነህ ስብከት ዓላማ የአድማጮቻቸው ቀልብና ስሜት ግጥም አድርጎ ለማሰር ምስጋናና አድናቆት ከሰዎች ለማትረፍ በመሆኑ፤ ስብከታቸው በንጽሁ ወንጌል ላይ ብቻ የተመሰረተ ሳይሆን በላቀ ዓለማዊ ጥበብ የሚገለጥ ነው።

ዶክተር ወዳጄነህ በወንጌላዊነት ያገልግሉባት ከነበረችው የሙሉ-ወንጌል ቤተ እምነት ለምን ወጡ? የመጀሪያይቱ ምስታቸውን ፈትተው፤ ሁለተኛ ሚስታቸው ዘማሪት ሶፍያ ሽባባውን ስላገቡና፤ የወንጌላዊያን አብያተ ክርሰቲያናትም በፍች ላይ የጸና አቋም ስላላቸውና ምእመኑም ማንም ይሁን ምን መጽሐፍ እንደሚያዝ ከዝሙት ውጭና በሞት ከመለየት ውጭ በሌላ ፍችን ስለማይቀበል፤ በዚህ ጠንቅ ቁቡልነት ማጣታቸው ነው። ይሄ አላንስ ብሎ፤ ዶክተር ወዳጀነህ ሁለተኛ ያገብዋትንና የሁለት ልጆቻቸው እናት ከሆነችው ከዘማሪ ሶፊያ ጋር ተፋቷል። በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ፊችው የተፈፀመው የቤተ-ክርሰቲያኒቱ አማኒ ባልነበሩበት ወቅት የተፈጸመ ስለ ሆነ ፍቺው አይቆጠርባቸውም እንዳይባል እንጂ፤ የፈታ ቄስ ማለትም ያፈረሰ ቄስ እንደማይቀድስ የታወቀ ነው።

ዶ/ር ወዳጄነህ ከሙሉ ወንጌል ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን በወንጌላዊነት ማገልገላቸው ከማቆማቸው በፊት፤ አሁን በነገረ-መለኮትና በፖሊቲካው መድረኮች የሚያነስዋቸው ምልከታዎች አያነሱም ነበር። እንዲህ ዓይነቶቹ ለውጦች የተከሰቱት ከአገልግሎታቸው ከተገለሉ በኋላ ስለ ሆነ፤ የአስተምሕሮ (ዶክትሪን) ልዩነቱና ሞቅ ያለው የፖለቲካ አምሮት የተከሰተው ከቤተ ክርስቲያንቱ ከወጡ በኋላ እንጂ፤ በዶክትሪን ልዩነት ሰበብ እንዳልወጡ ነው። ሲጀምር ዶክቶሩ ስብከታቸው ሰዎችን ለመሳብ ከዚህም ከዚያም በንግግር ጥበብ ከሽነው የሚያቀርቡ እንጂ፤ ጥልቀት ያላቸውን የወንጌሉ አስተምሕሮቶችን ቆፍሮ በማቅረብ አማኙን መመገብ ታዋቂ አልነበሩም። ዶክተር ወዳጃኔህ እንደ ብዙዎቹ የዘመኑ ሰባኪዎች አነቃቂ ወይም ቀስቃሽ ሰባኪ (motivational speaker) እንጂ፤ ተንታኝ/በላች (expository preacher) አይደሉም። ይህ ካስተማርዋቸውና ከሰበክዋቸው ካሴቶችና ክሮች በቀላሉ ማረጋጋጥ ይቻላል።

በመቀጠል ዶ/ር ወዳጄነህ በየመድረኩ ከሚናገርዋቸው የነገረ- መለኮትና ፖለቲካ ንግግሮች በመንደርደር ባንዳንዶቹ ላይ ማሄስ አስፈላጊ ነው። ዶ/ር ወዳጄነህ ስለ ብፅዕት ድንግል ማርያም በቅርብ ጊዜ፤ ከሚያነሱት ብንጀምር በጎ ነው። ስለ ቅድስቲቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርሰቶስ እናት ስለ ድንግል ማርያም በሕያው ቃሉ የተጻፉት በርካታ መልእክቶች ምእመን ሳያጎድልና ሳይጨምር መቀበል የተገባ ነው። ሁላችንም መናገር ያለብን እንደ ቃሉ መሆን እንዳለበት ከላይ ባየነው መሰረት፤ ቀንሶና ጨምሮ ማቅረብ አይፈቀድም። እናማ ዶ/ር ወዳጄነህና ሌሎች ሰባኪዎች ቅድስት ድንግል ማርያም የወለደችው በድንግልናዋ (perpetual virginity) ሆና ነው ሲሉ ይደመጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይኼን አስተምሮ ከሆነ ሳያቅማሙ ለመቀበል አዳጋች ባልሆነ ነበር። ዳሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ቅድስት ማርያም ድንግል ሆና ኢየሱስን እንዳረገዘች እንጂ፤ ድንግል ሆና እንደ ወለደች አይናገርም። ድንግልናዋ ሳይፈርስ ወይም ፈርሶ ቅዱሱን ብላቴና ኢየሱስን እንደ ወለደችውም ቃሉ አይናገርም።

በመሆኑም እንደ ቃሉ መናገር አለብን በሚለው መርህ መሰረት መጽሐፍ ቅዱስ ባልተናገረው ላይ የራስ አመለካከት ጨምሮ ማሰተማር ተገቢ አይደለም። መናገር፤ መስበክና ማሰተማር ያለብን መጽሐፍ ቅዱስ እንድንናገር በፈቀደልን መጠን እንጂ፤ ዝም ባለበት ጉዳይ መናገር ተቀባይነት አይኖረውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን እንደ ጸነሰች እንጂ፤ ድንግልናዋ ሳይፈርስ እንደ ወለደችው የሚጠቅስ የለም። በካቶሊክና ባኦርቶዶክስ በድንግልነት እንደ ወለደች የሚጠቅሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ሌሎች መጻሐፍት ላይ ተጽፏል ቢባሉም፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ሌሎች መጻሕፍት እንደ ማስረጃ መውሰድ፤ እንደ ቃሉ መናገር የሚለውን መርህ የሚጋፋ ነው። ስለዚህ በድንግልና ወልዳለች ወይም አልወለደችም የሚለው ሙግት ፋይዳ የሌለው ነው።

ሌላው ዶክተሩ ቅድስት ድንግል ማርያምን አስመልክቶ የሚያነሱት ነጥብ ቅድስት ድንግል ማርያምን እመቤታችን ብንላት ጥፋቱና ችግሩ ምንድ ነው? ካሉ በኋላ የእንግሊዝዋ ንግሥት እንኳ እመቤት ተብላ ትጠራ የለም ወይ? በማለት ንጽጽሮታዊ ምልከታቸውን ያቀርባሉ። ለዚህ ምልከታም መልስ ማግኘት የሚቻለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በአዲስ ኪዳን ሃያ-ሰባቱ መጻሕፍት የብጽዕት ድንግል ማርያም ስም በአዎንታዊ መልኩ ለበርካታ ጊዜ የተጠቀሰ ቢሆንም፤ አንድም ቦታ ላይ እመቤታችን ተብሎ አልተጻፈም። ሌላው በእንግሊዝ አገር ሃውስ ኦቭ ሎርድስ (Houseof Lords)፤ ሴቶቹ እመቤት (Lady) ወንዶቹም ጌታ (Lord) ተብለው እንደሚጠሩ ይታወቃል። ሳራም ባልዋን አብርሃምን ጌታየ (ሎርድ) ብላ ትጠራው እንደ ነበረ ይታወቃል። እግዚአብሔር አብን፤ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ጌታ (Lord) ተብለው ይጠራሉ።

እዚህ ላይ ለሰዎች እመቤትና ጌታ (Lady & Lord) ብሎ መጥራትና ለመለኮት ጌታ(Lord) ብሎ መጥራት አቻ ትርጉም ይኖራቸው ይሆን ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል? ምንም እንኳ አጠራሮቹ አንድ ቢሆኑም የተለያዩ እንደ ሆኑ ለመለየት አያዳግትም። ስለዚህ ቅድስት ድንግል ማርያምን እመቤት ብለን ለመጥራት እመቤትነቱ ከየተኛው ዘርፍ ይሆን? እንደ ሰው ከሆነ እርሷን እመቤት ብሎ መጥራቱ ችግር የማይፈጥር ቢሆንም፤ በመለኮት ደረጃ ከስላሴዎቹ በተጨማሪ ለእንስት ፆታ የጌታ እኩያ እመቤት ስለ ሆነ፤ ድንግል ማርያምን በስላሴና በአምላክነት ተርታ የሚያስቀምጣት ስለሆነ የእመቤትነቱ ማአርግ የተሳሳተ ይሆናል።

በፖለቲካው አደባባይና በመሪዎች ፊት ብቅ ማለት የተለማመዱትና ያፈቀሩት ዶ/ር ወዳጄነህ፤ በቅርብ ጊዜ ፖለቲካን መደላድል ባደረገው የማሕበረ-ቅዱሳን ስብሰባ ላይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሃይድሮጂን ቦምብ ስለ ተመቱት ሁለቱ የጃፓን ከተሞች (ሂሮሽማና ናጋሳኪ) መሳጭና ሳቢ በሆነ ንግግር የድርጊቱ አሰቃቂነት ገልጸውታል። በዚህ ወቅት ሁለቱ ከተሞች የተደበደቡት በሃይድሮጂን ቦምብ እንጂ፤ በኒኩለር ቦምብ እንዳይደለ ጠቅሶ ማለፉ አስፈላጊ ነው። ዳሩ ግን ስለ እነዚህ ሁለት ከተሞች ህዝቦች አሰቃቂ የቦምብ ጥቃት ሃዘናቸው በሚገርም ቃላት የገለጹት ዶክተር፤ ትንሽ ሳይቆዩ፤ አብይ አሕመድና ታላላቅ የሃገሪቱ ባለሥልጣናት በተገኙበት፤ ስለ ኢትዮጵያ የወቅቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥና መፍትሄው የተናገሩ ሲሆን፤ይቅርታ ሊደረግለት የማይችል ከአንድ እግዚአብሔርን እከተላለሁ ከሚል ምሁር የተነገረው ቃል መስማት ዘግናኝ ነው። በዚህ ወቅት በፌስ ቡክ በተለጠፈ የራሳቸው የቪድዮ ክሊፕ የሚከተለው ብለዋል፦

ከአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ የእርሰ በርስ ጦርነቶች ተድረጓል፤ እና የቀጠሉት ዕድሜ የተሰጣቸው አንዳንዶቹ በንግግር/ ውይይት (Nogotiation) አቆሙ፤ አንዳንዶቹ በአንዱ አሸናፊነት አቆሙ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አንዱን እርዳታውን በመቆለፍ አቆሙ። ስለዚህ የሚያስፈልገው ምንድነው እርድታውን መቆለፍ ነው ጦርነትን እንዲቆም ለማድረግ የጥቅሱ መጨረሻ

ይህ ካንድ ክርስቲያን ቀርቶ ጤነንት ከጎደለው አእምሮ የሚጠበቅ ስው ንግግር አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም ይሄ ንግግራቸው በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስከስሳቸው ነው! ዶክተር ወዳጄነህ የተናገሩት ክፉ ምክር በፍርድ ወንበር ፊት የሚያስቆማቸው መሆኑ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የእርስ በርስ ጦርነትን የሚያቆሙበት አንዱ አማራጭ እርዳታን መቆለፍ እንደ ሆነ በይፋ በገዛ አንደበታቸው ተናግሯልና። ዶክተሩ የወንጌል ተከታይና የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ እያሉ እንዲህ ዓይነቱ በአረማዊያዊያኑ እንኳን የማይነገር ጸያፍ ንግግር ሲናገሩ ማድመጡ ከቶ ምን እየሆነ ነው? የሚያስብልና ግራ የሚያጋባ ነው። ለመሆኑ በአዲስ ኪዳን የእምነታችን ጀመሪና ፈጻሚ የሆነው ጌታ ኢየሱስና ታማኙ የጌታ ባሪያ ሐዋሪያው ጳውሎስ ምንም እንኳ በጊዜአቸውና በሰፈራቸው በርካታ ጦርነት የነበሩ ቢሆኑም አንድ ቃል ጦርነትን ደግፈውና ተቃውመው የተናገሩት ይኖር ይሆንን? በሃያ ሰባቱ የአዲስ ኪዳን መጸሓፍትስ ጦርነትን ደግፎ ወይም ጦርነትን አስመልክቶ የተሰጠ አስተያየት ይኖር ይሆን? እርስዎ ታድያ ከ200 በላይ የርስ በርስ ጦርነቶች ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አስካሁን ድረስ በዚች ዓለም ተደርጓል ብለው የሚዘበዝቡትና የአፈታታቸው መንገድ በሦስት ዘርፎች መሆኑ ገልጸው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት የሚፈታው እርዳታ እንዳይደርስ ማንቁርትን በመቆለፍ ነው የሚል የመፍትሔ አቅጣጫ፤ አማራጩን እንደ መፍትሄ እየተጠቀመበት ላለው መንግሥት ማቅረብዎ ከእርስዎ ከምር የሚጠበቅ ነው ወይ?

ለሂሮሽማና ለናጋሳኪ ህዝብ የልብ ሃዘናቸው በቃል ጥበባቸው የተሰብሳቢውን ልብና ቀልብ ያነሆለሉት ምሁር፤ የትግራይ ህዝብ እርዳታ እንዳይደርሰው ማንቁርቱን በመቆለፍ ጦርኖቱን ማቆም እንደሚቻል መናገራቸው፤ ሳይኮሎጂስት ነኝ አሉን እንጂ፤ የጤና ምርመራ ይደረግላቸው ዘንድ ሌላ የስነ አእምሮ የሚያሻቸው፤ በተለይም ያለ አንዳች የስነ አእምሮ ዕርዳታና እገዛ ለሁሉም ምክር ለአእምሮና ለነፍስ ፈውስ ሙሉእ- በኩሉሄ (Self- sufficient) የሆነውን የወንጌሉን ቃል ብቻ የሙጥኝ ብለው ቢይዙ እንዲሁ ከዝንተ መጎትና አመክንዮ መንሻፈፍ በዳኑ ነበር።

ስለ መባ፤ አሥራትና በኩራት በቡልይ ኪዳን አያሌ ነገሮች የተጻፉ እንዳሉ ይታወቃል። በዚህ መድረክ ስለ እያንዳንዱ በጥልቀት መሞገት ሆነ መተንተን አይቻልም። በአዲስ ኪዳን ስጦታ በፍቅር ነፍስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ስለ ሆነ አማኞች ስጦታን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በሐዋሪያት ሥራ አማኞች የነበራቸው ንብረት በጋራ እንዲኖሩ፤ ሃብትም በጋራ እንዲጠቀሙ ወሰነው አብረው ይኖሩ እንደ ነበሩ ተጽፏል። ይሁንና በአዲስ ኪዳን ስለ በኩራት፤ መባና አሥራት ከቡሉይ ጠቅሶ አንድም የተሰጠ ትዕዛዝ ወይም ግዴታ የለም። ዶ/ር ወዳጄነህ አሥራቴ ለአክሱም ጽዮን እከፍላለሁ ማለታቸው፤ የሚከፍሉት አሥራት የቡልይ ኪዳኑን ተከትለው ይሆን ወይስ በአዲስ ኪዳኑ በፍቅር የሚሆነውን ስጦታ ተሞርክዘው። እዚህ ላይ አያሌ አጭበርባሪ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፤ የቡልይ ኪዳኑን አሥራትና መባ ጥቅሶች በመጠቀም የብዙዎቹን ኪስ እንዳራቆቱ ማወቅ አስፈላጊ ነው።

ለመሆኑ ዶክተሩ አሥራቴ በየወሩ ለአክሰም ጽዮን እከፍላለሁ ካሉን፤ አክሱም ጽዮን እርዳታ እንዳይደረሰው ከሚቆለፍበት ህዝብ አንዱ ስለ ሆነ፤ እርዳታ እንዳይደረሰው ይቆለፍበት ላሉት ህዝብ አሥራትን መስጠት ምን ይጠቅሟል፤ እንዴትስ ሁለቱን ማስታረቅ ይቻላል? እርዳታ እንዳይደረሰው ይቆለፍበት በማለት የመፍትሔ አቅጣጫ (Recommondation) ላሳለፍክበት ህዝብ፤ አሥራቴን በየወሩ እከፍላለሁ እንዴት ማለት ይቻላል?

የዶክቶር ወዳጄነህ ማንነትና እምነት በግልጥ ሲታይ፦

ከአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ የእርሰ በርስ ጦርነቶች ተድረጓል፤ እና የቀጠሉት ዕድሜ የተሰጣቸው አንዳንዶቹ በንግግር/ ውይይት (Nogotiation) አቆሙ፤ አንዳንዶቹ በአንዱ አሸናፊነት አቆሙ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አንዱን እርዳታውን በመቆለፍ አቆሙ። ስለዚህ የሚያስፈልገው ምንድነው እርድታውን መቆለፍ ነው ጦርነትን እንዲቆም ለማድረግ የጥቅሱ መጨረሻ

 

 

 

Back to Front Page