Back to Front Page

አሜሪካና አውሮፓ፥ የኢትዮጵያ ባለንጣ ወይስ ባለውለታ?

አሜሪካና አውሮፓ፥ የኢትዮጵያ ባለንጣ ወይስ ባለውለታ?

 

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል 08-22-21

 

የዐቢይ አህመድ ዓሊ ዓይነቱ የትንሽ እውቀት ባለቤት የሆነ ቅሌታምና ደካማ ሰው በሰዎች ፊት ብርቱና አዋቂ ሰው ሆኖ ለመታየትና ለመምሰል የማያንከባልለው ድንጋይ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለውም። ጉንጭ አልፋ፤ አንድም፥ ያልበሰለና የተውሶ እውቀት ባለቤት የሆነ ሰው ፈጽሞ ስለማያውቀው እውቀት ማውራት፣ በሰዎች ፊት አዋቂ መስሎ ለመታየትና ለመቅረብ በሚያደርገው ጥረትም ስላላለፈበት እውቀት እያነሳ ነገር መቀላልቀልና መለፈፍ የባህሪው ነው። ይህን ዓይነቱ የማንነት ቀውስ ተከትሎ የሚፈጠርና የሚጎለብተው መጥፎ ባህሪይ ታድያ በዐቢይ አህመድ ዓሊ ህይወት ብቻ የሚስተዋል በሽታ ሳይሆን በድህነት ተወልደው በድህነት አድገው ከድሃ አፍ እየመነተፉ ኑሯቸው ያደላደሉ ዳሩ ግን በድህነት አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቀው የሚዳክሩ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ልሒቃን ሁነኛ መታወቂያም ነው። በተለይ በአፋቸው ኢትዮጵያዊነት ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው! የሚለው ምዋርተኛ መፈክር በማስተጋባት የሚታወቁ ዳሩ ግን ሰውን እንደ ከብት አጋድመው የሚያርዱ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸውና የማያውቁ፣ ኃይማኖት አልባ የአማራ ልሒቃንና ከበሮ መቺዎቻቸው እንቶፈንቷቸው በማገርሸት የሚታወቁ ኃፍረት የሌላቸው ናቸው። ጥያቄው፥ አገር የዚህ ዓይነቱ የበከተ አስተሳሰብ ውጤት የሆኑ ግለሰቦች እጅ ስትወድቅ ዜጎች ምን አተረፉ? የሚል ነው።

 

ሁላችን እንደምናውቀው ድንገተኛ ፖለቲከኛ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ኢትዮጵያ፥ ውድቀትና ኪሳራ፣ ጦርነትና ሞት ኤክፖርት በማድረግ የሚታወቁ የመቃብር ስፍራዎች ሶማሊያና ኤርትራ ባለ እንጀራ ከሆነች ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር ያልተነገረ እንጅ ያልሆነና ያልታየ ትንግርት የለም። በተለይ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ ቁጠባቸው ይሄ ነው በማይባል ፍጥነት ቁልቁል እየነኩት ከሚገኙት ዙምባቤና ቬንዜላ የመሳሰሉ የወደቁ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ውድቀትዋን እያፋጠነች ያለች፥ ዳቦና ነዳጅ በወረፋ ሞት እጦትና ችጋር የተትረፈረፈባት የበከተች አገር ሆናለች። ኢትዮጵያ፥ ምዋርተኞቹ ፖለቲከኞችዋ የስልጣን ጥማቸው ለማርካትና ወንበራቸው ለሟሞቅ ሲሉ የሰው ልብ በሚሰልቡና በሚያማምሉ የቃላት ጋጋታ እንደሚቀቧቧትና አሸብርቀው እንደሚስሏት አገር ሳትሆን አገሪቱ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ድህነቷ የተገለጠ፣ በግልኮስ እንደሚኖር ህመሙ የጸናበት የአልጋ ቁራኛ ሰው ከአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዕርዳታ የሚደረግላቸው የአፍሪካ አገራት መካከል በቀዳሚነት የምትሰለፍ በየዓመቱ ቢልዬን ዶላሮች የምትቀበል የበለጸጉ አገራት (የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት) ተመጽዋች አገር ናት።

 

ኢትዮጵያ እንደ አገር ይህንና ያንን ለዓለም ገበያ አቀርባለሁ በማለት የምትታወቅ አገር ብትሆንም ሐቁ ግን አገሪቱ ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው ምርት የሚገኝ ገቢ ሁሉ ተሰብስቦ አገሪቱ አይደለም መንግስታዊ ተቋማት ልታስተዳድርና ልትደጉም ቀርቶ በቁጥር ለአስር ሺህ የመንግሥት ሠራተኛ የስድስት ወር ደመወዝ ክፍያ መፈጸም የማትችል እንደ ዐቢይ አህመድ ዓሊ አባባል ድሃ አገር ናት። ኢትዮጵያ እንደ አገር በምትመድበው ዓመታዊ በጀትዋ ሦስት አራተኛው ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገራት በእርዳታ መልክ ከምታገኘው የምጽዋት ገቢ ነው። ይህ ማለት፥ የአገሪቱ መከላከያ ጸጥታና ደህንነት ጨምሮ ኢትዮጵያ ለጤናና ለትምህርት እንደ አገር ከምትመድበው በጀት ከግማሽ በላይ የሚሸፈነው በእርዳታ መልክ ከአሜሪካ ብቻ በሚገኘው የምጽዋት ዶላር ነው። ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ ግን፥ ኢትዮጵያ እንደ አገር ህልውና እንዲኖራት ያላለሰለሰ ጥረት ያደረገችና እያደረገች የምትገኝ አገረ አሜሪካ ጸረ ህልውናችን ነች፣ አሜሪካ ጸረ ሉዓላዊነታችን ነች፣ ኢትዮጵያን እንደ ሲሪያ፣ ሊብያና አፍጋኒስታን ሊያደርጓት የተነሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች፣ ከአሜሪካ የምናገኘው የነቀዘ ስንዴ ነው፣ እርዳታቸው ይቅርብን! እየተባለ በውሸት ውንጀላ ጸረ-አሜሪካ የሚጎሰም የጥላቻ ነጋሪት መስማት የተለመደ ሆኗል። የሚደንቀው፥ እነዚህ በጠላትነት ተፈርጀው በይፋ በአደባባይ እየተብጠለጠሉ የሚገኙ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት የእርዳታ እጃቸው የሰበሰቡ ቅጽበት በቀናትና በሳምንታት ውስጥ ኢትዮጵያ አገር መሆኗ ይቀርና ኦናና ቆሻሻ መጣያ ስፍራ/ቆሼ እንደምትሆን ሳስበው ነገሩ እጅግ ይሰቀጥጠኛል።

Videos From Around The World

 

ከነተረቱ ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ኖሮ በዉኑ ደርቆ ይሞት ነበር እንደሚባለው ሆነና ነገሩ፥ ኢትዮጵያውያን በምንም ነገር የማይመጥኗቸው አገራትና መንግስታት ወደ ኢትዮጵያ ደረጃ በማውረድ አገራቱና መንግሥታቱን እንደ የቆሎ ጓደኛቸው መሳለቅ፣ ማንጓጠጥ፣ ማንኳሰስ፣ መቦጨቅ፣ ማሳጣት፣ ማቃለል፣ ማብጠልጠልና መወረፍ ተክነውበታል። ይህን በማድረጋቸው የሚፈጥርላቸው ወንዝ የማያሻግር ባዶ ስሜትም ልዩ ነው። ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ አደንዛዥ ዕፅ ለበሬ ወለደ ዓይነቱ ክፉ ወሬ ያላቸው ልዩ ፍቅር የላቀ ከመሆኑ የተነሳ ወሬ ፍለጋ የማይገቡበትና የማይሄዱበት ስፍራ የለም። በጠላትነት የፈረጁት ህዝብና አገር እንዲሁም የአሜሪካ ዓይነቱ የበለጸጉ አገራት በተመለከተ ክፉ ዜና ሲሰሙም እጃቸው በኢትዮጵያ ስላነሱ ነው፣ የኢትዮጵያ አምላክ ተፋረዳቸው ወዘተ እያሉ ደስታቸው ሲገልጹ በፍቅር ነው። ነገር ግን በጦርነት፣ በርሃብ፣ በበሽታ፣ በችጋርና በእጦት በተቀመጠበት ሞት የሚወስደው፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወጥቶ የምድር አራዊትና የዓሳ ነባሪ ሲሳይ ሆኖ የሚቀረው ዜጋ ሁሉ ትተን፥ የአዲስ አበባው ቆሺ የቆሻሻ ክምር ተራራ ተንዶ፣ ሰሙኑ ደግሞ ከተማው ላይ የተከሰተ ጎርፍ የተነሳ የጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት አስመልክተው አፋችን በሰው አገር ላይ ስለከፈትን ነው፤ የአሜሪካና የአውሮፓ አምላክ ተፋረደን አይሉም። በነገራችን ላይ፥ አገራት በተናጠል አምላክ ቢኖራቸው ኖሮ የኢትዮጵያ ዓይነቱ ድሃ አገራት አምላክ እውነተኛ አምላክ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ጋር በተያያዘ እዚህ ላይ አንድ ነገር ቁም ነገር ለማንሳት እወዳለሁ፤ ይኸውም፥ በአባታቸው ሆነ በእናታቸው ወገን ሰባት ትውልድ ወደ ላይ ወደ ግራና ወደ ቀኝ ቢቆጠርና ቢፈለግ አይደለም የመኪና ባለቤት ሊሆኑ ቀርተው የመኪና ባለቤት የሆነ ሰው በጎረቤት ደረጃ ኖራቸው የማያውቁ ሰዎች ማለትም አሜሪካ መጥተው መኪና የመንዳት ዕድሉ የገጠማቸው፣ ዓመት ሙሉ ሰርተው ባጠራቀሙትና አንዳንድ ጊዜም ከዚህም ከዚያም በሚገኝ የብድር ገንዘብ በአመት በዓል ሰበብ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ዶሮ ወጥ በፍቅርና በስስት ከመብላት ህይወት ወጥተው በየቀኑ ዶሮ ወደ መብላት፣ በሳምታትና በቀናት ወንዝ ዳር አልያም ሳፋ ላይ ተቀምጦ ገላው ሲታጠብ የነበረ በቀን ሁለትና ሶስት ጊዜ ሙቅ ሻወር መውሰድ፣ አንተን/ቺን ያረገዝኩበት ዕለት ምን ነው ውሃ ሆነህ/ሽ በቀረህ/ሽ እየተባለ እየተረገመ/ች ያደገ ሁላ አርባና አምሳ ዕድሜ ሞልታቸው በርዝ-ደይ ፓርቲ አለኝ! እየተባለ ዓመት በመጣ ቁጥር ሃፒ በርዝደይ ለመዝፈን የታደሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ፈጣሪ ይቁጠረው። አንድም፥ አሜሪካን አገር ሰርተው ወደ ኢትዮጵያ በሚልኩት ገንዘብ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተሰቦቻቸው ፍራሽ ላይ መተኛት የተቻላቸው ዜጎች ቁጥር ፈጣሪ ነው የሚያቀው። ታድያ የሚልክም የሚቀበልም አሜሪካ ትውደም! እያለ ሰው ያደረገችው አገር ሲራገም የአሜሪካውያን አእምሮ ያፈራው በረከት እንዲካፈል ዕድሉ የሰጠው ፈጣሪ ምን ይለኛል አይልም።

 

ሌላው፥ በተለይ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው! ኢትዮጵያዊነት አንድነት ነው! በማለት የሚታወቁ አረመኔዎች በባህሪያቸው፥ ከማይደርሱበትና ሊደርሱበት ከማይችሉት አካል ጋር ራሳቸው ማስተካከል፣ ማወዳደርና ማነጻጸር፤ ብሎም ስለማያውቁት እውቀት እንደ አዋቂ ሰው አፋቸው ሞልተው ማውራትና ባላለፈባቸው እውቀት መፈትፈት፤ ለምሳሌ ያህል፥ ስለ ሞሳድ፣ ሲ.አይ.ኤ፣ ኤም.አይ ሲክስ የመሳሳሉ የበለጸጉ አገራት ትላልቅ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት እንዲሁም እንደ ሮዝቻይልድስ፣ ኢሉሚናቲና ፍሬማሶን የመሰሳሰሉ ህብረቶች እያነሱ መጣልና መሰልቀጥ፤ ለጥቆም፥ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ላይ ያሴሩት ሴራ ከሸፈ፣ ኢትዮጵያውን የመበተን ምስጢራዊ አጀንዳቸው ተጋለጠ ወዘተ እያሉ ማለቂያ የሌለው አሳፋሪ በሬ ወለደ ወሬ ማውራትና መቃዠት፣ መታጠንና ማራገብ፣ በዚህ መልኩ የሚነገሩ ምክንያታዊነት የሚጎድልባቸውና የእውነት መሰረት የሌላቸው ሐሰተኛ ወሬዎች ተጠምዶ መዋልና ማደር ለኢትዮጵያውን የሚፈጥርላቸው ስሜት ቀደም ሲል እንደተገለጸው ልዩ ስሜት ሲሆን ሰዎቹ ለእንደዚህ ዓይነት የክፉ ደብተራ ድርሰትና ተረት ተረት ያላቸው ፍቅርም የተለየና የላቀ ነው።

 

ባጎረስኩ ተነከስኩ

 

አሜሪካና አውሮፓ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ ነው የሚለው ክስ መነሻው በእውነቱ ነገር አገራቱ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ስለ ገቡ ሳይሆን በዋናነት፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር መክሮና ዘክሮ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸሙው የዘር ማጥፋት ወንጀል ለምን ተቃወሙኝ ነው። ይህ የእኔ ቃል ሳይሆን፥ ዐቢይ አህመድ ዓሊ ራሱ በፓርላማው ፊት ቀርቦ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሶማሊያ ሳይጠይቁኝ ለምን አሁን በትግራይ ይጠይቁኛል? ሲል ያሰማው አቤቱታ ልብ ይሏል። በመቀጠል፥ የፈለኩትን ባደርግና ብፈጽም ለምን ከእኔ ጋር አልቆሙም የሚል የመረበሽ ስሜት የፈጠረው ውንጀላ ነው። በተጨመሪም፥ የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በመጣስ በትግራይ ላይ ወረራ የፈጸመ ኢሳይያስ አፈወርቂ ከትግራይ ለቆ ይወጣ፤ በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ ይድረሳቸው፤ ደም መፋሰሱን አቁሙና በሰላማዊ መንገድ ለመደራደርና ለመወያየት ተስማሙ ነው። አገራቱ ይህን በማለትና በማድረግም በገዛ እጁ መንግስትነቱን ያጣ፣ ህልውና የሌለው፣ ያበቃለትና የፈራረሰ መንግሥት ህልውና እንዳለውና አገሪቱም በተመሳሳይ የፈራረሰች አገር ሆና ሳለች እንደ አገር በማስቀጠል ረገድ በአሁን ሰዓት ጉልህና ቀዳሚ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኙ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ግን በተቃራኒው የዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን ማምለጫ ጆከር ሆነው በጠላትነት ተፈርጀው ወታደር ለመመልመልና ህዝቡን ለመቀስቀስ እንዲሁም ገቢ ማሰባሰቢያ አድርጓቸው ይገኛል። ባጎረስኩ ተነከስኩ ይሉኋል እንግዲህ ይኸ ነው!

 

በርግጥ፥ አሜሪካ ጦርነቱ መቼ፣ የት፣ እንዴትና በማን እንደ ተጀመረ ብቻ ሳይሆን የዐቢይ አህመድ ዓሊ አጀንዳ በመደገፍ በትግራይ ህዝብ ላይ ለተፈጸመ የተቀነባበረ ወረራ ይሁንታዋ የሰጠች አገር ለመሆኗ የኒውዮርክ ታይምስ ሴኔተር ክሪስ ኩንስ ጠቅሶ ለአደባባይ ያሰጣው ሐቅ ሁላችን እናስታውሳለን። በኢሳይያስ አፈወርቂ አስተባባሪነት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ከአማራ ልሒቃን፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኢምሬት ጋር መክሮና ዘክሮ የፈጸመው ሁሉም ዓይነት ህግ የሚጥስ ወረራ ለመሆኑ አሜሪካ ሆነች የአውሮፓ አገራት አሳምረው ያውቃሉ። ምዕራባውያኑ ይህን እያወቁ ግን፥ የአሜሪካው ሴክረታሪ ኦፍ ስቴት ማይክ ፖምፒያ ኤርትራ በትግራይ ላይ የፈጸመችው የጦር ወንጀል በማውገዝ ፈንታ እናመሰግናለን በማለት ሲያወድሱ፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በፊናው ከዐቢይ አህመድ ዓሊ ባገኘሁት መረጃ በማለት ኤርትራ በትግራይ ላይ የፈጸመችው ወረራ አላየሁም አልሰማሁም በማለት በስሌት ሐሰተኛ ምስክርነት መስጠታቸው ሳያንስ ሰሙኑ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የሚመራው ዕርቀ ሰላም በኢትዮጵያ እንዲካሄድ በማለት ያስተላለፉት አደገኛና መርዛም መልዕክት ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በተመለከተ ባላንጣነት ሳይሆን ግልጽ የሆነ ውለታ የሚያሳይ ነው።

 

የአሜሪካና የአውሮፓ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ላለፉት ስምንት ወራት ሙሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሠራዊት ትግራይን በአራት አቅጣጫ ከበባ ውስጥ በማስገባትና በመነጠል በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸሙት በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም፣ የጦር ወንጀለኛነትና ህዝብን እንደ ህዝብ ለማጥፋት ያለመ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸማቸው በተጨባጭ እያወቁ በትግራይና በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል በስሙ በመጥራት፥ ይህን ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል የጻፉ፣ የነደፉ፣ ያስተባበሩና የፈጸሙ ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ ዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፊት በማቆም ፍትህ ማድረግና ማረጋገጥ ሲጠበቅባቸው የራሳቸው ጥቅም ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ሲሉ ብቻ ግን ከአፍኣ በዘለለ እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ ያረጋገጡት ፍትህ የለም። የርዕሰ ኃያላኑ አገራት ጸረ-ፍትሕ የሆነ አቋምና ለኢትዮጵያ እንደ አገር ያላቸው ወገኝተኝነት ታድያ በዚህ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ ዐቢይ አህመድ ዓሊና የአማራ ልሒቃን ያሰማሩት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወራሪ ሠራዊትና ሚኒሻ ከባድ ወታደራዊ ሽንፈትና ኪሳራ ደርሶበት ትግራይ ለቆ እንዲወጣ ከትገደደ በኋላም ሐሰት የማይሰለቸው የውሸት ፋብሪካ ዐቢይ አህመድ ዓሊ የደረሰበት ወታደራዊ ሽንፈትና ኪሳራ ለማስተባበልና ለመደበቅ የእርሻ ወቅት በመሆኑ የትግራይ ገበሬ እንዲያርስ ከትግራይ ወጥቻለሁ ብሎ ሲያበቃ ከጥይት የተረፈ የትግራይ ህዝብ በርሃብና በበሽታ ለመጨረስ ትግራይ ዳግም ከበባ ውስጥ በማስገባት ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እየፈጸመው ያለ ግሃድ የሆነ ወንጀል እየታወቀ ዳሩ ግን ዐቢይ አህመድ ዓሊ በራሽያ የጦርና የፖለቲካ አማካሪዎች እየታገዘ በትግራይ ህዝብና በዓለም ማህበረሰብ ላይ እየሰራው ያለ ድራማ እንደ ፖለቲካዊ ብልጠት ተቆጥሮ ርዕሰ ኃያላኑ ኃላፊነታቸው በመወጣት ከምግብና የመድሃኒት ዕጦት የተነሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ቅጠል ሊረግፍ የሚችል የትግራይ ህዝብ ለመታደግ በመቁረጥ ፈንታ የለመዱት የቃላት ጨዋታ በመጫወት እያሳዩት ያለ ዳተኝነት በጥቅሉ አገራቱ ለኢትዮጵያ እንደ አገር ያላቸው ጠላትነት የሚያሳይ ሳይሆን በእውነት ላይ በማመጽ ለኢትዮጵያ እንደ አገር ያላቸው ባለሟልነት ደግመው ደጋግመው አረጋግጠዋል።

 

በውሸት የተጠመቀ፣ ያለ ውሸት መኖር የማይችል፣ እውነት አላርጅክ የሆነበት ስምዓ ሐሰት ዐቢይ አህመድ ዓሊና በሬ ወለደ አሉባልታ በማራገብና በማናፈስ ቀዳሚና ተከታይ የሌላቸው ልሳኖቹ እንደሚያስተጋቡት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ታድያ አሜሪካና አውሮፓ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነ አቋም የሚያራምዱ አገራት ቢሆኑ ኖሮ ኖቨምበር አራት ኢትዮጵያ ኦፊሻሊይ ያበቃላት ነበር። የምዕራባውያን አገራት ምኞትና መሻት ሀገረ ትግራይ እውን ሆና ማየት ቢሆን ኖሮ ትግራይ ዛሬ አዲስ ምስራቅ አፍሪካዊት አገር ተብላ ትታወቅ ነበር። የታይዋን የሀገራዊነት አጀነዳ በተመለክተ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት የሚያራምዱት አቋም የበረዶ ያህል የጸዳ ነው። አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ሀገረ ታይዋን የማየት ብርቱ መሻት አላቸው፤ ይህን አጀንዳቸው ሲያራምዱም በድብቅ ሳይሆን በይፋ በአደባባይ ነው። ታድያ ምዕራባውያኑ ቻይና ካልፈሩና ለቻይና ካልተመለሱ፥ በምህረታቸው የምትኖር፣ ሌላው ይቅር የዕለት ጉርሻ ለማግኘት የሚቸግራት፣ በቀን አንድ ጊዜ ለመብላት መከራ የሆነባት ኢትዮጵያ የሚፈሩበት ምክንያት አለ ብሎ የሚያምን ሰው ካለ በእውነቱ ነገር ፈጣሪ ምህረቱን ይዘዝለት ከማለት ውጭ ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ለማስረዳት መሞከር በጭልፋ እየቀዱ ሰላማዊ ውቅያኖስን አደርቀዋለሁ ብሎ ማመን ይቀላልና። ዐቢይ አህመድ ዓሊ

 

በተረፈ፥ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራትና መንግስታት ፍላጎትና ጥረት እጁን ይዘው ለመንግስትነት ያበቁት ወዶ ገብ አገልጋይ ዐቢይ አህመድ ዓሊና የዙፋኑ ተሸካሚዎቹ የአማራ ልሒቃን እንደሚያራግቡት ፕሮፓጋዳንዳ ማለትም ኢትዮጵያ መገነጣጠል ነው የሚል ሐሰተኛ ውንጀላ ሳይሆን ከምንም በላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለ-ሥልጣናት ሰሜን ዕዝ ተጠቃ በሚል ሐሰተኛ ውንጀላ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ግፍ ማስቆም፣ ከዚህ የተነሳ ለርሃብ የተጋለጡ ወገኖች እህል ውሃ እንዲደርሳቸው በማድረግ ዜጎች ከሞትና እልቂት ማትረፍና መታደግ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝብ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥና ተጠያቂነት ማስፈን ያተኮረ በመሆኑ የፈለገው ሊያገኝ ያልቻለና ውሎ አድሮም ከተጠያቂነት እንደማይመልጥ የገባው የውሸት ቋት ዐቢይ አህመድ ዓሊ ግን በቀድሞ ጌቶቹ፣ ባለውለታዎቹና ሳይሳሱ ባጎረሱት ምዕራባውያን እጆች ላይ ክህደት የለመደ ጥርሱ ለመሳል ተገዷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፥ ኢትዮጵያን የመበተንና የማፈራረስ ዓላማና ፍላጎት ያለው ብቸኛ የኢትዮጵያ ጠላት ሌላ ማንም ሳይሆን ከኢትዮጵያውያን በላይ ኢትዮጵያዊነት በማራጋብ የሚታወቀው የጎንፎ ውስጥ ስንጥር ኢሳይያስ አፈወርቂ ለመሆኑ የማያውቅ ባለ አእምሮ ሰው ይኖሯል የሚል እምነት የለኝም። ግብዝ፣ አስመሳይ፣ አጉረምራሚ፣ ምዋርተኛና ሴሰኛ ዜጋ ግን ሁል ጊዜ ጠላቱን ወዳጅ ወዳጁን ጠላት አድርጎ መቆላመጥ፣ መጮህና ነገርን ማሳበቅ ስለሚቀናው ኢትዮጵያን ሳላፈርስና ደም ሳላቃባ አልተኛም! ብሎ የምኞቱን ያደረገና ያገኘ ኢሳይያስ አፈወርቂን ወዳጅ፥ አገሪቱ ከድህነት እንድትወጣና ዜጎችዋም እንደ ሰው እህል በልተው እንዲያድሩ ለማስቻል የአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ቀዳዳዋ በመድፈን ላይ የተሰማሩ አገራትና መንግስታት ደግሞ በጠላትነት መፈረጅ ተያይዘዉታል። ምን ያህል ርቀት ይጓዛሉ? ለሚለው ጥያቄ በቅርቡ ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል።

 

E-mail: mahbereseytan@gmail.com

Back to Front Page