Back to Front Page

ጎንደርና ኤሪትርያ:- አገኘሁ ተሻገር እውነታውን ፍርጥ አደረገው

ጎንደርና ኤሪትርያ:- አገኘሁ ተሻገር እውነታውን ፍርጥ አደረገው

ኻልኣዩ ኣብርሃ 07-26-21

የዘንድሮይቱ ኢትዮጵያ የምትደንቅና የምታስደምም ሆናለች። "ሰውየው ከመሞቱ በፊት ሲቅበዘበዝ ነበር" የሚለው አባባል ሳይመለከታት አይቀርም። "ኢትዮጵያ ከመናዷ በፊት ለያዥ ለገራዥ አስቸግራ ነበር፣ ተይ በቅጡ ያዢው አለዝያ ትጎጃለሽ ብትባል ከጁንታስ ሞት ይሻላል ብላ ቁራጭ ገመድ ይዛ እየሮጠች ነው" ብሎ ማለት ትክክል አይደለምን? ኢትዮጵያ ዋና ከተማዋን ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር- ባህርዳር ቀይራለች፣ ፕሬዚደንቷ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሯ፣ ጠቅላይ ጦር እዛዧ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤቷ ሁሉንም ጠቅልሎ አገኘሁ ተሻገር ሆኗል።

አገኘሁ ተሻገር ቅዱስ ያልሆነ ጦርነት እየመራ፣ የአማራን ህዝብ በሓምሌ ጨለማ ከሞቀ ቤቱ፣ ከሚያርስበት ማሳ፣ ከየህዝብ አገልግሎት ስራ እያፈናቀለ፣ በቂ ስንቅ ሳይኖረው፣ በቂ ልብስም ሳይደርብ፣  ለእልቂትና ለምርኮ ለመላክ ክተት ሲያውጅ ውቅያኖስ በሚመስል ጥቁር ሰማያዊ ሙሉ ልብስ፣ የፀሃይ ብርሃን የመሰለ ነጭ ሸሚዝና ክራባት ለብሶ ነው። ይህ የሚያመለክተው ከውስጡ ያለው አስተሳሰብ ከህዝባዊ አላማ የራቀ የግልና የቡድን አላማ መሆኑ ነው። "የአማራን ህዝብ ለማጥፋት የትግራይ ህዝብ እየመጣ ነው" ብሎ የሚያውጅ ሰው የሚለው እውነት ቢሆን ኖሮ ወገቡን ታጥቆ ፎጣውን ጠምጥሞ ከየቤቱ እየጎተተ ለሞት ከሚልከው ምስኪን ህዝብ ጎን ይዘምት ነበር። የአማራ ዘማች ድሮን ቢሆን ኖሮ ከቢሮ ሆኖ ማሰማራት ተገቢ አሰራር ነበር። ለነገሩ እብድ ሲያሳብደው ሳይጠይቅ ሳያጣራ የሚያብድ ህዝብ ድሮን መሆን ሲበዛበት ነው። መሪዎቹም ለሱ የሚገቡ ናቸው ማለት ይቻላል።

Videos From Around The World

የአስተሳሰብ ልዩነት ከቃላት ይልቅ በተግባር ይገለፃል። ለራሱ ድሮ ለቆረጠባት አንዲት ህይወቱ ብሎ ሳይሆን ምራን ብሎ እምነት ለጣለበት የትግራይ ስድስት ሚልዮን ህዝብ ህይወትና ደህንነት ከሰውነት ውጪ ሆኖ ከበርሃ መቐለ የገባው / ደብረፅዮን አንገቱ ላይ የህዝባዊ ትግል አርማ የሆነችውን ሽርጥ ለብሶ ይታያል። ከጦርነቱ በፊት ግን በሙሉ ልብስ፣ ነጭ ሸሚዝና ክራባት አምሮ ለሚድያ ይቀርብ ነበር። የህዝብ እውነተኛ መሪ ህዝብ የሆነውን ይሆናል። ይህ ሁሉ ተአምር የሚሰሩት ጄኔራሎችም ስለደረቡት ልብስ ጥራት ሳይሆን ስለህዝባቸው ነፃነት እየተጨነቁ ከሰውነት ውጥተው ይታያሉ። በዚህ የትግራይ የነፃነት ትግል መሪና ተመሪን በተግባር ላይ እንጂ በእይታ ብቻ መለየት አይቻልም። አገኘሁ ተሻገር ጆርጅ ቡሽን እየኮረጀ ያለ ይመስላል። ጆርጅ ቡሽ ጦር ወደ አፍጋኒስታን ልኮ ቴክሳስ ከሚገኘው የቤተሰብ ቤት ለእረፍት ይሄድ ነበር። ድንጋጤውና ተስፋ መቁረጡ ከንግግሩ መላቅጥ መጥፋትና አደገኛ መሆን የሚታወቅ ቢሆንም ህዝብ አስፈጅቶ፣ አገሪቱን አመሳቅሎ ምንም ሳይነካ የመቆየት ተስፋ እንደሰነቀም ሁኔታው ያሳብቃል። አገኘሁ ተሻገር አውዳሚ የሆነና በህዝቦች መሃል መቸውም ሊሽር የማይችል ደመኝነት የሚያስከትል ጦርነት እያወጀ የትልቅ ኩባንያ ዋና አስፈፃሚ መስሎ የሚቀርበው እውነትም ይህን ጦርነት ለትልቅ ቢዝነስ ሊጠቀምበት እንደሆነ ራሱ በገዛ አፉ ፍርጥ አድርጎታል። አገኘሁ ተሻገር ፍርጥ ያደረገውና የኢትዮጵያ ህዝብ ለእነ አገኘሁና ለነኢሳያስ ሴራ አገሩን መስዋእት ከማድረጉ በፊት ሊረዳው ስለሚገባው አብይ ጉዳይ ላይ ላተኩር።

ለምንድነው ትግራይን እንዲህ የመረረ ጠላት ተደርጋ የተሳለችው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። እውን ይህ ሁሉ የትግራይ ጠላት ኢትዮጵያን ከልቡ የሚወድ ነውን? እውን ትግራይ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመቻቸው ለህልውናዋ አደገኛ የሆኑ ነገሮች በተጨባጭ ማስረጃ ዘርዝሮ ማቅረብ የሚችል አለን? እውን ትግራይ ኢትዮጵያን ከጣልያን፣ ከድርቡሽ፣ ከግብፅ ከማዳን፣ በቅርቡም አገሪቱን ከፍታ ላይ ከማድረስ በስተቀር ሁለት የባህር ዳርቻዎችን ለቅኝ ገዢዎች አሳልፎ ከመስጠት የከፋ ጥፋት በኢትዮጵያ ላይ ፈፅማለችን? ነገሩ ሌላ ነው። አማራ-መር ሆኖ የኖረው፣ አሁንም በኦሮሞ "የበላይነት" በስተጀርባ ተጠናክሮ የቀጠለው፣ የእጅ አዙር የአማራ ልሂቃን አገዛዝ አሁን በአገኘሁ ተሻገር "ያላዋቂ ሳሚነት" ግልጥልጡ ወጥቷል። በተጋለጠው የድምፅ ቅጂና በተለያዩ አጋጣሚዎች አገኘሁ ተሻገር በሚያደርጋቸው ንግግሮች ውስጥ ይፋ ከወጡት ከብዙ ነገሮች አንዱ ከአራት ኪሎ ጀርባ ሆኖ ኢትዮጵያን የሚነዳት የአማራው ጥምር የፓለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቅ መሆኑን ነው። ይህ ወሳኝ መረጃ ነው። እነዚህ ልሂቃን ገብቶትም ሳይገባውም የአማራ ጉዳይ ነው በሚል በስሜት የሚያጫፍረው የአማራ አካደሚክ ልሂቅን በማሰማራት "ኦሮሞ የመንግስት ስልጣንን በሞኖፓል ይዟል፣ አማራ እየተጠቃ ነው" እያሉ በማማረር አገሪቱን ቢያደነቁሩም ምርጥ የሆኑትን የኦሮሞ ልጆችን ከርቸሌ ያከረመው ግን በውስጥ ዋናውን ተግባራዊ ስልጣን የያዘው የአማራው ፓለቲከኛና ለማዳዎቹና እያለቀሱ የሚተባበሩት ጎበናውያን ናቸው። የወጣው እውነታ እንዲህ ያላል:- "የኢትዮጵያ ጉዳይ በኛ እጅ ነው ያለው" የሚል ነው። ጉድ ያሰኛል አይደል? በዚህ አላበቃም። የወልቃይት ጉዳይ "የአማራ የማንነት ጉዳይ" ነው ሲባል ከረመ። "ምእራብ ትግራይ ተደርገው የተካለሉት የኛ ወገኖች ናቸው" ተባለ። የአማራ የማንነት ጉዳይ ከሆነ የአማራ ጉዳይ ብቻ መሆኑ ነው አይደል? የቦረና ጉዳይ የሶማሊ የማንነት ጉዳይ ነው ከተባለ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን አገባው? ወልቃይት 98 ከመቶ ትግርኛ ተናጋሪ ቢሆንም አማራ ነው መባሉ አስቂኝ ቢሆንም ያው ተነስቷልና በፌደራል ህግ ይፈታል። የቦረና ኦሮሞዎችም ሶማሊ ናችሁ ከተባሉ እንደ ኮሜዲ እየሰሙ መዝናናት ነው።

ወልቃይት ያሉት ተጋሩ አማራ ናቸው ብሎ ከወረረ በኋላ ልቀቅ ሲባል "ወልቃይትን ልቀቅ ማለት ኢትዮጵያ ትፍረስ ማለት ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ወልቃይትን ለማዳን ዝመት" ከተባለ ከዚህ ቅጥፈት በስተጀርባ ሌላ ግዙፍ ሴራ እንዳለ ያመለክታል። አገኘሁ ተሻገር ለታማኝ በየነ እንዲህ ብሎ ነገረው: "የወልቃይትን ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለማድረግ እየሰራን ነው"

ይህ ማለት የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም አልነበረምም፣ ገና አሁን የኢትዮጵያ ጉዳይ ለማድረግ ከነአገኘሁ ተሻገር የፓለቲካ ፋብሪካ ውስጥ እየተፈበረከ ለመላ ኢትዮጵያ ሊከፋፈል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን የመሰሪዎች የፓለቲካ ሸቀጥ የሚገዛው በገንዘብ ሳይሆን ጎንደርና ትግራይ ዘምቶ ህይወቱን በመስጠትና አካሉን በማጉደል ነው። እኔ ኢትዮጵያውያን ነገር የሚገባቸው አርቆ አሳቢ ህዝብ ይመስሉኝ ነበር፣ ለካ ማንም አጭበርባሪ እያስጨፈረና እያስፎከረ በቀላሉ ሊነዳቸው ይችላል? እገኘሁ ተሻገር የወልቃይት ጉዳይ የጎንደር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ አስመስሎ እያጭበረበረ መሆኑ ከተሰማ በኋላም ልዩ ሃይልና ሚሊሻ የሚልኩ ክልሎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን መስቀል አደባባይን ያጥለቀለቀው ሰልፈኛም "ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ" እያለ ነበር የዋለው! ኢትዮጵያ ምን ሆነች? ምን መጣባት? ትግራይ ልታጠፋት ነው? ወይ መደናቆር! ትግራይ ያለችው "የምእራብ ትግራይ መሬቴንና ህዝቤን መልሱ" ነው። ነገሩ እኮ ብሬን መልስልኝ ሲባል ልትገድለኝ ነው ብሎ ከአጀንዳ ውጪ እንደሚጮህ ሰው መሆኑ ነው። አራምባና ቆቦ!

ኢትዮጵያን ከመፈረካከስ አፋፍ ያደረሰው ይህ ሁሉ ውሸት፣ ይህ ሁሉ ማጭበርበር፣ ይህ ሁሉ የፓለቲካ ትብተባ የጎንደር የቢዝነስ ኮሚዩኒቲ ከኤሪትርያ ጋር የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ቆርጦ ስለተነሳ ነው። የጎንደር የኢኮኖሚ ልሂቃን በአገር ውስጥም  በውጪም ከሌላው አማራ በላቀ የቢዝነስ ክንዳቸውን አፈርጥመዋል። ይህን የቢዝነስ አቅማቸውን መሬት እውርደው ለማስፋፋት በማይመቸው የጎንደር ጂኦፓለቲካ ተቀይደዋል። ጎንደርን የኢትዮጵያ ቁንጮ እንደሆነች አድርገው የሚያስቡት የጎንደር ልሂቃን የድሮ የበላይነቷ እንዲመለስ ይመኛሉ። ከዛም ሲያንስ የአማራ ማእከልነቷን ይሻሉ። ይህ ሁሉ ተግባራዊ ይሆናል ብለው የሚያስቡት በኢኮኖሚም የበላይ በማድረግ ነው። እርግጥ ነው ይህን የሚያደርጉት ለሰፊው የጎንደር ህዝብም አይደለም፣ ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው ጥቅም ነው። የጎንደር ህዝብ የአማራ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ እየሞተ እየቆሰለ በባዶ ሆዱ እያቅራራና "ኸረ ገዳይ" እየዘፈነ ድልድይ ሆኖ ሊያሻግራቸው እንጂ ምንም የሚያገኘው ነገር የለም።

ከኤሪትርያ ነፃነት በፊት ጎንደር ለውጭ ንግዷ ስትጠቀም የነበረችው የጂቡቲን ወይንም የአሰብን ወደብ ሳይሆን ምፅዋን ነበር። ከጎንደር በሽረ፣ አድዋ፣ ዓዲዃላና አስመራ ወደ ምፅዋ የሚያደርሰው አውራ ጎዳና ያለ ገደብ መጠቀም ይቻል ነበር። ጥቁር አዝሙድ፣ ሰሊጥ (ከሁመራ) ጥራጥሬ፣ ሌሎች የጎንደር ምርቶች በዚሁ ወደብ ይስተናገዱ ነበር። የውጭ ንግድ ብቻ ሳይሆን የኤሪትርያ ያገር ውስጥ ገበያም ከጎንደር በሚላኩ የግብርና ምርቶች ይሸፈን ነበር። የኤሪትርያ ትግል በተለይም የትግራይ የፓለቲካ እንቅስቃሴ መጋጋል ሲጀምር ግን ይህ የንግድ መስመር የመቋረጥ እጣ ገጠመው። ዋናው ገበያቸው አዲስ አበባ የሆኑትና በዛውም ጂቡቲ የሚመቻቸው ጎጃም፣ ወሎና፣ ሸዋ በኤሪትርያ ገበያ መቀዝቀዝና በምፅዋ መስመር መዘጋት የጎንደርን ያህል አልተጎዱም። ስለዚህ የኤሪትርያ መስመር የጎንደር እንጂ የቀሪው አማራ ክልል ጥያቄም ችግርም አይደለም።

በደርግ ጊዜ አሁን ካለው የአማራ ክልል ውስጥ እንደ ጎንደር በቀይ ሽብር የተጠቃ የለም። የኢህአሠ የበርሃ ትግል የተጧጧፈውም በበለሳ፣ በአለፋ፣ በአርማጭሆ በርሃዎች ውስጥ ስለነበር ኢህአፓ ሲፈርስ በአስር ሺዎች የሚቆጠር የከተማ ወጣት፣ የገጠሩ ሰው ሳይቀር እንዳለ ወደ ሱዳን ገብቶ የአሜሪካ ቪዛ አግኝቷል። በኋለኘቹ አመታትም በቤተሰብና በጋብቻ ቪዛ የአሜሪካ የጎንደር ኮሚዩኒቲ እጅግ ግዙፍና ወሳኝ እንዲሆን አድርጎታል። በአገር ውስጥም የጎንደር ሰዎች የሃይማኖቱን፣ የፓለቲካውን ተቋማት በስውርም በይፋም በመቆጣጠራቸው ለኢኮኖሚው የበላይነት በር ከፍቶላቸው ነበር። በውጭም በአገር ውስጥም በአማራ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ ራሳቸውን የመረጡ ተወካዮች ሆነው ስለተገኙ ቀሪው አማራ እነሱ በቀደዱት ቦይ የመፍሰስ አዝማሚያ ሲያሳይ ቆይቷል። "ጠላትህ ትግራይ" ነው እያሉ ሲያደነቁሩት ስለቆዩ በሌለ ነገር በራሳቸው የጂፓለቲካ ጥያቄ ቅርቃር ውስጥ እየከተቱት መሆኑን መገንዘብ አልቻለም። በዛውም ኢትዮጵያን የሚጎዳ መስመር መያዙን በትክክል የተረዳ አይመስልም።

አሁን የጎንደሮች ሃብት ሲከማችና ከበርቴ ጎንደሬ ሲበረክት ጎንደር በቂ እግር መዘርጊያ የላትም። 1/ለሰፊ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገው መሬት መገኘት አለበት 2/ ሰፊ የቅርብ ገበያና የውጭ ንግድ ያስፈልጋታል። ሰፊ እግር መዘርጊያ መሬት ጉዳይ ሲነሳ ናዚ ጀርመንን ያስታውሰናል። የጀርመን ኢኮኖሚ አድጎ በነበረበት ወቅት የጀርመን ምድር ለዚህ ኢኮኖሚ የሚመጥን በቂ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት አልነበረውም። በሂትለር የሚመራው የናዚ ጂኦፓለቲካ አስተሳሰብ "ሊበንስ ራውም" ወይንም "የመስፋፊያ ቦታ" የሚል መርህ አንግበው ነበር አውሮፓን የወረሩት። ጎንደር፣ በተለይ የበላይ ነን የሚሉት ደቡብ ጎንደር ተራራማ፣ ሰበርባራና ሸለቋማ መሬት ሲሆን ድርቅም የሚፈታተነውና ቅዝቃዜው የበረታ ምድር ነው። ብዙ ህዝብ ከሰፈረባቸው ለም ግን ውስን የጣና ዳር መሬቶች ውጪ ቀሪው ጎንደር በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ እጅግ ተራራማ ነው። ወደ መካከለኛው ምእራብ ያለው አርምጭሆም ሰበርባራና ህዝብ የሰፈረበት ነው። ምእራቡ ባመዛኙ የቅማንት ማህበረሰብ የሰፈረበት ሲሆን ከዛ ቀጥሎ ያለው መተማም በርካታ አራሽ የሰፈረበትና ምርት ለመጓጓዝም የማይመች ነው። ጎንደሮች ያለባቸው የመሬት እጥረት ሱዳን ግዛት ውስጥ ድረስ በመግባት ለመፍታት ሞክረው ቆይተዋል፣ ይህ ከትልቁ የውጭ ጎረቤታቸው ከሱዳን ጋር ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ወሳኝ ፍላጎቶች ሊሟሉ የሚችሉት 1/እጅግ ለም፣ ሰፊና፣ በህዝብ ያልተጨናነቁ፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ መሬቶች ያሉት በሰሜን በኩል ምእራብ ትግራይ ተብሎ በተካለለው አራት ወረዳዎች የያዘ በተለየ ትኩረት የወልቃይትና ሁመራ መሬት ነው። ይህ መሬት ለዘመናት የሚኖሩበት ትግርኛ ተናጋሪዎች በመሆናቸው በፌዴሬሽኑ አወቃቀር መሰረት በትግራይ የተካለሉ ናቸው። በርግጥ አለአግባብ በአድልዎና ማናለብኝነት የሃይለስላሴ ዘውዳዊ መንግስት ከትግራይ ተነጥቀው ለጎንደር እንዲሰጡ በመወሰኑ ለተወሰኑ አስርት አመታት ጎንደር ስር ቆይተዋል። 2/ እነዚህ የምእራብ ትግራይ ወረዳዎች ከኤሪትርያ ጋር ድንበር ስለሚጋሩ ጎንደር ለምትመኘው ሰፊ የኤሪትርያ የግብርና ውጤቶች ገበያና ለውጭ ንግድ የምፅዋ በር አመቺ መሸጋገሪያዎች ናቸው። እነዚህ ለጎንደር ሁለት ወሳኝ ጥቅሞች የሚሰጡት የምእራብ ትግራይ ወረዳዎች በትግራይ አስተዳደር ስር በመሆናቸው እንዴት ከትግራይ እጅ ተፈልቅቀው ይውጡ ሆነ የመላ ጎንደር የቀን ቅዠትና የሌሊት ህልም።  በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻቸውን አልነበሩም። ኤሪትርያም ተመሳሳይ አመለካከት እያስተናገደች ነበር።

ኢትዮጵያን ያመሰውና ትግራይን ጥፋት አፋፍ ያደረሰው፣ የአማራና የመላ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው የተባለው ምስቅልቅል የተፈጠረው የጎንደርና የኤሪትርያ የጋራ ጥቅማቸውን መሰረት ያደረገ ሴራ ነው። እዚህ ላይ ሊሰመርበትስ የሚገባው ጉዳይ ኢሳያስ የኤሪትርያን ወጣቶች ትግራይ አስገብቶ ግፍና ዘረፋ ላይ እንዲሰማሩ ያደረገው የግል የበቀል ስሜቱን ለመወጣት ብቻ ሳይሆን በመድፍ ድጋፍ የአማራ ምሊሻን ምእራብ ትግራይን እንዲወር ከማድረግ ጋር ለዚሁ አላማ ትግራይን አድቅቆ በጎንደር በኩል የሰሜን ምእራብን ገበያ የሚያገኝበትን ዘላቂ ዋስትና ለማረጋገጥ ነው። ከጅምሩ ኢሳያስና ቡድኑ ለኤሪትርያ ሁለት አማራጭ ነበራቸው። አንደኛው፣ የነፃነት ትግሉን እንደመደራደሪያ በመጠቀም ኤሪትርያ በኢትዮጵያ ላይ የወሳኝነት ሚና በመያዝ ውህደት እንዲፈፀም ሲሆን፣ ሁለተኛው ግን ነፃ ኤሪትርያ  ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ቅኝ ግዛት በማድረግ የጥሬ እቃ አቅራቢና የኢንዱስትሪ ውጤት ተቀባይ ልታደርጋት ነበር የተወጠነው። ሁለቱም ውጥኖች የከሸፉት በትግራይ ነው የሚል እምነትና ቁጭት በኤሪትርያና በኢትዮጵያ ውስጥ ነበረ፣ አለም። ህወሓትን ከስልጣን ያገለለው ለውጥ ኤሪትርያ የተሳተፈችበት ትግራይን አድቅቆ የከሸፈውን እቅድ ለመተግበር ነው። ይህ ከሰላም ጋር ያልተገናኘውና ምእራቡን አለም የሸወደው ሴራ በኢትዮ-ኤሪትርያ ሰላም ስም የኖቤል ሽልማት እስከማሰጠት ደረሰ። በለውጡ የምእራባውያን ፍላጎትና ግፊትም ተጨምሮበት ስለነበር ነገሩ ሰላም ሳይሆን ነገር መሆኑ የገባት ትግራይ ውጥረት ውስጥ ገባች። ኤሪትርያ ላሰበችው የኢኮኖሚ ቅኝ ገዢነት አላማ በር ወለል ብሎ የተከፈተላት በጎንደር በኩል ነበር። በአፋር ሊሆን አይችልም፣ በትግራይ ሊሆን አይችልም! ቀሪው አዋሳኝ ከትግራይ ተቀምቶ ለጎንደር መሰጠት ያለበት ብቸኛ የወልቃይት ሁመራ ኮሪደር ነው። እዚህ ላይ የሁለቱም ፍላጎት ተገጠጥሟል። ጎንደርና ኤሪትርያ ከአንድ ውሃ ተቀድተዋል፣ ሁለቱም  ሊከብሩ ወስነዋል! የሚከብሩት ግን የህዝብ የመኖር መብት ጨፍልቀው ነው። እዚህ ላይ ጥቅም ብቻ ነው። ጎንደር ኤሪትርያን ምንም ለጥቅም ብትፈልጋት ባእድ አገር መሆንዋን ታውቃለች። ጎንደር ትግራይን ምን ያህል ጥቅሟ ላይ የተጋረጠች እንቅፋት ብትሆን ባእድ ሳትሆን የኢትዮጵያ ክልል መሆኗን ታውቃለች። በህገ መንግስቱ ብቻ ሳይሆን በሞራል ደንቦችም መሰረት ከባእድ ጋር አብሮ የራስን ወገን መምታት አይቻልም፣ አይገባምም። ይህ አይነት አገራዊነት ለጎንደር ምኗም አልሆነ፣ ሳሩን እየተከተለች የአገር ክህደትት ገደል ትገባለች እንጂ።

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ጎንደሮች አፄ የሃንስ ለኛ ብለው (ለሃይማኖት ብለው እያሉ ነው የሚያረክሷቸው) እዚች ተሰዉ ሳይሆን ያሉት ኢሳያስን ጋብዘው አያትህ እዚህ ነው የተቀበሩት ብለው ጭራ መቁላቱን ነው የመረጡት። ጎንደሮች የፈለጉት ካቅማቸው በላይ የሆነውን ምእራብ ትግራይን የመውረር አላማ እንዲያሳካላቸውና ለዘለቄታውም ትግራይን አጥፍቶ ዋስትና እንዲያስገኝላቸው መለማመጣቸው ነበር። ኢሳያስ ግን ምንም እንኳን ይህ ትግራይን የማስወረርና የማጥፋት ጉዳይ በዋናነት የሱ ፍላጎት ቢሆንም እየተግደረደረ እንደ አዳኝ መሲህ መቆጠርን አትርፎበት ነበር። ኢትዮጵያ ላይ ለመንገስ ህወሓት ስላልተባበረችው ጭልጥ ብሎ ወደ ጎንደሮች ጉያ የገባው አቢይ የኢሳያስ አምላኪና ታዛዥ አድርገውት መስመሩን ስቶ ወዳልሆነ አዘቅት ገባ። ህወሓት በመከረችው ቀና መስመር ቢጓዝ ኖሮ የጎንደሮች የቢዝነስ ጂኦፓለቲካ ረግረግ ውስጥ ገብቶ አይዋጥም ነበር። የትግራይ መከላከያ ስራዊት ደባርቅ በር ላይ ባለበት ሁኔታም አገኘሁ ተሻገር የጎንደር ቢዝነስ ጂኦፓለቲካ ተስፋውን አንገቱ ላይ እንዳንጠለጠለ ነው። አሁንም የወልቃይት እግር መዘርጊያና ከኤሪትርያ ጋር መገናኛ እውን ይሆናል የሚል ተስፋ ሰንቋል። የኤሪትርያን ድጋፍ አሁንም እንደ ወሳኝ ግብአት እየቆጠረ ነው። አሁንም ለኤሪትርያ እግር ኳስ ቡድን አባላት ባህር ዳር (ጎጃም) ሆኖ የጎንደሬ ባህል ጃኖ አልብሶ፣ አስመራ ሲገቡ እሱን ለብሰው እንዲገቡ ተማፅኖ አስጨበጨባቸው። የጎንደር ባህል ልብስ አማራን ይወክላል ብሎ መሆኑ ነው። የአስመራ ህዝብ ሲቀበላቸው የኢትዮጵያ ባህል ልብስ ለብሰው መጡ ተብሎ ይታሰባል። ለኢሳያስም ስጦታ በእግር ኳስ ቡድኑ በኩል እንዲሰጠው በጭብጨባ ተሰጥቷል። ቁልምጫውና ማጎብደዱ ጥቅም የለውም። ኢሳያስ ከነጭፍራው ራሱን የማዳን እንጂ በጎንደር የተወረረ ግዛትን የመጠበቅ ስራ ሊሰራ አይችልም። ለትዝብቱ ግን አገኘሁ ተሻገር ለስፓርተኞቹ የነገራቸው ነገር በአማራ ጉዳይነት በኢትዮጵያ ጉዳይነት በወልቃይትና ሁመራ ህዝብ መብት ሲመኻኝ የቆየው የመሬት ወረራ እውነታውን የሚገልፅ ነው። በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ ለስፓርተኞች የሚነገር አልነበረም። መጨነቅ መጠበብ ምስጢርህን ለድመትህ ለመናገር ሳይገፋፋ ይቀራል?

እንደ አገኘሁ ተሻገር አገላለፅ:- "እኛ የእርሻ ሰብል ውጤቶች አሉን፣ ኤሪትርያ የኢንዱስትሪ ውጤቶች አሏት ይህን መለዋወጥ እንችላለን፣ ለዚህ መልካም ግንኙነት እንቅፋት የሆነችን ትግራይ ናት" የኢንዱስትሪ እቃ ተቀባይና የግብርና ውጤት አቅራቢ መሆን የቅኝ ተገዢነት የኢኮኖሚ ግንኙነት ነው። ጎንደሮች ኤሪትርያ ቅኝ እንድትገዛቸው ይለምናሉ፣ ገፀ በረከት ይሰጣሉ። ራሳቸው የኢንዱስትሪ ምርት አምርቶ እንደመወዳደር ኤሪትርያ የኢንዱስትሪ ምርት አምርቺልን እኛ ገበሬዎች ሆነን እንቅር ይላሉ። ብዙ አገር ቅኝ ተገዝቶ የኖረው በንደዚህ አይነት ሆዳም ባንዶች አማካይነት ነው። ጎንደሮች አርበኞች ነን እያሉ ያቅራራሉ፣ ግን ቅኝ አገዛዝን በልመና ይቀበላሉ። ቅኝ አገዛዝን ከመለመን ከትግራይ የኢንዱስትሪ ውጤት ከዶላር ይልቅ በብር መግዛት አይቀልም ነበር? ከባእድ ጋር ሆኖ የትግራይ የሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪን በቅናት ስሜት ከማውደም? አገኘሁ ተሻገር የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ ከሚሰይልና ጄት በላይ ለድል ጠቃሚ ናቸው። ይህ በወልቃይት በኩል በጎንደርና በኤሪትርያ መካከል የሚደረግ ንግድና እንቅፋት የምትፈጥረው ትግራይ ጉዳይ ነው ከአማራ ጉዳይነት አልፎ የመላ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲሆን "የተሰራበት" ለምን ጎንደርና ኤሪትርያ ወልቃይትና ሁመራን ወረው ንግዳቸውን እንዳያጧጥፉ እንቅፋት ሆንሽ ተብላ ነው ትግራይ በኢትዮጵያ አፍራሽነት የምትከሰሰው። ትግራይ እንቅፋት የሆነችው ኢትዮጵያ ከኤሪትርያ ጋር በተዛባ የንግድ ግንኙነት እንዳትጎዳ በሚል ነበር። ይህ አገርን ማፍረስ ከሆነና የጎንደር የቅኝ ግዙን ጥሪ አገር መውደድ ከሆነ ላለመስማማት እንስማማ እንጂ ሃቅ ይዘን በወንጀለኞች አንወንጀል አለች ትግራይ!

 

Back to Front Page