Back to Front Page

ከጭንቀትና ዋይታ፤ ወደ እረፍትና እፎይታ!

ከጭንቀትና ዋይታ፤ ወደ እረፍትና እፎይታ!

ከ (ዐብይ ኢካቦድ)

07-10-21

ከተበደለና ከተጨፈጨፈ ሕዝብ እፎይታና እረፍት በላይ ለልብ ደስ የሚያሰኝ ነገር ምን ሊኖር ከቶ ይችላል? ይህ ቅን ልብ ላለው ሰው ሁሉ የሚመለከት ነው። እግዚአብሔር ሁሌም ከተበደለና ከተጠቃ፣ ከተዋረደና ከተናቀ፣ ከወደቀና ከሚፍገመገም፣ ከሚያዝንና ከሚጨነቅ፣ ተስፋ ከቆረጠና ከጠወለገ፣ ግራ ከተጋባውና የረዳት ያለህ ብሎ ከሚጠራና ወዮው ጠፋን ብሎ ከሚጮኽ ሚስኪን ጋር ነው። በእነዚህ አስጨናቂ ስምንት ወራት በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰው ግፍና ፍዳ ከሚገባው በላይ ዘግናኝ ነው። ይኼን በዓለም ዙሪያ ያስተገባ የሚስኪን ሕዝብ ጭኾትና ዋይታ፤ በሰማይም በምድርም የተሰማ ከመሆኑ ባሻገር፤ የሚያሳዝነው መራራውና ጎመዛዛው ጽዋ እንዲጎነጭ የተደረገው ሕዝብ ምንም ጥፋት ሳይገኝበት የተፈጸመ መሆኑ ነው።

የትግራይ ሕዝብ እንደ ማንኛውም ሕዝብ በደለኛ ተደርጎ መገደል፤ መንቋሸሽ፤ መሰደድ፤ ፆታዊ አመጽ መፈጸም፤ በጅምላ ዘርን በርሃብ ለማጥፋት ሆን ብሎ እርሻን መከልከል፣ በሬዎችን አርዶ መብላት፣ መፎርና ቀንበርን ሰባብሮ ማቃጠል፣ ከቤቱና ከሞቀ ጓዳው አባሮ ማሳደድ፣ እህሉን ማባከንና በገዛ የጋማ ከብቶቹ ጭኖ መዝረፍ፣ ግራና ቀኛቸውን የማያውቁት ሕጻናት ያለ ረዳትና ተንከባካቢ ወላጆች ማስቀረት፣ የሚደርስበት አረሜናዊ በደል የውጭው ዓለም ስምቶ ለእርዳታ እንዳይደረስ የመገናኛ ብዙሃንን ጥርቅም አድርጎ ለወራቶች መዝጋት፤ የባንክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የነዳጅ፣ የስልክና የመጓጓዣ አገልግሎቶች እንዳያገኝ ሆን ብሎና አቅዶ ማቋረጥ ፈጽሞ ሰብአዊነት የጎደለው ነው። በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰው ዘግናኝና ሊሸከሙት የማይችሉት በደልና ፍዳ፤ ከበደሎች ሁሉ የከፋ በደል ነው ብሎ መናገር ማጋነን አይደለም።

የጥቃት አድራሾቹ ጉባኤ ወይም ማሕበር ይሄን መራራ ፅዋ ለመጠንሰስ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰዳቸው ሲሆን፤ በርካታ የተለያዩ የውስጥና የውጭ የክፋት ባለ ድርሻዎች የትግራይን ሕዝብ ላንዴና ለመጨረሻ ከምድር ገጽ ለማጥፋት በቅንጅት የሸረቡት ሴራ ነው። በዚህ እኩይ ተግባር ላይ ግንባር ቀደም ተዋናያኑ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ተስፋፊ ሊሕቃን፣ የሶማሊያ መንግሥትና ዘመናዊ ድሮንን በማበርከት የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግሥት ናቸው።

እነዚህ የጥፋትና የበደል ማሕበር፤ ጥቃቱን ለመፈጸም እንደ ሰበብ የተጠቀሙበት “የሰሜን ዕዝ ላይ የተወሰደው ጥቃት ለመበቀል” የሚል ሲሆን፤ “ሕግና ስርዓትን ማስከበር” በሚል የማጨበርበሪያ የሕግ ቃል ስም አሽሞንሙነውና አሳምረው አቅርበውታል። ፈዴራላዊት ተብያዋ ኢትዮጵያ ከሕገ-መንግሥቱ በሚጻረር ፈዴሬት አድርጋ ባቀፈቻት በገዛ አካሏ በሆነችው በትግራይ ላይ፤ ከበላንጣው ጭራቁና ነፍሰ በላው ወዲ ኣፈውረቂ ጋር ከሁለት ዓመታት በላይ መክራና ዘክራ፣ ከተሰፋፊዎቹና ከትምክህተኞቹ የአማራ ሊሕቃን አውጥታና አውርዳ፣ ከ UAE ዘመናዊ ድሮኖች ተበድራ፤ በሁሉም ግንባሮች ምንም ጥፋት ባልተገኘበት በትግራይ ሕዝብ ላይ ድንገት በአየርና በምድር ጭፍጨፋውን ተያያዘችው። ይህ ይጭካኔ ትርዒት ለ8 ወራት የዘለቀ ሲሆን፤ የጦርኖቱ ግብም ከተቻለ የትግራይን ሕዝብ ከነካቴው ከምድር ገጽ ማጥፋት፤ ያለበለዚያም በጦርነት አድቅቆና በጤኔ ጉልበቱንና ክንዱን አብረክርኮ ተገዥ ለማድረግ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ትግራይን አድክሞና አላሽቆ የመግዛት ዓለማ፤ በምንሊክ፣ በሃይለስላሴና በመንግሥቱ ቤተ-ምኮራ ተፈትኖ የወደቀ ቢሆንም፤ ዐብይ አሕመድ ላንዴና ለመጨረሻ ግብረ-አበሮችን አሰባስቦ ዓላማየ በእርግጠኝነት ግቡን ይመታል ብሎ ጦርነት ቢያውጅና ቢከፍትም፤ ከሌሎቹ በጣም ባጠረ ጊዜ በርካታ ጦሮቹ ፍርክስክሳቸው ወጥቶ በገዛ ዓይኖቻችን ገራሚ ትእይንቶች እያየን ነው።

ዐብይ አሕመድና ግብረ አበሮቹ ተቀባይነትና አግባብነት የሌለው ምርጫ ከማካሄዳቸው ከጥቂት ሳምንታት በፊት፤ አዳዲስ ከባድ የጦር መሣሪያዎች አሰገብተው፤ ድል አናደርጋቸዋለን ብለው በከፈቱት የመጨረሻው የማጥቃት እርምጃ፤ በርካታ ሠራወታቸው በትግራይ መከለከያ ኀይል ተሽመድምዶ አያሌ ወታደሮች ሙትና ሙርኮኛ መሆናቸው ይታወቃል። በዚህ ብርቱ ምት ወገቤ ያሉት ያገሪቱ አምባገነን ጠቅላይ ምንስተር፤ “የትግራይ ገበሬ እንዲያርስ የጽሞና ጊዜ ሰጥተነዋል፤ የተናጣል የቶክስ አቁም አዋጅ አድርገናል” ማለታቸው፤ የሰውየው የመዋሸት የውስጥ አባዜ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ጠቅላይ ምንስትሩ በገሃድ ያሰለፉት ሠራዊት በመሬት ላይ ድል መነሳቱ ዓለም በገሃድ እያየና፤ መስረጀዎቹም በመገናኛ ብዙኅን ተዘርግተውና ተሰራጭተው ሁሉም እየተመለከተው፤ ፊታቸውን በጨው አጥበው፤ ‘መቐለን ለቀን የወጣነው ተሸንፈን ሳይሆን፤ የጽሞና ጊዜ ለመውሰድና ገበሬው እንዲያርስ ነው’ በማለት ምክንያት ማቅረባቸው መዋሸት የውስጥ ባሕሪያቸው መሆኑ ያሳይባቸዋል።

Videos From Around The World

እዚህ ላይ ስለ ውስጥ ማንነትና፤ ሰው መሰጠት የሚችለው በኪሱ ካለው ብቻ እንጂ፤ ከሌለው መሰጠት የማይችል እንደ ሆነ ሊገልጽ የሚችል በአንድ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ልብ-ወለድ መጽሐፍ ለማቅረብ እፈልጋለሁ። በእንግሊዝ ሃገር፤ ሁለት የሚዋደዱ ፍቅረኛሞች ነበሩ። ሴቷ አፍቃሪ ኅይለኛና ቁጡ ስለ ነበረች፤ ሁለቱም ተጣልተው ተለያዩ። እርሷ መኖሪያዋን ወደ ሌላ ከተማ ቀይራ ትኖር ነበርና፤ ለገና በዓል ተጣልታ ለተለየችው የድሮ ወዳጅዋ፤ ምን ስጦታ ልስደድለት ብላ አውጥታና አውርዳ፤ አንድ ሃሳብ በመጣላት መሰረት፤ በፖስታ እበትን ወይም ሰገራን አሽጋ ለገና (Chrismas) ስጦታ ለድሮ ጓደኛዋ “አንተ ይሄንን ትመስላለህ” ብላ ትልክለታለች። እርሱም በጉጉት ፖስታውን ከፍቶ ሲያይ፤ በጣም ተገረመ።  ስሜቱን በትዕግስት ለጉሞና ሁኔታውን ተቋቁሞና ገቶ፤ ግድ የለም እኔ በጎ ነገር መላክ አለብኝ ብሎ ወሰነና፤ አበባ በፖስታ ውስጥ አሽጎ “ሰው መሰጠት የሚችለው ካለው ከዚያችው ነው” ብሎ ልኮላታል።

በኪሱ 20 ብር ያለው ሰው 21 ብር ከቶውኑ መስጠት አይችልም። በልቦናው ወይም በውስጡ ደግነት ታጭቆ ያለበት ሰው፤ ለሰው የሚሰጠው ደግነት ነው። በውስጡ ክፋትና ጭካኔ እንዲሁም ውሸትና ማደነጋገር የሞላው ሰውም ለሌላው መሰጠት የሚችለው ይኼው ነው። ከውሸተኛ ሰው እውነት አይጠበቅም፤ በውስጥ ነግሦ ያለ ውሸት ነውና። የዐቢይ አሕመድ ባሕሪም በውስጥ ባስቀመጠውና ባለው ነገር የሚወሰንና የሚንጸባረቅ ነው። በእርግጥ ሰው መሰጠት የሚችለው በውስጡ ካለው ብቻ እንጂ፤ በኪሱ ውስጥ ከሌለውማ እንዴት መሰጠት ይችላል?

የኢትዮጲያ መንግሥት መዋቅሮች በውሸት የተገነቡ መሆናቸው እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለምን ጉድ ያሰኘ ሆኗል። በትግርኛ “ሕማምያ ጎሮቤትስ ተሓላላፊ” የሚል ምሣሌ አለ። ይኼም ወደ አማርኛ ሲተረጎም “በጎሮቤት ያለ በሽታ ይተላለፋል” እንደ ማለት ነው። ባንዱ ሰው ውስጥ ይሰተዋል የነበረ የመዋሸት በሽታ እንደ ሰደድ እሳት በሚገርም ፍጥነት በመዋቅር ተላልፎ የመስሪያ ደንብና መመሪያ ሆኖ ብግልጽ ማየቱ ልብን የሚያቀልጥ ነው።

ቀጥለን ፊታችንን ወደ ሕያው ቃሉ መለስ እናደርጋለን። በ (2 ጢሞትዮስ 3፡16-17) ላይ ሐዋሪያው ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስን አስመልክቶ እንደሚከተለው ጽፏል፦

“ቅዱሳት መጸሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሄር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”

ከዚህ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ቱምቢ/ውኅ-ልክና የሕይወት መመሪያ እንደ ሆነ በሌላ ስፍራ ተጽፏል። በዚህ መሰረትም ውሸትና ነፍስ ገዳይነት የምን ባሕሪ መገለጫዎች እንደ ሆኑ  ከሕያው ቃሉ በጨረፍታ እናያለን። ከልጅነት አኳያ ማንም ሰው አንድም የእግዚአብሔር ልጅ አለያም የዲያብሎስ ልጅ መሆን እንጂ ግራጫ የሆነ ሦሰተኛ ልጅነት ሊኖር አይችልም። ከእግዚአብሔር መወለድ ወይም የእግዚአብሔር ልጅ ስለ መሆን ወይም ስለ ዳግም ልደት የሚያወሱ አያሌ ቁጥሮችና ምዕራፎች  በመጽፍ ቅዱስ የቀረቡ ሲሆኑ፤ ከዚህ በተቃራኒው የዲያብሎስ ልጅ መሆንን የሚጠቅሱ በርካታ ቁጥሮችም ተጠቅሷል። ከማን እንደ ተወለዱ የሚለየው ልጁቹ የማን ባሕሪ እንደሚንጸባርቅባቸው በማየት ነው።

በዮሐንስ ምዕራፍ 8 ላይ ጌታ ኢየሱስና አይሁድ ስለ ልጅነት አስመልክተው ሲነታረኩ እናነባለን። በቁጥር 48 ላይ አይሁዶቹ ኢየሱስን “አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል ማለታችን ትክክል አይደለምን?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እኔስ አባቴን አከብረዋለሁ እንጂ ጋኔን አላደረብኝም፤ እናንተ ግን ታዋሩድኝላችሁ (ቁጥር 49)። ኢየሱስ በእነርሱ ውስጥ ያድሩ የነበሩት አጋንንትን በቃሉ ገስፆ ያስወጣላቸውና ያባርርላቸው እንደ ነበር እነርሱ የሚዘነጉት አይደለም። ከብዙ ደዌና ሕመም ይፈውሳቸውና ዙሪያውን ከበው ፈውስንና አድነን እያሉ ይዞሩ እንደ ነበሩና አርነት እንዳወጣቸውም አይረሱትም። ዳሩ ግን እውነቱን ክዶ የተገላቢጦሹ መናገር ከአባታቸው ከዲያብሎስ የወረሱት ነውና፤ ውሸት ሲለጡፍበት ይስተዋላሉ። በቁጥር 49 ላይ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነና አባቱን እንደሚያከብር፤ ነገር ግን አባቱን የሚያከብረው ወልድን በግልጽ በክፉ አንደበት እንደሚያዋርዱት ይናገራል።

በመቀጠልም የአብርሃም ልጆች ነን ብለው የሚመኩት አይሁዶች፤ ኢየሱስ ስለ አብርሃም አንስቶ ሲያብራራላቸው “አንተ ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን፤ እርሱ ሞተ፤ ነቢያቱም እንዲሁ፤ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?” አሉት ቁጥር 53። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ፤ አየም ሐሴትንም አደረገ” ቁጥር 55። አብርሃም ከእርሱ አንድ ብቸኛ ዘር፤ ማለትም በይስሐቅ በኩል ክርስቶስ ተወልዶ ድንቁን የመለኮት የማዳን ሥራ እንደሚፈጸም በሕይወት እያለ ተስፋ ተሰጥቶት ያንን ተፈጽሞ አይቶ ደስ ተሰኝቷል። የአይሁዶቹ ግብረ መልስ “ገና አምሳ ዓመት ያልሞላህ አንተ አብርሃምን አይተሃል! አሉት ቁጥር 57። ኢየሱስም “እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም  ከመወለዱ በፊት እኔ ነኝ” አላቸው። እዚህ ላይ በጥንቃቄ የሚያነብ ሰው ስዋስዉ (The grammer) በትክክል የተጻፈ አይመስልም። መባል የነበረበት “አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” ነው። ዳሩ ግን እንደ ሰው በጊዜና በቦታ ሰጥን የማይወሰነው ኢየሱስ ከሥላሴ አንዱ የሆነ፤ ለዘመኑ ጊዜ፤ ወራቶችና ዓመታት የማይወስኑት አልፋና ኦሜጋ ነው። ከጊዜና ከቦታ ሳጥን ውጭ የሚኖርና ከፈለገም ወደዚህ ሳጥን መግባት የሚችል አምላክ ነው። በእርሱ ዘንድ፤ አምና፤ ታች አምና፤ ትናንት፤ ዛሬና ለወደፊቱ የሚሆኑት ሁሉም ዛሬ ናቸውና “አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ አለሁ” ማለቱ ትክክል ነው።

ወደ ኋላ ትንሽ መለስ ብለን በክርስቶስና በአይሁዶቹ መካከል የነበረው ስድብ አዘል ክርክር ስናይ፤ በቁጥር 36-38 ላይ አይሁዶቹን “እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፤ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ። የአብርሃም ልጆች መሆናችሁን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌን ስለማትቀበሉ ልትገድሉኝ ተነሥታችኋል። እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋለችሁ” ይላቸዋል። ከኅጢያት ባርነት አርነት የሚያወጣ ኢየሱስ ብቻ ነው። በ(ማቴ 1፡21) ላይ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኅጢያታቸው ያድናቸዋልና በማለት መልአኩ በሕልም ለዮሴፍ ተናግሮታል። እነርሱ ግን በሥጋ ከአብርሃም ስለ ተወለዱ ባሪያ አይደለንም ብለው ይመኩ ነበር። ዳሩ ግን ከሁሉም የባርነት ቀንበር የከበደውና የከፋው የኅጢአት ባርነት ሲሆን፤ ከዚህ ቀንበር አርነት የሚያወጣው ኢየሱስ ብቻ ነው።

ምንም እንኳ የአብርሃም ልጆች ነን ብለው ቢመኩም፤ የዲያብሎስ ልጆች ናቸውና እንደ አባታቸው እውነትን ሲናገራቸው ሊገድሉት ተነሣስቷል። እዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊታይ የሚገባው በ (ዮሐ 8፡44) ጌታ ኢየሱስ ስለ አይሁዶቹ የዲያብሎስ ልጅነት አሰረግጦ የተናገረው ነው።

“እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍስ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፤ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፤ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው”

ነፍስ ገዳይነትና ውሸት የዲያብሎስ ዋና መገለጫ ባሕሪያት ናቸው፤ እነዚህን እንደ የሕይወት ስልት አድርገው የሚገለገሉባቸውና የሚለማመዱ ሁሉ የዲያብሎስ ልጆች እንደ ሆኑ ያሳያሉ። እናማ ዐብይ አሕመድን በዚህ ቁጥር ሚዛን ላይ አስቀምጦና በዚህ መነጽር ስር አድርጎ ሳይሳቀቁና ሳይጨነቁ የማን ልጅ እንደ ሆነ መናገር ይቻላልን? ለሚለው ጥያቄ፤ ዐብይ ነፍስ ገዳይና ውሸታም ነውን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ግድ የሚል ነው። ጥያቄው በአግባቡ ለመመለስ በትግራይ የታየው አስጨናቂ የግፍና ፍዳ ትዕይንት ማቅረብ በቂ ነው። በትግራይ አያሌ ንጹሐን ተጋሩ በእርሱ ትዕዛዝ በመደዳ ተገድለዋል፣ ወጣቶች በጥይት ተገደለው ወደ ገደል ተጥሏል፣ ሰዎች በሰው ሰራሽ ርሃብ እንዲሞቱ ተደርጓል፣ ሕዝቡ በርሃብ እንዲሞትም ሆን ተብሎ የምግብ እርዳታ እንዳይደርስ ከልክሏል፣ የገበሬዎች ማሳ እንዲቃጠል፣ እርሻ እንዳይታረስ ከልክለዋል፣ ትንሿ በሻሻ ወደ ውቢቱ የሰሜንቱ ከተማ ወደ መቐለ ከማሳደግ ይልቅ፤ መቐለን ወደ በሻሻ ዝቅ አድርገናታል በማለት በገዛ አንደበቱ አፍረሻና አጥፊ መሆኑ ተናግሯል። በዚህ ድርጊቱ አንድም ሰው ዐብይ አሕመድ አጥፊና ነብስ ገዳይ አይደለም በማለት ተቃውሞ ማቅርብ የሚችል አይመስለኝም።

ሁለተኛው ዐብይ ወሸተኛ ነው ወይ? የሚል ሲሆን፤ መልሱ አጠያያቂ አይደለም። ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ለዓለም በገፍ ኤክስፖርት የምታደርገው ምርት ውሸትና ውሸት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ውሸት መዋቅራዊ ሆኖ የሚሰራበት ሲሆን፤ ዓለም በኢትዮጵያ መንግሥት ተደራራቢ ውሸት እየተደመመች ናት።

ከእግዚአብሔር ወይም ከዲያብሎስ መወለድ፤ ከተወለዱ በኋላ ለሚኖሩ ተቃራኒ ባሕሪያት ውሳኝ ሲሆን፤ ሰው ከእግዚአብሔር ወይም ከዲያብሎስ የተወለደ መሆኑ የሚታወቀውም በዋናኝነት በነፍሰ ገዳይነትና በውሸት ነው። ይህን ከመቋጨታችን በፊት አይሁድ ጌታን ትውልዱን አስመልከተው እንዴት እንደሚሰድቡት ማየት ያስፈልጋል። በቁጥር 41 ላይ  እንዲህ ይሉታል፤ “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ አባታችንም አንዱ እግዚአብሔር ነው”። ብፅዕትና ቅድስት ድንግል ማርያም ከእጮኛዋ ከዮሴፍ ሳይሆን ከሌላ አባት በዝሙትና በኅጢአት አርግዛህ የተወለድክ ዲቃላ ነህ ብለው መሳደባቸው ነው።

ነፍሰ ገዳይነትና ውሸት ዋናዎቹ የዲያብሎስ ልጅነት መለያ (Acid Tests) መሆናቸው በሕያው ቃሉ በማያሻማ መልኩ ተጽፎ እያዩ፤ አንዳንድ የክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ነን ባዮች፤ በምስባክ ፍላጎታቸውንና አምሮቶቻቸውን የሚሰብኩ ግብዝ ሰባኪዎች ዐብይ አሕመድ በዚህ መነፅር በግልጽ ሁለቱ የዲያብሎስ ልጅነት የሚጦቁሙ ባሕሪያት እያዩበት፤ “በጌታ እንደ ሙሴ ቀይ ባህርን የሚያሻግረንና ወደ ከፍታው የሚያወጣን የእግዚአብሔር ነብይ ነው” ብለው መናገራቸው የሚገርም ነው። ይሁንና እነርሱ ስለሚሉት ነገር አንድም ከቃሉ አንስተው ሞግተው መርታት አይችሉም። የሚነዱትና የሚመሩት በሕያው ቃሉ ሳይሆን በሚጋልበው በራሳቸው ስሜትና ምኞት ነውና!

ሌላው በበርካታዎቹ አማኞች ዘንድ ዘረኝነትና ብሔረኝነት ኢትዮጵያን የጎዳና ያመሳት መሆኑ በጋራ የሚያወግዙ ሲሆን፤ ከወገን፣ ከዘር፣ ከቋንቋና ከሕዝብ ጌታ ኢየሱስ እንደ ዋጀ በ (ራዕይ 5፡9) መጠቀሱ ይቆረቁራቸዋል። የዓለም ፍጻሜ እስኪሆንና የመጨረሻው ሰው እስኪዋጅ ድረስ ዘር፣ ወገን፣ ቋንቋና ሕዝቦች እንደሚኖሩ በሕያው ቃሉ በግልጽ ተጽፏል። ምንም እንኳ ክፉ ዘረኝነት አደገኛና አላስፈላጊ ቢሆንም፤ ጎጂ ዘረኝነት ለማስወገድ ዘርን ማጥፋት አያስፈልግም። መጥፎ ብሄረተኝነትን ለማክስም ተብሎ፤ ብሄሮችንና ሕዝቦችን ማጥፋትና ማውገዝ ፈጽሞ የተገባ አይደለም።

አንዳንድ አማኞች ራሳቸው በክፉ የዘረኝነት አረንቋ ተዘፍቀው እያሉ፤ ሌላውን ዘረኛ ብለው ማወግዛቸው የሚያሳዝን ነው። እንደ ምሣሌ በፌስ ቡክ (Faca Book) እና በዩ ቲዩብ (You Tube) መልእክት የሚያስተላልፍና በርካታ ተከታታዮች ያሉት በዘሩ አማራ የሆነ ሰው፤ ስለ ዘረኝነት ክፋትና ክርፋት ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ውስብስብ ችግሮች ጋር አቆራኝቶ በድፍረት ያስተምራል። ተከታዩቹ አብዛኛው ጊዜ ‘አሜን!’ የሚሉና እርሱን በደመ-ነፍስ የሚያወድሱና የሚያቆላጳጵሱ እንጂ በሕያው ቃሉ መሰረት ሊማጎቱት የማይሹ ናቸው። ይህ ሰባኪ ከአማራ ወገን ሲሆን፤ የሚወደው የሚያወድሰውን እንጂ፤ ሕያው ቃሉን ተደግፎ የሚሞጉተውን ለማስተናገድ አይሻም።

በቅርብ ጊዜ ስለ ጠባብነትና ስለ ክፉ ብሔረተኝነት ለአንድ ስዓት ተኩል ያክል ያስተማረ ሲሆን፤ በርካታ ትምሕርቱን “አሜን” በሚል ቃል አጀበው ያቀረቡ ብዙ ነበሩ። እኔም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተንደርድሬ ጠባብነትና መጥፎ ዘረኝነት በእርሱ ዘንድ ቁልጭ ብሎ እንደሚታይ ስነግረው፤ ሌሎች እንዳያነቡት መልእክቴን ወዲያዉኑ አጥፍቶብኛል።

ይህ ሰባኪና አስተማሪ ለሙሉው የእግዚአብሔር ቃል ተገዥ ነኝ ባይ ቢሆንም፤ በዚህ ወቅት በትግራይ ሕዝብ ላይ በገዛ መንግሥቱና ክልሉ ስለሚደርሰው ግፍና ፍዳ አንድም ቃል ትንፍሽ ብሎ አያውቅም። እግዚአብሔር አንድም ሰው ሆነ ሕዝብ እንዲበደል የማይፈልግ ብጽድቅ የሚፈርድ አምላክ ነው። እግዚአብሔር ወላጅ ለሌላቸው አባት ነው፤ በትግራይ ከ 60 ሺሕ ቀኝና ግራቸው የማያውቁ ሚስኪን ሕጻናት ያለ ወላጅ እንደ ቀሩ ሰምተዋል፤ ዓለም ሁሉ ያወቀው ስለ ሆነ፤ በጓዳው ስለሚደረገው ግፍና በደል እርሱ ሳይስማ ቀርቶ አይደለም። ስለነዚህ ወላጅ አልባ ሕጻናት አንድም ተናግሮ አያውቅም። እግዚአብሔር ዝሙት በተለይም በአመጻ የሚፈጸመውው የግፍ ፆታዊ ርኩሰት እጅጉን የሚጠየፈው ነው። ከእርሱ ወገንና ብሄር የሆኑ ታጣቂዎች ሴቶችን በመፈራረቅ ያመጻውቸው ሲሆኑ፤ ይህንን የፈጸሙት “የረከሰው ደማችሁ ይቀደስና ይነጻ ዘንድ ነው” በማለት ነው። ስለዚህ አስነዋሪ ድርጊት ለመኮነንና በይፋ ለመገሰጽ አልሞከረም። እንዲህና እንዲያ እያሉ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ አያሌ ዘርፈ ብዙ ግፎችና ፍዳዎች ማቅረብ ቢቻልም፤ ስላ እነዚህ ቅጥ ያጡ ነውሮች ላይናገር ምን ተዳየ ብሎ ከነፍሱ ጋር ተዋውሏል።

የምትጨነቀው፣ የምትጸልየውና የምትማልደው የገዛ ወገንህ ላይ በደል ሲደርስበት ብቻ መርጠህ ነው እንዴ? አዳኙ የጌታ ቃል የሚያስተምረን እንዲሁ ይሆን ወይ? የገዛ ወገንህ ሲበደል መጮኽ፤ ሌላው ወገን ሲጠቃና ሲበደል ጭጭ ማለት የተገባ ነውን? ከዚህ በላይ ክፉ ዘረኝነትና ወገንተኛ መሆን ምን ሊኖር ይችልና? ይህ ስለ ወገኑ ጥቅም ብቻ ግድ የሚለው ሰባኪ፤ ወገኖቹ በሌሎች ወገኖች ላይ የሚያደርሱትን አረሜናዊ ግፍና በደል ለመሸሸግ የሞኮረ ዳተኛና ጠባብ ነው።

ቤተ-ክርስቲያን የክርስቶስ አካል እንደ ሆነች በቃሉ ተገልጿል። እያንዳንዱ ሰውም የአካሉ ብልት ነው። ቤተ-ክርስቲያንን ለማነጽና ወገኖችም እርስ በርስ እንደ ጅማት ይያያዙ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ብልት እርሱ እንደ ወደደና እንደ ፈቀደ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ሰጥቷል። የሥጋ አካል ብልቶች ልዩ ልዩ እንደ ሆኑና አገልግሎታቸው የተለያየ እንደ ሆነ፤ የቤተ ክርስቲያን ብልቶችም እንዲሁ ናቸው። ለምሳሌ ዓይን የሚያየው ለራሱ ብቻ ሳይሆን መላ አካል ይንቀሳቀስ ዘንድ ነው። ዓይን ከታመመ ሕመሙ የሁሉም ብልቶች ነው። በኢትዮጵያ ፈዴሬት ያደርጉት ሕዝቦችም ባንድ ሃገር አካልነት ለጋራ ጥቅምና እድገት፤ በመስማማት፣ በመፈቃቃድ፣ በመቻቻልና በእኩልነት የተመሰረቱ የአንድ አካል ልዩ ልዩ ብልቶች ናቸው። ይኹንና የአካሉ አንድ ብልት የሆነችው ትግራይ፤ የገዛ ራስዋ መንግሥት ሌሎች ነፈስ ገዳይና ጭራቅ መንግስታትን ጋብዞና አስተባብሮ፤ አፈር ድሜ ሲያደርጓትና ታይቶ በማይታወቅ ጭካኔ ሲጨፈጭፏት፤ ሌሎቹ ብልቶች በአካል ላይ የደረሰውን በደል ደገፉ እንጂ ሕመሙ ሲሰማቸው አይታዩም። ሌለው ይቅርና ከትግራይ ውጭ የሚኖሩ ምእመናን፤ የአካል ብልት በሆኑት የትግራይ አማኞች ላይ በሚደርስባቸው ሕመም ደስተኞችና ደጋፊዎች ሆነው መታየቱ “ምን እየተደረገ ነው?” የሚያስብል ነው።

በመጨረሻ የኢትዮጵያዊነት ፋይዳ ከመንፈሳዊ እይታ አኳያ ምን ይሆን? የሚለው ማየት ያስፈልጋል። ሕዝብ ቁም ስቅሉ የሚያይባትና ሲዖል በምድር የሚገለጥባት አገር መንፈሳዊ ግዴታ ተጥሎበት በጭንቀትና በፍርሃት ተውጦ ኢትዮጵያየ! ማለት ይችል ይሆንን? እንዲህ ዓይነቱ ቀንበር በጫንቃው ላይ ጭኖ፤ ወደደክም ጠላህም ኢትዮጵያዊ ነህ የሚል አምላክስ ይኖር ይሆን ወይ? በእርግጠኝነት እኔ የማመልከው አምላክ ይህን ሮሮና ጭንቀት፤ በደልና ፍዳ እየተሰተናገደ፤ ግዴታ ኢትዮጵያዊ ሆነህ ኑር የሚልና ጽድቅን እንደ መጎናጸፊያው መልበሱ አቁሞ እርቃኑ የቀረ ጌታና ንጉሥ ከቶ አይደለም። ይልቅስ ሕያውና ጻድቁ እግዚአብሔር በሰውና በሕዝብ ላይ በደልና ግፍ በሚያደርሱት ላይ በሰዓቱና በጊዜው በአንዱም ወይም በሌላ መንገድ የሚበቀልና የሚቀጣ አምላክ ነው እንጂ።

አንዱ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ መኖርን የሚመርጠው፤ እየተበደለና አሳሩን እያየ በግዴታ የሚኖርባትና የገሃነ የእሳት ባህር ሆና፤ የሚቀጣበት ሃገር ሳትሆን፤ መብቱና ግዴታው የሚከበርለት፤ ሌሎቹን ወገኖቹ አከብሮና በእነርሱም ተከብሮ፤ ወዶና ተወዶ፤ ሃገሩ የምትጠቅመው እንጂ ጥፋት የምታቀርብበትና የምታሰነዳበት ካልሆነች ብቻና ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊነት ሕዝብን በመሳሪያ አፈሙዝ እየገደልከው፤ በብረት ወደ ዘብጢያ እያወረድከው፤ የውርደት ስድብ ሸማ እያከናከብከው፤ በርሃብ እንዲያልቅና እንዲጠፋ እያደረግከው የግድ በሆነ መለኮታዊ ትዕዛዝ ተገደህ የምትኖርበት የስቃይ አገር አይደለም። ሕዝብ ሆነ ግለሰብ በመንፈሳዊው ሆነ በፖለቲካው አሰራርና መርህ፤ እየተበደለና እየተጨፈጨፈ በግድ መኖር አለበት የሚል አስገዳጅ ትዕዛዝ ሊኖር አይችልም።

ኢትዮጵያዊነት በመፈቃቀድ፣ በመቻቻልና በእክልነት የምትኖርበት ከመሆን ይልቅ፤ ግፍና ፍዳ የምትጠግብበትና የምትጎነጭበት ከሆነ ኢትዮጰያዊነት ለምኔ ጃል? የሚያስብል ነው። ኢትዮጵያዊነት ከ60 ሺህ በላይ ግራና ቀኛቸው የማያውቁ ህጻናት ያለ ረዳትና አጋዥ፣ ያለ ወላጅ የሚቀሩበት ከሆነ፤ ኢትዮጵያዊ የመሆኑ ፋይዳው የቱ ጋር ይሆን? የኢትዮጵያን ልዓላዊነት ለማስከበር በሚል ስም፤ በርካታ ንፁሐን ተጋሩ ሴቶች ታይቶና ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ ፆታዊ ጥቃት ሲፈጸምባቸው እያዩ፤ ተጋሩ እንዴት ኢትዮጵያዊ ነን ማለት ይችላሉ? የኢትዮጵያዊነት ክብሩና ፋይዳውስ የቱ ጋር ነው?

በአዲስ አበባና በሌሎች ከትግራይ ውጭ ኢትዮጵያዊያን ነን ብለው የሚኖሩ፤ ተጋሩ ስለ ሆኑ ብቻ ከቤታቸው ተገደው ወደ እስር ሲጋዙ፤ ንብረታቸው ሲዘረፍ፤ ሲንገላቱና ሲሰደቡ፤ እንዴት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለህ የመናገር ግዴታ አለብህ ይባላል? ገበሬዎቹ በርሰታቸውና በጉልታቸው፤ በወላጆቻቸው ማሳ፤ አርሰው ምርት እንዳይሰበስቡ በርሃብና በጠኔ አንጀታችሁ አሮ፤ ጉልበታችሁ ተብረክርኮ ሙቱ ሲባሉ፤ እንዴት ከምር ኢትዮጵያን ሃገሬ ሊሉ ይችላሉ? ከአንድ ሚልዮን ሕዝብ በላይ ሆን ተብሎ (By design) በረሃብ ገደል አፋፍ አስቀምጦ፤ በርሃብ እንዲሞት የተደረገ ሕዝብ፤ ይኼን የሞት ክፉ ድግስ ያዘጋጃችለትን ሃገር፤ እንዴት ሃገሬ ብሎ ይጥራት? ወጣቶቹን በጥይት ግንባራቸው ከቆሉ በኋላ፤ እየፈኮሩ እልም ወዳለ ገደል የሚጣሉበት ክፉ ድራማ እያዩ የኢትዮጵያነት ለዛና ጣዕሙ የቱ ጋር  ይሆን?

ወላጅ ስላጡ ሕጸናት፤ ዘግናኝ ፆታዊ ጥቃት ስለ ተፈጸመባቸው ሴቶች፤ እንዳያርስ ስለ ታገደው ገበሬ፤ በመደዳ ያለ አንዳች ጥፋት ስለ ተገደሉና ስለ ተረሸኑ አያሌ ወገኖች፤ ግድ ሳይለን ሾላ በድፍን “ኢትዮጵያ!” እና “ኢትዮጵያየ!” በማለት በምስባክ ዘወትር ማወጅና መለፈፍ፤ ማሸብሸብና መተንበይ ምን ይሉታል? ኢትዮጵያዊነት ሲዖል በምድር የሚሰለጥነበት ሃገር ከሆነ፤ ኢትዮጵያዊነት ለምን ጥንቅር ብሎ አይቀርም! ኢትዮጵያዊነት በዚህ መልኩ የሚያሰቀጥል መለኮታዊ ግዴታ የሌለ መሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ የሚቻል ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊነት ከፊሉ በስቃይ ባሕር እየተለበለበ የሚኖርባት መንፈሳዊ ኩነኔ እንደ ግዴታ ተደርጎ የታወጀባት ሃገር ተደርጋ መቅረብና መሳል ተገቢ አይደለም።

በመደምደሚያው፤ ለ8 ወራት የትግራይ ሕዝብ ጥቁር የሞት ደመና አጥሎበት፤ የተናቀውና የታዋረደውን ሕዝብ የሚረዳ ቸሩ እግዚአብሄር የተበዳዩ ሕዝብ ቅልጥም አበርትቶ የትግራይ ሕዝብ ከአርያም ደማቅ ብርሃን ስለ በራለት ልዑል አምላክ ስለ አንጸባራቂው ድል ለሚሰገን የተገባው ነው። መራራ መከራን የጠገበው አባት ኢዩብ በአግራሞት፤ “ደካማውን እንዴት ረዳኸው?” እንዳለ፤ በዘመናችንና በትውልዳችን ደካማው፣የተናቀውና የተዋረደውን ሕዝብ ስትረዳው አይተናልና እኛም ከኢዮብ ጋር “ደካማውን እንዴት ረዳኸው?” ብለን፤ ድል እንድንነሣ የረዳኸን አምላክ አንተን እናመሰግንህለን!!! ከጠላቶቻችንና ካባልንጣዎቻችን ተግዳሮት፣ ንክሻና ሴራ ሙሉ በሙሉ አርነት ለመውጣት ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች ስላሉ መትጋት የሚጠበቅብን መሆኑን ተገንዘበን፤ የተበደለውንና የተጠቃውን ሕዝብ ክንድን፤ ጉልበትንና ቁርጭምጭምትን የሚያበረታውንና የሚያጸናውን ታማኙ ልዑል አምላክ ከተበዳዩቹ ከእኛ ጋር ነውና፤ ድል እናደርጋለን። ለዚህም ምስጋናና ውዳሴው ተደምሮና ተቆልሎ ለእርሱ ለጌቶቹ ሁሉ ጌታ ለእግዚአብሔር መቅረብ ይኖርበታል እንጂ በራሳችን ፈጽመን ልንመካ የተገባ አይደለም።

 “እነዚህ በሰረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤ እኛ ግን ትምክህታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው። እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፤ ጸንተንም ቆምን።” (መዝሙር 20፡ 7-8)

 

Back to Front Page