Back to Front Page

የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች ዴፕሎማሲ ማሽቆልቆል

የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች ዴፕሎማሲ ማሽቆልቆል

ከአብይ ኢካቦድ 05-29-21

በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አሁን በመድረስ ላይ ያለው ዓለም አቀፍ ጫና፤ በምድሪቱ በዋናነትም በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰውና በመፈጸም ላይ ያለው እኩይና አረሜናዊ ፍዳና ግፍ ውጤትና ነጸብራቅ እንደ ሆነ ለመረዳት አዳጋች ከቶ አይደለም። የኢትዮጵያ ፈዴራላዊ መንግሥት፤ ፈዴሬት ካደረጉት አሥር ብሔራዊ መንግሥታት አንዱ በሆነው የትግራይ መንግሥት ላይ እንዲህ ዓይነቱ ጭፍን እርምጃ መውስዱ አግባብነት የሌለውና በሥራ ላይ ያለውን ሕገ- መንግሥት የሚጻረር ነው።

የብሔራዊ መንግሥታቱ የቃል ኪዳን ውል ማለትም ሕገ-መንግሥቱ በማያወላዳ መልኩ የሚያስረግጠው፤ የቃል ኪዳኑ መሥራች ብሔሮች መብት እስከ መገንጠል የሚደርስ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት (Self-determination) የሚሰጥ መሆኑ ነው። ይሄ የሕዝቦች መብት በርካታ የብሔሮች መብት ያካተተ ሲሆን፤ አንድ ብሔር ከቃል ኪዳኑ ከተገባው ውል በተቃራኒ በደልና ጥቃት የሚደርስበት ከሆነ፤ በሕዝብ ድምጸ-ውሳኔ (Referendom) መሰረት መገንጠልን የሚፈቅድ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ወቅት የሚተዳደረው በዚህ ሕገ-መንግሥት ስር ስለ ሆነ ተወደደም ተጠላ ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ተቀባይነት ባለው በሌላ ሕገ-መንግሥት እስካልተተካ ድረስ እንዲተገበር ግድ የሚል ነው።

በኢትዮጵያ ምድር እየሆነ ያለው ምስቅቅሉ የወጣ አሰተዳደርና አመራር፤ ባለ ብዙ መልክና ደርዝ ቢሆንና ብዙ ትንታኔዎች ማቅረብ ቢቻልም፤ ዋናው ችግር በዶ/ር ብርሃኑ ነጋና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ እንዲሁም በክርስትና እምነት ደንደስ፤ አሉታዊ ተጽእኖ በማድረስ ላይ በፖሊቲካው ኮሮቻ ተቆናጦ ያለው የክርስቶስ ኢያሱስ እውነተኛና ቅን ዲያቆን ባልሆነው በመሰሪው በዳንኤል ክብረት የሚዘወረውና የሚናዳው የዶ/ር አብይ አሕመድ መንግሥት ነው። እኚህ ሰዎች ኢትዮጵያ የአንድ ሕዝብ አገር ማለትም ብሔር እንጂ ሕዝቦች እንዳይደለች፤ በሃገሪቱ መሪ አፍ ስልቅጠው በይፋ እንዲናገሩና እንዲያውጁ ተደርጎ ሰምተናል። ይህ ሊለወጥና ሊሻር የሚችለው ሕገ መንግሥቱ አግባብነትና ተቀባይነት ባለው በሌላ ሕገ መንግሥት ከተተካና፤ ሕዝቦች ወይም ብሔሮች የሚለው ቃልና ጽንሰ-ሃሳብ አላስፈላጊ እንዳልሆነ እስከታመነበት ድረስ ብቻና ብቻ ነው።

በወቅቱ በኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ተደረጉ የዴፕሎማሲ ግድፈቶችና ሕጸጾች ዞር ስንል፤ በቅድሚያ የምንመለከተው በሃገሪቱ ውስጥ የተነገሩ ኢዴፕሎማስያዊ፤ በጥባጭና አዋኪ አያሌ ንግግሮች ናቸው። የአንድ አገር መሪ አስተዳድረዋለሁ በሚለው በአንድ ሕዝብ ላይ፤ “የቀኝ ጅብ” ብሎ ታርጋ መለጠፍና፤ የሕዝቡን አንገት ለማስደፋት የተደረገ አፍራሽ የለበጣ ንግግር ከዴፕለሚያሲያዊ ንግግር አንጻር አግባብነት የሌለው ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላዩ ወያኔን ለመበቀልና ስሙን ለማጥፋት፤ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በጋራ የተፈጸሙትን ጥፋቶችና ግድፈቶች በሙሉ በእርሱ ላይ በመጫንና በማላከክ እንደ ዲያብሎስ አድርገው ስለው ከማቅረባቸው ባሻገር፤ ዓለም ያደነቀውና የመሰከረው በኤኮኖሚው ዘርፍ የተደረገው እድገትና እመርታ አጣጥለውና አኮስምነው “ለ27 ዓመታት በጨለማ ስር ነበርን” የሚለው ትልቅ ሃቀኘነትና ዲፕሎሚያሳዊነት የጎደለው ንግግራቸው ነው። የሰሜኑን ሕዝቦች አስመልክተው የኦሮሞዎቹን ጊዚያዊ ቀልብና ስሜት ለመሸመትና ለመቆጣጠር ለባሌ ሕዝብ ያደረጉት ተገቢ ያልሆነ ተንኳሽ ንግግር የዴፕሎማሲ ግድፈት ያለው መሆኑ ታሪክ ሊፋቅ በማይችለው ደማቅ ቀለሙ ዘግቦታል፤ ከትቦትማል።

Videos From Around The World

በሕዝብ ዘንድ አድናቆትና ክብር ለመቀዳጃት ከሚደረግ ስሜት ቀያጅና ናዋዥ ንግግራችው፤ በመቐለ ንግግራቸውን ለማዳመጥ ታድሞ ለነበረ ሕዝብ የተናገሩት ከልባቸው ያልፈለቀ ንግግር የሚጠቀስና የሚታወስ ነው። “ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ፤ መኪና ያለ ሞትር የማይታሰብ ነው” በማለት የተናገሩት የትግራይን ሕዝብ ለማማለልና ለራስ ዝናና ክብር ፋይዳና ፉጆታ የተነገረ ግብዝ ንግግር ነው። ግብዝ ማለት ልብ ወይም ወስጥ አንድ ነገር ሆኖ፤ ውጭ ግን ተቃራኒው ሆኖ መገለጥ የሚያሳይ ቃል ነው። “ልቡ ጩቤ፤ አፉ ቅቤ” የተሰኘው ቃል ደህና አድርጎ ይገልጠዋል። ኢየሱስም፤ “እናንተ ግብዝ ፈሪሳዊያዊያን፤ በውስጡ የበሰበሰ ነገር እንደያዘ፤ በውጭ ግን የተቀባ መቃብርን ትመስላላችሁ” በማለት የተናገረውም ግብዝነት ምን እንደ ሆነ ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው።  ጠቅላዩ ይሄን አማላይ ቃልና ቀልብ ቀያጅ ዲስኩር ለትግራይ ሕዝብ በገዛ ከንፈራቸው የተናገሩት፤ ትግራይን ለማጥፋት ቀን ሌሊት ደፋ ቀናና ቁጭ ብድግ ይል ከነበረው ከጭራቁ የኤርትራ አምባገነን መሪ ታላቁን የሚጎመዝዝ የጥፋት ሴራና ጽዋ እያዘጋጁና እያቀናጁ በነበሩበት ወቅት ነው። ይሄ “ግብዝነት” ተብሎ ካልተጠራ ግብዝነት ታድያ ምን ሊሆንና ሊባል ነው? ግብዝነት ሁለት ተቃራኒ ባሕሪያትን ተራ በተራ ሳይሆን ባንድ ወቅት ላይ ማስተናገድ እንደ ሆነ ከላይ ከቀረቡት ሁለት ምሳሌዎች መረዳት ይቻላል።

ጠቅላዩ ትግራይ በኢትዮጵያ ያላት ጠቃሚነትና ድርሻ አስመልክተው “መኪና ያለ ሞተር፤ ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ” በማለት ተናግሯል። መኪና ያለ ሞተር ልትንቀሳቀስ እንደማትችል፤ ያለ ትግራይም ኢትዮጵያ መኖርና መንቀሳቀስ አትችልም ማለታቸው ነው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ወይም መኪና እርሷቸው የሚነድዋት ወይም የሚሸፍሯት መኪና ናት፤ የመኪናዋ ሞተርም የትግራይ ሕዝብ! ታድያ ጠንቃቃ የሚኪነዋ ነጂና ባለቤት መኪናዋ በጤና ትሰራና ትሽከረከር ዘንድ የአካሏ እምብርትና አስኳል የሆነው ሞተርዋን ልዩ እንክብካቤና ጥብቃ ያደርግለታል እንጂ፤ እንዳይኖርና እንዲጠፋ መቀጥቀጥና ማበለሻት የለበትም። በዓለም ውስጥ ሞተሩን አጥፍቶና ከጥቅም ውጭ አድርጎ መኪናየን እንዳለሁ የሚል ሽፌር ታይቶ አይታወቅም።

ዶ/ር አብይ አሕመድ ግን ከውጭ ቂመኛ መንግሥት ጋር ተመካክረው 110 ሚልዮን ተሳፋሪ የያዘች ኢትዮጵያ የተሰኘችው መኪና ሞተርዋን በማጥፋትና ከጥቅም ውጭ በማድረግ ለመንዳት የሚታትሩ ሽፌር ናቸው። (ኦሮሞዎቹ ሰሙ ቶርቶራ ማለትም የበሰበሰ ጭንቅላት” በማለት ባንድ ሰልፍ ላይ እንዳቀረቡት)፤ ያለ ሞትር መንዳት የሚሞክረውን ሽፌር አይተን እኛም “ሰሙ ቶርቶራ” ብንል ማን ሊከሰን ይችላል? የአገሪቱ ሽፌር ዶ/ር አብይ አሕመድ አንድም ምሳሌየ ትክክል አልነበረም ብለው ማስተባበያ ይስጡን፤ አለያም ሞተር ያላትን መኪና ጨፈላልቀን በእግር፤ በብስክሌት፤ በግመልና በበቅሎ መፈጠንኮ ይቻላል ይበሉንና ወደ ድንጋዩ ዘመን ወደ ኋላ ይመልሱን! ከኢሳያስ ድሮስ ምን ምክር ይገኝና!

ሕዝብን ነጥለው “የቀን ጅብ” ብለው የሚያስጠላ ስም ከለጠፉበት ሌላ፤ “ጸጉረ-ልውጥ” ብለው ለመጥራትም አልተጠየፉም። እንዲህና እንዲያ ያሉ አጠራሮችና ቅጽሎች ይቅርና ባንድ መሪ በዴፐሎማሲው አደባባይና መድረክ ሊነገሩ፤ በተራ ሰው እንኳ መነገር የሌላቸው አፍራሽ ትንኮሳዎች ናቸው። የአንድ አገር መሪ የሚናገራቸው ቃላት ከአፉ አምልጠው ከመውጣታቸው በፊት አልሚነታቸውና አፍራሽነታቸው በጥንቃቄ ታይተው፤ ተፈትሽውና ተመዝነው መነገር ይኖርባቸዋል። የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች የሚናገሩት ጥንቃቄ የጎደለው ንግግር፤ አገሪቱን በእጅጉ በዲፕሎማሲ ተዳፋት ቁልቁል እንድትንከባለልና እንድትምዘገዘግ እያደረጋት ነው። በሦስቶቹ ዓመታት የአብይ አሕመድ አገዛዝ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ሆነ ለውጭው ዓለም ያቀረበችው ምርት፤ ከዴፕሎማሲ ደረጃው በእጅጉ የወረደና አሰተዉሎት የጎደለው በአደባባይ የተነገረ፤ በስድብ የተሽሞነሞነ ባዶ ንግግር ነው።

ቃለ እግዚአብሔር አንደበት ወይም የአፍ ቃል መድኃኒት ወይም አጥፊ፤ የሕይወት ዛፍ ወይም ዛፎችን ለማጥፋት የሚጭሩት ክብሪት እንደ ሆነ ይገልጻል። ይሄ ለእያንዳንዱ ሰው የአንደበት ቃል ወይም ንግግር የሚናገር ቢሆንም፤ አብሦ ሕዝቦችን ለሚመሩ በስልጣን ማማ ላይ ተንቋራርጠው ላሉት መሪዎች ሁሉ በእጅጉ የሚመለከት ነው። ዶ/ር አብይ የክርስትና ተከታይ ነኝ ሲሉንና፤ የክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ነኝ ብለው ሲነግሩን ይሄን በግልጽ የተጻፈውን መሠረታዊ የሕያው ቃሉ እውነት እንዴት ሊዘነጉት ቻሉ? በተቃራኒው አጥፊና አፍራሽ የሆነውን አንደበት ለመናገር ለምን ፈለጉ? ክብሪት በተገቢው መንገድ ከተጠቀምንባት ፋይዳዋ ትልቅ መሆኗ ብናውቀም፤ ሚጢጥየዋ ክብሪት ያለ አግባብ ከተጠቀምንባት ታላላቆቹን የአገሪቱ ደኖችና ጫካዎች አቀጣጥላ ማጥፋት እንደምትችል እኮ እኛም እናውቃለን፤ ኣበክረንና አጽንተን እንድናውቅም በመጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ቁልጭ አደርጎ ገልጾልናል።

እናማ አሁን መላ ኢትዮጵያን እያቀጣጠለ ያለው የሰደድ እሳት በትንሿ ክብሪት ያላግባብ በአደባባይ የተነገረ የስንፍና ቃል ሰበብ አይደለም ማለት ይቻል ይሆን? የክርስትና ሁሉም መሰረታዊ አውነቶች ተጨልፈውና ተቀድተው የሚወሰዱት ከሕያው ቃሉ ከሆነ፤ ክቡር መሪያችን በአደባባይ በዘፈቀደ የሚናገሩት አገር የሚጎዳና ከቃሉ ጋር ፊት ለፊት የሚጣረስ (Colliding Head-on) እንደ ሆነ አጥተውት ይሆኑን? መርዘኛና ነዳፊ ቃል ከአፍ ስትወጣ ተጭራ ጫካውን ሁሉ አቀጣጥላ አመድ እንደምታደርገዋ ትንሽየዋ የክብሪት ቅጣይ ትንሽ ስትሆን፤ ከዚያ በኋላ ግን ደኑን፤ ዱሩንና ጫካውን በሰደድ በልታና አውድማ ወደ አመድ የመለወጥ አቅም ያላት ናት።

ከዚህ ጎን ለጎን በጥበብና በጥንቃቄ የሚነገር ቃል ሕይወትን እንዴት እንደሚያድንና ከጥፋት እንዴት እንደሚታደግ ከማርና ከወተት የበለጠ ጠቃሚና ተወዳጅ ከሆነው ከሕያው ቃሉ አንድ ክፍል ማንሳት ያስፈልጋል። በብሉይ ኪዳን ጌዲዮን የተባለ ከቢንያም ወገን የሆነ ሃያልና ጽኑእ ሰው እግዚአብሔር አስነስቶት ነበር። ከአሥራ ሦስቱ የእስራኤል ነገዶች በጣም የተናቀውና ዝቅተኛ የነበረው ይሄው የቢንያም ነገድ ነበር። አንድ ወቅት ላይ በእስራኤል ነገዶች ላይ ፍልስጤሞች ተጠናክረው ድንገት ወደ ግዛታቸው ሲመጡ አንድም ወራሪዎችን የሚመክት ሃይል ጠፋ። ይኼኔ በሁኔታው ግራ የገባው ከተናቀው የቢንያም ነገድ የሆነው ጌዲዮን፤ ታላላቅና ብርቱ ወደ ተባሉት ነገዶች ሄዶ፤ “በምድራችን እየሆነ ያለው ነገር አያያችሁ ነውን? እባካችሁ ሊያጠፉን የመጡትን ባላንጣዎቻችንን ተባብረን እንመክት” ብሎ በትህትና ልመናን ያቀርብላቸዋል። እነርሱ ግን ንቀት ስለ ነበራቸው “አንተ ማን ነህ? ደግሞስ የእስራኤል ዳር ድንበር የሚጠበቀው በእናንተ በቢንያም ነገዶች ነውን?” በማለት አንኳሰሱት።

ገዲዮን ግን ታላቁና ሃያሉ አምላክ ልቡን አበርትቶለትና ደግፎት ስለ ነበረ፤ የራሱ የቢኒያም ነገዶችን መርቶ በሚገርም ሁኔታ ጠላቶቹን ድል ነስቶ ተመለሰ። ዳሩ ግን ድል ነስቶ ከተመለሰ በኋላ፤ ያልጠበቀው ከፍተኛ አደጋ ገጠመው። የይሁዳና ሌሎች ሃያላን ነገዶች ጦራቸውን ሰብቀው እሳት ለብሰውና ጎርሰው “ለምን እኛ ሳንሳትፍበት ብቻህን ሄደህ ድል ነስተህ ትመለሳለህ?” ብለው አፋጠጡት። አንደበቱ በእግዚአብሔር ጥበብ የተሞላው ጌድዮን ከተደገሰበት ሞት የዳነውና ወገኖቹን ቢንያሚያዊያኑን ከጥፋት የታደገው እንዲህ በሚል ገራሚ ቃል ነው። “ወንድሞቻችን ሆይ እኛ የቢንያም ልጆች ታናሽ መሆናችን እናውቃለን፤ በእውን የእኛ አውድማ፤ ከእናንተ ቃርሚያ እንደሚያንስ አታውቁምን?” በማለት ለጥፋት በዝግጅት ላይ የነበረው ጦራቸው ዘቅዝቀው ”እህህ! በል ሁለተኛ እኛን ሳትጠራ ብቻህን እንዳትዋጋ” በማለት ሰንካላ ምክንያታቸውንና የነደደ ቁጣቸው ባንዲት በጥበብ ተከሽና በቀረበች ዓርፍተ-ነገር ጸጥ-ረጭ ማድረግ ችለዋል።

ማንም ሊከለክለውና ሊቸረው የማይችለው መብት የሆነው የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ዘርፍ የሆነውን መሪዎቹን የመምረጥ መብት፤ በሰበብ አስባቡ “የጨረባ ምርጫ” ብሎ በይፋ ማንኳሰስ ዴፕሎማሰዊ የንግግር ዘይቤ የጎደለውና የሦስት ሚልዮን መራጭ ሕዝብ የልብ ትርታ ከቁጥር ውስጥ ያላስገባ ነው። የቃሉ ትርጉም ለማሰስ ወደ መዝገበ ቃላትና ኢንሳይክሎፖዲያ መሄድ አያስፈልግም እንጂ “ጁንታ” በማለት የአገሪቱ መሪዎች የሚጠቀሙበት ቃልም ትክክለኛ ትርጉም ያለው አይደለም። ሌላው መሪው በመደጋገም የተናገሩትና ወደ ራሳቸው ተስፈንጥሮ ጉዳት ያደረሰባቸው ጥንቃቄ የጎደለው ሐሰት ለበስ የለበጣ ንግግር ነው።

ይሄም በግንበር ላይ ያሰማሩት ሠራዊትና ግብራበሩ የጭራቁ የኤርትራ አውሬ ሰራዊት ግብግብ ገጥሞ ያለውን የትግራይ መከላከያ ሰራዊትን በገዛ ራሰቸው አንደበት “ዱቄት አድርገን በትነነዋል!” ብለው መናገራቸው ነው። ዱቄት ማድርጉ በገቢር ተፈጽሞ ከሆነ በጄ፤ ያለበለዚያ በውሽት ቃል በመሬት ላይ ከሚሆነው ትእይንት በተቃራኒ ከሆነ ትንሽ ጭንቅንና ስሜትን ለአፍታ ረገብ ያደርግ እንደ ሆነ እንጂ፤  ቆይቶ ወደ እውነቱና ገሃዱ ዓለም ባነው ሲነቁ ግን ወደ የበሳ የጭንቀት ባሕር የሚያስምጥና የሃፍረትን ካባ የሚያከናንብ ነው። እነዚህ ሁሉ በድምርና በተናጠል በሃገሪቱ ደርሶ ባላው አስጨናቂ ቁልቁል የመንከባለል አደገኛ ክስተት አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳላቸው፤ አሁን ኢትዮጵያዊያን ነን ለሚሉ፤ የነጌ ዕድል ፈንታቸው ግን ያልታወቀው በሚገባ ያውቀት ዘንድ፤ አውቀውም ይሰንዱትና ይዘግቡት ዘንድ የተገባ ነው። የጠቅላዩ ግድፈት የሞላቸው ኢዲፕሎማሳያዊ ከሆኑት ሦስት በአዳባባይ በይፋ የቀረቡ ንግግሮች ቀጥለን እናያለን።

በቅርብ ጊዜ በተወካዮች ምክር ቤት ፊት በትግራይ ስለ ተደፈሩ እንስቶች አስመልክተው የተናገሩትና ጭብጨባ የተቸረበት ንግግራቸው በጣም የሚያሳዝን ነበር። “የትግራይ ሴቶች የተደፈሩት በወንድ ነው፤ የሰሜን ዕዝ የተጨፈጨፈው ግን በመሣሪያ ነው”። በእውን ይሄ ንግግር ከአንድ አገር መሪ ለፓርላማ አባላት ማቅረብ የተገባ ነበርን? አድማጮቹ የሕዝብ ተወካዮችስ ለዚህ ለወረደና ለዘቀጠ ንግግር የቀለጠ ጭብጨባ ማቅረብ ነበራቸውን? የኢትዮጵያ የአሁኖቹ የሕዝብ ተወካዮች ሕዝቡ የመረጣቸው ለማጨብጨብ ብላጫ ያለው የእጅ መዳፍ ያላቸው ሰዎች ይመስል፤ ስለ ወከላቸው ሕዝብ ቁም ነገር ከማውራትና መሞጎት ይልቅ ስርክ ሲያጨበጭቡ ማየት የተለመደ ነው።

የሰሜን ዕዝ በመሣሪያ የመጨፍጨፉ ሃቅነት ጉዳይ ለጊዜው እንተወውና፤ በማንኛውም መስፈረትና መለኪያ በእውነተኛ አሰተዳደርና ሃይማኖት ሴቶች በወንዶች መደፈር ይኖርባቸዋልን? የትግራይ ሴቶች የተደፈሩት እርሰዋቸው ባሰማርዋቸው ሰራዊቶችና አጋሮቻቸቸው ሲሆን፤ ይህም የሰሜን ዕዝ በመሣሪያ ተጨፈጨፈ ካሉት በኋላ መሆኑ የታወቀ ነው። እናማ የሴቶቹ መደፈር ለስሜኑ ዕዝ ጭፍጨፋ ማካካሻ ነው ማለታቸው ይሆን? በሚዛናቸው፤ በተጋሩ ሴት ወገኖቻችን የተፈጸመው ግፍና ነውር የሞላበት እርኩሰት፤ በመሣራያ ተጨፍጨፎአል ከሚሉት የሰሜን ዕዝ ጥቃት ቀሎ ተገኘ ማለታቸውስ አይደለ? ይሄ ይቅርና የኖቤል ሽልማት ከተቀበለ መሪ፤ ከተራ ሰውም የሚጠበቅ አይደለም። በዚህም መሪው፤ በአፍ ሴቶችን እንደሚወዱና እንደሚያከብሩ ይናገሩ እንጂ በገቢር ለሴቶች ያላቸው ክብር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ከዚህ ለመረዳት አዳጋች አይደለም።

ሁለተኛውና በአሉታዊ መልኩ አስቂኝና አሳፋሪ የሆነ ንግግራቸው፤ በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረ የአንበጣ መንጋ ትግራይን ከወሎ የሚለየው ቀጭን ምድር ነጥለው፤ ወሎ የአንበጣ የመከለከያ ኬሚካል እንዲረጭ ፈቅደው ትግራይን እንዲተው በተደረገ አድላዊ ድርጊት፤ አንበጣውን አስመልክተው የተናገሩት ለዝንተ ዓለም ሊረሳ የማይችል ልብን የሚሰብር ንግግራቸው ነው።  አበው “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንዲሉ ከዚህ ምሳሌ በተቃራኒ የመሪው ንግግር “ከድርጊቱ ክፉ አንደበቱ ይከፋል” የሚያሰኝ ነው።

አብይ አሕመድ በዚህ ወቅት በትግራይ ላይ ጦርነት ለማወጅ አፋፍ ላይ ነበሩና  “አንበጦቹም ከእኛ ጋር ተደምሯል” በማለት፤ በመደመር ፍልስፍናቸው አንበጣዎቹን ሳይሆን፤ እነርሱን የሰደደላቸው አምላክ ከእርሷቸው ጋር ተደምረዋል የሚል እግዚአብሔርን የሚያንኳስስ ቃል ጣል አድርጓል። ይህ የሚያሳየው እግዚአብሔር የእርሳቸው ተደማሪ መሆኑና የትግራይ ሕዝብ ደግሞ ተደማሪ ባደረጉት በእግዚአብሔር የተጠላና የተረገመ በመሆኑ አምላካቸው አንበጣው ከእርሷቸው ጋር እንዲሰለፍ እንዳደረገ የሚገልጽ ነው። ለዶ/ር አብይ ታላቁና ሃያሉ ያሕዌ የቆሎ ጓደኛቸው ነው። እርሳቸው በሄዱበት ሁሉ ዝናብ እንዲጥል እንደሚያደርግላቸው እንደ አመላቸው ሲያወሩ፤ በኬኒያው መሪ በእህሩ ኬኒያታ “ማሙሽ” ከሚል ስድብ በተጨማሪ ከቡጢ ጉሽሚያ ለጥቂት ተርፏል።

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በመቅድሙ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ዜጎችና ሕዝቦች መብት ይጠቅሳል። በመሆኑም የሕገ መንግሥቱ የማዕዝን ድንጋይና የጀርባ አጥንት የዜጎችና የሕዝቦች መብት ነው። እነዚህ ባለ ሁለት ዘርፍ መብቶች ከተናዱ ሕገ መንግሥቱ ሕልውና አይኖረውም። ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መብትና አንድነት እናምናለን እያሉ ቆይተው፤ ድንገት “የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሕዝቦች የሚባል የለም፤ ሕዝቦች የሚባለው ለምሳሌ በአፍራካ አገሮች ለሚኖሩ ሰዎች ነው” በማለት በአማርኛና በግዕዝ ብዙ ቁጥሩ ምን እንደሚያመለክት ፈታ ያለ ትንታኔ ሳይሰጡ ለማቅረብ ሞክሯል። በዚህም የሕገ-መንግሥቱ ዋና ምሦሦ በማፍረስ ሕገ መንግሥቱን ለመሻር ዳድቶአቸዋል። ሕዝብ የተሰኘው ቃል በተለያየ መንገድ ሊቀርብ ይችላል። የአዳማ ሕዝብ ከማለት ጀምሮ የኦሮሞ ሕዝብ እስከ ማለት የሚለጠጥ ነው።

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮችና ብሔረ-ሰቦች ያቀፈች ሕብረ-ብሔራዊት አገር ስለ ሆነች፤ መጠራት ያለባት (የኢትዮጵያ ሕዝቦች) ተብላ እንደ ሆነ አጠያያቂ አይደለም። ሕዝቦች ብሎ ለመጥራት በተላያዩ አገሮች ለሚኖሩ የተለያዩ ሰዎች ብቻ ነው ብሎ መቋጨት ስህተት ነው። የአገሬ ሰው “ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታ” እንዲል፤ ዶ/ር አብይ የአመል ነገር ሆኖባቸው እንጂ በአሃዳዊት አገር እናታቸው የነገርዋቸውን ንጉሥ ትሆናለህ የሚል ትንቢት በራሳቸው ፍጻሜ ላይ ለማድረስ ሌት ተቀን የሚታትሩ ከመሆናቸው ባሻገር ይህ እውን የሚሆነውም ኢትዮጵያን አሃዳዊት አድርጎ ጠቅልሎ በመግዛት ነው። የእኝህ መሪ ሁለት ባህሪያት ለያይቶ ለማየት ባያዳግትም ሁሉም ነገር የሚጠነጠነው ለራሳቸው ጥቅምና ፋይዳ፤ ሁሉም ነገር የሚሸከረከረው በራሳቸው ዛቢያ ነው። ይሄም “እርካብና መንበር” በተባለ መጽሐፋቸው ራሳቸው በግልጽ የገለጹት አደገኛ ባሕሪ ነው።

ከዚህ በኋላ የዴፕሎማሲው ሕጸጽና ግድፈት ከአገር ውጭ በዓለም አቀፉ አደባባይ ያደረሰውና እያደረሰው ያለው አሉታዊ ተጽእኖ አንድ ባንድ ለመቃኘት እንሞክራለን። ኢትዮጵያ በውጭው ዴፕሎማሲ ከፍተኛ ወድቀትና ተቀባይነት ያጣችበት አስደንጋጭ ጊዜ ላይ ናት። የውጭው ዓለም ፊቱን ከሃገሪቱ ያዞረበት በቂም ከበቂም ምክንያት አለው። የገዛ የማስተዳድረው ሕዝቤና ምድሬ ነው በምትለው የትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲህ ዓይነቱ አሬሜናዊ ግፍና ፍዳ፤ ከቂመኛና ተበቃይ ጎሮቤት ሃገር ላይ ከሁለት ዓመት በላይ የጦርነት ዝግጅት አድርገህ በገቢር ማዋል በእውን ተገቢ ነውን? 

ከሦስት ሺህ በላይ የሚበልጡ ሕጻናት ወላጆቻቸው እንዲያጡ የተደረጉት ምን ስላጠፉ ነው? እንስት እህቶች በጋለ ብረት ማሕጸናቸው እንዲቃጠል የተደረጉት በየትኛው ጥፋታቸው ነው? ከአንድ ሚልዮን ሕዝብ በላይ እግዚአብሔር እንዲኖር ከቸርው ከትውልድ ወደ ትውልድ አገኘም አጣ ደስ ብሎት ከኖረበት ከርስቱና ከጉልተ፤ ከሞቀ ቤቱና ጓዳው በነቂስ የሚገድሉትን በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ገድሎ የተረፈውን ማሳደድና ማባረር ምን በደል ፈጽሞ ነው? አርሶና አለስልሶ፤ አጭዶና አውድማ አግብቶ፤ ለልጆቹ ሰርግ ደግሦና ወዳጅ ዘምድ ሁሉ ጋብዞ ከኖረበት ምድር ሳንጃ ድንገት ወድሮ፤ ቢላ አስልቶና ገጀራ ስሎ “ልቀቅ ከዚህ ምድር አሁንኑ ውጣ!” ተብሎ በነቂስ እንዲወጣና እንዲሰደድ የተደረገው ምን አበሳ ኖሮትና ተገኝቶበት ከቶ ይሆን?

በድሃ ጉልበቱና አቅሙ፤ ማንም ሳያግዘውና ሳይረዳው፤ ጥርሱን ነክሶና ጉልበቱ ተላልጦ ድኽነትን እቋቋማለህ ብሎ የተከላቸው የመሰረተ-ልማት አውታሮች፤ ፋብሪካዎች፤ የትምሕርትና የጤና ተቋማት እንዳይጠቀምባቸው ወደ ኤርትራ፤ ወደ አዲስ አበባ፤ ወደ ጎንደርና ወደ ጎጅም በጠራራ ፀሐይ በገዛ የራሱ የመጓጓዣ መኪኖቹ አይኑ እያየ መንጠቅና መዝረፍ ምን የሚሉት ቅጣት ነው? “በልዓላዊነትና ሕግ ማሰከበር” ስም በሚፏልለውና በሚፏንነው መንግሥት አሳሩና ፍዳው ቋቅ እስኪለው ድረስ እንዲጎነጭ የተደረገው ትግራዋይ ኢትዮጵያን አገሬ ብሎ እንዴት መጥራት ይችላል? በእንዲህ ዓይነቱ የገሃነ ኑሮ እያኖሩትስ አይደል  ”በምድሪቷ መንፈሳዊት ገነት በኢትዮጵያ” ትኖራለህ የሚሉት? የኢትዮጵያዊነት ፋይዳ እንጦርጦስ ጥግና ወለሉ ድረስ ገድሎ መጣል ነውን? ታድያ እንዲህ ዓይነቱ ግፍና ፍዳ እየተፈጸመበት ትግራዋይ “ኢትዮጵያዊነት ለምኔ?” ብሎ ቢናገር ማንስ ሊኮንነው ይችላል?

እናማ እንዳያዩና እንዳይስሙ ሁሉም ነገር ተዘግቶባቸው የነበሩት በሰብአዊ መብት ላይ የማያመቻምቹትና የማይደራደሩት ታላላቅ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ አገሮች፤ ምስጋና በምድሪቱ ክበብ ሆነው ሌት ተቀን ለሚታገሉት የትግራይ የዳያስፖራ አርበኞች ይድረስና፤ የማንቂያ ደወሉ ድምጽ በርትቶ እነሆ እንዳይሰሙና እንዳያዩ የተፈሩት ሃገራት በምድሪቱ የተፈጸመው ግፍ እንዲስሙትና እንዲያዩት ተደርጓል።

በአገሩቱ የሚደረገው ግፍና ፍዳ በዓይናቸው አይተው ሃዘናቸውና ስብራታቸው የበረታና ዝም ለማለት ከቶ የማይስችላቸው መሆኑ ተገንዝበው በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚደርስው በደል እንዲያቆምና፤ ግፈኛው የኤርትራ ሰራዊትና ተስፋፊው የአማራ ሃይል ያለ ይዋል ይደር ከትግራይ ለቀው እንዲወጡና፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ እንዲደርሰው የማድረግ ሃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት በዴፕሎማሲያዊ መንገድ በውይይት፤ ሁለቴ ከአውሮፓ ሕብረት ልዑክ፤ እንዲሁም ሁለት ጊዜ በአሜሪካ ከፍተኛ ልኡካን ተካሄዷል። በልዓላዊነት አሳብቦ የገዛ ሕዝቤ የምትለውን በጭካኔ ያለ ምሕረት ከሌላ አገር ሆን ብሎ መክሮና ዘክሮ መጨፍጨፍ የተገባ ነውን? ስለ የሰው ልጅ መብት መጣስ ግድ የሚላቸው ብርቱ አገራት “ተው! እንዲህማ ፈጽሞ መደረግ የለበትም” ብልው ሲመክሩና አልፎም ሲያሰጠነቅቁ “በውስጣችንና በልዓላዊነታችን እንድትገቡብን አንፈቅድም” ማለት ሰንካላ ምክንያት ነው።

በጋብቻ ተሳስረው አንድ ሆነው የሚኖሩ ባልና ሚስት፤ ባሏ ዘወትር የሚቀጠቅጣት፤ የሚደበድባትና የሚዘልፋት ከሆነና፤ ዘመድ ጎሮቤቶቿ ይሄ ተገቢ እንዳልሆነና በመጨረሻም ሊገድላት እንደሚችል አውቀው “ተው አትበድላት፤ ዱላውና ንዝንዙም ያቁም” ብለው ቢመክሩትና ቢያሰጠነቅቁት “እናንተ በትዳሬ ላይ ጣልቃ ለምን ትገባላችሁ?” ማለት ይችላልን? እነርሱስ በትዳር መቀጠሉ የከፋ አደጋ ከማስከተሉ በፊት ፊች እንድትጠይቅ አይገፋፋዋትም ወይ? የኢትዮጵያ የፍታብሔርና የወንጀል ሕግስ ፍችን የሚፈቀድ አይደለም ወይ? ሃያላኑ አገራት በፊታቸው አንድ ሕዝብ በተቀነባበረና በተባበረ ክንድ በጥቂት ወራት ከምድር ገጽ እንዲጠፋ ሲደረግ እያዩ ዝም ማለት ይኖርባቸዋልን?

ዶ/ር አብይ ሰመራ ላይ በነበረው የምረቃ ስነ-ስርዓት ለተጋበዘው ሕዝብ የተናገርዋቸው ሁለት ከባድ ሚዛን ስህቶቶች እነሆ። የመጀመሪያው፤ ሕዝብ መበደል የለበትም ብለው ለመከሩትና ለገሰጹት አገሮች ጠቅለል አድርገው “ታሪክ የሌላቸው፤ ከጥንት ጀምሮ ታሪክ ላለን...” በማለት የተናገሩት በግድ የለሽነት የተነገረ ተንኳሽ ንግግር ነው። አዎ! የረዥም ታሪክ ባለቤት መሆን መልካም ነው። ነገር ግን ገናና ታሪክ ይዞ በድህነት ሰልፍ የመጀመሪያ ሆኖ መቆም ፋይዳ የለውም። ታሪክ ብቻውን ሊበላና ሊጣጣ፤ ሊቦካና ሊጋገር አይችልም። ታሪክን ጠብቆ በብልጥግና ቆጥ ላይ መውጣት ተከታይ የሌለው ብቸኛ ምርጫ  ነው። ታድያ ረዥም ታሪክ ኖሯት በብልጽግና ዝቅተኛ ደረጃ ያለች አገር፤ በብልጸግና ከሁሉም በላይ የሆነችውንና ሳትሰስት ችግር በደረሳት ቁጥር የምትረዳውንና ተሎ የምትደርስላትን ወዳጅ አገር አንጋጣ “አንቺ ምን ታሪክ አለሽና?፤ ጫፌን ንክች ታደርጊና ዋ!...!” ብላ ስትጮኽና ስታጓራ መስማት ግራ ያጋባል።

ድሮ አንዱ ጓደኛየ በመጸሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻዎቹ መጀመሪያ፤ የመጀመሪያዎቹ መጨረሻ ይሆናሉ” የሚለው ጥቅስ አንስቶ ምን ማለት እንደ ሆነ ጠይቆኝ ከኔ መልስ ሲያጣ “የመጀመሪያ የነበረቸው መጨረሻ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የመጨረሻ የነበረቸው አሁን ግን የመጀመሪያ የሆነችው አሜሪካ ነች” በማለት የነገረኝ አልረሳውም። ምንም እንኳ ፍችው ትክክል ባይሆንም እዚህ ላይ አርሱ እንዳለው ተቀብለን ለማየት እንሞክር።  በሰልፍ የመጀመሪያ ሆኖ ቆይቶ አሁን የመጨረሻ ከመሆን፤ የመጨረሻ ሆኖ ቆይቶ አሁን የመጀመሪያ መሆኑ በአያሌው የተሻለ ነው።

ሌላው በዚህ ለሕዝብ በአደባባይ የተናገሩት ጸያፍ ቃል፤ እነዚህን ሕዝብን አትበደሉ ብለው ለመከሩና ላሳሰቡ በእውቀትና በጥበብ በሕዝባቸው ተመርጠው ሕዝባቸውን በዴሞክራሲ ለሚመሩት ሃያላን መንግሥታት “እነዚህ ጎልማሶች” በማለት የተናገሩት ግልብ ንግግር ነው። በዴፕሎማሲው ዓለም እንዲህ ዓይነቶቹ  እንደ ጭንቁር የሚዋጉ ቃላት ብዙ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ናቸው። ጎልማሳ ማለት ከዚህ ንግግር አውድ ጥጋበኛ ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ቃል በዴፕሎማሲው መድረክ መጠቀም የራስ የፖለቲካ ብስለት ደረጃ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት ከመሆኑ ባሻገር፤ ለመንግሥት የሚሰጠው ክብርና ትኩረት ዝቅ እንዲል ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው።

“የአባ ዱላ ካፖርት ተሸካሚ ነበሩ” ተብለው ብዙ የተነገረላቸው የኦሮሚያው መሪ አቶ ሽመልስ መገርሳ ደግሞ በአፍ መንሸራተትና ሊጠገን በማይችል በምላስ ወለምታና ስብራት ገናና ናቸው። እኚሁ መሪ ዋና ዓላማቸው አድማጮቻቸውን እንደ ምንም ብለው ማሳቅና ማዝናናት እንጂ የዴፕሎማሲ ንግግር የሚባለው ከናካቴው መኖሩንም የሚያውቁ አይመስሉም። ከሰሞኑ እየጦዘና እየከረረ የመጣው በኢትዮጵያ መሪዎች ላይ አሜሪካ የወሰደችው የቪዛ እገዳ የተናገሩት ገራ-ገር ያልተገረዘ ንግግራቸው ከማየት በፊት፤ በአገር ውስጥ ስለ አማራ ፖለቲከኞች አስመልክተው የተናገሩት ስድ ንግግር ይታወሳል  ፤ ይሄም “አንዳንዶቹን Convince ሌሎቹም confuse አደረግናቸው” በማለት ለሕዝብ በይፋ የተናገሩት በሕዝቦች መካከል ጥላቻን የሚጭር ንግግር ነው።

ከሰሞኑም “የሚቀርብን የነቀዘ ስንዴ ነው!” በማለት አሜሪካን ሲያወግዙ ተደምጧል። የነቀዘ ስንዴ ተቀብሎ ለገዛ ሕዝቡ የሚያቀርበው ከሰጪው የበለጠ ተጠያቂ እንደ ሆነ ሳያጤኑ ነው የሚናገሩት። ስንዴው የነቀዘ ከሆነ ለምን ተቀበሉ? የነቀዘ ስንዴ ነው ብሎ መናገር አሁን ለምን አስፈላጊ ሆነ? ደግሞስ ወገብን የሚሰብርና የጀርባን ጅማት የሚፈታው የሰሞኑ የዶላር ማዕቀቡስ “የሚቀርብን የሻገተ ወይም የበሰበሰ ዶላራችው ነው” ለምን አላሉም?

ከዚህ በተጨማሪም አቶ ሽመልስ “እግዚአብሔር በኛ ላይ ጠላቶች ያስነሳብን እንድንበረታ ወይም እንድናሸንፍ ነው” ብሏል። ይኼም ሌላ ኢዲፕሎማሳያዊ የሆነ መደዴ ንግግር ነው። እግዚአብሔር ብዙዎች ጠላቶች ሆነው እንዲነሱ የሚያደርገው፤ ከእነርሱ ጋር በክፉ ስራቸው ተደምሮ ዙሪያቸውን ከበው ያሉትን ጠላቶችን እንደ ጉም ሊበትንላቸውና እንደ ማለዳ ጤዛ ሊያረግፍላቸው ሳይሆን፤ አካሄዳቸውና አደራረጋቸው ተግቢና የጥፋት ስለ ሆነ፤ ይህን እንዲያዩና እንዲታረሙ የከበቡዋቸው አገሮች እንደ መቅጫ አለንጋ አድርጎ መጠቀሙ ነው። እግዚአብሔር የሚወዳቸውን ለማቃናትና ለማስተካከል የሚቀጣ አምላክ መሆኑ ቀድሞ ማወቅ ያሻል። ይሁዳ በበደልዋና በኀጢአትዋ ሰክራ እንጣጥ እንጣጥ ስትል አግዚአብሔር ከዚህ ክፉ ሁኔታዋ ይታደጋት ዘንድ አሕዛብ በሆነችው በመራርዋና እግዚአብሄርን በማታውቀው አረማዊት ሃገር በከለዳዊቷ በባቢሎን እንደ ቀጣትና እንዳቃናት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስለ ቪዛው እገዳ አስመልክተው ከተናገሩት ንፋስ እንደሚወስደው ገለባ ልዝብና ቀሊል የሆነው “ከባሌ እስከ አድዋ ድረስ እንጂ እነርሱ ጋር እንደማልሄድ ንገሩልኝ” በማለት በፌዝ በአደባባይ የተነገሩት ነው። አባባላቸው የሃገሪቱ መሪዎች ዲፕሎማሲ ቁልቁል መምዘግዘግ (Free fall) ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ወክለው በታላላቅና ባለጸጋ ሃገሮች ጉባኤ ተጠርተው እጹብ ድንቅ ንግግር አድርገው ውጤት ያመጡት መለስ ዜናዊን ላለማንሳት አይቻልም። በዛሬዎቹ መሪዎችና፤ ኢትዮጵያ እንደ ዕንቁ ተፈላጊና ተወዳጅ አድርጓት በነበሩ መሪዎች መካከል የነበረው የዲፕሎማስያዊ ንግግር ክህሎት ልዩነት በሰማይና በምድር ባለ ከፍታ ልዩነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።

አቶ ሽመልስ እንዳሉት ከባሌ ወደ አድዋ በሚያደርጉት ጉዞ፤ በመንገዳቸው ሁሉ ሰው እየረገጡና እየጨፈለቁ ነው። አዎን! ከባሌ መረገጥ ጀምረው አድዋ እስኪደርሱ እንዲሁ ይነዳሉ። አንድ ወቅት ላይ አንድ ሾፌር ከረዳቱ ጋር ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ጭንብስ ብለው ጠጥተው በሌሊት ሰው እየገጩ ይጓዙ ነበር አሉ። ሽፌሩ ረዳቱን “አንተየ አዲስ አበባ የገባን መሰለኝ!” አለው። ረዳቱም “እንዴት አወቅህ?” ብሎ ሲጠይቀው፤ “ይኸውና አሁን ብዙ ሰዎችን መረገጥ ጀምሬለሁ” አለው ይባላል (የቃል ልውውጦቹ ከሰካራሞች አፍ እንደ ወጣ ተደርጎ ይነበብ)። እናማ አቶ ሽመልስ እስከ ቆቦ ድረስ በጥቂት እየገጩ ከነዱ በኋላ፤ ዋጃን አልፈው አላማጣ ሲደርሱ ቁጥር ስፍር የሌለው የትግራዋይ ነፍስ እየገጩና እየገደሉ እንደሚሄዱ የታወቀ ነው።

በኢትዮጵያ መሪዎች በዘፈቀደ በሃገር ውስጥና ለውጭው ዓለም የሚነገሩ ቃላት ለሃገሪቱ የሚያደርሱት አደጋ ከፍተኛ ሲሆን ውድቅትና መለያይትን የሚያስከትሉ መሆናቸው በመጠቆም፤ የተዳፋት ቁልቁል ጉዞ በምን መልኩ እንደ ተፈጸመ ከሞላ ጎደል ለማሳየት የሞኮርክ ይመስለኛል።

Back to Front Page