Back to Front Page

አንድነትና አሃዳዊነት:-የሃፄያውያን የቃላት ማምታታትና የኢትዮጵያ የቁልቁለት መንገድ

አንድነትና አሃዳዊነት:-የሃፄያውያን የቃላት ማምታታትና የኢትዮጵያ የቁልቁለት መንገድ

ኻልኣዩ ኣብርሃ 07-29-21

ሰሞኑን ከምንሰማቸው ንግግሮችና ነገሮች የምንገነዘበው ከኩይሳ ተራራ እየሰሩ፣ በቀላሉ የሚፈታውን ችግር እያወሳሰቡ፣ እኛ ከሞትን ሰርዶ አይበቅልም ብለው ህዝብን ከህዝብ በማፋጀት ኢትዮጵያን ይዘዋት ለመውረድ ከፍተኛ ዘመቻ ላይ እንደተሰማሩ ነው። እነዚህ እነማናቸው? እነዚህ ጎሬአቸው የበዛ ግን አላማቸው አንድ የሆኑት ኢትዮጵያን አንድ ላይ ጨፍልቀው መግዛት የሚመኙት ሃፄያውያን ናቸው። ሰሞኑን ሚዛናዊና ዴሞክራሲያዊ ለመምሰል ቃላትን እያሽሞነሞኑ፣ ሲመች በሳቅ ሲከፋ በለቅሶ እያጀቡ የአሃዳዊነትና የአማራ የበላይነት መርዛቸውን የሚረጩት እነ ኤርሚያስ ለገሰ "ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል" ሆነው አርፈውታል። የትግራይ ህዝባዊ ጦር የትግራይን ህዝብ ከምድረገፅ ለማጥፋት ከተደረገው ርብርብ ህዝቡን ነፃ ለማውጣት የሚያካሂደውን የመከላከልና ወንጀለኞችን የመቅጣት ጦርነት የኢትዮጵያን አንድነት የሚንድ አገር አፍራሽ ጦርነት ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን ለማዳን በትግራይ ህዝብ ላይ በመነሳት ግዴታውን እንዲወጣ በመሪውም በምሁሩም ጥሪ ቀርቦለታል። ትግራይ ከዘር ማጥፋት መአት መትረፏና የተቀማችውን መሬት ማስመለሷ በእጅጉ ያቃጠለው ኤርሚያስ ለገሰ የጋዜጠኝነት የውሸት ክንብንቡን አውልቆ ጥሎ ያፈጠጠ የናዚ ግልገል ሆኖ ተገኘ። ትግራይን ለማጥፋትና የሃገሪቱን አስተዳደር ወደ አማራ-መር ሃፄያዊ አገዛዝ ለመቀየር የተደረገው ጥረት ከሽፎ አገሪቱ በአሃዳዊያን አልሞት ባይ ተጋዳይነት ስትናጥ ኤርሚያስ ለገሰ ያቀረበው መፍትሄ እንደጋዜጠኛ ሰላማዊውን መንገድ መምረጥ ሳይሆን የከፋና ለኢትዮጵያ መፍረስ የማረጋገጫ ሰርቲፊኬት የሚሰጥ ነው። ከዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ ከርቀት በምቾት ተቀምጦ ውሃ ከመልቀቅ ይልቅ እሳት ማቀጣጠል ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀል ነው።

Videos From Around The World

ኤርሚያስ ያቀረበው የዲያብሎስ መፍትሄ እንዲህ ይላል:- "አገሪቱ ከምትፈርስ ማእከላይ መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ህገ መንግስቱን ማፍረስ" ይህ ማለት ወልቃይት ከአማራ እጅ መልሶ ከሚነጠቅና ትግራይ የምታራምደው ፌደራላዊ ስርአት ከሚያሸንፍ ህገመንግስት አልባ የሆነ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት ይመስረት ነው። ሰው ኢትዮ360 ዲግሪ ብሎ ለራሱ ስም አውጥቶ 45 ዲግሪ እንኳ ዞር ብሎ ማየት ያቅተዋል? ለነገሩ የኢትዮጵያ ትምህርትና ዲግሪ ለብዙዎቹ የፓለቲካ ጭፍኖች ህዝብን ለማሳበድ የሚጠቀሙበት የደብተራ ድግምት ሆኗል። ደብተራ የላቀ የእምነት ሰው እንዲሆን የተማረውን ትምህርት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲጠቀምበት መኖሩ ከዚህ የተለየ አይደለም። ሰብአዊነት የሚያጎናፅፈውን ፍልስፍና እስከ ጣርያ ድረስ ተምሮ ዳኛቸው አሰፋ "በትግራይ ላይ ተነሱ፣ ህዝቡንም ፍጁ" ካለ፣ በሰላምና በህዝብ ደህንነት የትምህርት ዘርፍ የመጨረሻውን ዲግሪ የተቀዳጀው አቢይ አህመድ ህዝብን ያህል የአምላክ ስራ "ካንሰርና አረም ነው ዝመቱበት" ካለ፣ አባይን ገድቦ ብርሃን ይሰጠናል ያልነው የውሃ መሃንዲስ ስለሺ በቀለ በአጉል አድርባይነትና ጠባብነት "የትግራይ ህፃናት ሓሺሽ እያጨሱ ኢትዮጵያን ይወጋሉ" ካለ የዲግሪዎች መክሸፍ ይባላል እንጂ ሌላ ምን ይባላል?

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትርምስ ዋና መንስኤው በአንድነት ስም አሃዳዊነትን ለማስፈን የሚደረግ መሰሪ ዘመቻ ነው። የኢትዮጵያን አየር የሞላው በኢትዮጵያ አንድነት ላይ በትግራይ ሃይሎች አደጋ ተጋርጧል የሚለው እሪታና አቤቱታ ነው። እውነታው ግን በትግራይ ሃይሎች አደጋ የተጋረጠበት የኢትዮጵያ አንድነት ሳይሆን የአንድነት ለምድ ለብሶ አራት ኪሎና ባህርዳር አብያተ መንግስታት ውስጥ የመሸገው አሃዳዊነት ነው። አንድነት ከአሃዳዊነት ጋር መምታታት የለበትም። አንድነት ማለት አንድ ወጥ መሆን ማለት አይደለም። ወጥ ከሆነ "አንድ" ይባላል። ይህ ማለት አንድ ቅርፅ፣ አንድ ቀለም፣ አንድ ይዘት ያለው ማለት ነው። "አንድነት" ማለት "አንድ" መሆን ማለት አይደለም። "አንድነት" የሚለው ቃል ቁጥርን ለመግለፅ ወይንም የሆነ ቁስ አካልን ባህርይ የሚያመለክት ሳይሆን አስተሳሰብን የሚወክል ፅንሰ ሃሳብ ነው። ይህን በሚገባ ለማብራራት የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስትያናትና የአዲስ አበባን አንዱ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል። የላሊበላ ጊዮርጊስ ደብር ከአንድ ወጥ ድንጋይ ነው ወለሉም፣ ግድግዳውም፣ ጣርያውም፣ መስኮቱም፣ ምሶሶውም የታነፀው። ይህ "አንድ" እንጂ "አንድነት" አይደለም። ለምሳሌ "አንዲት ኢትዮጵያ" ማለት ኢትዮጵያ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል፣ አንድ አስተሳሰብ፣ አንድ ታሪክ አላት ብለው የሚቃዡ ሰዎች የሚጠቀሙበት አባባል ነው። አንዲት እስራኤል፣ አንዲት ግብፅ፣ አንዲት ጃፓን፣ አንዲት ፊንላንድ ቢባል ትክክል ሊሆን ይችላል፣ እሱም በጥንቃቄ ነው። አንድ የሚመስል ማህበረሰብ ምን የሚለያይበት ነገር እንደሚኖር ለመገንዘብ መሞከር ጠቃሚ ነው።

የአዲስ አበባን አንድ ህንፃ ብንወስድ የላሊበላ አንድ ወጥ ድንጋይ አለመሆኑን እንገነዘባለን፣ አይናችንን ካልጨፈንን በስተቀር። ይህ ህንፃ ከምን ከምን እንደተሰራ መዘርዘር ሁሉም የሚያውቀውን ነገር መድገም ይሆናል። ማለት የሚገባው ነገር ግን በተለያየ ቦታና ማምረቻ የተመረቱ፣ ለህንፃው ውበት ጥንካሬና አገልግሎት አሰጣጥ የሚበጁ፣ የየራሳቸው ባህርያት ያሏቸው ማቴርያሎች ተቀነባብረው በአንድነት የፈጠሩት ህንፃ መሆኑ ነው። እነዚህ ማቴሪያሎች ተጨፈላልቀው ወይንም በአንድ ቀልጠው ወይንም በአንድ ተፈጭተው አንድ ማቴሪያል ተደርገው ቢሆን ኖሮ ህንፃው ህንፃ አይሆንም፣ የሚጠበቅበት አገልግሎትም አይሰጥም። ህንፃው ህንፃ ሆኖ ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጠው እነዚህ የተሰካኩት የተለያዩ ማቴሪያሎች ምንነታቸው ተጠብቆ ድርሻቸውን ሲወጡ ብቻ ነው። አርማታ ብረት ብረትነቱ ቀርቶ ተፈጭቶ ከስሚንቶው ጋር በማዋሃድ " ኮለን ሆነህ ቁም፣ ስላብ ሆነህ ወለልና ጣሪያ ሁን ቢባል ይናዳል እንጂ አይጠብቅም። ኮለን ኮለን ሆኖ ህንፃ የሚሸከመው ብረት በጥንካሬው ስሚንቶ ባጣባቂነቱ ምንነታቸውን ጠብቀው "አንድነት" ሲጣመሩ ነው። የአንድ መሆንና የአንድነት ልዩነት በሌላ ምሳሌ መረዳት የሚቻለው በተፈጥሮ ሳይንስ "ኮምፓውንድ" እና "ሚክስቸር" ያላቸውን ልዩነት በማስተዋል ነው። ኮምፓውንድ የተለያየ ባህርያት ያላቸውን ንጥረነገሮች አዋህዶ አንድ የተለየ ነገር መፍጠር ሲሆን የተዋሃዱት ንጥረነገሮች ስማቸው ብቻ ሊኖር ይችላል፣ አንዳንዴም ጨርሶ ይጠፋል። ሚክስቸር ማለት ምንነትን ጠብቆ ተፈላጊውን አገልግሎት በጋራ መስጠት ማለት ነው። የስንዴና የሽምብራ ቅልቅል ቆሎ ይጣፍጣል። እዚህ ላይ ሽምብራም ሽምብራ ነው፣ ስንዴም ስንዴ!

የኢትዮጵያ አንድነት ሲባል የኢትዮጵያ ኮምፓውንድ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሚክስቸር ማለት ነው። ኢትዮጵያ እንደ ላሊበላ ደብር አንድ ወጥ አለት ሳትሆን እንደ ፍንፍኔው ህንፃ የብዙ ማቴርያሎች ስብጥር ናት። አንድ ወጥ ሳትሆን አንድ ወጥ ለማድረግ መታገል የፓለቲካ ጥፋት ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮም ጋር እንደመታገል ይቆጠራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የታሪክ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ልዩነትን መካድ ወይንም መኖሩ ቢታመንም "በታኝ" ስለሆነ ከአንዱ ብሄር ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ስር ገብቶ ቅመማ ቅመም ሆኖ ያገልግል ብሎ አገር እስክትናወጥ ድረስ በአቋሙ የፀና የግትርነት ፓለቲካ ጎጂ ብቻ ሳይሆን አጥፊ ነው። የዱር እንስሳትን አንበሳ፣ አጋዘን፣ ነብር እያልን መለየት ካላቃተን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከበር የሚገባው የራሱ ማንነት ያለው ሲዳማ፣ አፋር፣ አኝዋክ መኖሩ የሚካደው ለምንድነው? ሁለቱም ተፈጥሯዊ ክስተቶች ናቸው እንጂ የሰው ልጅ ሆን ብሎ የሚፈጥራቸው ልዩነቶች አይደሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ፈተና የሆነው ብሄር ብሄረሰቦችን "ህገ መንግስቱ ከአንዲት ኢትዮጵያ ፈልጦ ፊላልጦ ያረገፋቸው ትንሽና ትልቅ የእንጨት ቁርጥራጮች" እንደሆኑ አድርጎ የማሰብ የተደናበረ ፓለቲካ ነው። ፍጥጥ ግጥጥ ያለው እውነት ልዩነቱ ህገመንግስቱን ፈጠረ እንጂ ህገመንግስቱ ልዩነቱን አልፈጠረም ህገ መንግስቱ ያደረገው ነገር ቢኖር አንድ ወጥ ለማድረግ በሃፄያውያን ሲቀጠቀጡ፣ ሲፈጩ፣ ሲቀልጡ የነበሩት ብሄር ብሄረሰቦች አንድ ውሁድ ሆነው ሳይሆን ማንነታቸውን ጠብቀው በአንድነት እንዲኖሩ ነው። አንድ ማድረግ አሃዳዊነት ነው፣ አንድነት ግን ፌደራላዊነት ነው። አሁን በትግራይ የሚመራው የፌደራሊዝም ሃይል እየተወነጀለ ያለው በግልባጩ ነው። "የኢትዮጵያ አንድነትን ለማፍረስ" ብሎ መክሰስ ትርጉሙ ፌደራሊዝምን ለማፍረስ እንደማለት ነው። ፌደራሊዝምን በማፍረስ የኢትዮጵያ አንድነትን ለማፍረስ እየታገሉ ያሉት አሃዳውያን ናቸው፣ "የአባየን እከክ እማየ ላይ ልክክ" ነው ነገሩ። አንድነት የሚኖረው ልዩነት ሲኖርና በጋራ ጉዳዩች ላይ አብረው እየኖሩ አብሮ ለመስራት በፍላጎት ስምምነት ላይ ሲደረስ ነው ህንፃ ግንባታ ላይ ብረትና ስሚንቶን በግዴታ የሚያገናኘው ሰው ነው፣ በአገር ግንባታ ላይ የየራሱ ማንነት ያለውን ህዝብና ህዝብን የሚያገናኘው ግን ፍላጎትና ፈቃደኛነት ነው። አሃዳዊያን የነሱ ባልሆነው አንድነት እያጭበረበሩ በአንድነት ባለቤት ፌደራላዊያን ላይ ህዝብን አጭበርብረው በማነሳሳት ኢትዮጵያን መቀመቅ እያወረዷት ነው።

የማይቆጨው ነገር ግን "ደባ ራሱን፣ ስለት ድጉሱን" የሚሆን መሆኑ ነው። የአማራ ፓለቲከኞች ግልፅ በሆነ ቋንቋ ጀሯችን እስኪጠዘጥዘን ድረስ "ኢትዮጵያ ማለት አማራ፣ አማራ ማለት ኢትዮጵያ ነው" ብለውናል። እና ኢትዮጵያ ከፈረሰች ማነው የሚፈርሰው? አማራ ብቻ መሆኑ አይደለም እንዴ? ሌላውማ አንድ ወጥ የአማራ ድንጋይ ሆነህ ካልተሰራህ ኢትዮጵያ አይደለህም ተብሎ እኮ የየራሱ ስም ይዞ በተጠንቀቅ ቆሟል እንጂ አይፈርስም። ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ተስማምቶ በእኩልነት መኖርን ተፀይፎ፣ ጨፍልቄ ካልገዛኋችሁ እያለ ሌላው ላይ የክስ ናዳ በማውረድ የቆመበትን መሬት የሚቆፍረው ማነው? የኢትዮጵያ ሰሪና ፈጣሪ፣ ጠባቂና አሻጋሪ እኔ ብቻ ነኝ እያለ ሌሎችን ብሄር ብሄረሰቦች እንደተለጣፊ እየቆጠረ የሚያሳንሰው የአማራ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚና የአካዳሚክ ልሂቅ ነው። ስለዚህ መነሻውና መድረሻው:- የኢትዮጵያ አንድነት እያፈረሰ ያለው አሃዳዊነት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አፈሙዝህን ወደ መሰሪው እውነተኛ ጠላትህ አዙር። አንድነትን እጠብቃለሁ ብለህ በአንድነትህ ላይ አትዝመት። ከደነዘዝክበት ንቃ! ጁንታ እያልክ የምትዘረጥጠው ህዝብ የአንድነትህ መከታ መሆኑ በጊዜ ነቅተህ ተገንዘብ። ኤርሚያስም ከነፃ አገር ተቀምጠህ መርዝህን አትርጭ። ኢትዮጵያን አበጣብጠህ ከፈረሰች በኋላ የሚኖርህ ቻናል ኢትዮ 000 ነው።

Back to Front Page