Back to Front Page

ኢትዮጵያ:- በኣንድ ህዝብ ጥላቻ ብቻ አንድ የሆነች አገር

ኢትዮጵያ:- በኣንድ ህዝብ ጥላቻ ብቻ አንድ የሆነች አገር

ኻልአዩ እብርሃ

09-30-21

አይነ ስውሩና ልበ ብርሃኑ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋይ በኢትዮጵያ ላይ ያለው ችክ ያለ ፍቅር ይደብረኛል። "አትወጣጠሪ አትበይ ጠምበር ገተር፣ እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር" የድሮውን ኤሪትርያን የሚያካትተውን የኢትዮጵያ ካርታ በመግቢያ ምስልነት እያሳየ "የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች" አይነት ስሜት ይለቃል፣ አርበኞቹ ተጠቃሚዎች የነበሩ ይመስል! እርግጠኛ ነኝ ቴድሮስ አይሳካለትም፣ ምክንያቱም በዚች አገር የሚሳካለት ኢትዮጵያን ከልቡ የሚወድ ሳይሆን ወደድኩሽ እያለ ቃላት የሚያዝጎደጉደው ነው:-"ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው" እያሉ አይደል አገሪቱን ለትርምስ የዳረጓት? "ኢትዮጵያን እናድን" በሚል ተረት ተረት አይደል የውጭ ሃይል ጋብዘው የገዛ ወገናቸውን እንደ አውሬ ያደኑት? ቴዎድሮስ ፀጋይን እወደዋለሁ፣ የትንተና ችሎታው ወደር አልባ ነው፣ የኢትዮጵያ ፍፁማዊ አንድነት ሲነኩ ንዴቱ አይጣል ነው እንጂ። በላይ ዘለቀን የሰቀለች አገር፣ ስዩም መስፍንን የረሸነች ኢትዮጵያ፣ ዮሃንስን ያራከሰች ምድር፣ አብዲሳ አጋን ከነመፈጠሩ የዘነጋች ውለታ ቢስ እናት ለቴዎድሮስ ፀጋየ ትሆናለች ብሎ ማሰቡ የዋህነት ነው። እግረ መንገዴን የተሰማኝን ጣል ባደርግም ቴዎድሮስን ያነሳሁበት ዋና ምክንያት ባለፈው ሰሞን የተናገረውን የማይረሳ እጅግ ገላጭ የሆነ ሃይለቃል ለዚህ ፅሁፌ በድጋፍነት ለመጠቀም ነው።  ቴዎድሮስ እንዲህ አለ:- "ኢትዮጵያን እግዜር ይወዳታል እየተባለ የምትሆነውን እያየን ነው፣ የጠላት ቀን ምን ልትሆን ነው?"

ኢትዮጵያን አንድ ያደረጋት ምንድነው? ብየ ራሴን ስጠይቅ የተማርኩት ይህ ሁሉ እውቀት እልም ብሎ ይጠፋብኛል። ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሚጋራው ቂልነት ውስጥ ተነክሬ ራሴን ባታልል ለጊዜውም ቢሆን እረፍት አገኛለሁ። የምሁር መሃይም መሆን ስለማልፈልግ ግን "ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሚጠብቃት እግዚአብሄር ነው" ብየ በፈጣሪየ አልሳለቅም። እግዚአብሄር አያዳላም፣ የሚያዳላ ቢሆን እንኳ ለኢትዮጵያ የሚያደላበት ምንም በቂ ምክንያት የለውም፣ ይቺ የጭቆና አገዛዝ ምድር! ስለዚህ ብዙ ሰው ሊቀበለው ወደማይመርጠው ሃቅ እንሂድ። ኢትዮጵያ አንድ ሆና የኖረችው በጉልበት ነው እንጂ በውስጧ ያላት ልዩነት መበታተን ሳይሆን እርስ በርስ የሚያጠፋፋ ነው። በነገስታቱና በወታደራዊ አገዛዝ ዘመናት ከተወሰነ አካባቢ በተነሳና ከተወሰነ አንድ ማህበረሰብ በወጣ የገዢ መደብ ቀንበር ስር ተይዛ የቆየችው ህብረብሄራዊትዋ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጨፈለቀውን ህብረብሄራዊነቷን የሚያስተናግድ ስርአት በመዘርጋቱ ላለፉት ሶስት አስርት አመታት አገሪቱ ውስጥ የግዴታ ሳይሆን የውዴታ አንድነት ሰፍኖ ቆይቷል። በአንድነት ማእቀፍ ውስጥ የራስ አስተዳደር ያመጣውን የኢትዮጵያ አብሮነት ለአገዛዝ ምኞታቸው አንድ አንገት አልሆንላቸው ስላለ፣ ይህን ህብረብሄራዊነት አገር የመበተን ሴራ ነው የሚል ስም አውጥተውለት እያራከሱትና እያስኮነኑት ይገኛሉ። ፍትሃዊ የሆነውን የፈቃደኝነትን አንድነት ሽረው በጉልበት አንድነት ማምጣት የሚፈልጉት የድሮ ስርአት ናፋቂዎች ለሰላሳ አመታት የኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነታቸውን አክብረው አብሮነታቸውን ወደው በሰላም መኖራቸውን ሸምጥጠው ይክዳሉ። "አፓርታይድ" ይሉታል በተውሶ ስድብ! ምን አገናኝቶት ነው ዱባና ቅል? አፓርታይድ መብት ከልካይ እንጂ መብት ሰጪ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አባዜ ስድብ መዋስና አለ አግባብ መጠቀም ነው። ሲቪላዊን መንግስት "ጁንታ" የሚል ምሁርም መሃይምም ያለባት አገር:- ኢትዮጵያ!

Videos From Around The World

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ለጠላትህም አይስጠው የሚያሰኝ ነው። ማን እንዲህ አደረጋት? እንወድሻለን እያሉ የሚያጭበረብሯት ጥቅመኛ ልጆቿ! እነዚህ ጥቅመኞች እንደ ቁጥራቸው ልዩነታቸው የበዛና የተወሳሰበ ነው። አንድ በረት ውስጥ የሚያሳድር የጋራ ነገር የላቸውም። አንድ በረት ውስጥ አንበሳን፣ ሚዳቋን፣ ጅብን፣ አህያን፣ እባብን፣ አይጥን፣ ወዘተ በሰላም ማሳደር ይቻላል? አይታሰብም! ይህ በኖህ ዘመን የቀረ ነው። ታድያ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የእምቧይ ካብ ሆና እያለ እስካሁን ያልፈረሰችው በምን ሃይል ነው? "በአምላክ ሃይል" እንዳትሉኝ፣ ሃጥያት ነው። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ አንድ ሆና የቆመችውና ኤሪትርያም ሳትቀር አቅፋ የያዘችው በትግራይ ህዝብ ጥላቻ ብቻ ነው። የአንድ ህዝብ የመረረ ጥላቻ ያስተባበረው ህዝብ! የራሷን ማህበረ-ፓለቲካዊ እውነታ ተቀብላ የአንድነቷ ዋስትና አድርጋ የፈተለችውን የህብረብሄራዊነት ድር እየበጣጠሰች ያለችው ኢትዮጵያ የቆጡን አሃዳዊነት ለማውረድ የብብቷን ህብረብሄራዊነት እየጣለችው ነው። ይቺ የአህያይቱ እጣ የደረሳት አተርፍ ባይ አጉዳይ አገር ኢትዮጵያ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል፣ አንድ ሃይማኖት ካልሆንኩ ሞቼ ልገኝ ብላ ወስናለች። ልጆች እያለን ስምንተኛ ክፍል ሲወደቅ ገመድ ይዞ ሄዶ ራስን መስቀል የተለመደ ነበር። ኢትዮጵያም መሬት ላይ ባለው እውነታ ተግባራዊ ሆኖ ሁሉም አሽናፊ የሚያደርግ አማራጭ በጋራ ከመፈለግ ይልቅ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ላሊበላ ህንፃ አንድ ወጥ ድንጋይ ካላደረግሁት ራሴን ባጠፋ እመርጣለሁ ካለች "መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ" ብሎ መመረቅ ነው። ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግር ልጅ እኮ በስህተት ምላጭ ወንድነቱን ሊያሳጣው ይችላል። የማን ያለህ ይባላል? "ቀድሞ ነበር'ንጂ መጥኖ መደቆስ..." በትግርኛ " ታይሞ'ግበር ደኒንካ ይንባዕምበር" ይባላል።

በሚያስደምም ሁኔታ ኢትዮጵያ እስከሞቷ ድረስ አንድ ያደረጋት የእውነተኛ አንድነት ዋስትናዋ የሆነው ህብረብሄራዊነት እውን ያደረገው ህወሓትና የትግራይ ህዝብን ከምድረገፅ ለማጥፋት ያላት ሰይጣናዊ ፍላጎት ነው። ይህን ትግራይን የማጥፋት ፍላጎት ምክንያቱን ለመረዳት "በሌሎች አለማት ፍጡራን አሉ ወይ?" ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚያዳግተው ያህል እንቆቅልሽ ነው። ትግራይ የኢትዮጵያ ስልጣኔና ሃይማኖቶች መሰረት ነው እያለች ለመጣው ጎብኚ ሁሉ የምትናገረው ኢትዮጵያ፣ አምባገነን መንግስትን በከፍተኛ መስዋእትነት አስወግዶ ለኢትዮጵያ በህዝቦች ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አብሮነትን ያመጣው የትግራይ ህዝብ እያለች ስትተርክ የኖረችው አገር፣ የውጭ ወራሪ ሃይሎችን እየመከተ ነፃነትን ለትውልዶች ያወረሱ የትግራይ አርበኞች እያለች ስታወድስ የኖረችው ምድር አሁን ይህንን ህዝብ "የማሪያም ጠላት" አስመስላ በማቅረብ ከህፃን እስከ ሽማግሌ፣ ከቄስ እስከ ሃይማኖት የለሽ ያነሳሳችበት ምክንያት ምንድነው? ይህን ጥያቄ እንኳንና እኔ ደካማ የሰው ፍጡር አምላክ ራሱም ቢሆን ለመመለስ የሚቸገር ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የተቀመጠችበትን ቅርንጫፍ ስትቆርጥ ሁሉም እጅ በእጅ መጥረቢያ በማቅረብ እየተረባረበ ይገኛል። በትግራይ ላይ ያለው ጭፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻ በህዝብ ማእበልነት በትግራይ ላይ እንዲዘምት አድርጎታል። ተው ሲባልም "በውስጥ  ጉዳያችን ጣልቃ አትግቡ" ይባላል። ትግራይ ሲመች ከኢትዮጵያ ውጪ፣ ሲቸግር የኢትዮጵያ አካል እየተደረገች ነው። ስትጠነክርና አልሞት ስትል "ትግራይ የኢትዮጵያ መስራች" ትባላለች። አትሌቶቿ ሲያሸንፉ  "ኢትዮጵያ ከፍ አለች" ተብሎ ይደለቃል። የትግራይ ምሁራን "ህዝብ ተጨፈጨፈ፣ ሴቶች ተደፈሩ፣ ይሁንታ የተሰጠው ረሃብ ህፃናትን ፈጀ" ብለው አቤቱታ ሲያቀርቡ "ከሃዲዎች፣ አገር አፍራሾች" ይባላሉ። "ህዝብ ተራበ" ብሎ መናገር ወንጀል የሆነባት አገር ኢትዮጵያ፣ ወይስ "ሚዞፕያ" እንበላት።

የኢትዮጵያ ህዝብን አንድ ያደረገው የትግራይ ጥላቻ ማብቃቱ አይቀርም። ጥላቻው ባይቀርም ጥላቻ የወለደው ክፉ ድርጊት ግን ያበቃል ብቻ ሳይሆን እያበቃ መሆኑን በተግባር እያየን ነው። ኢትዮጵያ አንድ የሆነችበት የትግራይ ህዝብ ጥላቻና ህዝቡን የማጥፋት የከረረ ፍላጎት ትግራይ ከዚህ የዘመናት የበደል አዙሪት ለመውጣት በምትወስነው ውሳኔ ምእራፉ ይዘጋል። በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሚያስቀጥላት አስተሳሰብ ከቶ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚናገር ሰው አለ? እስካሁን "ጥሩ" ኢትዮጵያዊነት ማረጋገጫ  ሰርቲፊኬት የሚሰጠው ትግራይን አዳዲስ ስሞች እየፈበረኩ በመሳደብና "በለው! ጨፍጭፈው!" ብሎ በየመድረኩና በየሚድያው በማቅራራት ነው። አሁን የቀረ ነገር ቢኖር ትግራይን በመሳደብና በመራገም መአርግ መስጠት ብቻ ነው:- "ሲንየር ተሳዳቢ፣ ጁንየር ተሳዳቢ፣ ማይነር ተሳዳቢ" ወዘተ። ውስጡን በሚገባ ለመረመረ ሰው የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ላይ ከማፍጠጡ በስተቀር የጋራ አላማና ራእይ የለውም። ለአስር ሺዎች ይህ የትግራይ ጥላቻና ዘመቻ የእንጀራ ገበታቸው ሆኗል። በትግራይ ላይ በማነሳሳትና ባላቸው የጥላቻ መጠን በየደረጃው ሹመት ያገኙና ያንን ስልጣን ለማስጠበቅ አዳዲስ የጥላቻ መግለጫዎችን "በምርምር" የሚፈልጉ ብዙ ናቸው፣ ሁሉም ናቸው ለማለት ባልደፍርም። ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግና ተብሎ በቴሌቪዝን የሚቀርበው ምላሱ እጅግ የረዘመው ሁሉ ነው። ከሁሉም በላይ መዋሸትና መሳደብ የሌለበት የጦር መኮንን ሆኖ እያለ ስለ ትግራይ መዋሸትና መሳደብ በጦር ሃይሉ ውስጥ ሜዳልያ ባያስገኝ ደማቅ ጭብጨባ ግን በገፍ ይበረከትለታል:- ካሳየ ጨመዳን አንድ በሉ፣ ባጫ ደበሌን ሁለት አላችሁ? ብርሃኑ ጁላን መቁጠር እንዳትረሱ! የሲቪል ባለስልጣናትን እንቁጠር? ተውት ይደክመናል! ሰዎቹም ዋሻችሁ ሲሏቸው ስለሚብስባቸው አለመነካካቱ ይሻላል እንደ አቧራ!

ኢትዮጵያውያን የትግራይን ህዝብ መወገድ ያለበት "ካንሰር፣ አረም፣ እባጭ፣ እንቅርት" እያሉ በጥይትና በረሃብ ሊጨርሱት ሲታገሉ ኢትዮጵያዊ አለመሆኑን ወስነው ነው። መንገድ ሲዘጉበት፣ በጀት ሲነፍጉት፣ በአገሪቱ መንግስት ውክልና ሲያሳጡት፣ ሰርቶ በላውን የትግራይ ተወላጅ ድንበር ሾልኮ ወደ አሜሪካ የገባ የሜክሲኮ ሰው ይመስል ከየቤቱና ከየድርጅቱ እየለቀሙ ማጎሪያ ቤት ሲከቱት፣ ትግርኛ ቋንቋ መናገር ወንጀል ሆኖ የትግርኛ ሙዚቃ መስማት እንደ አገር ክህደት ተቆጥሮ ትግራዋይ ሁሉ በያለበት ሲሸማቀቅ የውጭ ዜጎች የሆኑት ኤሪትርያውያን እንደልባቸው ህብረተሰቡን በአንድ እግሩ  ሲያቆሙት፣ ትግራዋይን ኢትዮጵያዊ ነህ እያሉት ነው? ራሳቸው በተግባር ያሳጡትን ኢትዮጵያዊነት "ኢትዮጵያዊ አደለህም የሚል ግልፅ መልእክት ደርሶኛል" ያለ ትግራዋይ "ኢትዮጵያዊ አይደለሁም" ቢል ምን ያስገርማል? ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ በቃልም በተግባርም የተነገረው ህዝብ የግድ ኢትዮጵያዊ ልሁን ብሎ እንዲታገል ነው የሚጠበቅበት። ልጅ እያለሁ አባቴ ሊመታኝ ከዘራውን ሲያነሳና ሲመታኝ ሮጬ ከማምለጥ ይልቅ  ወደሱ ሄጄ ወገቡን አቅፈው  እንደነበረ ታላላቆቼ ነግረውኛል። ይህ ለአባት ይሰራ እንደሆነ እንጂ በአገር ደረጃ አይሰራም። ዜግነት ጋብቻ ነው። ሁል ጊዜ ከሚቀጠቅጥህና አምርሮ ከሚጠላህ የትዳር ጓደኛ ጋር መኖር እትገደድም። በዜግነትም በትዳርም መዋደድና መከባበር ግዴታ ነው! ኢትዮጵያውያን (በጅምላ የምፅፈው በተግባር ልዩነት ማየት ባለመቻሌ ነው) የትግራይን ተወላጆች በተግባር ኢትዮጵያውያን አለመሆናቸውን በግልፅ ካሳዩዋቸው በኋላ "እሺ፣ ኢትዮጵያውያን ካልሆንን የራሳችን አገር እንፈጥራለን፣ መቸም 6 ሚልዩን በላይ ህዝብ አገር አልባ ሆኖ አይኖርም" ሲባል ቡራ ከረዩ ይባላል! "እንዴት ትግራይ ነፃ አገር ትሁን ትላላችሁ? እናንት ከሃዲዎችእያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላሉ። "አምላኬ ሆይ ቅጥ ያለው፣ የሚጨበጥ እጀታ ያለው ጠላት ስጠኝ" ብሎ ፈጣሪን መለመን አስፈላጊ ሆኗል። ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ሁሉ ትግራዋይ ላይ ይህ ሁሉ መአት ሲያወርዱበት መላ አለም ጉድ አለ፣ አወገዘ፣ ለማስቆም ሞከረ። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ምን አለች? "በአገር ሉአላዊነት ጣልቃ አትግቡ" ጉድ! ጉድ! ጉድ! (የፈረንጁ ጉድ አይደለም፣ የአማርኛው ነው) ይህ ማለት "ልጄን ልገድለው ነውና በቤቴ አያገባችሁም" ያለ አባት እሪ ሲባል ተሯሩጦ የመጣውን ጎረቤት ያባርራል ማለት ነው። ልጁ ከሆነ ከሌላ ገዳይ መጠበቅ እንጂ ከሌላ ጋር ተባብሮ ልጅን መግደል ልጅ ነው ያሰኛል? የግድያ ሙከራው ከከሸፈ በኋላስ ልጁ አባቴ ነህ ብሎ ከቤቱ ውስጥ ይኖራል? "በህግ ልጄ ስለሆንክ የትም አትሄዳትም" ብሎ ማስገደድ ይቻላል? ቤተሰብ ልክ እንደ ሃገር የሚያስተሳስረው ፍቅርና መተሳሰብ እንጂ የህግ አንቀፅ የሚጥቅስ ግዴታ አይደለም።  የልብን እየሰሩና እንደ ባእድ እየቆጠሩ የተባበሩት መንግስታት የጣልቃ አትግቡ አንቀፅ እየጠቀሱ ገላጋይን ማስጨነቅ፣ ማዋረድ፣ ማስፈራራት፣ ግንኙነት ማቋረጥ፣ መክሰስና መውቀስ የሚያባብሰው እንጂ የሚፈታው ችግር የለም። በትግራይ ላይ የተፈፀመው ታሪክ የማይረሳው ታላቅ የወንጀል ድርጊት እንኳንና በአንቀፅ በልመናም የሚሻር አይደለም። ትግራይ በተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለችው ካርታ ላይ ብቻ ነው። እሱም ጊዜውን ጠብቆ ኢዲት ይደረጋል!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የተያያዘችው በደካማ ክር ነው። ይህ ክር የትግራይ ጥላቻ ነው። ኢትዮጵያውያን አንዳንድ ጊዜ ማምለጫ ሲፈልጉ ይታያል። በከፍተኛ የዘረኝነት የፓለቲካ ስካር ውስጥ ሆነው ትግራይን ከኢትዮጵያ ውጪ ብቻ ሳይሆን ከሌላ ፕላኔት የመጣች የኢትዮጵያ ጠላት አድርገው በዛ እንደ ዝንጅብል የተጠማዘዘ አማርኛቸው ሲራገሙ ይቆዩና የውጩ አለም ጩኽት ሲበረክትባቸው "እኛ የምንናገረው ስለ ህወሓት እንጂ ስለ ትግራይ ህዝብ አይደለም" ብለው የመጣባቸውን ውግዘት ለማለዘብ ይሞክራሉ። ስለ ሸፍጡ ትንሽ ይቆይና ስለ ህወሓት እናውራ። ማንኛውንም የፓለቲካ ድርጅት መጥፎ ሲሰራ ማውገዝ፣ በጎ ሲሰራ ማሞገስ ያለ ነገር ነው። ህወሓት የሰራችውን ስህተት ከሰራችው የገዘፈ በጎ ተግባር ጋር ጨፍልቆ "የህወሓት መር አስተዳደር የጨለማ ዘመን ነበርና ይችን የፓለቲካ ድርጅት ከምድረ ገፅ እናጥፋት" ብሎ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ሲነሳ በአለም ላይ ያልተለመደ ክስተት ነው። የዚህ ሰይጣናዊ ስሜት መንስኤውም የአስተዳደር አለመስተካከል ብቻ ሊሆን አይችልም። የእስተዳደር በደል ጥያቄ የሚኬድበት ርቀት ገደብ አለው። ሪፓብሊካን ፓርቲ ስላጠፋ ፓርቲውና አባላቱ ሁሉ ይደምሰሱ ከተባለ ከአስተዳደሩ ጉዳይ የላቀ ሌላ ችግር አለ ማለት ነው። ይህ ምን እንደሆነ ግልፅ ነው። የተጠላው የፓርቲው ድርጊት ሳይሆን አባላቱም ሁሉ ናቸው። ጥላቻው ሁሉንም የማጥፋት ፍላጎት ደረጃ ከደረሰ የዘር ጥላቻ መሆኑ አያጠያይቅም። በቲዮሪና ለውጪው አለም ፍጆታ ሲባል "ካመፀ ፓርቲ ላይ የሚወሰድ የህግ ማስከበር እርምጃ ነው" ቢባልም እርምጃ እየተወሰደ ያለው በህዝብ ህልውና ላይ ስለሆነ ዋናውን አላማ መደበቅ አይቻልም። ስለዚህ ኢትዮጵያ በእብሪት ያስተሳሰሯት ብሎኖቿን ፈታለች። አሁን የቆመችው በትግራይ ጦርነት ቀጭን ክር ነው። ያለ ድርድር በጦርነት ብቻ ከተጠናቀቀ አንድ የሚያደርጋት ሌላ ነገር ስለሌለ ጦርነቱ እንዳይጠናቀቅና ህዝብን እየማገዱ ስልጣን ላይ መቆየት ብቸኛ ምርጫ ሆኗል። ግን እስከ መቼ?

በሚገርምም በሚያሳዝንም ሁኔታ ህወሓት ጥላቻ የተደቀነባት በኢትዮጵያ በኩል ብቻ አይደለም። የስልጣን ፍላጎት ያሳወራቸው የትግራይ ተወላጅ የተቃውሞ ፓለቲከኞችም ጭፍን ጥላቻ ካለባቸው የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች ጋር አንድ መዝሙር እየተጋሩ ናቸው። ለጊዜው ውዳሴ እያገኙ ስለሆነ ነገ እነሱ ራሳቸው አንገት ውስጥ የሚገባው ገመድ ያስተዋሉት አይመስሉም። በአሁኑ ጊዜ ህወሓትን ለማግለል መሞከር ስልት የጎደለው የዋህነት ወይንም ስውር እጅ ያለበት መሰሪነት ነው። ህወሓት የመልአክነት ክንፍ ትከሻዋ ላይ ያበቀለች መልአክ ነች ማለቴ አይደለም። የትም ብትሄዱ እንዲህ ያለ ፓርቲ አታገኙም። አንድ ፓርቲ የሚገመገመው የሃይል አሰላለፍን ጠንቅቆ በመገንዘብ፣ ትንሹን ፎቶ ሳይሆን ትልቁን ስእል በማየት፣ ባለፈው ታሪክ ብቻ ላይ ተገትሮ የወደፊቱን ለመተንበይ በመሞከር አይደለም። በሰው ሃይል ጥራትም ፓርቲ አይገመገምም፣ ፓርቲ የአካደሚክ ዲፓርትመንት አይደለምና! ዋናው ቁምነገር ለተሰለፈለት አላማ ያለው ቁርጠኝነትና የሰለጠነውን የሰው ሃይል አስተባብሮ አቅም መስጠት መቻሉ ነው። እስቲ በእውነት እንነጋገር ከተባለ ህወሓት ሁሉንም ጠቅልላ እያስተዳደረች ትግራይ በሁለት እግሯ እስክትቆም ድረስ ብትቆይ የሚጎዳው ማነው? ይህ ስለሆነ ብቻ "ቆዳ ቆርቁር ወፍ ሆና ራሳችን ላይ ተቀመጠች" ብሎ በዚህ ቀውጢ ጊዜ መናገር የትግራይ  ፍቅር ነው ወይስ የራስ ፍቅር? አሁን ትግራይ ውስጥ ስልጣን መያዝ ማለት ድካም፣ መስዋእትነት፣ መንገላታት፣ ሳይተኙ ማደር፣ መራብ፣ ማለት አይደለም እንዴ? "አንተ ሁን" የሚያሰኝ እንጂ "እኔ ልሁን" የሚያስብል አይደለም። እኔ መቸም አሁን ፃድቃንን፣ ደብረፅዮንን፣ ወዲ ወረደን ሆነ ምግበይን መሆን አልመኝም። የፃፍኩት ስድብ አይምሰል፣ ምክር ነው! የህዝብ ፍላጎት ነው ወሳኙ። የህዝብን ፍላጎት ጠብቆ በአክብሮት መቀበል እንጂ ባልተሰራ የህዝብ ፍላጎት መለኪያ ቆጠራ (survey) እኛ የምንፈልገው ብቻ ነው ህዝብ የሚፈልገው እያሉ ግምት ውስጥ መግባትና መመፃደቅ፣ በዛ ላይ ተመስርቶም ህወሓትን ለምን "ነፃ አገር ትግራይ ብለሽ ካልተነፈስሽ ገደል ግቢ" እያሉ በየሚድያው ወከባ መፍጠር ለትግራይ ህዝብ ጠላቶች መድፍና ታንክ ከማቀበል የበለጠ ነው። እየተገኘ ካለው ሰፊ ድል መሃል እንዲህ ያለ አዋኪና አዘናጊ አጀንዳ አስከፍቶ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ትልቅ ግብአት ማበርከት ይቅር ሊባል አይችልም። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም "ራስ ሳይጠና ጎተና" አትሁኑ። ገና ብዙ የምትማሩበትና ለወደፊቷ ትግራይ አመራር የምትዘጋጁበት /ቤት ውስጥ እንዳላችሁ አትርሱ። የትግራይ ህዝብ ወንዝ እያቋረጠ በቅሎ አይቀይርም። ትግስት ይኑራችህ፣ በፊት በር ውጊያ ባለበት የጓሮ በር አትክፈቱ። ቤት በጅብ የሚደፈረው የቤት ውሻ አጥሩን ሲቀደው ነው።

የትግራይ ህዝብ ላይ እያነጣጠሩ "አይ መስሏችሁ ነው እንጂ የምንተኩሰው ህወሓት ላይ ነው" ይላሉ። ፀባቸው ያለው ግን ትግራይ ህዝብም ዘንድ ነው። እያመለጣቸው ይሁን ሆን ብለው ጠላታቸው ህዝቡ መሆኑን በግልፅ የተናገሩባቸው መድረኮችና ሚድያዎች አሉ። በርግጥ ትናንት የተናገሩት እየረሱ ዛሬ ተቃራኒውን እንደሚናገሩ የተለመደ ነገር ነው። ሲደመርም ሲባዛም ዋናው ነገር እንደሚከተለው ነው:- ህወሓትን ማጥፋት የሚፈልጉት የትግራይ ህዝብ ልምድ ያካበተ ጠንካራ መከታ እንዳይኖረው በመፈለግ ሲሆን፣ የትግራይን ህዝብ ማጥፋት የሚፈልጉት ደግሞ ህወሓትን ማጥፋት ቢሳካላቸው እንኳ የትግራይ ህዝብ አስር ህወሓት መፈልፈል ይችላል ብለው ስለሚያስቡ ነው። በዚህ አቅጣጫ አየነው በዛ ያለው አላማ ሁለቱንም ማጥፋት ስለሆነ "ፀረ-ህወሓት ብቻ" ፕሮፓጋንዳ እንዳንጭበረበር እንጠንቀቅ። የድል ዜና በተነገረ ቁጥር ቀበቷችንን የምናላላ ከሆነ ቀጣዩን የድል ዜና ልናዘገየው ወይንም ልናስቀረው እንችላለን። ተቃዋሚዎች ይችን የዩቲዩብ እንጀራን ከህዝብ አታስበልጧት። "የትግራይ ሰራዊት አባላት ምን እየበሉ ነው ዶሽቃ ተሸክመው መቶ ኪሎሜትር በሰአታት የሚጓዙት" ብሎ ማሰብና መጨነቅ ነው የጤናማ አስተሳሰብ አንኳሩ። ሶፋ ላይ ተቀምጦ ሶዳ እየተጎነጩ የትግራይ ሰራዊት ማን እንደሚመራው መፈላሰፍና ከዛ አልፎም ጤነኛ የሆነውን የትግራይ ሚድያ መበከል ሃላፊነት የጎደለው የግዴለሽነትና የራስ ወዳድነት ተግባር ነው። በዚህ ቀውጢ ያለየለት ጊዜ፣ ጠላት መቐለን ለመቆጣጠር ተንደርድሮ በነበረበት አስጊ ወቅት ስለፓለቲካ ልዩነት በአለም አደባባይ ወጥቶ ዝናን ለማትረፍ መሞከር ክህደት ነው። በአንዳንድ ያልበሰሉ ተጋሩ ፓለቲከኞችና አክቲቪስቶች የተነሳ ወሳኝ የህልውና ማስከበር ስራ የሚሰሩ ጦር አዛዦችና ፕሬዚደንቱ ራሳቸው መግለጫ መስጠት ተገደዋል። መሪዎቻችንን ስራ ማስፈታት አለብን? ስለ መከላከል ትግሉ ያውሩ ወይስ ወንበር ላይ ተቀምጠን ስለምንለቀው በታኝ ትርክት?

Back to Front Page