Back to Front Page

ምክር ለአማራ ልሂቃን:- ሃቁን ዋጡና ለራሳችሁም ለሌላውም ሰላም ስጡ

ምክር ለአማራ ልሂቃን:- ሃቁን ዋጡና ለራሳችሁም ለሌላውም ሰላም ስጡ

ኻልአዩ አብርሃ 08-16-21

የገዢና ተገዢ ግንኙነት በመልካም ስሜት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በገዢዎች በኩል በተገዢዎች ላይ በሚጣለው አስገዳጅነት ነው። በሬ ሰው ቢሆን በዝምታ ቀንበር አንገቱ ላይ አይሸከምም። ፈጣሪያችን በሬ ሰውን እንዲያገለግል አድርጎ ፈጥሮታልና በዝምታ ይገዛል። በሰዎች ዘንድ ግን አምላክ ለባርነት፣ ለበታችነት፣ ለድህነት፣ ለበደል፣ ለውርደት ብሎ የፈጠረው የለም። በአርአያ ስላሴ ሰውን ፈጥሮና እኩል አድርጎ ነው ወደ ምድር የላከው። ሲልከው ራቁቱን ሲመልሰውም ራቁቱን ነው። ገዢ የሚሆነው ወርቅ ለብሶ አይወለድ፣ ወርቅ እንደለበሰም አይሄድ። ስለዚህ ላይና ታች፣ ገዢና ተገዢ መሆን የአምላክ ፈቃድ ሳይሆን ሰው ህገ አምላክን ሽሮ የሚፈፅመው ሃጥያት ነው። ምድራችን እንድታምርና አምላክም ደስ እንዲለው መልክአ ምድሩን፣ የዱር አራዊቱን፣ እፀዋቱን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ዘርን አይነቱ የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል። በተለይም የሰው ልጅን የተለያየ ቋንቋ፣ የተለያየ ቀለም፣ የተለያየ ባህል፣ የተለያየ የአስተዳደር ወግና ስርአት እንዲኖረው ሲፈቅድ የየራሱን ባህርያት አቅቦ በእኩልነት እንዲኖር እንጂ አንዱ ተነስቶ "የኔ ቋንቋና ባህል የበላይ ነው፣ ሁሉም የራሳቸውን ትተውና የኔን ወግና ስርአት ተቀብለው ተገዢ ይሁኑ" የሚል ካለ የዘላለም እሳት ውስጥ እንደሚገባ ለፍጡራን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነው።

በጊዜ ሂደት ግን ሰርቶም ሆነ ቀምቶ ሃብት ያፈራና ጉልበት ያካበተ ሁሉ በሌላው ላይ የበላይ ልሁን እያለ፣ ይህን ሰሜቱንና ድርጊቱንም ከትውልድ ወደ ትውልድ እያስተላለፈ፣ በጥቅም ተጋሪና ህገ አምላክን የሻሩ የሃይማኖት መሪዎች ድጋፍና ቡራኬ እየተጠናከረ የሌላውን ህዝብ ቋንቋ፣ ባህልና የአስተዳደር ስርአት ጨፍልቆ በባርነት ይገዛል። ይህ የበደል ስርአት በመላ አለም በየዘመናቱ ተንሰራፍቶ የኖረ ቢሆንም የሰው ልጅ እውቀቱ እየሰፋ፣ ጥበቡ እየመጠቀ በሄደ ቁጥር ከጅምሩም ቢሆን የፈጣሪ ፈቃድ የነበረውን እኩልነት እየተገነዘበ፣ አለማችንን ከጭቆናና ባርነት ለማላቀቅ ትግል እየተደረገ፣ ከጥቂት የአለም ክፍሎች በስተቀር ሃቀኛ እኩልነት ከሞላ ጎደል ሰፍኗል። አንዱ በሌላው ላይ የያዘውን የበላይነቱን ተፈጥሯዊ እንደሆነ አድርጎ በማሰብ ለእኩልነት የሚደረገውን ትግል በአምላክ ፈቃድ ላይ የተነሳ ሰይፍ አድርጎ የሚቆጥር ማህበረሰብ ካለባቸው ጥቂት የአለም አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ይቺ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት እየተባለች ስትሞካሽ የኖረችው አገር "ውስጡን ለቄስ" ሆና አንዱ ህዝብ ከሌላው ህዝብ ያነሰ ተደርጎ በመቆጠሩ ጭቆናና ግፍ የሰፈነባት የባርነት አምባ ሆና መኖሯን የሚገነዘብ የሌላው አለም ህዝብ ብዛት ያለው አይደለም። ከዛ በፊት የነበረው አቢሲኒያ ውስጥ የትግራይና የአማራ፣ የአማራና አማራ ፉክክርና ድርድር ወደ ጎን እንተወውና 19ኛው ክፍለዘመን መገባደጃ ጀምሮ በሚኒሊክ የአማራ ተስፋፊነት ፓሊሲ መሰረት በሃይልም፣ በማስፈራራትም የራሳቸው የተከበረ ቋንቋ፣ ወግ-ባህል፣ የአስተዳደር ዘይቤና፣ የእምነት ስርአት ያላቸው በደቡብ፣ በምእራብና በምስራቅ የኖሩትን ከመቶ ያላነሱ ህዝቦች ኢትዮጵያ ከተሰኘችና አማርኛን የበላይ ቋንቋ፣ የአማራ ባህልና ሃይማኖትን የአምላክ ዋናው ምርጫ ባደረገ የጭቆናና የተፈጥሮ ሃብት በዝባዥ በሆነ የአስተዳደር ስርአት ስር ወደቁ። በጊዜ ሂደት ይህ ህዝቦችን ወደ አንድ ቅርጫት የመሰብሰብ አካሄድ "ኢትዮጵያዊነት በአማራነት" የሚል በስውርም በይፋም በሚተገበር ፓሊሲ በጉልበትም፣ በማታለልም፣ በማዋረድም፣ ህዝቦቹ የራሳቸውን ተፀይፈው ወይንም አፍረውበት የአማራ ባህልንና የኑሮ ዘይቤን ተክተው እንዲኖሩ ተደርገዋል። የነበረው የአእምሮ እጥበት ምን ያህል ጠንካራ እንደነበር ከሚያመለክቱት እልፍ መገለጫዎች አንዱ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው በቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ የገባ ኦሮሞ ሆነ ወላይታ፣ ሌሎችም፣ ቋንቋቸውን መጠቀም

Videos From Around The World

ይፈሩ ወይንም ያፍሩ እንደነበረ ለትውልዶች የሚተላለፍ ታሪክ ነው። የተጫነው የበታችነት ስሜትና የአማርኛ የበላይነት ክትባት በገበሬው ዘንድ ብቻ ሳይሆን በተማረውም ዘንድ እንደነበር የሚያረጋግጥ ጥቁር ታሪክ ነው። በአማራና አማርኛ የበላይነት ስሜት ያበዱ አንድ የዩኒቨርሲቲው የአማርኛ መምህር በተማሪዎች ስም ግሬድ ይሰጡ ነበር እየተባለ እንደቀልድ ይወራል። ፈይሳና ሓጎስ ኤፍ ሲያገኙ፣ እነ አንዳርጋቸው ሲሰጣቸው ነበር አሉ። እውነት ሊሆን ይችላል! ለዚህም ይሆናል ዩኒቨርሲቲው የአማራ ትምክህተኛ ምሁራን መናሃርያ የሆነው።

በሌሎች ህዝቦች ላይ ሰፍኖ የኖረው የአንድ ቋንቋና ባህል የበላይነት የራሱ የሆነ ባለ ሶስት ቀለም ልሙጥ ባንዴራ ብቻ ሳይሆን የራሱ የሆነ አምላክም እንዳለው በሰፊው ይነገራል። ይህ አምላክ ግን የአማራ አምላክ ሳይሆን የሚባለው "የኢትዮጵያ አምላክ" ነው። አማራ ከመቶ ያላነሰውን ሌላውን ህዝብ ቀላቅሎ አማራ እንዲሆን ካደረገ በኋላ ስም ያወጣለት ኢትዮጵያ ብሎ ነው። በውስጠ ታዋቂ ኢትዮጵያ ማለት አማራ ማለት ነው። ይህን ሚስጥር የሚያውቅ አማራ የሆነችውን ኢትዮጵያን አልቀበልም ሲል "የኢትዮጵያ ጠላት" ተብሎ ይፈረጃል። ሃቁ ግን ወዲህ ነው። እየተጠላ ያለው "ኢትዮጵያነት በአማራነት" እንጂ "ኢትዮጵያዊነት በእኩልነት" አይደለም። በእኩልነት ከሆነማ አለም አንዲት አገር ብትሆን ማን ይጠላል? ከመለያየት እኮ ህብረት ይበልጣል! ህብረቱ በአንዱ የበላይነት ከሆነ ግን እንኳን በአገር ደረጃ በወረዳም ደረጃ ተቀባይነት የለውም።

የአማራ የአስተዳደር የበላይነት ብቻ ሳይሆን ድጋፍ ሰጪ የሆነው የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት የበላይነትም ጭምር ያካተተ ነበር ሲባል አማራ የተባለ ሁሉ ገዢና ከበርቴ፣ ግፍ ሰሪ፣ ቀማኛና ገዳይ ነበረ ማለት አይደለም። በሸዋ እስከ ጎንደር ድረስ የበሬ ግንባር የምታክለውን መሬቱን እያረሰ በችጋር የኖረው የአማራ ህዝብ ቤቱ ይቁጠረው። ይህ ድህነቱንም ለትውልድ አውርሶታል። ድህነት የወረሰው የአማራ ትውልድም በሚያሳዝን ሁኔታ በድሮ ስርአት ናፋቂዎች እየተገፋ በከንቱ የጥይትና ቦምብ እራት እየሆነ ነው። በሚኒሊክ ዘመን የተወረሩትና በኃይለስላሴ ዘመን የጭቆናው ቀንበር የከበደባቸው ህዝቦች በዳያቸውና ገዳያቸው አማርኛ የሚናገርና የእነሱ ቋንቋ እየተናገረ የሚተባበር፣ እንዲሁም ባንዴራ እያውለበለቡ መስቀልና ፀናፅል ይዘው የመጡባቸው አማሮች ባህላቸውን ማጥፋት፣ ስማቸውን መቀየር፣ አስፀያፊ ስድብ መሳደብ ብቻ ሳይሆን መሬታቸውን ቀምተው በገዛ ቀያቸው ባይተዋር ስላደረጓቸው ይህ ጨቋኝና በዝባዥ ስርአት የአማራ ስርአት ተሰኝቷል። ይህ ብዙዎቹ የአማራ ልሂቃን ሆዳቸው ሃቁን እያወቀ በአደባባይ ግን ይክዱታል። "የአማራ የበላይነት የሚባል አልነበረም" ይላሉ። እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? "አውቆ የተኛ ቢረግጡት አይነቃም" ነው። ይህ ስርአት የትግራይ ህዝብ ባካሄደው ረዥምና መራራ ትግል ተውግዶ የእኩልነት ስርአት ለሶስት አስር አመታት ሰፍኖ ነበር። ደርግ ፊዩዳሊዝምን እንደ ኢኮኖሚያዊ ስርአት ቢያስወግድም የኖረውን የፓለቲካና ማህበራዊ ስርአቱን በአሃዳዊ አስተዳደር ጠብቆ አቆይቶታል። በሶሻሊዝም ስም የራስ ገዝ እያለ የብሄሮችን የራስ-አስተዳደር ጥያቄና የብሄር ትግሎችን ለማምከን ተጠቅሞበታል። 1977 የኢትዮጵያ ካርታ ላይ ትግራይን ቆራርጦ ጉንዳን እንዳሳከላት እናያለን። ስለዚህ የብሄር ጭቆና በህግ የተወገደውና ፍፁም ባይሆንም የራስ- አስተዳደር መሰረት የተጣለው በኢህአዲግ-መር የሽግግር መንግስት ነው። በደርግ ዘመን መንግስታዊ ስርአቱን ተቆጣጥረው የዘለቁት የአማራ ልሂቃን ከሽግግሩ መንግስት ጋር በመተባበር በበጎ መንፈስ እኩልነትን የሚያሰፍን ህገመንግስት ለመቅረፅ ፈቃደኞች አልነበሩም። የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነትና የራስ-አስተዳደር ዋስትና የሚሰጠውና መቶ አመት የዘለቀው አሃዳዊ የአንድ ብሄር የጭቆና ስርአት ታሪክ የሚያደርገውን ህገ መንግስት በአማራ ህልውና ላይ እንደመጣ ጠላት አድርገው ቆጠሩት። አንድ ህዝብ "የበላይ ካልሆንኩኝ" ህልውናየ ይጠፋል ብሎ እንዴት ያስባል? ከመቶ ብሄር ብሄረሰብ ተለይቶ አማራ ከጠፋ ኢትዮጵያ ትጠፋለች ማለትስ ነውር አይደለም እንዴ? ይህ ማለት በግልባጩ ሲታይ "ቀሪው 99 ብሄር ብሄረሰብ ቢጨፈለቅም አማራ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ምንም አትሆንም" ነው። "ቀሪው ብሄር ብሄረሰብ ለኢትዮጵያ ቁጥር ማብዣና ለአማራ ጌጥ መሆኑ እንጂ ለኢትዮጵያ ህልውና ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል" እየተባለ መሆኑ ነው በውስጠ ወይራ። በነገራችን ላይ የአማራ ልሂቃን ስለ ዴሞክራሲና እኩልነት ማውራት አይወዱም። በየሚድያውና የድርጅት መግለጫው የሚተረከው ስለ ፊዩዳሊዝምና የአማራ ነገስታት ስለ ፈፀሟቸው ትልቅም ትንሽም ድርጊቶች እንባ ቀረሽ ናፍቆት እንጂ ኢትዮጵያ ህዝቦቿን እንደየ ባህላቸውና ስሜታቸው አቅፋ በእኩልነትና ዴሞክራሲ ለወደፊት እንድትገሰግስ የሚመኙ አይደሉም። የአማራ ልሂቃን አንገት የዞረው ወደኋሊት። የአሜሪካ ሆሊውድ የነገስታትን ታሪክ ፊልም እየሰራ ብር ያፍስበታል እንጂ የፓለቲካ መመሪያው አድርጎ ነጩ ቤተ መንግስት ውስጥ አላስገባውም።

ባለፉት ሶስት አመታት የፌደራሊዝም ቁንጮ ሆኖ አገሪቱን በማረጋጋት ወደ እድገት ጎዳና የወሰዳትን የኢህአዲግ መንግስት በወከባ አስወግደው ካበቁ በኋላ ህገ መንግስቱን አፍርሰው የተቀበረውን አሃዳዊነት ሊያሰፍኑ ሲታገሉ የኛ ናት የሚሏት ኢትዮጵያን በእልክ ሊያፈራርሷት ነው። "እኛ በበላይነት የምንመራትና አንድ ወጥ የሆነች ኢትዮጵያ ካልሆነች በፌደራሊዝም አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያ ድራሿ ትጥፋ" ብለዋል። ይህን ግን በተዘዋዋሪ እንጂ ቀጥታ የሚናገሩት አይደለም። ለፌደራሊዝም የቆሙትን ሃይሎች በአገር አፍራሽነት በመወንጀልና ተንኮሉ ያልዞረለት ኢትዮጵያዊ በአገር ፍቅር ቅስቀሳ በማነሳሳት ነው። በትግራይና በኦሮሚያ ኢትዮጵያን ለማዳን በሚል ውሸት ተገፍቶ ሄዶ የሚሞተው ንፁህ ዜጋ በኢትዮጵያ ስም የተጎነጎነው ሴራ ሳይገባው ህይወቱ እያለፈ ነው። የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የአገው፣ የቅማንት፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል፣ የጋምቤላ ታጋዮች አንዳቸውም ኢትዮጵያን የማፍረስ አላማ የላቸውም። የማን ጩኸት ጎልቶ ይሰማል ከተባለ ግልፅ ነው፣ መንግስትን የያዘው ሃይል ጩኽት ነው። ኢትዮጵያን የሚመለከት ሃቅ ያለው ግን ለእኩልነት በሚታገሉት እጅ ነው። ይህ የራስን ስልጣን ለማዳን የሚደረግን ትግል የአገርን ቀለም ቀብቶ በአገር ስሜት ህዝብን ማሳበድ የተለመደ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃ ነው። በናዚ የተመራችው ጀርመን የአውሮፓ አገሮችን ወራ ህዝቡን ስታሰቃይና ስትፈጅ ቆይታ 50 ሚልዮን የአለም ህዝብ በጦርነት እሳት እንዲያልቅ አደረገች። የመረረው አለም የጀርመንን ጦር እያሳደደ ወደ በርሊን ገሰገሰ። በዚህ ጊዜ የናዚ ጀርመን የፕሮፓጋንዳ አለቃ ጆሴፍ ጎቤልስ የተናገረው ንግግር ለታሪክ በቅቷል። እንዲህም አለ: "ጠላት የጀርመንን ምድር እንዳይረግጥ እስከ መጨረሻ ትንፋሻችን እንዋደቃለን፣ ወጣቶችና አዛውንትም ሳትቀሩ ተነሱና አባት አገርራችሁን አድኑ" የጀርመን ህዝብ ከተሞቹ ድምጥማጣቸው እስኪጠፋ ድረስ ተዋጋ። ናዚን አሸንፎ የገባው አሜሪካ ጀርመንን አጠፋት? ምን ያጠፋታል አለማት እንጂ ዶላሩን እየመዘዘ! ህወሓት-ኢህአዲግ ደርግን አሸንፋ ስትገሰግስ መንግስቱ ሃይለማሪያም ኢትዮጵያውያንን "አገራችሁን የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነው ወያኔ ታደጓት" እያለ ስንቱን ምስኪን ህዝብ ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳርጎት ሃራሬ ቤተ መንግስት የመሰለ ቤት ገዝቶ እየኖረ ነው። እነ ሂትለርስ ምንም ክፉዎች ቢሆኑ ቃላቸውን ጠብቀው ራሳቸውን ነው ያጠፉት። የህዝባቸውን መሉ ድጋፍ አግኝተው ፍትሃዊውን የእኩልነት ስርአት ለመመለስ እየተዋጉ ያሉትን የትግራይና የኦሮሞ ሃይሎችን "ኢትዮጵያን ለማፍረስ" ነው የሚገሰግሱት በሚል ውንጀላ የህዝቡን ሆድ እያባቡት ነው። አገሪቱን የጦርነት ኢኮኖሚ ስላሰፈኑባት ህዝብ ኑሮው ቁልቁል እየወረደ ነው። ጃል መሮና ደብረፅዮን አዲስ አበባ ገብተው አገሪቱን በግሬደር የሚያፈርሷት አይነት የሚመስል ሽብር እየተነዛ ነው። በማን? በአማራ ልሂቃን! ለምን? የድሮው አገዛዝ ካልተመለሰ ህዝቡ እርስ በርሱ ይፋጅና አገሪቱ ትጥፋ ነው። ይህን አስተሳሰባቸውን ማን ላይ ነው የሚለጥፉት? በህወሓት ላይ! ለህዝብ እየተነገረ ያለው ተንኮል ያዘለ ቅስቀሳ:-"ህወሓት የበፊቱ ስልጣኔን መልሼ ካልጨበጥኩ ኢትዮጵያ ትፍረስ ብላ ነው የተነሳችው" ነው እየተባለ ያለው። የኢትዮጵያ የትምክህት ፓለቲከኞችና በውሸት ትርክትና በውሸት ዜና የደነዘዘው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግራይ ውስጥ የተፈፀመው አለምን ጉድ ያሰኘ ግፍ "አላየሁም አልሰማሁም" ብሏል። "የትግራይ ሰራዊት እየገሰገሰ ያለው ስልጣን መልሶ ለመያዝ ነው" ተብሎ ተተርጉሞበታል። መሪዎቻቸው ትግራይን እንዲህ አድርገው ሲያወድሟት ድምፃቸው የጠፋው ወይንም ደስታቸውን የገለፁት ኢትዮጵያውያንን ለማስተዳደር የትግራይ ሰራዊት የሚገሰግስበት ምክንያት የለውም። እየገሰገሰ ያለው ያጎሳቆሉትና የፈጁትን ለመቅጣት ብቻ ነው። የትግራይ መሪዎች ህዝባቸውን ከማጥፋት ወደ ኋላ ያላለውን ህዝብ ከሚያስተዳድር ራሳቸውን ቢያጠፉ ይመርጣሉ።

የአማራ ልሂቃን ከዘመኑ ጋር ቢራመዱና ሃቁን ተቀብለው በድሮ በሬ ለማረስ ባይሞክሩ ይመከራል። ከምር ኢትዮጵያን የሚወዱ ከሆነ ፍላጎቷን ማክበር ነው። ኢትዮጵያ መኖር የምትችለው የአማራ ሆና ሌላውን ደፍጥጣ ሳይሆን
በእኩልነት ብቻ ነው። አማራ ክልል ብቻ የሚውለበለብ ልሙጥ ባንዴራ ይዞ "ኢትዮጵያ!" እያሉ ማቅራራት ለማንም አይበጅም። ሁሉም ቤት እሳት አለና፣ ብሄር ብሄረሰቦች መብታቸውን በሚገባ አውቀዋልና፣ ካለው የእኩልነት አንድነት ወደ ድሮው የጭቆና አንድነት ለመመለስ ከቶ አያስቡምና የአማራ ልሂቃን ከእውነታው ጋር ታርቃችሁ፣ ጭፍን የመሃይም ህልመኛነታችሁ የጋራ ጉዳት እንዳያስከትል በፍጥነት መስተካከል ያስፈልጋችኋል። የምትሰሩት የሞተውን ስርአት በጩኸትና በግርግር በኢትዮጵያ ህልውና ስም ለመመለስ ነው። ቅስቀሳችሁም ስልት የጎደለው ነው። "ኢትዮጵያ አማራ ናት፣ አማራም ኢትዮጵያ" እያሉ አደባባይ ላይ በማስተጋባት ሌሎች ህዝቦችን ኢትዮጵያዊ ማድረግ አትችሉም። የንብ ቀፎን በመርገጥ ንቦቹን እያስቆጡ በሰላም ማር መቁረጥ አይቻልም። ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያ የናንተ ብቻ አለመሆንዋን ማመን ያስፈልጋል። የኛ ናት በምትሏት ኢትዮጵያ ውስጥ በባርነት መኖር የሚፈልግ ህዝብ የለም። ከአደገኛው ቅዠታዊ ህልማችሁ ንቁ! የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንም ለቀቅ አድርጓት፣ የትምክህት ፓለቲካ ማራመጃ አታድርጓት። እንደ ዳንኤል ክብረት ያሉ "አስር አስር ቦምብ በየከተማው ጥለው ትግራይን ለማጥፋት" የሚመኙት ዲያቆኖቻችሁም መአርጋቸውን ግፈፉ። "ኢትዮጵያ የማይታይ ጦር አላት" እያሉ እግዚአብሄርን የነሱ ታጣቂ በማድረግ እምነት የሚያረክሱት የሃይማኖት መሪዎች አስወግዱ። ሃቅን ተቀብሎ በእኩልነት አብሮ መኖር የተቀደሰ አስተሳሰብ ነው። ይህን ሃቅ ሽሮ የአምላክን ሃይል ተጠቅሞ የአማራ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር መታገል የሃጥያቶች ሁሉ እናት ነው። እኩልነት በተሻረ ቁጥር የሚመጣባቸውን የነፃነት ትግል "የኢትዮጵያ አምላክ ይመልሰዋል" እያሉ መመፃደቅ አምላክ የፈጠረውና የሚጠብቀው የአማራይቱን ኢትዮጵያን ብቻ ነው እንደማለት ነው። የሚገርመው ነገር ግን አምላክን ቀድመው ያወቁት ትግራዮች መሆናቸውን መዘንጋታቸው ነው። ሆኖም ግን የአክሱም ስልጣኔ የአማራ ነው፣ ላሊበላም የአማራ ነው ስለሚሉ እግዚአብሄርን በሞኖፓል ይዘውታል። "የኢትዮጵያ አምላክ" ስለሚባለው አጉል ብልጠት ሳስብ አንድ ደቡብ ኮርያዊ ወዳጄ የነገረኝን አስታወሰኝ።  አንድ ቀን "ሃይማኖትህ ምንድነው?" ብየ ስጠይቀው "ካቶሊክ ነበርኩ፣ ግን ተውኩት" ብሎ መለሰልኝ። "ለምን?" ብለው እንዲህ ብሎ ምክንያቱን አብራራልኝ:- "የማመልከው የእስራኤል አምላክ መሆኑ እየተነገረኝ ነበር፣ የማነበው ቅዱስ ታሪክም የእስራኤላውያን ብቻ ነው፣ የኮርያ አምላክ እስኪፈጠር ድረስ ወጥቼ ልቆይ ብየ ነው" ይህ ሃይማኖትን መጋፋት ይመስላል ግን ሃቅ ነው። አምላክን ለአንድ ህዝብ ብቻ በንብረትነት መመደብ የዲያብሎስ ተግባር ነው። የአማራ ልሂቃንና የሃይማኖት መሪዎች ለፓለቲካ ፍጆታቸውና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የአማራን ህዝብ በሃጥያት መንገድ እየመሩት ነው። አምላክ የሁሉም ነው! አምላክ የምድር ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርስም ጌታ ነው! "ለሃጥአን የወረደ መአት ለፃድቃን ይተርፋል" ተብሏልና ከዚህ ራስን ማግለል ያስፈልጋል። ሰሞኑን ታዋቂው የትግራይ ሚድያ ሃውስ ጋዜጠኛ ስታሊን ገብረስላሴ አድማጮችን የጠየቀው ጥያቄ እንዲህ ይላል:- "የኢትዮጵያ አምላክ ስሙ ማን ይባላል?" (ሳቅ በሳቅ!) እድሜ ይስጥህ ስታሊን ይህን ነገር እንዴት እንደምገልፀው ግራ እየገባኝ ነበር። የኢትዮጵያ አምላክ ለብቻዋ ሊኖራት ስለማይችል ይህ አምላክ የተባለው ሰው ይሆን ይሆናል። ስሙ ማን ይሆንእንገምት እስቲ:- ሚኒሊክ? ታማኝ? አገኘሁ? ዳንኤል? "ዶር" ቴዲ አፍሮ? መሳይ? በቃኝ!

Back to Front Page