Back to Front Page

የአብይ አህመድ የጨነገፈ አመራር፤

 

የአብይ  አህመድ የጨነገፈ አመራር፤

ከባለ አገሩ 1-5-22

  የአብይ አሕመድ  የከሸፈበት  አመራር በሚል  ርዕስ ለአንባባያን  ባደረስኩት  አጭር ማስታወሻ  አብይ አህመድ የአገር እዳ ሸክምና ጋሬጣ መሆኑን ለማሳየት ሙከራ አድርጌ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት  አቶ ልደቱ አያሌው  አብይ አህመድ  ለአገራችን ብሄራዊ ስጋትና አደጋ መሆኑን  ሲናገሩ  ተደምጠዋል ፡፡ ከአቶ ልደቱ ጋር በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ያለን ቢሆንም የአብይ በስልጣን መቆየት  ለህዝቦች አንድነትና ለአገር ህልውና  ትልቅ እንቅፋት መሆኑን  ሁለታችንንም  የሚያግባባ  ሃሳብ   ነው ፡፡ አብይ የጨነገፈ አመራር ብቻ ሳይሆን  ወደ ካንሰር የተቀየረ የማይድን ሃገራዊ ነቀርሳ ሆኗል ፡፡ ሰሙኑን ደግሞ አብይ ራሱ  ድንቁርና  በተመለከተ በምፀት  ሲነጋር  ተደምጠዋል ፡፡ በድንቁሩና አገር በማፍረስ ላይ መሆኑን ነግሮናል፡፡ ዶ/ር ቢኒያም ተወልደም በአብይ ጎራ ስላለው ፍርሃት የወለደው ጭንቀትአገር በማፍረስ ላይ መሆኑን   ተናግሯል ፡፡  ኢሳያስ አፈወርቂን በጥሩ  ተምሳሌትነት የምታሞግስ ኢትዮጵያ የአብይ ኢትዮጵያ ናት ፡፡  በአፍሪካ  አብይ አህመድን ያህል  ከአለም ከአገሩ ህዝብም  የተገለለ መሪ የለም ፡፡  ራሱ ያፈረሳትን  ኢትዮጵያ እናድን በሚል ለማጭበርበር ቢሞክርም የነጋበት ጅብ ሆኗል ፡፡ አብዛኛው  ሰው በዝምታ  ተሸብቦ   ውስጡ በግኗል ፡፡ ተክፍሏቸው ለሰልፍ በወጡ ፈረሰኞች  የሚጠገን ፖለቲካ  የለም ፡፡   የጨነገፈ መሪ ማለት በጨነገፈች ላም የሚመሰል ነው ፡፡

Videos From Around The World

የአብይ መንግስት ከአለም ማህበረሰብ የተገለለ  መሪ ስለመሆኑ የሚያከራክር  አይደለም፡፡ በአገር ቤት ከተገለለ ቆይቷል፡፡ አለም አቀፉ ማሕበረሰብም  ወንጀለኛ አይፈልግም  ፡፡    የሰው ህይወት የቀጠፈ  የአገር ምሰሶ ዋልታና ማገር ያፈረሰ  መሪ  ለመሸከም የሚችል ዜጋ የለም ፡፡ የአብይ  መንግስት ከበሰበሰ እንቁላል ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ በመጀመሪያ ህይወት የለውም፡፡  ህይወት የሌለው ፤ የነገ ተስፋው  የሞተ፤ ብዙሃን ወገኖችን መቀመቅ የሚከት አመራር ነው፡፡ መደመር የሚለው የተወረወረልን ቃልም  በመርዝ የተለወሰ ማር  ነው ፡፡ የዲሞክራሲ ተቃራኒ ነው፡፡  አብይ  የፖለቲካ ልዩነትን ማስተናገድ አይፈልግም ፡፡ ብዙ ሰው መደመር ሳይገባው ስለመደመር  አውርቷል ፡፡ መደመር ማለት በማር የተለወሰ መርዝ ቃል መሆኑ የገባው ከአመታት በኋላ  ነው ፡፡  ሁሉም  የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብይ ስር እንዲሰባሰቡ ታቅዶ የተመረጠ ማማለያ ቃል ነው ፡፡ ተደመረ የሚባለው ፓርቲ ከአብይ ስር ሆኖ የሚሰራ እንጂ ራሱን ችሎ የፖለቲካ ማንነቱን ጠብቆ በፖለቲካ ምህዳሩ ለመሳተፍ የሚሞክር በጠላትነት የሚፈረጅ ነው ፡፡፡ የአገራችን የችግር ምንጭ  ሁሉንም በአንድ ሰው ስልጣን ስር የመጠቅለል  ነው፡፡   

በአገራችን   የተቀጣጠለው የጥፋት  ጦርነትም የአብይ ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡  ከዲሞክራሲ ሂደ ት  ጋር ለመጋጨት የቆረጠ መሪ ነው ፡፡  በሰላማዊ ድርድር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ  ወደ ወረራ የገባው  ድርድር ከመደመር እሳቤ ጋር ስለሚጋጭ ነው ፡፡ መደመር በእኩልነት መነጋገርን አይፈቅድም፡፡ አሁንም የአገሪቱን ችግሮች በሰላማዊ ድርድር  ለመፍታት  የፖለቲካ  ሁኔታው የሚፈቅድ አይደለም  ፡፡ከትግራይ ጋር  የተፈጠረው ችግር  የጠቅላይነት ችግር ነው፡፡ 

 አብይ አህመድ ትግራይን  በማሰይጠን  የትግራይ ልሂቃንን በቀላሉ ማፍረስ ወይም ማስወገድ ይቻላል በሚል ትእቢት ተነሳስቶ ሰላም የነበረውን  የትግራይ  ሰማይ  በጦርነት በክሎታል፡፡  

 ይህ  ችግር ትግራይ ላይ ዘረኝነት በመቀስቀስ የሚፈታ አይደለም ፡፡ አብይ መወገድ አለበት ፡፡ የእናቱ ህልም ከኢትዮጵያውያን የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ አልሄደም ፡፡  የኢትዮጵዊያን ፍላጎት  ዲሞክራሲና ያልተሸራረፈ ነፃነት ነው፡፡

 በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት  በትግራይ ህዝብና በማእከላዊው መንግስት መካከል የሚካሄድ ብቻ የሚመስለው ጥቂት አይደለም ፡፡  የኢትዮጵያ ሚድያዎችና የመንግስት  ባለስልጣናትም ጭምር  ጦርነቱ  በመንግስትና  በትግራይ ህዝብ መካካል እንደሆነ  ለማሳመን ከመጠን በላይ ሲወቅጡት ይሰማል፡፡ የሰሜን  ጎንደር  የሚሊሻ  መሪ የነበረው  አገኘሁ ተሻገር  የትግራይ ህዝብ  የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች  ጠላት ነው ብሎ ሲናገርም  ተሰምተዋል ፡፡ ለትግራይ ያልተሰጠ ምድራዊና ሰማያዊ ሰይጣናዊ ቃል የለም፡፡ አማርኛ በዚህ ደረጃ ብዙ ስድቦች እንዳሉትም ተምረናል ፡፡ ምድር ላይ ያለ እውነታ ግና ከዚህ የተለየ ነው ፡፡ በመጀመሪያ አብይ አህመድ በመደመር ሽፋን  የፖለቲካ ስልጣኑን  ለማጠናከር  ጠንካራ ፍላጎት አለው፡፡ የሚገዳደሩትና  አንጻራዊ ነፃነት  ያላቸው  ተቋማትን ማየት ያስፈራዋል ፡፡ በህገ መንግስቱ የተቀመጠው የክልሎች ስልጣን ያስፈራዋል ፡፡ ሁሉም በምኒሊክ ቤተመንግስት ስር እንዲሰባሰብ አድርጓል ፡፡ በዚህ ምክንያት አብይ  ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች  ጋር የታወጀና   ያልታወጀ ወረራ  ፈፅሟል  ፡፡

  የአብይ አህመድ  የመጀመርያ  ጦርነት  ከኦሮሞ ህዝብና ወጣቶች ጋር ነበር ፡፡  አብይ አህመድ  ወደ ስልጣን የመጣው  የኦሮሞ ወጣቶች የዲሞክራሲ  ትግልን  በመንጠቅ ነበር፡፡ የኦሮሞ ወጣቶችና ታጋዮች የታገሉት ጥሩ ኦሮምኛ የሚናገር  ሰው  ወደ ስልጣን ለማምጣት አልነበረም ፡፡ የወጣቶቹ  ጥያቄ  አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር ነበር ፡፡ ወጣቶቹ  ትግላቸው በጭልፊት እንደሚነጠቁ  አልገመቱም ፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ሆነና   ቄሮዎች የመጀመርያ  የአብይ  ክፋትና እመቃ ሰለባ በመሆን  ለግድያ፤ ለእስርና ለስደት ተዳረጉ፡፡ በአገራችን የህዝብ ትግል በዚህ መልኩ ሲነጠቅ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ደርግም በዚህ መልኩ  የህዝብ ትግል ውጤት ነጥቋል ፡፡ የህዝብ ትግል ሲነጠቅ ደግሞ የሚጠናቀቀው  በፍጅትና በእመቃ ነው ፡፡ የነጻነት ትንታግ ፈንጥቃ  የነበረችው ኦሮምያ  ታይቶ ወደ ማይታወቅ  ድቅድቅ  ጽልመት ተደፈቀች፡፡ ብዙዎቹ  የኦሮሞ ልሂቃንም የአብይነረ እርጥባን ሲቀላውጡ  ህዝባዊ ትግሉን ኣሳልፈው ሰጥተዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ትግል ከወትሮው በተለየ በወጣት ታጋዮች ሊመራ ግድ ሆኗል ፡፡የአሁኑ ታጋዮች  የኦሮሞን  ህዝባዊ ትግል ለድርድር እንደማያቀርቡትና  የታላላቆቻቸውን ስህተት እንደማይደግሙት  ቃል በመግባት ትግላቸውን በማካሄድ ላይ ናቸው ፡፡  የአብይ መንግስት ግን የኦሮሞ ህዝብ  የሚያካሂደው ትግል  በሚድያ እንዳይነገር  ትእዛዝ  በማስተላለፉ   ቄሮዎች  ወደ ትግሉ እንዳይቀላቀሉ እንቅፋት ለመፍጠር ሲታትር ይታያል ፡ ፡  የጨነገፈበት አብይ   አረመኔያዊ ጭካኔ የተለማመደው በምእራብ ወለጋና በቤኒሻንጉል ህዝቦች  ነበር፡፡ በጉሙዝ ህዝብላይ  የደረሰው በደል ለሰሚው የሚዘገንን ነው ፡፡  በጅምላ የተገደሉት እንዃ በወጉ  የመቀበር  መብት ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ አስከሬኑ በአማራ ሊሂቃን መወረሱ ነው፡፡ የጉሙዝ ህዝቦች በነራስ ሃይሉ ለባርነት ሲሸጡ የቆዩ ስለሆነ ዛሬ ልጆቻቸው  አስከሬን  ቢሰረቁ  አይገርምም፡፡   

የጨነገፈው መሪ ከፊል ወዳጅ ከፊል ጠላት  ሆኖ መቀጠል አይችልም፡፡ የሞያሌ ሰው ፤ የጅግጅጋ  ወጣት፤ የጉሙዝ ልጅ፤ የአክሱም  ሽማግሌ  የኔ  አካል ናቸው፡፡ አብይ ስለ ራሱ ዋሽቶናል ፡፡ ስለ ራሱ  የነገረንን ልናምነው አንችልም፡፡ እሱን ላለማመን ብዙ ምክንያቶች  አሉን፡፡  ብዙ ግዜ ዋሽቶናል ፡፡ አብይ በቅርብ ከዋሸን ትላልቅ ጉዶች  መካካል ኤርትራን በተመለከተ ነው ፡፡ ኤርትራ ወደ ትግራይ መውረር  ስንተ ግዜ ነበር የተዋሸነው፡፡ የኤርትራ  መንግስት የአብይ ብቻ ወዳጅ የሆነበት ምስጢር  አሁንም አልተፈታም ፡፡  ከኤርትራ ጋር ያለው ፍቅር ግን ከፍየልዋ ሞት በላይ ነው እንደሚባለው  ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከፍቅሩ የለንበትም ፡፡ አለንበት ሊሉ የሚፈልጉ  እንዳሉ በመዘንጋት ግን አይደለም

አብይ አህመድ  የኢትዮጵያ ህዝብ በቀደደለት ቦይ የሚፈስ ፤በቀላሉ በተረትና ምሳሌ  የሚያታልለው  ህዝብ ሆኖ አግኝቶታል ፡፡  ከትግራይ ህዝብ  ጋር አብይ በማንኛውም ሁኔታ ሊደማመጥ አይችልም፡፡ የትግራይ ህዝብ እንዴት ለምን መቼ ማን ብሎ ይጠየቃል ፡፡ ውሸት አይቀበልም፡፡ አብይ የአማራውን ተረት ብሂልና ወግ ከሓይማኖት ጋር በመቀመም ሲግተው ይታያል፡፡ የመንግስት ንግግሮች  በሙሉ ወይም በአመዛኙ ኦሮሞን፣ ሶማሌን ፤ሲዳማን፣ ወላይታን የሚመለከቱ አይደሉም፡፡  ደግሞም ተረት ተናጋሪዎችና ተረት ፈጣሪዎችም መልምሏል ፡፡ የዳንኤል ክብረት ተረቶች ሲመዘኑ መቶ ግራም ዳቦ  አይመዝኑም ፡፡ ነገር ግን የተረቱ ባለቤት ሊያደምጠው ይችላል፡፡ አብይ ቀስቃሽ ወይም አስለቃሽ ከዲያስፖራ የጋበዘው ያው የአማራን ህዝብ ለመቀስቀስ ነው ፡፡ ሌላው ማህበረሰብ ከአብይ ጋር የነበረው ፍቅር እርሙን አውጥቷል ፡፡ አማራም በተለይም ገበሬው ከአብይ ጋር ፍቅር የለውም፡፡ ፍቅሩ ያለው አራዳ ኢትዮጵያዊ ከሚባለው ጋር ነው ፡፡ ብሄራዊ ትያትር፤  ሃገር ፍቅር የዋለ ከየትም ይምጣ  አራዳ ይሆናል ፡፡ አብይም የነሱ ብጤ ነው ፡፡ ይህ ባይሆን እዚህ አካባቢ የሚውሉ  ጅብ በልተህ ተቀደስ ብለው ባልተረቱ ነበር፡፡   

 የአብይ አህመድ ትግራይን የማሰይጠን ፖለቲካ  በሌላው ወገን  ድጋፍ አላስገኘለትም፡፡የኦሮሞ   የቤኒሻንጉል ፤የአገው ፤የጋምቤላ፤ የአፋር ፤ የወላይታ  ታጋዮች ምስክር ናቸው ፡፡  የአብይ ቡድንና የአማራ ተስፋፊዎችን  የከፋፍለህ ግዛ  ተንኮል ሰባብረውታል ፡፡  የተቀደሰች የተባለች  አገር  አካልዋን ሰይጣን የማድረግ ተግባር  አልተሳካም፡፡ ዳንኤል ክብረት  የትግራይ ተወላጆች አልነበሩም አልተፈጠሩም እንዲባሉ እነሱን የሚያስታወስ  በሙሉ እንዲፋቅ ጥሪ አቅርቧል ፡፡  ዳንኤል 1984 የተባለው የጆርጅ ኦርዌል መፅሓፍ ያነበበ ይመስለኛል ፡፡ መፅሀፉ የተፃፈው አምባገነኖች  ጠላቶቻቸውን ለማጥፋት የሚጠቀሙበት  ተግባር ነው፡፡ ዳንኤል የነገረን የመጨረሻውን የጭካኔ ደረጃ ነው፡፡

የተቀደሰ ተግባር  የሚባለው የሰው ልጅን ማዳን ብቻ ነው፡፡ አገር ማዳን  በሰው በህይወት የመኖር መብት መከበር  መጀመር አለበት ፡፡ የተቀደሰ አገር የለም፡፡ የተከበረ የተቀደሰ የሚባለው ሰው ብቻ ነው ፡፡ 

 በሰላም  ግዛ የተባለ መሪ ካልተዋጋሁ ብሎ ሞተ የተባለው ዓይነት ነው ፡፡አብይ በስለጣን ላይ በቆየ ቁጥር  የአገራችን ችግር እያመረቀዘ መሄድ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የኑሮ ውድነት የትግራይን  ማህበረሰብ በማጠልሸት  ሊፈታ አይችልም ፡፡ በጀልባዋ ነበርኩ፤ ተራራ ላይ ወጣሁ  በማለት የሚፈታ ችግር የለም  ፡፡

የጨነገፈ መሪ ፤ የገለማ እንቁላል  ምናችን ?


Back to Front Page