Back to Front Page

የያኔው ድምጸ-መረዋው ጋዜጠኛ፣ (ሴኮቱሬ ጌታቸው)

የያኔው ድምጸ-መረዋው ጋዜጠኛ፣ (ሴኮቱሬ ጌታቸው)

ኤልሳቤጥ ስዩም

01-26-21

 

ህወሓት በኋላም ሕወሓት/ኢህአዴግ ገና ከደርግ ጋር በትግል በነበረ ግዜ በየወቅቱ የትግሉን የድል ብስራት የሰሜን ተራሮችን እያቆራረጠ በመላው ኢትዮጵያ እንዲደመጥ ዝግጅቱን ያቀርብ የነበረው ድምጸ መረዋው ሴኮቱሬ ጌታቸው ከሌላ ባልደረባው ጋር ነበር። ይህንን ዝግጅት ያኔ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጉጉት ይጠበቅና በድብቅ ይደመጥ የነበረ ትዝታችን ነው።

ሴኮቱሬ ጌታቸውን የበለጠ ሊገልጹት የሚችሉ የትግል ጓዶቹና የቅርብ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ነገር ግን እኔም ያወቅኩትን ለዚህ ለሕዝብ ልጅ ትንሽ ልበል ብዬ ነው።

በመምህርነት ወደ ትግራይ ዓዲግራት ተመድቦ ይሰራ በነበረበት ወቅት በነበረው ቆይታ ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ ወዶ ከህወሓት ጋር ለመታገል በረሃ ገባ። ደርግ ተሸንፎ ህወሓት/ኢሕአደግ አሸንፎ አዲስ አበባ ሲገቡ ሴኮቱሬም እንደሌሎቹ ታጋዮች ከመስዋእትነት ተርፎ ትርፍ ህይወቱን ይዞ ገባ።

በስራ ምክንያት ለማወቅ ባጋጠመኝ እድል ሴኮን ሳውቀው ለማንም የማይከብድ ቀልድና ቁምነገር አዋቂ፣ ሰውን በስራ ደረጃው ሳይለይና ሳይመርጥ በሰዋዊ መልኩ የሚያይና የሚያናገር፣ መኮፈስ ብሎ ነገር የማያውቅ፣ ፈገግታ ከፊቱ የማይለየው መልካም ሰው ነበር። ሴኮ የዋህና ርህሩህም ነው፣ ወደ ትግል ያስገባችው ታጋይ ሴት ስለመስዋእትነቷ ሲናገር እንባውን መቆጣጠር ያቅተው ነበር፣ በረሃ ገብቶ ጥይት የተኮሰም የተተኮሰበት አይመስልም። የ11 ዓመት ሴት ልጁ በአጭር ግዜ ህመም ሞታበት፣ ልጄ ጓደኛዬ እያለ ሲያለቅስ ሃዘኑ ልክ አጥቶ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ከሴኮ አባባሎች አንድ ነገር ላስታውስ። እንዴት ነህ ሴኮ ሲባል አለሁ እወዛወዛለሁ፣ እተነፍሳለሁ ይል ነበር። ለመጨረሻ ግዜ በ2011 ዓ/ም ክረምት ትግራይ መቐለ በአጋጣሚ አገኘሁት፣ ምን እየሰራ እንደሆነ ስጠይቀው፣ ትግራይንና የትግራይን ህዝብ ከመውደዱ የተነሳ ሲገልጸው ሀብታሞች ለሽርሽር ወደ ዱባይ እንደሚሄዱ ሁሉ እኛ ደግሞ ወደ መቐለ ሰላምና ፍቅር ያለበት ቦታ እንመጣልን ነበር ያለኝ። በመጨረሻም ንህዝቢ ተግራይ ክንቃለስ መጺእና በማለትም አከለበት። አሁን ትዝ ሲለኝ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን አስቤ ቀናሁበት፣ ኮራሁበት አከበርኩትም።

እውነት ነው ሴኩቱሬ ጌታቸው ከትግራይ መሬትና ከትግራይ ሕዝብ ልቡ በፍቅር የሸፈተው ያኔ ከወጣትነት ከለጋነት ዕድሜው ጀምሮ ነው።

ሴኮ ዘረኛነትን የተጸየፈ ነገር ግን ለህዝቦች ነጻነት፣ ለዲሞክራሲ ማበብና ለእኩልነት የታገለ ጀግና ነው። እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ፍቅር በተለይም የተገፋን ሕዝብ መውደድ፣ ጥግ የሌለው እስከ መስዋእትነት ድረስ የሄደውን የዓላማ ጽናትህና ጥንካሬህ ያስቀናል፣ ያኮራልም።

ውድ ወንድሜ፣ ለየወደድካት መሬትና ህዝቧ ደግመህ ተሰውተሃል። ከቀደሙት የትግል ጓዶችህ ጋር እቅፍ ድግፍ አድርጋ፣ ፍቅርዋን እናትነትዋን ያለንዳች ስስት በመለግስ በእቅፏ ለዘለዓለም ታኖርሃለች።

ሴኮዬ እንዴት ነህ? አውቃለሁ መልስህ እንደድሮ አለሁ እወዛወዛለሁ፣ እተነፍሳለሁ እንዳልሆነ፤ ግን በቃ ሰማይ ጣሪያው በሆነ የህዝብ ፍቅር ተሞልተህ፣ የእበላ ባይ ሆዳሞች ጫጫታ ሳይበግርህ፣ የዓላማ ጽናት፣ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ወዶ መሰዋት፣ ዘረኝነትን ተጸይፎ ለህዝቦች መኖርና መሞትን አስተምረኸናል። እውነትም መምህር ነህ። እኔ ሁሌ አስታውስሃለሁ፣ አባባሎችህን እጠቅሳለሁ፣ አከብርሃለሁ፣ እኮራብሃለሁ።

በቃ ሴኮዬ ተደላድለህ በምትወደው መሬት ለዘላለም እረፍ፣ ለመላው ቤተሰብህ፣ ለትግል አጋሮችህ፣ ለትግራይ ህዝብ እንዲሁም ለእናት መሬት ትግራይ ጽናትን እመኛለሁ፣ላንተም ፈጣሪ ነፍስህን በገነት ያኖርህ ዘንድ የዘውትር ጸሎቴ ነው።


Back to Front Page