Back to Front Page

በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ (ቴቄል )

በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ (ቴቄል )

ከዐብይ ኢካቦድ 06/06/21

ይሁዳ በከለዳዊው ንጉሥ በናቡከደነፆር ከተጋዘች፤ ከተወረረችና ናቡከደነጾር ከሞተ በኋላ ብልጣሶር የተባለ ልጁ ነግሦ ነበር። አንድ ቀን ብልጣሶር በሺህ ለሚቆጠሩ መሳፍንቱና መኳንንቱ ድግስ አዘጋጅቶ ጠራችውና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር። በወይን ጠጁ ተገፋፍቶ ብልጣሶር አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ-መቅደስ ዘርፎ ባመጣቸው የወርቅና የብር መጠጫዎች እርሱና መኳንንቱ፤ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጡለት አዘዘ። በእነዚህ መጠጫዎች እየጠጡ በነበረቡት ጊዜ ሁሉም የወርቅና የብር፤ የናስ፤ የብረት የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን ያመልከና ያመሰግኑ ነበር። በዚህ ወቅት በድንገት የሰው እጅ ጣቶች ታዩ፤ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ ጻፉ፤ በዚያ ጊዜ ንጉሡ በድንጋጤ ተሞላ፤ ፊቱም ተለዋወጠ፤ እጆቹና እግሮቹ ካዱት፤ ጉልበቶቹም ተብረከረኩ።

በግድግዳው ላይ የሰው ልጅ ጣቶቹ የጻፉት ማኔ ማኔ፤ ቴቄል ፋርስ የሚል ነበር (ዳን 5፡27)። ማኔ ማለት፤ እግዚአብሔር የመንግሥትህን ዘመን ቆጠረው ማለት ሲሆን፤ ቴቄል ማለትም፤ በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት መንግሥትህ ለሁለት ተከፈለ ለሜዶናዊያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው (ዳን 5፡29-30)

ዛሬም አያሌ በክርስቶስ ስም የሚሸቅጡ የይስሙላ ክርስትያኖችና (Nominal Christians) በከበረው የቤተ-መቅደሱ መጠጫዎች እየጠጡ እንዳሉ ይታወቃል። እነዚሀ በመለኮታዊው ሚዛን ተመዝነው ቀለው የተገኙ ናቸው። ያኦኮሃለማው ሰኔተር ኢኒሆፍ (Senator Inhofe) በወቅቱ በሚዛኑ ተመዝነው ቀለው ከተገኙት (ቴቄል) የይስሙላ ክርስትያኖች አንዱ ናቸው የሚያስብላቸው ተጨበጭ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል።

የሴነቴሩ የይስሙላ ክርስትያን መሆንና በመለኮታዊው ሚዛን ተመዝነው ቀለው መገኘት፤ ከኢትዮጵያው መሪ ከአብይ አሕመድና እርሳቸው ከሚሚሯት ሃገር የተቆራኘ ስለ ሆነ፤ ቀድሞ አብይ አሕመድንና የሚመሩት መንግሥትና ፓርቲያቸው ብልጽግናን ማየት ያስፈልጋል። አብይ አሕመድ በጥቅሉ የፕሮቲስታንት እምነት ተከታይ ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያ ጴንጤ-ቆስጣዊ አማኞች ከሆኑት አንዷ የሆነችው የሙሉ ወንጌል ቤተ-ክርስትያን አማኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። በዚህ ምክንያቱም በበርካታ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያዊያን አማኞች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ክብር እንዲያገኙ አድርጎአቸዋል።

ከካሪዝማቲክና ከጳንጤ ቆስጣዊ እምነት ወጥተውና ተገንጥለው የቃል እምነት (Word of Faith) የተባለ አዲስ አስተምሕሮ ይዘው ብቅ ያሉት ከ 100 ዓመት በፊት በ (E W Kenyon) የተቋቋመ ሲሆን፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ፊት ለፊት የሚጋጩ አሰተምሕሮቶችን የያዘ ነው። በኢትዮጰያ የቃል እምነት ተከታዮች ቢኖሩም፤ የወንጌላዊያዊን አብያተ ክርስትያናቱ መጽሐፍ ቅድስን ተመርኩዘው ያለ አንዳች ማቅማማትና ማወላወል አሰተምሕሮቶአቸውንና ልምምዳቸው በግልጽ ሲንቅፉትና ሲቃወሙት የሚታይ ነው።

Videos From Around The World

የቃል እምነት አንዱ ዘርፍ የብልጽግና ወንጌል ነው። የብልጽግና ወንጌል፤ ምሦሦው፤ ማህሉና ዳሩ ብልጽግና ነው። ሁሉም የሚሽከረከረው በብልጽግና ዛቢያ ነው። ብልጽግናው ደግሞ ገንዘብና ቁሳቁስን በማከማቸትና በማግበስበስ የተመሰረተ ነው። የብልጽግና ወንጌል አራማጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥሮቸን ከአውዳቸው ውጭ ቆንጽለውና ቆርጠው በማውጣት እነርሱ ሊሉት የፈለጉትን እንዲላላቸው ቁጥሮቹን ያለ አግባብ የሚደፈጥጡ ናቸው። በእንግሊዝኛ (Text without Context is Pretext) ይሉታል። አንድ ቁጥር በተገቢ ስነ-አውዳዊ የአተረጓጎም ስልት (exegesis) ተተረጎመ የሚባለው፤ ከቁጥሩ ከላይና ከታች ያሉት ምንባቦች በሚገባ አገናዝቦና፤ በሌሎች የመጸሐፍ ቅዱስ ክፍሎችና ምንባቦች ተመሳሳይ ሃሳብ ካላቸው ጋር አስተያይቶና አወራርሦ ከተተረጎመ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ስለ ሆነ፤ በራስ ወይም በግል አመለካከት የሚተረጎም አይደለም። እንደ ፈለጉ የራስን አመለካከት ለማሰረጸና አሸልኮ ለማስገባት አንድን ጥቅስ ወይም ቁጥር ያለ አግባብ ቦጭቆና ቆርጦ መተርጎምና አስተምሕሮ መፍጠር ያልተገባ ከመሆኑ ባሻገር፤ አያሌ በክርስትና እምነት የሚነሱ የሐሰት ትምሕርቶች መንስኤቸው ይሄው ነው።

የብልጽግና ወንጌልና በድምርም የቃል እምነት አስተምሕሮ የተመሠረተው ከላይ በተገለጸው መልኩ ስለ ሆነ፤ በትክክለኛው የአተረጓጎም ዘይቤ (exegesis) ቀርቦ የሚሞግታቸው በቀላሉ ስሕተታቸውን ለማግኘት አይከብደውም። ምንም እንኳ ስለ ቃል እምነት በጣም ብዙ ማለት የሚቻል ቢሆንና፤ ታሪካዊ አመጣጣቸውና ዳራቸው ማወቁ ለእውነተኛ አማኝ እጅግ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም፤ የዚህ መድረክ ዓላማ ይኼን ማስተናገድ ስላይደለ፤ በአጭሩ ሁኔታውን ገረፍ አድርጎ በማሳየት ወደ ርእስ ጉዳዩ ማለፍ ያስፈልጋል።

የቃል እምነት ወይም ብልጽግና ወንጌል ተከታዮች በዋናነት በሁለት ነጥቦች ላይ ያነጣጥራሉ። የመጀመሪያው አማኝ፤ በሚገባ የሚያምን ከሆነ ሊታመም አይችልም የሚል ሲሆን፤ ለዚህ መረጋገጫ እንደ ሆነ አድርገው የሚያቀርቡት ኢሳያ 53፡5 ነው። ይሄም በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን የሚለው ነው። ክርስቶስ በመስቀል ተገርፎ የቆሰለው ስለ እኛ ፈውስ ነውና፤ ካመንን የግድ መዳን አለብን ይላሉ። አማኝ የሚታመመው፤ እምነቱን ስለማይጠቀምበት እንጂ፤ በእምነቱ ቢበረታ ይቅርና ከባድ በሽታ ጉንፋንም ዝር አይልበትም ይላሉ። ምንም እንኳ በአፋቸው እንዲህ ቢናገሩም፤ ብዙዎቹ በጸና ታመው ሃኪም ቤት እንደሚገቡና እንደሚሞቱም ይታወቃል። ሁለተኛው አማኝ ድሃ ሊሆን አይችልም የሚል በይፋ የሚያስተምሩት አስተምሕሮቶአቸው ነው። ለዚህ ማመሰካሪያ እንዲሆን የሚጠቀሙበት ቁጥርም በ(2 ቆሮ 8፡9) ላይ ሐዋሪያው ጳውሎስ ያስተማረውና የጻፈው ሲሆን፡ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሃብታም ሆኖ ሳለ ለእናነተ ሲል ድኻ ሆነ ተብሎ የተጻፈው ነው። የብልጽግና ወንጌል ማጠንጠኛውና አስኳሉ እንግዲያውስ ይኼው ነው። ድኽነት ያለ ማመን ጉዳይ ነው ይላሉ። ዳሩ ግን ኢየሱስ ድሃን እንድንረዳ አስተማረን እንጂ፤ አንድ ስፈራ ላይ ድሕነት ባለማመን ጠንቅ የሚመጣ ነው በማለት አላስተማረም። ሐዋሪያው ጳውሎስም፤ ለተቸገሩትና ለተራቡት እንዲረዱዋቸው፤ በሚያገለግልቸው አብያተ ክርስትያናት ለነበሩ ምእመናን ጠየቀ እንጂ ባለማመናቸው ምክንያት አጡ ነጡ ከቶውኑ አላለም። ስለ መታመም አስመልክቶም ጳውሎስ ልጄ ለሚለው ለጢሞቲዎስ ለሆድህ ትንሽ የወይን ጠጅ ጠጣ በማለት መከረው እንጂ፤ በእምነት ደካማ ስለ ሆነክ ነው አላለውም። ራሱም ከነበረው ሕመም ይፈወስ ዘንድ ሦስት ጊዜ ጸልዮ ጸጋው ይበቃሃል የሚል መልስ ከአምላኩ አገኘ እንጂ፤ በእምነት ደካማ ስለሆንክ ነው አልተባለም።

በአብይ አሕመድ ብልጽግና ፓርቲ በመባል የተሰየመው ገዥው ፓርቲ የብልጽግና ወንጌል ከተባለው የእምነት ዘርፍ መሕጸን የወጣ የፖለቲካ ልጅነት ይዞ የወጣ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። ከስሕተት አስተምሕሮ ማሕጸን የተወለደ ፖለቲካ፤ የአስተምሕሮው ተገዥና ቁራኛ መሆኑ ሰለማይቀር፤ ሃብት ወይም ብልጽግና ሊገኝ የሚችለው የብልጽግና ወንጌል በሚለው፤ በሚያስተምረውና በሚለማመደው መሰረት መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ የአብይ አሕመድ የብልጽግና ፓርቲ የሚያስብ ሰው፤ ስለ ብለጽግና ወንጌል ማሰላሰሉና መብላለቱ አይቀርም። እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው፤ የብልጽግና ወንጌል አማኞች ወደ ቤተ-ክርስትያናቸው በግንባር ቀደምትነት የሚመጡት ሃብታም እንዲሆኑና እንዳይታመሙ ነው። በዚህም ለዘይት፤ ለጨርቅና፤ ለተጸለየበት ውሃ ተብሎ ሰባኪው ሲያውጅ፤ ብዙዎች በሺ የሚቆጥር በወር ያጠራቀሟት ገንዘብ አስረክበው ከዓመት ወደ ዓመት በድህነት የሚኖሩ ናቸው። በእንዲህ ዓይነቱ አብያተ ክርስትያናት የሚበለጽጉት በመሪነት የሚኖሩት ፓስቶሮችና ቢሾፖች እንጂ፤ ድኻው ምንም ጠብ የሚልለት ነገር አይኖርም።

ዶ/ር አብይ አሕመድ ክርስትያን ነኝ ባይ ቢሆኑም፤ ከክርስትና እምነት በተቃራኒ መሪ ሆነው ባጭር ጊዜ አያሌ ውሸቶችን ለሚመሩት ሕዝብና ለዓለም ሕዝብም ተናግረው፤ ሃሰተኛነታቸው አረጋግጧል። የተናገርዋቸው ነጭ ውሽቶች እዚህ ላይ መዘርዘር ባይቻልም፤ በጨለማ የተፈበረኩት የውሸት ምርታቸው፤ ፀሐይ ስትወጣ እርስ በርሳቸው ተላትመው ሲደቁ ታይቷል። በገዛ ራሴ አስተዳድረዋለሁ የሚሉት ሕዝብ ባይተዋርና ጭራቅ ከሆነ መንግሥት ጋር ተባብረው የጥፋት ድግስ አዘጋጅተው በጭካኔ ጨፍጭፈውታል፤ ክፉ ሴራ አቀነባብረው አቻ የሌለው በደል ፈጸመውበታል። አብይ አሕመድ ዋሾ መሪ ብቻ ሳይሆኑ፤ ጨካኝና ምሕረት የለሽ ነፍሰ ገዳይም ናቸው።

ከ6 ሺህ በላይ ሕጻናት ያለ ወላጅ እንዲቀሩ ሲደረጉ፤ በሺዎች የሚቆጦሩ እንስት ተጋሩ ታይቶ በማይታወቅ ጭካኔ በሠራዊታቸውና በጋበዝዋቸው የኤርትራ ሠራዊቶች ሲደፈሩ፤ ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከሚኖርበት ርስቱና ጉልቱ፤ ከቤቱና ከማጀቱ ተነቅሎ እንዲሰደድ መደረጉ፤ በርሃብ መልአተ የትግራይ ሕዝብ እንዲጠፋ፤ ለእርሻ ወሳኝ ስፍራ ያለቸውን ሞፎሩን የሚጎቱተለት በሬዎቹ ዓይኑ እያየ በፊቱ ታርደው ሲበሉ፤ ሞፈርና ቀንበር ሲቃጠሉ፤ የመሰረተ ልማት ቁሳቁሶች ወደ ኤርትራና ወደ አማራ ተጭነው ሲዘረፉና የማይነቀሳቀሱትን ሆን ብለው እንዲጋዩ ሲደረጉ፤ ወጣቶችን በአደባባይ ተገድለው በገደል ሲወረወሩ፤ ከ5.2 ሚልዮን በላይ የትግራይ ሕዝብ በጠኔ እንዲያልቅ ሲደረግ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ የክፍለ ዘመኑ ቁንጮ አረሜናዊና ግፈኛ መሪ መሆናቸው ቁልጭ አደርጎ ያሳያቸዋል። ታድያ የክርስቶስ ደቀ-መዝሙርነት በውሸት ቀዳሚ በነፍስ ገዳይነት ገናና መሆንን የሚያመለክት ይሆንን?

እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ልጆች ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ ነው። በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፤ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፤ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው (ዮሐ 8፡44)። በዚህ ቁጥር ሁለቱ የዲያብሎስና የልጆቹ ባሕሪያት ተግልጿል። እነዚህም ነፈሰ-ገዳይነትና ሐሰትን ከራስ አፍልቆ መናገር ናቸው። በክርስቶስ አምናለሁ ብሎ ይለፍፍ፤ ወይም አላምንም ብሎ እነዚህ ሁሉት ባሕሪያት የሚሰለጥኑበት ሰው ተወደደም ተጠላ ያለ አንዳች ጥርጣሬ የዲያብሎስ ልጅ መሆኑ የሚያሰረግጥበት ነው። አንድ ሰው ነፍሰ ገዳይና ውሸታም ከሆነ የዲያብሎስ ልጅ እንጂ ከቶውኑ የእግዚአብሔር ልጅ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ዓይነት ባሕሪያት እያለው፤ ክርስትያን ነኝ ብሎ ቢያውጅ፤ ይኼ የይስሙላ ክርስትያን ነው እንጂ እውነተኛው የክርስቶስ ተከታይ ሊሆን ከቶ አይችልም።

ነፍሰ በላውና ጭራቁ የኤርትራ አምባገነን መሪ ኢሳይያስ አፈወርቂ፤ ቂመኛና ተበቃይ ከመሆኑ ባሻገር፤ የብዙዎችን ነፍስ በጭካኔ የቀጠፈ አረመኔ መሆኑ የታወቀ ነው። ኢሳያይስ የሁሉም ሃይማኖት መሪዎችና ምእመናን፤ የገደለ፤ በኮነቴይኔር ከፍተኛ ሙቀት ባለበት ስፍራ አጉሮ ለበርካታ ዓመታት ያሰቃየ ከመሆኑ ሌላ፤ ብዙዎችን ለሕልፈተ-ሞት ዳርጓቸዋል። ዶ/ር አብይ ከዚህ ክፉና ጨካኝ መሪ ጋር በቀለበት በአረቦቹ ነገሥታት ያስሩ ዘንድ ምን አደረጋቸው? ባሕሪውን ሳያውቁ እንዲሁ ድንገት ያጠለቁት የውል የቀለበት ኪዳን ይሆንን? እግዚአብሔር ይቅር ይበል፤ አሳምረው እያወቁ ነው እንጂ!

ሌላው ለጊዜው እንተወውና እርሳቸው የወንጌላዊት ቤተ ክርስትያን አማኝ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነኝ ሲሉን፤ በኤርትራ ከፍተኛ በደል፤ ድብደባ፤ ስቃይ፤ ስደትና ሞት ይደርሳቸው የነበሩት ወንጌል ስብካችኋል ተብለው ይታሰሩ የነበሩ ወንጌላዊያን ናቸው። እናማ ለቃል ኪዳን ጓዳቸው እንደ አማኝ፤ ይሄንን ማድረጉን አቁም ብለው አሳስበውት ይሆኑን? አይመሰለኝም! ይልቅስ የእርሳቸው የልብ ትርታ ቀጥፎና ዋሽቶ ከግብረ-አበራቸውና በኪዳን ቀለበት ካሰሩት ባላቸው/ሚስታቸው በጥናትና በቅንጅት የትግራይን ሕዝብ አስከናካቴው እንዲነጥፍ ማድረግ ነው። በውሰጥ የሚሰለጥንና የሚገዛ በሕሪ፤ ከውጭ በመቀባባት አሳምሮና አሸበራርቆ ለጥቂት ወራት ማቅረብ ይቻል እንደ ሆነ እንጂ፤ ውሎ አድሮ ፈንቅሎ በመውጣት እርቃኑ መውጣቱ አይቀርም። የነፍሰ ገዳይነትና የውሸት የዲያብሎስ ልጅነት ማሳያ ባሕሪያትም፤ ውለው አድረው ይኼውና ራቆታቸው ወጥተው ዓለም ሁሉ አይቶ እየተገረመ ነው።

ለመሆኑ አንድ የክርሰቶስ ደቀ-መዝሙር ነኝ የሚል ሰው፤ በግፍ ሕዝብን ከሚጨፈጭፍና በነፍ ውሸትን ከሚናገር ሰው ጋር ሕብረት ሊያደርግ፤ ለክፉ ድሪጊቱና ባሕሪው እውቅናን ሊሰጥና፤ በክርስቶስ እግር ተንበርክኮ፤ እግዚአብሔር ሆይ የሚያስበውን አከናውንለት፤ ነፍሳትን በመቅጠፉና በመጨፍጨፉ ሥራው እንዲሳካለትና፤ ጠላቶቹን በውሸት እንዲያደናግርና እንዲያስበረግግ አድርግለት፤ በኢየሱስ ስም! ብሎ መጸለይ ይችል ይሆንን? ሴናተር ኢንሆፍ ያደረጉት ይሄን ሲሆን፤ በሚዛን ተመዝነው ቀለው ተገኝቷል። በአሜሪካ ሁሉም ሴኖቶች በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚደረሰውን ሶቆቃና ፍዳ አይተው ባንድ ድምጽ ድርጊቱ ወዲያውኑ እንዲቆም ሲወስኑ፤ ክርስትያን ነኝ ባዩ ሴናቴር ኢኒሆፍ የትግራይን ሕዝብ ጥቃትና በደል ገሸሸ አድርገው፤ ከሚዋሸውና ነፍስ ከሚገድለው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን መቆማቸውና መሰለፋቸው እየየና ወዮው! የሚያሰኝ ነው። በዚህም ክቡር ሴነቴሩ በሚዛኑ ተመዝነው ቀለው ተገኝቷል (ቴቄል)።

ክቡር ሴናተሩ ከአብይ አሕመድ ጋር በቤተ-መንግሥቱ ተንበርክከው የጸለዮት ከቶ ምን ይሆን? በበደለህና በነፍሰ ገዳይነትህ ትበረታ ዘንድና በውሸትህ ትጠነክር ዘንድ እጸልይልሃለሁ የሚል ይሆን? የፈለገው ይሁን በምድር በሰማይ ግልጽ ሆኖ የወጣው የትግራይ ሕዝብ በደል ቸል ብሎ፤ በዳዩ፤ ግፈኛውና አመጸኛው እንዲሳካለትና እንዲቀናው ወደ አምላክ በኢየሱስ ስም የሚቀርበው ጸሎት፤ ከ 2 ሜትር ከፍ ብሎ ወደ ላይ የማይወጣና እግዚአብሔርን ዘንድ ፈጽሞ ሊደርስ የማይችል ነው። ለመሆኑ ኢንሆፍ የተበደለውን የትግራይ ሕዝብ ለማየት እንዴት ተጸየፉት? እንደ እውነተኛ ክርስትያን መጠየቅ፤ ማበረታትና ማጽናናት የነበረባቸው አበሳውንና ፍዳውን የሚያየው ሚስኪኑን የትግራይ ሕዝብ መሆን አልነበረበትም እንዴ?

እግዚአብሔር ብዙ አውሎ ነፋስና የውቂያኖስ ማዕበል ፍንክችና ንቅንቅ የማያደርጉት ጽኑዕ አምላክ ነው። ይሁንና አንድ ተበድሎ የሚያለቅስ ሰው አይቶ ውስጡ የሚናወጥበትና የሚባባ አምላክ ነው። በትግራይ ሕዝብ ላይ በአብይ አሕመድ፤ በኢሳያስና በአማራ ሊህቃን በቅንበር እየተፈጸመ ያለ የሚጎመዝዝ ጽዋ ከእግዚአብሔር ዓይን ከቶውኑ የተሰውረ አይደለም። የሴናቴሩ ከበዳዮች ጎን ቆሞ መጸለይ፤ ግብዝና ተቀባይነት የሌለው የይስሙላ ክርስቲያን ጸሎት እንደ ሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል። ለመሆኑ ሴናቴሩ ወላጅ አልባ ሆነው ስለ ቀሩት የትግራይ ሕጻናት ምን ተሰማቸው? ምንስ ጸለዩ? በወዳጃቸው በአብይ አሕመድ ወታደሮችና በጋበዝዋቸው የኤርትራ አውሬ ሰራዊት በሴቶች ስለ ተፈጸመባቸው ዘግናኝ ፆታዊ ጥቃትስ ምን አሉ? በግፍና በፍዳ በመደዳ በገዛ ቤታቸው ስለ ተገደሉት ንጹሐን ተጋሩስ ምን ብለው ይሆን? በሬዎቹ ታርደው ስለ ተበሉት ሚስኪን የትግራይ ገበሬ በቀጣዩ ክርምት እንዳያርስ ሞፈርና ቀንበሩ በወዳጃቸው በአብይ አሕመድ ሠራዊቶች ሆነ ተብሎ ሞፈርና ቀንበሩ ሲቃጠሉበትስ ዝምታን መርጠው አብይ! አብይ! የሚል አባዜ እንደ ዘመንኛዎቹ አማኝ ተብየዎች በተለከፉበት ልክፍት ተለክፈው ይሆኑን? በጥቅሉ የተከበሩት የኦኮሃልማ ሴናተር፤ በበዳዮቹን ቤተ-መንግሥት ከበዳዮች ጋር መክረውና ጸልየው የትግራይን ሕዝብ ሮሮ፤ ስቃይና ፍዳ ከመ-ጤፍ ሳይቆጥሩ ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው በሚዛኑ ተመዝነው ቀለው ተገኙ (ቴቄል) ማለት አያስደፍርምን?

ዶ/ር ዐብይ የተውኔቱ ዋና ተዋናይና የበደሉና የሰቃዩ ዋና ተጠያቂ መሆናቸው እንደ ጓደኛቸው ብቸኛው ገራሚ ሴነቴር በሚዛኑ ተመዝነው ቀለው የተገኙ ከመሆናቸው ባሻገር፤ ሁለት ጊዜ ማኔ፤ ማኔ ተብሎ በግድግዳው ላይ ከፊት ለፊት በጣቶቹ የተጻፉት የሚመለከታቸው ነው። ይኼም እግዚአብሔር የመንግሥትህ ዘመን ቆጠረው የሚል ትርጉም ያለው ነው። የክፉዎችና የአረሜያዊያን መንግሥታት ዘመን እግዚአብሔር የቆጠረው መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይኼም የመንግስቱ ዘመን አጭር እንደ ሆነ የሚያመለክት ነው።

ማኔ ፤ ማኔ (ዐብይ አሕመድ)

ቴቄል (ዐብይ አሕመድ + ሴናቴር ኢንሆፍ)

Back to Front Page