ህገ መንግስትን አፍርሶ መደራደር? ኻልአዩ ኣብርሃ 08-11-21 የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በወረቀት ሳይሆን በተግባር መንግስት በገዛ እጁ ሽሮታል። ህገ መንግስቱ እንዲከበርና ስርአት አልባነት እንዳይነግስ የሰጋው የትግራይ ህዝብንም በአገር ክህደት በተነከረ ወረራ የዘር ማጥፋት ሰይጣናዊ ድርጊት እየተፈፀመበት ነው። አሁን ባገሪቱ ያለው ሁኔታ የሮቢን ሁድ ታሪክን ያስታውሰኛል። በአውሮፓ የመስቀል ጦርነት ዘመን የእንግሊዙ ታላቅ ንጉስ "ጆን ዘ-ላየን-ሃርትድ" ወደ እየሩሳሌም ሲዘምት እንግሊዝ የቀሩት ባለስልጣናት በህግ አልባነት አገሪቱን ቀውጢ አደረጓት፣ ድሃ ተበደለ፣ ፍትህም ተጓደለ። ሮቢን ሁድ የሚባል የህዝብ ልጅ የሆነ ሽፍታ ህዝባዊነት ከነበራቸው ጥቂት ቆራጥ ጭፍሮቹ ጋር በመሆን በተጨማለቁት ባለስልጣናት ላይ ጦር መዞ እንግሊዝን ሳትፈርስ ለንጉስ ጆን አቆይቶለታል። ኢትዮጵያ ትሻልን ፈታ ትብስን ካገባች በኋላ ለሰላሳ አመታት በሰላምና በመልካም የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግስጋሴ ጎዳና ላይ ያቆያት ህገ መንግስት በህግ አልባነት ተተካና የአገሪቱ ህዝብ ከዘመነ መሳፍንት በባሰ የክልል ሹመኞች የደካማውን ማእከላይ መንግስት እጅ እየጠመዘዙ የሌላውን ሉአላዊ ክልል መሬት ሲወሩ፣ ሲዘርፉ፣ ሲደፍሩ፣ ሲገድሉና ሲያፈናቅሉ ከቆዩ በኋላ ያ የማይቀረው ሽንፈት መጣ። ህገ መንግስቱ እርስበርስ ይተራረማሉ ተብሎ ሲጠበቅ እርስበርስ በተደጋገፉት በህግ አውጪው፣ በህግ አስፈፃሚውና በህግ አስከባሪው አካላት ሲናድ ሶስት የውጪ መንግስታት ተጋብዘው የኢትዮጵያ አካል የሆነውን ትግራይን ድምጥማጡን አጠፉ። የአማራ ክልል ወራሪ ሃይልም ከትግራይ ሲሶውን መሬት በህገ ወጥነት ያዘ፣ አሁንም በምእራብ ትግራይ ሰፊ መሬት እንደተቆጣጠረ ነው። የህግ ማስከበር የተባለው የህግ ማፍረስ ዘመቻ "መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ" ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብን አሳበደ፣ ቄሱም ባረከ፣ አላህ ወአክበርም ተባለለት፣ ፓስተሮችም "እየሱስ ያድናል" አሰኝተው የመቅደስ አዳራሽ ሙሉ አስጨፍረዋል። አሁን የትግራይ ህዝባዊ ጦር አማራ ክልል ገብቶ ከሲሶ ግዛት በላይ ተቆጣጥሯል። ህግ ማስከበር ማለት ይህ ነው፣ ህግ አፍራሹን ወራሪ ወደ መሸገበት መገስገስ! ለወራሪው ሃይል ግን ህግ እየፈረሰ ያለው ትግራይ ስትወረርና በህዝብ ላይ ግፍ ሲፈፀም ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ከወረራውና ዘር ማጥፋት ዘመቻው ራሱን ለማዳን የሚያደርገው ትግል ነው። ነገር በእግሩ ሳይሆን በጭንቅላቱ የሚያቆሙ ጉደኞች የበረከቱበት ጊዜ ሆኗል።
ይህ በዚህ እንዳለ አንዴ ቴድሮስ ነን፣ ሚኒሊክ ነን፣ አበበ አረጋይ ነን፣ አንዳርጋቸው ነን፣ ጣይቱ ነን እያሉ ትግራይን ዱቄት አድርገናል ብለው የፎከሩት እባጮች ተንፍሰው መድማትና መጉደል ሲጀምሩ የነብስ አድን ጥሪአቸውን የሚያቀርቡት በለቅሶ ሳይሆን አሁንም በቀረርቶ ነው። ያቺ የገደሏት ህገ መንግስት ነፍስ ዘርታና ዘንዶ አክላ ስትመጣባቸው በአንድ እጃቸው እነሱን ሳይሆን "አገርህን አድን" እያሉ ህዝቡን እሳት ውስጥ ሲማግዱት በሌላኛው እጃቸው ደግሞ የእንደራደር ጥያቄ ያቀርባሉ። ድንገት ቢሳካልን ብለው የቀራቸውን ጦር እያደራጁ ሲዋጉ፣ ውስጣቸው ደግሞ መሸነፋቸውን ስለሚነግራቸው ድርድርን እየተመኙ ነው። የሚያስደምመውና ጉድ የሚያሰኘው ግን መደራደር የሚፈልጉት የጣሱት ህገመንግስት ጥሰቱ እንደተጠበቀ ነው። የሰው ንብረት ነጥቆ ንብረቱን እንደያዘ ከህግ አስገባሪ ጋር ስለ መታሰርና አለመታሰር የሚደራደር ሌባ ሲኖር አይነ ደረቅ ይባላል፣ ወይንም "ፈጣጣ" በአራዳኛ። የአማራ ክልል መንግስት ህገ መንግስቱን ጥሶ የትግራይ ሉአላዊ ግዛት የሆኑትን ምእራብና ደቡብ ትግራይን ሲወር በአገሪቱ የመከላከያ ሃይልና፣ በሶስት የውጭ መንግስታት እርዳታ ነበር። ይህ በሞት የሚያስቀጣ የአገር ክህደት ወንጀል ነው። የህግ ጥሰቱ በዚህ አያበቃም ከወረራው ቀጥሎ የተፈፀመው አውዳሚ የሆነው ዝርፊያ፣ ንብረት ማቃጠል፣ ሴቶችን መድፈርና፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አስር የሞትና እስከ አለም ፍፃሜ ድረስ እስር የሚያስፈርድ ነው። ይህን ሁሉ ወንጀል ተከናንበው አደባባይ ላይ ወጥተው እንደራደር የሚሉት ያ ሁሉ ዲያብሎሳዊ ድርጊታቸው እንዳልተፈፀመ ተቆጥሮ በስልጣናቸው ላይ ተደላድለው ለመቆየት ወይንም ቢያንስ ህይወታቸውን ለማዳን ነው። ድርድር እንኳ ይደረግ ቢባል ህግ ተጥሶ ባለበት ሁኔታ አይደለም። የጣሱትን ህግ እንደተጣሰ ለማቆየትና ህጋዊነትን ለማላበስ ራሱን ከነሱ ወንጀል ለመከላከል እየታገለ ያለውን ህዝብ ላይ ጭቃ መወርወር ቀቢፀ ተስፋን ያመለክታል እንጂ ከወንጀላቸው ነፃ አያወጣቸውም። "ህወሓት የኤሪትርያና የኢትዮጵያን ጦር ዩኒፎርም ለብሳ ንብረት ዘረፈች፣ አቃጠለች፣ ሴቶችን ደፈረች፣ ወጣቶችን ፈጀች" ሲባል ከረመ። አሁን ደግሞ "ህወሓት ህፃናትን አስታጥቃ አሰለፈች፣ ሃሺሽ እየሰጠች ጦር ሜዳ ትልካለች" ይላሉ። ይህን የሚሉት ህወሓት በዲሲፕሊንና በሞራል ልእልና በልጣ ለሁለተኛ ጊዜ ድል እንደመታቻቸው አሳምረው የሚያውቁት የድሮና የታደሰው የደርግ አቀንቃኞች ናቸው። ከሃይማኖተኛው የትግራይ ህዝብ አብራክ የወጡት የሰራዊት አባላት እንደጠላቱ ጦር ድፈሩ፣ ንፁህ ሰው ግደሉ ተብለው በረከሰ መስቀል ተባርከው የዘመቱ አይደሉም። እንደክርስቶስ ህዝብን ለማዳን እየደሙ ያሉ ናቸው። በነገራችን ላይ የትግራይ ህፃናት በርግጠኝነት አልዘመቱም እንጂ ዘምተውስ ቢሆን አስገራሚ ነውን? አይናቸው እያየ ቤተሰባቸው ሲገደልና እናቶቻቸው ሲያለቅሱ፣ ሲደፈሩም ያየ ህፃን እንኳንና ከአስራ ስምንት በታች ከሶስት በታችስ ሆኖ ቢዘምት ምን ጉድ ያሰኛል? በእስራኤል ቦምብ እናቶቻቸው ቤታቸው ፍርስራሽ ስር የተቀበሩባቸው ተስፋ ያጡ የፍልስጤም ህፃናት አይደሉም እንዴ ከእስራኤል ታንክ ጋር በድንጋይ የሚፋለሙት? የትግራይን ህፃናት ለመከራና ለሞት እየዳረጉ "አዛኝ ቅቤ አንጓች" ሆኖ ይህን ለከሰረው ዲፕሎማቲክ ፍጆታ መጠቀም በሃይለኛ ጎርፍ እየተወሰዱ የወንዝ ዳር ሰምበሌጥን መያዝ ነው። ድርድር የሚባለው አንዱ ህግ አክባሪ አንዱ ህግ ደፋሪ ሆኖ ባለበት አይደለም። ለሰፊው ህዝብ ደህንነት ሲባል ከህግ ደፋሪው ጋር መደራደር አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝም እንኳ የማይመለሰው ወንጀል ለኋላ ፍርድ ትቶ ሊመለስ የሚችለው ከተመለሰ በኋላ መነጋገር ይቻላል። መለስ ዜናዊ የኤሪትርያ ጦር ባድመን ከወረረ በኋላ ስለ ድርድር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። በዚህ መግለጫው ለድርድሩ ያቀረበው አንድ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነበር። ይህም "status quo ante" ወደ አማርኛ ሲመለስ "ከወረራው በፊት ወደ ነበረው መመለስ" የሚል ነው። እንደምናስታውሰው መለስ ራሱን የገለፀው ከፊቱ የነበረውን ተለጣፊ ማስታወሻ ልጦ መልሶ በመለጠፍ ነበር። አሁን ቁራጭ መሬቷን ባድመን ሳይሆን የኤሪትርያ ጦር መላ ትግራይን ወሮ እያጠፋት መሆኑ ሲታወቀው መለስ መቃብሩ ውስጥ መቶ ጊዜ ተገለባብጦ ይሆናል። ተክቶት የሄደው ድኩም አገሪቱን ለማን እንዳስረከባት ሲያስብ በቁጭት በግኗል። የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት የሆነውን ባድመን አለም አቀፍ ህግን በመሻር ወረራ ያካሄደው የኤሪትርያው ወንጀለኛ መንግስት የዘረፈውን እንደያዘ መደራደር ማለት ሌላ ህግ አፍራሽ መሆን ነው። የሌባ ተባባሪ ሌባ ነው እንደሚባለው መሆኑ ነው። በሚያስደንቅ ሁኔታ በኢትዮጵያ መንግስትና በኤሪትርያ መንግስት የታገዘው የአማራ ክልል በትግራይ ላይ የመሬት ወረራና ህዝብን የማፈናቀል ድርጊት እንዳይቀለበስ እየታገሉ ያሉት አማራ ብቻ ሳይሆን ከላይ የተጠቀሱት መንግስታት ጭምር ናቸው። ትግራይ መሬቷን ለማስመለስ የምታደርገውን ትግል በኢትዮጵያ ህልውና ላይ እንደተከፈተ ጦርነት እያስመሰለ ሽብር የሚረጨውም እነዛ የትግራይ መሬቶች ከአማራ እጅ እንዳይወጡ ነው። ይህ ከእንጀራ ልጇ አሻንጉሊቷን ቀምታ ለራሷ ልጅ እንደምትሰጥ ክፉ እንጀራ እናት ጋር ይመሳሰላል። የእንጀራ ልጂቱ አሻንጉሊቷን ለማስመለስ ጥረት ስታደርግ በሚፈጠረው ፀብ ሌሎች የቤት ልጆች፣ አባትየው ሳይቀር በእንጀራ ልጂቱ ላይ መነሳታቸውም የኢትዮጵያና የትግራይን አሳዛኝና ተስፋ ቢስ ግንኙነት ያመለክታል። የተወረረው የትግራይን መሬት ማስመለስ የነበረበትና ወራሪዎቹን መቅጣት የነበረበት የኢትዮጵያ መንግስት ሆኖ እያለ ግን ፍርደ ገምድልነት ስለነገሰ ትግራይ አስፈላጊ ባልነበረ መስዋእትነት መሬቷን እያስመለሰች ነው። ይህ ማለት ህግ በፈረሰበት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያዋጣው "በህግ አምላክ" ማለት ሳይሆን ሽፍትነት ነው! የቀማኸውን ይዘህ መደራደር! ስለዚህ ህግ ሊመለስ ከሆነ ቢያንስ ቢያንስ በአማራ ክልል የተወረረው መሬት ለትግራይ መመለስ አለበት። ቀሪዎቹ ወንጀሎች ህግን ወደ ቦታው መልሶ ህግን በሚንዱ ሳይሆን ህግን በሚጠብቁ አዲስ የፍትህ አካላት በኩል እልባት ያገኛሉ። በፍትህ እጦት የአርሲ እናቶችን አስለቅሶ መቅረት ተችሏል። ይህ ግን በትግራይ አይደገምም! የትግራይን ሴቶች ደፍሮ፣ የትግራይን መሬትና ንብረት ወሮ፣ የትግራይን ሰብል አሳርሮ ተኝቶ ማደር አይቻልም። "So it shall be written, so it shall be done!!" ፈርኦን ራምሲስ ሁለተኛ እንዳለው። (የአማርኛ ትርጉሙ ስሜት ስለማይሰጥ ነው)። |