Back to Front Page

ያየሰው ሽመልስ ማሰር በነፃ ሐሳብን የመግለፅ ላይ ጥቃት መፈፀም ነው።

 

ያየሰው ሽመልስ ማሰር በነፃ ሐሳብን የመግለፅ ላይ ጥቃት መፈፀም ነው።

 

ጋዜጠኛ ያየሰው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈታ!

ከእንዳለ ዘለቀ

ከመቐለ

መጋቢት 2012 ዓ/ም

 

 

ያየሰው ሽመልስ ታሰረ የሚል ዜና መሰራጨት ከጀመረ ቀናት አስቆጥሯል። ለምን እንደታሰረ ማንም በእርግጠኝነት መናገር ባይችልም በርግጠኝነት መገመት ግን ይችላል። ምክንያቱ ግልፅ ቢሆንም ሰበቡ ላይ የተለያየ ሐሳብ እየቀረበ ነው። ሌሎችን ትተን ዋናዋና የተሰጡ የሰበብ ግምቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

1.   ያየሰው ሽመልስ የታሰረው አምባሰደር ስዩም መስፍንን በኢትዮ-ፎርም በተባለው ፕሮግራሙ ቃለ መጠይቅ በማድረጉ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

2.   በደህንነት ሹሙ ደምመላሽ ገ/ሚካኤል ትግራይ እንዳትሄድ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሳለ ማስጠንቀቅያውን ጥሶ ትግራይ በመሄዱ ነው የታሰረው የሚሉም ቁጥራቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

3.   ስለ ኮሮና ቫይረስ አደጋ ስለሚያስከትለው የሞት ኪሳራ በመንግስት የተገመተ ቁጥር ምስጥር በማጋለጡ ነው የሚል ሰበብም በሰፊው እየተገለፀ ነው።

4.   በለውጡ ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳ በማቅረቡ በፀረ ለውጥ ተፈርጆ ነው የሚሉም አሉ።

 

ሰበቡ የትኛው ይሆን የሚለው በርግጠኝነት ለመገመት እስቲ ያየሰው ከመታሰሩ በፊት በፌስቡኩ የፃፋቸውና ከታሰረ በኃላ መታሰሩን በመቃወም የተለያዩ ኢትዮጵያውያን በፌስቡካቸው ሐሳባቸውን የገለፁቱን እስቲ ለአብነት እንይ።

 

ከዘር ወደ ሳኒታይዘር (ያየሰው ሽመልስ ከመታሰሩ በፊት በፌስቡክ ገፁ የፃፈው)፡-

አስፈሪ ጊዜ ላይ ብንሆንም እናቴ እንደምትለው ከዓለም ጋር የመጣ አደጋ ነው የገጠመን። ማማዬ የሆነ ማህበራዊ ችግር ሲገጥም ''ከአገር ጋር የመጣ ነው፣ ሰው እንደሆነው እንሆናለን'' ትላለች።

Videos From Around The World

ኮሮናም ከመላው ዓለም ጋር የምንታመመው ወረርሽኝ ነው። ይህ አንድ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ፈረንጆቹ ለራሳቸው ሲሉ ቢሆንም ሕክምናውን ማፈላለጋቸው ስለማይቀር ተጠቃሚ ነን። እኛ አገር ብቻ ቢሆን እኮ ''በሰሜን ምሥራቅ ሙሉበሙሉ፣ በማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል በከፊል፣ በደቡብ በአብዛኛው፣ በሰሜን ምዕራብ በሁሉም ወረዳዎች ታመዋል...'' ወዘተ እያልን የምናወራው ክፉ ወሬ ነበር።

 

የሰማዩ ጌታ የምድሩ ባለቤት ድህነታችንን ዓይቶ በሽታውን ከዓለም ጋር የመጣ አደረገው። ይህ ወረርሽኝ ከሀብታሙ የዓለማችን አካባቢ የመጣ መሆኑ በአንድ በኩል ተሯሩጠው ሕክምናውን እንዲፈልጉ ያደርጋል- ልክ አሁን እንደሚጥሩት። ለምሳሌ ኢቦላ ድሀ አገራት ላይ በመከሰቱ ከታመሙት ግማሽ የሚደርሱትን ገድሏል። ኮሮና ግን በሀብታሞቹ በኩል ስለመጣ challenge እየተደረገ ነው።

 

በሌላ በኩል ደግሞ late comer advantage እንዲኖረን ያደርገናል። ስለዚህ ልንከላከለው የምንችል ወረርሽኝ እንደሆነ አውቀን፣ ሀኪሞቻችንና ሚዲያዎቻችንን መከታተል መልካም ነው። እዚህ ጋር አንድ ጥርጣሬ ወለድ ጥቆማ ልስጥ። ቻይና ለወራት ወረርሽኙን ደብቃዋለች። በዚያን ወቅት በርካታ ቻይናዊያንና ሌሎች (ኢትዮጵያዊንንም ጨምሮ) ወደ ኢትዮጵያ ያለምንም ምርመራ ገብተዋል። ሌላው ቀርቶ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ግብአቶች ኮሮናው ከተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ግዛት የሚመጣ ነው። በዚህ አጋጣሚ ኮሮና እንዳልገባ ማረጋገጫ ይኖረን ይሆን? ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ሰዎች በድንገተኛ ሕመም የሞቱትና በከፋ ጉንፋን የታመሙት ለምን ይሆን? መለስ ተብሎ ቢታይ ጥሩ ነው።

 

በተረፈ እንደማህበረሰብም እንደ መንግሥትም ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረግን ነው ማለት አይቻልም። በአዲስ አበባ life as usual እንደቀጠለ ነው። አዲስ አበቤ ይተቃቀፋል፣ ይሳሳማል፣ ከቦ ያውካካል፣ በማስ ትራንስፖርት ይጋፋል። ምንም የተከሰተ አይመስልም።

 

መንግሥትም ቢሆን እንዲህ ላሉ ነገሮች ዝግጅት ያለው አይመስልም። ለምሳሌ ትናንት ምሽት ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ከሳዑዲ አረቢያ Deport የተደረጉ ኢትዮጵያዊያን ምንም የህክምና ምርመራ ሳይደረግላቸው፣ በፖሊስ እየተባረሩ ወደ ከተማ እንዲገቡ ሲደረግ አይቻለሁ። እንዲህ ያለው ግዴለሽነት አሳሳቢ ነው!! ሌላው ቀርቶ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና የጤና ተቋማት ምን ዓይነት ቅንጅት፣ መጠባበቂያ በጀት፣ ወዘተ እንዳላቸው አይታወቅም። ጠሚሩ ከቢሮአቸው ሆነው የሚሰጡት መግለጫ መልካም ቢሆንም ቅንጅት የሚታይበት አይመስልም። ለምሳሌ ያወጁትን አዋጅ በሕገመንግስቱ አንቀፅ 93 መሠረት በፓርላማው ማስፀደቅ ነበረባቸው። አላደረጉትም። ክለቦች ይዘጉ ቢሉም፣ ይህ መፈፀሙ የሚከታተል አካል የለም። በጥቅሉ ፕሬዚደንታዊ የሚመስለው ትዕዛዛቸው ተደማጭ ሆኗል ማለት አይቻልም። ጉዳዩን በባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ ይሻላል።

 

በተረፈ ኮሮና እግዜር ያጥፋውና የፌስቡክንም ወሬ ከዘር ወደ ሳኒታይዘር ቀየረው። እነዛ በብልፅግና ፓርቲ በኩል ቀጣዮቹ ጠቅላይሚኒስትር ይሆናሉ የተባሉት ነጋዴዎች የሳኒታይዘርን ዋጋ በማናር ወረርሽኙን እየተባበሩት ነው። (በነገራችን ላይ 30 ሚሊዮን under poverty level ለሚኖር ሕዝብ፣ ለ85 ሚሊዮን አርሶ አደር ለሚኖርባት አገር ነጋዴና ድሀ እኩል የአንድ ፓርቲ ማህበራዊ መሠረት የሚሆኑት እዚች የሽንገላ ንግግር በሚያሰክራት ኢትዮጵያ በተባለች አገር ነው። እንዲህ ያለ great paradox ሳይሰሙ እነማርክ እንኳንም በጊዜ ሞቱ)። ይኸው ጠሚሩ እንኳን የሰደቧቸውን ምሁራን በኮሮና ሰበብ መጥተው ይቅርታ ጠየቁ። (በበኩሌ በጥንቃቄ ስሰማው ደግመው ተሳደቡ እንጂ ይቅርታ አልጠየቁም)። በነካ አፋቸው የቀን ጅብ፣ ፀጉረ ልውጥ፣ እያሉ ያስቀጠቀጡትን ድሀ ይቅርታ ቢጠይቁ መልካም ነበር።

 

ኮሮና ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነትም ይወስነዋል። በሱዳንና በኬኒያ ኬዙ ተመዝግቧል። በሱማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በጅቡቲና በኤርትራ የሆነውን እንጃ። መቼም Rahel እንዳልሽው ኤርትራዊያን አስቀድመው ራሳቸውን ከዓለም በማግለል quarantine ስላደረጉ ዜናው አያሳስባቸው ይሆናል። ከዳያስፖራ ዜጎቻቸው ሁለት በመቶ ሲሰበስቡ የኖሩት አቶ ኢሳያስ ግን የኮረናን መሠራጨት ሲሰሙ ''ሁለት ፐርሰንት ከከፈለ ይግባ'' ሊሉ ይችላሉ... Senait ይቺን ለአብርሽ አድርሽልኝ።

 

ከኮሮና የነፃ ቅዳሜ፣ደግ ነገር የምንሰማበት ሰንበት ይሁንልን (ያየሰው ሽመልስ ከመታሰሩ በፊት በፌስቡክ ገፁ ማርች 16 የፃፈው)፡-

መጋቢት 24 እየመጣ ነው፡፡ ምጽ!...ቀን መቁጠር አይቀር፡፡ ለውጡ ክሱት የሆነበት ሁለተኛው መጋቢት ሊከሰት በኮሮና ታጅቦ እየገባ ነው፡፡ ሕዝቤ እንደ አምናው ነው፡፡ መሞቱና መፈናቀሉ እንደቀጠለ ነው፡፡ የሟቾች አሀዝ አምና ከነበረበት በ1000 ጨምሯል፡፡ አምና 2000 ነበር፡፡ አሁን ሶስት ሺህ ሆነ፡፡ የተፈናቃዮች ቁጥር ስንት እንደደረሰ እንጃ! ኢኮኖሚያዊ እድገቱ አምና ከነበረበትም አሽቆልቁሏል፡፡ 6.5 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ሠላምና ልማት የፒያሳ አራዶች ‹‹ወፍ የለም›› እንደሚሉት ያለ ነው፡፡

 

ይህ ቁጥር ከሟቾቹና ከተፈናቃዮቹ አንዱን ወንድማችን፣ እህታችን፣ ልጃችን፣ እናታችን አድርገን ካላሰብነው አይገባንም፡፡ በብልጽግና ዘመን ኑሮ ተወድዶ ሞት ረክሷል፡፡ በመደመር ጊዜ ሰው ተቀንሶ የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ ተደምረዋል፡፡ መቀጠል ከተባለ መንግሥትም ቀጥሏል፡፡ አንድም ፍትህ፣ አንድም ሠላም፣ አንድም ልማት ሳያመጣ መንግሥትም ቀጥሏል፡፡ አዎ ለውጡ ልማትም፣ ሰላምም፣ ፍትሕም ማንገስ አቅቶት ቀጥሏል፡፡

 

ሙስና ተባብሷል፡፡ የደህና አስተዳደር ጥያቄ ቅንጦት ነው፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ አንድ ሰው ሰበታ ደርሶ መምጣቱ፣ ቡራዩ ደርሶ መመለሱ ይታወቃል ወይ ነው፡፡ ወለጋን፣ ሞያሌን፣ መተማን ወዘተን እንርሳ!.. እዚህ ጫፍ፣ ከቤተመንግሥቱ 30 ኪሜ ውሎ ገባ መሄድ ይቻላል ወይ ነው፡፡

 

ሸበላው ብልጽግና ያኔ በኢሕአዴግ ስም በሚንቀሳቀስበት ሰሞን በመንግሥት ገንዘብ ‹ከመጋቢት እስከ መጋቢት›› የሚል ወፍራም ድርሰት አሳትሞ ነበር፡፡ ድርሰቱን ፎቶ አልበም ብንለው ይቀላል፡፡ አንድ ሰው ከጫፍ ጫፍ ሰው ሲያቅፉ፣ ሲታቀፉ፣ ሲስቁ፣ ንግግር ሲያድርጉ ወዘተ የሚያሳይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ልንመረቅ ስንል ከምናሳትመው መጽሔት የሚለየው የኛው ብዙ ሰዎች ያሉበት መሆኑ ነው፡፡

እኔ ግን የማልረሳት ድንቅ ንግግር በመጋቢት 24 - 2011 ሰምቻለሁ፡፡ ‹‹እኔ ከመጣሁ ወዲህ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 23 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች›› አሉ፡፡ ኦማይጋድ! ቁጥሩ አስገራሚ ነበር፡፡

 

አሀዙ በዚያ ዓመት 34 የአፍሪቃ አገራት በየግላቸው ያስመዘገቡትን ጂዲፒ ይበልጣል፡፡ የዛምቢያ፣ የቦትስዋና፣ የሞዛምቪክ፣ የኮንጎ፣ የኒጀር ወዘተ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርታቸው እኛ በዘጠኝ ወር ‹ካስገባነው 23 ቢሊዮን ዶላር› ያነሰ ነበር፡፡ ወይም ከ10 በላይ የአፍሪቃ አገራት ተደምረው ያስመዘገቡትን ጂዲፒ ይበልጣል፡፡

 

ብልጽግና ሞቅታና ውሸት የጀመረው ገና ኢሕአዴግ ሳይፈርስ ነው፡፡ እንደው በፈጣሪ 23 ቢሊዮን ዶላር ቢኖረን ዛሬ ማስክ መግዢያ ገንዘብ እናጣለን? የኢኮኖሚያችን የንግድ ሚዛን ልዩነት 17 ቢሊዮን ይደርሳል? አጃኢብ እኮ ነው፡፡

 

እና ዘንድሮ አገሩ ደህይቶ መንግሥት ግን በልጽጎ ወደዚህኛው መጋቢት እየመጣ ነው፡፡ ለዚያውም በአንድ ምሽት ቢሊየነር እየሆነ፡፡ የአገሬ ሰው ግን በወረርሽኙም በድህንቱም በሠላም እጦቱም አንገቱን ደፍቶ መጋቢት 24ን እንደ መጋቢት 23 እና 25 ከማሳለፍ ውጭ ምንም ምርጫ የለውም፡፡

 

በበኩሌ ስለ ብልጽግና ሳስብ በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ ‹‹ባለፉት 27 ዓመታት የሕወሓት ተላላኪ ነበርን›› የሚለውን የአሁኑን መሪዎቻችንን ንግግር መቼም ለታሪክ አስቀምጠነዋል፡፡ ‹‹አሁንስ ለማን እየተላላኩ ይሆን›› የሚለውን የደብረጽዮን (ዶ/ር) አሽሙረኛ ንግግርም ለታሪክ እናስቀምጠውና አንድ ጥያቄ እንጠይቅ፡፡

 

ሰሞኑን የትግራይ የብልጽግና ፓርቲ በጠቅላይሚኒስትሩ ቢሮ እንደተመሠረተና ‹‹ሕዝቡ በነፍሴ ድረሱ›› እያለ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃንም ይህንኑ ሲያፌዙበት እያየን ነው፡፡

የኔ ጥያቄ መሪዎቻችን ከአንድ ትውልድ እድሜ በላይ ሲላላኩ መኖራቸውን እንደ ሐጢዓት ከቆጠሩት አዳዲስ ተላላኪዎችን ለምን በቤተመንግሥት ውስጥ ይጠፈጥፋሉ? የሚል ነው... የብቀላው አካል ነው?

እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ በፕሮግራሜ ላይ እንግዳ ለማድረግ ያልሞከርሁት የፒፒ ሰው የለም (ከዋናው ውጭ)፡፡ እምቢ አሉኝ፡፡ መሞከሬን እቀጥላለሁ፡፡

 

እስከዛው ድረስ ያለኝ ምርጫ የአቦይ ስብሃት ነጋን ቃለ ምልልስ ክፍል ሁለት ማስኬድ ነው፡፡ አዎ የዛሬው ኢትዮ-ፎረም ከሳምንት የቀጠለውን የአቶ ስብሃትን ቆይታ ያቀርባል፡፡ አዛውንገቱ ፖለቲከኛ ከሽግግር ምሥረታ እስከ ብልጽግና ያለውን የአገሪቱን ፖለቲካ ይዳስሳሉ፡፡ አቶ Gemechu Merera Fana‹‹ኧረ በሥላሴ፣..›› የምትለው ቃልም ዛሬም ልትሰማ ትችላለህ፡፡

 

‹‹በ27 ዓመት ውስጥ የረባ ሥልጣን አልነበረኝም›› የሚሉት አቶ ስብሃት ‹‹ታዲያ የመሃል አገር ፖለቲከኛ እርስዎ በተናገሩ ቁጥር ለምን ይንጫጫል›› ስላቸው ተበሳጭተውብኛል፡፡

የጡረታ ደመወዛቸው በረሃ ከመውረዳቸው በፊት በነበራቸው የመምህርነት ሙያ የተሰላ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡እናም የብልጽግና መንግሥት ‹‹በወር 744 ብር የጡረታ ደመወዝ ይከፍለኛል›› ይላሉ፡፡
ምሽት 2፡30 ላይ ትግራይ ቴሌቭዥንን ይመልከቱ!

 

ዛሬ ቺርስ አልልም! በኮሮና ዓለም፤ችርስ ማለት የለም፡፡ በተንተን ብላችሁ ፕሮግራሜን እዩልኝ (ያየሰው ሽመልስ ከመታሰሩ በፊት በፌስቡክ ገፁ ማርች 23 የፃፈው)፡-

የዛሬው ማስታወቂያ በእጅ መጨባበጥና በትከሻ ሰላምታ መለዋወጥ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከጣሊያን ወረራ ጋር ከ1928 ወዲህ መሆኑን አቶ ጥላሁን ብርሀነሥላሴ ቤተ የ20ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያ በሚለው መፅሃፋቸው አስፍረዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የኢትዮጵያውያን የሠላምታ ባሕል አሁን ጃፓኖች እንደሚያደርጉት ከወገብና ከጉልበት ሸብረክ በማለት ያለ ንክኪ የሚከናወን ነበር።

 

አሁን የመጨባበጥ ሠላምታ ለእኛ ሥጋት ለጣልያን ደግሞ ሞት የደገሠ ክፉ ነገር ሆነ።

 

አብሮነት፣ ጋርዮሽና ትብብር ከሚያዘወትረው ነባሩ ባሕላችን ጋር የሚያላትመን ክፉ ድርጊት በራችን ላይ ቆሟል። እናም ባለመነካካት ኮሮናን ላለመተባበር እንሞክር።

ለምሳሌ እኔና አምባሳደር ስዩም መስፍን በዛሬው ኢትዮ-ፎረም አልተጨባበጥንም። ርቀታችንንም ለመጠበቅም ሞክረናል።

 

በነገራችን ላይ ይህ ፕሮግራም ከምሽት 2:00 ዜና በኋላ በትግራይ ቴቪ የሚቀርብ ነው። በጋዜጠኝነት ዘመኔ ከፖለቲከኞች ፊት ካሜራ ይዤ ስቀርብ አዳዲሳ መረጃ የማግኘት አጋጣሚዬ ጥቂት ነው። ከብዙዎቹ ጋር በሚኖረኝ ክርክር አዳዲስ perspectives and thoughts እንጂ አዲስ መረጃ የማግኘት ነገር ብዙ አይደለም። ለጋዜጠኛ ደግሞ News እንጂ History ብዙም ለዕለት ፍጆታ አይሆንም።

 

ፖለቲከኛ ከፊቴ አስቀምጬ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ ነገር ያገኘሁት አቶ ኃይለማርያም ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ የሚል መግለጫ የሰጡ ዕለት ነበር። ከአቶ ኃይለማርያም ወዲህ በርካታ አዳዲስ መረጃዎች ያገኘሁት ከአቶ ስዩም መስፍን (አምባሳደር) ጋር ሰሞኑን ባደረግሁት ቆይታ ነበር።

 

በውነቱ አንዳንዶቹ መረጃዎች የሚያስፈሩ፣ አንዳንዶቹ የሚያስቆጩ፣ ከፊሎቹ ደግሞ የሚያበሳጩ ናቸው። የግብፅና የኢትዮጵያ መሪዎች በካይሮ በዝግ የመከሩት ጉዳይ፣''ሞተው ተገኙ'' ስለተባሉት ኢንጅነር ስመኘው፣ጠሚሩ ወደ ቡጂንብራ እንዳይሄድ ስለከለከሉት የልዑካን ቡድን፣ስለ ሕዳሴ ግድብ ለመደራደር በ1988 ዓ.ም (ልብ በሉ ዓመተምህረቱን አልተሳሳትሁም) ወደ ሮም ስለሄደው ልዑክ፣በአዲስ አበባ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጁ ስላሉ ሶስት አካላት፣በአዲስ አበባ በሕቡዕ እየተንቀሳቀሰ ስላለ የአንዲት አገር የደህንነት መዋቅር፣...ወዘተ አምባሳደሩ አውርተዋል።

 

ያየሰው ሽመልስ ከመታሰሩ በፊት በፌስቡክ ገፁ የፃፈቸው እነዚህን ነው፡፡ እነዚህ ሐሳብን ከመግልፅ ውጭ የሚያሳስር ነገር አላቸው እናንተው ፍረዱ፡፡

 

ያየሰው ሽመልስ ከመታሰሩ በኃላ በፌስቡክ ገፆቻቸው ተቃውማቸው ያሳሙት ደግሞ እስቲ  እንይ፡፡

 

#ጋዜጠኛው (ነፃ ጉተማ በፌስቡክ ገፁ የፃፋው)፡-

=> ወጣቱ ጋዜጠኛ፣ ባለ ርቱእ አንደበት፣ ባለተባ ብእረኛው፣ ባለ ብሩህ አይምሮው፣ ደፋሩና ታታሪው #ያየሰው_ሽመልስ መቶ ሽሆች መቃብሮች ይቆፈሩ ተባለ ብሎ ዘገበ ተብለን አፍታ ሳይቆይ ወዲያው ደግሞ ታሰረ የሚለውን ሰማን። የኢህአዴግ ልጅ ብልጽግና ልሰርህ ካለች በውሀ ቀጭንነት ህግ አጸድቃ ልትቀፈድድህ ትችላለች። የአባቷ የኢህአዴግ ልጅ ናት። በኩርነቷን የወረሰችው ግን ደካማ ደካማውን ጎን መርጣ መሆኑ የአገራችን ያልተቋረጠ የቁልቁለት ጉዞ ህያው ምስክር ነው።


=> ጋዜጠኛው ዘገበ የተባለው መረጃ ያስከስሳል ወይ??? ያሳስራል ወይ??? ከተባለ አዎን ግጥም አድርጎ ነው የሚያስቀፈድደው። በቅርቡ የጸደቀው ህግ እንኳን በእሬሳ ገድጓድ ዘገባ ይቅርና በሬሳ ጉድጓድ ፎቶ ስር ላይክና ኮመንት መስጠትም ወንጀል ሆኖ እንኳን የመናገርን የመስማትን ነጻነት የሚያሳቅቅ አውድ ይዞ ነው ከች ያለው። እኔ በዚህ ላይ ችግር የለብኝም። ያየሰው ሽመልስን ማሰራቸውና መመርመራቸውም ችግር የለብኝም። ችግሬ ይህች አገርና የሚመራት መንግስት የዜጎች ደረጃ መዳቢነታቸው ከየት እስከየት ነው የሚለው ላይ ነው።


ካሁን ቀደም
#ብርሀኑ_ጸጋዬን የሚያክል ግፈኛና በሙስና እስከ አንገቱ የጠለቀ ሰው የአቃቤ ህጉ ጉምቱ ሆኖ እሱ ከሳሽ በሆነበት መድረክ ሙሰኛው፣ አሸባሪው፣ ነውጠኛው፣ ጥፍር ነቃዩ የአንድ ወገን ባለስልጣን ሆኖ እኩል ሲገድል፣ እኩል ሲያስርና ህዝብ ሲያስለቅስ የነበረው አካል የተደመረ ከሳሽ፣ ያልተደመረ ተከሳሽ ሆኖ የፍትህ መድረክ የፖለቲካና የስልጣን ሚዛን ማስጠበቂያ መሆኑ የሁልጊዜ ተቃርኖዬ ነበር። ሌባና ሙሰኛ፣ ግፈኛና ዘራፊ በትክክል ይጠየቅ ከተባለ የትኛው የብልጽግና አመራር ነው ነጻ??? የደህንነቱ ጉምቱ ዶር አብይ??? የኦሮምያ ፖሊስ አቶ ለማ??? የብአዴን መሪ አቶ ደመቀ???? የአማራ ክልል መሪ አቶ ገዱ??? የጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሀኑ??? የፌደራል ፖሊስ ዶር ወርቅነህ??? የረጅም ጊዜ የኦህዴድ መሪ አባዱላ??? የትኛው ነው እጁ ከደምና ከእንባ ነጻ የሆነው???? ማነው በኢትዮጵያውያን ላይ የግፍ ጽዋ ያላነሳው??? ከፌደራል እስከ ክልል ከዞን እስከ ወረዳና ቀበሌ ሁሉንም መርምር!! ሁሉም በሀያሰባቱ አመት በጎም ክፉም ስራ እስካንገቱ የጠለቀ ነው። ታዲያ ማን ከሳሽ ማን ተከሳሽ ሊሆን!!! ይህንን ስልጣን የሰጣቸውስ ማን ነው??? ያሰለጉት መንጋ ወይስ የፈበረኩት ዶክመንተሪ????


"ከናንተ ሀጢአት የሌለባት ይውገራት" ያለው የክርስቶስ ቃል ህያው ሁኖ ዛሬም ይፋረዳል። እነ ጄነራል ክንፈን ለማሰር፣ እነ አቶ በረከትን ዘብጥያ ለማውረድ፣ እነ ጌታቸው አሰፋን ለማሳደድ፣ እነ ኮሎ ገመቹን እንዲያ በገላቸው ላይ ለመቀለድ
#ብልጽግና_ማን_ነው????? እጆቹስ ምንድናቸው????


=> ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ተጽእኖ ፈጣሪነቱ እያደገ መምጣቱ በተለይ በቅርቡ ከነባር
#የህወሀት ታጋዮች ጋር በሚያደርጋቸው ቃለመጠይቆች ጠንከር ጠንከር ያሉ ሚስጥሮች መውጣት መጀመራቸው የብልጽግናን ባለስልጣናት ማስጨነቅና እንቅልፍ መንሳት መጀመሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴክሬተሪያት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የደርግን ካባ ለብሰው እሱንና ሌላኛውን ብርቱ ጋዜጠኛ #በቃል_አላምረውን ከአብዮታዊ ይቅርታ ከብልጽግናዊ መሪያችን ከጓድ ዶር ኮሎኔል ሎሬት አብይ አናት ላይ ካልወረዳችሁ አስራለሁ፣ እገድላለሁ ማለታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነበር። አልታደልንም እንጅ እንዲህ አይነት አምባገነንነት እንኳን እንደ ንጉሱ በውሸት የላቆጠ አንድ ቃል አቀባይን ይቅርና የሀገር መሪን አስከስሶ ፍርድ ቤት የሚያቆም አደገኛ የህግ ጥሰት ነበር። አገሩ እኛ ጋር ነዋ!! ልክ እንደ ዘመኑ ፓስተር መሪው ይናገራል መንጋው ያጨበጭባል። ሳር ቢያስግጥ፣ እባብ ቢያበላ፣ መርዝ ቢያጠጣ፣ ሴት ቢደፍር፣ ሀብት ቢያጋብስ ማንም ምንም እንደማይላቸው እንደ ዘመኑ ነብያት ሆነናል። ምንም ቢሆን ማንም ምንም አይልም!! ጸጥ ረጭ ያለ የቁልቁለት ጉዞ!!!


ያየሰው ሽመልስን ያሳሰረው ወይም ያሳፈነው የራሱ ድክመት፣ የተዘጋጀለት ወጥመድ ወይንስ ባልተገባ ጊዜ የዘገበው እውነት???? ቀጥለን እናየዋለን።

 

#ጋዜጠኛው_ልቤን_በላው አለ ዘፋኙ።

ቀጠልኩ...

                      

ናሁሰናይ በላይ (በፌስቡክ ገፁ ማርች 30 የፃፈው)፡-

 

ግልገል አምባገነኖች ከሁሉም በላይ የሚያስፈራቸው በራሱ የሚተማመን ብቁ ሰው ነው፡፡ አሽቃባጭነት በነገሰበት ዘመን ለእውነት መቆም ያስቀዝፋል፡፡ ያየሰው ሃጥያቱ ለህሊናውና ለሙያዊ ስነ ምግባሩ ታማኝ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ያየሰው እንደ አብይ "ትግራኛ ተናጋሪዎች፥ የቀን ጅቦች፥ ዘራፊዎች፥ ወደ አገራናቸው አባረርናቸው" ብሎ አንድ ብሄር ላይ ህዝቡ ዘር ተኮር ጥቃት እንዲፈፀም አላነሳሳም፥ አልያም እንደ ስዮም ተሾመ " ትግራይ፥ ትግራይ፥ ወያነ፥ አቶ ተወልደ፥ ጌታቸው ይባረሩ፥ እርምጃ ይወስድባቸው" እየሉ በግልፅ ዘረኝነትን በመንግስት ተደግፎ አልሰራም፥ ያየሰው እንደ ኤሊያስ መሰረት የመንግስት ተቺዎችን እያሳደደ አላሳሰረም ወይም በፌክ ኒዊስ አለርት ስም የመንግስትን ውሸት አላድበሰበሰም፡፡ ያየሰው እንደ ዋልታ ቲቪ "ዶ/ር ደብረፅየን ሞቱ" ብሎ አልዋሸ? ያየሰው ሃጥያቱ ለግልገል አምባገነኖች አለመምበርከኩ ነው፡፡ ትግራይን ያለ ወዳጅ እናስቀር ሲሉ አፈር ቃሙ ከህዝቤ ጋር አልጣላም ማለቱ ነው፡፡ ያየሰውን በጥቅም ለመደለል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፥ ትላልቅ ባለስልጣናትም ቢሮ ድረስ ጠርተው አስፈራርተውታል፥ ደህንነቶች በክትትል ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ልጁ አልተሰበረም፡፡ እንገድልሃለን ያለው ንጉሱ ጥላሁን በስተመጨረሻ አስሮታል፡፡ ፈሪ አምባገነን ሃሳብን ይፈራል፡፡ ያየ ደግሞ ባለ ትልቅ ሃሳብ ነው፡፡ ክብር ይገባሃል ወዳጄ፡፡ የደደቦች ጥርቅም ሰለባ መሆንህ ያንገበግበኛል፡፡ ይህም አልፎ እናየዋለን!

 

#ጋዜጠኛው (ነፃ ጉተማ በፌስቡክ ገፁ የፃፋው)፡- ክፍል ሁለት

 

=> ወጣቱ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በህግ ጥላ ስር ከሆነ ቀናት አልፈዋል። ለምን ታሰረ የሚለው ጥያቄ በብዙዎች መላምት ውስጥ የሚንገዋለል የምናብ መቂናጥ ሆኗል። እኔም ከዚህ ተነስቼ የራሴን አተያይ ከተብኩ።

 

ጋዜጠኛውና ብልጽግና:-

1-ጋዜጠኛው ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ሲሰራበት የነበረው የሚዲያ ተቋም በለውጡ ሀይል በክፉ አይን የሚታይ፣ በወያኔ ልሳንነት የሚፈረጅ በለውጡ ዋዜማም መንጋውን ትቶ በራሱ የእውነትን ጭላንጭል ለመዘገብ ስለሞከረ የለውጡ ሳንጃ የተመዘዘበት ተቋም ነበር። የወቅቱ ተፋላሚ የነ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ቡድን ዋንጫውን አንስቶ ቻምፒዮን ሲሆን ያንን ተቋም አንገቱን በጥሶ ለመጣል የወራት ትእግስት እንኳን አልነበረውም። እናም የመደመርና የነ ያየሰው ፍትጊያ እዚያ ላይ ጀመረ።


2-ይቅር ባይ ነኝ እያለ የሚዘምረው ነገር ግን በቂምና በበቀል ያበደው የለውጡ ሀይል የራሱን ቤት ሲያቃጥል የተቃወሙትን ሁሉ አያደነ መቆልመሙንንያየነው ጉዳይ ነው። የያሰውም ከብልጽግና ጋር የተያያዘው አንገት ለአንገት ትግል ሊያስቆለምመው እንደሚችል ከአቶ ንጉሱ አንደበት የወጣው ዛቻ በቂ ምልክት ነበር።

3-ያየሰው ሽመልስ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ስዩም መስፍንን ቃለመጠይቅ ካደረገላቸው በኋላ ወትሮም በያየሰው ላይ ደሙ ሲፈላ፣ ሲዝትና ሲያስፈራራ የነበረው ብልጽግና አንዳች ምክንያት ፈልጎ ልሳኑን ለመዝጋት ወጥመድ ለመዘርጋት ሲሯሯጥ እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነው።


የጋዜጠኛው የመታሰሪያ ጭብጥ ምንድነው????

 

1-ያየሰው ሽመልስ አስተላልፎታል የተባለው መረጃ የውሸት ዜና ቢሆን፣ ዜናውን ከመለጠፍ ይልቅ ለሚመለከተው ክፍል ማሳወቅ ነበረበትና ህዝብን በማሸበር ያስከስሰዋል።
2-ጋዜጠኛው ያስተላለፈው ዜና እውነት ቢሆንም ከፍተኛ የመንግስትና የደህንነት ምስጢር (Classified file) በመሆኑ እንደ አንድ ዜጋ ዜናውን ከመለጠፍ ይልቅ የበለጠ መረጃ በመሰብሰብ ጊዜውንና ሁኔታውን ጠብቆ ከመንግስት አካላት ማብራሪያ መጠየቅ ነበረበትና ያስከስሰዋል።
3-የጋዜጠኛው ዜና በመንግስት የተዘረጋ ወጥመድ ቢሆንም ከወቅቱ ጋር አደገኛና ህብረተሰቡን ቫይረሱን ከመከላከል ሂደቱ ተስፋ አስቆርጦ አደጋ ላይ ይጥላልና፣ በወጥመዳቸውም ሰተት ብሎ ገብቷልና ሊያስከስሰው ይችላል።


ጋዜጠኛው ልቤን በላው!! አለ ዘፋኙ።


በየትኛውም መለኪያ በብልጽግና አይን እንኳን ይህንን የሚያክል የገዘፈ ወጥመድ ውስጥ ዘጭ ያለ ሰው ይቅርና እነ ኮሎኔል ገመቹ አያና፣ እነ ዶክተር ቢንያም ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ተልካሻ ምክንያት ብቻ የግፍ ነዶ ወርዶባቸው ተጠርተው እንደታሰሩ ተጠርተው ተፈተዋል።


እኔን የሚያሳስበኝና ብእሬን ያስነሳኝ ግን ይሄ አይደለም። በአንድ ሀገር ላይ፣ በአንድ አይነት ወንጀል ዜጎች የሚከሰሱበት ልዩነት ነው። የዜጎች ማንነት የደረጃ ዜግነት መሆኑን እስከምጠራጠር ድረስ እኩል ዘርፈው፣ እኩል በስብሰው አንደኛው አሳዳጅ ሆኖ ጎፈር ነስንሶ ያሳድዳል፣ ሌላኛው ዜጋ ከሱ አልፎ በሚነዛበት ውንጀላ መሰሎቹ ደማቸው እንደ አቤል ደም፣ እምባቸውም እንደ ራሄል እምባ በከንቱ ይፈሳል። ይሄ ክፉ አባዜ ብልጽግና ከኢህአዴግ የወረሰው ክፉ ልክፍት ነው። ብርታቱንና በጎ ጎኑን ግን በዞረበት አልዞረምና ኢህአዴግ ክፋቱን በተወሳሰበ መንገድና በጠንካራ ክንዶች ሲከውን ብልጽግና ያንኑ ክፋት በቀላል መንገድና በደከመ ብቃት ይከውነዋል። የሩቁን እንተወውና በቅርቡ እንኳን ከስዩም ተሾመ እስከ እህተ ማርያም፣ ከአቶ ንጉሱ እስከ አቶ ታዬ፣ ከአቶ ጃዋር እስከ አቶ ነብዩ የተናገሩት ቢመረመር በራሱ በብልጽግና ሚዛን ቢመዘን እንደ ያየ ሰው ሁሉ ዘብጥያ የሚያወርድ የወህኒ በሮችን በላይ ላይ የሚያስከረችም ነበር። አሁን ያየሰው ለምን???? ለህዝብ ተወግኖ ወይስ የመሪዎቻችን የፖለቲካ ቆሽት በግኖ???? ያየሰውን ያስወነጀለ የዜግነት ግዴታ በሌሎቹ ላይ ያጎናጸፈው የዜግነት መብት ደረጃው ምን ነበር???


ይሄ ነጥብ ዛሬም ሌላ የውዝግብ ሌላ ያለመተማመን መድረክና ምእራፍ ይከፍታል። ትናንት መደመርን
#ከህወሀት ጋር አላትሞ በኋላ #የትግራይን ህዝብ ከልቡ አሳጥቶ የነ አቶ ነብዩ መጫወቻ ያደረገው ይሄ ክፉ ውርስ ነው። የነ ጃል መሮን ልብ አሸፍቶ ወለጋን ሆድና ጀርባ ያደረገው ይሄ ክፉ ልክፍት ነው። ዛሬም የዜግነት ልኬት እንዲህ ትርጉም አልባ ሆኖ አንዱን ሰይጣን ሌላኛውን መልአክ ማድረጉ በያየሰው ቢገለጥ አሁን ያየሰው ከመንጋው ጋር አይደለምና የሚጮህለት አካል ላይኖር ይችላል። ይህ ክፉ አመል ይህ ክፉ ደዌ ግን ነገ ከነገ ወዲያ የኢትዮጵያን ህዝብ በብልጽግና ተቃራኒ በታላቅ ቁጣ እንደሚያሰልፈው ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። ዝቅጠት እንደ #ኮሮና ከአንገት ሳይወርድ ሊታከም ይገባዋል። ካለዚያ ሳምባ ውስጥ ገብቶ ትንፋሽን ይቆርጣል።

 

ብልጽግና ሆይ ለራስህ ስትል ስማ!!!

ካለዚያ ማንነትህን እየተረክልን ነው!!!

ዛሬ እየነገርኩህ ነው፣ ነገም እነግርሀለሁ።

 

ቀጠልኩ።

 

ከዚህ ከላይ የፌስቡክ ፅሑፎች የትኛው ያየሰው ሽመልስን ሰበብ ሆኖ ወይም ምክንያት ሆኖ አሳሰረው? እንመርምር። የኔ አስተያየት ደግሞ በክፍል ሁለት እገልፃለሁ። ቸር እንሰንብት።

 

Back to Front Page