Back to Front Page

ያየሰው ሽመልስ ማሰር በነፃ ሃሳብን የመግለፅ ላይ ጥቃት መፈፀም ነው።ክፍል ሁለት

ያየሰው ሽመልስ ማሰር በነፃ ሃሳብን የመግለፅ ላይ ጥቃት መፈፀም ነው።

ክፍል ሁለት

ጋዜጠኛ ያየሰው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈታ!

ከእንዳለ ዘለቀ

ከመቐለ

04-11-20

 

መጋቢት 18 ከለገጣፎ በጥዋቱ ታስሮ የተወሰደው ጋዜጠኛው ያየሰው ያለፍርድቤት ትዕዛዝ ነበር። ለምን እታሰራለሁ? ምን አጠፋሁ? ሲላቸው ህዝቡን አሸብረሃል። መንግስት ይህን ያህል ጉድጋድ ይዘጋጅ ብሏል ብለህ ሐሰተኛ ዜና አሰራጭተሀል አሉት። የያዙት ደግሞ ዩኒፎርም የለበሱና ያልለበሱ የደህንነት መስርያቤት ሰራተኞች የሚመስሉ ሰዎች ናቸው። ያየሰውም ከኪሱ ወረቀት አውጥቶ መንግስት ጉድጋድ እንዲቆፈር ያዘዘ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃውን እንዲያነቡ ይሰጣቸዋል። አንብበው ሲጨርሱ ሊከሱት የፈለጉትን ማስረጃ ገና ከጅምሩ ዋጋ እንደሌለው ቢገባቸውም ድርቅ ብለው ማዕከልዊ ወስደው አሸጉት።

ማስረጃውን ለማጥፋት መረጃ ብርበራ በሚል ሰበብ ቤቱንና ኮምፒተሩን በረበሩ ሌላ የሚሰሩትን ሰርተው በሁለት ጉዳይ ላይ ክስ መስርተውበታል። አንደኛ የመንግስትን ስም በማጉደፍ እና ሁለተኛ በሽብር ወንጀል በሚሉ ክሶች የመዝገብ ምርመራ ተደረገበት ተባለ። ፍርድቤትም ቀረበ። ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ይሰጠን በሉት መሰረት ፍ/ቤቱ ሁለት ጊዜ ቀጠሮ ሰጣቸው። ተጨማሪ ምርመራ በጋዜጠኛ ላይ? የፃፈውን ይዞ ለመክሰስ ምን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ያስፈልገዋል? ነው ጥያቄው፡፡

Videos From Around The World

ያየስው ሽመልስ እኔ እሰከማቀው ድረስ ቢያንስ በሚድያ ለውጥ ተደርል ባይ ከሆኑት ጋዜጠኞች የሚመደብ ነው። ጋዜጠኛ ያየሰው ENN ተዘግቶበትም ከናሁም በቀጭን ትዕዛዝ ቢባረርም ሚድያ ላይ ለውጥ አለ ከሚሉት ወገን ነው። ንጉሱ ጥላሁን እሱንና ወዳጆቹ የሆኑት በቃሉንና አንሙትን ማስፈራርያ ቢሰጣቸውም በሚድያማ ለውጥ አለ ብሎ ያምን የነበረ ጋዜጠኛ ነው። የደህንነቱ ሐላፊ ደምመላሽ የምታስተላልፈው ፕሮራምና ቦታ ከትግራይ በመሆኑ በጎ ስሜት እንደማይሰማው ገልፆ በህይወቱ ለሚደርስበት ችግር ተጠያቂ እንደማይሆን ደጋግሞ ቢገልፅለትም ያየሰው ሽመልስ በሚድያማ ለውጥ አለ ብሎ ነፃነቱን አውጆ ያመነበትን ሲፈፅም መጋቢት 18 በለገጣፎ ተያዘ።

ኢንጅነር ስመኘው የገደለ ማን ተጠያቂ ሆነ? ጀነራል ሰዓረና ገዛኢን የገደሉ መቼ ተጠያቂ ሆኑ? ዶ/ር አምባቸውና ምግባሩን የገደሉ መቼ ተጠየቁና ነው ደምመላሽ ተጠያቂ አንሆንም የሚለው? ጋዜጠኞቹስ ሊገደሉ እንደሚችሉ እንዴት አወቀ? ጁሃርን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ምክንያት የጣፋው የቡዙ ሰው ህይወት ማን ተጠያቂ ሆነና? ለነገሩ ነው እንጂ ጁሃር ራሱም ህይወቱን ለማዳን የደረሱለትን ወጣቶች የገደሉ ወይም ለግድያው ምክንያት የሆኑ ተጠያቂ ናቸው ያላቸው ኮ/ል አብይም የደህንነቱ ሹሙ ደምመላሽን መቼ እንዲጠየቁ ተከራከረ? ጆሃር ከሞት ከዳነ በኃላ በሽምግልና ፋይሉን አልዘጋውም እንዴ? ያየሰው ተንታኙ በሚድያ ለውጥ አለ ብሎ ከልቡ አምኖ የመሰለውን ያመነበትን በማስረጃ ተደግፎ ይፅፋል። ይተነትናል። ያቃሉ የሚላቸውን ሰዎች ጋብዞ ይጠይቃል። ይሞግታል፡፡ ይከራከራል።

አንዴ የያዝከውን ስልጣን እንዴት ትጠቀምበታለህ? ቂምህን የምትውጣበት ሊሆን ይችላል። ሰው ፈርቶ ያልከውን አሜን ብሎ እንዲቀበል ልታደርገው ትችላለህ። የስልጣንህ ዕድሜ ሊረዝምበት የሚችል ሁኔታ ለመፍጠር የተቻለህን ሁሉ የምታደርግበት አድርገህ ልትጠቀምበት ትችላለህ። ኮ/ል አብይ እስካሁን ስልጣናቸውን እንዴት ተጠቀሙበት? የህዝብን ችግር ለመፍታት ምን ያህል ተጠቀሙበት? ልማት ለማስቀጠል ምን ያህል ተጠቀሙበት? ዲሞክራሲ ለማስፋፋት ምን አደረጉበት? የሚሉት ጥያቄዎች ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መጠየቅ የሚገባው ነው፡፡ በተለይ ሁሉም ጋዜጦኞች በተለይ ደግሞ እንደ ያየሰው የመሳሰሉት ጋዜጦኞች በድፍረት ሊጠይቁዋቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

መድፈር ያስከስስ ይሆናል? ዕድሜ ያሳጥራል? መፍራትስ ዕድሜ ያስረዝማል? በአገራችን አሁን ትልቁ ወንጀል ትግራይ መሄድ ነው? ቪዛ ማግኘት ያስፈልግ ይሆን ትግራይ ለመሄድ? በቀለ ገርባ፣ አስፋ ወዳጆና ብዙ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ትግራይ ለምን ሄዳቹህ ተብለው በአደባባይ ተጠይቀዋል። ማስፈራራት እንግልት እንዲደርሳቸው ተደርገዋል። ትግራይ መሄድ ብልፅግናን ለውጡን እንደ መቃወም ይታይ ይሆን? ያየሰውም በድፍረት ገሃድ ሀቅ የሆነውን እንዳለ በማቅረቡ ሳይፈራ ሳይሸፋፍን ለህዝብ ይፋ በማድረጉ ባለማጨብጨቡ በድፍረት ያለ ፍቃድ ያለ ቪዛ ትግራይ በመሄዱ ይሆን ዘብጥያ ወርዶ የምርመራ ጊዜ እየተራዘመበት ያለው? ውጭ ሆኖ መከሰስ አይችልም ነበር? ምንኛ አደገኛ ወንጀል ፈፅሞ እንዳያመልጥ ተፈርቶ ነው በእስርቤት እንዲቆይ እየተደረገ ያለው? ወይስ ለውጡ ተቀልብሷል? ያውም ከነበረ??????

ያየሰው ሽመልስ የተከሰሰበትን ጉዳይ እንይ። የመንግስት ስም ማጥፋት የሚለው ስናየው ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያደርገናል። መጀመርያ መንግስት ማን ነው። ኮ/ል አብይ? ፓርላማው? ፍ/ቤቱ? አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ? መንግስታዊ ስልጣን የጨበጠ አካል በበጎም በመጥፎም ስሙ ማንሳት የተለመደ ጉዳይ ነው። ዲሞክራሲ ካለ ያለምንም ፍርሃት መደገፍም፣ መቃወም፣ መተቸትም ይቻላል። ዲሞክራሲ በሌለበት ተደብቆ ማማት ሲብስ ደግሞ ተናግሮ ወይም ፅፎ እስርቤት መታጎር የተለመደ ነው። ዲሞክራሲ በሌለበት በነፃ አለመናገር ብቻ ሳይሆን በአደባባይ እንድታሞግስም የምትገደድበት ስርዓት ይዘረጋል። ከዚህ አቅጣጫ ወጣ ማለት ያስከፍላል። እንደ በዓሉ ግርማ ያስገድላል።

ያየሰው የመንግስትን ስም አጥፍቷል? ከፃፋቸው ከተናገራቸው ቃለመጠይቅ ካደረጋቸው ጋር ሲከራከር ስም አጥፍቶ እንደሆነ እንመርምር? አቶ ኢሳያስን ሁለት ፐርሰንት ከከፈለ ይግባ ሊሉ ይችላሉ የኮረና መሰራጨት ግድ አይላቸውም በማለቱ ይሆን? ወይስ መጋቢት 24 እየመጣ ነው። ምጽ!...ቀን መቁጠር አይቀር። ብሎ የሞቱት ሦስት ሺ ደርሷል። ተፈናቃዮችም ስንት እንደደረሰ አላቅም። ኢኮኖሚ ዕድገት አሽቆልቁሏል። ሰላምና ልማት የለም። ብሎ በፌስቡኩ መፃፉ ነው ወይስ የኮ/ል አብይን ስም አግዱፏል። ለውጡን ጥላሸት ቀብቷል። ተብሎ ነው የተከሰሰው? ወይስ በመጋቢት 24 2011 የኮ/ል አብይ ንግግር የጠቀሰው እውነት አይደለም? እኔ ከመጣሁ ወዲህ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 23 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች ብለዋል የተባሉት ኮ/ል አብይ ይህን ቃል ብለውታል ወይስ አላሉትም? ያየሰው ሾርት ሞመሪ ቢኖረው ይህን አያስታውስም ተብሎ ተወንጅሎ ነው? ደግሞ ክፋቱ ትንታኔው ነው። አሀዙ በዚያ ዓመት 34 የአፍሪቃ አገራት በየግላቸው ያስመዘገቡትን ጂዲፒ ይበልጣል፡፡ የዛምቢያ፣ የቦትስዋና፣ የሞዛምቪክ፣ የኮንጎ፣ የኒጀር ወዘተ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርታቸው እኛ በዘጠኝ ወር ካስገባነው 23 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነበር፡፡ ወይም ከ10 በላይ የአፍሪቃ አገራት ተደምረው ያስመዘገቡትን ጂዲፒ ይበልጣል፡፡ የሚለው ሰለዘገበና ያየሰው በጣም አልተዳፈርክም? በሚል ነው፡፡

መዳፈር /defamation/ በውሸት ወይም ባልተረጋገጠና ማስረጃ በሌለው መንገድ የአንድን ሰው ወይም አካል ጥሩ ስም ወይም ዝናን ማጉደፍና ጭቃ መቀባት ማለት ነው። ያየሰው እንደ ጋዜጠኛ የሚደነቀው ለሚያደርግው ቃለመጠይቅ ተዘጋጅቶ፣ በተወሰነ መልኩም ማስረጃም ጥናትም አድርጎ ስራውን ሰለሚሰራነው ነው። ማይክሮፎን ጨብጫለሁ ወይም ፌስቡክ የግሌ ነው ብሎ ያገኘውን ኢንፎርሜሽን ጫፍ ይዞ የሚናገር ወይም የሚፅፍ ጋዜጠኛ አይደለም። ደፋር እንጂ አጉል ጀብደኛ አይደለም። እውነትን መደባበቅ የለብንም ባይ ነው። ከፒፒ ለቃለመጠይቅ ፍቃደኛ የሚሆን ስላጣ ስዩም መስፍን፣ ልደቱ አያሌው፣ ወንድወሰን ከበደ እና . . . ወዘተ እያቀረበ የኮ/ል አብይን፣ የፒፒን ወይድግሞ የለውጡን ዝና እያጎደፈ ነው የሚል ከሆነ ሰበቡ በያየሰው ሚድያ ቀርቦ መሟገት እንጂ መልእክቱን ስለጠሉ መልእክት አቅራቢውን ለመበቀል ማሰር ዲሞክራሲ ላይ ጥቃት መፈፀም ነው፡፡ ነፃ የሃሳብን መግለፅ መብትን ማፈን ነው። የትኛው ዝና ጥሩ ስም ነው ጭቃ የተቀባው? ህዝቦች አልተፈናቀሉም? አልተገደሉም? አልታሰሩም? አገሪቱ ከስልሳ በመቶ ህጋዊ ባልሆነ አስቸካይ ግዜ አዋጅ ስር አልወደቀችም? በአብይ የምትተዳደር ኢትዮጵያ ሰላም የሌላት አገር አልሆነችም? ኢኮኖሚዋ ላሽቆ እየፈራረሰ አይደለም? የውጭ ሃይሎች እጅ የበዛባት፣ ነፃነትዋ፣ ላዕላዊነትዋ የተደፈረች አገር አይደለችም አሁን? ይህን እውነታ ለመግለፅ ሌሎች ሚድያዎች ቢቸገሩና እንደ ያየሰው ለእውነት የቆሙ ቢገልፁ እንደስም ማጥፋት እንዴት ተብሎ ያስከስሳል። ታድያ ነፃ ሚድያ ህወሓትን የትግራይን ህዝብ መስደብ ብቻ ነው መመዘኛው። ኮ/ል አብይ ባሌ ሄደው ያሰሙትን መርዛማ ንግግር ያስተላለፉ ጋዜጠኞች ለምን አልተጠየቁም ታድያ? ኮ/ሎች ስናስር ጀነራሎች (እነ ጄነራል ሰዓረ/ ብርሃኑ / አስራት) ምንም ማስፈታት አልቻሉም ያለውን አሸባሪው ተፈራ ማሞን ዝም የሚልና በሚድያ እንዲተላለፍ የሚፈቅድ መንግስት ተደፈረኩ ብሎ ጋዜጠኞ ያየሰውና ሌሎች ጋዜጠኞች ማሰር ምን አመጣው? ወይም ጋዜጠኞች ምን ማለት እንዳለባቸውና ምን ማለት እንደሌለባቸውም የኮ/ል አብይ መንግስት በግልፅ ያውጅ። ሳንሱርም በግላጭ ስራ ላይ እንደዋለ ለሁሉም ይግለፅ። የደህንነት ሹሙ ስልክ እየደወለ ዛሬ ምን ታስተላልፋላህ? ንገረኝ ለማለት የሚያስችል ህግም በይፋ ይውጣ።

ሁለተኛው ጋዜጠኛው ያየሰው ሽመልስ የተከሰሰበት በሽብርተኝነት ጉዳይ ነው። ሁለት መቶ ሺ ሰው በኮሮና ወረርሽኝ ሰበብ ሊሞት ይችላል ብሎ መንግስት የመቃብር ጉድጋድ እንዲቆፈር አዘዘ ብሎ አጭር በድምፅ የተደገፈ ዜና በማህበራዊ ሚድያ ዘረጋ የሚል ክስ እንደተመሰረተበት ታውቃል። መጀመርያ መንግስት ይህን መረጃ ሲያተባብል አልተሰማም። መንግስት ባላስተባበለለት ሁኔታ ያየሰው እንዴት ሊጠየቅ ይችላል? መንግስት ተብዮው ይህንን መረጃ በድብቅ ይዞ ዝግጅት እያደረገ ከነበረ ደግሞ ዝግጅቱ ያስመሰግነዋል እንጂ የሚያስወቅሰው አይሆንም። የሚያስወቅሰው ለህዝቡ ግልፅ አለማድረጉ ብቻ ነው። ሰለዚህ ያየሰው ሲያዝ ለያዙት ሰዎች መንግስት መቃብር ጉድጋድ እንዲቆፈር ማዘዙን የሚያስረግጥ የመንግስት ደብዳቤ በእጁ መያዙን ሲያሳያቸውና የደብዳቤው ምንጭ ሲያቁ ለምን ይቅርታ ብለው አልለቀቁትም? ወይስ ደብዳቤው ሆን ተብሎ በነደምመላሽ የደህንነቱ ሹመኛ ተፅፎ የተሰጠው ከሆነ ደግሞ ሌላ ወንጀል በመንግስት ባለስልጣን እየተፈፀመ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ያየሰውን ያሰሩ ሰዎች ወንጀለኞቹ እነሱ ስለሆኑ ጋዜጠኛውን ፍትተው እነሱን ቢከሱ በተገባ ነበር። የኮረና መድሃኒት አግኝተናል ብለው ህዝቡ በንቃት እንዳይከላከል ያወጁት የብልፅግናዎቹ አብርሃም በላይና ሊያ ታደሰ በህግ ያልጠየቀ መንግስት ጋዜጠኛ ያየሰውን እንዴት ለመጠየቅ ሞራል ያገኛል። ይገርመኛል፡፡

ያየሰው በግፈኞቹ እንደታሰረ ለምን ትግራይ ሄድክ? ስንት ብር ነው የሚከፍሉህ ተብሎ ተጠይቓል። ለአቶ ስዩምን ለምን ቃለ መጠይቅ አደረግክለት? ስንት ከፈለህ? ተብሎ ተጠይቃል። ያየሰውም ለገንዘብ ክፍያ ቢሆንማ ከናንተ ብሰራ ሚሊዮን በተከፈለኝ ብሎ መልሶላቸዋል። ኮ/ል አብይ ይህን ፕሮግራም በጥሞና ይከታተሉታል። የአቶ ስዩምን ቃለመጠይቅ በትዕግስት ማዳመጥ አልቻሉም። በንዴት ተቃጥለዋል። ውርደት ተሰምቷቸዋል። ደግሞ ኮ/ል አብይን የሚጋብዘው የአቶ ስዩም መስፍን ቃለመጠይቅ ከባድ ነው። የህዳሴው ግድብ ጉዳይ አሜሪካ ወስደው ከግብፆች ጋር በሚስጥር የተነጋገሩበትን ለህዝብ በድፍረት ይግለፁ ተብለው ተጠይቀዋል። ይህ ቁሽታቸውን እንዳቃጠላቸው ብግን ብለው እንደተናደዱ ይታወቃል። ጁሃር ላይ እርምጃ ውሰድ ብለው ባዘዙት ሚስጥራዊ ስልካቸው ደምመላሽን አግኝተው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን እስርቤት ክተትልኝ ብለው በቁጣ አዘዙ። አረ እንካን አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድበት አላሉ። ራሱ ገደለ ቢሉን ምን እንል ነበር? ለአንድ ሳምንት አውርተን ፎክረን ይጣራል ብለው ሊያስተኙን ይችሉ ነበር።

ጋዜጠኛ ያየሰው ፖለቲካዊ እስረኞች እንደሆኑት እንደ የሜቴክ፣ የደህንነት፣ የፌደራልና የማረሚያ ቤት ፖሊሶች የፖለቲካ እስረኛ ነው። ይህንን የተረዱትና ቢዘገዩምና መርጠው ቢሆንም መግለጫ ያወጡት የአሚኒስቴ ኢንተርናሽናልና ሲፒጂ ሳላመሰግናቸው አላልፍም። የጋዜጠኛ ያየሰው መታሰር ግን ያገሬ ጋዜጠኞችን ለትዝብት የዳረገ ክስተት ሁናል። ትንፍሽ አላሉም። በነፃ ጋዜጠኝነት ሽልማት የወሰደው ሪፖርተርም ጭምር! እናንተየ ኢጋማ ግን በህይወት አለ? ከሌሌ ነፍስ ይማር!

ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!

ኮረና ቫይረስን በተመለከተ ለህዝብ ከልብ ያስተማረው ያነቃቃው ያየሰው ይፈታ!

ህገ ወጡ መንግስት ይውረድ!

ስልጣን በህገመንግስት መሰረት ይመስረት!

በስብከት ወረርሽኙ መከላከል አይቻልም!

ተጨባጭ እርምጃ በተግባር እየወሰዱ በግል ከልብ ሲፅልዩ እንጂ ለታይታ የሚደረግ ስብከት ከፕሮፖጋንዳነት አያልፍም!

ፈጣሪ ይጠብቀን።

ቸር ሰንብቱ።

 

Back to Front Page