Back to Front Page

የጫጉላ ሽርሽር ሲያበቃ....

 

የጫጉላ ሽርሽር ሲያበቃ....

ከአብሳር 06-21-20

የጫጉላ ሽርሽር ሲያበቃ ከእውነታ መጋፈጥ አይቀሬ ነው ። የአብይ መንግስትም ኮምጣጣ የፖለቲካ እውነታ ሊጋት ተገደዋል ። ይህ መንግስት ከሌሎች ገዢ መደቦች የተለየ ባለመሆኑ ዕጣው ተመሳሳይ ነው። ዛሬም ስለ አገራችን የፖለቲካ እውነታ አብረን እናወጋለን ።

ሰሞኑን የሲዳማ ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ዕድል በመጠቀም የራሱን መንግስትና ክልል ማቆም በመቻሉና ለህገመንግስቱ ጽኑ ጥብቅና በማሳየቱ ያለንን ጥልቅና ትልቅ ክብር እንገልጻለን። የጦና ልጆችም ይሁን ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ህገመንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም መብታቸውን እንዲያስከብሩ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ዲሞክራሲ እክል ያጋጥመው እንደሆነ እንጂ ወደኋላ የተመለሰበት ታሪክ የለም። አራት ኪሎ የተሰባሰቡት አሃዳዊ ጨፍላቂ ፀረ ህገ መንግስት ሃይሎች አይሳካላቸውም የምንለው ከሁለንተናዊ የታሪክ ጉዞ አንጻርም ጭምር በማየት ነው። ሌላው ለዜና የበቃው ጉዳይ የአገር ሽማግሌዎች ሰላም ለማውረድ ያደረጉት ጥረት ነው። አገራችን የፖለቲከኞች የግል ንብረት አይደለችም። በአገራችን ጉዳይ ላይ ሁላችንም ይመለከተናል። ከዚሁ አኳያ የሽማግሌዎቹ እርምጃ ሊያስመሰግናቸው ይገባል። ብዙ ወገን የረሳው ነገር ቢኖር ግን በኦሮምያ እየደረሰ ያለው እልቂት ነው። በኦሮምያ እየሆነ ያለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳስበው በተገባ ነበር። ቤተ መንግስት የተሞሸሩ የትላንት ተሸናፊዎች የኦሮሞ እና የትግራይ ብሄረተኞች እንዲመቱላቸው ከበሮ እየደለቁ ይገኛሉ። አብይን የሚደግፉት በእነሱ አነጋገር እዛና እዚህ ያሉትን እሾሆች እንዲነቅልላቸው ነው። በእሾህ የሚመሰሉት ደግሞ ህብረብሄራዊነትን የሚያቀነቅኑት ነው።

Videos From Around The World

የአገራችን ታሪክ እንደሚያስተምረን በፖለቲካ አንዴ መሰረታዊ ስህተት የፈጸመ ዳግም ለማስተካከል የማይቻል መሆኑን ነው።መንግስቱ ሀይለማሪያም ስድሳዎቹን ከገደለ በኋላ መልሶ ሊያገግም አልቻለም። አቶ አብይም የጫጉላ ዘመኑን ለተሸናፊ የደርግ አባላት፣ ለስደተኛ አዛውንት ፖለቲከኞች፣ለታሪካዊ ያገራችን ጠላቶች አሳልፎ በመስጠቱና ምዕራባዊያንን ለማስደሰት ቅድሚያ በመስጠቱ ሞቶ የተወለደ ጨቅላ አምባገነን ሆኗል። የትግራይ ብሄራዊ መንግስት ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑ ሁሉም ወገን ሊደግፈው ይገባል። የአገራችን ህዝቦች አንድ የዲሞክራሲ ደጀን ያስፈልገናል።አሁን የአሀዳዊ ሃይል ካሸንፍ የምንታገለብት ወረዳ ያስፈልገናል። የተደማሪው ቡድን በትግራይ ምርጫ የመረረ ቁጣ የሚመነጨው የዲሞክራሲ ወገን ሁሉ ለመንቀል ያለውን ህልም ስለሚያጨናግፍበት ነው። የትግራይ ምርጫ ለሁሉም አምባገነን ስጋት ነው። ጉዳይ በምስራቅ አፍሪካ በዲሞክራሲና በጸረ ዲሞክራሲ ሀይሎች መካከል በማካሄድ ላይ የሚገኘው ትግል አካል ነው ። አሰላለፋችንም ከዚህ አንጻር ማየት ተገቢ ይሆናል። አገራችንን ከዲሞራሲያዊ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ውጭ ልናገኛት መመኘት የቀን ህልም ነው። ከህዝባዊ ምርጫ ውጭም የህዝብ ይሁንታ ማግኘት አይቻልም።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ወቅታዊነቱን እንዳገኘ ነው። የአቢይ መንግስት በድርድሩ የኢትዮጲያን ጥቅም ማስጠበቅ ሲያቅተው ያልሆነ ሽመና ጀምሯል።ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በመደረግ ላይ ያለው ድርድር ፋይዳ የለውም ። በእውነት ከሆነ አብይ ካይሮ በሄደበት ግዜ አሳልፎ ሰጥቶታል። ዛሬ የሚደረገው ውይይት የኮሮና ማስክ ነው ።በጉዳዪ ላይ የብዙ ባለሙያዎችን ምክር በመርገጥ ወደ ዋሽንግተን የወሰደው ራሱ ነው። ጉዳዩን የሚከታተሉ ተደራዳሪዎች የተለየ አስተያየት ነበራቸው።ዛሬ ደርሶ ባንዳ ፍለጋ ምን የሚሉት ፖለቲካ ነው? አገሪቱ መሪ የላትም ። ዛሬ በአገራዊ ጉዳይ ላይ መሰባሰብ ሲገባ እከሌ ባንዳ ነው መባባሉ የተመረጠ የሳምንቱ ነጠላ ዜማ ሆኗል። ለነገሩ የአሁኑ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ይልቅ የኤርትራውን አቶ ኢሳያስን የበለጠ ያምናል።አገሪቱ ቅኝ ተይዛለች። ነጻ የሚያወጣን እንፈልጋለን። መከላከያ እንደሆነ ተላላኪ ሆኗል። አሁን ደግሞ የተጣሉ ፖለቲከኞች ተፈልገው ትንሽዬ የፕሮፖጋንዳ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተጋበዙ ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ አትሽጡት ሲባሉ ለመሽጥ የተገደድነው ከኛ በፊት የነበሩ ሃላፊዎች አፋጥነው ስላልሰሩት ነው የሚል ሲበዛ ደካማ ፕሮፖጋንዳ ጀምረዋል ። እነዚህ አይነቶቹ ሰዎች ደግሞ በአቶ ጌታቸው አገላለጽ skillful survivors ይባላሉ።መሰል ሰዎች በሁሉም የታሪክ ወቅቶች የሚያጋጥሙ ናቸው።

በአገራችን የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ የፈጠረው የአራት ኪሎው የተደማሪ ቡድን መንግስት ነው። ተደማሪው ቡድን እስካሁን በሴራ ፖለቲካ ዕድሜውን ለማራዘም ሲሞክር ነበር። በዲሞክራሲ የሴራ ፖለቲካ ሩቅ አያስኬድም። ሴራውን ማየት የግድ ይላል። አብይ በኤርትራ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋር በመገናኘት መረጃ ይሰጥ እንደነበር አሁን የአደባባይ ሚስጥር ነው። አብይ የአገራችንን ሚስጥር ለኤርትራ አሳልፎ ይሰጥ ነበር ማለት ነው። ኢህደግን ለመጣል የተደረገው ሴራም መታየት ያለበት ነው። ኦሮማራ የተባለው ቡድንተደራጅቶ በአገራችን ፖለቲካ አለመተማመን ስር እንዲሰድ ሆኗል። ጉዳዩ ከግንባሩ መፍረስና አለመፍረስ ጋር የተያያዘ አይደለም። የሚያሳስበን በውስጡ የተፈጸመው መካካድ እንጂ በሃሳብ የመሸናነፍ ጉዳይም ሊሆን አይችልም። ተቧድኖ ከመርህ ውጭ መሄድ አደገኛነቱን እያየን ነው። መካካድ በደርግ ዘመን ነበር። በተለያዩ ቡድኖች መካከል እርስ በእርስ ለመዋዋጥ የተደረጉት መካካዶች ያስከተሉት ጦስ የሚታወስ ነው። ፖለቲካ መርህ ላይ ካልተመሰረተ የብርሀኑ ነጋ ፖለቲካ ይሆናል። አብይ በድርጅት ውስጥ በተፈጸመ ሴራ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላም እስካሁን ድረስ ሴራ በመስራት ላይ ይገኛል። የመጀመሪያው የዘመኑ ሴራ የመስቀል አደባባይ የቦንብ ውርወራ ነው። ይህ ሴራ አለማቀፍ ቅንብር ያለው ይመስለኛል። አከታትሎም ኢንጂነር ስመኘው ተገደለ። እሱን መግደል የተፈለገው እንደ ግለሰብ አልነበረም። በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ሚና የነበራቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች የማጥፋት እና የማፈራረስ ተልዕኮ ነበር። ግድቡ ያለባለቤት የቀረውም ለዚሁ ነው። ግድቡን ለመሸጥ አስቀድሞ የታሰበበትና የታቀደ ነበር፡፡የኢንጂነር ስመኘውን መገደል ስታስብ አሁንም ቅንብሩ ኢትዮጵያዊ ብቻ ስለመሆኑ ትጠራጠራለህ። ለነገሩ ተደማሪው ቡድን ደርግ እና ሌሎች የደርግ ዘመን ተሸናፊ ደርጅቶች ቅይጥ በመሆኑ ሰው ለማጥፋት ሴራ እነሱም አያንሱም። የጄኔራል ሰዓረ በራሱ ጠባቂ መገደልም ሌላው የዘመናችን ትልቁ ሴራ ነው። የአማራው ክልል ዶ/ር አምባቸው እና ጓዶቹ በተመሳሳይ ሁኔታ በሴራ ፖለቲካ መቀጠፋቸው ሌላው አሳዛኝ ድርጊት ነው። የሴራ ፖለቲካው በፓርላማም ጭምር መታወጁ ደግሞ ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል። አንዳንዴ አብይ ብዙ ስለሚናገር ሳናስተውለው ሊያመልጠን ይችል ይሆናል። ነገር ግን ሰውየው በግልጽ ተናግሮታል። የዘመናችን ትልቁ ሴራ ደግሞ በህግመንግስቱ ላይ እየተፈጸመያለውን ነው ።አሁን አገራችን የህገ መንግስት ቀውስ ውስጥ ያስገባትም ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው።

የተደማሪው ቡድን ታላቁ ሴራ አገራችንን ህገመንግስት አልባ በማድረግ የአንድ ግለሰብ ስልጣን ለማጠናከር በመፈጸም ላይ ያለውን ነው። ሰውየው ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርላማ ባደረገው ንግግር የተሰጠው ስልጣን የብሄር ብሄረሰቦች መሆኑን ሳይናገር ማለፉ ለእኔ ትልቅ መልዕክት ነበረው። የፖለቲካ ስልጣኑ የመስዋዕትነት ውጤት መሆኑንም አላስታወሰም። ለነገሩ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሲባል ራሱ ለኔ አስደንጋጭ ነበር። በወቅቱ የብሄር ብሄረሰቦችን የፖለቲካ ስልጣን በአንድ ግለሰብ እጅ መነጠቁን አልገመትንም ነበር። ህገ መንግስቱን የመጣስ ጉዳይ ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እየተሰራበት የመጣ ነው።አብይ አስቀድሞ የህገመንግስቱ ወዳጆች የተባሉትን ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች ማሳደድ ጀመረ። በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረውን ሴራ እና ስልት በመጠቀም ቀስበቀስ ካለ አዋጅ ህገመንግስቱን ያፈርስ ያዘ። በመጀመርያ ህወሃትን አውሬ በማስመሰል የኢትዮጵያዊያንን ቁጣእና ጥላቻ በመቀስቅስ ከፍተኛ የመነጠል ስራ ተሰራ።ህወሃቶችም እየተለቀሙ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ተወረወሩ። ትግራይ የሌቦች መደበቂያ ናት ተባለች። የትግራይ ልጆችም ተጠርጣሪ ሆኑ። ከትግራይ ሰው ጋር የተነጋገሩትም በጥርጣሬ እንዲታዩ ሆነ። በከሀዲነትም ተፈረጁ። ትግራይን ለማጥፋት ከባዕዳንም ጭምር ተመከረበት። ተደማሪው ቡድንም ትግራይ እንቅፋት ሆነችብኝ በማለት መክሰስ ጀመረ። ይህ የመነጠል ፖለቲካ በዶኩሜንተሪም ጭምር ተደገፈ፡፡ በመጨረሻም ጦር ለማስዘመት መዘጋጀቱን አወጀ። ያለፈው ሳምንት ደግሞ ሽማግሌዎች በመቀሌ አዳራሾች መታየታቸው ተነገረ። ይህ በትግራይ ላይ የተፈጸመው በደል ህገ መንግስቱን ለማፍረስ ከሚደረገው ሴራ አንዱ አካል ነው።

አሁን ያለንበትን ወቅት ፈታኝ የሚያደርገው ህግ መንግስትን ለማፍረስ በመደረግ ላይ ያለው ሴራ ጫፍ ላይ የደረሰበት ምእራፍላይ በመገኘታችን ነው።ተደማሪው ቡድን ያለምርጫ በስልጣን ላይ ለመቆየት ወስኗል። ይህ በአገራችን ከተደረጉ የፖለቲካ ስትራቴጂክ ስህተቶች በቀዳሚነት የሚመደብ ነው አገራችንንም ሊያፈርስ የሚችል ነው። እየሆነ ያለውህጋዊ ባልሆነ የደቦ መንግስት እንድንተዳደር ነው። ይህ አካሄድ ህዝባዊ ድጋፍ ስለሌለው በየአካባቢው አመጽ መቀስቀሱ አይቀሬ ይሆናል ሄዶ ሄዶም አመጹ ወደ እርስ በርስ ጦርነት መሸጋገሩ እንደማይቀር የሌሎች አገራት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ስለዚህ አገር ወዳድ ሀይሎች ይህ ከመከሰቱ በፊት ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ማፈላልግ የግድ ይላቸዋል። በአገራችን ጉዳይ ላይ ደፍረን መውጣት አለብን። አገራችን የሚልዮኖች መኖርያ የሊቃውንቶች አገር ዝምታን መስበር አለባት ።

ተደማሪው ቡድን ህግ መንግስቱን ጥሶ የክልል መሪዎችን ከአዲስ አበባ መሾም ጀምሯል። የፓርቲው ደንብ ላይ የክልል መሪዎች በብልጽግና ፓርቲ መሪ ከአዲስ አበባ እንደሚመደቡ ደንግጓል። በሌላ አነጋገር ህዝቦች በመረጡት ሰው አይተዳደሩም ማለት ነው። የድሮ ጠቅላይ ገዢ እንደ ማለት ነው። የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትም አብሮ ተሰርዟል ማለት ነው። ለምሳሌ ሲዳማዎች ዛሬ የራሳቸውን ክልላዊ መንግስት መመስረት ቢችሉም የክልሉ አመራር በብልጽግና ፓርቲ እስከቆዩ ድረስ በመስዋዕትነት ያገኙትን መብት በሌላ አቅጣጫ ተጠልፈዋል ለማለት ያስችላል። ይህ ሂደት በአስቸኳይ ካልቆመ ባገራችን ቀጣይ ቀውስ እየፈጠረ መሄዱ አይቀርም። ይባስ ብሎይህ ሂደት በመከላከያ ሃይል የተደገፈ ነው ባለፈው ሳምንት ብርሃኑ ጁላ የሰነዘሩት ዛቻም አስገራሚ ነገር ነበር፡፡

በዚህ ጉዳይ በአገራችን የመከላከያ ሃይል ላይ አንዳንድ ነጥቦች እናነሳ ዘንድ እንገደዳለን። በቅድሚያ ለአገር መከላከያ ያለንን ክብር መግለጽ ያስፈልጋል። ከመከላከያችን ጎንም እንቆማለን። ነገር ግን መከላከያ ሀይላችን የራሱን ክብር ከሚቀንሱ ተግባራት እጁን መሰብሰብ አለበት። መከላከያ ራሱ ህግ ማክበር እንዳለበት መርሳት የለበትም። መከላከያ ህገመንግስትን የመጠበቅ አደራውን ያልተወጣ ቢሆንም ፤ራሱ ግን በህገ መንግስት ጥሰት ላይመሳተፍ የለበትም። ብርሃኑ ጁላ የተደማሪው ቡድን መሳሪያ ሆኖ ህዝቦችን አስፈራርቷል። ከጅጅጋ እስከ ወለጋ እየተፈጸመ ባለው ወንጀልም ከተጠያቂነት የሚያመልጥ የለም፡፡ የፌዴራል ስልጣን ሁሉም ክልሎች በእኩል የሚያስተዳድሩት የጋራ መንግስት ነው፡፡ለፌዴራል ስልጣን የሚታጭ ሰው ለህዝብ እና ለብሄር ብሄረሰብ ክብር ያለው ሰው መሆን አለበት፡፡ብሄር ብሄረሰብ እየተሳደበ በፌደራል እርከን ለሀላፊነት ከቶውንም ቢሆን መታጨት የለበትም።የፌደራል መንግስት የክልሎች መሆኑ እየተረጋገጠ መሄድ መቻል አለበት ።

መቀሌ ደርሰው ስለተመለሱ ሽማግሌዎችም ትንሽ የተሰማኝን ልናገር፡፡በትግራይ የተበዳይነት ስሜት ማየታቸውን በመገረም መግለጻቸው ያሳዝናል። ሁላችንም በአንድ አገር ውስጥ ሆነን የሚሆነውን ማየት ካልቻልን ለሽምግልና መብቃታችን ጥርጣሬ ይፈጥራል። ፊት ለፊት የሚታይ እስር፤ ግድያ፣ ስም ማጠልሸት ፤ ማሳደድ ሰው እንዲነግራቸው የሚጠብቁ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። በንግድ ዘርፍ ፤በመንግስት ስራ ቅጥር፣በዕድገት፣ በበጀት ምደባ፤ሌላው ቀርቶ የኮሮና በጀት ላይ አድልዎ እየተፈጸመ መሆኑን አስቀድመው ማወቅ ነበረባቸው። አገር በሙሉ አንድ ትልቅ ሰው ጠፍቶ ተደማሪው ቡድን አገራችን የተሰራችበትን ድርና ማግ ሲበጣጥሰው እየታየ በትግራይ የተበዳይነት ስሜት መኖሩ ሊያስገርም ባልተገባ ነበር። አብይ ራሱ ሰባበርናቸው እያለ ሲፎክር አልሰምቶም ወይ ያስብላል። ይህን ለማወቅ ቃሊቲ ሄዶ ማየት ነው። ቃሊቲ እስርቤት በኦሮሞ እና በትግራይ ልጆች ተሞልቶ ስታገኙት ደግሞ የታሰሩት የትግራይ ልጆች ብቻ አይደሉም እንደማትሉ ተስፋ እናድርግ።

በየምክንያቱ የኢትዮጵያዊያን በህገ መንግስት የመተዳደር መብት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት የሚደረጉ ጥረቶች ከወዲሁ ካልቆሙ በስተቀር መዘዙ አደገኛ ይሆናል። ከአንድ መቶ ሚልዮን በላይ ህዝብ ከህገ መንግስት ውጭ ለማስተደዳር ማሰቡ ራሱ የጤንነት ምልክት አይደለም። አሁን ያለው የአገራችን ህገ መንግስትም በልካችን የተሰፋ ነው።አገራችን የብሄር ብሄረሰቦች አገር ናት። ህገ መንግስቱም ይህንን ያንጸባርቃል። በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ አንድነት የሁሉም ፍላጎት ነው። በየአገሩ ያሉ ህገ መንግስታት እንደየአገሩ ታሪክ ቢለያዩም መሰረታዊ ይዘታቸው ግን ተመሳሳይነት አለው። ሁሉም ለየአገሩ እንዲበጁ ተደርገው የተሰሩ መሆኑን የሁሉም አገራት ታሪክ ያሳያል። ህገ መንግስቱን ማፍረስ ማለት አብሮነትን ማፍረስ መሆኑን መሳት የለብንም። ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ በድንገት በመጣ ሽፍታ መገዛት ይሆናል። ህገ መንግስት የግለሰቦችን ፍላጎት በህግ ለማስተዳደር የሚጠቅም ሰነድ ነው እንጂ፤ ግለሰቦች ህገመንግስቱን እንደፈለጉ የሚያደርጉበት መሳሪያ አይደለም፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን ።

 

 


Back to Front Page