|
ዐቢይ አህመድ፥ የለውጥ ወይስ የነውጥ መሪ?
ሙሉጌታ ወልደገብርኤል (ስትራቴጂስት) 09-25-20
ለውጥ ምንድ ነው? የሚለው ጥያቄ ቀዳሚ ጥያቄአችን ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። ለውጥ የሚለው ቃል በግርድፉ የተመለከትነው እንደሆነ፥ በአስተሳሰብና ሆነ በአሰራር ቀድሞ ከተለማመድነው ህይወት ወይም ድርጊት የተለየ መንገድ ወይም አንጻራዊ አቅጣጫ መከተል፤ አዲስን ነገር ገንዘብህን ማድረግ፤ አሮጌ ማንነት በመጣል አዲስ መገለጫ መላበስ የሚል በዋናነት ፈቀቅ ማለትንና ዕድገትን የሚያመላክት ቃል እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ታድያ፥ መንግስታዊ ለውጥ፣ የሥርዓት ለውጥ፣ የአመራር ለውጥ ሲባል ምን ማለት ነው? በማለት ጥያቄ ያነሱ እንደሆነም በተመሳሳይ ቃላቶቹ “ለውጥ” የሚለው ቃል ጨመረው በመያዛቸው የለውጥ ትክክለኛና እውነተኛ ትርጓሜ/ፍቺያ አሻሚ አድርጎታል።
የአገሬ ሰው ሲተርት፥ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም፤ እንዲል ለውጡ ሥር ነቀል ወይም ከልብ የሆነ ህዝባዊና አገራዊ አጀንዳ ያነገበ እውነተኛ ለውጥ ካልሆነ፥ የህወሐት መሪዎች መንግስትነት ተነቅሎ የዐቢይ አህመድ መንግስት ስለተተከለ፣ የቀድሞ ስርዓት ተንዶ ሌላ ስርዓት ስለተገነባ፣ ነባሩ አመራር ዘወር እንዲል ተደርጎ አዳዲስ ሰዎች ስለመጡ ክስተቱ ለውጥ ተብሎ መተርጎሙ መሰረታዊ ስህተት ነው። ለውጥ ሲባል፥ የቃላት ጨዋታ አንድም ለውጥ አለ! ተብሎ ሲለተዘፈነና ስለተጨፈረ ሳይሆን እውነተኛ ለውጥ፥ በሰዎች ህይወት በዓይን የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ ሳር ቅጠሉ የሚመሰክረው ተጨባጭ ህይወት ነው።
የስርዓት ሆነ የግለሰቦች መለዋወጥ በዋናነት አገርና ህዝብ ሊያሳርፍና ሊገላግል ካልቻለ የሆነው ነገር ነውጥ እንጅ ለውጥ አይደለም። በኢትዮጵያ የሆነው ነገር፥ ለውጥ ወይስ ነውጥ? ለሚለው ጥያቄ በቂና ትክክለኛ ምላሽ ሊሰጥ የሚችለው የስርዓትና የሰዎች መለዋወጥ እንደ ትኩስ ድንች እየፈጀው ያለ ሰውፊው ህዝብ ብቻ ነው። አዲሱ አመራር ራሱን “የለውጥ አመራር” ብሎ በቁልምጫ ስም ስለጠራ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አለ ማለት አይደለም። አንድም፥ ደሙ ቢመረመር፥ ከችኩልነት፣ ከታይታና የማስመሰል አታላይ ባህሪይ በስተቀር፥ ጥበብ፣ እውቀትና መረዳት የማይገኝበት ሰው የለውጥ “መሪ” ነኝ ስላለ ነው ማለትም አይደለም። በሚገባ ከደሙ ጋር የተወሃደ፣ የገባው፣ በሙላት በጥልቀትና በስፋት የሚገልጸው ርዕዮተ ዓለም የሌለው ሰው አይደለም አገርና ህዝብ ለመልካም ሊለውጥ ቀርቶ ለራሱ እንደማይሰነብት የታወቀ ነው። እንደውም ዕዳ/ጦስ ነው።
ነውጥ/ቀውስ በተመለከተ፥ እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው ማለፍ የምፈልገው ነጥብ ቢኖር፥ ነውጥ ሲባል በምናየውና በምናውቀው በችግሩ ታላቅነት ብቻ የሚገለጽ ነገር ሳይሆን ይልቁኑ መሠረታዊ ግምታችንና ቅድመ ግምትዎቻችንን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን በአግባቡ ከተያዘም ለቀጣይ ጉዞአችን እንደ ኮምፓስ ሆኖ ሊያገለግለን የሚችል ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ነውጥ ሁል ጊዜ አሉታዊ ብቻ ሳይሆን አውንታዊ ገጽታ ጭምር እንዳለው ልብ ማለቱም አስፈላጊ ነው። ነባራዊ ሁኔታዉን በመፍጠርና በማስቀጠል ረገድ ድርሻ ያላቸው የተለያዩ ጉዳዮች በሚገባ እንድንፈትሽ፣ እንድንመረምርና እንድናጤን ከመርዳት ያለፈ ጥሰን እንድንወጣ የሚያስችለንም ነው። አገራችና ህዝባችን እያመሰና እያተረማመሰ የሚገኘው ቀውስ እንዲፈጠር አስተዋጽዖ ያደረጉ መሠረታዊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ብለን እንድንጠይቅ፤ መፍትሔ ፍለጋ እንድንተጋ የማነቃቃት አቅም ያለው ነውና።
በተረፈ፥ ለውጥ ፍሬ ነው ሲባል አባባሉ በሚገባ ሊበራልን ይገባል። ህዝብ በተስፋ ቃል ብቻ አይኖርም፤ የሚታይና የሚዳሰስ፣ የሚላስና የሚቀመስ፤ የተጨበጠ ነገር ይፈልጋል። ሐቁ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ፥ ከነበረበት በከፋ ሁኔታ ስጋት ውስጥ የሚገኝና የሚደርስለት አጥቶ የሞት ጣር ያለ ህዝብ ነው። የኢኮኖሚ ውድቀት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ሰላሙ አስጥቶት ህዝቡ ስጋት ውስጥ ከትቶታል። ይህ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን ሐቅ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቀውና ለማየት የሚሻው አመራር፥ የማይክና የካሜራ ሱስ ያለበት ግለሰብ ሳይሆን የፖለቲካ መረጋጋትና የኢኮኖሚ መሻሻል ለመፍጠር የሚያስችል ጠንካራ አቅም፣ ብቃትና ክህሎት ያለው አመራር ነው። ህግና ስርዓት ባልተረጋገጠባት አገር ልማት ሆነ ሰላም የማይታሰቡ ናቸውና አንድ ህዝባዊ ቅቡልነት ያለው ዲሞክራሲያዊ መንግስት በህግ ከተሰጠው ተግባርትና ኃላፊነቶች አንዱ የዜጎቹን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ነው። ጥያቄው፥ የዐቢይ አህመድ መንግስት የቁጥር ጨዋታና ፕሮፓጋንዳ ከከንፈር ሽንገላ ያለፈ፥ በተጨባጭ ፍትህና ዳቦ ለተጠማና ለተራበ ህዝብ ማቅረብ አልተቻለውም። ፍላጎት ሆነ ዝግጁነቱ የለውም።
ወገን፥ የቤተ መንግሥት ግድግዳ ቀለም በመቀባት በድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የዕለት ዕለት ኑሮ ላይ የሚያመጣው አንዳች ትርጉም የለውም። ነገሩ ጥንቆላ ካልሆነ በቀር፥ የቤተ መንግሥት ግድግዳ ቀለም በመቀባት የሚለወጥ የህዝብ ችግር የለም። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትስ ቢሆን ግድግዳው ቀለም ሳይቀባ ቀርቶ ነው? የነበረው ሥርዓት ፎቶ አንሺዎችና ካሜራ ቀራጮች ጋብዙ ቤተ መንግስት ምን እንደሚመስል ስላላሳየን የጉድፍ መሰብሰቢያ ነበር ማለት አይደለም። ቁምነገሩ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀዳማዊ ኢህአዴግን በከፍተኛ ድምጽ የተቃወመ የቤተ መንግሥት ግድግዳ ቀለም ለማስቀየር ሳይሆን የተሻለ ህይወት ይገባኛ! ብሎ ስለሚያምን ነው። የቤተ መንግሥት ግድግዳ ቀለም መቀባቱ እየተቃወምኩ አይደለም። ቢሆንም ግን ድርጊቱ ከህዝብ ጥያቄ ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለማይገባኝ ነው። የሚያገናኘው ነገር አለ ተብሎ የሚታመን ከሆነ ደግሞ፤ ነጮች፥ "leaders eat last" እንደሚሉት የተራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ቤት ቀለም በመቀባት መጀመር ነበረበት። የህዝብ አገልጋዮች የራሳቸው ምቾች ለመጠበቅ በሚያደርጉት ሽርጉድ ሳይሆን የሚያገለግሉትን ህዝብ በማስቀደም የሚታወቁ ናቸው። መጽሐፍ፥ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መስፈሪያ አላቸው የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” ሲል፥ ድሆች በማሰብና በመርዳት ትጉህ የነበረ ጳውሎስ ደግሞ “ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” ነበር ያለው። የህዝብ አገልጋይ ባህሪይ ይህ ነው። የህዝብ አገልጋዮች ሀብትና ንብረት ቁሳቁስ ከማሳደድ ያለፈ የሚያገለግሉት ህዝብ እርካታ ነው። ደስታቸውም የህዝብ ደስታ ነው።
ታድያ፥ በአይ.ኤም.ኤፍ (IMF) እና በዓለም ባንክ (World Bank) የብድር መዓት የሰመጠች፤ ከግማሽ አካልዋ በላይ በኮሚኒስቱ የቻይና መንግስት ዕዳ የተያዘች አገር ተይዞ ስለ ቀለምና ስለ መኪና ማውራቱ ትክክል አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምናልባትም ዘንግተውት እንደሆነ ይሆን ነው እንጅ እየመሩት ያለው ህዝብ፥ ቁርስ በልቶ ምሳ የማይደግም፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እርም የሆነው፣ ፍትህ ማግኘት የሰማይ ከዋክብት ያህል የራቀበት፣ ሙስና ያጎበጠው፣ ነጻ ህዝብ መሆን ያልተቻለውና እርም የሆነበት ህዝብ ነው። ወይስ፥ ህዝብ ተራበ ስትባል ለምን ኬክ አይበሉም! አለች የቦሌ ልጅ እንደሚባለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ነው በዚህ ወቅት ስለ የግድግዳ ቀለም የሚያወሩብን? “ሳታማኸኝ ብላኝ!” አለ አዝማሪው።
ለውጥ፥ ታከለን ነቅለህ ታከለችን መትከል አይደለም
እዚህ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ አዲስ አበባን ሲያስተዳድሩ በቆይታቸው፥ ዝርፍያ፣ ጋጠ-ወጥነት፣ አድሎአዊ አሰራር፣ ዓይን ያወጣ ሙስና መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ በማስተዋወቅ በማን አለብኝነት ያሻቸውን ሲሰሩ የነበሩ አቶ ታከለ ኡማ እና በሌላቸው ትምህርት፣ እውቀትና ችሎታ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በመሆን ፍት ህንና ፍርድን ሲያተረማምሱ የከረሙ አሁን ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ አዲስ አበባን እንዲያስተዳድሩ የተሾሙ ታከለች aka ወ/ሮ አዳነች አበቤ ማንሳት የፈለጉት ምክንያት የእነዚህ ሁለት ሰዎች ወግ በተለይ ለአዲስ አበቤው በሚገባ ስለገባውና ሰለባ እየሆነ ያለ ህዝብ እንደመሆኑም የህወሓት መሪዎችና የዐቢይ አህመድ መንግስት በንጽጽር ለማስረዳት ስለ ወደድኩ ነው።
ከመጋቢት 2010 ዓ/ም ጀምሮ በተለይ ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ፥ የለውጥ ጉዞ፣ የለውጥ አመራር፣ የለውጥ ዘመን፣ የለውጥ መንግስት እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምተናል። ርግጥ፥ በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተስተጋባው “ለውጥ” የሚለው ቃል ለመቀበል የሚያስገድድ በርካታ ክስተቶች ተፈጥሯል። ለምሳሌ፥ የመጀመሪያ ሦስትና አራት ወራት የታዩ ክንዋኔዎች የተመለከትን እንደሆነ የሆነው ነገር ለማመን የሚከብድ ስለ ነበር እውነትም ለውጥ መጥተዋል ይኖሯል ብለን አስጨበጨብን። ቀዳማዊ የኢህአዴግ መንግሥት በሽብር ክስ ወደ ውህኒ ያወረዳቸው ግለሰቦች በነጻ ተለቀዋል፤ ኦነግና ግንቦት 7 ጨምሮ በትጥቅ ትግል የሚያምኑ የፖለቲካ ሰዎችና መሪዎች ከነ ድርጅቶቻቸው ወደ አገር ቤት ለመግባት ችሏል፤ ከፖለቲካ ልዩነት የተነሳ ለሁለት ተከፍለው በባላንጣነት ሲተያዩ የነበሩ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎች ውግዘታቸው ሳይነሳ እንዲሁ ተቀላቅሏል፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግስት መካከል የነበረው የሻከረ ግንኙነት በከፊል ተስተካክሏል፤ በጎረቤት አገር አከባቢ የነበሩ እስረኞች ወደ አገር ቤት ተመልሷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ለረጅም ዘመናት ሰምቷቸው የሚያውቅ ቃላቶች እየተጠቀሙ ሲናገሩ የህዝቡ ተስፋ ለመለመ። ይህ ሁሉ “ለውጥ” መጣ ተብሎ ሲነገር መጣ የተባለውን ለመቀበል አስገዳጅ ክስተቶች ነበሩ። እነዚህ ክስተቶች በመሉ አመራሩ ለሚያስተጋባው ቋንቋ ህዝቡ ተቀብሎ ያስተጋባ ዘንድ አስገዳጅ ሁነቶች ነበሩ። ከአምስትና ከስድስት ወራት በኋስ ምን ተፈጠረ?
ምን ተፈጠረ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠቴ በፊት ግን በድጋሜ ለውጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ ለማስረዳት እወዳለሁ። ኢትዮጵያ በተጋጋሚ የድርቅ ሰላባ የሆነች አገር ናት። ይህ ለሁላችን ግልጽ ነው። ድርቅ ሲከሰት የሚያጠፋውና የሚመነጥረው የሰው ህይወት ነውና። በመሆኑም፥ ድርቅ መጣ ወይም ድርቅ ሆነ ሲባል የማይደነግጥ ሰው የለም። ድርቅ በዋናነት መሬት ዘር ተቀብላ ፍሬ መስጠትን ስትከለክል፤ አንድም፥ ፍሬው በአንድም በሌላም መንገድ ዘሪው እጅ ሳይደርስ ሲጨናገፍ ነው። ለውጥ የሚለው ቃልም እንዲሁ ፍሬ እንጅ ዘር አይደለም። ለውጥ ጅማሮ ሳይሆን ውጤት ወይም ግብ ነው፤ መጽሐፍ፥ ባለጀራህን በማለዳ መመረቅ የመርገም ያክል ነው እንዲል። ታከለ ተነቅሎ ታከለች ስትተከል የተለወጠ ነገር እንደሌለ ሁሉ መጋቢት 2010 ዓ/ም በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሆነው እንዲሁ ነው።
ጊዜና አጋጣሚ የማይለውጠው ሰው የለም ተብሎ ስለሚታመን ዕድሉ ተሰጣቸው እንጅ የለውጥ አመራር ተብሎ ብዙ የተዘፈነለት ቡድን አገርና ህዝብ የሚለውጥ ቁመናና ተክለ ሰውነት ሊኖረው ቀርቶ ለራሱ ያልተወጠ አንድም፥ ኮኮቡ የጠፋበት አንጃ ለመሆኑ መነጸሩን አስተካክሎ ማየት ለሚሻ ሰው ከመጀመሪያው ግልጽ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕለተ ሲመታቸው በማስመልከት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት የብዙዎች ቀልብ የሳበ ንግግራቸው የአቶ መለስ ዜናዊ ስም ባለመጥራታቸው ብቻ ብዙዎች ሲደነቁና ደስታቸውን ሲገልጹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ አገራችንን ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት በሁሉም መስክ መሰርታዊ ለውጥ ያመጣ ህገ መንግሥታዊና ፌደራላዊ ሥርዓት ገንብተዋል” ብለው ተናግረው ሲያበቁ፥ በሰሜን አሜሪካ ባደረጉት ዑደት ደግሞ ምላሳቸው መቶ ሰማኒያ ዲግሪ ታጥፎ “በሁሉም መስክ መሰርታዊ ለውጥ ያመጣ” በማለት ያሞኳሹትን ሥርዓት እንደ ጭራቅ በመሳልና በማውገዝ ብዙዎቹን ሲያንጨበጭቡ ሳስተውል ሩቅ እንደማይጓዙ በሚገባ ታይቶኝ ነበር። ይህን ስጋቴ መጀመሪያ “አንደመርም” በመቀጠል “የተከበሩ ወንጀለኞች” በሚሉ መጻህፍቶቹ በሚገባ አስፍራለሁ።
“እንደውሻ በመጮህ ማምለጫን ማመቻቸት ዘላቂ መፍትሔ ባይሆንም ለጊዜው ይጠቅማል” (ዲራአዝ: ገጽ 38) የሚል የተፋለሰ አባባል የህይወቱ መርህ አድርጎ የሚያምን ዐቢይ አህመድ አዲስ መሪ ሆኖ ወደ ስልጣን ሲመጣ፥ ተሳፍሮባት የመጣ ጀልባ በሙስና፣ በወንጀል፣ በዝርፍያና በጸረ ዲሞክራሲያዊነት የበሰበሰበችና የጠሰጠሰች እንደሆነች፤ ሰውዬው በቀጣይ ጥንቃቄና ማስተዋል ገንዘቡን ካላደረገ ምላሱና አስተሳሰቡ ጠልፎ እንደሚጥለው ቅንጣት ታክል ጥርጥር አልነበረኝም።
ምንድ ነው ያተረፍነው?
እውነተኛ የመንግስትና የሥርዓት ለውጥ መጣ ሲባል፤ ብዙዎቻችንም የምንጠበቅነው፥ አዲሱ አመራር ሥልጣኑን በተቆናጠጠ ማግስት ለፍትህ መዛባትና ለሙስና መንሰራፋት ቀዳሚ ተዋናዮች የነበሩ የቀድሞ ሥርዓት ሹማምንትን ትልቁም ትንሹም በሙሉ ያሰናብታል፤ ሥርዓቱን ለማገልገል በክፉ ልብ ሆነ ተብለው የተሰሩና የተበጃጁ አፋኝ ህጎች ሁሉ ይሽራል፤ ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ከፓርቲ አመራር ሙሉ በሙሉ የጸዳ የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ የደህንነት፣ የዳኝነት ስርዓት ይተክላል፣ በአንድም በሌላም መንገድ የተዘረፈው የሀገርና የሕዝብ ሀብት ይመለሳል፤ ወንጀለኞች በህግ ፊት አቅርቦ ተጠያቂዎች ያደርጋል፤ ሕዝባዊ ምርጫ ተካሂዶ አብላጭ የሕዝብ ድምጽ ላገኘው አሸናፊ የፖለቲካ ድርጅት ሥልጣኑን ያስረክባል፤ በህዝቦች መካከል፥ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ወንማሞችነን ለማምጣትና ለማስፈን በቃልም በስራም ይበረታል የሚል ተስፋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበር። ከተመለከትናቸው የዲሞክራሲያዊ መንግስት ባህሪያት የዐቢይ አህመድ መንግስት አንዳቸውንም ተግባራዊ አላደረገም። ኦነግና ሌሎች በትጥቅ ትግል የሚያምኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት የገቡበት ግልጽነት የጎደለበት መንገድ ትተን ከኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ብንነሳ እንኳ ሁለት ዓመት ውስጥ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በለውጥ ስም በመላ አገሪቱ የፈተጸመው በደሎች፣ ዝርፍያና ወንጀሎች ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ተፈጸመ ተብሎ ከሚነገረው ትርክት ይልቅ የከፋ እንደሆነ ነው እንጅ የሚያንስ ሆኖ አናገኘውም።
የምንሰማውን ማስተዋል፤ የምናየውን መመልከት ተሳነን እንጅ ስድስት ወር ባልሞላው ጊዜ ውስጥ የተቀባባው ሜክአፕ ፌድ ሲያደርግበትና ሲረግፍበት በቀጥታ የገባው የተለመደው ኢህአዴጋዊ (በህዝብ የመቆማር የበከተ ልማድና መሰሪ አሰራር) በለውጥ ስም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ድራማ መስራት ነበር።
v የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ወክሎ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ዓረብ አገራት ድረስ ሄዶ ስለተፈራረመው ውል ዝርዝር ይዘት እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምስጢር ነው። አመራሩ በዚህ የሚመለስ ቡድንም አይደለም፥ የስምምነቱ ይዘት ለማውቅ ተንሰፍስፎ ይጠባበቅ የነበረው ህዝብ ቀልብ ለማስቀየስ ሆነ ተብሎ፣ ከፍተኛ የሰው ኃይልና በጀት ተመድቦለት፣ በተቀነባበረ መልኩ በዕቅድና በዓላማ የቡራዮ እልቂት ደገሱልን። ስለ ጠፋው የንጹሐን ዜጎች ህይወትና ስለወደመው የሰው ህይወት እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም፤ ተጠያቂ ሆኖ በፍትህ ፊት የቀረበው ወንጀለኛም የለም።
v የኢንጅነር ስመኘው አሰቃቂ ግድያ እንደ ፖሊስ ትረካ ፍርዱም እንዲሁ ተረት ተረት ሆኖ ቀርቷል። መሳሪያው በሚገባ ተደላድሎ የተቀመጠበት በስተቀኝ፥ ተተኩሱ የተገደሉበት በስተግራ ሆኖ ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንጅነሩ ራሱ ነው ያጠፋ አሉን። ምናልባትም ኢንጅነሩ ራሳቸው ካጠፉ በኋላ በሚገባ ተደላድለው ሳይቀመጡ ካሜራው ስለ ደረሰባቸው ተደናገረው መሳሪያው በስተቀኛቸው ጥለውት ይሆን እንዴ? በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓይን ያወጣ ፍርደ ገምድል ብያኔ ያጣጣለ ህዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም።
v የሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳ ተውኔት ስክሪፕት እንመልከት፥ የፍንዳታው ዋና ዓላማ ይህን ያደረጉት የህወሓት መሪዎች ናቸው ተብሎ ህዝቡ በህወሃት መሪዎች ላይ ያለውን ጥላቻ እንደገና እንዲያገረሽና የዐቢይ አህመድ ተቀባይነትና ገናነነት ለማስቀጠል በንጹሑን ኢትዮጵያ ደምና አጥንት ላይ የተሰራ ዘግኛኝ ድራማ ነበር።
v የመከላከያ ሠራዊት ወደ ቤተ መንግሥት በማምራት ያደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከሸፈ! ተብሎ ሲሰማ ያልደነገጠ ዜጋ የለም። ሐቁ ግን፥ ይህ ዓይነቱ ድራማ እውነት ሊመስል የሚችለው፤ አይደለም ሁለት መቶ የሚያህል ሰራዊት አንድ ወታደር ከከተማ ከተማ ቀርቶ ካምፕ ውስጥ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ወታደራዊ ደንብና አሰራር ለማያውቅና እውቀቱ ለሌለው ሰው ብቻ ነው። በዚህ በተሰራው ድራማ አንድ፥ ቀድሞ ይፈለጉ የነበሩ የመከላከያ አባላት በህግ ለመምታት፤ ቀጥሎ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተግዳሮት ውስጥ እንዳሉና የህዝብ ድጋፍ ለመሸመት በተለይ የኦሮሞ ወጣቶች ድጋፍ ለማግኘት ታስቦ የተሰራ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መንግስታችን ተነካ ብለው ተነሱ” ያሏቸው ወጣቶች ልብ ይሏል።
v አዲሱ አመራር፥ የአማራ ክልል ለማንበረከክና ለማዳከም አስቦ ሲነሳ ያደረገው መጀመሪያ ሹመት በሚመስል አሰራር አመራሩን ወደ ፌዴራል መንግስት ስልጣን የመሳብ አዝማምያ ቢስተዋልም ድርጊቱ የታሰበው ያህል ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ የክልሉን አመራሮች በአውቶማቲክ መሳሪያ ሰውነታቸውን አፈራርሶ ሬሳቸው በመጥረጊያ ሰብስቦ ክርታስ ውስጥ ካሸገ በኋለ ከወደ ኦሮሚያ “መፈንቅለ መንግስት” ተደረገብን ተባለ። የሚደንቀው፥ ከሞት አመለጥን በማለት ለትረካው መጣፈጥ የተሰጣቸው ድርሻ በሚገባ የተወጡ የክልሉ አመራር አባላት ነበር ዛሬ በፌዴራል ሥልጣን ላይ የሚኒስትርነት ማዕረግ መሸለማቸው ልብ ይሏል።
v የኢታማጆር ሹም ሰዓረ መኮነንና የጓዳቸው የጀነራል ገዛኢ አበራ ግድያም ተመሳሳይ ነው። ሰዎቹን በጠራራ ጸሐይ ላይ ገድለው ሬሳቸው ካነሱ በኋላ በጠባቂዎቻቸው ነው የተገደሉ አሉን። ይህን በማስተባበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነበረው የደህንነት ቢሮ ዋና አዛዥ ጀኔራል አደም በሰሩት አኩሪ ስራ በኢታማጆርነት ወደ መከላከያ እንዲመጡ ተደርጓል። በነገራችን ላይ፥ እስከ አሁን ድረስ ልብ ብለው የሆነ እንደሆነ እነዚህ ሁሉ ድራማዎች “ሰበር ዜና” እያለ የሚተርክልን ሌላ ማንም ሳይሆን የራሱ የመንግስት ልሳኖች የሆኑ ፋና፣ ዋልታና ኢቲቪ ናቸው። የዓይጥ ምስክርዋ ድንቢል አለ ያገሬ ሰው። ይህ ከብዙ በጥቂቱ ነው።
ዐቢይ አህመድ ለመደገፍ ያስገደደን ምክንያት ምንድን ነበር?
ካቀለልከው የማይቀል ካከበድከው የማይከብድ ነገር የለም፤ ቀላሉን ማከበድ ከባዱን ማቅለል የሰው ተፈጥሮአዊ ባህሪይ ቢሆንም ትክክል ግን አይደለም። አንድ ነገር ከሚገባው በላይ ማጋነን አልያም ዝቅ ዝቅ ማድረግ የጤና ሳይሆን ነፍስን የሚያቀጭጭ በሽታ ነው። ምን ነው? ቢሉ፥ ቀላሉን ስናከብድ ከባዱን ስናቀል ነገሩ በራሱ የሚከብድና የሚቀል ሆኖ ሳይሆን ሚዛናዊነት ስለሚጎድለንና አድሏአዊነት ስለሚሰለጥብን ብቻ ነው። የህወሓት መሪዎች ስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ኮሽ ባለ ቁጥር ሰማይና ምድር እስኪታወኩ ድረስ ይነሳ የነበረ አቧራ የቅርብ ትውስታችን ነው። ሲሰርቅ እጅ ከፈንጅ የተያዘ ሰው በህግ ፊት ቀረበ ሲባል ተገደለ፤ ታመመ ሲባል ሞተ፤ አቶ እገሌ በፈቃዳቸው ስራ ለቀቁ ሲባል የለም አማራ/ኦሮሞ ስለ ሆነ ነው የተባረረ እየተባለ ሲጮህ ነበር። ይህ ሁሉ የተደረገም በዲሞክራሲ፣ በፍትህ፣ በነጻነትና በእኩልነት ስም ነበር።
ዛሬ በአንጻሩ፥ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ተልዕኮ ባላቸው ሰዎች አማካኝነት አገር በጠራራ ጸሐይ ስትወረር፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች ለህልፈት ሲዳረጉ፣ ሚልዮኖች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ፣ ከተሞች በእሳት ሲወድሙ፣ ሴቶ እህቶቻችን ሲገቱና ክብረ ንጽህናቸው ሲደፈሩ፣ ቤተ ክስርቲያን በይፋ ሲዘመትባት ግን ዝምታ ጥበብ ነው ተባለ። በርግጥ ይህ የሚያሳየው፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የፍትህ፣ የዲሞክራሲ፣ የነጻነትና የእኩልነት ጥያቄ ወይም ችግር ሳይሆን የብሔር የበላይነት ጥያቄ እንደሆነ ይህ ግልጽ ማሳያ ነው። አንድም፥ ፈጣሪ እንኳን ትግሬዎቹ ነቀለልን እንጅ ኦሮሞ አይደለም እኔን የልጅ ልጄም ባሪያ አድርጎ ቢገዛን ደስተኛ ነኝ! ካልሆነ በቀር። ባይሆን ኖሮ፥
v የዐቢይ መንግሥት ሰፍ ብለን የተቀበልነው እስረኖች በመፍታቱ ከሆነ፥ ወቅት እየጠበቀ በገፍ እያፈሰ የሚለቃቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ሳይጨምር በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አርባ ሺህ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ይገመታል። የተጠቀሰው ቁጥር በማንነታቸው ለእስር የተማገዱ አይጨምርም። (ጸሐፊው፥ ጃዋር መሓመድ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አውራቂሶች የፖለቲካ እስረኞች ናቸው ብሎ አያምንም)።
v የዐቢይ መንግሥት አጨብጭበን የተቀበልነው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎች በማስታረቁ ከሆነ ይሄው የዕርቁ የፌርማ ቀለም ሳይደርቅ፤ ሰዎቹ የሚስቧት “ኦሮሚያዊት ኢትዮጵያ” ለመፍጠር ዕንቅፋት ትሆንብናለች በማለት በጠላትነት የፈረጇት የኦርቶዶክ ቤተ ክርስትያን በድጋሜ ለሁለት በመክፈል የኦሮሞ ቤተ ክህነት በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ እየናጣት ይገኛል።
v የዐቢይ መንግሥት ደረታችን እየደቃንና እየዘፈንን የተቀበልነው የኢትዮ - ኤርትራ ችግር በሰላም በመፍታቱ ከሆነ፤ በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት ፈጥሮ የመቐለና የአዲስ አበባ መንግስት እየተባለ ህዝቡ ሰላሙ አጥቶ አገሪቱ ለጦርነት እያዘጋጃት ይገኛል። በእርግጥ፥ ዐቢይ አህመድ ከትግራይ ክልል ጋር ሊከፍተው የሚችለው ጦርነት በዋናነት “የህግ የበላይነት” ለማስከበር ሳይሆን በመላ አገሪቱ ያጣው ተቀባይነትና ጭብጨባ ለመመልስ ነው።
v ሌላው፥ በአፍሪካ አገሮች በችግር ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ በማድረጉ ከሆነ፥ በዐረቡ ዓለም የቤት ዕቃ ያህል ክብር ተነፍጓቸው በረሃብ፣ በበሽታ፣ በችጋር እያለቁ ያሉ ኢትዮጵያውያን በዐቢይ አህመድ ዘመነ መንግስት ነው። ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገራት በተሻለ ሁኔታ እንገኛለን እያለ በሚድያ ሲመጻደቅ የነበረ መንግስት ይኸው፥ ዜጎቹን አልቀበልም ብሎ በሩን በመቆለፉ ኢትዮጵያውን በዐረቡ ዓለም እያለቁ ይገኛል።
v የጩኸታችን ዋና ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥልጣን በትግሬዎች ቁጥጥር ወድቋል የሚል ነበር፤ አሁንስ? ያልነበረ አዲስ ህግ እየጻፈና እያስጸደቀ አገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ እየገዛ ያለ የአገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ማን ቢሆን ነው? የውጭ ምርት ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩ እንደ’ነ ቻይና፣ ቱርክ፣ ህንድ፣ ዱባይ፣ ታይዋን የመሳሰሉ አገራት ብሔር ተኮር አዲስ ስም ዝርዝር ይዞ እየዞረ ያለና ኢ፡ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልና አድሎአዊ አሰራር እየፈጠረና እየዘረጋ ያለው የዐቢይ መንግስት አይደለምን?
v ቀደማዊው ኢህአዴግ መንግሥት ሰብዓዊነት የራቀው አሸባሪ መንግስት ነበር ሲባል ይሰማል፤ ይህ እውነት ነው። የዐቢይ መንግስትስ ምን እየሰራ ነው? ሴቶቻችን እያገተ ህዝቡ የመንግስት ጥበቃ እንዲለምንና የመንግስት ጥገኛ እንዲሆን ተግቶ እየሰራ አይደለም ወይ? ህዝብና አገር በጠራራ ላይ የሚዘርፉ ነውጠኞችና ጋጠወጦች እያደራጀ የዋሁን ህዝብ እያዋከበ፣ እያሸበረና እያስጨነቀ መንግስትነቱን እያደላደለ ያለ የዐቢይ መንግስት ነው።
v በቀዳማዊ የኢህአዴግ ዘመን የህወሓት መሪዎች የበላይነት አለ ሲባል ነበር፤ አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ነው፥ ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ ፍትሕ ግድ ይለናል! እያሉ በጋዜጠኝነት፣ በአክቲቪስትነትና በአገር ልጅ ስም ሰማይ ምድሩን ሲያዳርስ የነበረው ተቃዋሚ ዛሬ ምን ዋጠው? አገር እየመራ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ቱባ ቱባ ባለስልጣን ከዘጠና በመቶ በላይ የኦዴፓ ሰዎች፤ አንድም፥ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የበላይነት ቁጥጥር ስር አይደለም ወይ? አቶ ሽመልስ በግልጽ እንደተናገሩት ብልጽግና የኦሮሞ የበላይነት ለማረጋገጥ ለእኛ በሚመቸን መንገድ የሰራነው ፓርቲ ነው ማለታቸው ልብ ይሏል።
v የህወሓት መሪዎች ህግን ሽፋን በማድረግ ያሹትን ሲፈጽሙ ነበር የሚለው ክስ ከምር ለህግ የበላይነት መከበር ካለን ተቆርቋሪነትና ታማኝነት የመነጨ/የሚመነጭ ከሆነ፤ በአደባባይ በህግ ሽፋን ነገሩን ማከናወን አንሶት የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነ ህገ መንግስቱን በመጣስ የወደደውን በመሾምና በመሻር ኢትዮጵያ የአንድ ግለሰብ ርስት እያደረጋት ያለው ዐቢይ አህመድ አይደለምን?
v ለዐቢይ አህመድ ያለን ድጋፍ በአደባባይ በከፍተኛ ሁኔታ የገለጽንበት ምክንያት፥ ዐቢይ ወደ ስልጣን እንደመጣ ኮማንድ ፖስቱ ከላይ ላያችን በማንሳት ሸክማችንን ያቀለልን ሰው ስለነበር ከሆነ ይኸው፥ ከሞላ ጎደል ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኮማንድ ፖስት የትምትገዛ አገር ሆናለች። በሱማሌ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ ወዘተ የተደረገና እየተደረገ ያለ አረመኔያዊ ድርጊት ለሁላችን ግልጽ ነው። እንግዲህ የመዋሸት አመል ያለበትና ጥላቻ የጸናበት ሰው ካልሆነ በስተቀር የህወሓት መሪዎች ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በአውሮፕላን የደበደቡት ህዝብና ክልል አለ ለመለት የሚደፍር ሰው የለም። በለውጥ ስም ወደ ስልጣን የመጣ የዐቢይ መንግስት ግን ተዋጊ አውሮፕላን አሰማርቶ የወላጋ አከባቢ ነዋሪዎች እንደጨፈጨፈ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ሰራዊት በማዝመት የክልል ርዕሰ መስተታድር መገልበጥ እንደተቻለው በፓርላማ በግልጽ ተናግሯል። ጥያቄ የሚያነሳ ሌላ ህዝብም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ የዛተው በይፋ ነው።
v ጠ/ር ዐቢይ አህመድ በአሁን ሰዓት የቀረው ነገር ቢኖር የጀመረው ማስፋና በዓለም መድረክ አምባገነን ተብሎ መታወቅ ካልሆነ በቀር በስራው እነ ማኦና ጆሴፍ ስታይን ያልመሰለበት ነገር ተፈልጎ አይገኝም። ሲዋሽ አቡሃ ለሐሰት (የሐሰት አባት) ነው፤ በተለመደው መንገድ አስተካክለዋለሁ ብሎ ፎክሮ የፎከረውን ያደረገ ገዳይ ነው፤ ስድብ፣ አሽሙርና ማሽሟጠጥ ስራው ነው፤ በህግ ሽፋን የሚሰራ ህገ ወጥ ስራ እንደሆነም ተክኖበታል፤ የሥልጣን ዘመኑ በማራዘም የአገሪቱ የገንዘብ ኖት መለወጥ ተችሎታል፤ ይቀናቀኑኛል የሚላቸው ግለሰቦች ማጠልሸት፣ መቅጨትና ማጨናገፍ ስራው ሆኗል። የኢትዮጵያ ብልጽግና ሊያረጋግጥ የሚችል ሰው እኔ ብቻ ነኝ! ብሎ የሚያምን፤ በለውጥ ስም በሰፊው እየሰራው ያለ ስራ/ፕሮፓጋንዳ የኢትዮጵያውያን ህይወት ለመለወጥ ሳይሆን የግሉ ስምና ዝና ግንባታ ላይ የተጠመደ ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ግለሰብ የበላይነትና የአምባገነን ስርዓት ለመትከል ሁሉን ነገር አድርጓል እያደረገም ይገኛል።
ስንቱን ዘርዝሬ እዘልቀዋለሁ። ለውጥ ተብሎ የሚነገረው ነገር፥ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የህዝቡን ልብ ማናወጥ ማለት ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ነውጥ እንጅ ለውጥ የለም። ለነገሩ አልበርት አንስታይን፥ “ዓለም ክፉ በሚያደርጉ አመጸኞች አትጠፋም፤ ይልቁንም ምንም ሳያደርጉ በሚመለከቷቸው እንጂ” እንዳለው ነው።
E-mail: mahbereseytan@gmail.com
|