Back to Front Page

ይድረስ ለህወሓት አመራርና አባላት በሙሉ

ይድረስ ለህወሓት አመራርና አባላት በሙሉ

 

ዑስማን ሙሉዓለም

ታህሳስ 21/2012

 

በቅድሚ እንኳን ለአርባ አምስተኛው የህወሓት ልደት አደረሰን ስል በትልቅ የትግል መንፈስ ነው። የካቲት 11 የጭቁኖች የትግል ልደትቀን ናት። የህዝብ ወገንተኝነት በተግባር የተጀመረባት ልዩ ቀን ናት። እንደገና መልካም ልደት! እላለሁ፡፡

 

የዘንድሮ የካቲት 11 በዓል ልዩ የሚያደርገው የትግራይ ህዝብ ከጫፍ ወደ ጫፍ በታላቅ የትግል መንፈስ ህገመንግስታችንና ፌደራላዊ ስርዓታችን እያፈረሰ ያለውን የአብይ አንጃ ቡዱንና መንግስትን ለመታገል ቆርጦ መነሳቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት የሚከበር መሆኑ ነው። የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ከኢህአዴግ ውስጥ የበቀሉ አረሞች ኢህአዴግን ውጠው አፍርስው ትክክለኛ ማንነታቸውን የሚወክልላቸው ጥገኛ ፓርቲ ሲመሰርቱ መሪ ድርጅቱ ህወሓት ግን በአቃሙ ፀንቶ የህዝብን አደራ አልበላም ብሎ እምቢ ማለቱ ሁለት ስሜቶች ጭሮውበታል። በአንድ በኩል ኩራት እና ደስታ በሌላ በኩል ቁጣ እና ስጋት ፈጥሮበታል።

 

የትግራይ ህዝብ ሁሌም አለኝታዬ ነው የሚላት ህወሓት በመስመሯና በህዝብ ጎን አሁንም በመቆም የወሰነችው ውሳኔ ይበልጥ እንዲኮራ እንዲደሰት አድርጎታል። በሌላ በኩል ልጆቹን የከፈለለት ዓላማና ስርዓት ባለፉት ሁለት ዓመት የውጭ ሃይሎች ተላላኪ በሆኑ ቡዱኖች ለውጡ ተቀልብሶ ትላንትና የገነባው የሚፈርስበትና የሚሸጥበት ሁኔታ መፈጠሩና ትላንትና በፍጥነት ሄደች ተመነደገች ስትባል የነበረች ሀገር ልትፈራረስ ህዝቦቿ ለእርስ በርስ እልቂት እየተዘጋጁ መሆኑን ሲያይና ሲሰማ ቁጣና ስጋት ተሰምቶታል።

 

ህወሓት ይህ የህዝብ ስሜት ተገንዝቦ ህዝባዊ ኮንፍረንስ መጥራቱ ምን ያህል ለህዝብ እንደወገነና የህዝብ ስሜት እንደሚረዳ የሚያሳይ ነው። የየካቲት 11 አንድ አደራ መጠበቁን በተግባር የሚያሳይ ነው። በህውሓት እንኮራለን። አንድ ወዳጄ የውጭ ዜጋ ያለኝን ጀባ ልበላቹሁ። የህወሓት ታሪክ ወደቁ አለቀላቸው ስትባሉ ምድር ልሳቹሁ ተነስታቹሁ አለን ትላላቹሁ። ዘንድሮስ ይህን ምድር ልሶ መመለሱን ልታሳዩን ትችላላቹሁ ወይ? ብዬ ፈርቼ ተጠራጥሬ ነበር ግን አሁንም ያን ታሪካቹሁን ልትደግሙት መሆኑን እያየሁ ነው ቀጥሉበት አለኝ። የፈጠረልኝ ስሜት መግለፅ የማልችለው የውስጥ መንፈሴ ሲታደስ የበለጠ መሪ ድርጅቴን እንድወድ ያደረገኝ ስሜት ነው።

 

Videos From Around The World

በአገራችን በዚህ ሁለት ዓመት ሁለት የለውጥ መዘውሮች ታይተዋል። የለውጥ መዘውር ትርጉም ላይ መጀመርያ ብንስማማ እኔ የሰጠሁት ትርጉም ልግለፅ። አንድ ነገር በመሰረቱ ባህርዩን ቀይሮ ሲገኝ ለማለት ነው። ይህ ለውጥ ከለውጡ በፊት ወደ ነበረበት የማይመለስ ለውጥ ነው። ለውጡ ከመጥፎ ሁኔታ ተላቆ ወይም በጎ ገፅታውን ትቶ ወደ ተቃራኒው ገፅታና ይዘት ሲቀየር እምርታ ሲያሳይ ነው። በዚህ አርእስት በአገራችን በዚህ ሁለት ዓመት የታዩ ሁለት መዘውሮች ስል ከመሻሻል ይልቅ ወደ የማይመለስ ችግር ወደ የማይታከም በሽታ ሽግግርን የሚያሳይ የለውጥ መዘውሮችን ለማሳየት ነው።

 

አንዱና የመጀመርያው በኢህአዴግ ውስጥ የሊቀመንበር ምርጫ ሂደትና ውጤት ወቅት የታየው ነው። ሁለተኛው ኢህአዴግ በህግ ፈርሶና በምትኩ ፒፒ ነኝ የሚል ፓርቲ ተመስርቶ በህዝብ ሳይመረጥ መንበረ ስልጣን ሲቆጣጠር ነው። እነዚህ ሁለት ክስተቶች ለምን የለውጥ መዘውሮች ናቸው እንዳልኩኝ ቀጥዬ አብራራለሁ።

 

ኢህአዴግ በሃይለማርያም ምትክ ሊቀመንበር ለመምረጥ ሲቀመጥ የመጣው ውጤት የዘራውን ነው ያጨደው ብሎ ዝም ማለት ይቻላል። ምንስ አደረገና? ኢህአዴግ ወደ ምርጫ የገባው የጥልቀት ተሃድሰው በቅጡ ሳይፈፅመው ከማለት ሳይጀምረው ነበር ማለቱ ይሻላል። ስለዚህ የምርጫው ውድድር በጥልቀት ባልታደሱ ዕጩዎች መካከል ነበር። ይህ መሆኑ ብቻውን ችግር አልነበረውም። የለውጥ መዘውር ያስባለኝም ይህ ሁኔታ እያለ ምርጫ ማካሄዱ አይደለም። የለውጥ መዘወር ነው ያሰኘኝ ምርጫው ከኢህአዴግ አሰራር ውጭ በውስጡ በተደራጁ አካላት ከምርጫው በፊት ውጭ ተስማምተውና የሚመርጡትን ወስነው መግባታቸው ነው። ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ አግባብ ስልጣን መቆጣጠር መቻላቸው ነው።

 

የለውጥ መዘውር የሚያስብለው ከፍተኛ ተጨባጭ ተቃውሞ የተነሳበት ግለሰብ ዕጩ ሆኖ ቀርቦ ውጭ ወስነው በገቡ የምክርቤቱ አባላት ተመርጦ ሊቀመንበር መሆኑ ነው። በቆየው አሰራር ሳይደራጅ ገብቶ የግለሰብ አስተያየቱና አቋሙ ይዞ ወደ ስብሰባ የሚገባና በእህት ድርጅት ላይ ቀዋሚና ጥላቻ ይዞ፣ በተደራጀ ሐሳብና አቋም፣ አድመኛ ቡዱን መካከል ቀዋሚ የሆነ የልዩነት መስመር ተፈጠረ። የፓርቲው አንድነት ላንዴና ለመጨረሻ የከፈለ ተግባር ነበር።

 

ይህ በድርጅት ውስጥ የተፈጠረው ችግር እንዳይፈታ ሁለት ነገሮች ሆነ ተብለው በአድመኛው አንጃ ተፈፀሙ። መጀመርያ አሜሪካ አዲሱ አመራር ለትውውቅ ብሎ ሄዶ ውጭ ለሚኖሮ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (አብዛኞቹ በቅንነት የተሰበሰቡ ቢሆንም ቀላል የማይባሉት ፀረ ህዝቦችና የተሸነፉ ደርጎች) ሰብስበው በግልፅ በኢህአዴግ ውስጥ ሁነው ኢህአዴግን መፋለማቸው ወያኔን ማባረራቸው በመግለፅ አስጭበጨቡ። አገር ቤትም ሃያ ሰባት የጨለማ ዓመታት ነበር። ወያኔ ነው ተጠያቂው ብለው በድፍረት ተናገሩ። ይህ እያሉ ህወሓትን ደግሞ ለውጡን መቀበል አለባቹሁ ብለው ይወተውታሉ። ሁለተኛ የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ እንዳይቀጥል ለማድረግ ነበር ሆነ ብለው የፈፀሙት። ይህም መድረክ በመከልከልና በህወሓት ውትወታ ስብሰባ ቢደረግም አድመኞቹ ተደራጅተው አጀንዳ በማስቀየርና ሌላ ጊዜ ብለው ቀነ ቀጠሮ በማብዛትና ስብሰባዎቹ አጫጭርና ስብሰባው ላይ የተባለውና ለአባላትና ለህዝብ የሚሰጠው መግለጫ የተለያየ እና ሆነ ተብሎ የሊቀመንበሩና አድመኞቹ ሐሳብ ብቻ የሚያንፀባርቅ ሆኖ ይገለፃል።

 

በሚድያ ፀረ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በግልፅ ዘመቻ ከፍተው በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻ ሰበኩ። ለህወሓት አርባኛ የልደት በዓል የተገኙ አርቲስቶች መርጠው ያኔ ለምን ሄድክ? መሄድህ አሁን ይቆጭሃል ወይ? ብለው እንዲጠየቁ በሚድያ ቁም ስቅላቸውን በማሳየት የሚድያ ጦርነት ከፈቱ።

 

ህወሓት በምርጫው ማግስት ጀምሮ ሁኔታውን በትክክለኛና ሳይንሳዊ ትንታኔ በማስቀመጥ ትክክለኛ ግምገማ አድርጋል። በኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ እንዲደረግ ምክንያት የሆነው የስርዓቱ አደጋ እንደሆነ (1993 ዓ/ም ጀምሮ የለየው የጥገኝነት ዝቅጠት ችግር የክራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር መዘፈቅ ያመጣው) ተገንዝቦና መጀመርያ ህወሓት በራሱ ውስጥ ያለው ህዝባዊነቱን የሸረሸረው ይህ አደጋ መፅዳት አለብኝ ብሎ ፀድቶ ለመገኘት የጀመረው የውስጥ ትግል በሌሎች ድርጅቶች ሳይካሄድ የተደረገው ምርጫ ከዚህ ውጭ ውጤት ሊኖረው አይችልም ብሎ ገምግሟል። ከዚህም በመነሳት የተመረጠውን ሊቀመንበር መደገፍ እንዳለበት የሱ ውድቀት የህዝባችን የአገራችን ውድቀት ነው ብሎ ከልብ አቅጣጫ አስቀመጠ። ትብብሩን በተግባር አሳየ። የማግለል እንቅስቃሴው እያየም መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በማትኮር ኢህአዴግ የሚድንበት ሁኔታ እንዲመቻች መድረክ እንዲፈጠር ትዕግስት አስጨራሽ ሙከራዎች ቢያደርግም በአንድ እጅ ማጨብጨብ ስለማይቻል ሳይሳካ ቀረ። ገዥው ፓርቲው በገዥው ሊቀመንበር እየተተካ አብሮ መወሰን ቀረ። አንድ ሰው ብቻውን ያሻውን ይወስን ጀመረ። በትግራይ ህዝብና በመሪው ድርጅት ህወሓት ላይ ሁለ ገብ ጥቃት ከመሻሻል ይልቅ እየባሱ መጡ። በግልፅ ኢህአዴግ በጥገኞች ስር መውደቁ መረጋገጡ ብቻ ሳይሆን የመዳን ዕድሉ እየጠበበ እንደመጣ ገሀድ ሆነ። ህወሓት በአንድ በኩል እየተጠቃ ያለውን ህዝብ መታደግ በሌላ በኩል ሀገራዊ ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ እያገረሸበት ወደ መበታተን ማምራቱ ቢያሳስበውም ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ የሚሰበከው የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ሚናውን ሊጫወት ቢሞክርም ሌላ ትርጉም እየተሰጠው ሆን ተብሎ እንዲቀረቀር የተደረገበት ሁኔታ ተፈጠረ።

 

ትብብር ድጋፍ ከውስጥ ይልቅ የውጭ የሚቀናው የአብይ መንግስት አገሪቷን መምራት አቅቶት ሁሉም ነገር ትርምስምሱ የገባበት ሁኔታ ተፈጠረ። የአገራችን ሁኔታ ከቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ ሆነ። ቀውሱን ከመፍታት ይልቅ ቀውሱን የሚያስረሳ አጀንዳዎች በተከታታይና በማያቃርጥ በመፍጠር የአብይ መንግስት ዕድሜውን ለማስረዘም ብቻ ጥረት አደረገ። ለቀውሱ ምክንያት ለውጡን ያልተቀበሉ፣ ሦስተኛ ወገን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይቅርታ ብለን አበባ ይዘን ያመጣናቸው ያጎረስንበት ጣታችን ነከሱን ይላል። ጣቱን ወደ ሌላ ይቀስራል። የራሴው የአመራር ችግር ነው የሚል ፈፅሞ አይወጣውም። ካልሆነም የበታቾቹን ተጠያቂ ያደርጋል እንጂ የአመራር ውድቀቱን መቼም ቢሆን አያይም።

 

የዚህ የለውጥ መዘውር ውጤት ምንድነው? አገራችንን በፍጥነት ዘርፈ ሁሉ ለውጥ እንድታመጣ ያደረገው አብዮታዊ ዲሞክራሲ በጥገኛ ለበራላዊ ስርዓት የሚተካ ቁርጠኛ ጥገኛ ሀይል በትረ ስልጣን መቆጣጠሩ ነው። በዚህ ምክንያት ኢህአዴግ የህዝብ ጥያቄዎችን እፈታለሁ ብሎ ቃል የገባውን ባለመመለሱና መመለስም የሚችል ባህሪ ስለሌለውም በአገሪትዋ ለውጥ መጥቷል ብሎ መረጋጋት ጀምሮ የነበረው ህዝብ በተለይም ወጣቱ ጥያቄያችን አልተመለሱም በሚል ተቃውሞውን በመቀጠሉና የአብይ መንግስት ይህን ተቃውሞ ለመጨፍለቅ በመሞከሩ በሁሉም የአገራችን ማዕዝን ግጭቶች በቀጣይነት እየታዩ ነው። ጆኖሳይድ በብዙ ቦታዎች ተፈፅሟል። አሁን ሰላም አንገብጋቢ የህዝቡ ጥያቄ ሁኗል። ብዙ ክልሎች ባልታወጀ ህጋዊ ባልሆነ ፓርላማ በማያቀው ጊዚያዊ አዋጅ እየተዳደሩ ይገኛሉ። ከሦስት ሚልዮን ህዝብ በግጭት ተፈናቅሎ እየተሳቃዬ ነው። ብዙ ሺዎች በፖለቲካ ምክንያት ታስረው ያለፍትህ እየተቸገሩ ነው። ሰዎች ባሰኛቸው ከአካባቢያቸው ወደ ፈለጉበት የማይንቀሳቀሱበት በስጋት የሚቀሩበት አገር ሁኗል። በዚህም ዩኒቨርስቲዎች በብዙ ቦታዎች መረጋጋት የሌለባቸውና ተማሪዎች በማንነታቸው በድንጋይ ተወግረው የሚገደሉበትና የትምህርት ስርዓት እየተቃረጠ በመዘጋት ይገኛሉ። በሰላም ዕጦትና የሚመራው ያጣው ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በመግባቱ ኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ ህዝቡን የሚያማርር ሁኗል።

 

ላይ ያየናቸው ክስተቶች ይህ በአብይ የሚመራው አንጃ መመረጥ ምክንያት የመጡ ለውጦችን ነው የለውጥ መዘውር የምለው። ላይመለስ ወደ ሌላ ሁኔታ ተዘውሯል ባይ ነኝ። አገራችን ከሰላም ወደ መረጋጋት የጠፋባት የስጋት ቀጠና ተቀይራለች። ከልማት አጀንዳ ወደ ጥላቻ፣ ግጭትና ትርምስ አጀንዳ ተዘውራለች። ይህን የተዘወርንበት ለውጥ ለማየት ሚድያዎቻችን ብቻ በማየት መመስከር ይቻላል። ሁሉም በሚባል ደረጃ ኢሣትን የሚያስንቁ ሁነው ተለውጠዋል። ጥላቻን የሚሰብኩና ግጭት እንዲፈጠር የሚሰብኩ ሁነዋል።

 

ሁለተኛው የለውጥ መዘውር የምለው የአብይ አንጃ ቡዱን ኢህአዴግን አፍርሶ የሱ የሆነችውን ፒፒን መፍጠሩ ነው። መፍጠሩ ደግ ነው። ለምን ብትሉኝ ጥገኛ አስተሳሰቡን የሚያራምድበት ፓርቲ ያስፈልገዋልና! በሱ ቅድ ባልተሰራ ኢህአዴግ ጥገኛ የሆነውን አስተሳሰቡን ይዞ ስልጣኑን ማስቀጠል አይቻለውምና። መደራጀቱ ስህተት የለውም። ይደራጅ። በዚህ አዲስ ፓርቲው ስልጣኑን ማስቀጠል ግን አይችልም። ሁለተኛው የለውጥ መዘውር የምለው ያልተመረጠ ፕርግራም ይዞ ያልተመረጠ ድርጅት ይዞ ስልጣን መያዝ አይችለም። ግን ችሏል። ይህን በተመለከተ እውቁ ሙሁር ፀጋዬ አራርሳ ከማዶ አውስትራሊያ ሆኖ ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ያለው ነው። የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮንም በቅርቡ ሳይቀር ደጋግመው ያሉት ጉዳይ ነው። ሌሎች የህግ ባለሙያዎች እየገለፁት ያለ ጉዳይ ነው። አሁን በአገራችን በህዝብ የተመረጠ ፌደራላዊ ይሁን ክልላዊ መንግስት ከትግራይ ክልላዊ መንግስት በስተቀር የለም። ታድያ በህዝብ የተመረጠ መንግስት የለም ብለን ዝም ማለት እንችላለን? ለውጡ ከህገመንግስታዊ ወደ አምባገናናዊ ስርዓት በግላጭ የተለወጠ መሆኑን መግለፅ ብቻ በቂ ነው ወይ?

 

የመጀመርያው ለውጥ በህዝብ በተመረጠው ፓርቲ ውስጥ ያለ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። አብይን ወደ ስልጣን ያመጣው ኢህአዴግ ራሱ ነው ኢህአዴግ ያርመው ካላረመው ብምርጫ እንቀጣዋለን ብሎ ህዝቡ ሊጠብቅ ይችላል። ባልተመረጠ ፕሮግራምና ድርጅት መመራት ግን ሌላ ጉዳይ ነው። ህዝቡን መናቅ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲኮኞች ጭራሽ ማሳነስ ነው። ኦህዴድ ውስጥ ሊሸውድ ይችላል። ኢህአዴግንም አንጃ ፈጥሮ አሰራሩን ለጥቅሙ አውሎ የነበረው የውስጥ በሽታ ምቹ ሁኔታ ረድቶት ጠቅላይ ሚኒስትርነትን እሺ ይቆጣጠር። ግን ባልተመረጠ ፕሮግራምና አዲስ ፓርቲ ስልጣን ማስቀጠል ግን ሊፈቀድለት አይገባም!

 

የህወሓት አመራርና አባላት ሆይ በቅርቡ የተካሄደው በታላቅ የትግል መንፈስ የተካሄደው ህዝባዊ ኮንፍረንስ ህዝቡ ለማንኛውም መስዋእትነት ከጎናቹህ ነኝ ብሎ ቃል ገብቷል። ቀጣዩ የድርጅቱ አስቸካይ ጉባኤ ታድያ ምን ይጠበቅበታል? ወደ ፒፒ አንገባም ብሎ መወሰን ብቻ ይሆናል ብዬ አልገምትም። የህወሓት ስራ አስፈፃሚውና በኃላም የህወሓት ማ/ኮሚቴ በታላቅ ህዝባዊነትና ቆራጥነት የወሰነውን ውሳኔ በአስቸካይ ጉባኤው በነፃ ተሳትፎ ማስወሰን ተገቢ ነው። ህዝባችን ከጎናቹህ ነኝ ሲል ለዚህ ውሳኔ ብቻ አይደለም። ህወሓት በቀጣይ ለምትወስናቸው የትግል አቅጣቻዎች ደጀንነቱን ነው በውሳኔው እየገለፀልን ያለው እላለሁ። ታድያ ከአስቸካይ የህወሓት ጉባኤ ምን ይጠበቃል።

 

1ኛ) አሁን በስልጣን ያለው መንግስት በህገመንግስቱ ከተደነገገው ውጭ ስልጣን በመያዙና በተመረጡበት ፕሮራምና ለዚህ ስልጣን ዕጩ አድርጎ ያቀረባቸው ድርጅት ኢህአዴግም ኦህዴድም በከሰመበት ሁኔታ ስልጣን ላይ መቆየት ለአንድ ሰከንድም ስለማይችል ስልጣኑን ለቆ በህገ መንግስቱ ሌላ ማተካከያ (arrangements) እንዲደረግ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በመሆን መታገልና መቃወም ይጠበቅበታል።

 

2ኛ) ይህ ህጋዊነት የሌለው መንግስት የተቆጣጠረ ሀይል ማንኛውም የሚወስነው ውሳኔ ተቀባይነት የለውም። በዚህ ህጋዊ ያልሆነው መንግስት የህወሓት አባላት በመሆናቸው ተሽመው በስራ የሚገኙ ሃላፊዎች ከሀላፊነታቸው በተቃውሞ መልቀቅ አለባቸው። ወይም ህወሓት አባላቱን ሰብስቦ እሱ ወደ መረጠው የስራ ሐላፊነት ማዛወር አለበት።

 

3ኛ) በአብይ መንግስት ተመርጠው ለፓርላማ ቀርበው የተሾሙት የምርጫ ቦርድ ይህ ህገ መንግስትን የተፃረረ አደረጃጀት በቸልተኘነት ወይም ሆን ብለው በተፋጣነ መንገድ በልዩ ሁኔታ የእውቅና ምስክር ወረቀት መስጠታቸው፣ በሲዳማና በሌሎች የተጠየቁ የህዝብ ጥያቄዎች አመላለስ ወቅት ባሳዩት ስህተት፣ የገዥው ወገን አስፈፃሚዎች እና አዜማ የተባለው ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ውስጥ ሰዎች አሉኝ ሲል ማስተባበያና እርምጃ እንዲወሰድባቸው አለማድረጉ እንዲሁም የወ/ት ብርቱካን ድሮ የቅንጅት ደጋፊና ህገ መንግስት በመፃረር ተከሰው ተፈርዶባቸው የነበሩ ሰው ገለልተኛ ስለመሆናቸው መተማመን ስለማይቻል ጠቅላላ ምርጫ ቦርዱ ላይ ለውጥ እንዲደረግበት መታገል ይኖርበታል። ምርጫ 100% አሸንፋለሁ። ኮሮጆ መስረቅ አያቅትኝም የሚል ጠቅላይ ሚኒስተር በግሉ ወደ ፓርላማ ያቀረበው ምርጫ ቦርድ ተዓማኒነት ሊኖረው አይችልም። ምርጫ መቼ እንደሚደረግ ከኖርወይ ተነግሮት የሚያውጅ በፍፁም የምርጫ ዳኛ ሊሆን አይችልም። በውጭ መንግስታትና አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚደገፍና ባጀቱ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ቦርድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሊሆን አይችልም። ይህን አጥብቆ መታገል ለሉዓላዊነታችን መቆማችን መገለጫ ነው።

 

4ኛ) በቅርቡ መድረክ ብሎ ራሱን ያደራጀው ህገመንግስታዊና ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማዳን ሀገራችንም እናድን ብሎ የተነሳው ሃይልንም የትግላችን አጋርነቱ እንዲጠናከር የሚያስችል ውሳኔ ከሚካህደው አስቸካይ ጉባኤ ይጠበቃል።

 

5ኛ) በመጨረሻ ግን ከሁሉም በፊት አገራችንና ክልላችን አሁን ወደ ገባንበት ችግር የከተተን በ1993 የምንገነባው ስርዓት ቁልፍ ችግር ብሎ የተሀድሶ መስመራችን በግልፅ ያስቀመጠው የክራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር አደጋነቱን ከልብ ባለመውሰዳችንና ባለመታገላችን ነው። አሁንም መውጫው ይህ በሽታ የለከፈው ስልጣን ላይ የወጣውን ሐይል ለመግጠምና ለማሸነፍ የምንችለው፣ እኛም ውስጥ ከዚህ አደጋ በአመለካከትም በተግባርም ፀድተን ስንገኝ ነው። ህዝቡን ስናገለግልና በየዕለቱ በጥገኛ መንገድ ስልጣንን መሰረት ያደረገ ጥቅምና ስልጣንን የህዝብ መገልገያ መሆኑ ቀርቶ ለግል የስልጣን ጥም የሚያውሉ ጓዶቻችንን ስንታገላቸው ነው። ህዝቡ በህዝባዊ ኮንፈረንሱ የወሰነውን ውሳኔ ተግባራዊ የሚያደርገውና በዘላቂነት ከህወሓት ሆኖ መታገል የሚችለው እኛ የእውነት የህዝብ አገልጋይ ሁነን ስንገኝ ነው። ስለዚህ አስቸካይ ጉባኤያችን ሊቀመንበራችን ደብረፅዮን እንዳሉት የህዝብ ተላላኪነታችን በትግል የምናረጋግጥበት እንዲሆን ህዝብን ለማገልገል የህዝቡ አገልጋይነታችን ከአደራሽ ውጭ በተግባር እንዲረጋገጥ እንደምንታገል ቃል የምንገባበት ጉባኤ እንዲሆን ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ባንዳነት በግልፅ ፀረ ትግራይ አንድነት ቆሞ ከፀረ ህዝቦች መሰለፍ ብቻ አይደለም። ንግግርና ተግባር አንድ ሳይሆን ቀርቶ ህዝባችን አለማገልገልና ማንገላታትም ባንዳነት ነው። አንድነታችንን የሚፈታተን ውጤት ስላለው አጥብቀን የምንታገለው መሆን አለበት። መሬት ልሶ መነሳት ልማዱ የሆነው ድርጅታችን ሲቆርጥ የማይሳነው ነገር የለም። እንደሚያሳካው አልጠራጠርም።

 

መልካም ልደት ለህወሓት!

ህዝባዊ ትግል ሁሌም ያሸንፋል!

ጥገኞች በህዝብ ትግል ውድቀታቸው አይቀሬ ነው!

 

Back to Front Page