Back to Front Page

ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች

ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች

Qananii Maatii 09-22-20

 ኢትዮጵያ እንደማንኛዉም አገር በተለያየ መስክ ዕዉቀት የተካኑ ምሁራን ያላት ቢሆንም ከሌሎች አገራት በተለየ ሁኔታ ከአገር ማባረርን ጨምሮ የተለያዩ የአፈና ዘዴዎችን በመጠቀም አገራቸዉን እንዳያገለግሉ ከልክላችሁ በተቃራኒዉ እናንተ አንድም የታወቀ ኮሌጅ ግቢ ሳትረግጡ ባለብዙ ድግሪ የሆናችሁ ሰዎች ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ሥልጣን ይዛችሁ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ በታሪካቸዉ አይተዉት የማያዉቁት ግፍ በመፈጸም ላይ ትገኛላችሁ።

 ይህን መልዕክት እንዳስተላልፍላችሁ ያስገደደኝ በአሁኑ ጊዜ ሥልጣንና ከህዝብ የዘረፋችሁት ሀብት አስክሮአችሁ በህዝብ ላይ እየፈጸማችሁ ያለዉን ግፍ ከዛሬ-ነገ ቆም ብላችሁ ምን እያደረግን ነዉ ያለነዉ? በዚህ ሥራችን ነገ ይህ ህዝብና አገር ምን ሊገጥመዉ ይችላል? የኛስ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆናል? በማለት ከአረመኔያዊ ተግባሮቻችሁ ትታቀቡ ይሆናል ሲባል፤ ስካራችሁ ጭራሽ ወደ እብደት ተሸጋግሮ እያደረሳችሁበት ያለዉ ግድያና አፈና ያነሰ ይመስል ”የኦሮሞ ህዝብ በክልልሉ ዉስጥ በሚኖሩ አማራዎች ላይ ’genocide’ እያካሄደ ነው” የሚል ፕሮፓጋንዳ ሚዲያና የዉጭ ኤምባሲዎቻችሁን ተጠቅማችሁ በተቀናጀ ሁኔታ በመርጨት ላይ መገኘታችሁ ነዉ።

Videos From Around The World

 ይህ እጅግ አሳዛኝ ድርጊታችሁ የሚያሳየዉ የቱን ያህል የኦሮሞ ህዝብ በሌሎች እንዲጠላ ብሎም እንዲጠፋ እንደምትመኙ፤ አሁን በጠመንጃ የምትፈጁት አንሶ ቢቻላችሁ የራሱ ህዝብ የሆኑትን ኩርዶችን በኬሚካል መሳሪያ ለማጥፋት በመሞከር ብቸኛዉ የዓለማችን ሰዉ እንደሆነዉ ሳዳም ሁሴን ከማድረግ እንደማትመለሱ ነዉ።

 ደግነቱ እናንተ ዕዉቀትን ሳይሆን ዉዥምብርና ወሬን ሥራ አርጋችሁ ስለኖራችሁ ዕዉነታ (fact) ምን እንደሆነ ስለማታዉቁ ዋሽታችሁ የምታመልጡ መስሏችሁ ነዉ እንጅ የአማራ ህዝብ በኦሮሚያ ዉስጥ ባሉ ከ600 በላይ ከተሞች፤ ከ7500 በላይ የገጠር ቀበሌ አስተዳድሮችና ከ27000 በላይ የገጠር መንደሮች ዉስጥ ከኦሮሞ ወገኖቹ ጋር ተዋድዶ በሰላም እንደሚኖርና፤ ጥቃት ደርሶም ከሆነ የናንተዉ ተግባር ስለሚሆን በ’GIS’ ተቀናብሮ ባለ መረጃ መሠረት በየትኛዉ ስፍራ፤ ስማቸዉ ማን-ማን በሚባል ግለሰቦች ላይ ምን-በማን-መቼ እንደተደተፈጸመ ተጣርቶ ወደፊት ለኢትዮጵያና ለዓለም ሀዝብ ተገልጾ እርቃናችሁን እንድትቀሩ ይደረጋል።

 በተመሳሳይ ሁኔታ ህዝብን ከህዝብና አንዱን ኃይማኖት ከሌላዉ የማጋጨት ሙከራ በህዝብ የሚታወቅ ተግባራችሁ ሆኖ እያለ ሌሎችን፤ በተለይም ጀዋር መሐመድና በቀለ ገርባን ብትከሱም፤ ይህን የትና መቼ እንዳደረጉ የሚያሳይ ቅንጣት ታክል እንኳ ማስረጃ ማቅረብ አልቻላችሁም። ይልቁንም እጅግ በሚያሳዝንና በሚያስገርም መልክ ኦሮሚያን በአካባቢ ለመከፋፈል የምትሞክሩትን ሴራ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ በማሰብ “እኔ ወለጋ ሄጄ ብሞት የጅማና የወለጋ ህዝብ ጦርነት ዉስጥ ይገባል” በማለት መቼም ቢሆን ይቅር የማይባል በደል በኦሮሞ ህዝብ ላይ የፈጸመዉ የናንተ መሪ ነዉ።. ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ላይ መድረክ አዘጋጅቶ “ኦሮሞ አገሩ ማዳጋስካር ስለሆነ ይዉጣልን....” ያለዉ ማነዉ? ሀጫሉን የገደላችሁት ዕለት ሀዝብ ሃዘኑን ለመግለጽ ሲወጣ ልደታ ቤተክርስቲያን ደወል በማስደወል “ኦሮሞ ሊወራችሁ መጥቷልና ራሳችሁን ተከላከሉ” ያለዉ ማነዉ? “ግብፅ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ድጋፍ እየጠየቀች ነዉ፤ በቀለ ገርባን ግንባሩን በጥይት ማለት ያስፈልጋል፤ እምቢ ብሎ ወደ መንገድ የሚወጣዉን ወጣት በጥይት ማለት ነዉ”፤ ያለዉ ‘OMN’ ሳይሆን የናንተ ሚዲያ አይደለምን?

 ከህዝብ ተነጥላችሁ ራሳችሁን ብቻ ሰለምታዳምጡ ነዉ እንጅ እያንዳንዱ ሰዉ በአሁኑ ጊዜ የምትሠሩትን በቻ ሳይሆን ለመሥራት ያቀዳችሁትን ተንኮል ጭምር ያዉቃል። ከነዚህ ዉስጥ ጀዋር መሐመድን አስመልክቶ ሕዝብ የሚለዉን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። የቀረበበት ክስ አመጽ ቀሰቅሶ ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መዉደም ምክንያት ሆኗል የሚል ነዉ። ነገር ግን እናንተ ልትገድሉት ስትሞክሩ ወጣቱ በንዴት ገንፍሎ ሲወጣ እንደገና በድብቅ ባደራጃችኋቸዉ ወንጀለኞች እነዚህን ወጣቶች በተለያዩ ስፍራዎች (በተለይም በአዳማ ከተማና አካባቢዉ በሚዘገንን ሁኔታ) ማስገደላችሁን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የመግደል ሙከራችሁ ቢሳካ ኖሮ መሪያችሁ ልክ “ሀጫሉን ለ10 ዓመታት አዉቀዋለሁ” እንዳለዉ ሁሉ በቲቪ ቀርቦ “ከጀዋር ጋር ለ15 ዓመታት እንተዋወቃለን፤ ለኦሮሞ ህዝብ አብረን ብዙ የሠራን ወንድሜ ነዉ፤ እሱን የገደለ እኔን የገደለ ነዉ፤ ወዘተ” በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ ይል እንደነበር የታወቀ ነዉ። ይኸ መሪያችሁ ለበርካታ ዓመታት የኖራችሁበትን ባዶ የካድሬ ዲስኩር ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማሸጋገር እንደ ነቢይ እንዲቆጠር በማሰብ በዓል በመጣ ወይም አንድ ድርጊት በተፈጸመ ቁጥር ካሰባሰባቸዉ ጥቅሶች ጋር በማዋሃድ ስለ ሰላም፤ እርስ በርስ ስለ መዋደድና መከባበር በሚያደርገዉ የማስመሰል ስብከት ህዝብ እንዲያመልከዉ ይመኛል። አሁን ያለው ታሪክ ሌላ ቢሆንም በዚህ የማስመሰል ተግባሩ የዚህን አገር ብቻ ሳይሆን የዓለምን ህዝብ ቀልብ በመግዛት የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ለመሆንም በቅቶ ነበር። ነገር ግን ሽልማቱን ሲቀበል ሌሎች ያዘጋጁለትን ጽሑፍ ለረጅም ጌዜ አጥንቶ ካደረገዉ ንግግር ዉጭ የቋንቋም ሆነ የሌላ ነገር ዕዉቀት ስለሌለዉ እንዳይዋረድ በመፍራት ማንም ታዋቂ ሚዲያ ፊት አልቀርብም ብሎ አዘጋጆቹን አስደንግጧል። አገር ዉስጥ ከሮቦት ያልተሻሉ ባለሥልጣኖቹን ሰብስቦ እንደሚፎክረዉ ሳይሆን ብቃት ስለሌለዉ ወደፊትም ማንኛዉም ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ፊት እንደማይቀርብ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

 ባጠቃላይ መንግሥታችሁ ተዘርዝሮ በማያልቅ ቅጥፈትና ማስመሰል ላይ የተመሠረተና በአምባገነናዊነት ወደር የለሽ ግፍ በህዝብ ላይ በመፈፀም ላይ የሚገኝ በመሆኑ በየትም አገር ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ ብቻ በህዝብ ተተፍቶ አዲስ አበባ ላይ ብቻዉን ቀርቷል።

 ስለዚህ ካሁን በኋላ እንደ መንግሥት ለመቀጠል የሚያስችላችሁ አንዳችም ሁኔታ እንደሌለ ተገንዝባችሁ ለራሳችሁ ካላሰባችሁ ቢያንስ ለልጆቻችሁ ስትሉ ያለችሎታችሁ የያዛችሁትን ቦታ ለሚገባቸዉ ዕዉነተኛ የህዝብ ልጆች ባስቸኳይ ልትለቁ ይገባል። ለልጆቻችሁ ስትሉ ማለት እነሱ በናንተ ወንጀል ይጠየቃሉ ማለት አይደለም። ንጹሃን ልጆች በወላጆቻቸዉ ጥፋት የሚጠየቁበት ሁኔታ በጭራሽ አይኖርም። ለማሳሰብ የተፈለገዉ ልጆቹ አድገው ወላጆቻቸዉ ህዝብን የበደሉ ወንጀለኞች መሆናቸዉን ሲረዱ የአዕምሮ ሰላም በማጣት ቀሪ ህይወታቸዉ ሊበላሽ ስለሚችል ከዚህ አስዛኝ ሁኔታ እንድትታደጓቸዉ ነዉ።

 ይህን ምክር የማትቀበሉ ከሆነ ግን የናንተና የመሪያችሁ እጣ የሳዳም ሁሴን ወይም የኮሎኔል ጋዳፊ እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ምናልባት የዘረፋችሁትን የህዝብ ሀብት ይዛችሁ ወደ ሌላ አገር ሸሽታችሁ ተሸሽጋችሁ ለመኖር ታስቡ ይሆናል። ነገር ግን አትሞኙ። እንደዛሬ ቴክኖሎጂ በተራቀቀበት ዘመን ቀርቶ ባልነበረበትም ወቅት፤ በወገኖቻቸዉ ላይ ግፍ የፈፀሙ የናዚ ወንጀለኞችን ከ70 ዓመታት በላይ በማደን ዕድሜያቸዉ 90 ዓመት የሞላ ወንጀለኞችን ሳይቀር ከተደበቁበት አገር ጎትተዉ ሲያወጡ እንደኖሩት የእሥራኤል ልጆች፤ እነዚያ በሰሜን አሜሪካና በአዉሮፓ እናንተን በመቃወም ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁ ወጣቶች እስከ ዓለም ዳርቻ ተጉዘዉ ከተደበቃችሁበት ጎትተዉ ያወጧችኋል።

 በዚህ መልዕክትም ሆነ በሌላ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አስተያየት qmaatii20@yahoo.com እንድትልኩልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ።


Back to Front Page