Back to Front Page

ህወሓትን እንጂ የትግራይ ህዝብማ ህዝባችን ነው

ህወሓትን እንጂ የትግራይ ህዝብማ ህዝባችን ነው (ለኤሊቶችና መሰሎቻቸው፣ ህዝብን ኣይመለከትም)

 

ክፍላይ ገብረሂወት (email: kflay77@gmail.com, twitter: @kfloma)

03-19-20

 

ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ያለፈውን ጊዜ እና የአሁን ሁኔታዎች ተመሳሳይነት ስላላችው እና ትምህርት ይሆናሉ ተብሎ ስለታሰበ እንጂ ቁርሾች በመቀስቀስ አጉል ንትርክ ለመፍጠር ኣይደለም። የእነ ኣአጼ ዘርዓ-ያዕቆብ እና ደቂቀ እስጢፋኖስን ትተን የሚከተሉትን እንይ።

1.   ደጃች ዉቤ (ብዘበነ ዉቤ ያ ዝዓርመመስ ዝባን ዉቤ እንዳበለ ይነብር)

ደጃች ዉቤ ጋኖች፣ ሸክሎች በማሰበር እና ጉድጓድ በማስቆፈር መርፌ ሳይቀር በየዓመቱ እየተመላለሱ ሲዘርፉ የኖሩ ሰው ናቸው። ታድያ ያኔ ህወሓት ነበር ጠላታቸው? የትኛውን ጠላት ለመደምሰስ ነበር ይህንን የሚያደርጉት? መልሱ ቀላል ነው፣ ትግራይን እና ተጋሩን አደኽይቶ ማጥፋት የሚል መርህ ነበር።

2.   አጼ ምኒልክ (እውነት ለመናገር አጼ ምኒልክ የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝባቸው ኣያይቱም (ገብረህይወት ባይከዳኝ))

ልብ ላለው እና ሚዛናዊ ለሆነ ሰው በአንድ ሀገር ለሚኖር ዜጋ ከዚህ በላይ ዘግናኝ ኣገላለጽ ሊገኝ ኣይችልም። ይህ ሀይለኛ ህዝብ አንድ ላይ ከሆነ ስልጣኔ ረግቶ ኣይቆይም በማለት በፊርማ ለሁለት ከፈሉት (በዚሁ ዘመን እንኳን ሓሳዌ ሀይማኖተኞች የሆኑት መጋቤ-ፖለቲከኞች እግዝአብሔር የሚሰራዉን ስለምያውቅ ነው ኤርትራን እና ትግራይን ያጣላቸው ሲሉ በአደባባይ ለሐጫቸውን እያዝረከረኩ ነው)። ኣንድ ኣንዶች እንደሚሉት ስንቅ ስላለቀ ነው መሻገር ያልቻሉት እንበል (ለምን ሌላ ጊዜ አልሞከሩም የሚለዉም እንተወው)። ያሁሉ የወታደር ትግራይ ላይ ሲኖር ምግቡን ከዬት ነበር የሚያገኘው? ከትግራይ ነበር። በዚህ ዙርያ የሚገባውን ምስጋና ለማን ነው የተሰጠው? በሚቀጥለው ዓመት የትግራይ ዕጣፈንታ ስደት ነበር፣ ምክንያቱም የነበረው ሀብት ለሰራዊቱ ነበር ያስረከበው፣ እስክያገግም ረጅም ግዜ እንደሚወስድበት ኣይጥራጥርም። ግን ስደተኛ ተብሎም ተሰድቧል። ከዝያ በኋላ ደግሞ አጼ ምኒልክ የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝባቸው ሳያዩት ዓረፉ። ታድያ ያኔ ህወሓት ነበር ጠላታቸው? ትግራይን እና ተጋሩን አደኽይቶ ማጥፋት የሚል መርህ ነበር።

Videos From Around The World

3.   አጼ ሃይለስላሴ (ዓለም ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለውን መርዛማ ጋዝ ያለአንዳች ማመንታት በማይጨው ምድር ላይ ኣርከፈከፉት)

ይህ ዘግናኝ ግፍም በትግራይ እና ተጋሩ ላይ የተፈጸመ ነው። ዓለም ላይ በራሱ ህዝብ ላይ በተላይ ደግም ኣርሶ ኣደሮች ላይ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ድርጊት የሚፈጸመ ኣሁንም ድረስ እንደ ቅዱስ የሚያዩት ኣረመኔው የአጼ ሃይለስላሴ መንግስት ነበር። በተጨማሪም የአጼ ምኒልክን ሌጋሲ ለማስቀጠል ከወንድሙ የኤርትራ ህዝብ እንዳይፈጽም ያልተጎነጎነ ሴራ የለም። ታድያ ያኔ ህወሓት ነበር ጠላታቸው? ትግራይን እና ተጋሩን አደኽይቶ ማጥፋት የሚል መርህ ነበር።

4.   የደርግ ኣገዛዝ (ደርግ ጨቋኝ ቢሆንም እንኳን እንደ በሓውዜን እንዳደረገው በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በኣንድ ጀምበር ላይ ከ2500+ ገበያ ላይ ዶግ አመድ ኣላደረጋቸዉም)

እዚህ ላይ ከደርግ ስራ በላይ፣ የደርግን እኩይ ድርጊት ምክንያታዊ ለማድረግ እና ሌላ ተወቃሽ ሲፈልጉ እንደማየት የምያበግን ነገር የለም። ይሄንን ድርጊት ግን ያለፉትን መንግስታት ድርጊት ከፍ ባለ ሁኔታ የምያስቀጥል እንጂ ብዙም የተለየ ኣይደለም። ገንጣይ ኣስገንጣይ በሚል ሽፋን ቢሆንም ታጋይ ምሽግ ዉስጥ እንጂ ገበያ ዉስጥ እንደማይገኝ ኣይደለም ለመንግስት ለህጻን ልጅም ቢሆን የተደበቀ ኣይደለም። ከዛም በከፋ ሁኔታ በ1977ዓ/ም በትግራይ እና ተጋሩ ያደረሰው በደል መቼም ቢሆን የማይረሳ ቁስል ነው። ታድያ ያ ሁሉ በደል የፈጸሙት ህወሓት ላይ ነበር? ኢትዮጵያ ድኻ የምትባለው ከዚህ ክልል በሚነሳ ችጋር ምክንያት ነው እና ሌሎች ብለው በኣደባባይ የተናገሩት ህወሓትን ለማጥፋት ነው? እንደተለመደው ትግራይን እና ተጋሩን አድኽይቶ ማጥፋት የሚል መርህ ነበር።

5.   በኢህአዴግ ዘመን (ዕቃ ወደ ቀበሌ ትግሬ ወደ መቀሌ፣ ኣላልንም ቢሉም ድርጊታቸው የናገራል)

ኢህአዴግ እስከ 1990ዎቹ መጀመርያ ትግራይን ከኢትዮጵያ ባልተለየ መልኩ ወቅቱ በሚፈቅደው መልኩ የሰላሙም የልማቱም ተቋዳሽ ነበረች። ከዛ በኋላ ግን ኢትዮጵያን ለማሳደግ ትግራይን ማደኽየት የሚል መንግስታዊ በሽታ ተነሳባቸው። ተጀምረው የነበሩት ሀገራዊ ፕሮጀችቶች እንዲቋረጡ በማድረግ ዉስጣዊ ፍላጎታቸውን እንዲሳካ ኣድርገዋል። በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑት ኣንዱ የራያ መስኖ ፕሮጀችት መቋረጥ አንዱ ነው። ይህም ጦሱ ሄዶ ሄዶ በኣንድ ኣንድ ኣስመላሽ ኮሚቴዎች የማንነት ጥያቄ አለን ተብሎ ጥያቄ እስከማስነሳት ደርሷል። በተጨማሪም ባገኙት ኣጋጣሚ በጋዜጣ፣ መጽሄቶች፣ ፊልሞች፣ ቴያትሮች በቻሉት መጠን ጸር-ተጋሩ ፕሮፖጋንዳቸውን በህዝብ እንዲሰርጽ አደርጉ። ወጤታማም ሆኑ እና በ1997 እንዲሁም ከ 2005 ዓ/ም ወጤት ኣፍርቶ የተጋሩን ስቃይ ኣበዛው። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ትግራይን እና ተጋሩን አድኽይቶ ማጥፋት በሚል መርህ በእውቀትም የሁን ባለማወቅ የክልሉ ተወካይ ህወሓትተሳታፊ መሆኑ ነው።

6.   በብልጽግና ዘመን (ባቡር ፕሮጀክት እና ሊሎች መሰረተ ልማቶች እንዲቋረጡ)

ይኽ ትግራይን እና ተጋሩን አድኽይቶ ማጥፋት የሚል ምንግስታዊ መርህ በተጥናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚፈልገው ብልጽግናም በመንግስታዊ ሚድያ በትግርኛ ተናጋሪዎች ላይ የዘር ማጥፋት ኣዋጅ ለማወጅ ነጋሪት ጎሰመ። ኣያሌ ሙከራዎችም ኣደረገ እንዲሁም እያደረገ ነው። እኔ እንደተረዳሁት ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደማያገኝ የገመተ ይመስላል። ይህንን ማጠናከርያ ይሆንለት ዘንድ በጣልያን የተሰራ መንገድ ሳይቀር ኣሁን የተሰራ ኣኣስመስሎ በማቅረብ ምንም ዓይነት የመንገድ ፕሮጀችት እንዳይኖር ወስኗል። በተጨማሪም በበጀት እጥረት ሰበብ ትግራይ ድረስ የሚዘልቅ የባቡር ፕሮጀክት እንዲቋረጥ በማድረግ በሌሎች አከባቢዎች ኣዳዲስ ፕሮጀችቶችን ማስቀጠል የአዲሱ ብልጽግና ባህሪ ነው። እንዲሁም በትግራይ የሚገኝ የኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት ሰበብ እያቋረጥክ በሌላ ኣከባቢ ይህንን መሰል ፕሮጀችት መጀመር እውነተኛ ባህሪው ነው። በሌላ ኣከባቢ ፕሮጀችቶቹ መሰራታቸው ተገቢ ቢሆኑም የትግራይን እና ተጋሩ የመልማት እና መኖር ፍላጎት እየገታህ ግን መሆን የለበትም። የብልጽግና መንግስት ማድረግ ያልፈለገውን የውጭ ኢንቨስተሮችን ሊያደርጉት ሲሞክሩ እያደናቀፍክ መሆን የለበትም። ታድያ አሁንም ህወሓትን እንጂየትግራይ ህዝብማ ህዝባችን ነው እያሉ ቢያወሩም ተግባራቸው ግን የሚያሳየውትግራይን እና ተጋሩን አደኽይቶ ማጥፋት የሚል መርህ አጠናክሮ መቀጠላቸውን ነው።

ድንጋይ እና ቁልቋል

ቀላል በማይባል ኤሊት እንዲሁም በመንግስቱ ሃይለማርያም ያለምንም ማመንታት የተነገረው እና ጥቂት በማይባል ህዝብ ልብ ውስጥ የገባ ኣንድ ኣባባል ኣለ፣ ይህም ትግራይ የድንጋይ እና ቁልቋል ሀገር መሆኗን (እነሱ ናቸው ሀገር የሚሏት እንጂ እኛስ ትግራይ ዓደይ ነው የምንለው)። እነሱም ጸጋ መሆናቸውን ማን በነገራቸው?

ዋናው ነገር ግን ተጋሩ በስኳር ድንች እና ገብስ እየተመጸወቱ ኣይደለም የኖሩትም የሚኖሩትም። ኣንደኛ ነገር በትግራይ በቂ የሆነ የእርሻ መሬት ኣለ። ሁለተኛ ሰው በእርሻ ብቻ ኣይደለም የሚኖረው። ቀላል የማይባሉ ኣገራት እርሻ ሳይኖራቸው የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ። ከሁለት ትልቅ የዓለማችን ትላለቅ ከተሞች (7-14ሚል ገደማ ህዝብ) የማይበልጥ ምንያህል በጀት እንደሚያስፈልገው ይታወቃል።

ሌላውን ትተን የቀድሞ ገቢዎች ሚንስተር ወ/ሮ ኣዳነች አበቤ ትግራይ ላይ ሂደው እንደተናገሩት፣ ትግራይ በየዓመቱ 20 ኩንታል ወርቅ ታስገባ ነበር አሁን ግን ኣሽቆለቆለ ብሏል። በተመሳሳይ ዓመት ይመስለኛል የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ 98 ሚልዮን ዶላር ገቢ እንዳደርገ ገልጿል። የበረት፣ ሳፋየር እና ሰሊጥ ትተን ቀድሞ የተገለጹት ብቻ ምንያህል የክልሉ ዓመታዊ በጀት እንደሚሸፍኑ ለሚረዳ ሰው በጣም ቀላል ስሌት ነው። ቢሆንም ግን በኣኤሊቶች ዓይን አሁንም የድንጋይ እና ቁልቋል ኣገር ነች።

ኣንድ ክልል ወይም ሀገር የመግዛት ኣቅም እስካዳበረ ድረስ የሚበላዉን ነገር ኣይደለም ከጎረቤቱ፣ ከራሽያም ይሁን ከስሎቫክያ መግዛት ይችላል። ማናው ኣቅሙ መኖሩ ነው። ላምርት ካለም ከህዝብ ብዛቱ ኣንጻር ሲታይ ከበቂ በላይ መሬት ኣለ፣ ዋናው ኣጠቃቀሙ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ወደ 10 ሚልዮን ገደማ ህዝብ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ሲል የትግራይን ብቻኣይደለም፣ በሁሉም ክልሎች ተመጣጣኝ የሚባል ተረጂ ኣለ። በመሆኑም በጋራ የህዝባችን ችግር መፍታት እንጂ የድንጋይ እና ቁልቋል እያሉ የራሳቸውን ጎስቋላ ኑሮ ገነት ከሚያስመስሉ ኣስመሳዮች ራሳችን መጠበቅ ኣለብን።

ጦርነት የሰው ህይውት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሃብትንም ነው የሚበላው

ትግራይ ለምን በደን ሽፋን እና ዓፈር ለምነት ተጎዳች? መቼስ ፈጣሪ ስለረገማት የሚል ቀሽም ኣማኝ ኣይኖርም ኣይባልም። የተፈጥሮ ሂደትን ትንሽ እውቀት ያለው ግን ምክንያቱ ጠንቅቆ ያውቃል። አጼ ሃይለስላሴ ማይጨው ላይ የተጠቀሙትን በዓለም የተከለከለው መርዛማ ጋዝ መሬት ላይ ስያርፍ ሰው ብቻ ኣይደለም የሚገድለው፣ ተፈጥሮውን ጭምር እንጂ። መርዛማ በመሆኑ ዓፈር ውስጥ ያሉ ለዓፈር-ለምነት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ተሃዋስያን (soil/underground biodiversity) ድራሻቸው ያጠፋቸዋል። ሳር እንጨቱን ያነደዋል በዚሁም ምክንያት እጸዋት የማብቀል እድሉ እየተመናመነ ይሄዳል፣ ለዓፈር መሸርሸርም ተጋላጭ ይሆናል። ኢትዮጵያ ካደረገቻቸው ታላላቅ ጦርነቶች እንግዲህ ከ90 ከመቶ በላይ የተከናወኑት ከዘመነ ኣኽሱም ጀምሮ እዚሁ ትግራይ ውስጥ ነው።

ጣልያን እንኳን ያሁሉ ዓመታት ትግራይ ውስጥ ሲዋጋ ኢትዮጵያ የሰላም እንቅልፏ ስትለጥጥ ነበር። ጣልያን ማይጨው እንዳለፈ አዲስ እባባ ለመድረስ ስንት ወራት ፈጀበት? ጎንደር ላይ ተዋጋ? ጎጃም ላይ ተዋጋ? ሸዋ ላይ ተዋጋ? ደቡብ/ኦሮምያ ውስጥ ተዋጋ? ሰተት ብሎ እየበላ እየጠጣ ታጅቦ ነው አዲስ ኣባባ ውስጥ የደረሰው። ታድያ ልምን ብሎ ኣከባቢው ይራቆት? ኣክሱማውያንም ቢሆን የውጭ ንግዳቸዉን የሚያጧጡፉት ከዚህ ክልል በሚገኝ የተፈጥሮ ሃብት ነበር። ታድያ ለምን ኣይራቆጥ? ላስታ ከትግራይ በምን ይለያል? በምንም። የስልጣኔ እና ጦርነት ሰይጣናዊ ጎኑ ከዚሁ መረዳት ይቻላል። አሁን ደግሞ በአዲስ ኣባባ እና ዙርያዋ ተፈጥሮ ወዴት እየሄደ እንዳለ ልብ ላለው ወዴት እያመራን እንደሆነ ማየት ይቻላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሰሩ ያሉት ኣከባቢን የመልሶ ማገገም ስራዎች ግን በጣም ኣንጻባሪቂ እና በኣጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጥሩ ሁኔታ ሊመለስ እንደሚችል ኣመላካች ነው። ይህ በጎ ተግባር ሌሎች ኣከባቢዎችም ተግባራዊ ቢያደርጉት ለኣህጉራችንም ይተርፋል። እንዲህ ካልሆነ ግን ጦርነት እና የኣየር ጸባይ ለውጥ ተጨምሮበት ወደበረሃነት መቀየሩ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ማጠቃለያ፥- የሚናገረውን የሚተገብር መንግስት እስኪመጣ ድረስ፣ ህወሓትን እንጂ የትግራይ ህዝብማ ህዝባችን ነው የሚለው ቧልት ከቀልድ የዘለለ ፋይድ እንደማይኖረው ኣውቀን፣ ከታሪክ ተምረን ትግራይን እና ተጋሩ እንካስ እላለሁ።

 

Back to Front Page