Back to Front Page

የትግራይ ህዝብ የሚተማመነው ጥርት ባለ መስመሩና በመሪ ድርጅቱ ህወሓት ነው።

የትግራይ ህዝብ የሚተማመነው ጥርት ባለ መስመሩና በመሪ ድርጅቱ ህወሓት ነው።

ብርሃን ንርአ

brhannrae@gmail.com

በዚህ ሳምንት ውስጥ 50% የህወሓት አመራር ወደ ብልፅግና ፓርቲ መቀላቀላቸውና ስም ዝርዝራቸውም በቅርብ ቀን እንደሚገለፅ የሚያትት ፅሑፍ ከብልፅግና ፓርቲ ድህረገፅ ተገኘ ተብሎ በማህበራዊ ሚድያ ሲዘዋወር ሰንብተዋል።በዚህ ዘመን የትግራይ ህዝብ የሚተማመነው በህወሓት አመራር ውስጥ ላሉ ግለሰበቦችና አበላት ነው?ወይስ ጥርት ላለው መስመሩና ለመሪ ድርጅቱ ህወሓት ነው? የሚል ጥያቄ እንድጠይቅና ይህንን አስመልክቶ አጭር ፅሑፍ እንድፅፍ አነሳስቶኛል።የዚህ አጭር ፅሑፍ ዓላማም ብልፅግና ፓርቲ የፃፈውን ፅሑፍ መልስ ለመስጠት ሳይሆን በዚህ ዘመን የትግራይ ህዝብ የሚተማመነው በህወሓት አመራር ውስጥ ላሉ ግለሰቦችና አበላት ነው?ወይስ ጥርት ላለው መስመሩና ለመሪ ድርጅቱ ህወሓት ነው?ለሚለው ጥያቄ ያለኝን አቋምና እምነት ለመግለፅ ነው።ከዚህ በተጨማሪም ይህንን ጥያቄ በመመለሱ ረገድ እንድንወያይበትና ትክክለኛውን አቋም ለመያዝ ያግዛል ከሚል እምነትም ጭምር ነው።

ሁላችን እንደምናውቀው በዘመነ መሳፍንት የነገስታት ሰራዊት በአንፃራቸው የሚገኝን ሰራዊት ጋር ጦርነት ገጥመው ንጉሱ ሲሞት፣ሲቆስል፣አልያም ሲማረክ አስከትለውት የነበረውን ሰራዊት የሚሸነፍበት መሪ አጥቶ የሚበታተንበት ታሪካዊ አጋጣሚዎች እንደነበሩ የኢትዮጵያ ታሪክ አስተምሮናል።እንደዚህ ዓይነት ታሪክ በትግራይ መሳፍንት ሰራዊትም አጋጥመዋል።ንጉሱ ሲሞት ሰራዊቱ የሚሸነፍበት ምክንያትም እምነቱ በንጉሱ ላይ ብቻ ስለሚንጠለጠል ነው።ይህ በዘመነ መሳፍንት እያጋጠመ የነበረን የሽንፈት ታሪክ የዘመነ መሳፍንት አስተሳሰብ በመያዝ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመድገም መሞኮር ነው ስህተቱ።በቅርቡ በብልፅግና ፓርቲ ድህረገፅ የወጣውን እና የተነበበውን ፅሑፍ መሰረታዊ ስህተቱም በዘመነ ሚኒልክ የነበረን አስተሳሰብ መሰረት በማድረግ የተፃፈ መሆኑ ነው።

Videos From Around The World

የትግራይ ህዝብ ካለፈው ጠንካራ ታሪኩና ከነበሩት ውድቀቶቹ በመማር በየካቲት 11/1967ዓ/ም የትግል ችቦ ለኩሶዋል።ይህ የትግል ችቦ ሲለኮስ እንደዘመነ መሳፍንት ንጉሱን(በድርጅቱ ውስጥ በመሪነት የነበሩ ግለሰቦች)በመተማመን ሳይሆን በጠራ መስመሩ እና ጠንካራ አደራጃጀቱ በመተማመን ነው።ከመስፍንነት፣ጥገኛ ቢሮክራስያዊ ርእሰማልነት(ጥገኛ ካፒታሊዝም) ከአፀያዊ ጣልቃ ገብነት(ኢምፐራሊዝም)ኣንፃር ፍትለፊት ገጥሞ በድል የተወጣውም በጠራ መስመስሩና ጠንካራ አደራጃጀቱ መሆኑን ታሪክ ያስተምረናል።

የትግራይ ህዝብ ትግል ለድል የበቃው በትግሉ ሂደት ያጋጠሙት ፈተናዎች በፅናት ስለተወጣቸው ነው።በዚህ ፅሑፍ የትግራይ ህዝብ ትግል ውስጥ የገጠሙት ፈተናዋች ሁሉንም ለመግለፅ ባይቻልም ከዚህ ፅሑፍ ይዘት ተዛምጅነት ኣለቸው የሚባሉ ፈተናዎች በኣጭሩ ለመጥቀስ እፈልጋሎህ።

የትግራይ ህዝብ ትግል ከገጠሙት ፈተናዎች ውስጥ የ1969 ዓ/ም ሕንፍሽፍሽ ተብሎ የሚጠራው አንዱ ነው።በአውራጃውነት ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነበር።የኛ አውራጀ በህወሓት የድርጅት መሪነት ተገቢ ቦታ አልተሰጠንም የድርጅቱ አመራሮች የተቆጣጠሩት የጥቂት የትግራይ አውራጃዎች ተወላጆች ናቸው የሚል ውዥምብር በድርጅቱ ውስጥ እንዲፈጠር አደረጉ።በዚህ የውሸት ወሬ የተደናገሩ ቀላል የማይባሉ ታጋዮች ምርጥ ምርጥ መሳራያዎችን(ትጥቅ)ይዘው ወደ ጠላት ገቡ ወደ ውጭ ሃገራትም ከቦለሉ።በዚህ ጊዜ የትግራይ ህዝብ ትግል ከፍተኛ ፈተና ላይ ወደቀ።ድርጅቱ ህወሓት ያገጠመውን ፈተና ለመፍታት ለውይይት ተቀመጠ።ታጋዮች የሚታገሉለት ዓለማ በኣውራጃ ለመካፋፈል ሳይሆን የትግራይ ህዝብ አሁን ካጋጠመው አስከፊ ጭቆናና ውርደት ለማላቀቅ መሆኑን በስፈው ተወያዩበት መግበባትም ተደረሰ።የትግሉ ዓላማ ወደ የህዝብ እንዲሰርፅ በስፋት ተንቀሳቀሱ ሓፋሽ ይንቃሕ ይወደብ ይተዓጠቕ(ብዙኋኑ ህዝብ ንቃተ ህልናው ይጎልብት ይደራጅ ለትግሉም ይሰለፍ)የሚል መሪ ቃል ኣንግበው ተንቀሳቀሱ።ህዝብ ህዝባዊ(ለህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ በህዝቡ የተሰጣት ስም)ብሎ ወደሚጠራት ድርጅት በስፋት ተሰለፈ።ድርጅቱ ህወሓትም አጠናከረ። የ1969ዓ/ም ሕንፍሽፍሽ ከላይ በተጠቀሰው መንገድ በማለፍ ከፍተኛ ድል ለማስመዝገብ ተንደረደረ።

ሌላኛው በትግራይ ህዝብ ትግል ያገጠመ ፈተና 1977ዓ/ም ደውታን ምንቁልቃልን(ትግሉ ወደ ማቆምና ማሽቆል ያስገባ ፈተና)ብሎ የጠራው ነው።ይህ ችግር ሊከሰት የቻለው መስመሩ ለመድረኩ በሚመጥን መልኩ ጥራቱ አለመጠበቁ የተፈጠረ ችግር ነበር።ህወሓት ይህን ችግር የፈታው የመስመር ማጥራት መድረክ በመጥራት ነው።በዚህ መድረክ የህወሓት ታጋዮችና የትግራይ ህዝብ በመስመሩ ማጥራት መድረክ በስፋት ተሳተፉ።የነበሩ የተሳሰቱ አስተሳሰቦች በማስወገድ የጠራ መስመርን ጨበጡ።በዚህ መስመር የማጥራት ሂደት ድርጅቱ ሲመሰረት ከነበሩና በወቅቱ ከፍተኛ አመራሮች ከሚበሉት አንዱ ግደይ ዘርአፅዮን የመስመር ልዩነት አለኝ ስላለ ትግሉንና ህዝቡን በመካድ ከትግሉ እንዲሰናበት ጠየቀ።ህወሓትም በዲሞክራስያዊ መንገድ ግደይ ዘርአፅዮን በጠየቀው መሰረት ከትግሉ አሰናበተው።አረጋዊ በርሀም(በሪሁ) ህወሓት ሲመሰረት ከነበሩትና ከፍተኛ አመራሮች ከሆኑት አንዱ ነው።በዚህ የመስመር ማጥራት ወቅት ወደ ውጭ ሂዶ እንዲታከም ፍቃድ ጠየቀ።ድርጅቱም ፈቀደለት።ለህክምና በሄደበት ውጭ አገር ትግሉን በመክዳት በዛው ቀረ።የትግራይ ህዝብም በግልፅ ከተሰናበተው ግደይ ዘርአፅዮንና ትግሉን በመክዳት ውጪ አገር የጠፋው አረጋዊ በርሀ ይልቅ የጠራ የህወሓት መስመርና መሪ ድርጅቱ ህወሓትን መርጦ ከህወሓት ጎን ተሰለፈ።በፀሓይ ብርሃን ፍጥነት ትግሉ ኣጠናክሮ ቀጠለ።ወደ ከፍተኛ ድልም ተሸጋገረ።የትግራይ ህዝብ ትግል ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ተዳምሮ የድህነትን ዘበኛ የነበረውን ደርግ አሽቀንጥረው ጣሉት።

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ የትግራይ ህዝብ ትግል ከገጠሙት ፈተናዎች ደርግን ከተገገረሰሰ በኋላ ያጋጠመው የመዝቀጥ አደጋም ተጠቃሽ ነው።ይህ ዝቅጠት የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ለሁለት ከፍሎ የትግራይ ህዝብ ትግል ኩፉኛ አደጋ የወደቀበት ወቅት ነበር።በዚህ ወቅትም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የሚታገሉለትን ዓላማ በመተግበር ላይ ያገጠሙት ችግሮች ወደ መገምገም ነው የገቡት።ያገጠመውን ዝቅጠት በህዳሴ መስመር ለመፍታትም ተንቀሳቀሱ።የህዳሴው መስመር የትግራይ ህዝብ ችግር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን በትግራይ ህዝብና በመላው የህወሓት ኣባላት ታመነበት።ከትግሉ ያፈነገጡትን ከ10 በላይ የሚሆኑ ማእከላይ ኮሚቴ በማሰነበት ህወሓትና የጠራ መስመሩን በመምረጥ ትግሉ አጠናክሮ ቀጠል።በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣የኢኮኖሚ እድገት የዲፕሎማሲ ድል ተመዘገበ።የትግራይ ህዝብ እንደማንኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድሉ ተቋዳሽ ሆነ።

የትግራይ ህዝብ ትግል ከገጠሙት ፈተናዎች አንዱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ህልናም የማይጠፋ በጣም አስደንጋጭም የነበረው የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ህልፈት ነው።የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ህልፈት ለትግራይ ህዝብ ትግል ብቻ ያጋጠመ ፈተና ኣልነበረም።ለማላው የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ለመላው የአፍርካ ህዝብና ለመላው የዓለም ጭቁን ህዝቦች ትግል ፈተና ሁኖ አልፈዋል።ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የታላቁ መለስ ዜናዊ ህልፈት አሁኑም ፈታና እንደሆነባቸው ቀጥለዋል።የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ህልፈት ምክንያት ለትግራይ ህዝብ ትግል ያገጠመውን አደጋ በብቃት ያለፈውም በጠራ መስመሩና በጠንካራ መሪ ድርጅቱ ህወሓት በመተማመን ነው።በታላቁ መሪ ህልፈት ምክንያት የህወሓት ማአከላይ ኮሚቴና የህወሓት ኣባል ከፍተኛ መደናገጥን ፈጥሮ ነበር።ትግሉ እንዴት ነው የምናስቀጥለው?ትግሉ ማነው በብቃት የሚመራው? የሚል ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ወደቁ።በዚህ ጊዜ የትግራይ ህዝብ አንድና አንድ ነው የነበረው መልሱ።መለስን የፈጠረው የትግራይ ህዝብ የትግል መስመር ነው።መለስን መለስ ያደረገው የጠራ የህወሓት መስመር ነው።ከህዝባዊ መስመር ውጭ ቢሆን ኑሮ መለስ መለስ ባልሆነ ነበር።የመለስ የግሉ የማይተካ የመሪነት ሚናው ብናጣውም እየተታገለለት የነበረ ህዝባዊ ዓላማ አህንም አለ።እየተታገለለት የነበረው መሪ ድርጅ ህወሓትም ኣሁንም ኣለ።ከህወሓት ጎን ተስልፎ ህወሓት ሁኖ እየተታገለ የነበረ የትግራይ ህዝብም ኣሁንም አለ።ይህንን እምነት በማያዝ በፅናት ምሩን እኛ ከጎናችሁ ነን በማለት መሪዎቹና የህወሓት ኣባላትን አፅናና።ትግሉም አጠናክሮ ቀጠለ።አሁንም የትግራይ ህዝብ ትግል ከድል ወድል እየተረማመደ በድል ጎደና እየተጓዘ ነው።

አዲሶቹ የዘመነ ሚኒለክ አስተሳሰብ ያነገቡ የነውጥ ሓይሎቸ ማእከላይ የፈደራል መንግስት ስልጣን የታሪክ ኣጋጣሚ ሁኖ ተቆጣጥረውት ይገኛሉ።አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንደዘመነ መሳፍንት የነበረ ሁኔታ ግን አይደለም ያለችው።ህዝቦቿ 27 ዓመት የዲሞክራስያዊ ስርዓት ግንባታ፣የተመዘገበው ፈጣን እደገት የነበረ የተረጋጋ ሰላም ፍረው ኣጣጥመውታል።ለጊዜው ሊዳናገሩ ይችሉ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ ጥቅማቸው ከሚያረጋግጥላቸው ልማታዊ ዲሞክራሲ መስመር ወጥተው መሄድ አይችሉም።የኢትዮጵያ ህዝቦች አሁን ያገጣማቸው ጊዝያዊ ሽንፈት የመታገያ መስመር ማጣት ኣይደለም።አንዱ ችግራቸው ለልማታዊ መስመር እየተጋለ የነበረ ድርጅት ኢህአዴግ በገጠመው ከፍተኛ ዝቅጠት መክሰሙ ነው።ሁለተኛ ያገጠማቸው ችግር ኢህአዴግ ሲከስም በፍጥነት ለልማታዊ ዲሞክራስያዊ መስመር የሚታገል መሪ ድርጅት መመስረት ኣለመቻላቸው ነው።ይህ አሁን እያጋጠማቸው ካለ ችግር ተምረውና ተመኩሮ ቀስመው ብቁ መሪ ድርጅት ወደ መመስረት በመሸጋገር በነውጡ ሓይሉ እየተጫናቸው ያለውን የጭቆና ቀንበር ኣሽቀንጥረው እንደሚጥሉት ጥርጥር የለውም።

የትግራይ ህዝብ ማእከላይ የፈዴራል መንግስት ስልጣን የተቆጠቀጠረውን የነውጥ ሓይል በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ለመጫን እየተመኮረ ያለውን የጭቆና ቀንበር አሽቀንጥሮ ለመጣል የሚያስችል ጥርት ያለ መስመርና ጠንካራ መሪ ድርጅት ያለው ህዝብ ነው።የትግራይ ህዝብ ከአፄ ዮሃንስ ህልፈት በኋላ ያጋጠመውን ሽንፈት ለማስተናገድ በፍፁም ፍቃደኛ አይደለም።

ማእከላይ የፈዴራል ስልጣን የተቆጣጠረውን የነውጥ ሓይል የትግራይን ህዝብ ቅስሙን ለመስበር የተላያዩ ሙኮራዎች አድርገዋል።የመጀምረያው ሙኮራው የህወሓት መሪዎች በሓሰታኛ ክስ ማሰርና ማሳደድ ነው።ከነበራቸው የፌደራል ስልጣን መባረር ነው።የጠራ መስመርና የጠንካራ ድርጅት ህወሓትን ባለቤት የሆነውን የትግራይ ህዝብ የነውጥ ሓይል በሚያሴረው ሴራ ትግሉ ሊያኮላሽ ኣልቻለም።የትግራይ ህዝብ ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠሉ የተቆጣ የነውጥ ሓይል እጅና እግሩ አጣጥፎ ቁጭ ለማለት ፍቃደኛ አይደለም።የህወሓት መሪዎች ለመግደል የተላያዩ ሙከራዎች አደረገ።በትግራይ ህዝብ ጠንካራ ትግል ይህንንም ሊሳከለት አልቻለም።የነውጥ ሓይሉ በዋልታ ቴሌቪዥን የትግራይ ርእሰ መስተዳደር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩየሚል ሓሰተኛ ዜና በማሰራጨት መሪዎቹ እየተሰዉ በሌላ መሪ እየተካ ትግሉን እያስቀጠለ ለመጣው የትግራይ ህዝብ ለደቂቃ ብትሆንም ለማደናገጥ ሞኮረ።ይህም ሳይሳከለት ቀረ።በዚህም ኣላበቃም የነውጥ ሓይሉ ገሚሱ የህወሓት አመራር ቀንና ለሊት ሲሰራ ገሚሱ ግን ለትግራይ ህዝብ አይጨነቅም የሚል ወሬም እንዲሰራጭ አደረገ።በዚህ ያሰራጨው ወሬ የህወሓት መሪዎች የተካፋሉ ለማሰመሰል ጥረት አደረገ።በመስመሩና በድርጅታዊ የውስጥ ጥራት የሚተማመነው የትግራይ ህዝብ አሁምንም ሴራው እንዲከሽፍ በማድረግ ትግሉ ኣጠናክሮ ቀጠለ።ይሁንና በህወሓት ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር አሁንም የነውጥ ሓይሉ ጠንክሮ እየሰራ ነው።በቅርቡ በብልፅግና ፓርቲ ድህረ ገፅ የተፃፈው የዚህ ተግባር ተቀፅላ ነው።የነውጥ ሓይሉ ልብ ያላለው ባለው ተፈጥሮ ምክንያትም ልብሊለው የማይችለው ነገር ኣለ።ከትግራይ ህዝብ የትግል ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ከፍተኛ መሪዎች ተሰውተው ኣንዳንድ መሪዎችም ኣባለትም ክህደት ሲፈፅሙ የትግራይ ህዝብ ትግል ግን ሊቀለበስ ኣልቻለም።አሁኑም ቢሆን ከፍተኛ መሪዎቹ በመስዋእትነት ሊለዩት ይችላሉ። እንደ ዘመነ አፄ ዮሃንስ የትግራይ ህዝብ ሰራዊት ግን አይበተንም።ለተሰዉት ተጋዮች በክብር ሸኝቶ ትግሉ አጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ።ከከፍተኛ መሪዎች እስከ ተራ ኣባል ትግሉን በመካድ ወደ ፀረ ህዝብ ጎራ ሊሰለፉ ይችላሉ።የትግራይ ህዝብ መልሱ እንደተለመደው ኣንድና ኣንድ ነው።ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ኣልያም ድንጋይ ነህ ተብለህ ትወረራለህ የሚል ነው።የትግራይ ህዝብ ይህንን ያህል አቅም ያገኘው የተለየ ህዝብ ስለሆነ አይደለም።ሚስጥሩ የትግራይ ህዝብ የጠራ መስመርና የጠንካራ መሪ ድርጅት ህወሓት ባለቤት መሆን ስለ ቻለ ብቻ ነው።

የትግራይ ህዝብ ትግል አጣንከረህ ለመውሰድና ከግቡ ለማደረስ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ማድረግ የሚገባቸው ነገር አለ።እርግጥ ነው በ45ኛው የህወሓት ልደት የተሰሩ ስራዎች ኣሉ።የትግራይ ህዝብ የጠራ መስመሩና ድርጅቱ ህወሓት ብቻ ተማምኖ እንዲታገል የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ተሰርተዋል።የ45ኛው የህወሓት ልደት ሲከበር የነበረ መስመርና አፅኒዕና ንመኸተ!(መስመራችን አጥብቀን በመያዝ እንመክት)የሚለው መሪ ቃል የተለየ ትርጉም አለዉ።የትግራይ ህዝብ የግለሰቦች አምልኮት እንዳይጠናወተውና ከዚህ ችግር ወጥቶ መስመሩ አጥብቆ በመያዝ እንዲታገል ለማድረግ ነው።ሌላው በ45ኛው የህወሓት የልደት በዓል በሂወት ያሉ የህወሓት መሪዎች ፎቶ ማንኛውም ሰልፈኛ ይዞ ወደ ሰልፉ እንዳይገባ በጥብቅ መከልከሉንና የሰማእታት ፎቶ መያዝ ግን እንደሚፈቀድ መመርያ ወደ ህዝቡ ወርዶ ነበር።ይህ መመርያ በሰላማዊ ሰልፉ ህዝቡ ተግባረዊ አድረጎታል።ይህም የሚያመላክተው የሰማእታቱ አደራ መተግበር እንዳለበት፤ በሂወት ላሉ መሪዎቹ ደግሞ ለማይተካ የመሪነት ሚናቸው ማክበር እንጂ ማምለክ እንዳይማይገባው መልእክት ያስተላለፈ ነበር።እነዚህ በ45ኛው የህወሓት ልደት ክብረ በዓል ላይ እንዲተላለፉ የተፈለጉት መልእክቶች የዛቀን መልእክቶች ብቻ ሁኖው መቅረት የለባቸውም።የነውጥ ሓይሉ የትግራይ ህዝብ መስመሩና ጠንካራ ድርጅቱ ከመተማመን ይልቅ በሂወት ላሉ መሪዎች እንዲያመልክ ሆንተብሎ እየተሰራ ነው።ይህንን የግለሰብ አምልኮት በማህተምነት ደረጃ በህዝቡ አእምሮ ላይ እንዲታተም ካደረጉ በኋላ አምልኮ የተጣለበት ሰው በነውጥ ሓይሉ ሴራ በግድያ እንዲወገድ በማድረግ (አፄ ዮሀንስ ለህለፍ የተዳረጉበት መንገድ እንደሚነገረው ከሆነ) የትግራይ ህዝብ ሞራል ለመምታት ታስቦ እየተሰራ ነው።ህወሓት ይህንን ሴራ እንዳለ ስለ ተገነበም ጭምር ነው መስመርና አፅንዕና ንመኸተ!የሚል መሪ ቃል የተጠቀመው።በሂወት ባሉ የህወሓት አመራሮች ፎቶ ወደ ሰልፉ እንዳይገባ የከለከው።ይሁንና ይህንን ህዝቡ በመደባዊ ንቃተ ህልና እንዲጨብጠው ማድረግ አስፋላጊ ነው።በተለይ ወጣቱ አጥብቆ መያዝ ያለበትን የህወሓት መስመር በረጅምና በኣጭር ስልጠናዎች እንዲጨብጠው ማድረግ ይገባል።ከዚህ ከሰለጠነውና በተግባር ከተፈተነው ወጣት አሁን ላሉ መሪዎች የሚተኩ በብዛት መልመለህ ማዘጋጅ ይገባል።ህወሓትና የትግራይ ህዝብ እነዚህ ተግባራት ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት አሁን ያለውን ችግር መቀልበስ ብቻ ሳይሆነ ቀጣይነት ያለው የማያቋርጥ የትግል ማዕበል መፍጠር ይቻላል።

መስመርና ኣፅኒዕና ንመኸተ!

መስመራችን አጥብቀን በመያዝ እንመክት!

Back to Front Page