Back to Front Page

ኢትዮጵያ የሞኝ ዳቦ ይመስል ከተበላች በኋላ ኪስ ውስጥ አትገኝም፡፡

ኢትዮጵያ የሞኝ ዳቦ ይመስል ከተበላች በኋላ ኪስ ውስጥ አትገኝም፡፡

ዮሃንስ አበራ (ዶር.) 03-21-20

ፈረንጆች እንደሚተርቱት አንዲት ዳቦ ካለችህና እሷንም ከበላሃት ይችን ዳቦ ኪስህ ውስጥ አታገኛትም፡፡ በልቶ ከጨረሳት በኋላ እንደነበረች አገኛታለሁ ብሎ ኪሱን የሚዳብስ ሰው ካለ አሱ የለየለት ቂላቂል ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት አመታት እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የምትጠፋበት ዘዴ 24 ሰአት ሙሉ ሲያስብ፤ ሲያቅድና ሲተገብር የሚውልና የሚያድር ሁሉ ተሳክቶለት ኢትዮጵያ ብትጠፋ ሌላ ተለዋጭ ኢትዮጵያ ከኪሱ አውጥቶ የሚኖርባት የሚመስለው ሰው አሁን በሚልዮን ካልሆነ በመቶ ሺዎች የሚቆጥር ሆኗል፡፡ ነገሩ ሰውንም ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄርንም ሊያስገርም የሚችል ነው፡፡ እግዚኣብሄር ከፍጡራኑ ሁሉ ለሰው ዘር የተለየ ስጦታ የሰጠው በረቱን እንደከብት በእዳሪ አበላሽቶ አለማደሩ ነበር፡፡ የዚህ ምሳሌነቱ ለኢትዮጵያ ነው፡፡ መዋያ ማደሪያውን መዋልና ማደር እንደማያስችለው አድርጎ የሚያበላሽ ቢኖር ከብት፤ አሳማና፤ ደሮ ካልሆነ በስተቀር የሰው ፍጡር ባህርይ ሊሆን አይችልም፡፡

Videos From Around The World

ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ በዚህ ኢትዮጵያን በማፍረስ ዘመቻ ላይ ሸሚዙን እስከ ትከሻው ጠቅልሎ የሚታክተው ባብዛኛው የኢትዮጵያ መንግስት ደሞዝተኛ የሆነው ነው፡፡ ራሱንና ቤተሰቡን የሚያኖረው በዚህ ደሞዝ መሆኑን እያወቀ፤ ልጆቹን ትምህርት ቤት እየመረጠ የሚያስተምረውና ለወደፊት ለሱም ለራሳቸውም ተስፋ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ የቻለውም በመንግስት ደሞዝ ላይ እምነቱንና ክብደቱን ጥሎ ነው፡፡ የመንግስት ደሞዝ ወሩን ቆጥሮ ሊመጣና የተረጋጋ መደበኛ ህይወት ሊኖር የሚችለው ከዳር አስከ ዳር አገር ሰላም ሆኖ፤ ንግድ ተጧጡፎና ኢንቨስትመነት ተስፋፍቶ ከሚሰበሰበው ግብር በማእከልና በፓርላማ ፀድቆ እንደየ ግብር አስተዋፅኦው ሳይሆን እንደየ ህዘቡ ብዛት በበጀት መልክ ሲከፋፈል ነው፡፡ ይህ አካሄድ በሰላም እንዳይካሄድና እንዲሰናከልም የሚጥር ግለሰብ ሆነ ቡድን ወር ሲመጣ ደሞዙን እንደተለመደው ማግኘት እንደ ተፈጥሯዊ መብቱ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችን አስበጥብጦ ወታደራዊ ካምፖች ሲመስሉ የማይደንቀው፤ እንደድልም የሚቆጥረው የተበላሸ ዜጋ ልጆቹ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንዲማሩለት ጊዜውን፤ ገንዘቡንና ጉልበቱን የሚያፈሰውንም ይጨምራል፡፡ አገርን ከስሯ ምንግል አድርጎ የሚነቅላት የውጭ ወረራ አይደለም፡፡ አገር ላትመለስ የምትጠፋው በውስጥ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ግን ይህን በሚገባ አይረዱም፡፡ ይህ ቂልነት በኢትዮጵያ ታሪክም በተደጋጋሚ ተከስቷል አሁንም እያየነው ነው፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት የኢትዮጵያ ስም የት እንደገባ ሳይታወቅ የብሄሮች ስም ብቻ አየሩን ሞልቶት ከረመ፡፡ እዛም ግጭትና ግድያ እዚህም ግጭትና ግድያ፤ አንዱጋ ሲያባራ በሌላው ይለኮሳል፡፡ በየሰአቱ የማህበራዊ ሚድያና መደበኛው ሚድያ የተሞላው በልማት ዜና ሳይሆን በግድያ፤ በተቋማት ቃጠሎ፤ በውጡልን ዘመቻና፤ በተፈናቀለ ህዝብ አሃዞች ነው፡፡ የግድያ፤ የቃጠሎ፤ የማባረር ዜና ሳይሰማ ማደር የለበትም የሚል አስገዳጅ ሁኔታ የተጣለ ይመስል ሁሉም በየክልሉ፤ በየዞኑ፤ በየወረዳውና በየቀየው የግድያ ዜና እንደይቋረጥ አስተዋፅኦውን የሚያበረክት ይመስላል፡፡ ድሮ (ልበለው) በየዞኑ የነበረው የህዝብ ጥያቄ ዩኒቨርሲቲ ይገንባልን ነበር፡፡ አሁን የዞን ጨርሰናል ወደ ወረዳ ዩኒቨርሲቲ ልንገባ ነው ብለው አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያ/ባለስልጣን ስብሰባ ላይ ቀልድ ጣል ያደረጉበትን አጋጣሚ አስታውሳለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ለዞንና ለወረዳ በኮታ የሚዳረስ መሆን ባይገባውም ጥያቄው ሰላማዊና ለሃገር ጠቃሚ ነበር፡፡ በዛ አጋጣሚም የ45 ዩኒቨርሲቲዎች ባለቤት ሆነናል፡፡ ይህ ለወደፊቱ ልማታችን ጠቃሚ ግብአአት ነው፡፡ አሁን በየዞኑ ያለው አካሄድ ግን ከፊተኛው በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ እነዚህ በየዞኑ የተመሰረቱት ዩኒቨርሲቲዎች ሲበጠበጡ አቋቁሙልን ብሎ የወተወተ ዞን ሁሉ ወይ ዝም ብሎ ያያል ወይ እሳቱ ላ ጋዝ ይጨምራል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሙያ የምታሰለጥንበት እድሏ በግዴለሽ ዜጎቿ የሚሰናከል ከሆነ የወደፊት እጣ ፈንታዋ ብዙ ትንንሽ ሆና ወደ ጥንታዊ ጋርዮሽ መመለስ ነው፡፡

በውስጥ ኢትዮጵያን ቅንቅን እንደበላው ግንድ ቦርቡረን ካዳከምን በሁዋላ ግብፅ አገራቸውን በማይወዱ ግን እንደሚወዱ ደጋግመው በሚናገሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለተደረገላት ውለታ እያመሰገነች የራሷን ፍላጎት ኢትዮጵያ ላይ ለመጫን ሞከረች፡፡ የግብፅን ድረጊት ያየ ያ ኢትዮጵያን ከውስጥ ቦርቡሮ ያዳከመው ሁሉ ከሌላው ቅን ዜጋ ጋር አብሮ ዘራፍ ላገሬ ማለት ጀምሯል፡፡ ምን አይነት አባዜ ይሆን፡፡ አሁን ሁሉም የየብሄሩ ምሽግ ይዞ የሚፎክረው ኢትዮጵያ ብትቀር እያንዳንዳቸን አገር ሆነን ከበፊቱ የበለጠ ቀና ብለን እንሄዳለን የሚል በአሸዋ ላይ የተመሰረተ እምነት ይዞ ነው፡፡ በዙሪያው ከቦ ሊቀራመተው የሚያደባውን ግዙፍ ሃይል ለማየት አይኑ የተሰወረ ፖለቲከኛ ኢትዮጵያ ከፈረሰች እጣ ፈንታው የሚሆነው ስልቻውን ቋጥሮ ወደ ስደት እንጂ ወደ ስልጣን ወንበር ሊሆን አይችልም፡፡ የሰማኒያ ብሄረሰብ መሪዎች ሰማኒያ አገርና ሰማኒያ ዙፋን ይመኛሉ፡፡ ተግባራዊ ለማድረግ ከሞከሩ በማግስቱ ያውሬ እራት እንደሚሆኑ እሙን ነው፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚፈፅሙት የበታታኝነት ድርጊት ለትውልድ የማይጠቅም ጎጂም ስለሆነ በወላጆቹ መጥፎ ተግባር የሚሰቃይ ትውልድ ከመፍጠር መውለድ ማቆም ፍትሃዊ ይሆናል፡፡ ይህ አገርን የመበታተን ስራ በፍጥነት ካላቆምንና ቁጭ ብለን በእርጋታና በሃላፊነት ስሜት መነጋገር ካልጀመርን የምንወልዳቸው ልጆች በእልልታ ሳይሆን በለቅሶ ብንቀበላቸውና ሞት የሚገላግላቸውን ደግሞ በእልልታ ብንሸኛቸው ይመረጣል፡፡

 

Back to Front Page