Back to Front Page

የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ቄራ ላይ ተገኘ

የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ቄራ ላይ ተገኘ

ከአብሳር

13/09/2013

 

 

የአገራችን መዋዕለ ዜና አስፈሪ ፤ ንጉሳችንም ጦር ሰባቂ መንግስቱን ናፋቂ ሆነዋል ።የጦሩነት የባዶ ቤት ቱማታ ተመልሶ መጥተዋል ። ተመነደገች አደገች የተባለችው በእድሳት ጉዞ ከፍታን ስታማትር ሩቅ አዳሪ ብላ ሁላችንም ያሳፈረች ጀልባ መቅዘፍያዋ ጠፍቶባት ትዋልላለች ። እንዳው ቆፈን ይዞናል።ብዕራችን እፎይታ መርጣ የቆየች ብትሆንም አገር እንደ ትሮይ ከተማ ለመፍረስ ጫፍ ላይ ስትደርስ የዝምታን ቆፈን መስበር የግድ ሆኗል። የኢትዮጵያውያን ንጋት እየራቀ ሄደዋል። ፖለቲካችን ከግለሰብ ወደ ህዝብ ለማሸጋገር የተደረገው ትግል አደጋ ላይ ነው። ዲሞክራሲ ህዝቦችን ከግለሰብ ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ነጻ ማውጣት መሆኑ ተረስቶ ህዝብ ጠፋ እንጂ መሪማ ተገኝተዋል የሚለው ባልትም ሰማን።ህገመንግስታችንም በአንድ ሰው ቅድ እንዲበጅ ቀደዳውን ተጀምረዋል። ሰው ችግሩ የጋራ መሆኑን ዘንግቶ አንዱ በሌላው በጥርጣሬ እንዲተያይ እየተሰራበት ነው። ወገኖቻችን ከአንዱ ገዢ ወደ ሌላው እየተሸጋገሩ ፍዳቸውን በማየት ላይ ናቸው። የዛሬዎቹ ደግሞ ከሁሉም ቀደምት ገዢዎች ሲበዛ በበግ ለምድ የተጀቦኑ ተኩላዎች ናቸው።የግጭት ጉም በመፍጠር በተመሰቃቅለ ሁኔታ ውስጥ በመደበቅ ስልጣኑን ለማራዘም የሚያልም ቡድን ነው ። ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉት ለማለት ነው።በሌላ አነጋገር የመርካቶ ሌባ ፡ሌባ ሌባ እያለ ይሮጣል እንዲሉት የአሁኑ መሪ ራሱ ግጭት ይፈጥራል ስልጣኑን ለማራዘም ይጠቀምበታል ። ክሮናን እንደ መልካም ነገር ወስዶ የሚጠቀም ነውር የለሽ ነው።

Videos From Around The World

በአገራችን ጫንቃ ላይ የተጫነው ቡዱን ያለን የእይታ ቅኝት አስቀድሞ መግባባት ያስፈልጋል።አንዳንድ ወገኖች ቡድኑ ከመጣበት ብሄር አንጻር የሚመለከቱት ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ሆኖም እይታችን መቃኘት ያለበት ከቡዱኑ ዕለታዊ ድርጊት እንጂ ከመጣበት ብሄር እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አሰፈላጊ ነው። ቡድኑን ማየት ያለብን እንደ ቀዱሞ ገዢ መደቦች ከሚያራምዳቸው ፖሊሲዎች እንጂ ከመጣበት ብሄር መሆን የለበትም አብይ የሚመራው ቡድን በቀድሞው ኢህአዲግ መንግስት ውስጥ እየፋፋ የመጣ ከውጭ ኒዮሊበራል ሃይሎች ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሀገርን ለገበያ ያቀረበ ቅንጣት ታህል የህዝብ ፍቅር የሌለው መንግስት ነው። ወደ ስለጣን በመጣ ብዙ ሳይቆይ ከኦሮምያ ታጋዮች ጋር የተጣላውም ለዚሁ ነው።ገዥዎች ሰውን እያታለሉ ብዙ መዝለቅ አይችሉም። እውነተኛ ማንነት መደበቅ የሚቻለው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። የቀደሞ ገዢዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያታልሉት የምንወድህ እና የምትወደን ብለው ቢያወድስቱም የእግር እሳት ሆኖ መቃብር እስኪወርዱ ድረስ ታግሎቸዋል ።የአሁኖቹ ደግሞ በተራቸው ስትኖር ኢትዮጵያዊ ስትሞት ኢትዮጵያ እያሉ ለጊዜው ሞታችንን ቢያበዙትም ታሪክ ውሉ አይስትም ።

በአሁኑ ወቅት አገራችን በመንታ መንገድ ላይ ስለመሆንዋ ብዙ ወገኖች ይናገራሉ።በመጀመሪያ አሁን ያለው አመራር ጸረ ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን በፍርሃትና በስጋት ውስጥ ሆኖ ቀንም ሌሊትም ወደ ፊት እየሸሸ የሚኖር የሚያሰጉትን በመግደል፤ በማስወገድ ብሎም በማራቅ አንዳንዴም ጦርነት በማወጅ ሲባዝን ይውላል።ለነገሩ ገዢ መደቦች ከጦርነትና ከግጭት ውጭ መኖር አይቻላቸውም። ቡድኑ ጠቅልሎ ወደ ገዢ መደብነት ተሸጋግሯል።የጭብጨባ ዘመን አብቅተዋል። ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሊያበቃ አስራአንደኝው ሰአት ደረሰዋል። ትግሉም በዲሞክራሲና በጸረ ዲሞክራሲ ሃይሎች መካከል ሆኗል። የትግሉ አሸናፊ የማታ ማታ ማን ይሆናል ለሚለው የዲሞክራሲ ሀይሎች አሸናፊ ስለመሆናቸው መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ ዛሬ የጸረ ዲሞክራሲ ሃይሎች የአገሪቱን የፍትህ እና የጸጥታ ተቋማት በመቆጣጠር ሃይላቸውን ለማሳየት ቢሞኩሩም ጸጉራም ውሻ ከመሆን አላለፉም።

አንዳንድ ወገኖች የጠቅላይ ሚንስትሩ የጦርነቱ አወጅ በትግራይ ህዝብና መንግስት ላይ ነው የሚሉ ቢኖሩም ጦርነቱ የታወጀው በሁሉም የዲሞክራሲና የፌዴራል ስርአቱን በሚደግፉ ወገኖች ላይ ነው፡፡ የኦሮምያ ታጋዮች ብቻቸውን ብምዕራብ ወለጋ እየተፋለሙ ይገኛሉ።እዚህ ላይም የማታ ማታ የፌዳራል እና የዲሞክራሲ ሃይሎች በአሸናፊነት እንደሚወጡት ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ጦርነት ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር ነው። በህዝብ ላይ ጦርነት ያወጀ መንግስት ሁሌም ተሸናፊ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ስልጣን ለማራዘም የሚለኮስ እሳት ሄዶ ሄዶ ያቀጣጠለውን ይበላል። ደርግን አስታውሱ።ሆኖም ጦሩነቱ ባላ ብዙ ፈርጅ መሆኑ መገነዘብ አስፈላጊ ነው።

አንዳንድ ወገኖች የጠቅላይ ሚንስትሩ የጦርነቱ አወጅ በትግራይ ህዝብና መንግስት ላይ ነው ማለታቸው መሰረታው ምክንት አላችው። የአብይ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣበት ቀን ጀምሮ የትግራይ ተወላጆችን የማሸማቀቅ፤ የማሳደድ፤ የማሰር እና ከስራ የማፈናቀል ድርጊቶችን ፈጽሟል፡፡ ይህ ጉዳይ አመቺ ጊዜ ሲኖር በህግ መጠየቁ አይቀርም ፡፡ ሰኔ 16 በመስቀል አደባባይ በነበረው ራሱ አመራሩ ባቀነባበረው በሚመስል የቦንብ ፍንዳታ የምርመራ ውጤት ሳይጠብቅ የቀን ጅቦች የሚል የውንጀላ ናዳ በማውረድ በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ የአሁኑ ቡድን ፕሮፖጋንዳ ስልት መንግስቱ ሃይለማሪያም የመጨረሻ አመታት የተከተለው የአጥፍቶ መጥፋት የፕሮፖጋንዳ ዘይቤ ነው፡፡ገዢው ቡድን በተደራጀ አኳኋን በአገሪቱ ቴሌቪዥኖች የትግራይ ተወላጆች አሰቃቂ ተግባር ሲሰሩ እንደነበር ዶኩመንተሪ አሰራጭቷል፡፡ መንግስት የትግራይ ተወላጆች ላይ በያሉበት ጥቃት እንዲደርሳቸው አድርጓል፡፡ የሚዲያ ሰዎችም ተመሳሳይ ዘመቻ አራምደዋል፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው የትግራይ ተወላጆች ላይ የአካል ጥቃት እንዲደርሳቸው ለማድረግና በኢትዮጵያ ፖለቲካላይ ሚና እንዳይኖራቸው፤ ተቀባይነት እንዳያገኙ ስማቸውን ለማጠልሸት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአሁን ቀደም ሲፈጸም የነበረ ወንጀል አካል ነው፡፡ የትግራይ ሰው በራሱ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በዝምታ የማለፍ ባህርይ ማቆም አለበት፡፡የትግራይ ህዝብ በ 1936 /ም ያካሄደውን ትግል ተከትሎ ጄኖሳይድ ተፈጽሞበታል፡ በ 1977 /ም የረሃብ ጄኖሳይድ ተፈጽሞበት በዝምታ አሳልፎታል፡፡ ሃውዜን ላይ 1981 /ም በቦንብ ሲጋይ በዝምታ አልፎታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትን ለመክሰስ ጊዜው አልረፈደም። የትግራይ ህዝብ በታሪኩ የደረሰበትን በደል ለኢትዮጵያ ሲል የመርሳት ባህርይ ማቆም አለበት ፡፡ ይሀ ካልሆነ የሚደርስበት በደል ይቀጥላል።

የአሁኑ ገዢ ቡድን በብዙ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በታላቁ የህዳሴ ግድብ፤ በኤርትራ እና በህገ መንግስቱ ላይ ክህደት ፈጸመዋል ። ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተሸጠው አሁን ዋሽንግተን ከተሄደ በኋላ አይደለም። ጠ/ሚሩ ካይሮን ሲጎበኝ የግብጽ ወገን በዕልልታ የተቀበሉበት ምክንያት ነበራቸው። በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ መንግስትን መጠርጠር ብቻ ሳይሆን በዚህ ምክንያት ብቻ ከስልጣን መውረድ በተገባው ነበር፡፡ የአባይ ጉዳይ አልቀዋል።አብይ የተባለው ሰው ካይሮ ድረስ በመሄድ የአባይን ውሃ እንደማይነካ መሃላ ፈጽሞ ተመልሷል ።ጉዳዩ ያለቀው ካይሮ ላይ ነው ከዛች እለት ጀምሮ ይህ ሰው በሃገር ከሃዲነት መጠየቅ ነበረበት፡፡ ሰውየው በካይሮ ሳያበቃ ሃገራዊ ጉዳያችንን ከኔ በላይ አዋቂ ላሳር በማለት ማውረድ ከማይቻልበት ከፍታ ወስዶ በዋሺንግተን የበላይነታችንን አሳልፎ ሸጧል፡፡ ኢንጂነር ስመኘው ለምን ተገደለ? ለሚለው ጥያቄም ምላሽ ያስፈልጋል ።

የአብይ መንግስት በኤርትራ የተከተለው አካሄድም በክህደት የተሞላ ነው።የኤርትራ የሞተ ስርዓት የአገራችንን የዲሞክራሲ አበባ ለማርገፍ እንዲንቀሳቀስ እድል ተሰጥቶታል። በትግራይ ላይ በጋራ ጦሩነት ለማካሄድ ተስማምተዋል።አቶ ኢሳያስ የሞራል ብቃት የሌላቸው ቢሆኑም ስለ ኢትዮጵያ ምርጫ፤ ስለ ዲሞክራሲ፤ ስለ ሰብአዊ መብት የማማከር መብት ተችረዋል ። የኤርትራው መሪ የኢህአዴግ የቀድሞ መሪዎች ያደረሱባቸውን ሽንፈት ለመወጣት ላይ ታች ሲሉ ይገኛሉ ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ የደህንነት ሃይሎች በእለታዊ ኑሮአችን ላይ ስጋት ፈጥረውብናል፡፡ የአዲስ አባባ ነዋሪ ኤርትራዊያንም ስጋት ውስጥ ገብተዋል። መታወቅ ያለበት ጉዳይ ሄዶ ሄዶ አደጋው በኤርትራዊያን ነጻነት ላይ ስጋት የሚፈጥር መሆኑ ነው ። ዛሬም ነገም ኢትዮጵያውያን በኤርትራውያን የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ እንድንገባ እድል ይፈጥራል፡፡ ኢትዮጵያ በኤርትራ ጣልቃ በመግባት በ 1952 /ም የነበረውን ፌዴሬሽን ማፍረሷን መዘንጋት የለብንም፡፡

የአሁኑ ቡድን በህገ መንግስቱ ጉዳይም የሚታመን አይደለም ስንል፤ ደርግ ስልጣን ሲይዝ ካለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን መፈክር ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ደርግ አጼውን የጣልነው ያለደም መፋሰስ ነው ሲለን የአሁኑ ቡድንም ኢህአዴግን ያፈረስነው አንድ ጥይት ሳንተኩስ ነው ብሎናል፡፡ ኢህአዴግ ላይ የተፈጸመው መፈንቅለ አመራር ለበጎ ነው ቢባልም ጦስ ይዞ መጥቷል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ህገ መንግስቱ በግላጭ እየተጣሰ ይገኛል፡፡ ትንሽ ቆይቶም ህገ መንግስቱን ያለ አንድ ጥይት አፍርሰነዋል እንደሚለን መገመት አይከብድም፡፡

ተቀራራቢ አጀንዳ ያላቸው የፖለቲካ ሃይሎችም በመሃከላቸው በታሪክ ተፈጥሮ የነበረውን ቂም መሻገር አቅቷቸው ክንዳቸውን አስተባብረው ቤተ መንግስት የመሸገውን አሃዳዊ ሃይል ለመመከት አልቻሉም፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ሊሂቃን ይህንን ሰብረው ለመውጣት ቢሞክሩም የሚዘንብባቸው የስድብ ናዳ ከባድ ነው፡፡ አንዳንዱ ጁሃርና ልደቱ በቴሌቪዥን በአንድ ላይ መቅረባቸውን ሲያወግዝ፤ ሌላው በቀለ ገርባ ስለ ህወሃት አዎንታዊ ነገር ተናገረ ብሎ ይጮሀል፡፡ይህ የሚያሳየን የአገራችን ፖለቲካ ከአንድ አይነት ሃሳብ ውጪ ማንጸባረቅ እንደ ወንጀል እንደሚቆጠር ነው።

መቋጫ

የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ትልቅ ፈተና ላይ ነው፡፡ አገሪትዋም ትለቅ ጭንቅ ውስጥ ናት ።የውጭ ሃይሎችም እጃቸው አስገብተዋል። ፖለቲካን በገንዘብ መግዛት ባህል ሆኗል። የህዳሴ ግድብ ከእጃችን ውጥትዋል ።ፖለቲካውን ከዝገትና ከዝግመት ለማዳን ሰፊ ትግል ይጠይቃል። አገር ወዳድ ሃይሎችም ጊዜው የምጥ ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ዳር መቆም ሳይሆን የመፍትሄው አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል።

Back to Front Page