Back to Front Page

ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ተጠያቂውና ሃላፊነት መውሰድ ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ነው

በዳንኤል ብ. ተክሉ

ቶሮንቶ ካናዳ

7-22-20

Danielekfta74@gmail.com

 

ከታዋቂው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት በኋላ የተቆጡና ያዘኑ የኦሮሞ ብሄር ወጣቶች ከአርባ በላይ በሚሆኑ የኦሮሚያ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመትና የህይወት አደጋ አድርሰዋል። በተለይም በሻሸመኔ፣ በዴራ፣ በአርሲ ነገሌ በባሌና በሃረር ብዙ የአማራና የትግራይ ብሄር ተወላጆች ንብረታቸው ተቃጥሏል፣ በርካታ ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል። በመንግስት በኩል 239 ሰዎች ተገድለዋል ቢባልም ቁጥሩ ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል። የተቃተሉት ሆቴሎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የንግድ ተቋማት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲሆኑ ሰው ተገድሉ ዓይኑ እንዲወጣ አከላቱ እንዲቆራረጥ አድርገዋል። ሰው ከሞተ በኋላም ቁልቁል ተደፍቶ እንጨት ላይ ተሰቅሏል።

 

Videos From Around The World

በተለይም በጣም አሳዛኙ ጉዳይ በሁሉም ወረዳዎች ላይ በተደረጉት የማቃጠልና የግድያ ተግባራት ላይ የመንግስት ታጣቂዎች ፖሊስና መከላከያ ቆመው በመመልከት ችግሩን ለማስቆም ምንም ጥረት ሳያደርጉ ቀርተዋል። እባካችሁን አድኑን እያሉ ሲለምኗቸው ለነበሩት ሰዎች ከመንግስት ምንም እንዳምናደርግ መመሪያ ስለወረደልን ምንም ልንረዳችሁ አንችልም በማለት ቆመው እየተመለከቱ ሰው ተገድሏል። በኢትዮጵያ መንግስት በጣም ተዳክሞ የመንግስት ፖሊስ በቆመበት ንፁሃን ሲቪሎች ሲገደሉ ማየት በጣም አስፈሪና ወደፊትም እንደዚህ ያለ ነገር ቢፈፀም የመንግስት ሃይል ንፁሃን ዜጎችን ተከላክሎ በህይወት እንዲኖሩ ለማድረግ ብቃቱም ሆነ ፍላጎቱ እንደሌለው ያሳያል።

 

አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ወደ ስልጣኑ ከመጣ ሁለት ዓመት ያለፈው ቢሆንም በነዚህ ሁለት የመከራና የስቃይ ዓመታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉና ሰዎች በዘራቸው ምክንያት ሲገደሉ መንግስት ችግሩ እንዲገታና እንዳይባባስ ያደረገው ጥረት የለም።

 

ባለፈው ዓመት የታዋቂው አክቲቪስትና ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ አጃቢዎች ሲነሱ በተፈጠረው ስጋት ምክንያት የተቆጡ የኦሮሞ ወጣቶች ምንም በማያውቁ 89 ንፁሃን ዜጎች ላይ ግድያ ሲፈፅሙ መንግስት ምንም እርምጃ ባለመውሰዱ በቅርቡም ለሌሎች 239 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል። በመጀመሪያ ሃጫሉም ሆነ ሌላ ከምንም የፖለቲካ ስራ ውጭ የሆነ ንፁህ ሰው በወንጀለኞች እንዳይገደል የመከላከል ሃላፊነት የመንግስት ነው። መንግስት በሃገሪቱ ያለውን የሰላም ሁኔታ ለማረጋገጥ ተግቶ ቢሰራ ኖሮ ሃጫሉም ሆነ በየቀኑ በወንጀለኞች የሚያልቀው ኢትዮጵያዊ ዜጋን መከላከል ይቻል ነበር።

 

የመንግስት ሰዎች ወደ ሚዲያ እየቀረቡ እንደተናገሩት ግድያውን የፈፀሙት አካሎች እናውቃቸዋለን ብለዋል። ቀድመው መደራጀታቸውንም እንደሚያውቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የኦሮሚያ ምክትል ፕረዚደንትና ጠቅላይ ዓቃቤ ህጓ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ መንግስት ችግር ከተፈጠረ በኋላ ማን ችግሩን እንደፈጠረው በፖሊስ ሳይጣራ ማብራሪያ መስጠት የሰዎችን ሞት ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀመበት እንደሆነ ለማወቅ ቀላል ነው። ይህ ድርጊት ባጭሩ ካልቆመ ነገም በርካታ ንፁሃን ኢትዮጱያውያን ካለምንም የመንግስት ጥበቃ ህይወታቸውንና ንብረታቸውን እንደሚያጡ ለመገመት አያዳግትም።

 

በተለይም ባሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የዘር ጥላቻ በመሰበኩ ምክንያት የተለያዩ ብሄር ተወላጆች የሆኑና በኦሮሚያ የኖሩ ኢትዮጵያውያን ለህይወታቸው በመስጋት እየኖሩ እንደሆነ ሲታወቅ መንግስት የፖለቲካ ጨዋታ ላይ ከመጠመድ በስተቀር ነገ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለማስቆም የሚያደርገው ጥረት የለም።

 

የኢትዮጵያ መንግስት በሚዲያና በፕሮፓጋንዳ ተጠምዶ በትክክል እየሰራ ያለ ለማስመሰልና የዓለም ህብረተሰብን ለማሳሳት ቢጥርም አሁን ያለው ችግር በፍጥነት ሊቆጣጠር ካልቻለ ሃገራችን ወደ ዘር ፍጅትና ዕልቂት ሄዳ ወደ መበታተን እንዳታመራ እጅግ በጣም ያሰጋል። የመንግስት ሃላፊነትን ረስቶ በተራ የፕሮፓጋንዳና የፎቶ መነሳት ፕሮግራም ላይ ተጠምዶ የሚውል ጠቅላይ ሚኒስትር ባለበት ሃገር ዜጎች በሰላም ሰርተውና በሰላም ኖረው ህይወታቸውን አስቀጥለው ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ ለማለት አይቻልም።

 

ከሁሉም በላይ በዘር ጥላቻ ላይ መንግስትና የመንግስት ባለስልጣናት እያደረጉት ያለ አስተዋፆኦ ማስተዋል ለተሳናቸው ወጣቶች በቂ የንዴትና አደጋ የማድረስ ምክንያት ተደርጎ እየተወሰደ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሞቱና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

 

አሁን በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ከነበረው ችግር ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውና እንደውም የመንግስትን ድርጊት የተቃወሙ የፖለቲካ ሰዎችና አክቲቪስቶች እንደነ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋና ሌሎች ከ5000 በላይ ሰዎች በኦሮሚያ ከ1500 ሰዎች በላይ ደግሞ በአዲስ አበባ ታስረው በመሰቃየት ላይ እንደሆኑ መንግስት እራሱ ካወጣው ዘገባ ለመረዳት ይቻላል።

 

እንዲህ ያለ ተግባር በየትኛውም ጊዜ ለዕለቱ ሰላም የሚያመጣ ቢመስልም ሲውል ሲያድር ግን ሁከትና ብጥብጥ ማስከተሉ እንደማይቀር ካለፈው ልምዳችን አይተነዋል።

 

እንዲህ ባለ አስቸጋሪና አሳሳቢ ወቅት መንግስት የመንግስትን ስራ እስካልሰራ ድረስ ምንም ሰላም እንደማይኖርና ዜጎች የመኖር መብታቸው ሊጠበቅ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። ሁሉም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊም የዓለም ህብረተሰብ ይህንን የኢትዮጵያ መንግስት ወንጀልን እንዲያጋልጥና ሰፊ ተፅእኖ የመፍጠር ተግባር ላይ እንዲሰማራ ስጠይቅ በዚህ ግፈኛ አገዛዝ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ መፅናናቱን እየተመኘሁ ነው።

 

 


Back to Front Page