Back to Front Page

የስርኣቶች መመሳሰል: ታሪክ ራሱን ሲደግም

የስርኣቶች መመሳሰል: ታሪክ ራሱን ሲደግም

ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ

22 ጥቅምቲ 2013 ዓ.ም

 

ከውጭ መንግስት ጋር በማበር ኣንድ በራሳቸው ግዛት ሥር የሚገኝ ህዝብና የፖለቲካ ሃይልን ለማጥቃት የሚሰሩ ኣራት ኪሎ የሰፈሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ናቸው። ሚኒሊክ ከጣሊያን ጋር፣ ሃይለ ሥላሴ ከእንግሊዝ ጋር፣ ደርግ ከሩሲያ ጋር ኣብይ ኣህመድ ከሰው በላው ኢሳያስ ኣፈወርቂ ጋር ይሄንን ታሪክ ደጋግመውታል። ሴራና ክህደት፣ ረሃብ፣ በሽታ እና የውጭ ሃይል እንደ መሳሪያ መጠቀም ስር የሰደደ ፖለቲካዊ ባህል ነበር ኣሁንም ቀጥሏል። እስቲ ዘርዘር ኣድርገን እንያቸው። የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩን የሸዋው ሚኒሊክ ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲል ከግብጾች፣ ከመሃዲስቶች፣ ከፈረንሳዮች እና በሰፊውም ከጣሊያኖች ጋር ወግኖ ሀዝቡን በመጭፍጨፍ ብቻ ሳያበቃ ኣገር እስከመሸጥ ደርሰዋል። እስከዚህ ትውልድ የሚዘልቅ ችግርም ትቶልን ኣልፈዋል። እንደሚታወቀው ሃጸይ ዮሃንስ ከመሃዲስቶች ጋር ሲፋለሙ በተሰዉ በሁለት ወር ውስጥ ሚኒሊክ ጣሊያኖች ከነበሩበት የቀይ ባህር ወሰን ኣስመራ እንዲገቡ በደብዳቤ ከመጋበዝ ኣልፎ የውጫሌ ውል በመፈረም የተወሰነውን የኤርትራ ክፍል ሰጠ። በዓድዋ ጦርነት ተሸንፎ የተበተነውን የጣሊያን ጦር በማሳደድ ጠራርገን ባህር እናስገባው ሲሉ ሚኒሊክን የጠየቁ እንደ እነ ራስ ኣሉላ የመሰሉ ጀግኖችም እርምጃ እንዳይወስዱ በመከልከል ሳይቆም ድል ኣደረግን በተባለው ማግስትም ኣዲስ የክህደት ውል ፈረስ ማይ ላይ መፈረሙ ይታወቃል።

Videos From Around The World

ሚኒሊክ ከሰሜን ኢትዮጵያ የሚመጣበት የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ ለማክሸፍ ሲል ግማሽ ህዝቡና መሬቱ ለጣሊያን በመሸጥ ንግስናውን ኣጠናክረዋል። ትግሬው እንዳይንቀሳቀስ እናንተ ከሰሜን እኛ ደግሞ በደቡብ በኩል ወጥረን እንጠብቃቸው የሚል የተማፅኖ ደብዳቤም ለጣሊያኖች ልከዋል። ትግራይ በሰው ሃይልና እና ኢኮኖሚ የበለጠ እንዲዳከምም የምዕራብ ትግራይ፣ ማለትም ከለማልሞ እስከ ወልቃትና መተማ የተዘረጋው ግዛትም በርስተ ጉልት ለቤገምድር እንዲገብር ኣድርገዋል። እንደርታም በተመሳሳይ ለሸዋ እንዲገብር ኣስገድደዋል። በዓድዋ፣ ገረዓልታ ሓውዜን፣ ክልተ ኣውላዕሎ፣ ኣፅቢ፣ እንደርታ እና ራያም በሚኒሊክ ሰራዊት ህዝብ ተጨፍጨፈዋል፣ ንብረት ተዘርፈዋል፣ ቤት ተቃጥለዋል፣ የቤተክርስቲያን ታቦት፣ ቅርሶችና ንብረቶች ተዘርፈዋል፣ ኣናዘርፍም ያሉ ቄሶች ተገድለዋል፣ ወጣት ወንዶች ተሰልበዋል፣ ወጣት ሴቶች በኣስገዳጅነት ለሚስትነት ወደ ሸዋ ተወስደዋል። የሆነውን ሁሉ በወቅቱ የራስ መኮነን ኣገልጋይ የነበሩትን ፍስሃ ጂወርግስ የኣይን ምስክርነታቸውን በመፅሃፋቸው ኣስፍረውታል። በዚህ ኣይነት ኣሰቃቂ ኣኳሃን ትግራይ ሁለተኛ እንዳይነሳ ለማድረግ ተሞክረዋል። የትግራይ መሳፍንቶች የውስጥ ችግርም ተጨምሮበት ህዝቡ ወደ ኣስከፊ ሁኔታ ሊገባ ችሏል።

ከሚኒሊክ ሞት ቀጥለው የመጡት የልጅ እያሱና የንግስት ዘውዲቱ መንግስታትም በውስጥ ሽኩቻ ተጠፋፍተው በሃይለ ሥላሴ ኣሸናፊነት ሲጠናቃቅ ቀድም ሲል የነበረውን ጭቆና እጅግ በከፋ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በመሆኑም ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያክል ፍዳውን ያየው የትግራይ ህዝብ የተጫነበትን የመከራ ስርኣት ማስወገድ እንዳልበት ኣመኖ ተንቀሳቀሰ። የቐዳማይ ወያነ ትግልም ተጀመረ። በቐዳማይ ወያነ ታጋዮች የተርበደበደው የኣፄ ሃ/ሥላሴ ስርኣትስ ትግራይ ላይ የተከተለው ኣምበርክኮ የመግዛት ፖሊሲ ካለፈው የኣገዛዝ ዘመን እጅግ የከፋ ነበር

የንጉሱን ስርኣት ያንገሸገሸው የትግራይ ህዝብ ሠብኣዊ ክብሩን እና መብቱን ለማስመለስ ቆርጦ ሲነሳ የሸዋው መንግስትም በሃይል ለመደፍጠጥ ወሰነ። በመሆኑም ከጎንደር እስከ ወሎ እና ትግራይ የተዘረጋ ብዛት ያላቸው ወታደራዊ እዞች በማስቀመጥ የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክ ሞከረ። ወያኔዎቹ ቀላል ኣልነበሩምና የመጣውን የንጉሱ ሰራዊትና የጦር መሪዎች ሙትና ሙርከኛ ኣደርገው በታተኑት። መቐለንም ተቆጣጠሩ። በዚህ የተደናገጠው ንጉስ የእንግሊዝ መንግስት ኣየር ሃይልን (British Royal Airforce) ለምኖ የትግራይ ህዝብ፡ ታጋዮች፡ ገበሬዎች፡ መንደሮች እና ከተሞቻችን በቦምብ ኣስጨፈጨፈ። ለጊዜውም ቢሆን ትግሉ እንዲከሽፍ ኣደረገ። ልክ ሚኒሊክ እንዳደረገው ከጠ/ግዛቱ የሚመጣበትን ስጋት ለመቀነስም ራያን ከነ ህዝቡ ወሎ ለነበረው ልጁ ልዑል ኣስፋወሰን ሰጠ። ቀደም ሲል በሚኒሊክ በርስተ ጉልት ብቻ ለጎንደር ተሰጥቶ የነበረውን የምዕራብ ትግራይ ግዛትም (ከለማልሞ እስከ ወልቃይት ጸገዴ፣ ኣገረብና መተማ) ሙሉ በሙሉ የጎንደር ግዛት ኣደረገው። ህዝቡ ተምሮ ኣንዳይነቃም በወቅቱ ከነበሩት 35 ት/ቤቶች 33 ተዘግተው ለቤተክህነት እንዲሰጡ ኣደረገ። ከዝርፊው በተጨማሪ ከባድ ግብር ተጭኖበት ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ለድህነት ተጋልጦ ይበታተን ዘንድም ፖሊሲ ተቀርጾ ተሰራበት። ተሳካላቸውም። ራሳቸው ኣደህይተው የበተኑት ህዝብም ተመልሰው የፌዝ ቀልዶችና ግጥሞች ተሳልቁበት።

ሰው በላው የደርግ መንግስትም በሩሲያውያን ወታደርዊ መኮንኖችን እና የጦር መሳሪያዎች ታጅቦ መብቴን ያለውን ህዝብ በእግርኛ ወታደር ኣረዱት፡ በታንክ፡ በመድፍና በክላስተር ቦምብ ፈጁት። በዓለም ፊት ለረሃብና ለመከራ ዳርገውት ሲያበቁ ዓለም ኣቀፍ ማህበረሰብ እርዳት እንዳይሰጥም ከልክለው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሰፈራ ያን ያሚያክል ደግሞ ለስደት ዳረጉት። የ1977 ዓ.ም ድርቅ፣ የደርግ ፋሺሽታዊ ዘመቻ፣ እርዳታ መከልከል እና ሻዕቢያ መንገድ ዘግቶ ህዝቡን ለጥቃት የማጋልጥ እኩይ ተግባ በጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍረዋል። በክልሉ የሚኖር ህዝብም እንደፈለገው ተንቀሳቅሶ እንዳይሰራ የከተማና መንደር እሰረኛ ኣድርገውት በብዙ ወራት ኣንድ ቀን በወታደራዊ ኮንቨይ ብቻ ፈቃድ ኣውጥቶ እንዲንቀሳቀስ ተደረገ። የሸቀጣሸቀጥ እና ንግድ ዝውውርም እንደዚሁ በሚኖር የወታደራዊ ኮንቨይ እንዲወሰን ሆነ። በዚህ የመኖርና ያለመኖር ሁኔታ ሆኖ ሃብት ማፍራትና ኢንቨስትመንት ፍፁም የማይታሰብ ጉዳይ ነበር። ያ ሳያንስ ደግሞ በሚዲያ የማጥላላት ዘመቻ በማካሄድ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በጠላትነት እንዲታይ ኣደረጉ። የትግራይ ህዝብ ግን የትግል ወኔው የበለጠ ተጠናክሮ ግማሽ ሚሊዮን ሰራዊት ያለውን ጨካኝ የፋሽሽቶች መንግስት ላይመለስ ገረሰሰው። እውነት ነው ሙርከኞቹና ልጆቻቸው በትግራይ ህዝብ ላይ ያላቸውን የመረረ ጥላቻና ሽንፈታቸውን ለማወራረድ ስራቸውን በኣዲስ መልክ ቀጥሏል። ውጤቱ ለወደፊት የሚታይ ይሆናል።

በ የኛዎቹ ስህተት የመጣው የኣሁኑ ግልግል ፋሽስት ኣብይ ኣህመድስ ወዴት ይሆን? ይህ ፋሽሽት ካለፉት ኣገዛዞች ስላልተማረ በሩሲያ ተደግፈው ሲዋጉ የተማረኩ የደርግ ጀነራሎች እና ዘር በማጥፋት የተወነጀሉ ደርግ ኢሠፓዎችን በኣማካሪነት ከማስቀመጥ ኣልፎ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን ደመኛ ጠላት የሆነውን ፋሽሽቱ ኢሳያስ ኣፈውርቂን ተወዳጅቶ በህብረት ትግራይን ለማንበርከክ እያሴረ እንደከረመ የኣደባባይ ሚስጥር ነው። ከዚህ ጎንለጎንም ነገስታቶቹና ደርግ ኣንዳደረጉት ሁሉ የትግራይን ህዝብን ለጀኖሳይድ በሚያጋልጥ ሁኔታ በሚዲያ ከማጠልሸት ኣልፎ በኢኮኖሚ ለማዳከምም ያላስቀመጠው መሰናክልና ክልከላ የለም። መንገድ ከመዝጋት ጀምሮ ከትግራይ ውጭ ባሉ ተጋሩ ተራ ዜጎችና ነጋዴዎች እየፈጸመው ያለውን ግፍም ታሪክ የማይረሳው ነው። ሌላው ቀርቶ የኣምበጣ እና የኮረና ወረርሽኝም እንደ ትልቅ ጸጋ ወስዶ የጥቃት መሳሪያ ኣድርጎ እየተጠቀመበት ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ከዓለም ዓቀፍ ማህብረሰብ የተገኘው የኣፍ መሸፈኛም የትግራይ ተማሪዎች ብቻ ለይቶ እንዳይሰጣቸው ከመከልከል ኣልፎ ፀረ ኣምበጣ መከላከያም በጎረቤት ክልል ብቻ በመረጨት የትግራይ ገበሬ እገዛውን እንዳያገኝ ኣድርገዋል። በዚህ ረገድ በሰብኣዊነት ላይም በጀኖሳይድ የሚመደብ ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል። ረሃብ፡ ኣምበጣ እና የበሽታ ወረሽኝ እንደ ፖለቲካ መሳሪያነት መጠቀም በዓለም ኣቀፍ ህግ ስለሚያስጠይቅ ተጋሩ የህግ ባለሙያዎች እዚህ ላይ ልትሰሩ ይገባል።

ይህ ወደር የሌለው ዋሾ (Pathological liar)፡ ከሃዲና ኣገር ሻጭ ኣስከ ኣሁን የተከተለው የጥፋት መንገድ መጀመሪያ የነበረውን የህዝብ ድጋፍ በወሳኝ መልኩ እንዳጣ ቢገነዝብም ስልጣን ወይም ሞት በማለት እስከ መጨረሻ የህዝቡን ደም ለማፍሰስ ዝግጁነት እንዳለው ግልጽ ሆነዋል። ይህ ይሳካለት ዘንድም የሰው በላው ኢሳያስን መንገድ መከተል መርጠዋል። ከኢትዮጵያና ከታዋቂ የሻዕቢያ ካድሬዎች እንደምንሰማው ደግሞ የኤርትራ ወታደራዊ መኮንኖች እና የደህንነት ኣመራሮች በኢትዮጵያ መከላከያና ብሄራዊ ደህንነት ውስጥ እጃቸው ኣስገብተው ኣገሪቱን ኢሳያስና ኣብይ ወደሚፈልጉት ኣቅጣጫ እየነድዋት ይገኛሉ። የኣብይ ኣህመድ ቀደም ካሉ መሪዎች (ንጉሶችና ደርግ) የሚለየው እና መሰረታዊ የስትራቲጂ ውድቀቱ ሲታይ መጀመሪያ ላይ የተሰጠውን የህዝብ ድጋፍ በሚያስጣው መንገድ ከመጓዙም በላይ ይባስ ብሎ በሁሉም ኣይነት ሳይንሳዊ መለኪያ ከኢትዮጵያ ያነሰ ኢኮኖሚ፣ ጦር ሰራዊት፣ ብሄራዊ ደህንነት ካለው እና እጅግ ያነሰ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ካስመዘገበው ኢሳያስ ኣፈወርቂ ጋር መንጠልጠሉ ነው። ለማነኛውም ይህ በከፍተኛ ደረጃ የኣገር ክህደት የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን ማስታወስ ጠቃሚ ነው።

በኣጭሩ ፋሺሽቱ ኣብይ ኣህመድ ኢትዮጵያ ያጋጠማት የዚህ ዘመን ስሕተት ነው። የተከተለው መንገድ ደግሞ ዘላቂ ጥፋት እና የኣገር መፍረስ እንደሚያስከትል ግልፅ ሆነዋል። እስከ ኣሁን እንደ ኣገርም ሆነ ኣንደ ትግራይ ብዙ ጉዳት ኣድርሰዋል። ከዚህ በላይ እንዳይሄድ ግን በኣገዛዙ ላይ ትርጉም ያለው ስራ መሰራት የግድ ይላል። ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችም በ27 ኣመታት ያገኙትን ራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንገስታዊ መብትና የፌደራል ስርኣቱ ከነኣካቴው ከእጃቸው ሳያፈተልክ ቆርጠው መታገል ያለባቸው ዛሬ ነው። በዚህ ዘመን ከኣራት ኪሎ በሚመደብ ምስለኔ (ምስለ እኔ - ዛሬ ምስለ ኣብይ) መተዳደር በፈቃደኝነት ባርነትን መቀበል ነው። ስለዚህ ''ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ኣለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል'' እንደተባለው በጊዚያዊ የጥቂት ጥገኛ ሊሂቃን ጥቅም ሳይታለሉ ለዘላቂ መብታቸው መታገል ይኖርባቸዋል። የትግራይ ህዝብም ከዚህ በፊት በነበሩ ኣሃዳዊና ጨፍላቂ ኣገዛዞች እንደታገላቸው ሁሉ ኣሁንም ኣሃዳዊ የጠቅላይ ኣግላይና የፋሺሽትቶች ኣገዛዝ ለምቀበል ዝግጁ ስላልሆነ እስከ መጨረሻ ታግሎ መብቱን ያስከብራል ብቻ ሳይሆን በኣጠቃላይ የገባበት የፖለቲካ ኣዙሪትም ለኣንዴና ለመጨረሻ እልባት ለማድረግ ቆርጦ ተነስተዋል።

ለትግራይ ህዝብ፡- በመጨረሻ ማስታውስ የምፈልገው የትግራይ መንግስት፣ ህወሓት፣ ብክልሉ ያላቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ተጋሩ ሙህራንና በኣጠቃላይ ሊሂቃን፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ጀግኖች ኣባቶችና እናቶች፣ ወጣቶች እና የንግድ ማህብረሰቡ ሁሉ መብታቹ ሊደፈጥጡ ለቋመጡ ኣዲስ ፋሺሽቶችን ለመጋፈጥ በኣንድነት እንደቆማቹ ሁሉ፣ የኮረናም ሆነ የኣምበጣ ወረራ በኣንድነት እንደመከታቹ ሁሉ ለመብት ከመታገል በዘለለ መልሶ መላልሶ የሚያገረሽብንን የፖለቲካ ኣዙሪት ለኣንዴና ለመጨረሻ ምዕራፉን ለምዝጋት የሚያስችል ግልፅ የሆነ ግብ ማስቀምጥ ይገባናል። ከዚህ በኋላ ኣንድ ውድ የትግራዋይ ሂወት መስዋእት የሚከፈለው ለትግራይና ግልፅ ለሆነ ግብ ብቻ ነው።

በእርግጠኝነት ይህ የፋሺሽቶ ሴራም እንደለፉት ያልፋል! 


Back to Front Page