Back to Front Page

ተደማሪው ቡድን ፤በአገራችን ጉሮሮ ላይ የተሰነቀረ አጥንት፤

 

ተደማሪው ቡድን ፤በአገራችን ጉሮሮ ላይ የተሰነቀረ አጥንት፤

ከአብሳር 06-16-20

የአገራችን የፖለቲካ ጡዘት እየጨመረ መሄዱ አልቀረም ። አሁንም ትልቁ ጉዳይ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ይሽከረከራል። ቅራኔው ለህዝብ ስልጣን የመስጠትና ያለመስጠት ጥያቄ ሆኗል ።የለውጡ ሃይል ጸረ ለውጥ ከሆነ ሰነባብቷል። ምርጫ እንደማይካሄድም ተነግሮናል። ምርጫ እናካሂዳለን ባሉትም ላይ ጦርነት ታውጇል። ከሳምንት በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬርያ ከሀላፊነታቸው በፈቃዳቸው ሲለቁ ግልገል አምባገነን እየተከሰተ መሆኑን በማመላከትም ጭምር ነበር። የአመንስቲ ኢንተርናሽናል በአገራችን የሰብአዊ መብት አያያዝላይ ያቀረበው ሪፖርትም በተደማሪው ቡድን ላይ የማይድን ራስ ምታት ሆኗል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከፓርላማው ጋር የነበራቸው ቆይታም ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የተድበሰበሰ መልስ በመስጠት ተጠናቋል ።

አገራችን በፖለቲካ ድርቅ ምች በተመታችበት የፖለቲካ አውድ ላይ ሆነን ስናየው የወይዘሮ ኬርያ እርምጃ ትልቅ ክስተት እና ታሪካዊም ጭምር ሆኖ እናገኘዋለን። ወይዘሮ ኬርያ ግለሰቦች ፍንትው ብለው ታሪክ ሰሪዎች መሆናቸውን አረጋግጣለች። የወይዘሮ ኬርያ ድርጊት የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ፣ የአዲስ ዘመን መባቻን ያመላክታል ። የፖለቲካ ምህዳሩ አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ የኬሪያ ደፋር እርምጃ ለቀጣይ ትውልዶችም በተምሳሌትነት የሚታይ ፈር ቀዳጅ ነው። በአገራችን የፖለቲካ ባህል ትልቅ አሻራ ጥሎ ለማለፍ ታሪክ ዕድል ሰጥቷታል።የአምባገነኖችን ህልም አምክናለች። የኬርያ ድርጊት በታሪክ ላይ ያለው ተጽእኖ ተደማሪው ቡድን ከሚመጻደቅለት ለውጥ በላይ ሚዛን የሚደፋነው። ኬርያ የፖለቲካ ስልጣን በህግወጥነት ለመያዝ በመደረግ ላይ ያለውን ሴራ አጋልጣለች። ኬርያ ሴቶችን ወጣቶችን የተለያዪ እምነቶችን ብሄር ብሄርሰቦችን በመወከል ህገ መንግስቱ እንዲከበር የትግል ጥሪዋን አስተላልፋለች ። ኬርያ የሁላችንም ተምሳሌት ናት፤ ነገን ያማተረች ታጋይ ናት። ለአገራችን የፖለቲካ ሰዎችም ትልቅ ትምህርት አስተላልፋ ተሰናብታለች ።

Videos From Around The World

ተደማሪው ቡድን ዲሞክራሲያዊ ስርአቱን እየናደ ስለመምጣቱ አጠያያቂ አይደለም ። የቡድኑ ጸረ ዲሞክራሲያዊነት መገለጫው የፖለቲካ ስልጣንን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ለማራዘም የሄደበት ርቀት ነው።የሚገርመው ደግሞ ምርጫ መካሄድ አለበትያሉትን ወገኖች በህገወጥነት ይከሳል። የጨረባ ምርጫ በማለትም ከወዲሁ ያጣጥላል። ደርግ ወታደራዊ መንግስት እንኳ ሳይቀር የይስሙላ ምርጫ ያካሂድ እንደነበር የሚታወስ ነው። ተደማሪው ቡድን ጎርፍ እያያሳቀ ይወስዳል እንዲሉ ቀስ በቀስ ህገ መንግስቱን በማፈራረስ ላይ ይገኛል። አካሄዱ መንግስቱ ሃይለማርያም ምሳ ሊያደርጉን ሲያሴሩ ቁርስ አደረግናቸው እንዳለው አድፍጦ ህገመንግስቱን በመቅደድ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እና ህልውና ለመደፍጠጥ በትጋት እየሰራ ነው፡፡ለዚህ ውለታውም ተደማሪዎች ነን ባዮችብልሁ፤ቆራጡ፤ተተኪ የሌለው መሪያችን በማለት እያዜሙለት ይገኛሉ።

ብዙ ወገኖች ስለ ህገመንግስቱ ብሎም ስለ ፖለቲካ ምርጫው የሚቆረቆሩት ህገ መንግስቱ የአንድነታችን ማሰሪያ ቃል ኪዳን በመሆኑ እንጂ ሌላ መነሻ ትርጉም የለውም።የፖለቲካ ምርጫ አስፈላጊ ነው የምንለው ህዝቦች በመረጡት ሰው መተዳደር ስላለባቸው ነው። ህዝባዊ ተቀባይነቱ እየተመናመነ የመጣው ቡድን ምርጫውን ላልተገደበ ጊዜ በማስተላለፍ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም እየሞከረ ነው ። ሆኖም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ይህን ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለም፡፡ ህዝቦች በመረጡት መንግስት የመተዳደር መብት ስጦታ ሳይሆን መብት መሆኑ ማወቅ በተገባ ነበር፡፡

ገዢው ቡድን በአንድ ሳምንት በተከታታይ የፖለቲካ ሞቱን የሚያፋጥኑ ሁኔታዎች አጋጥመውታል፡፡ከኬርያ የጀግንነት ፍጻሜ ሌላ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በተደማሪው ቡድን ላይ የቦንብ ናዳ ያወረደ ፍጻሜ ነበር። ቡድኑ በአለማቀፍ ደረጃየት ይደርሳል እንዳልተባለ፤ አሁን ግን ስሙ ተቀይሮ የአምባገነኖች መታወቂያ ተሰጥቶታል። ተደማሪው ቡድን ከእንግዲህ እንደቆሰለ ጅብ ቁስሉን እየበላ እያስታመመ ከመኖር ሌላ ተስፋ የለውም። ዕድሉ እንደሁሉም አምባገነኖች ከመሆን አላለፈም።

 

ህዝቦች በሂደት በተደማሪው ቡድን ላይ የጋራ ግንዛቤ እየያዙ መጥተዋል ። ተደማሪውን ለመረዳት ማያችን የሌሎች አለማት ፖለቲካ ለመረዳት ከምንከተለው የትንታኔ ዘይቤ የተለየ አይደለም። ከዚህ አንጻር በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር በህዝቦችና በተደማሪው ቡድን የህዝቦችን ትግል አድብቶ በመንጠቅ ወደ ሥልጣን ሾልኮ የመጣ ቅይጥ ነው።ተደማሪው ቡድን የሚጻረሩትን እየገፋ ብጤዎቹን እያቀፈ ዛሬ መደባዊ ቅርጹ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ይህም ሆኖ የፖለቲካ ሁኔታው ተንሸራታች በመሆኑ መደባዊ ቅርጹ የተረጋጋ ነው ማለት አይቻልም። በቡድኑ መካከልም ሙሉ መተማመን አለ ለማለት አይቻልም። እንደ ጅብ ጎን ለጎን የሚሄድ፤የማይተማመን ስብስብ ነው። በአገራችን ያለው አለመረጋጋትም መነሻው የቡድኑ አለመረጋጋት ነጸብራቅ መሆኑ ግልጽ ነው።በአሁኑ ወቅት የቡድኑ መሰባሰቢያ መፈክሩም ስልጣን ከለቀቅን ሁላችንም እስር ቤት እንገባለን ወደሚለው ወርዷል።

የተደማሪው ቡድን አባላት እነማን ናቸው የሚለውንም ፍንትው አድርጎ ማየት ያስፈልጋል። የቡድኑ አባላት በተለያዩ ወቅቶች በአገራችን በተደረጉ ፍልሚያዎች የተሸነፉ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ያቀፈ ነው።በአገራችን ባለፉት አመታት በተካሄዱት የፖለቲካ ትግሎች በተደረጉ ፍልሚያዎች ተሸንፈው ከፊሎቹ በስደት አለም ከፊሎቹ በአገር ቤት ሌሎቹ ደግሞ በጎረቤት አገር ሆነው ታሪካቸውን በመጻፍ የስንብት ዘመናቸውን ሲጠባበቁ የነበሩናቸው።የዘመኑ ተደማሪዎች ደርግ ሲወድቅ የተሸነፉ፣ በምርጫ 97 የከሸፈባቸው ግለሰቦች፤ በህወሃት ትግል ተሸንፈው የተሰደዱ ናቸው። ተደማሪዎቹ በኢህአዴግ ውስጥ ሆነው እየተላላኩ አድፍጠው የቆዩ የፖለቲካ ስብእና የሌላቸው ለባእድ ሃይሎች የሚሰልሉ በቀድሞው የኢህአደግ አገላለጽ በኒዮ ሊበራል አስተሳሰብ የተሰለቡ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ተሸናፊዎች ናቸው፤ የሽንፈት ታሪካቸውም አንድ ያደርጋቸዋል።

አሁን የፖለቲካ ስልጣን የተቆጣጠረው ቡድን የተሰባሰበው በአመለካከት እና በጥቅም ተቀራራቢ የሆኑ ተሸናፊዎች ከአዲስ አበባ እስከ ዋሺንግተን በመጠራራት የተፈጠረ የጥምረት መንግስት እየሆነ መጥቷል፡፡ አላማውም ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ለሁሉም ወገን የተስፋ ምድር መሆን የጀመረችን አገር ተስፋ ለማጨለም ነው፡፡ በመደመር ስም ተደብቀው የሚገኙ ባለጊዜዎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከኤርትራና ከግብጽ ጋር በማበር አገራችንን ሲወጉ የቆዩ፤በየፈርጁ የሽንፈት ጽዋ የቀመሱ ግለሰቦች ናቸው። የኤርትራ አምባገነን መሪም ከዚሁ ጋር የተደመረው በተግባር እና በአስተሳሰብ የከሸፈበት መሪ በመሆኑ ነው። የኢሳያስ አፈወርቂ ያልተገደበ ፍላጎትም በጦር ሜዳ ተሸንፏል። በኤርትራ የጀመረው የአገር ግንባታም ከሽፏል። ዛሬ በስተርጅና ሆኖ የወጣትነት ህልሙ የተሳካ ይመስል በኢትዮጵያ አደባባዮች ቢንጎማለልም ከሽንፈት ታሪኩ ሊያገግም አይችልም፡፡ ግብጽም ከዚህ ጎራ ጋር የተሰለፈችበት ዋናው ምክንያት በህወሃት መራሹ መንግስት ያጋጠማትን ሽንፈት ለማካካስ ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመንግስት ስልጣን የአገር ውስጥ ተሸናፊዎች እና የጠላት መንግስታት በጥምረት የመሰረቱት መንግስት ሆኗል፡፡

በአሁኑ ሰአት ቤተ መንግስት ውስጥ ሁለቱ ቡድኖች እየተጣረሱ ቢሆንም የሃይል ሚዛኑ ወደ አሀዳዊው ወገን ያመዘነ ይመስላል። ይህ ክንፍ ህገመንግስቱ ቶሎ እንዲቀደድለት ይገፋል። ይህ ቡድን የአስመራው ቡድን ይባላል። አስተባባሪው የአስመራው መሪ ሆነው በግለሰብ መብት ዙሪያ ተደራጅተናል የሚሉ ቡድኖችን ያቅፋል። ብሄር በሄረሰቦች ለመጥራት ይጠየፋል። ውስጣዊ ይዘቱ አሃዳዊ ነው። ሞዴሉም አቶ ኢሳያስ በኤርትራ የሚያራምደው የአገር ግንባታ ፖሊሲ ነው።

ሁለተኛው ተደማሪ የፌዴራል ስርአቱን ቢወደውም አስተሳሰቡን ለማራመድ የሃይል ሚዛን የለውም። ይህ ቡድን በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደው ትግል እንዲጠናከር ፍላጎት አለው፡፡ በተለይም የፌዴራሊስት ሃይሎች መጠናከር ጉልበት እንደሚሆኑት ያምናል፡፡

የፖለቲካ ስልጣን ከኢህአደግ ለመንጠቅ በተደረገው ትግል የኦሮሞ ብሄረተኞች የነበራቸው አሰላለፍ ከተደማሪው ቡድን የተለየ ነው። የኦሮሞ ታጋዮች ብሄራዊ እንቅስቃሴ የሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ የነበረው በመሆኑ ዲሞክራሲያዊ ባህሪይ ነበረው። በይዘቱ ከተደማሪው ቡድን ጋር የሚያገናኘው ባይኖርም ተደማሪው ቡድን ወደ ስልጣን ለመውጣት ተጠቅሞበታል፡፡ ደርግ የኢትዮጵያ የተማሪዎችን ትግል የመነተፈውን ያህል የኦሮሞ ትግልም በተደማሪው ቡድን ተነጥቋል ።በኦሮሞ ወጣቶች ትግል አማካይነት ወደ ስልጣን የወጣው ቡድን ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ እየዳዳው ስለሆነ፤የኦሮሞ ታጋዮች ይህን የማክሸፍ ታሪካዊ ሀላፊነትና ግዴታ ያለባቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

የቡድኑ ዕለታዊ ድርጊቶች ግልጽ በመሆናቸው ዜጎች በተቀናጀ አግባብ ለመታገል የበለጠ ጥምረት እንደሚያስፈልግ ሁኔታው ያሳስባል። ዜጎች የተቀናጀ ትግል ለማካሄድ አስቀድመው የተደማሪዎቹን ስብስብ እና ጥንቅር፣ አመጣጥ፣ የኋላ የፖለቲካ ታሪክ፣ ተደማሪዎችን ያስተሳሰረ ክርላይ መግባባት ይጠይቃል። በዚህ ትይዩ ከተደማሪው ቡድን በተቃራኒው ጎራ ለይተው ተደማሪ ነኝ ባዩ የሚያራምደውን ፖሊሲ ገና ከጅምሩ ተረድተው በመታገል ላይ የሚገኙትን መነሻቸው ምን እንደሆነ ማወቅ እና አሰላለፍ ማስተካከል የወቅቱ አስፈላጊ ጥሪ ነው። ትላንት ሳይገባቸው ተደምረናል ብለው የነበሩ ወገኖችም ንጋት ሲደርስ አሰላለፋቸውን በማስተካከል ሳይረፍድ ወደ ትግሉ የሚቀላቀሉበት ወቅት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። በአገራችን ጉዳይባለቤት ነን የምንል ዜጎችም ተደማሪው ቡድን በየዕለቱ በሚያዘንብልን አዳዲስ ማርከሻ ቃላት ተዘናግተን ህልማችንን እንዲያጨነግፍ መፍቀድ የለብንም።

 

 


Back to Front Page