Back to Front Page

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 101 ሴራዎች መቋጫ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 101 ሴራዎች መቋጫ

ተስፋየ ለማ  10-05-20

መስከረም 25 ቀን 2013 ዓም እንሆ ደረሰ። ጠቅላይ አሚኒስትር አብይ አህመድና ግብረ አበሮቻቸው በአገሪቱ ላይ የተለየ ሃላፊነት የሌላቸው እንደ ማንኛውም ዜጋ፣ ቡድን ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ሆነው ይቀጥላሉ ወይም በሰሩት ወንጀል ዘብጥያ ይወርዳሉ የሚሉ በርካቶች ናቸው። በሃይል የህዝቡን ፍላጎት በማፈን አሁንም ሌላ የህዝብን እምብይተኝነት አቅጣጫ የሚያስቀይር ትኩረትን የሚይዝ ሁኔታ ይፈጠራል የሚሉም አሉ።

Videos From Around The World

እርግጥ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡበት ማግስት ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ የተቸረው መሪ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የመጀመርያ ንግግራቸውን ባደረጉበት ወቅት "ይቅርታ፣ ፍቅር፣ አንድነት" የሚሉ ሶስት መሰረታዊ ፅንስ ሃሳቦችን ይዘው በመምጣታቸው 2006 2007 2008 2009 በበአገሪቱ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የነበረ የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት ይስተካከላል፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ተሰርተው በነበሩ ስኬታማ የጸረ ድህነት ትግል ላይ ኣዳዲስ ስራዎች እየተጨመሩ የአገራችንን ህዳሴ አንድ ላይ ሆነን እውን እናደርጋለን የሚል አስተሳሰብ በበርካቶች አእምሮ ናኝቶ እንደነበርም ይታወቃል፡፡

በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎች እየዞሩ መልካም የሚባሉ ንግግሮችን በማድረግ ቀላል የማይባል ድጋፍ ማሰባሰብ ችለው ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችም ሆነ የአንዳንድ አገራት መሪዎች ተቀባይነት አስገኝቶላቸው ነበር።

ይሁን እንጂ ከመጀመሪያ በአንደበታቸው እንደገለጹት የንግስና ምኞታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ለዚሁ ይረዳኛል ባሉት ጽንፈኛ ቡድን በመከበባቸው ከገቡት ቃል አንዷን እንኳን ወደ መሬት ማውረድ ተስኗቸው በምትኩ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን መፈጸም ሲጀመሩ ነበር የበርካቶች ተስፋ መጨለም የጀመረው፡፡ ተስፋ ያደረገ ህዝብ ተስፋው ህልም መሆኑን መገንዘብ የጀመረው። ሁሉም ነገር "ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን አላይ" ዓይነት ነገር መሆኑን የተረዳው። ቆየት እያለ ሲሄድም የያዘውንና የነበረውን ማጣት የጀመረው።

በሆይ ሆይታ ግዜ እንደሚታወቀው በእስር የነበሩ ፖለቲከኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተፈቱ፡፡ በተለያዩ የውጭ አገራት ተጠልለው የነበሩትንም ወደ ኣገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ፡፡ ከዚያም በዘለለ በኢትዮጵያና በኤርትራ የነበረውን 20 ዓመታት የዘለቀ ችግር አስመራ ድረስ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ጋር በመወያየት በሁለት አገራት ሰላም ለማስፈን አስችሏል የተባለለትና የዓለም የሰላም ሽልማትን ያስቸረ የሁለቱ አገራት መሪዎች ግንኙነት ተጀመረ፡፡

ዳሩ ግን ይህ ሁሉ የተሰራው መርህን መሰረት በማድረግ ለህዝቦች ጥቅም ሳይሆን በሌላ አሻጥርና ተንኮል የታጀበ በማር የተጠቀለለ እሬት መሆኑ እየተገለጠ መጣ፡፡

በተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች ምትክ አገር ውስጥ የነበሩ በኢህኣዴግ ዘመን ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ፣ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ጠንክረው ሲሰሩ የነበሩ፣ ለህዝብ ደህንነት ሲሉ ህይወታቸውን አደጋ ላይ በማስገባት አገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሲረከቧት የደረሰችበትን ደረጃ እንድትደርስ ያደረጉ ፖለቲከኞች፣ የደህንነት ሃላፊዎችና የመከላከያ አመራሮች እየተመረጡ ወደ እስርቤት እንዲገቡ አደረጉ፡፡

ድርጊቱ በሃላፊነት ላይ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን ለማስወገድ ያለመ ስለነበር "ሰላም፣ ይቅርታ፣ ፍቅርና አንድነት" የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወርቃማ ቃላት የይምሰል ሆኖ በመቅረቱ የለውጡ ሁኔታ ወደ ሌላ አቅጣጫ አመራ፡፡ መንግስት ከእስር ቤት በሺዎች እየፈታ ተመልሶ በአስር ሺዎች ማሰሩን ተያያዘው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላምም በህዝቦች መካከል እውነተኛ እርቅ እንዳይመጣ ለሳምንት የተከፈቱ የሁለቱ አገራት ድንበሮች እንደገና እንዲዘጉ ተደረገ፡፡ ይህ የዓለም ህብረተሰብን ሳይቀር ያታለለና የዓለም የሰላም ሽልማት ያስገኘ ሌላ ህቡእ ዓላማ ያለው ማታለያ ተግባር እንጂ እውነት አለመሆኑ ታወቀ፡፡

ሐቀኛ ስምምነት ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ በሁለቱ አገራት ያሉ ህዝቦች የእርስበርስ ግንኙነታቸው መሻሻል ነበረበት፡፡ በተለይ ደግሞ ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የትግራይና የኤርትራ ህዝቦች ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማድረግ ነበረባቸው፣ ድንበሩም መልሶ ባልተዘጋ ነበር።

ኢሳያስ አፈወርቂና አብይ አህመድ በአስመራና በአዲስ አበባ የሚያደረጉት ምልልስ እውነትም ሌላ ተንኮል አዘል መሆኑ ተደረሰበት፡፡ በዋናነት የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን ለማጥፋት የጋራ ጥምረት መፍጠር እንደሆነም ብዙ ተንታኞች አስምረው ተናገሩ፡፡

ህወሓት በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት መስራች እንደመሆኑ መጠን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያቀዱትና የተነሱበት አሃዳዊ ስርዓት በአገሪቱ የመትከል አስተሳሰብ አይቀበልም፡፡

የትግራይ ህዝብ የደርግን አሃዳዊ ስርዓት ለመደምሰስ 60 ሺህ በላይ ወጣቶችን ገብሯል፤ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ አካላቸው ጎድሏል። ከዚያ ሁሉ መስዋእትነት በኋላ በአገሪቱ የተጀመረው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ሂደት በቀላሉ እንዲጨናገፍና የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ዳግም እንዲጨፈለቅ አይፈቅድም፡፡ በመሆኑም ህወሓትን ማጥፋት፣ በህወሓት የተመሰረቱ የተለያዩ የአገር ደህንነት የሚጠብቁና ሌሎች ተቋማትን ማፍረስ የመጀመርያ ተግባር ተደርጎ ተወሰደ፡፡

በዚህም መሰረት ዓለም የመሰከረለት ጠንካራ የደህንነት ተቋም እንዲፈርስ በደህንነት ተቋሙ ሲሰሩና አገራቸውንና ህዝባቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ ዜጎች እንዲታሰሩ ተደረገ፡፡ በመከላከያ ሰራዊቱ ሲያገለግሉ የነበሩ መኮንኞች፣ ጀኔራሎችና በተለያየ የሃላፊነት እርከን ሲሰሩ የነበሩ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ዜጎች ማንነታቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ በሰበብ አስባቡ ከሃላፊነት ተባረሩ፡፡

የአብይ አህመድ መንግስ ሃላፊዎቹን በማባረር ብቻ ያበቃ አልነበረም። በእስር ቤት ያጎራቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ መልክ የአገሪቱ የደህንነት ተቋም እንዲፈርስ በአገሪቱ የመከላከያ ተቋማት የሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች እንዲባረሩና እንዲታሰሩ ተደረገ

የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊትም ለውጥ በሚል ሽፋን ዓይኑን በጨው አጥቦ በሚፈልገው መልክ እንዲደራጅና እንዲመራ ተደረገ፡፡ አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ይህ ሁሉ ተደራራቢ ስህተት ተፈጸመ፡፡ በእርግጥ ስህተተ ብቻ ሊባል አይችልም። በእቅድ ተይዞ የተሰራ ስራ እንደሆነ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ከፍተኛ አመራሮቹ በፖለቲካ ሴራ እንዲሰው ተደረገ።

የአብይ አህመድ ተግባር በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ የክልሎችን ልዑላዊነትን በመጣስ በሶማሌ ክልል ሰራዊት እንዲገባ በማድረግ በህዝብ የተመረጠ አመራር በቁጥጥር ስር እንዲውልና በምትኩ ሌላ ሞግዚት አመራር እንዲተካ ተደረገ። በክልሉ የነበረው አመራር በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የሚያምን የአሃዳዊ ስርዓትን የሚቃወም ስለነበር የመጀመሪያው በትር በሶማሌ ክልል ላይ አረፈ።

ይህ ተግባር ደግሞ የክልሉ ሰላም እንዲደፈርስ አደረገው፡፡ በኦሮሞና በሶማሌ ብሄሮች መካከልም ግጭት በመፈጠሩ ቀላል የማይባል ህዝብ ለሞት ተዳረገ። በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብም ከቤት ንብረቱ ተፈናቀለ፡፡ እስካሁን ድረስ በሶማሌ ክልል ሰላም የለም፡፡ ህዝቡ ከነበረው የተረጋጋ የልማት ስራ ወጥቶ ውጥረትና ሁከት ውስጥ ገብቶ በኮማንድ ፖስት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ነገር ተፈፀመ፡፡ አመራሮች ተቀየሩ ክልሎች በኮማንድ ፖስት እንዲጠበቁ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ የተደረገው በመሰረታውነት የፌደራል ስርዓቱን በማፍረስ አሃዳዊ ስርዓት ለማንገስ እንደሆነ በርካቶች ይናገራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመሰቃቀለና እየተባባሰ ሄደ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና ደጋፊዎቻቸው በፌደራል መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ የትግራይ ተወላጆችን ማባረር ስራየ ብለው ተያያዙት፡፡ በአማራና በሌሎች ኣከባቢ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም ያለምንም ምክንያት ተባረሩ፡፡ ንብረታቸውም ተዘረፈ፡፡ በዚህ መልክ ከአንድ መቶ ሺህ ህዝብ ከነበረበት የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ትግራይ እንዲባረር ተደረገ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ የሚወስደው በፌዴራል መንግስት የሚተዳደር አውራ ጎዳና መንገድ እንዲዘጋ ተደረገ፡፡ ትግራይን በኢኮኖሚ ለማሽመድመድ ታስቦ የተፈፀመ ተግባር እንደሆነ በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡ የአብይ አህመድና የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያደርሱት ግፍና በደል በዚህ የሚቋጭ አልነበረም።

በትግራይ ተነፃፃሪ ሰላም በመኖሩ የኢንቬስትመንት ፍሰቱ በመጨመሩ ይህንን ለማደናቀፍ የተለያዩ ተገቢነት የሌላቸው እርምጃዎችንም ተወሰዱ። የቻይና መንግስት ሉኡካን ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በኢንቨስትመንት ለመፈራረም ከውጭ ጉዳይ ጋር ያላቸውን ሁሉ ተገቢ ተግባራት ከፈፀሙና መሟላት ያለባቸውን ነገር ሁሉ አሟልተው ወደ መቀሌ ለመጓዝ አውሮፕላን ከተሳፈሩ በኃላ እንዲወርዱ በማድረግ ወደ ትግራይ መሄድ እንደማይችሉ ተነግሯቸው ታገዱ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ የተለያዩ ኢንቨስትመንት ያላቸው የትግራይ ተወላጆችን በመሰብሰብ ወደ ትግራይ ድርሽ እንዳይሉ በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ማስጠንቀቅያ ተሰጣቸው ፡፡ የአብይ መንግስት የትግራይን ልማት ለማደናቀፍ በፌዴራል ይሰሩ የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች በሙሉ የገንዘብ እጥረት አለብኝ በሚል እንዲስተጓጎሉ አደረገ፡፡ ትግራይን በኢኮኖሚ ለማሽመድመድ በአብይ አህመድ የተሰራውና አሁንም እየተሰራ ያለው ሴራ የትየሌለ እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡

የአገሪቱ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ላልተወሰነ ግዜ በመዛወሩ የትግራይ ህዝብ ምርጫ አካሂዳለሁ በማለቱ ይህንን ለማደናቀፍ የተለያዩ ሴራዎች ተፈጸሙ። ሆኖም ግን ህዝቡ ጫናውን በመቋቋም ያሰበውን ከመፈጸም የሚከለክለው አካል እንደሌለ በተግባር አስመሰከረ።

በማሕበራዊ ረገድም ቢሆን በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ቀላል አይደለም። ከአንድ መቶ ሺህ በላይ የትግራይ ተወላጆች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለዓመታት ሰርተው ያካበቱት ንብረት እየተዘረፋ እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ የፌዴራል መንግስት ያደረገው አንድም ዓይነት ድጋፍ ወይም የወሰደው እርምጃ የለም።

በሌላ በኩልም በፌዴራል መንግስት በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችም ያለምንም ምክንያት ከስራ እንዲባረሩ በመድረጉ እስከነቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ እንዲወድቁ ተደረገ፡፡ የአብይ አህመድ መንግስት ከመጣ ጀምሮ በየትኛውም አካባቢ ይሁን በማንኛውም የስራ ዘርፍ በግልም ይሁን በመንግስት የተሰማሩ ተጋሩ ፈተናው ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡ ለሞት፣ ለስደትና ለስቃይ ተዳርገዋል። በዚህ ብቻ የተቋጨ አይደለም። የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለማጋጨት ያልተደረገ ጥረት የለም።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል "በተገባደደው 2012 ዓም የአማራና የትግራይ ህዝብ ለማጋጨት የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ። የመሬት አስመላሽ ነፃ ኣውጪ ኮሚቴዎችና ሌሎች የተፈለፈሉ በማሰማራት" ትህነግ የምትባል ፍጡር እስካለች ድረስ የአማራ ህይወት ከምስቅልቅል አይወጣም" እያሉ የህዝቡ ስቃይ ለማራዘም ቢሞክሩም የአማራ ህዝብ ማጭበርበሩ ይብቃቹ የራሳቹን ችግር ፈትሹ ከትግራይ ህዝብ ጋር አንጋጭም እረፋ እያለ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በመታገሉ ለአማራ ህዝብ ክብር እንዳለን ለመግለፅ እንወዳለን፤" ነበር ያሉት።

የትግራይ ህዝብ ይህን ሁሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ በደል ተቋቁሞ ግን በምንም መልክ ከያዘው መስመር ዘንበል ኣላለም፡፡ አሁንም ሰላሙን አስከብሮ፣ አንድነቱን ጠብቆ፣ የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማስፈን የሚያስችሉ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

ጳጉሜን 4 ቀን 2012/ የፈፀመው ታላቅ ታሪክ ምን ግዜም ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ያን ሁሉ ጫና በመቋቋም የራሱን አመራሮች በዴሞክራሲያዊ ኣግባብ መምረጥ ችሏል፡፡ ይህ በምስራቅ ኣፍሪካ ሆኖ የማይታሰብ ተግባር እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች መስክረዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ 1983 ዓም ከስር መሰረቱ ንዶ ቀብሮት የነበረ አሃዳዊ ስርዓት እንደገና አንሰራርቶ ጠቅላይ አገዛዝ አሰፍናለሁ ብሎ በተነሳበትና የውስጥና የውጭ ሃይሎች ተሰባስበው የፌዴራል ስርዓቱን በአሃዳዊ ስርዓት ለመተካት የሞት የሽረት ያህል ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ምክንያትም በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ሁከትና ብጥብጥ ነግሶ ባለበት ሁኔታ የትግራይ ህዝብ ይህንን ተቋቁሞ የራሱን እድል በራሱ መወሰን የቻለበት ታሪካዊ ምርጫ በማካሄድ የአሃዳውያንን ግብኣተ መሬት ዳግም መቅበሩን ብዙዎች ይስማማሉ።

ይህንን ሁሉ ተግባር የተገነዘቡት የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን እንደገለጹት በትግራይ ህዝብ ላይ ጫና ለማሳደር ከውጭ ሃይሎችም እየተባበራቹ ሁሉም ኣይነት ግፍ እየፈፀማቹሁ የምትገኙ የድሮና ኣዳዲስ ኣሃዳውያንና ሌሎች ተስፈኞች እና ተላላኪዎችና ከተላላኪዎች በታች የሆናቹ ሁሉ ማሳወቅ የምንፈልገው የትግራይ ህዝብ የማያከብር ጨው ለራሱ ብሎ ይጣፍጥ ነው።"

የትግራይ ህዝብ ለዘመናት የታገለለት የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና የራስን እድል በራስ የመወሰን የህዝብ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት ዳግም በክልሉ እንዲረጋገጥ አድርጓል፡፡ ይህንን ያደረገው ሁኔታዎች ተመቻችተውለት አይደለም።

"2012ዓም ከባድ ፈተናዎችና ቀውሶች የገጠሙበት፣ በህዝባችን ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች የደረሱበት፣ በኮቪድ -19 ምክንያት ምርጫ የተራዘመበት ዓመት ነው። የትግራይ ህዝብ ግን የራስን እድል በራስ የመወሰን ህገመንግታዊ መብቱን ተጠቅሞ መሪዎች ስልጣን ላይ የሚቀመጡት በራሴ ውሳኔ እንጂ በኮሮና ሰበብ ምርጫ አልሰርዝም በማለቱ ኮቪድ-19 እየተከላከለ ምርጫውን ኣካሂዷል" ብለዋል።

ምርጫው ማስቆም ያልቻሉ ትምክህተኞች ምርጫው ህጋዊ አይደለም እያሉ እያምታቱ ይገኛሉ። ይህ መሰረት የለሽ ነው። በትግራይ ህዝብ የተካሄደው ምርጫ በህዝቡ ውሳኔ አግኝቷል።

ለዚህም ነው ዶክተር ደብረጽዮን " የትግራይ ህዝብ ምርጫ የሚወስነው የትግራይ ክልል መንግስት ህወሓት ወይም ሌሎች ፓርቲዎች ኣይደሉም። የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት የትግራይ ህዝብ ነው። ዳኛው ይግባኝ ሰሚው የመጨረሻ ፍርድ ሰጪው የትግራይ ህዝብ ብቻ ነው፤" ሲሉ ያሰመሩበት። ሆኖም ግን አሁንም የአብይ አህመድ መንግስት ከስህተት ዝላይ ስህተት እያነባበረ ለራሱ ሊወጣው ወደማይችል አረንቋ ኦየዘቀጠ ይገኛል። ህጋዊነቱ በመጠናቀቁ ግን ከዚህ በኋላ አይደለም በትግራይ በሌላው አካባቢም የሚያስፈጽመው ነገር አይኖሮም። 101 ሴራዎች በኋላ ይሄው ለፍርድ የሚቀርብበት ግዜ ደርሷል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። የሽግግር መንግስት እስኪቋቋም ድረስ አገሪቱን ተረክቦ ማስተዳደር ይኖርበታል። ይህ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጥያቄ ነው። 101 ሴራዎች መቋጫም ይህ ይሆናል።

Back to Front Page