Back to Front Page

የእስረኞቹ መፈታት ድራማ

የእስረኞቹ መፈታት ድራማ

አጭር አስተያየት

 

ፋቶ ምዕራፍ ጻድቃናት

20/06/2012 /

 

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መንግስት በቅርቡ 63 እስረኞችን መፍታቱ ይታወቃል። በዚህም አጋጣሚ በአብዛኛው ያለሃጢያታቸው ታስረው የተሰቃዩትንና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ። ይህንን እውን እንዲሆን ለተጋችሁ ሁሉ የጥረታችሁ ብልጭታ በማየታችሁ ደስ ይበላችሁ። ለበለጠ ጥረት እንደሚያነሳሳችሁም እርግጥ ነው። ዜጎቹ ለምን ታሰሩ ብሎ መጠየቅ የዋህነት ከመሆኑ ባሻገር ያንባቢያን ጊዜ ማባከን ነው። ዋናው ጉዳይ ለምን ተፈቱ በማንስ ተፈቱ የሚለውን መመልከቱ ግን አስፈላጊም ጠቃሚም ነው።

ዜናው የተነገረን በህግ ስልጣን ከተሰጠው የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሳይሆን ሰበር ዜናው የመጣው እንደተለመደው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አከባቢ ነበር። ሁሉም ነገር ከኔ በኔ እኔ ብቻ የሚሉትና የሚወዱት ጠቅላያችን በዜና መልክ እስረኞች ጥናት ተደርጎ እንዲፈቱ አመራር ሰጥቷል ተብሎ አስቀድመው አዘግቧል። ዜናው እንደወጣ አዘጋገቡና ምንጩ ወይ ጥያቄው ያቀረቡት የትግራይና የአማራ ክልሎች ብልፅግና ፓርቲ ተወካዮች መሆናቸው ሲነገረን ጉዳዩ ዶሮ ጭራ የምታገኘው ተራ ድራማ መሆኑ ግልፅ ነበር። የዘመናችን ደፋርና አስተዋይ የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኛው ያየሰው ሽመልስ ዘገባ እስረኞቹ የተፈቱት በአሜሪካ መንግስት እንደሆነ አሳማኝ በሆነ ትንተና አቅርቦታል። ያየሰው በመቀጠልም አሜሪካም ይህን ያረገችው የተበደሉት ፍትህ እንዲያገኙ ከሚል ቀና ተነሳሽነት ሳይሆን እንዲህ ያለነገር ከአሜሪካ እንደማይጠበቅ ከታሪክ እንማራለን አብይን ስልጣን ላይ ለማቆየት ያግዛል በሚል ከትግራይ እየተነሳና እየጋለ ያለውን ተቃውሞ ለማብረድ ሕገውጡ የብልፅግና ፓርቲ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማገዝ እንደሆነ አብራርቷል። ሆኖም ግን ሴራውና ተንኮሉ ደካማ ቢሆንም መነሻውና ስፋቱ ግን ከዚህ በላይ ነው።

የትግራይ ተወላጆችን በተመለከተ ለምን በዶ/ር አብርሃ በላይ ቀረበ ያውም ይህንን አጭር ጉዳይ ለማቅረብ በፅሁፍ መደረጉ ምንን ያሳያል?! የፃፈውስ ማነው የአማራ ተወላጅ ለሆኑትስ ጥብቅናው ለምን አማራ ሳይወክለው ራሱን የአማራ ተወካይ አድርጎ በሾመው ንጉሱ ጥላሁን በኩል እንዲቀርብ የተደረገው ለምንድነው ክሱስ ለምን በዚህ ጊዜ ሆነ ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች መፈተሽ ያስፈልጋል።

የትግራይ ተበዳዮችን በተመለከተ በዶ/ር አብርሃ የቀረበበት ምክንያት አንድም ሰውየው ለትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መሆናቸውን ለማሳመን፤ ሲቀጥልም ፓርቲው የትግራይ ህዝብ ጥያቄ መመለስ መጀመሩን ለማሳየት የተደረገ ከንቱ ጥረት ነው። ከንቱ የሆነበት ምክንያት ብዙ ነው። በምርጫ የትግራይ ህዝብ ውክልና ያገኙትንና ሌሎች በርካታ ተጋሩ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ተጠራርገው በተባረሩበት ማግስት በሺዎች ከሚቆጠሩት የፖለቲካ እስረኞች ውስጥ ጥቂት ሰዎችን በመፍታት ብቻ የትግራይን ህዝብ ድጋፍ መሻት ከንቱ ጥረት ነው። በሌላም በኩል የትግራይ ህዝብ በብልጥግና ፓርቲ ተወካዮች እንዳሉት በምስል ጭምር ለማሳየት የተደረገ አስመሳይ ድራማ ከመሆን የማያልፍ ግብዝ ድርጊት ነው። ስለሆነም፥

የተዘጋን የፌዴራል መንገድ ሳይከፈት፣

ትግራይን ለማንበርከክ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሚደረገውን ሴራ ሳይቆም፣

ትግራይን በኢኮኖሚ ለማድቀቅ እየተወሰደ ያለውን ርምጃ ሳይቆም፣ የትግራይ ተወላጅ ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት ለይቶ ማጥቃት ስራ እንዳይሰሩ በመንግስት ጨረታዎች እንዳይሳተፉ መከልከል የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙ መከልከል የውጭና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ትግራይ እንዳይሄዱ መከልከል ወዘተ ሳይቆም፣

ትግራይን የማግለል ዘመቻ ሳይቆም፣

ጠቅላዩ ህዝቡን በግላጭ የተሳደቡትንና ያዋረዱትን በይፋ ይቅርታ ሳይጠይቁ፣

ሌሎች በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን ሳይፈቱ እንዲሁም

የትግራይን የግዛት አንድነት ለመሸርሸር የሚደረገውን ሙከራ ሳይኮንኑ ሳያስቆሙ

አሁን በተፈቱት ጥቂት ሰዎች ብቻ የትግራይን ህዝብ ማሳመን አይቻለም። የአማራ ክልል ተወላጆች በንጉሱ ጥላሁን መቅረቡ ከላይ ከተገለፀው ውጭ አይሆንም። ምናልባትም እየተሸረሸረ የሄደውን የንጉሱ ጥላሁን ተቀባይነት ለማግኘት ነው። ጥያቄው በፅሁፍ የተደረገበት ምክንያትም ደራሲው ሌላ ሰው መሆኑን ያሳብቃል።

ለምን አሁን ተፈቱ የሚለውን ስንመለከት ደግሞ ከሚከተሉት ምክንያቶች ባንዱ ሊሆን ይችላል።

ተከሳሾቹ በትክክል ለማስቀጣት የሚያስችል በቂና ያማያወላዳ ማስረጃ እጥረት

ከፈተኛ አካላዊ በደል የደረሰባቸውና አስሮ ማቆየት የመንግስትን ተአማኒነት የሚያጓድል በመሆኑ

አብዛኛዎቹ ቢፈረድባቸው ከታሰሩት ጊዜ በላይ የማያሳስራቸው መሆኑ ሲገመት

በጣም የተጠናከረ ባይሆንም በተለይ በትግራይ ህዝብ የተደረገው ተፅእኖ ቀስ በቀስ እየተጠናከረ በመምጣቱ

የአሜሪካ መንግስት ተፅእኖ እያየለ መምጣቱ ወዘተ ወይም በተመሳሳይ ምክንያት ሊሆን ይችላል

Videos From Around The World

ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ የምናገኘው ተገማች ሃሳብ ግን ዶ/ር አብርሃ ቃሊቲና ቂሊንጦ ሄዶ እስረኞቹን ከማነጋገሩ ጋር ይግናኛል። ከዚህ የምንገነዘበው ግልፅ ነገር የተፈቱትን ሰዎች በውለታ፣ በማስፈራራት፣ ጫና በመፍጠር ወይም ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ወዘተ ከተፈቱ በኋላ የብልጥግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሆኑ ወይም እንዲቀበሉ ለማስገደድ ነው። የፓርቲ አባልነት እንዴት በማስገደድ ይሆናል ሊባል ይችል ይሆናል። መልሱ ቀላል ነው። ብልጥግና ፓርቲ አንድም በመርህና የፖለቲካ እምነት የተመሰረተ ሳይሆን በጥቅም፣ በስልጣን ፍለጋ የግልም የቡድንምእና በህወሓት ላይ ባላቸው ጥላቻ ወይም ፍርሃት ላይ ነው። ስለሆነም ፓርቲው የሚፈልገው ለጊዜው በዋናነት ደግሞ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አባላት አሉኝ ለማለት ብሎም በምርጫ ጫና ለመፍጠር እንዲሁም እንደብረት የጠነከረው የትግራይ ህዝብ አንድነት ለመበጥበጥ ነው። ነገር ግን ከሙከራ የማያልፍ ከንቱ ጥረት ነው።

ስለሆነም የተፈቱትን ሰዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ከማይገባችሁ ቦታ ወጣችሁ ማለቱ ተገቢ እንደሆነ ሁሉ የተፈቱበት ዋነኛ ምክንያት ግን መንግስት እንዳለው በችሮታ ሳይሆን ተገዶ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ያለሃጢያታቸው አስሮ በሆደ ሰፊነት ለአንድነት ውዘተ ተፈቱ የሚለው ምክንያት ዶሮን ሲያታልሉዋት በመጫኛ ጣሉዋት ከመሆን አያልፍም። የሰኔ 16 እና 15 አንዱ በጠ/ሚኒስትሩ ተደረገ የተባለው አጓጉል ድራማ ሌላኛው ደግሞ ምርጥ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በጠራራ ፀሐይ የተገደሉበት ፍፁም የተለያዩ ጉዳዮች ናቸውተጠርጣሪዎችም በተመለከተ የመጀመሪያው ምንም ጭብጥ ያልተገኘበት ሲሆን ሁለተኛው ጉዳይ ግን ቀጥተኛ ተዋናዮችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተፈተው ሹመት ከተሰጣቸው በኋላ በአብዛኛው የአብን አመራሮችና ጋዜጠኞችን አስሮ ማቆየቱ ለመንግስት ኪሳራ እንጂ ጥቅም እንደሌለው በማወቃቸው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በአማራ ክልል እየተፈጠረ ያለውን ፀረ ብልጥግና ፓርቲ ለማለዘብ እንደሆነ ለመገመት አያስቸግርም።

በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እስከሚፈቱ ድረስ ትግሉ መቀጠል ይኖርበታል።

Back to Front Page