Back to Front Page

ፀጉረ ለውጥ የሚለው ፍረጃ አደገኛ አጠቃቀም

ፀጉረ ለውጥ የሚለው ፍረጃ አደገኛ አጠቃቀም

ዮሃንስ አበራ (ዶር)

7-28-20

ማስታወሻ፡ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ በአይጋ ፎረም ፅሁፍ ካወጣሁ ሁለት አመት ሊሆነው ነው፡፡ ይህ ምክር አዘል ፅሁፍ የሚመለከታቸው ሰዎች ጆሮ የደረሰ አይመስልም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተለመደ የመጣው የቃላት ጭቃ መወራወር እንጂ መደማመጥ አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የኢህአዴግን ጉባኤ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ፀጉረ ለውጦችን ነቅታችሁ ጠብቁ ብለው ለሰፊው ህብረተሰብ የሰጡትን ምክርመነሻ አድርጌ የፃፍኩት ጠንካራ ማሳሰቢያ ነበር፡፡ሰከን ብሎ መስማት ለሚችል ሁሉ ይህንን ጉዳይ አጠንክሮ መድገሙ አስፈላጊ ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡

 

ሰሞኑን ከአማራ ክልል አመራር በኩል ከተሰማው ነገር ሁሉ አሳሳቢ የሆነው ፀጉረ ልውጥ የሆኑ ሰዎች ስታገኙ መታወቅያ ጠይቁ፤ ማን እንደሆነ ከየት እንደመጣ ወዴት እንደሚሄድ አጥብቃችሁ ጠይቁ የሚል መመሪያ በምስጢር ለሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ሳይሆን ባደባባይ ለ20 ሚልዮን የአማራ ህዝብ መነገሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ ህወሓት ወደ አማራ ክልል ታጣቂ እየላከች ነው አይደለም ወደሚለው ጉዳይ ልገባ አልፈልግም፤ የማውቀው ነገር ስለሌለ፡፡ አማራ ክልል ወደ ትግራይ ታጣቂ እየላከ ነወይ የሚለውም ቢሆን ማስረጃ ስለሌለኝ አላስተናግደውም፡፡ ፖለቲከኞች የራሳቸውን የውስጥ ችግር ወደ ሌላው ማላከኩ ከድንጋይ ዳቦ ዘመን ጀምሮ የተለመደ ስለሆነ ቁምነገር ነው ብየ ትኩረት አልሰጠውም፡፡ ሊገርመኝ የሚችለው ነገር ቢኖር ይህ ያረጀ ያፈጀና ድሮ የተነቃበት ዘዴ ልክ እንደ አዲስ ፈጠራ የሚጠቀሙበት ሰዎች መኖራቸው ብቻ ነው፡፡

Videos From Around The World

ማንም ሰው በፍትህ ሂደት ሳይረጋገጥ ወንጀለኛ አይባልም፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ይህ በኢትዮጵያ ቲዮሪ እንጂ ተግባር አይደለም፡፡ የአለመሰልጠናችን አንዱ መገለጫ ይህ ነው፡፡ መንገዱን ይዞ ወደ ጉዳዩ የሚሄደውን ሰው ለዚህ ስራ የተመደበ፤ ዩኒፎርም የለበሰና ህጋዊ መታወቂያ የያዘ የፖሊስ ባልደረባ ሳይሆን እንዲሁ አንዱ መሰል መንገደኛ አስቁሞ ማነህ፤ ወዴት ነህ፤ ከየት መጣህ ብሎ በጥያቄ ቢያጣድፈው ለዚህ የሚሰጠው የህግ ትርጉም ምንድነው? ጠያቂው ሲጠየቅስ የክልል መሪዎች የሰጡኝ መመሪያና መብት ነው ማለቱ ይቀራል? ለግለሰብ መብት ትኩረት ሰጥተው ለውጥ አመጣን የሚሉ የፖለቲካ መሪዎች የግለሰብ መብትንና እንደ ዜጋ በራስ መተማመንን የሚሽር መመሪያ በግዴለሽነት ማስተላለፍ መሰረታዊ የፍትህ መርህን ጥሶ ጊዜያዊ ተሰሚነትና ተወዳጅነት ለማትረፍ ካልሆነ በስተቀር ምንም ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ከሁሉም ቀድመው ተሽቀዳደድመው ህዝብ ከህዝበ የሚያጋጩ፤ ህዝብ ከህዝብ የሚያለያይ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ እያሉ ሲወነጅሉ ድምፃቸው ጎልቶ የሚሰማው የነሱ ነው፡፡

በጉዳዩ ያለኝን ሃሳብ መግለፅ ከመቀጠሌ በፊትመጀመሪያ ፀጉረ ልውጥ የሚለው የፍረጃ ቃል ትርጉም፤ በቅርቡ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ እንደገባና ማን እንዳስገባው እንመልከት፡፡ ፀጉረ ልውጥ የተለየ የፀጉር ቀለም ያለው ሰው ለማለት አይደለም፡፡ በከርዳዳ ባለፀጉሮች አገር ባለ ዞማው ፀጉረ ልውጥ ነው ማለት አይደለም፡፡ ጠጉረ ልውጥ ማለት የአካባቢው ነባር ኗሪ የማያውቀው፤ ለአካባቢው አዲስና ለመጀመሪያ ጊዜ ባካባቢው የታየ፤ለየት ያለ ሰው ነው፡፡ ፀጉረ ልውጥ በአጠቃቀም ላይ የእንግዳነት በጎ ያልሆነ ጎኑን የማንፀባረቅ አዝማሚያ ቢኖረውም ባይተዋር የሆነ፤ ድጋፍና መስተንግዶ የሚያስፈልገው የሰው አገር ሰው ለማለትም ይሆናል፡፡ በዚህም ሆነ በዛ ፀጉረ ልውጥ የአካባቢው ያልሆነ ባእድ ሰው ለማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ አካባቢ ምን ማለት ነው? ወደዚህ መንደር ከሌላ መንድር የመጣ ነው? ወደዚህ ወረዳ ከሌላ ወረዳ የመጣ ማለት ነው? ወደዚህ ክልል ከሌላ ክልል የመጣ ነው? ወደዚህ አገር ከሌላ አገር የመጣ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ስሜታዊ መልስ ይሰጣቸው ይሆናል የህግ አንቀፅ የሚመልሳቸው አይደሉም፡፡ ከሌላ አካባቢ የመጣ ሁሉ በወንጀል ተጠርጣሪ ነው የሚል ህግ ሊኖር አይችልም፡፡ ወደ አገራችን የገባ ቱሪሰት ሁሉ የወንጀል ተጠርጣሪ ለማድረግ እንደመሞከር ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ፖሊቲከኞች በፍትህ አካላት ተቀባይነት ሊያገኝ የማይችለውን ፍረጃ በህግ አንቀፆች ላይ ተመስርቶ የሚሰራው የፍትህና የህግ አስከባሪ ተቋምን በጎን አልፈው በጥላቻ ስሜት ለታወሩት ደጋፊዎቻቸውና ተከታዮቻቸው የመፍለጥ የመቁረጥ መብት የሚያቀዳጁት፡፡

ፀጉረ ልውጥ የሚለው ፍረጃ መቼ ጥቅም ላይ መዋል እንደጀመረ ባላውቅም በነጋሲዎች ዘመን ሲነገር እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ይህ በደርግና በኢህአዲግ ዘመናት ብዙም ያልተሰማው ሃረግ በድንገት ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ ከገባ ሁለት አመት ሆነው፡፡ ልማትና ጥፋት የተቀላቀለበት የኢህአዴግ የ27 አመት አስተዳደር በገዢው ግንባር የውስጥ ሴራና በውጭ ግርግር ማእበል ሲመታ ከመርከቡ ውሰጥ አንድ ዮናስ ወደ ባህሩ ተወረወረና ወጀቡ ፀጥ አለ፡፡ ይህ ከመፅሃፍ ቅዱሱ ታሪክ የሚለየው በዚህ የኢህአዴግ መርከብ ውስጥ ብዙ የቀሩ ዮናሶች መኖራቸው ነው፡፡ ሁሉም ዮናሶች ወደ ባህር ሳይወረወሩ ቢቀሩም ወደብ እስኪደርስ ድረስ ለጊዜውም ቢሆን ወጀቡ ፀጥ ያለው የተጣለለት ወገን ያጣ ዮናስ ላይ ሁሉም እንዲጮህበት በመደረጉ ማእበሉ የሚፈልገውን ያገኘ ስለመሰለው ነው፡፡ እዚህ ላይ ነበር ማእበሉን የሚያረጋጋ በአራዳ አባባል ቢዚ የሚያደርግ ዘዴ የተገኘው፡፡ ያኔ ነበር የቀን ጅብ ና ፀጉረ ልውጥ የተባሉት የጋሪ ፈረስ የአይን ከለላዎች የተሰሩት፡፡ የቀን ጅብ የሚለው አባባል በፊተኛው ፅሁፌ አስተያየት የሰጠሁበት ስለሆነ አልደግመውም፡፡ ከአይጋ ፎረም ድረገፅ ማከማቻ ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ ማለት የምፈልገው አንድ ቃል ግን በአርኣያ ስላሴ የተፈጠረውን ፍጡር የክርስትና ሃይማኖት ተከታይና መሪ ከሆኑ ሰዎች አፍ የቀን ጅብ የሚል ቃል መውጣቱ የአምላክ ስራን ማኮሰስ ነው፡፡ ባህርዩና ድርጊቱ ምን ይሁን ምን አምላክ ሰውን ሰው ጅብን ጅብ አድርጎ ነው የፈጠረው፡፡ ፖሊቲካና ሃይማኖትን እያጣቀሱ አንዱን በሌላው ማፍረስ ያስኮንናል፡፡

የቀን ጅብ የሚለው ፍረጃ ሞራልንና ሃይማኖትን ሲጋፋ ፀጉረ ልውጥ የሚለው ግን የሚጋፋው ህግን ነው፡፡ በወርዋሪዎቹ ዘንድ ህወሓት ብቸኛዋ ዮናስሆና ከተወረወረች በኋላ አሳ ነባሪው ውጦ ባህር ውስጥ ያስቀራታልና ሁሉም ሰላም ይሆናል የሚል ስሜት አልነበረም፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ታሪክ ዮናስ ቢያጠፋም ለአምላክ ከነበረው ቅርበት የተነሳ አሳ ነባሪው ወደ መሬት መልሶ እንዲተፋው አደረገ፤ ንስሃ ገብቶም አምላክን ማገልገል ቀጠለ፤ የአምላክ ልሳንም ሆነ፤ ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑ ትንቢቶችም ተናገረ፡፡ ህወሓትን ያሰወገዱ ሰዎች ህወሃትን የሚንቁ ሰዎች አልነበሩም፡፡ እንዲያውም ህወሓት ውልቅ ብላ ስትሄድ የበለጠ ፍርሃት ሳያሳድርባቸው የቀረ አይመስልም፡፡ ነገሩስ ለአዳምም ገርሞታል፡፡ ከለጋ ወጣትነት ጀምሮ ሁለት ፀጉር እስኪያበቅሉ ድረስ ከብረት ጋር ተዋህደው የኖሩት የህወሓት አመራሮች ኮሽታ ሳያሰሙ ከአራት ኪሎ መቀሌ መታየታቸው በሆዱ የሚያደንቅም፤ የሚገረምም፤ ግራ የሚጋባም፤ የሚፈራም በጣም በርካታ ነው፡፡

ህወሓትን በእንዲህ ሁኔታ ያሰናበተው ሁሉ፤ ከተሰናበተችም በኋላ ሲቀርብባት የነበረው ውርጅብኝና ውንጀላ ድንገት አራት ኪሎ መልሳ ከገባች ሰፊ የብቀላ ስራ ትሰራለች የሚል ስጋት ሊኖር ይችላል ብየ አስባለሁ፡፡ እኔ ነብይ ስላልሆነኩኝ ህወሓት አራት ኪሎ ትገባለች የጎዷትንም ትበቀላለችየሚል ትንቢት መናገር አልችልም፡፡ እንደ ተራ ሰው የምገምተው ግን በሃላፊነት ስሜት እንደለቀቀች ሁሉ በሃላፊነት ስሜት ተመልሳ ትሰራለች የሚል ነው፡፡ ህወሓትን የሚጠሉ ሰዎች ብዙ ምክንያት ያላቸው ናቸው፡፡ የኛ እጅ የጠራ ነው ብለው የሚያስቡት አንዳንዶቹ ህወሓት ሙሰኛ ናት እያሉ አይኗን ማየት ይጠላሉ፡፡ ሌሎቹ ስልጣን የኛ ብቻ ነው የሚሉና ህወሓትን እንደ ሃሳዌ መሲህ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ትግሬ የሚባል ነገር የሚያንገሸግሻቸው ሰዎች ደግሞ ወርቅ ቢያለብሳቸውም ከሚኒሊክ ቤተመንግስት ውስጥ ትግሬ ገብቶ ከሚያዩ ሞትን የሚመርጡ አሉ፡፡ አንዱ የአይጋ ፎረም ደምበኛ በአንድ ወቅት ህወሓትም አራት ኪሎ ትመለስና ሁሉም አብረው ተባብረው አገሪቱን በሰላም ይምሩ ብየ የሰጠሁትን አስተያየት ሲቃወሙ እንዲህ አሉ፡- ህወሓት አራት ኪሎ ከምትመለስ ኢትዮጵያ ብትጠፋ ይሻላል፡፡ የሚገርመው እኔ ራሴን አጠፋለሁ እኮ አላሉም፤ ኢትዮጵያን ነው እንደትጠፋ የተመኙላት፡፡ ስለዚህ የብዙዎች አስተሳሰብ ህወሓት ወደ አገር አስተዳደር አትመለስም ነው፡፡ ይህን ማረጋገረጥ የሚችሉት ግን የማይቻለውን ህወሓትን የማጥፋት ስራ በመከወን ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲፈራትና እንዲጠላት የማድረግ ዘመቻ ነው፡፡ ይህ ህወሓትን ነጥሎ በማጥላላት ሊሳካ እንደማይቻል ይታወቃል፡፡ ውስጥ ያለው ነገር ከበድ ያለ ነው፡፡ ህወሓት አራት ኪሎ እንዳትመለስ ሳይሆን ውስጠ ወይራው ትግሬ የተባለ ወደ አራት ኪሎ እንዳይገባ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ትግሬ የተባለ ሁሉ ከትግራይ ውጪ ባለው ኢትዮጵያ የሚፈራና የሚጠረጠር እንዲሆን በማድረግ ነው፡፡ የሚፈራና የሚጠረጠር ከሆነ ደግሞ እንዳቅሙ ሰርቶ ንብረት አበጅቶ አገሬ እንጀራየ ብሎ ሊኖር አይችልም፡፡ እንደ ባይተዋር እየታየ፤ ለሰፈር ሽምግልና እንኳ ካልበቃ እንደየ አቅሙ በሃገር ፖለቲካስ በምን ተአምር በህዝብ ተመርጦ ይሳተፋል?ፀጉረ ልውጥ የሚለው አሸማቃቂ ፍረጃ በመደጋገም የትግራይ ተወላጆች ከትግራይ ውጪ ባሉት የኢትዮጵያ ክልሎች ተረጋግተው እንዳይኖሩ የሚያደርግ የተንኮል ስራ ነው፡፡ ፀጉረ ልውጥ የሚለው ተንኮል ለመስራት የተዘጋጀ ወንጀለኛ ለማለት ተፈልጎ ከሆነ ይህ አላማ ያለው ሰው ከኢትዮጵያ አራት መአዝናት ሊመጣ ይችላል፡፡ ማን ትግሬ ብቻ ወንጀለኛና ተጠርጣሪ አደረገው?ሶስት አስርት አመታት አገሪቱ አንፃራዊ የወንጀል መቀነስ ያሳየችውስ ወንጀለኞቹ በሙሉ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ተጠቃለው ስለገቡ ነው እንዴ?ፀጉረ ልውጥ የሚለው ፍረጃ ለህዝብ የቀረበበት አጋጣሚ ሆን ተብሎ ከህወሓትና ህወሓትን ሸሽጓል ከተባለው የትግራይ ህዝብ ጋር ተገናኝቶ ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ፀጉረ ልውጥ ማለት ማነው ተብሎ ቢጠየቅ መቶ በመቶ ትግሬ ነው ብሎ እንደሚመልስ ጥርጥር የለውም፡

እዚህ ላይ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር አለ፡፡ የትግራይ ህዝብ ፅኑ ኢትዮጵያዊ ነው፤ እናት አገሩን ጥሎ አይገነጠልም፤ ይህ ቅስቀሳ የህወሓት ቅስቀሳ ነውእየተባለ ይነገራል፡፡ እኛም ይህን እያልን ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ አንለያይም፡፡ የትግራይ ህዝብ ዜግነት ሳይሆን የኢትዮጵያ ወላጅ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ይዘን በርካታ የትግራይ ልሂቃንና ተራ ሰዎች ለትግራይ ህዝብ በርዝ ራይት እየታገልን ነው፡፡ ትግላችን ግን ዉሃ ላይ እንደሚንሳፈፍ መሰረት የሌለው ቤት ነው፡፡ አንድ እጃቸው የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው እያሉ የሚፅፉት በሌላው እጃቸው ደግሞ የትግራይ ተወላጅ ይቺን አገር ማስተዳደር የለበትም፤ ሞተን እንገኛለን ብለው ይፅፋሉ፡፡ የማንኛውም አገር ህገ መንግስት ዜጋ የሆነ ሁሉ የመመረጥና አገርን የማስተዳደር መብት አለው ይላል፡፡ ይህ እንዳያማህ ጥራው፤ እንዳይበላ ግፋው የሆነ ነገር ነው፡፡ በየደረሰበት የኢትዮጵያ ክልል፤ ገጠር ሆነ ከተማ ፀጉረ ልውጥ ከተባለ ፤ ትግሬ በመሆኑ ብቻ የህወሓት የጥፋት መልእክተኛ ከተባለ ኢትዮጵያዊ መሆኑ በምን መንገድ እናሳምነው? ትግራይ ትገንጠል የሚሉት ወጣቶች ላይስ ምን አይነት የፖለቲካ ሆነ የሞራል ልእልና ሊኖረን ይችላል፡፡ ከትግራይ ህዝብና ከፖለቲካኞቹ ይልቅ ለትግራይ መገንጠል ምክንያት የሚሆኑት ግፊቶች እየተከሰቱ ያሉት ከመሃል አገር ነው፡፡ ህዝቡ የግድ ዘመድ የሆነ ያህል ሆኖ እየተሰማው ነው፡፡ እንደ እድሜ ጠገብነታችን ተስፋ ቆርጠው እንገንጠል የሚሉትን የትግራይ ወጣቶች ማረጋጋት የምንችለው በዛኛው ጎራ እሳት ሳይሆን ዉሃ ካየን ነው፡፡ ኤሪትርያውያን አቦና የሚሏቸው ወልደአብ ወልደማሪያም መጀመሪያ ላይ የኤሪትርያን መገንጠል አይደግፉም ነበር፡፡ እስቲ ነገሩን ቀረብ ብየ ልፈትሸው ይሉና አዲስ አበባ ተቀምጠው ሁሉን ነገር ሲያዳምጡ እንደከረሙ ይነገራል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔያቸው የሆነው ግን የኤሪትርያ መገንጠል አስፈላጊነት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ነገር በጣም አሳዛኝ፤ ልብ የሚሰብርና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ የትግራይ ተወላጅ የሆነ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ነበር፡፡ አገሪቱን ከነበረችበት አዘቅት አንስቶ የት እንዳደረሳት አምኖ መቀበል የጨዋ ህዝብ ባህል ነው፡፡ የአባይ ግድብን በድፍረት በማስጀመር ቁርጠኛ ኢትዮጵያዊነቱን ያስመሰከረ ታላቅ ሃውልት የሚገባው ሰው ነው፡፡ ያስጀመረው ግድብ ሲጠናቀቅ የሱን ስም የሰይጣን ስም ይመስል ጨርሶ አለማንሳትና አለማመስገን የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድነው? እንዲህ እየተሆነ ነወይ አብሮ የሚኖረው? የትግራይ ህዝብ መጥፎ ሲሰራ እየተወቀሰ፤ ጥሩ ሲሰራ እየተሞገሰ ካልሆነ ዜግነቱስ፤ የኢትዮጵያ መፍለቂያ ምንጭነቱስ ምን ትርጉም ይኖረዋል፡፡ የትግራይን ህዝብ ማዋረድና ማቃለል መወንጀል የሚያስቀጣ አይደለም፡፡ ህወሓት አዲስ አበባ እንደገባች ከጥቂት አመታት በኋላ አሜሪካ የሚኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር በኢትዮጵያ ሪቪው መፅሄት ላይ የኢትዮጵያን ካርታ ስለው፤ ትግራይ ላይ ክብ ሰርተው፤ ትግራይ እንድትገነጠል ጥያቄ እናቅርብ ብለው ቅስቀሳ አደረጉ፡፡ ማንም ሊያርማቸው የሞከረ የለም፤ ይህ ግን ትሪዝን (የሃገር ክህደት ወንጀል) ነው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ከመጡ በአገር ክህደት ወንጀል እከሶታለሁ ብየ መልስ መስጠቴን አስታውሳለሁ፡፡ሰውየው ብቻቸውን እንዳልሆኑ ግን በሚገባ እረዳለሁ፡፡ እነዚህ ግዴለሽና አደፍራሽ ልኂቃን የኢትዮጵያ ግዛት የሆነ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሲኖረው ብቻ እንዳይገነጠል የሚለመንና የሚቆላመጥ ጥቅም የለውም ሲባል ደግሞ እንዲገነጠል የሚገፋ ከሆነ ኢትዮጵያዊነት ከቢዝነስ ቁርኝት የተለየ አይሆንም፡፡ ኤሪትርያ እንዳትገነጠል ለወደብ ብቻ ሲል 30 አመት የተዋጋ ሁሉ ትግራይ ሂጅልኝ እያለ የሚገፋ ከሆነ የሞራል ዝቅጠት ነው፡፡ ባጭሩ ወደ ርእሱ ልመለስና አማራ ክልል ውስጥ ከዚህ የፀጉረ ልውጥ ዜና ጋር ተቀላለቅሎ በሺ የሚቆጠሩ የፀጥታ ችግር ፈጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተዘግቧል፡፡ ከትግራይ መጡ የተባሉት ታጣቂዎችና አማራ ክልል ውስጥ የበቀሉት ችግር ፈጣሪዎች ልዩነታቸው ብሄራቸው ብቻ ነው፡፡ የፀጥታ ችግር ፈጣሪዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ አንዱ በቁልምጫ ሌላውን በግልምጫ ማስተናገድ ክልልን ከሚመሩ ታላላቅ ሰዎች አይጠበቅም፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በግል ነፃ አስተሳሰብ የሚመራ የማንኛውም ፓርቲ አባል ሆነ ደጋፊ ያልሆነ ነው፡፡

 


Back to Front Page