Back to Front Page

ውጭ ከሚኖሩ የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት የኢትዮጰያን ብሎም የሲዳማን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ውጭ ከሚኖሩ የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት የኢትዮጰያን ብሎም የሲዳማን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ኖቬምበር ፲ ቀን ፳፳

 

በጦርነት እና ድርቅ ክስተቶች በሚታወቀው  የምስራቅ አፍሪካ  ቀጠና አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ይስተዋልባት የነበረች ሀገራችን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መግባትዋ ለዜጎችዋም ሆነ ለቀጣናው ህዝብ እንዲሁም  ውጭ ለምንገኝ ማህበረሰብ አስደንጋጭ ክስተት ሆኗል። በአፊሪካ በሚከሰቱ ግጭቶች በሰላም አስከባሪነት ፣አደራዳሪነት እና አስታራቂነት ተመራጭ ሆና የቆይችዋ አገራችን ከቅርብ አመታት ወዲህ የውስጥ ችግሯን እራሷ መፍታት ተስኗት የአስታራቂ ያለህ እያለች እየተጣራች የማየትን የመሰለ የሃገር ውርደት የለም ። ወደዚህ አገራዊ ውርደት ዳግም  ሃገሪቱን ያስገቧት ስግብግብ የስልጣን ጥመኞች እና ስለቀጣዩ ትውልድ ግድ የሌላቸው ቡድንተኞች መሆናቸው አሁን ላይ ግልጽ ነው። ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ገደማ ሃገሪቱን እንዳሻው ሲመራና ሲበዘብዝ የከረመ የኢህዴግ ቡድን አመራሮች ከቅርብ አመታት ወዲህ በውስጡ በተፈጠረ ጸብ እና የጥቅም ግጭት ጎራ በመለያየት ሲሰዳደቡ፣ ሲወነጃጀሉ እና የየራሳቸውን ቡድን ሲያጠናክሩ መክረማቸው ይታወቃል። ይህ ቡድን በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚገኝን ህዝብ ሲጎዳ፣ሰብሃዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጽም የቆየ እና በዚህም ከህዝብ ጋር ሲፋለም እየተሸነፈ የመጣ ሃይል ነው። ይሁንና በተለይም ከፈረንጆቹ ፳፩፰ ዓም ወዲህ  ራሱን እንደሚያርም ለህዝቡ ቃል በመግባቱ ህዝቡ ውስጥ ተስፋን በመጫሩ እድል ተሰጥቶት  ነበር። ሆኖም ከመሰረቱ የተበላሸ እና የበሰበሰ በመሆኑ ታጥቦ ጭቃነቱን ድጋሚ አሳይቷል።  በዚህም ህዝቡ ወደ ዳግም ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲገባ አድርጎል ።ይህ ያስደነበረው የኢህአዴግ ቡድን ምግባሩን ሳይሆን ስሙን በመቀየር የአገሪቱን ስልጣን ያለምርጫ ይዞ እንደሚኝ ግልጽ ነው ፣ ግማሹ ክፋይ ደግሞ በሃሳብ ልዩነት ግን ስልጣኑን በክልል ደረጃ እንደተቆናጠጠ ሁለቱም በየፊናቸው የወትሮ ግፋቸውን ላለፉት ሁለት አመታትም አጠናክረው ቀጥለዋል ።  የህዝቡን ንቃተ ህሊና በሚንቅ መንገድ ግን የመሃሉንም ስልጣን የተቆናጠጠው ክፋይም ሆነ ክልላዊ ሃይል ይዣለው የሚለው ሃይል ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አዳዲስ የፓለቲካ ሃይላት አድርገው ራሳቸውን ሲያቀርቡ ሰነባብተዋል ። ህዝብን ሲዋሹ አይፈሩም : አያፍሩምም ። ዛሬ ላይም ይህንን ውሸታቸውን ቀጥለዋል ። ላለፉት ስምንት ቀናት አገራችን ግልጽ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መሆኗ በአለመ አቀፍ ማህበረሰቡም ጭምር እየታወቀ ክስተቱ ወንጀለኛን ለመያዝ የሚደረግ ኦፕሬሽን እንደሆነ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጭምር ሲነገር ተደምጧል። እንደነዚህ አይነት አሳፋሪ ውሸቶችን እየዋሹ አገር መምራት ለእሳቸውም ስብእናና ሞራል ጠቃሚ ነው ብለን አናምንም ። ለእርስ በእርስ ጦረነት ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶችን እኛም እንደ ህዝብ አካል በቅርበት ስንከታተል የነበርን ሲሆን ፣የአገሪቱን የጦር ሃይል ወደ አንድ አከባቢ የማሰባሰቡ አዝማሚያም ከጅምሩ ይሄንኑ አመላክቷል።

እኛ የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት በትግራይ እና በፌዴራል እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ተደምሮ የሚደረገው ጦርነት የህዝብ እና የሀገር ደህንነት እና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ጦርነት ነው ብለን አናምንም ። ይልቁኑ ጦርነቱ ንጹሃንን ለጦርነት በመማገድ ፣ህዝብን ከህዝብ በማለያየት ፣ታሪካዊ የዳግም በዳይ እና ተበዳይ ቂም ለትውልድ የሚያስተላልፍ ይሆናል ። በጦረነቱ  የፓለቲካ የሃይል ሚዛን ለማስጠበቅ የሚራኮቱ የትላንት ወዳጆች የዛሬ ጸበኞች ግን አላማቸው ከህዝባዊነት የራቁ  ቡድኖች  የሚያደርጉት እንደሆነ እናምናለን ። ይህ ጦርነት ለተወሰነ ግዜ መግዣ ይሆናቸው ይሆናል ። ከዚያ ውጭ የኢህአዴግ አመራር እና አካል ሆኖ የቆየ ሁሉ የሚጠየቅበትን ወንጀል ሰብስቦ ወደ አንድ ስፍራ  ደፍድፎ ከደሙ ንጹህ ነኝ ብሎ ህዝብን በአደባባይ የሚዋሸን አካል ህዝቡ እስከ ወዲያኛው እንደማይቀበል ሁሉም ሊያውቅ ይገባል ። ይሄንን እና ያንን ወንጀል ሲፈጽምብህ የከረመው ይህ አካል ስለሆነ ልደብድብልህ ለሚል ሁሉ የሚያጨበጭብ ስነ ልቦና  እኛም የለንም ህዝባችም የለውም ። አገራችን  በአሁኑ ወቅት  ፍትሃዊ  የአስተዳደር  ስርአት አላት ብለንም አናምንም። ሁሉንም ወንጀለኛ ሊያስጠይቅ የሚችል ፍትሃዊ ስርአት ለመመስረት የሚያስችል  ሁኔታ እንዲመጣ  ሁሉን አቃፊ የሆነ አገራዊ ውይይት ለሁሉም ይበጃል ብለን እናምናለን። በአገራችን ውስጥ ያሉ ውስብስብ የፓለቲካ ችግሮችን በጦርነት፣ በእስራት ፣ግድያ እና መወነጃጀል ለመፍታት መቻኮል አገሪቱን ወደ ከፋ መቆራቆዝ ብቻ የሚያስገባ ይሆናል ። ስለሆነም ሁሉም የፓለቲካ ሃይሎች፣የማህበረሰብ እና ሃይማኖት መሪዎች በአገሪቱ እርቀሰላም እንዲወርድና ልዩነቶች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።

 

የሲዳማ ክልል በሚካሄደው ጦርነት እና መካሰሶች የገለልተኝነት ሚና መጫዎት እንዲችል ጥሪ እናቀረባለን ። አዲስ ክልል እንደመሆኑም መጠን ከዚህ ውጭ ግዴታ እንደማይኖርበት ለሚመለከተው ምላሽ ከመስጠት ውጭ በጦርነቱ ተሳታፊ በመሆኑ ህዝባዊ ቂም ውስጥ ህዝባችንን እንዳይከት ለማሳሰብ እንወዳለን

 

በአሁን ጊዜ የተከሰተውን አላስፈላጊ የእርስ በእርስ ጦርነት ተከትሎ በክልሎች አከባቢ የሚስተዋል ያልበሰለ አካሄድ መስተካከል ይኖርበታል ። የሲዳማ ህዝብ ላለፉት ሃያ ስምንት አመታት ሲጨቁነው የነበረውን አስትዳደራዊ ስርዓት እና በስርዓቱ ውስጥ ተጠልለው ንጹሃንን ሲያንገላቱ ፣ሲያስሩ፣ሲገድሉ እና ህዝባዊ መብቶችን ከአለቆቻቸው ጋር ሆነው ሲነፍጉ የነበሩትን በስም፣ በትውልድ ቄያቸው ጭምር ያውቃቸዋል።

ዛሬ ላይ ደርሶ የሃይል ሚዛኑን አቅጣጫ እያዩ የፓለቲካ ካርድ ለመጫወት የሚሞክሩ ተላላኪ ካድሬዎች ንጹሃን ዜጎችን የህዋሃት ተላላኪ የሚል ቅጥያ እየለጠፉ ወደ እስር ቤት ማጎር ጀምረዋል።  በቅርቡም አንድ የሲዳምኛ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ማሳሰራቸው ተረጋግጧል።  ሌሎች ወገኖቻችንም ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰ እንደሆነ ሰምተናል።  የሃሳብ ልዩነትን በሃሳብ ብቻ ማሸነፍን ባህሉ ባላደረገ ድርጅት ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው ከእነሱ ብዙ ባይጠበቅም ራሳቸውን ቢያርሙ ህዝባቸውን እንደሚያስከብሩ ከሌሎች ሊማሩ ይገባል ።

በሲዳማ ክልል የተለያዩ የፓለቲካ ሃይሎች እንዳይፈጠሩ እና  ያሉትም እንዲሟሽሹ የተጀመረው እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተልን እንገኛለን። በክልላችን የተለያዩ ሀሳቦች እና ልዩነቶች በዲሞክራሲያዊ መርህ በነጻነት የሚንሸራሸሩበት ከማድረግ ይልቅ ሁሉንም ወደ አንድ ወጥ አስተሳሰብ ለመሰብሰብ ፣ይህንንም የመንግስትን ስልጣን ተጠቅሞ መፈጸም ነውር ብቻ ሳይሆን ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ እንቅፋት መሆን ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ከሲዳማ ህዝብ ትግል ጋር የቆየ ታሪክ ያለውን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ በብልሃት ለማፈራረስ የነበረውን ሂደት ህዝብ እንዲገነዘብ ያደረጉ ጥቂት የድርጅቱ አመራር አባላት ላይ ያነጣጠረ ዛቻ እና የሚደረግ ማስፈራሪያ  ፈጽሞ የምናወግዝ እና ሊታረም የሚገባው እንደሆነ ለማስገንዘብ እንወዳለን።  ሁኔታውንም በቅርበት እየተከታተልን በመሆኑ በጉዳዩ ላይ እጃቸውን ያስገቡ የመንግስትም ሆነ ከውጭ ያሉ ግለሰቦች ከስህተታቸው እንዲታረሙ እናሳስባለን ። 

የቢሄር መሰረት ያላቸውን የፓለቲካ ድርጅቶች የማፈራረስ እቅድ ከገዥው መንግስት ከላይ የወረደ እቅድ አካል መሆኑን ብንገነዘብም መንግስትም ከዚህ ጉዳይ እጁን እንዲሰበስብ እንመክራለን።

 

በውጭ የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጅ ኢትዮጰያውያን ማህበረሰብ አባላት

ኖቬምበር ፲ ቀን ፳፳

ለተጨማሪ ማብራሪያ- issiani19@gmail.com


Back to Front Page