Back to Front Page

ውጭ ከሚኖሩ የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት የተላለፈ አገራዊ ጥሪ

ውጭ ከሚኖሩ የሲዳማ ማህበረሰብ አባላት የተላለፈ አገራዊ  ጥሪ  ኦክቶበር ፴ ቅን ፳ ፳

 

የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት የሚደርስበተን በደል እና እራሱን ለማስተዳደር የከፈለውን መስዋእትነት መላው የሀገራችን ህዝቦች ይገነዘቡታል ። በደሉ መንግስታዊ በመሆኑ አይነቱና ስፋቱ ይለያይ እንጂ በሌሎች ላይም ተመሳሳይ በደሎች  ሲፈፀሙ ኖረዋል ፣እየተፈጸሙም ይገኛሉ ። ችግሩን ከመሰረቱ ለመቀየር አንዱ እርምጃ ብሎ ህዝባችን ክልላዊ መንግስት መመስረትን ማእከል ያደረገ ተጋድሎ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም የክልል አደረጃጀቱ እውን ሆኗል ። ሆኖም የሲዳማ ህዝብ ውድ ልጆቹን ገብሮ በህዝባዊ ድምጽ እውን ያደረገው ክልላዊ መዋቅር የሲዳማ ህዝብ በራሱ ተከልሎ ደሴት እንዲፈጥር ሳይሆን በአገራዊ ፓለቲካ የበኩሉን እንዲያበረክት ጭምር ነው። ለአገራዊ ችግሮች አገራዊ መፍትሄ ማፍለቅ እንዲያስችለው ነው። የክልሉ ህዝብ የአገራዊ ችግሮች አካል ሳይሆን የመፍትሄ አካል እንዲሆን በክልሉ ያሉ ሃይሎችን ለማስተባበር ነው።

 

  አዲስ ክልል በመሆኑም ለአገሪቱ አዳዲስ ሀሳቦችን ፣ በክልሉም ሆነ ከዚያ ውጭ በአገር አቀፍ ደረጃ በህዝቦች መካከል የተበላሹ ግኑኝነቶችን ለማስተካከል አዲስ ሀይል እና አቅም ሆኖ እንዲወጣ ብዙዎች ተስፋ ጥለው ነበር ። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ራስን ችሎ ማሰብን ፣የራስን አቋም ያለ ምንም ተጽኖ መያዝ መቻል ፣ በአገራዊም ሆነ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የራስን ትንታኔና ውሳኔ መወሰን መቻልን የሚያጠቅልል ነው። ሆኖም ላለፉት ጥቂት ወራቶች በክልሉ ተወካዮች በኩል የተስተዋለው ነገር የክልሉም ሆነ የአገሪቱ ህዝቦች ከጠበቁት አንጻር ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ከነበሩ ነባር ክልሎችም በከፋ መልኩ የትዕዛዝ ተቀባይነት እና ሃይል አለ ብሎ የሚያስብበትን አከባብ በጭፍን የመከተል ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ ስርአት  እንዲቀጥል በማእከላዊ መንግስት የተዘረጋው ወጥ የፓርቲ ሰንሰለት ከፍተኛ አስተዋዕጾ ቢኖረውም የራስ አስተዳደር እንዲመጣ ዋጋ ለከፈለው የሲዳማ ህዝብ ተወክለናል የሚሉ የገዥው ፓርቲ አመራር አካላት ባህሪ በዋናነት ተጠያቂነት አለባቸው።

Videos From Around The World

 

  አገርን የሚመራው መንግስት በመካከሉ በተፈጠረ ልዩነት እና ክፍፍል ምክኒያት በህዝቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያመጣ የሚችል ውሳኔ ሲወሰን በየምክር ቤቱ እየተገኙ እጅ ማንሳትን የመሰለ ታዛዥነት የለም ። የሲዳማ ህዝብ በሲዳማ ላይ ሲደርስ የነበረ ግፍ እና በደል  በሌሎች ላይ ሲደገም መቃወም የማይቸል ተወካይ ሊኖረው አይችልም ። ከላይ ማእከላዊ መንግስቱን ጨብጠዋል የሚባሉ አካላት በተለዋወጡ ቁጥር ለሚመጣው ተላላኪና ታዛዥ ከመሆን ራስን በራስ እንደሚያስትዳድር አካል ገለልተኛ የሆነ ክልላዊ አቋሞችን መያዝ የሚችሉ አመራሮችን ዛሬም የሲዳማ ህዝብ ይፈልጋል። ይህ እውን የሚሆነው ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ምርጫ ሲኖር ብቻ ነው። አሁን ባለው አገራዊ  እና ፓለቲካዊ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ ፈጽሞ የማይታሰብ ብቻ ሳይሆን ከተደረገም ለቀጣይ የዲሞክራሲ ሽግ ግ ር ውስብስብ ችግሮች እንዲፈጠሩ በር ይከፍታል። በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በሃሳብ ልዩነት እና ፓለቲካ እምነት ተለይተው በእስር በሚገኙበት፣ ህዝብ በማንነቱ የተነሳ እየተጨፈጨፈ በሚገኝበት  ፣በክልሎች መካከል ጦርነት ቀረሽ ውጥረት ባየለበት እና ምርጫ ለማካሄድ ሃላፊነት ያለበት መንግስት በህዝብ አመኔታ ባጣበት በዚህ ወቅት ለምርጫ እንዘጋጅ የሚለው የገዥው መንግስት  ራስን በስልጣን ለማሰንበት ከታለመ አጀንዳ ውጭ አገራዊ ፋይዳ አይኖረውም ። ስለሆነም ያለ ምንም በቂ ምክኒያት ከህገ መንግስታዊ የጊዜ ገደቡ ውጭ እንዲራዘም የተደረገው  ምርጫ  የአገሪቱን ሁኔታ ከግንዛቤ ባስገባ መንገድ እና ጊዜ ብቻ ማካሄድ ያስፈልጋል። ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን  ሁሉን አቃፊ የሆነ የፓለቲካ ስርአት እንዲዘረጋ እና አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ሊያወጣት የሚችል አስታራቂ አገራዊ ሀሳብ  በአፊኒ ስርአት በመታገዝ እንዲያቀርብ አዲሱን የሲዳማ ክልል እንጠይቃለን ። የሀገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ አካላት ሁሉ  አገሪቱ የገባችበትን ቀውስ ያገናዘበ መፍትሄ ወደ ማፈላለግ እንጂ አዳዲሰና ውስብስብ ችግሮችን በተለመደው ግን አዋጭ ባለሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያደርጉትን ግብግብ አቁመው የህዝቦችን አንድነትን እና ሰላም የሚያስጠብቁ አማራጮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።

 

 አገራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ጦርነት ተሞክሯል፣ውጤቱ ህዝብን ፈጅቶ  እና ሃገራዊ ቀውስ ፈጥሮ አገሪቱ ከድህነት ወለል በታች እንድትሆን አድርጎል። የውሸት ምርጫ ማካሄድም ሞክረነዋል ለመንግስታዊ አምባገነንነት እና ጥቂቶች ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስርዓት ፈጥሮአል። ግለሰቦች በስም ተጥቅሰው እንዲያሻግሩም ተሞክሯል እሱም ባለፉት ሁለት አመታት ጉድ አድርጎናል። ሁለት ታላላቅ ቢሄሮች ከተያያዝን  ይህ አገር ይስተካከላል  በማለት ኦሮ አማራ ቡድን በመፍጥር የኢትዮጰያዊነትን አንድነት በተናጠል ለማምጣት ጥረት ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንም አይተናል። አንደኛው የሌላኛውን ቁስል ከማከክ የዘለለ መፍትሄ አልባ እንደሆነ እና ይልቁኑ አገርን የሚከፋፍል ፣መናናቅን ያበዛ እና የሌሎች ቢሄሮችን ሚና ያላገናዘበ አግላይ አደረጃጀት በመሆኑ ስልቱ በጊዜ ሂደት እራሱን የሚያከስም ይሆናል። ስለሆነም አዲሱ የሲዳማ ክልል በውስጡ ያሉ ባህሎቹን ፣ሽማግሌዎችን ፣ሙሁራንን እና ተቋማትን በመጠቀም ሀገሪቱ ከገባችበት የጦርነት አደጋ እንዲሁም ውስብስብ የፓለቲካ ችግሮች የምትላቀቅበትን አማራጭ ሀሳብ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን። 

 

በውጭ የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጅ ኢትዮጰያውያን ኦክቶበር ፴ ቅን ፳፳  ለተጨማሪ መረጃ issiani19@gmail.com  


Back to Front Page