Back to Front Page

ኧረ በህግ አምላክ!

ኧረ በህግ አምላክ!

ዮሃንስ አበራ (ዶር.)

1-16-20

ሁል ጊዜ የሚቸግርና መስዋእትነት የሚያስከፍል ነገር ቢኖር ወደ ፊት መሄድ ነው፡፡ የኋሊት ለመሄድማ ንፋስም ያግዛል፤ ከየኋሊት መድረሻ በፍጥነት ያደርሳል፡፡ ህግ ማክበር ወደፊት መሄድ ነውና ከባድ ነው፤ ህግ ማፍረስ ግን ቀላል ነው ፍላጎት እንጂ አውቀትና ችሎታን አይጠይቅም፡፡ እድገትና ልማት ከህግ ማክበር ጋር የተቆራኙ ናቸው; በህገወጥነት ያደገ/የለማ አገር የለም፡፡ ህግ ማክበር የስልጣኔ ምልክት ነው፡፡ ለዚህም ነው የሰው ልጅ ስልጣኔ ሲጀምር ከህግ ጋር ተጣምሮ ብቅ ያለው፡፡ የመጀመሪዎቹ የሱመርና የባቢሎን ስልጣኔዎች ሃሞራቢ የሚባል የዛ ዘመን ንጉስ ህግን በፅሁፍ አማካይነት ለህዝብ አሳውቆ ያስተዳድር ነበር፡፡ አይን ያጠፋ አይኑን፤ አግር የቆረጠ እግሩን፤ ነፍስ ያጠፋ ነፍሱን የሚል ህግ ነበር፡፡ የግድ ነው! የህዝብ መብት ተጠብቆ በሰላም ለማስተዳደር ከተፈለገ ህጎችን ማውጣት ብቻ ሳይሆን የሚከበሩ፤ የሚተገበሩ፤ ጥርስ ያላቸው ህጎች መሆን አለባቸው፡፡ አለበለዚያ የህግ አንቀፅ በቀለም ወረቀት ላይ ተለቅልቆ ቢቀመጥ ለብል ምሳና እራት ይሆናል እንጂ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ለዚህም መንግስታት ግንባር ቀደም ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ራሱ ያወጣውን ህግ የማይጠብቅ መንግስት ማንም ሌላ እንዲያከብርለት መጠበቅ የለበትም፤ ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ ባለ እዳ አይቀበለውም ይባላልና፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ህግ የማፍረስ ባህል ስር የሰደደ ነው፡፡ በመንግስት ይሁን በግለሰብ ደረጃ ህግ አፍራሽን የማይፀየፍ ማህበረሰብ የወደፊት እድሉ የተበላሸ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ በአንድ ወቅት ጎንደር ውስጥ ጭልጋ ከሚባል አካባቢ ተነስቼ ወደ ጎንደር ከተማ ስጓዝ ከአርማጭሆ የመጡ ሁለት ተሳፋሪዎች ከጎኔ ነበሩ፡፡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያወሩ ስለነበር የሚሉትን ሁሉ እየሰማሁ ነበር፡፡ አንድ የተናገሩት ነገር ግን እጅግ አስገረመኝ፡፡ እከሌኮ ሌባ ነው ጀግና ነው አለ አንዱ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እያዳነቅ አዎ፤ ነው እንጂ፤ እንዴት ያለ ጎበዝ!፡፡ ይህንን ዝም ብየ ማለፍ አልቻልኩም፤ ሰለዚህ ጥያቄ አቀርብኩላቸው፡- ሌባ እንዴት ጀግና ይባላል? እነሱ ግን በኔ ጥያቄ ተገርመው አያሾፉ ጀግና ነውንጂ፤ ተታኩሶ አይደል የሚሰርቀው ብለውኝ አረፉ፡፡ በርግጥ ቀደም ብየ አዛው ጎንደር ዳባት ከሚባል ከተማ ውስጥ የደርግ አባልና አስተዳዳሪ የነበረው አምሳ አለቃ ገብረህይወት ዳባት ከተማ ገበያ ላይ ቋሚ የመስቀያ እንጨቶች አዘጋጅቶ ዘወትር ቅዳሜ በረት ገልባጭ ተብለው ታስረው የመጡለትን የአርማችሆ የከብት ሌቦች (ማለት ጀግኖች) በስቅላት ይቀጣ ነበር፡፡ ይህን ሲያደርግ የነበረው ዝርፊያው ለፖሊሶች ካቅም በላይ ስለሆነባቸው ስቅላቱ የማስደንገጥ እርምጃ ነበር አሉ፡፡ ይህ ሌብነትና ስቅላቱ አላባራ ሲል በጉዳዩ የአገር ሽማግሌዎች ገቡበትና አምሳ አለቃውን እንዲህ ብለው አነጋገሩት፡- የአገሩ ባህል ነውና ሰዎች የተኩስ ችሎታ የጀግንነት ማስመስከሪያ ውድድር አድርገው ስለሚወስዱት አድሜ ልክህን ብትሰቅል አታስቆመውም፡፡ አስተዳዳሪውም ይህን ሲሰማ መስቀሉን አቋረጠና አገር ሰላም ሆነ፡፡

Videos From Around The World

በአሁኑ ዘመን አርማጭሆ አዲስ አበባም በሌሎቹም የኢትዮጵያ ከተሞችም ተዳርሷል፡፡ ማለቴ በረት መገልበጡ ሳይሆን ሌላ ሌላ ህግ ማፍረሱ፡፡ የሚኒ ባስ ሹፌሮችና ረዳቶች ትራፊክ ከፊታቸው ካልቆመ ወይንም ያየናል ብለው ከሚያስቡበት ርቀር ላይ ካላዩት የትራፊክ ህግ ማክበር ዘበት ነው፡፡ አሉ የተባሉት የትራፊክ ህጎች ሁሉንም ይጥሳሉ፡፡ አንድ ጊዜ ሜክሲኮ ላይ ሚኒ ባስ ጋቢና ውስጥ ተቀምጬ እያለሁ ሹፌሩ ረዳቱን የት ነው ያለው? አይተኸዋል? እያለ ይጠይቀዋል፡፡ እኔም ህግ አስከባሪ ከሌለ ህግ አታከብሩም ማለት ነው? ብየ ሹፌሩን ብጠይቀው በቅንነት እንዲህ ብሎ መለሰልኝ ሁሉም እኮ ነው ይህን የሚያደርገው፤ ብቻችን ህግ ብናከብር ሰባራ ሳንቲም ይዘን ቤታችን አንገባም፡፡ አውነቱን ነው! ከፍተኛ የሃብት ወይንም የስልጣን ወይንም የትምህርት ደረጃ ያላቸው ወፍራም ወፍራም መኪና የሚይዙ አሽከርካሪዎች ዜብራ ላይ፤ የእግረኛ መሄጃ ላይ፤ በሱቅ ወይንም የህዝብ አገልግሎት የሚሰጥበት መስሪያ ቤት በር ላይ ግጥም አርገው ዘግተው ሲያቆሙና አግረኛው ለአደጋ ተጋልጦ ወደ አስፋልት ገብቶ ሲራመድ እያዩ ዘውድ የደፉ ነገሰታት መስለው ሰውንም ከመጤፍ አይቆጥሩም፡፡ ምናልባት የትራፊክ ደምብ ያወጡ ሰዎቹም ከመሃላቸው ይኖራሉ፤ ትራፊክ ፖሊሶችንም ስራችሁን አልሰራችሁም እያሉ የሚቀጡም ቢሆን ከነዚህ አውቆ አጥፊዎች መካከል አይጠፉም፡፡

ህግን የማፍረስ ጎጂ ባህል ካሉት ማሳያዎች አንዱ የአማርኛ የሰው ሰሞች ናቸው፡፡ ሰውን ከመጉዳት ከመግደል ከመደብደብ ጋር የተገናዘቡ የሰው ስሞች አሉ፡- ለምሳሌ አናጋው፤ አሰታጥቃቸው፤ ድፋባቸው፤ ደምሰው፤ በለው፤ መርእድ፤ አራደ፤ ሽብሩ፡፡ በዘፈኑስ ቢሆን ህግ አፍራሽነት እንደ የመልካምነት መገምገሚያ ሆኖ ኖረ አይደል፡፡ ይርጋ ዱባለ ዋጋ የሌላት ሴት ናት ብሎ የናቃትን እንዲህ ብሎ ያዋርዳታል፡-ገዳይ ገዳይ ያልሺው አባትሽ አይገድል፤ አርሶ ያብላሸ እንጂ ሆድሽ እንዳይጎድል፡፡ አባትዋ ሰላማዊ አራሽ ገበሬ መሆኑ እንደ ድክመት ተቆጥሮ ገዳይ አባት ካላት ብቻ ተፈላጊ ጥሩ ሴት ትሆናለች፡፡ ባል የፈለጉ ሴቶች ሁሉ አባቶቻቸው ገዳይ እንዲሆኑላቸው መመኘት አለባቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ለሃገር ድንበር ማስከበር ቅስቀሳ ለማድረግ የተዘፈነ አይደለም፡፡ ለሱም ቢሆን ተገቢ አይደለም፡፡ አገር ጦረኛ ብቻ አያኖራትም፤ በዋናነት ገበሬም ጭምር እንጂ፡፡ ሙሰና ከሁሉ የከፋው ህግ ማፍረስ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም ግን በባህላዊ አባባሎች ሲሞገስ ከመኖሩ የተነሳ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ መገንባት በሚል ማለፍ በየትኛው አመቺ ባህል አልፎ ሙስናን እንደሚፀየፍ ለኔ ግራ ይገባኛል፡፡ ህብረተሰቡ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል በሚል ተረትና ምሳሌ ሳትበላ ከስልጣን ትወርድና ወዮልህ እያለ የሚያስጠነቅቅ ህብረተሰብ ተይዞ ሙሰናን በምን ዘዴ መዋጋት ይቻላል?

በፖለቲካውም የህግ ጥሰቶች እጅግ በርካታ ናቸው፡- ሰላማዊ ተቃዋሚን ማሰርና ያለ ፍርድ ሂደት በእስር ማቆየት ወይንም እርምጃ መውሰድ፤ የሃገር ሉአላዊነትና ጥቅምን የሚነኩ ወንጀሎች ውስጥ በማናለብኝነት መሳተፍ፤ ለዚህም ተግባር መንግስታዊ መዋቅሩን አገልግሎት ላይ ማዋል፤ የህግ አስፈፀሚ መዋቅሮችን ነፃነት ሽሮ ታዛዥና የግለሰቦች ወይንም የቡድን አገልጋይ ማድረግ፤ የመሪነት ስልጣንን ተጠቅሞ ምርጫን ማጭበርበር፤ ነፃ መሆን ያለባቸውን እንደ ፖሊስ፡ መከላከያና ደህንነት ያሉ የሃገር አለኝታዎችን የግለሰቦች አገልጋዮች ማድረግ ፤ ወዘተ፡፡ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ትልቅ ችግር የግንዛቤ ችግር ነው፡፡ ቤት ሰርሳሪንና ሃገርን ለጥቅም አሳልፎ የሚሰጠውን ሁለቱንም እንደ ሌብነት እኩል አያይም፡፡ ርቦት አንድ ዳቦ ሰርቆ የበረረውን በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ስራቸውን ትተው ሌባ! ሌባ! አየሉ ድንጋይና ቆመጥ ይዘው ሲያሳድዱት የሃገር ህልውናን በገንዘብ የለወጠው ይሁዳውን ግን ወንጀሉን ሊያቀሉለት ወይንም ሊሰርዙለት ሲታገሉ ይታያል፡፡ ህብረተሰቡ ለህግ ያለው ቀናኢነት ተስፋ የማይሰጥ መሆኑን ከገመገምኩ በኋላ ይህ ፅሁፍ ለመፃፍ ወዳነሳሳኝ ጉዳይ ልግባ፡፡

ሶሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የዜና አውታሮች የሚያቀርቡት ሪፖርት ግራ እያጋባኝ ነው፡፡ ብትናገረው ሰከንድ ባልሞላ ጊዜ ስልጣኑን የተቀማ፤ ጥቅም የቀረበት ትባላለህ፡፡ ኧረ እኔስ የተደራጀ ፖሊቲካ ውስጥ መሳተፍ ካቆምኩ አራት አስርት አመታት ሆኖኛል፤ በላቤ የማድር እንጂ ያገኘሁትም ያጣሁትም ጥቅም የለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የፍትህን መስመር ተከትሎ ነፃ ሆኖ መፃፍ የተለመደ አይደለም፤ ነጭ ካልሆንክ ጥቁር ነህ፤ ጥቁር ካልሆንክ ደግሞ ነጭ ነህ! ግራጫ የሚባል የፖለቲካ ቀለም ኢትዮጵያ ውስጥ አይታወቅም፡፡ ጠቅላዩን ከተቸህ ዲጂታል ወያኔ የሚል ሰሌዳ ይለጠፍብሃል፡፡ መቸም ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም በተለይ የአንድ አገር የህልውና መሰረት የሆነው ህግን የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ላይ ይሉኝታና ግዴለሸነት ሊኖር አይችልም፡፡ አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ለስራ ሃላፊዎች ስልጠና እየሰጠ ነው ተብሎ እንደተራ ዜና ሲነገር ስሰማ በሆዴ ውስጥ ጮክ ብየ ረ በህግ አምላክ አልኩኝ፡፡ ህጉ ምንም የሚያደናግር ነገር የለውም፤ አለም አቀፍም ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለመንግስት አመራር በህጋዊ ምርጫ ሳይመረጥ በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ ላሉ ሰራተኞች ሆነ ሃላፊዎች ለምርጫ ቀርቦ ህዝብ ያልመረጠው የፓርቲ ፍልስፍናና ፐሮግራም መሰረት ያደረገ ስልጠና ሊሰጥ አይችልም፡፡ ሲጀመር ሰራተኞቹን ሆነ ሃላፊዎቹን እንኳንና ስልጠና መስጠት ከስራ ቦታቸው ለሰከንድም ቢሆን እንዲነሱ የማዘዝ ስልጣን የለውም፤ በእረፍት ጊዜ በራሳቸው ፈቃድ ካልሆነ፡፡ ይህ በደጋፊ ብዛትና በእጅ በገባ ስልጣን የተሸፈነ ህገወጥነት ነው፡፡ ይህ ድርጊት ህገወጥ አይደለም የሚባል ከሆነ መጪው ምርጫ መካሄድ የለበትም ማለት ነው፤ ምክንያቱም የሚቀጥለው መንግስት የማን ፓርቲ እንደሆነ ታወቋል ማለት ነው፡፡ ለምን ህዘብ በምርጫ ጊዜውን ያባክናል፡፡ መቸም ስልጠና እየተሰጠ ያለው እስከ ምርጫ ላለው ስድስት ወር አይደለም፡፡ ከሆነ ቅሬታየን አነሳለሁ፡፡ የፓርቲ ፍልስፍና ላይ ማሰልጠን ግን የስድስት ወር የስራ አመራረር ስልጠና ሊሆን አይችልም የዘለቄታ እንጂ፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ህግ በማክበር ለሌላው ሁሉ አርአያ መሆን ካለበት የህዝብ ውሳኔ በምርጫ ካርድ እስኪታወቅ ድረስ ህዝብን አክብሮ መጠበቅና ፐሮግራሙን ግዴታ ባልሆኑ በህዝባዊ ስብሰባዎችና በሚድያ እያስተዋወቀ መቆየት ነው፡፡

ስለ ስሜትና የፖለቲካ ጨዋታ ማውራት እንተወውና ስለደረቅ ህግ እንነጋገር ከተባለ ይህ መንግስት በምርጫ አሸንፎ (እንበለው ችግር የለም) የመንግስት ስልጣን የያዘው (ፓርላማ፤ ሚኒስትሮች ምክርቤት፤ ጠቅላይ ሚኒስተር) ኢህአዴግ በሚባል የፖለቲካ ግንባር ነው፡፡ ይህ በህጋዊ ሰነዶች ላይ የተመዘገበ፤ አለም የሚያውቀው፤ ፓርላማ አባላትም፤ ሚኒስትሮችም፤ ራሱ ጠቅላይ ሚኒስተሩም የማይክዱት ነው፡፡ መቸም እንደ ሰጎን አላየሁም፤ አልሰማሁም ብለን ራሳችንን አሸዋ ውስጥ ቀብረን ካልሆነ በስተቀር ያለው መንግስት የኢህአዲግ መንግስት ነው፡፡ በዚህ ላይ ጉንጭ አልፋ ክርክር መከራከር ጊዜ ማባከን ነው፡፡ እዚህ ላይ ህፃንም ቢሆን በቀላሉ ሊገባው የሚችለው ሎጂክ፤ ተመርጦ ፓርላማ፤ ሚኒስትሮች ምክርቤት፤ ጠቅላይ ሚኒስተር የሆነው ኢህአዲግ በይፋና በህግ ከፈረሰ ወዲያውኑ ፓርላማ፤ ሚኒስትሮች ምክርቤት፤ ጠቅላይ ሚኒስተር በህግ ይከስማሉ፡፡

በ1991 ዓ.ም. ህንድ ስትመራ የነበረችው ቢጄፒ በሚባል የሂንዱ ብሄረተኛ ፓርቲ የበዛበት ጥምር መንግስት ነው፡፡ ከጥምር መንግስቱ ውስጥ 20 መቀመጫዎች የነበረው የታሚል ናዱ ፓርቲ ከጥምር መንግስቱ ድንገት ለመውጣት ሲወስን ያመንግስት ሊቀጥል እንደማይችል ግልፅ ሆነ፡፡ ቫጅፓዪ የተባለው ጠቅላይ ሚኒስትር (የቢጄፒ መሪ) እስከቀጣዩ ምርጫ ያለ ማጆሪቲ ወንበር መቀጠል ይፈቀድለት አይፈቀድለት እንደሆነ በፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ ተሰጠና አልተሳላከለትም፡፡ ስለዚህም የቫጅፓዪ መንግስት በዚህ ምክንያት ፈረሰና ባስቸኳይ ሌላ አጠቃላይ ምርጫ ተካሄደ፡፡ ይህ ታሪክ አንብቤው ሳይሆን ዴልሂ ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ራሴ የተከታተልኩት ነው፡፡ ይህ የሆነው በአለም ታላቋ ዴሞክራሲ በምትባለው አገር ነው፡፡ እኛስ? አሁን እንደምንሆነው እየሆንን ነው እነሱ ከደረሱበት ደረጃ የምንደርሰው? የባጅፓዪ መንግስት የፈረሰው እንዲያውም ፓርቲው ስለፈረሰ ሳይሆን የፓርላማ ወንበር ስለጎደለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዴሞክራሲ ግን ያስመረጠ ፓርቲ አፍርሶ እንዳሉ መቆየትና ስልጣን ላይ ሆኖ ሌላ ፓርቲ መስርቶ ለቀጣይ ውድድር መዘጋጀት የሚባል አስደናቂ ድርጊት ይፈፀማል፡፡ በህንድ የአገሪቱን ስልጣን አያያዝና አለቃቀቅ የሚቆጣጠረው ፕሬዚደንቱ ነው፡፡ ፕሬዚደንቱ ለማንም ፖለቲካ ያልወገነ መሆኑ ታይቶ ነው የሚመረጠው፡፡ ኢንድራ ጋንዲ ወይንም ቫጅፓዪ ያስቀመጡት ፕሬዚደንት የለም፡፡ ቫጅፓዪ የፓርላማ የመተማመኛ ድምፅ ሲያጣ ባለ አደራ መንግስት ሆኖ እንዲቆይና ሌላ ምርጫ እንዲያካሄድ ያዘዘው ፕሬዚደንቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥም ክብርት ፐሬዚደንቷ ይህን ስርአት አሲዘው የአገርን የወደፊት የዴሞክራሲ ተስፋ ከመጨለሙ በፊት እንዲታደጉት ይጠበቃል፡፡ እንደ ብርሌ የሃገር ዴሞክራሲ አንዴ ከነቃ አይሆንም እቃ ነው፡፡ ከእርሶ የበለጠ የምእራቡን አለም የዴሞክራሲ አካሄድ የሚያውቅ አለ ብየ አላስብም፡፡ ከነሱ ጋር እንደኖሩት እንደነሱ ይሁኑ፡፡ ኋላ ቀር ሆነን እንደኖርነው የበለጠ ኋላቀር እንድንሆን አይፍቀዱ፡፡ ቅኝ አገዛዝን መመከት በአለም ደረጃ ሊያስከብር ይችላል፡፡ ይህ ግን በቂ አይደለም፡፡ ህግ እየፈረሰና ዴሞክራሲ እየተጓደለ በአለም አደባባይ ቀና ብሎ በኩራት መራመድ አይቻልም፡፡ አርበኝነት ዴሞክራሲንና የህግ የበላይነት አይተካም፤ የየቅል ናቸው፡፡ ያለው መንግስት ምርጫ አስኪካሄድ ድረስ ባለ አደራ መንግስት ብለው መሰየም የሚችሉትና ያለብዎትም እርሶ ነዎት፤ በርግጥ የተመረጠበትን ፓርቲ ያፈረሰ ስለሆነ የማይገባው ቢሆንም፡፡ በአዋጅ የሃላፊነት ገደብ ተሰጥቶት ትልልቅና ዘላቂ የውስጥና የውጪ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዳይሰጥ፤ አስቸኳይ ከሆኑም ህዝብ አውቆት ይሁንታ እንዲሰጥበት መደረግ አለበት፡፡ የባለአደራ መንግስትነቱን ለራሱ ምርጫ ጥቅም ላይ እንዳያውለው ቁጥጥር ማድረግ የርስዎ ፈንታ ነው፡፡ እንደ ፕሬዚደንት የእርሶ ዋና ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ፖለቲካ ፓርቲዎች አይደሉም፡፡ የሃገሪቱ አቃቤ ህግም እንዲህ አይነት ጉዳይ በነፃነትና ያለ ወገናዊነት መርምሮ የህግ ትንተና በመስጠት ለድርጊት ካልተሰማራ እንኳንና ሃገርን ራሱንም መጠበቅ አይችልም፡፡ አቃቤ ማለት ጠባቂ ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ሌላ ስም ይሰጠው! እኔ ፍቅሬ ከኢህአዴግ ሳይሆን ከህግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሆነ ብልፅግና ህግ ካፈረሱ ይቅር ሊባሉ አይችሉም፡፡ ህግ የቀበጠ የቤት ልጅና የተቀጠቀጠ የእንጀራ ልጅ የለውም፡፡ ፓርቲ ራሱን መቶ ጊዜ ቢገነባና ቢንድ ማንም አይከለክለውም፤ ይህ ድርጊት ህግን ጠልፎ የሚጥል ከሆነ ግን ኡ!ኡ!ኡ! ብለን በህግ አምላክ እንበል፡፡

ለሃገር ህልውና፤ ለግላችንም ህይወትና ኑሮ አለኝታችን ግለሰብ ወይንም ቡድን ሳይሆን ህግ ነው፡፡ ህግ እንደ ጌታችን አልፋ ወኦሜጋ ነው፡፡ አምላክ የጀመረው ህግን በማስከበር ነው፡፡ እፀበለስ እንዳትበሉ አለ፤ ህግ አፍራሾቹ የአምላክን ህግ ሲጥሱ ለዘመናት የዘለቀ አይቀጡ ቅጣት ቀጣቸው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገው የተሻለ ነገር ነው፡፡ ይህ የማንኛውም ህዝብ ጤነኛ ስሜት ነው፡፡ ህዝብ ኢህአዲግን ህግ አፈረስክ ብሎ ቢጣላው ሌላ የባሰ ህግ አፍራሽ እፈልጋለሁ ማለቱ እንዳልነበር ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ህግ አፍራሽነትን የሚሸከም ደልዳላ ጀርባ ስላለን ህግ አፍራሾችን ለመታደግ አስር አይነት ማምለጫ አይደርደር፡፡ ህዝብ ሲፈናቀል፤ ሲገደል፤ ሲበደል ለምን ዝም አላችሁ ሲባል ኢህአዲግ/ህወሓትስ ከዛ በፊት ዝም ብሎ ሲያይ ነበር አይደል ይባላል፤ ለምን ሙስና ትሰራላችሁ ሲባል ኢህአዲግ/ህወሓትስ ሙስና ሲሰራ ነበር አይደል ይባላል፤ ለምን ታስራላችሁ ትገድላላችሁ ሲባል አሁን እኛ ላይ ደርሶ ነው ትችት የሚቀርበው፤ ኢህአዲግ ወይንም ህወሓትስ ይህን ሲሰሩ አልነበር ይባልና እርምጃ አይወሰድም፡፡ እንዲህ ብለው ግራ ግራውን በመመለስ ህዝብ ጥያቄ ማቅረብና መተቸትን ተሰላችቶና ተስፋ ቆርጦ እንዲተወው ያደርጉታል፤ ከዛ ይመቻቸውና ጌቶች ሆነው ይኖራሉ፡፡ በጆርጅ ኦርዌል የማነር እርሻ እንስሳቱ አምፀው ጨቋኙን ገበሬ ካባረሩት በኋላ የእንስሳቱ አብዮታዊ መሪዎች ራሳቸው ከተባረረው ገበሬ የባሱ እስከመሆን ደርሰው እያለም ነጋ ጠባ የአፍ መክፈቻ ሆኖ የቆየው አራት እግር ጥሩ፤ ሁለት እግር መጥፎ የሚለው መፈክር ነበር፡፡ አልጋ ላይ መተኛት ከልክል ነው የሰው ድርጊት ስለሆነ ብለው ህግ አወጡ፡፡ የእንስሳቱ አብዮት መሪዎች አልጋ ላይ ሲተኙ ያዩት እንስሳት ለምን ብለው ቢጠይቁ የተባባልነው እኮ አንሶላ ካለው አልጋ ላይ እንጂ ባዶ አልጋ ላይ አይደለም እያሉ ያጨናብሯቸው ነበር፡፡ አውጣኝ ጌታየ ከዚህ አይነት ህግን ወደጎን አስቀምጦ መሸዋወድ፡፡

Back to Front Page