Back to Front Page

ዘር ከሰውነት በላይ ሲውልክፍል 2

ዘር ከሰውነት በላይ ሲውል

ክፍል 2

በዳንኤል ብ. ተክሉ

danielekfta74@gmail.com

ቶሮንቶ ካናዳ

 

ውድ አንባቢያን ባለፈው ክፍል 1 ላይ በርካታ የአሁኑ መንግስት የፕሮፓጋንዳና የአካሄድ ስልትን በተመለከተ ለመዳሰስ ሞክረናል። ባሁኑ ክፍል ደግሞ የዚህ የአሁኑ የፖለቲካ መድረክ መሰረታዊ ጉድለትን በተወሳሰበ ሳይንሳዊ መንገድ ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው ማንም ሊረዳው በሚችል መልኩ ለማየት እንሞክር።

የዶክተር ዓቢይ አሕመድ ማለትም ቲም ለማ በመባል የሚታወቀው ቡድን በራሱ በወያኔ ኢሕአዴግ ውስጥ የኦሮሞ ፓርቲ ማለትም የኦህዴድ ወኪል ሆኖ በሚሰራበት ወቅት በግንባሩ በኢህአዴግ ውስጥ አንጃ በመፍጠር የራሱን ግንባር በተለያዩ መንገዶች በመፈታተንና ለሃገሪቱ ጠላቶች ማለትም የታሪክና የፖለቲካ ጠላቶች ሃገራዊና ወታደራዊ ምስጢር እስከመስጠት የሄደ ከፍተኛ ሃገራዊ ክህደት በመፈጸምና የግንባሩን አንድነት በማፍረስ የራሱን የበላይነት ይዞ ሲወጣ በወቅቱ የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ ሲል ስለ ሰላምና ስለ ምህረት እያወጀ ቢመጣም ቆየት ሲል ግን ውስጣዊ ባህሪው እየተገለጠና ሌላ ግጭት የሚጋብዝ መንገድ እየተከተለ መምጣት ጀመረ።

Videos From Around The World

በመጀመሪያ የዚህ ቡድን ሃላፊና መሪ የሆኑት አቶ ለማ መገርሳና ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ በስለላ መረብ ውስጥ ታፍኖና ተሰቃይቶ በሚኖርበት ወቅት የት ነበሩ የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ብዙ ሰው ስላልሆነ የኛ ህዝብ አሁን ከፊት ለፊት ያለውን ብቻ እያየና እየሰማ የሰዎች ውስጣዊና ታሪካዊ ሁኔታ እንዳይረዳ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ አጭር ርቀት ተመልካች (shortsighted) መሆኑ ያስገርማል።

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የዜጎችን ስልክ በመጥለፍ፣ ኢሜይላቸውን በመበርበር፣ የተለያዩ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠቀም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲታፈን በግንባር ቀደምትነት ሲተውኑ የነበሩት አንደኛው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። ዶክተር ዓቢይ ከራሳቸው ቃልም እንደሰማነው የመረጃና የደህንነት መረብ የተሰኘ የመንግስት የአፈና መዋቅር እንዲፈጠርና አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ መሪ ተዋናይ እንደነበሩ ያሳያል። ይህ የስለላና የአፈና መዋቅር ምክትል ሃላፊና ዋና ሃላፊ በመሆን መርተውታል። በሳቸው የአመራር ጊዜ በርካታ ሰዎች ስልካቸው እየተጠለፈና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ንግግር ሳይቀር እየተቀዳ በግድ ሌላ ትርጉም በመስጠት ለእስርና ለሞት ሲዳርጉ የነበሩ ሰው ናቸው። አቶ ለማ ከመጀመሪያውም የኢሕአዴግን ስርዓት የተቀላቀሉት በሰላይነት ነበር። እንዲሰልሉ የተቀጠሩበት ምክንያትም በኦሮሞ የነፃነት ታጋዮች ላይ ክትትል እንዲያደርጉና በነሱም ሆነ ሌላ ለየት ያለ ሃሳብ ያራመደ ኦሮሞ ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ብሎም በመግደል ሌሎች ለመብታቸው ምንም ዓይነት ሃሳብ እንዳያቀርቡ ለማሸማቀም ጭምር ነበር። በሳቸው ጠቋሚነትና መሪነት በሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ህይወታቸውን ነጻነታቸውንና ንብረታቸውን አጥተዋል።

ይህ ቡድን ወደ ስልጣን ሲመጣ እራሱ ከማንኛውም ሃላፊነት ነጻ ያደረገ በሚመስል አነጋገር ሌሎችን አንከስም አንተናኮልም ቢልም በተግባር ግን እራሳቸውን እንደ ንጹህ እያዩ በሌሎች ላይ የክስ ሃሳብ መሰንዘር በራሱ ህዝብን በጊዜያዊ ስሜት በመግባት ለማታለል መሞከር ይሆናል። ይህ ደግሞ ባገራችን ካለው የብሄርና ብሄርሰቦች የዘር ግጭትና ተያያዥ ውጥረት አንጻር የነሱ ትችትና እርምጃ ከግለሰብ በላይ እየተመነዘረ የዘርና የጎሳ ግጭት ወደ ማስነሳተ የሄደ ትልቅ የፖለቲካ ስህተት በመፈጸም ላይ ናቸው። እነሱ በመጀመሪያም የሽግግር ምክር ቤት አቋቁመው በህዝብ በተመረጡ ሽማግሌዎችና ምሁራን ለቀጣይ የምርጫ ጊዜ ለመዘጋጀት እንጂ አሁን እንዳደረጉት በተመሳሳይ ሃሳብና መንገድ አዲስ ፊት በማሳየትና ህዝቡን በማሳሳት ወደነበረው ለመመለስ አልነበረም።

ኢትዮጵያ የብዙ የተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ሃገር በመሆኗ ሁሉም ነገር ከዘር አንጻር እንዲታይ የሚያደርግ ስርዓት ውስጥ ስላደጉ ይህንን ስሜታቸው ከተራው ዜጋ በተሻለ መንገድ ገርተዉት ህዝብን ማስተዳደር ሲችሉ እነሱ የጎሳና የዘር ግጭት የሚያስነሱና የሚያባብሱ አስተሳሰቦችን ሲያራምዱ እነሱ ለውጥ ያሉት ሂደት እንደጨነገፈ ለመረዳት የፖለቲካ ምሁር መሆንን አይጠይቅም። እነሱ ግለሰቦችና ሃብታሞችም ስለሆኑ ነገ አንዳች ነገር ቢመጣ ሃገሪቱን ጥለው እንደሚኮበልሉ የታወቀ ነው። ትናንት የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች በእሳት ነበልባል ሲበሉ የዶክተር ዓቢይ ቤተሰብ አሜሪካ ውስጥ ተንደላቀው ይኖሩ እንደነበር ሃገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ምስጢር ነው። የለማ ልጆችም እንደዚሁ በተራ ትምህርት ቤቶች እንደማይማሩና በተለያየ መንገድ ባካበቱት ሃብት ካገር ውጭ የትም አገር ሄደው እንደሚማሩ የማይታበል ሃቅ ነው። አሁን እነሱ በዘሩት መርዛማ ፍሬ አማካኝነት ሃገርን የሚያክል ነገር አደጋ ላይ ስትገባ ማን ሰለባ እንደሚሆን መገመትም አያስፈልግም። ያው ሁሌም ቢሆን የጠገቡ ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው እንደሚባለው የጉዳቱ ሰለባ የኔው ብጤ በሳር የተመሰለው ስሃው ነው።

በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ህዝብ በነበረው የነሱ ስርዓት ተማሮ በየአከባቢው ከፍተኛ ህዝባዊ ዓመጽ ሲያስነሳ በፈረንጆች 2016 የኢሬቻ በዓል ላይ የተፈጸመው ዓይነት ወንጀል በህዝቡ ላይ ሲፈጽሙ የቆዩት እነዚሁ አሁን ቅዱስ ለመመሰል እየሞከርሩ ያሉት ሰዎች ናቸው። ህዝቡ ግን አፈናውና ግድያውን ሳይፈራና በከፍተኛ ትጋት በመመከት የአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋትና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በማሽመድመድ መንግስትን እጁን ጠምዝዞ ወደ እስረኞች መፍታትና ሳይወዱ የለውጡ ተቀባይ እንዲሆኑ ያደረገ ትግል አከናውኗል። ያ እስረኞችን በመፍታት ካሁን በኋላ ዲሞክራሲ እናሰፍናለን የወሰዱት ጊዜያዊ እርምጃ በራሱ ከበጎ ፈቃዳቸው እንዳልመነጨ የሚረዳ የውጭ ሃይል ብዙ አይደለም። ለሃያ ሰባት ዓመታት በጸረ ህዝብነት የኖረ ሃይል አሁን ምንም መሰረታዊ ምክንያት ሳይኖረው ዲሞክራት ሆኛለሁ ቢልም ያለፈን ስህተና ወንጀል በተገቢው መንገድ ሳይመረምር ምህረትም ከሆነ ማን ምን እንዳጠፋ ስለተጠየቀ ሳይብራራ በደፈናው ዲሞክራት ሆኛለሁ ቢልም ህዝብን ከማታለል የዘለለ ቁም ነገር የለውም። እነዚህ ሰዎ ዲሞክራት እንሁን ቢሉ እንኳ ያንን ባለፈው ያጠፉት ጥፋት እየተከታተለ ከስጋት ውጭ ሊያደርጋቸው ስለማይችል ያንን በህዝብ ላይ ያደረሱት በደልን ለመሸፈን ሲሉ ሳይወዱ ወደ አፈና መግባታቸው አይቀርም። ይህም ደግሞ በተለያዩ መንገዶች አይተናቸዋል።

ዶክተር ዓቢይ ወደ ስልጣን ሲመጣ ሁሉንም ዜጎች እኩል አያለሁ ቢልም በለገጣፎ፣ በሱሉልታ፣ በቡራዩና በሌሎች የኦሮሚያ ከተሞች ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች ህግን ያልተከተለና ዘርን ያማከለ በደል ሲደርስባቸው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው የሰጡት መልስ አሳዛኝና ለማመን የሚከብድ ነበር። ከኦሮሞ ብሄር ስለመጡ ብቻ በጉጂ ዞን ጉጂዎች የጌዶኦ ተወላጆች ላይ የፈጸሙት ሳይኮንኑት እንዲሁም ሳያጣሩት ቀርይተዋል። ከዚህም ሌላ የኦሮሞ ወጣቶችና አንዳንድ አክቲቪስቶች አዲስ አበባ ለኦሮሞ ብቻ የምትገባ ከተማ ናት፣ ሌሎች ነዋሪዎቿ የኦሮሞን ህዝብ ባህልና ቋንቋ ለማወቅና ለነሱ ሁለመና ተገዢ ሆነው መቀጠል ካልፈለጉ ይባረሩ የሚል ከፍተኛ ግጭትና ደም መፋሰስን የሚያስነሳ ሃሳብ ሲያመጡ ያንን እንደማረም እሳቸው በሊቀመንበርነት በሚቆጣጠሩት ኦህዴድ በተሞላው የኦሮሚያ ምክር ቤት በኩል ድርጊቱ ትክክል እንደሆነ መግለጫ እስከማውጣት የሄደ ከፍተኛ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት ፈጽመዋል።

አዲስ አበባን በተመለከተ በዩናይትድ ስቴትስ ጉብኝታቸው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በዚሁ ርዕስ ላይ ለጊዜው መልስ አልሰጥም ያሉበትን የተደበቀ ምክንያትም ባሁኑ ድርጊታቸው ኮለል ብሎ ተገልጿል።

በክፍል ሶስት ጽሁፌ በዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ለፖለቲካ ሲባል የትከወኑ ስራዎችና ወደፊት እንዴት ችግሩን ማስከንና በዘላቂነት መፍታት እንደሚቻል ለማተት እሞክራለሁ።

ሰላም እንሰንብት።

 

 

Back to Front Page